ቴዎድሮሥ ፀጋዬ – በተመክሮ፣ በንባብ፣ በውይይት፣ በክርክር እና  በተንሸራሸረ ተዋስዖ  በበርካታ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ የነጠሩ እና የተሻሉ ሐሳቦች ያገኘሁ በመሰለኝ ጊዜ አስቀድሞ የያዝኳቸውን አቋምና አመለካከቶች ከርክሜ፣ ቀይሬ፣ አፍርሼ፣ አጠናክሬም አውቃለሁ፡፡ ከእድሜዬ ማለዳ አንስቶ ዛሬ ድረስ ሲጠና እንጂ ሲላላ ያላየሁት፣ ሲበረታ እንጂ ሲደክም ያላስተዋልኩት ኢትዮጵያዊነቴ ነው፡፡ በልጅነት እንደ ወተት የጠባሁት፣ እንደ አፈር የቃምኩት፣ እንደ ውሃ የተራጨሁት፣ እንደ ጠበል የተረጨሁት ማንነት ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ይህም ማንነቴ የወረስኩት ብቻ ሳይኾን የመረመርኩት፣ የተቀበልኹት ብቻ ሳይኾን ያዳበርኩት፣ ያውጠነጠንኩት ብቻ ሳይኾን የኖርኩትም ነው፡፡ በደም ከተዋጀ ነጻነቷ ነጻነቴን ሰርቻለሁና፡፡ በመስዋዕትነት ከፍ ባለው ሰንደቅ በራስ እግሮች መቆምን፣ በራስ ጥበብና ታሪክ መኩራትን አውቄአለሁና፡፡

  1. ሚያዝያ 27/2009 ምን ኾነ?

ሚያዝያ 27/2009 በርዕዮት ኪን የፌስቡክና የዩቲዩብ የቀጥታ ስርጭት ልዩ የፋሲካ በአል ዝግጅት ላይ የቴዎድሮስ ካሳሁን ኢትዮጵያ የተሰኘ ዘፈን የመነጋገሪያ ጭብጥ ነበር፡፡ እኔና ወዳጄ፣ ባልደረባዬም ዳኝነት መኮንን ስለሥራው፣ በዚያው መነሾነትም ድምጻዊውን የተመለከቱ ነጥቦችን አነሳን፡፡ የዚያን ዕለት የርዕዮት ኪን መሰናድዖ ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት ከፍ ያለ የመነጋገሪያ ጭብጥ ኾኖ ሰነበተ፡፡ ብዙ ጥያቄ ቀረበ፤ ብዙ ቅሬታ ተስተናገደ፤ ብዙ አስተያየት ተሰጠ፤ ብዙ ዘለፋ ተሰነዘረ፡፡ የርዕዮት አባላትም ሁኔታውን ካጤንን በኋላ በጉዳዩ ያለንን አቋም የሚያሳይ መግለጫ አኖርን፡፡ አሁን ድረስ ምልከታችን ስህተት እንዳልኾነ ብናምንም፣ ምልከታችንን በተሻለ፣ በደረጀና በሰከነ መልኩ ለአድማጮቻችን ማቅረብ እንደነበረብን ስለተረዳን፣ ጭውውቱን ስንጀምር ከአንዳንድ ሰዎች በማኅበራዊ ድረገጾች ይሰነዘር  ለነበረው ስድብ እዚያው ምላሽ መስጠት አይገባ እንደነበር ስላስተዋልን፣ በዚሁ ግንዛቤያችን ልክ ብቻ፣ በአቀራረብ መንገዳችንና በቃላት ምርጫችን ቅር የተሰኙትን አድማጮቻችንን ይቅርታ ጠየቅን፡፡ ይቅርታችን ስላቀረብንበት መንገድ እንጂ ከቶ ስለይዘቱ አይደለም፡፡

ታድያ ይህ ሁሉ ከኾነ በኋላ አሁን ነገሩን መልሶ ማብራራት ለምን ፈለግሁ

1.1 ዛሬ ድረስ አቅም ቸረውኛል፣ ሠርተውኛልም  የምላቸውን ሰውነትን (ሰው መኾንን)፣ ነጻነትንና ኢትዮጵያዊነትን የተመለከቱ ኀልዮቶች ይበልጥ ለመማገርና ለማጠናከር በመሻት ነው፡፡ እንዲህ ያሉትን አጋጣሚዎች ከላይ ከሚታየው የችግር ገጽታቸው ተሻግረን ብንመረምራቸው እራስን፣ አገርን፣ ማኀበረሰብንና ዙርያገባውን እንደገና ለመመርመር፣ ከራስ ጋር በታማኝነት፣ ያለአንዳች ሽንገላ ለማውጋት፣ በእምነትና በሕይወት ጎዳና ላይ እግርን፣ መንገድንም ለማሳመር፣ እራስን መልሶ አበልጽጎ ለመውለድ ጭምር ይረዳሉና፡፡

1.2 የጠርሙስ ስባሪ የዋጥኩ ይመስል ልቤ ስር ኾኖ ከወደውስጥ የሚሸቀሽቀኝን እውነት ለመገላገልም ነው፡፡ እውነት፣ በተለይ እንዲህ ያለው አንጻራዊና አተያያዊ እውነት፣ ብዙውን ጊዜ ካለመገለጡ መገለጡ ይበጃል ስል አስባለሁ፡፡ የእውነቱ መገለጥ በፍጥነትና በቅርቡ የሚፈጥረው ለውጥ ባይኖር እንኳ፤ እውነት ያልነው ወይም እውነት የኾነው እውነት በእውነትነቱ የመገለጽና የመመስከር መዓርግ ሊደርሰው ይገባ ይመስለኛል፡፡ አሜሪካዊው ደራሲና የሲቪል መብቶች ተሟጋቹ ጄምስ ቦልድዊን ““የተጋፈጥነው ኹሉ ሊቀየር ባይችልም፣ እስካልተጋፈጥነው ድረስም የሚቀየር ምንም ነገር የለም ብሎ ማለቱ ለዚህ ነው፡፡

1.3 በተዋስዖ አደባባዩ ላይ በእኔም በኩል ያለውን የኹነቱን ክፍል ለማኖር ወይም ተደራሽ ለማድረግ በመመኘትም ነው፡፡

1.4 ነገርን ከየአቅጣጫው ሊመለከቱ ለሚፈቅዱ ኹሉ ምርጫ ይሰጣል ብዬ በማመንም ነው፡፡

1.5 በወጀቡ ወቅት በእኛ ጫማ ገብተው ኹኔታውን ለተመለከቱ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የማድረግ የኖረና የቀጠለ ዓላማችንን ተገንዝበው ለሌሎች ስለእኛ የመሰከሩ፣ ስለነጻነት፣ ስለመገናኛ ብዙኀን ሚና፣ ስለበጎ መነሻዎቻችን፤ በጥቅሉ ስለኛ እንደእኛ ኾነው የተሟገቱ አድማጮቻችን እውነታችንን  ከእኛው መስማት ይፈልጉ ይኾናልና ለእነርሱ፣ ላደግሁበት እውነተኝነትና ጨዋነትም ለተማርኩበት  ሰፊው ኢትዮጵያዊ ኅብረተሰብ ያለኝን ጥልቅ ፍቅር እና ክብር ቢገልጥልኝም ብዬ ነው፡፡

እነኚህ ከበረከቱ ምክንያቶች መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ስለቴዎድሮስ ካሳሁን የሞያ ጉዞና ሥራዎች ያለኝን ጥቅል ግምገማ ከማቅረቤ በፊት ሌሎች አበይት ፍሬ ነገሮችን መዳሰስ አስፈላጊ መስሎኛል፡፡

ማስታወሻ

ይህ ከራስ ጋር ተደርጎ ሌሎች እንዲካፈሉት የተፈቀደ የፍቅርና የክብር ወግ እንጂ፣ ከተጠያቂነት የሚመነጭና ለዚያ የሚሰጥ ምላሽ አይደለም፡፡  ታድያ ልብ እንዲባሉልኝ የምሻቸው 2 ነጥቦች አሉ፡፡ አንደኛ፣ በዚህ ጽሑፍ እኔ እውነትና ትክክል ያልኩትን ፍሬነገር ከማስረዳት በቀር፣ ሌላ ማንኛውም አይነት አሉታዊ ዓላማ የሌለኝ መኾኑ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ እዚህ ላይ በማነሳቸው ነጥቦች በእንግልት ስቃይና በደል ሥር ያለውን ሰፊውን ማኅበረሰብ በጅምላ ለመፈረጅ ፈጽሞ የማይቃጣኝ መኾኑ ነው፡፡

  1. የምናቤ ኢትዮጵያ?

በተመክሮ፣ በንባብ፣ በውይይት፣ በክርክር እና  በተንሸራሸረ ተዋስዖ  በበርካታ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ የነጠሩ እና የተሻሉ ሐሳቦች ያገኘሁ በመሰለኝ ጊዜ አስቀድሞ የያዝኳቸውን አቋምና አመለካከቶች ከርክሜ፣ ቀይሬ፣ አፍርሼ፣ አጠናክሬም አውቃለሁ፡፡ ከእድሜዬ ማለዳ አንስቶ ዛሬ ድረስ ሲጠና እንጂ ሲላላ ያላየሁት፣ ሲበረታ እንጂ ሲደክም ያላስተዋልኩት ኢትዮጵያዊነቴ ነው፡፡ በልጅነት እንደ ወተት የጠባሁት፣ እንደ አፈር የቃምኩት፣ እንደ ውሃ የተራጨሁት፣ እንደ ጠበል የተረጨሁት ማንነት ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ይህም ማንነቴ የወረስኩት ብቻ ሳይኾን የመረመርኩት፣ የተቀበልኹት ብቻ ሳይኾን ያዳበርኩት፣ ያውጠነጠንኩት ብቻ ሳይኾን የኖርኩትም ነው፡፡ በደም ከተዋጀ ነጻነቷ ነጻነቴን ሰርቻለሁና፡፡ በመስዋዕትነት ከፍ ባለው ሰንደቅ በራስ እግሮች መቆምን፣ በራስ ጥበብና ታሪክ መኩራትን አውቄአለሁና፡፡

እናም የሰርክ የዜግነት ጸሎቴ ይህ ነው፡፡

እነኾ የዜጋ ጸሎት …

“እርሷ በለገሰችን ልብ ውስጥ እርሷም የተቀረጸችበት፤ እርሷ በፈተለችው ማንነታችን ድር እና ማግ እርሷው የተሸመነችበት ኢትዮጵያ ኹልጊዜም ትኑርልን፡፡ ከየሰሞነኛ ግርግርና ከባለዘንጎች ቁርቁስ በላይ የኾነች ኢትዮጵያ፣ ከፖልታኪዎች ሴራና ከተዛነፈ ትወራ በላይ የኾነች ኢትዮጵያ ኹልጊዜም ትኑርልን፡፡ ጥላነቷ ከአውሬ የሚታደግ፣ ቤትነቷ ከ”ሰውነት” ቁር የሚከልል፣ ስበትነቷ ልጆቿን የሚያዋህድ አበቅየለሽ ኢትዮጵያ ኹሌም ለዘለዓለም ከፍ ትበልልን፡፡ በድኽነቷ ከእናትነት የማትፋቅ፣ በዘረኝነት ድቤና በጠባብነት ነጋሪት የማትሸበር፣ በአምባገነን ጭነት ያልተቀጨች፣ በሚፈራረቅ ውዝግብና ጦርነት መሠረቷ የማይናወጥ፣ “አለች”እስካልን ድረስ ያለች፣ የምናባችን ፈጣሪ፣ የምናባችንም ንግሥት፣ እርሷም እራሷ ምናባችን የኾነች ኢትዮጵያ ኹሌም ዘውትርም ትኑርልን፡፡ አሜን፡፡”

 4:3: 2016

  1. ነጻነትስ ወታደሮቿ ወዴት ናቸው??

ታድያ፣ ኹልጊዜ የሚቆረቁረኝ እና የሚገርመኝ ሐቅም አለ፡፡ ገና በጠዋት ጥበብንና ሥልጣኔን ያወቀ አገር የአማራጭ ሐሳቦች ችግኝ ማፍያ፣ የተለዩ ሐሳቦች ማብቀያ ማሳ ሳያበጅ እንዴት ቀረ? ከኹሉ ቀድሞ አስቦ የላቀ አገር እንዴት የተለያዩ አመለካከቶችን አቅፎና አቻችሎ የማስኬድ መላ አልመታም? ገና ጥንት የነጻነትን ጣዕም የተገነዘበና ለዚያም ለብዙ ሺህ ዓመታት ውድ ዋጋ የከፈለ አገር እንዴት የማሰብና የመናገር ነጻነትን የባሕልና የትውፊቱ አካል ሳያደርግ ቀረ ስል እጠይቃለሁ፡፡ ታሪካችንና ባህላችን በቀዳሚ ምክንያትነት እንደሚጠቀሱ አጥቼው አይደለም፡፡ ኾኖም ታሪካችንም ኾነ ባህላችንስ ለምን ይህንኑ መልክ ያዘ? ታሪካችን የባዕድን ቀንበር እምቢ የማለቱን ያህል ውስጡ እንዴት ሐሳቦችን ማዟዟርያ ቦይ፣ ነጻ ሐሳብን መግለጫ አደባባይ ላይሠራ ቻለ? ነው ጥያቄዬ፡፡

ይኸው በወል የተቋደስነው እና በግለሰብ ደረጃም  በየልባችን ኩራትና እርግጠኝነት ያኖረ ከባዕድ ቀንበር እራሳችንን ነጻ የማድረግ መሰጠት፤ ዥረቱ እንዴት ወደ እርስ በእርስ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መሥተጋብራችን  አቅጣጫ ሳይፈስስ ታገደ? ስለጀግንነት ያለንን እሳቤና መሥፈርት ከገዳይነት ባሻገር፣ በጎ ፈቃደኝነትን፣ ለሀገር የሚበረከት የትኛውንም ዓይነት ግልጋሎትን፣ ሐሳብን በሐሳብ ተፋላሚነትን፣ ሞያተኝነትን፣ መልካም ወላጅነትን ወዘተ ሳይቀር እንዲያካትት አድርገን መልሰን መከለስና ከለሉን ማስፋት እንደሚገባን ኹሉ፣ ስለነጻነት ያለንንም መረዳት መልሶ መተርጎምና ማስፋት ግድ ይለን ይመስለኛል፡፡ ከቃሉ በላይ የነጻነትን ሐሳብና ተግባር ማሰስ አለብን፡፡ ስለኾነም፣ እንዲህም እላለሁ፡፡ አገሬ ከኢትዮጵያዊ ማንነት በቀር፣ ከዜግነት ፖለቲካ በቀር፣ አባት አያቶቻችን እንዳደረጉት ተዋሕዶ፣ ተቀላቅሎ፣ ተዛምዶ አንድ የበለጸገ ማንነት ከመፍጠር በቀር ሌላ አማራጭ የሕልውና መንገድ እንደሌላት በጽኑ አምናለሁ፡፡ ፡፡ነገሩን ከዚህ በተለየ ርዕዮት የሚመለከት ኢትዮጵያዊ ወገኔን ግን በሐሳብና በሐቅ ምርኩዝነት እስከቻልኩት ድረስ እሞግተዋለሁ እንጂ “እንዴት ይህንን አሰበ” ስል አላነውረውም፡፡

በአብዛኛው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተዋስዖ ውስጥ በእጅጉ ችላ የምንለው የሚመስለኝና ጎድሎ የማየው፣ በአንደበት ስለመብትና ነጻነት ከመዘመር ባሻገር በሚታይ ድርጊት፣ የማንቀበለውም አመለካከት ሥፍራ እንዲያገኝ፣ እንዲደመጥ፣ እንዲንሸራሸር የማስቻል ባሕል ነው፡፡  ለዚህ ሰብዓዊ ክብር እና መብት ዘብ የሚቆሙ ተቋማት አልሰራንም፡፡ እነኚህን መሠረታዊ የሰው ልጅ አይገሠሴ መብቶችና እሴቶች ወታደር ኾነው ሊከላከሉ የሚጠበቅባቸው ምሁራንም በልዩ ልዩ ምክንያት ሚናቸውን በአመርቂ መንገድ እየተወጡ አይደለም፡፡ ከፊሎቹ በያገኙት የመደመጥ፣ የመታየት አልያም  የመነበብ እድልም ኾነ በመሠረቷቸው መገናኛ ብዙኀን አማካይነት ስለመናገር ነጻነትና መብት ይሰብካሉ እንጂ ጨርሶ አያምኑባቸውም፡፡  በተለያዩ ርዕዮተ ዓለማዊ እና ፖለቲካዊ ጥጎች ቢሰለፉም አፈናን እና ጭቆናን ለማዋለድና ምሑራዊ ገጽታ ለመስጠት የሚለፉ ናቸው፡፡ በሌላ ረድፍ ያሉት አብዛኛዎቹ  ጎምቱ ሊቃውንቶቻችን ደግሞ ያመኑበትን ቢናገሩ የሚመጣውን ድንጋይ ውርወራ ሰግተው ተሸሽገው በከባድ ዝምታ የሚኾነውን በበሮቻቸው ቀዳዳ እያጮለቁ የሚመለከቱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የእነኚህን እሴቶች እና ሐሳቦች Values and Ideals ዋጋ ቢያውቁም፤ በአድርባይነት ለራሳቸው ወይም ለመገናኛ ብዙኀናቸው ጥቅም ሲሉ የመጣውን አፍራሽ የአፈና አውሎነፋስ መጋለብና የዚያው አካል መኾን የመረጡ ናቸው፡፡ ይህም የመርማሪዎችና መንገድ አመላካቾች እጦት አደገኛ ሐሳቦች ሳይሞገቱና ሳይጋለጡ  ሥር እንዲሰድዱ ጊዜና ምቹ ኹናቴ ፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ያለውን ኹሉ ቢሰጥም ከኀብት፣ ከሥልጣን፣ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከፍትሕና ከእፎይታ ማዕድ የተገለለው የሀገሪቱ ሕዝብ የመከራውን ጊዜ የሚያሳጥርለት አጥቶ ክፉኛ ተቸግሯል፡፡ ኾኖም፣ በቁጥር ጥቂት ቢኾኑም፣ ከላይ ከተጠቀሱት 3 ረድፎች ውስጥ ለማይደመሩት፤ በቀረበው ሐሳብ ባይስማሙ እንኳ ስለሌሎች የመናገር ነጻነት በድፍረት ለቆሙት፣ ውግዘት ሳያስደነግጣቸው በአደጋና በሥልጣን ፊት ስለፍትሕና ነጻነት በልበሙሉነት ለተናገሩት፣ የተናገሩትንም ለኖሩት ምሑራን በያሉበት ምስጋናዬ እና አድናቆቴ ይድረሳቸው፡፡

ኢትዮጵያ በዘውገኞች ቱማታ፣ በውጪ ጠላት ጦር፣ በተፈጥሮ አደጋም ኾነ በድህነት ሕልውናዋ ይፈተናል ብዬ አላምንም፡፡ ኢትዮጵያ መከራን ተሻግራ፣ ፈተናን ተቋቁማ ብቅ የማለት ታሪክ ያላት እጹብ ሀገር ናት፡፡ ነገር ግን፣ ከመንግሥት የጠብመንጃ አፈሙዝ አልያም ከአንድ ፖለቲከኛ፣ የኃይማኖት አባት ወይም ከያኒ ተከታዮች ጩኸት በቀር ሌላ እውነት የምትፈልቅበት ምንጭ የለም በሚል እምነትና ያንን በተመረኮዘ የአፈና ተግባር ከቀጠልን፣ ያኔ ነው የኢትዮጵያን መዳን የምናርቀው፡፡ አተያይን በተሻለ አተያይ እንጂ በስድብ፣ እስራት፣ ግርፋትና ግድያ ማዳፈንን ካልገታን ትንሣዔያችንን ላይነሳ መግደላችን ነው ስል እሰጋለሁ፡፡ ፈጣሪ ያርቅልንና የሀገሪቱን የሕይወት እስትንፋስ የሚያቋርጠው ይኸው ልዩ ልዩ መልክ ያለው አፈናና የነጻነት እጦት  ነው፡፡ የኢትዮጵያ መዳን ያለው በነጻነት ማሰብና መናገር ዘንድ ነው እላለሁ፡፡ እኔ እንዲያብብ  የምሻው ኢትዮጵያዊነት ከዘመናቸው በቀደሙ ጠቢባንና ሀገራቸውን ከሕይወታቸው ባስበለጡ አርበኞች የተሰራ የመኾኑን ያክል፣ የማሰብንና የመናገርን ነጻነት የማይነፍግ ነው፡፡ እኔ የማውቀው ኢትዮጵያዊነት በወራሪዎች ፊት በውበትና በድፍረት የመቆሙን ያክል፣ አዲስ ወይም የተለየ ሐሳብ የማያስደነብረው ማንነት ነው፡፡

  1. ትግራዋይነት?

ምንድነኝ ምንድነህ ይሉት ጥያቄ በታላላቅ ፈላስፎች ሲጠየቅና ሲፈተሽ እጅግ ጥልቅ ትርጉም የሚኖረውን ያክል፣ ምንድነህ በቀሊል ሚዛን ተለክቶ ሲባል ግን በግ ለመግዛት ላት እንደሚያጤን ገዢ ሰውን ወደሸቀጥነት የሚደፍቅ የንቀት ጥያቄ ይኾናል፡፡ ሰብዓዊ ክብርን የሚመለከተውን ጭብጥ ወደኋላ እመለስበታለሁ፡፡ ብሔርን በተመለከተ የተለያዩ ኀልዮቶች አሉ፡፡ ገሚሱ ሥነ ሕይወታዊ (Primordeal) አድርጎት ከደምና የዘር ሐረግ ጋር  በጥብቅ ያቆራኘዋል፡፡ ሌላው ደግሞ እንደ ማኅበረ ባሕላዊ ሽመና ውጤት (Construct) ይገነዘበዋል፡፡ ከፊሉ ወደ ልዕልት ሀገሩ መሻገርያ ድልድይ ሲያደርገው፣ ሌላው ደግሞ ከወገኖቹ እራሱንና “ይመስሉኛል” የሚላቸውን መገንጠያ እና መነጠያ  (Instrumental) አድርጎ ይገለገልበታል፡ እኔ ደግሞ በወላጆቼ በኩል ያገኘሁትን ማንነት መጣል ሳያስፈልገኝ፤ ነገር ግን በምርመራ፣ በምርጫና በውሳኔ  ይበልጥ የማጎላቸውንና የምገለጥባቸውን ሌሎች ማንነቶች ያዋሃድኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡

እኔ ታድያ፣ በመቀሌ አፈር፣ በሻሸመኔ ጸሀይ፣ በደብረ ዘይት ነፋስና በአዲስአበባዬ ውሃ የተሰራሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ እናም፣ ከኢትዮጵያዊነት ቀጥሎ እራስህን እንዴት ትገልጣለህ ለሚለኝ ኹሉ፣ የዚያች የኹሉ የኾነች፣ የምንጊዜም የኢትዮጵያዊነት ኹነኛ ቋት የጣዪቱ ከተማ ዜጋ የኾንኩ አዲስ አበቤ ነኛ ብዬ እመልሳለሁ፡፡ ኾኖም፣ “ማንነትህን በብሔር በኩል ካልነገርከኝ  አይገባኝም” ለሚለኝ ተላላም እነኾ  ምላሽ፡፡ አዲስ አበቤነቴ ይህ በወላጆቼ በኩል ያገኘሁትን የትግራዋይነት ጸጋ አይገፍፈውም፡፡ ምክንያቱም፣ ለእኔ ትግራዋይነት፣ ኢትዮጵያን እንደ ሰፌድ ባስባት ሰበዙ ሊሰበዝ የጀመረበት አከባቢ መወለድ ማለት ነው፡፡ ትግራዋይነት ለእኔ፣ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ክርስትናና እስልምና የሚሰኙ ታላላቅ ሀይማኖቶች ወደሀገሬ የገቡበት በር አከባቢ መፈጠር ማለት ነው፡፡ ትግራዋይነት ለእኔ፣ ኢትዮጵያ የምትሰኝ ቤት ስትሠራ መሠረቱ በተቆፈረበት ሥፍራ መገኘት ማለት ነው፡፡

ትግራዋይነት በእኔ መዝገበ ቃላት ኢትዮጵያዊነት ሲወጠን ማለት ነው፡፡ የሰለባነት እንጉርጉሮ ሳይኾን የጠዋት የኢትዮጵያነት መድረክ ላይ አቀንቃኝነት ፣ የዳር አገርነት ባይተዋርነት ሳይኾን ኢትዮጵያን የመሰለች ሀገር መስራች የመኾን ታሪካዊ እድል ባለቤትነት ነው፡፡ በማከብራቸው ወላጆቼ በኩል ትግራዋይ ስለኾንኩ ደስ ይለኛል፤ በኢትዮጵያዊነቴ ደግሞ እጅግ እኮራለሁ፡፡ ትግራዋይነት የኢትዮጵያዊነት እልፍኝ እንጂ ዘውገኞቹ እንደሚሰብኩት ከኢትዮጵያዊነት የሚያሸሽ መውጫ በር አይደለም፡፡  ኢትዮጵያዊ ማንነት በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ዜጎች እኩል የሚደርስ፣ ለኹሉ ጥላ ላሉ ቤት የሚኾን ማንነት እንጂ፣ አንዳንዶች እንደሚስሉት እነኚህ በደማቸው የሚዘዋወር፣ እነኚያ ደግሞ ከላይ የሚለብሱት አልያም የሚታረዙት የኪራይ ወይም የውሰት ልብስ አይደለም፡፡

  1. ዘረኛ ማን ነው? (ደረጃ ምደባ)

እርግጥ ነው፣ ከአንድ ወይም ከሌላ ብሔር ወገን ነን የሚሉ፣ ባዕድና የማይገጥም ጽንሠ ሐሳብ ከየትም ተበድረው፣ ሀገርን መልሶ በመሥራት ሂደት ውስጥ የተፈጠሩትን ቁስሎች ቦርቡረው ታሪክ አዛብተው እንደብሔር የመጠቃትን ስሜት የፈበረኩና ያግለበለቡ፣ በዚህም ፍብርክ ስሜት መሰላልነት ሥልጣን ላይ የወጡም ኾነ አዲስ ሌላ ድንክ አገር መመሥረትን የሚያልሙ፣ ለአገራችን ሕልውና የሚያሰጉ  ብዙዎች መኖራቸውን አውቃለሁ፡፡ እቃወማቸውማለሁ፡፡ በዚያውም ልክ ግን፣ እራሳቸውን ከሌላው ይበልጥ ኢትዮጵያውያን አድርገው የሚሾሙ፣ ዘረኝነታቸውን ኢትዮጵያ በሚል ውብ ስም የሸሸጉ፣ በተግባር ግን የዘረኝነትን ኹሉንም ብየና የሚያሟሉ፣ ከእነርሱ የተለየ ሐሳብ የያዘውን ኹሉ በእነርሱ የዘውትር የዘረኝነት ሚዛን ሠፍረው ስም የሚሰጡ፣ ኢትዮጵያ የሚለውን የተቀደሰ ስም በአፋቸው የመደጋገማቸውን ያህል በነውራቸው የሚያራክሱ፣ ውድና ውብ ለኾነው፣ ኹሉን ለሚያቅፍ ለሚያስጠልለው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት እንደስድብ የሚቆጠሩ በርካቶችንም አስተውላለሁ፡፡ ከልዩነቱ ገደል ወዲህና ወድያ ያሉ ዘረኞች ኹሉ የቆሙበት አንጻር ይለያይ እንጂ አስተሳሰባቸው፣ አፈራረጃቸውና አፈጻጸማቸው በእጅጉ ተመሳሳይ ነው፡፡ በእነኚህ ሁለቱ የዘረኝነት ጎራዎች ሳቢያ የሚመጣው ዳፋ የሚወድቀውና እዳው የሚተርፈው፤ እርስ በእርስ ላይለያይ በተሳሰረው፣ እየተጋባ፣ እየተዋለደ፣ እየተገበያየ ዘረኝነትን እንደማይሻ በተግባሩ ሲያሳይ የኖረውና አሁንም እያሳየ ያለው ገበሬው፣ ነጋዴው፣ ተማሪው፣ ሠራተኛው፣ ነዋሪው፣ ሕዝቡ መኾኑ ግን ልብ ይሰብራል፡፡

ኢትዮጵያዊነት አንዱ በተፈጥሮ የሚጎናጸፈው፣ ሌላው ደግሞ በቸርነት የሚመጸወተው፣ እርከን ወይም ደረጃ ያለው  ማንነት ነው ብዬ በፍጹም አላምንም፡፡ ኾኖም፣ እርከን ወይም ደረጃ አለው የሚል ቢኖር እንኳ፣ በወላጆቼ ትግራዋይነት ምክንያት ከማናቸውም ደረጃ መዳቢዎች በበለጠና በቀረበ መልኩ እርከኑ ጫፍ ላይ ኾኜ ቁልቁል እመለከት ይኾናል እንጂ፤ ይበልጥ ኢትዮጵያዊ እኾን ይኾናል እንጂ፤ ደረጃ መዳቢዎቹ እንደሚገምቱት ከኋላ አልሰለፍም፡፡ ነገር ግን ልብ በሉልኝ፤ እኔ የእነኚህ እርከን ሰሪዎች አስተሳሰብ ውሀ እንደማይቋጥር ለማሳየት አነሳሁት እንጂ፣ ኢትዮጵያዊነት አንዱ ከስር ሌላው ከላይ የሚኾንበት እርከን አለው ብዬ በፍጹም አላምንም፡፡ ሁሉም ዜጎች፣ አሁን በታሪክ ክፉ እድል ከእኛ የተነጠሉትም ጭምር እኩል ኢትዮጵያውያን ስለመኾናቸው ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡

እናም ኢትዮጵያዊነቴን “ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ነኝ” እያለ ከብሔር ማንነት በቀር ሌላ ሚዛን ከሌለው ተመጻዳቂ እጅ እንደርጥባን አልቀበለውም፡፡ ኢትዮጵያዊነቴን፣ ካቀረብኩት ሐሳብ የጭብጥ ሐረግ መዝዞ መከራከር ሲያቅተው የዘር ሐረግ ሲስብ ከሚውልና እቃወመዋለሁ  ለሚለው ዘውጌ ብሔርተኛ ሥርዓት  የሚጠቅም ተግባር ከሚያከናውን ጭምብላም Hypocrite አልመጸወተውም፡፡ እናም እኔ ከኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ስለተገኘሁ ፈጣሪዬን የማመሰግን ልበሙሉ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡

እኔ ዘንድ የትግራዋይነት የፋይዳ ሚዛን የሚለካውና ትርጓሜው የሚፈታው አንድም ለኢትዮጵያችን መፈጠር ባለው መዋጮ፣ አንድም ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ወደሚባል ታላቅነት ለመጓዝ ባለው መንገድነት ነው፡፡

6 አንድነት ወይስ አንድ ዐይነትነት?

አንድነት ሲባል የሚነሽጥ፣ ሊወርሱትና ሊደርሱበት የሚመኙት የደኅንነት ቀጠና ይመስላል፡፡ እውነትነትም አለው፡፡ ኾኖም፣ እንደምን ያለ አንድነት ተብሎ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርበታል፡፡ ምነው ቢሉ፣ ከአንድ አይነትነት ጋር ሲምታታ ይስተዋላልና፡፡ ከወጥነት ጋር ሲሳከር ይታያልና፡፡ እንደእኔ ካላሰብክ ወይም ያመለክሁትን ካላመለክህ አንድነት አፍራሽ ነህ ሊልህ የማያፍር ሰው ወይም ቡድን ወይም አካል አንድነት ከአንድ አይነትነት ጋር የተሳከረበት ነው፡፡ አንድነት በወጥነት በሁሉም ጉዳዮች ላይ ያልተዛነፈ ሰልፍ መሥራት ወይም መከንዳት አይደለም፡፡ ይህ የአንድነት መረዳት፣ የራሷ የተፈጥሮም፣ የዕለት ኑሮም፣ የጥበብም፣ የውበትም፣ የአገርም ጠላት ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንደጥላ ከተቀበልን፣ ሕልውናዋ ላይ ካልተደራደርን ከዚያ በመለስ ያለው የሐሳብ ሜዳ ሁሉ ሳንጠፋፋ በሐሳብ ልንፋጭበት፣ ትግል ልንገጥምበት ምቹ ኾኖ ሊደለደልና ነጻ ተደርጎ ሊተው ይገባል፡፡ ያኔ ነው ከበርካታ የአስተሳሰብ አማራጮች ጥምረት፣ ውሕደትም ኾነ ፍጭት ሀገራችንን ከችግር እስራቷ የሚፈቱ መዳኛዎች  የምንሰራው፡፡

የተስፋ ቃል

ይህንን ኹሉ እያየሁም፤ በሀገሬ ሕዝብ፣ ጊዜና ኹኔታ እንደጠየቃቸው ስለኢትዮጵያ ዋጋ በሚከፍሉ ወገኖቼ፣ ስለሐሳብ ነጻነት ሲሉ በታሰሩና በተንገላቱ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች፣ የምናቤን ኢትዮጵያ በልባቸው በጻፉና በተጋሩኝ ዜጎች እንዲሁም ኢትዮጵያን በሚያቀነቅኑ ጥበብ ሠሪዎች ተስፋዬ ጽኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ ከዶክተር Martin Luther King, Jr ቃላት አዛምጄ ልዋስ፡፡

“ኢትዮጵያ ከዘረኝነት ድቅድቅ ጨለማና ከግጭት ጋር ላትለያይ ተሳስራለች፤ የሰላምና የወንድማማችነት ብርሀንም በምድሯ እውን አይኾንም” ይሉትን ሟርት ፈጽሞ አልቀበልም፡፡ በመጨረሻ ሰላም አምጪ እውነትና ቅድመኹኔታ አልባ ፍቅር ባለድል እንደሚኾኑ አምናለሁ፡፡

  1. ቴዎድሮስ ካሳሁን?

መተቸት መጥላት አይደለም፡፡

እዚህ ላይ በቴዎድሮስ ስራዎች ዙርያ ስላሉኝ እሳቤዎች ጠቅላላ ሥዕል በሚሰጥ መልኩ ብቻ የወፍ በረር ቅኝት አደርጋለሁ፡፡ አላማዬም ጤናማ የውይይትና ሐሳብ የመቀባበል አየር ንብረት ለመፍጠር መሞከር ነው፡፡

7.1 ግሩም ዜማና ግጥም የመድረስ ችሎታ እንዳለውና ድርሰቶቹን  ለመጫወት የሚያስችል ድምጽ እንዳለው አስባለሁ፡፡ ይህንን የምለው ለማንም ለመገበር አልያም ከማንም ጋር እርቅ ለማድረግ አይደለም፡፡ ጠብ በሌለበት እርቅ የለም፡፡ ሲፈጥረኝ መገበር አይኾንልኝም፡፡

ከነፈለቀ ኃይሉ ጋር በመኾን በሠራው የመጀመሪያው አልበሙ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ሥራዎች የመጀመሪያ አልበም ከሚያወጣ ድምጻዊ የተገኙ የማይመስሉ፣ ግጥምና ዜማቸውም ኾነ የሙዚቃ ቅንብራቸው ድንቅ ሥራዎች ናቸው፡፡ በአፍሮሳውንድ ባንድና በኤልያስ መልካ ቀማሪነት የተሰራው አቦጊዳም በብዙ መልኩ የቴዎድሮስ ካሳሁንን ችሎታዎች አጉልቶ የሚያሳይ፣ ምን ያህል በጥበቡ በፍጥነት እንዳደገ የሚያመላክትና ተስፋ እንዲጥልበት የሚያስገድድ አልበም ስለመኾኑ አስባለሁ፡፡ በያስተሰርያል፣ ጥቁር ሰውና ኢትዮጵያ አልበሞቹም መልካምና ጆሮ ገብ ሥራዎች ተበራክተው መገኘታቸውንም እንዲሁ፡፡

7.2 በልዩነት የማደንቃቸውና በአደባባይ የመሰከርኩላቸው እጅግ ውብ ሥራዎች ያሉትን ያህል፣ ከጥበቃዬና ከሞያዎቹ የጣዕም ልኬት Standard አንጻር ደረጃቸው ዝቅ ያለ፣ የታሪክና የአመክንዮ ዝንፈት ያላቸው ዘፈኖችን መስራቱንም አስተውያለሁ፡፡ ሞናሊዛ ይሉትን ዘፈን ሰምቼ አሁን ድረስ እንደምደመም ኹሉ፣ መንታ ወድጄን ሲጫወት ምነው ጥብቅና እቆምለታለሁ የሚለውን ኢትዮጵያዊውን ባሕል ዘነጋው በማለት እጠይቃለሁ፡፡ ካብዳህላክ ብሎ አንድ የነበረ አገር ለ2 ሲሰነጠቅ አብረው ለሚሰቀዩትና ለሚሰነጠቁት ነፍሶች ሲያቀነቅን አብሬው እንደቆዘምኩና እንደተደነቅሁ ሁሉ፣ በልኬ በሚሰኘው ዘፈኑ ላይ “ከአፈሩ ላይ የሠራሀት ነፍሴ ናት ብቸኛ” ብሎ ሲል፣ ምነው ቴዎድሮስ፣ ቅዱስ መጽኀፋችን እኮ ስጋ እንጂ ነፍስ ከአፈር እንደምትሠራ አያስተምረንም፤ ከአፈር የተሠራው ስጋችን ነው፤ ነፍሳችንማ የእግዜሩ እስትንፋስ ናት” በማለት ሐሳቤን እሰነዝራለሁ፡፡ ንገረኝ ካልሽማ ብሎ የመለየትን ጉዳት በውበት ሲስል ህመሙን እንደተጋራሁት ሁሉ፣ ጥቁር ሰውን ሲጫወት ጀግናውን ባልቻ ሳፎን ባልቻ አባቱ ነፍሶ ባይል፣ የሊቀመኳስ አባተን፣ የራስ መኮንን ወልደሚካኤልን፣ የራስ አሉላ አባነጋንና  የፊታውራሪ ገበየሁን ገድል ለፊታውራሪ  ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ባይሰጥ እመኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ብሎ ሲዘፍን፣ (በዜማውና በሙዚቃ ቅንብሩ ዙርያ ያለኝ ተአቅቦ Reservation እንደተጠበቀ ኾኖ) ኢትዮጵያን እንደሐሳብ መዝፈን ይህ ነው፣ እነኾ ኢትዮጵያ በረቂቅ ሐሳብነት የተነሳበት ዘፈን ተበረከተልን፤ ኢትዮጵያን በቅዱሳን ምህላና በአርበኞች ደም የቆየች ታላቅ ሀገር መኾኗን የሚያጎላ ተጨማሪ መወድስ አገኘን፤ ብዬ ሥራው በወጣ በሰዓታት ውስጥ ደስታዬን በርዕዮት ገጽ ላይ እንደጻፍኩ ኹሉ፣ “ማር እስከ ጧፍ” የሚሰኘውን የፍቅር እስከመቃብር ረዥም ልብወለድን ታሪክ  ጭብጥ ያደረገውን ዘፈኑን ደግሞ እንዲህ ተመልክቼዋለሁ፡፡ ይህንን ሥራ ከፍቅር እስከመቃብር ትልቅነትና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ካለው ጉልህ ሥፍራ አንጻር ሰፋ አድርጌ ልቃኘውም ፈልጊያለሁ፡፡

ከርዕሱ ልጀምር፡፡ “ማር እስከ ጧፍ” የሚለው ርዕስ ብዙ ሐሳቦች ያጨቀ ነው፡፡ የአጼ ቴዎድሮስ ዜና መዋእል ጸሐፊ የነበሩት አለቃ ዘነብ ኢትዮጵያዊ በመጽሐፈ ጨዋታ ላይ እንዲህ ይላሉ፡፡

“ማር ሁለት ጊዜ ያገለግላል፤ አንድ ጊዜ መጠጥ አንድ ጊዜ መብራት ኾኖ፡፡ ምነው ቢሉ የብልሕ ሥራ ነውና አሰርም የለው፡፡”

ቴዎድሮስ ካሳሁን ይህንን የማር መንታ ግልጋሎት ከፍቅር ሕይወትን አጣፋጭነትና ብርሃንነት ጋር ያዛመደበት ዝየባ ስኬታማ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም፣ ይህንን ፍቅርን በጧፍ የመመሰል ዘይቤ “ስለፍቅር” በተሰኘው ዘፈኑ ላይም ተጠቅሞበት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ “ልክ እንደአክሱም ራስ ቀርጸኀት ራሴን፣ በፍቅር ጧፍ ለኩሳት ነፍሴን…፡፡” የመጽሐፍን ታሪክ የዘፈን ፍሬ ነገር ማድረጉንም አደንቃለሁ፡፡ ነገር ግን፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን ታሪኩን ካስኬደበት መንገድ ጋር ልዩነት አለኝ፡፡

በዘፈኑ ላይ በዛብህ አዲስ አበባሸዋ ሩፋኤል ኾኖ በሰብለወንጌል መመንኮስና ገዳም መግባት ሲቆጭ፣ ሲጨነቅና ምነው ሲል ተተርኳል፡፡ ፍቅር እስከመቃብር ላይ እኮ ሰብለ ገዳም የገባችው በዛብህ ከሞተ በኋላ፣ እንዲያውም በዛብህ በመሞቱ ነው፣ በዛብህም በሽፍቶች ተደብድቦ የተገደለው ሰብለን ለማግኘት የአባይን በረሀ ሲያቋርጥ ነው፡፡ ሰብለም ለበዛብህ ስትል፣ ወላጆቿን ለሞት ዳርጋ፣ ከአንበሳና ነብር አፍ ተርፋ ወደአዲስ አበባ መነኩሴ መስላ ጉዞ ወጣች እንጂ በቴዎድሮስ ካሳሁን “ማር እስከ ጧፍ” ዘፈን ላይ እንደተሰናኘው በዛብህ አዲስ አበባ ኾኖ እርሷን ሲጠባበቅ ሳለ እርሷ ቃልኪዳኗን አፍርሳ ገዳም አልገባችም፤ ቴዎድሮስ ካሳሁን ያነሳው የፍቅር እስከመቃብሮቹን ሰብለና በዛብህ ነውና፣ በኪነጥበብ የፈጠራ ነጻነቱና በቀዳሚው ምንጩ ማለትም በፍቅር እስከ መቃብር ሐቆች መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ ነበረበት፡፡ እርግጥ በአልበሙ ሽፋን ላይ፣ በዛብህ የሰብለን ገዳም መግባት ቢሰማ በሚል የምናብ እይታ የተሠራ ነው ብሎ ጽፏል፡፡ ኾኖም የምናብ ፈጠራው በፍቅር እስከ መቃብር ላይ የተሣለውን የሰብለወንጌልን ሰብለወንጌልነትና የበዛብህን በዛብህነት ከስሩ ከመነገለው ዘፈኑ የፍቅር እስከመቃብርን ገጸባኅርያት ስሞችና መችየት መጥቀሱ ፋይዳ ያጣል፡፡ ምናባዊ ፈጠራው የፍቅር እስከመቃብርን ቁመና ካፈረሰው ምናባዊ ፈጠራነቱ ያከትምና እራሱን የቻለ ሌላ አዲስ ታሪክ ይኾናል፡፡ የፍቅር እስከመቃብሩ በዛብህ ቦጋለ ሰብለ ገዳም ስለመግባቷ ቢሰማ ወዳለችበት ሄዶ የራሱ ሊያደርጋት ህይወቱን ይከፍላል እንጂ በዘፈኑ ላይ እንደተጠቀሰው፣ እንግዲህማ ቆብ አስጥዬ፣ እንዳልወስዳት አባብዬ፣ ሰብልዬ ናት እማኾዬ፡፡ ብሎ ተስፋ ቆርጦ ፍለጋውን አይገታም፡፡ ሰብለወንጌልም በዛብህ ያለበትን ትክክለኛ ሁኔታ እንኳ ሳታውቅ በእግሯ ያንን ሁሉ መንገድ ትያያዘዋለች እንጂ ከእርሱ ውጪ ሌላ የሕይወት መንገድ አትመርጥም፡፡ የምናብ ፈጠራው የሁለቱን እስከ መቃብር መፋቀር ካጎደለ፣ በሕይወት እያሉ መፋቀራቸውን ካቋረጠ፣ የመጽሐፉን አምድ ንዶታል፡፡ በመኾኑም፣ በዚህ ሥራ ውስጥ የሚገኙት ተፋቃሪዎች በሰብለወንጌልና በዛብህ ስም የተጠሩ ሌሎች ጥኑ ተፋቃሪ ገጸባህርያት ናቸው፡፡ የፍቅር እስከ መቃብሯ ሰብለ ፍቅሯን በዛብህን ስትፈልግ ከአደጋና ከሞት ጋር ትፋጠጣለች እንጂ ጥላው፣ ያውም እየጠበቃት ገዳም አትገባም፡፡ የፍቅር እስከ መቃብሩ በዛብህም ሰብለ ለባል ልትሰጥ የመኾኑን ክፉ ዜና ሰምቶ መኖር ቸግሮት እርሷን ፍለጋ ሲጓዝ በሽፍቶች ተደብድቦ ይገደላል እንጂ፣ በቴዎድሮስ ካሳሁን “ማር እስከጧፍ” ላይ እንደተሳለው ሸዋ ሩፋኤል ተቀምጦ “ገዳም ገባችብኝ” እያለ አይቆዝምም፡፡ በዛብህ ልታገባ የመሖኑን ወሬ ሰምቶ ለሰብለወንጌል ከላከላት ግጥማዊ ደብዳቤ ጥቂት ስንኞች እጠቅሳለሁ፡፡

“እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወት መኖሬ፣ ተስፋ ሆኖኝ ነበር ፍቅርሽና ፍቅሬ፡፡ ግን እውነት ከሆነ የነገሩኝ ወሬ፣ ሊያገባሽ ነው ብለው ባለ ብዙ በቅሎ ባለ ብዙ በሬ፣ በፍቅር ለሞተ መታሰብያ ሆኖ እንዲኖር መቃብሬ፣ መኖር አልፈልግም ሞቼ ልደር ዛሬ፡፡”

እናማ፣ ምነው ታሪኩ ተዛነፈ፣ ምነው የሰብለና በዛብህ ድንግል ፍቅር ተዳሰ? የፍቅር እስከመቃብር ዋና አስኳል ማለትም የሁለቱ እስከ መቃብር መፋቀር ምነዋ ፈረሰ በማለት ጥያቄ አጭራለሁ፡፡ እስኪ እንነጋገርበት፡፡ ምን ትላላችሁ? የግጥሙን የአሰነኛኘት ውበት፣ የዘይቤ አጠቃቀምና የዜማውን ጥፍጥና ግን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ ከእርሱ ጋር ያለኝ ግንኙነት በጥበብ ሰሪና በጥበብ ወዳጅ መሃል ያለ ነው፡፡

7.3 አንድነትን የሚናፍቁ መናገሪያ ያጡ ብዙዎች እንደሚያደንቁት አውቃለሁ፡፡ በዚህ ኢትዮጵያዊነት በእስር ላይ ባለበት ጊዜ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ገዢ ርዕዮትነቱ ቀርቶ ከመገናኛ ብዙኃንና ከፖለቲካው ምኅዳር እንዲባረር በተደረገበት ወቅት፣ መልእክታቸውን እንዲያስተጋባላቸው ቢያጩት እጅጉን የተገባ ነው፡፡ ውሳኔውንና ድፍረቱንም አደንቃለሁ፣ አከብራለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ለማለት የሚያልፈውንም ጫናና የሚደርስበትንም እንግልት አውቅለታለሁ፡፡ ይህ ግን ከሂስ ወይም ከተለየ አስተያየት ነጻ የሚያደርገው የመከለያ ምሽግ እንዳልኾነም አልስተውም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለብዙ ሺኅ አመታት የተደከመበት ስሩ እንዲህ በቀላሉ የማይገኝ ነውና፣ የፊትና የኋላ በሮቹ ቢዘጉበት የራሱን በር ቀድዶ መውጣቱ የሚቀር አይደለም፡፡ ቴዎድሮስ ካሳሁንም ብዙዎች የሚያደንቁትና የሚጠብቁበት አገልግሎት ይህ ነው፡፡

7.4 እርሱም እንደሌሎች ከያኒያን ኹሉ በሥራዎቹ ላይ ሒስ፣ ነቀፌታ፣ አስተያየት፣ ትችት ወዘተ ሊቀርብነት የማይችል እንዳይደለም እገነዘባለሁ፡፡ ቴዎድሮስን ከእነኚህ ልዩ ልዩ ዐተያዮች ማዶ እንዲኾን ማድረግ አደጋዎች አሉት፡፡

ሀ፣ አስቀድሜ የጠቀስኩት ኢትዮጵያዊነትን የማስተጋባት ግልጋሎት እጅግ የበረታ ትከሻ የሚጠይቅ፣ እጅግ ጽኑ ልቦና የሚያስፈልገው ነው፡፡ ለዚህ የሀላፊነት ጣራ እንዲጠናም፤ ኢትዮጵያን በበለጠ ውበት ማቀንቀን፣ ታሪክ ያላዛነፈ ታሪክ ነክ ፈጠራ ማፍለቅ፣ የተዋበ፣ ያልተደጋገመ፣ አዲስና ኦሪጂናል የዜማ ድርሰትና ያደገ የሙዚቃ ቅንብር ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ይህም ከአድናቆት ውጪ ሒሳዊ ድጋፍ (critical support) እና ሌሎች አማራጭ ዐተያዮችን ሳያገኙ ሊደረስበት የሚችል ሥፍራ አይደለም፡፡

ለ፣ ለAP  በቅርቡ በሰጠው ቃለምልልስ በአደባባይ በሐሳቦች መሟገት ነውር ሊኾን እንደማይገባ ጠቅሷል፡፡ እውነት ነው፡፡ በሐሳብ መሟገት እጅጉን ጠቃሚ ብቻ ሳይኾን አማራጭ የሌለውም ነው፡፡ ይህ ታድያ የቴዎድሮስ ስራዎችን አስመልክቶ በሀሳብ መሟገትንና የሥራዎቹን ሕጸጾች ማንሳትንም ይጨምራል፡፡ እርሱም ሥራዎቹን በዚህ ጠቅላላ መርኾ ሥር የማይወድቁና የመርኾው ልዩ ኹኔታ Exceptionእንደኾኑ እንደማያስብ ተስፋ አለኝ፡፡ ከአረንቋ እንድትወጣ የሚዘፍንላት ኢትዮጵያ ካለመላት ትደርስ ዘንድ ዋናው ጎዳና ሐሳቦች የመንግሥትን ኀይልም ኾነ የብዙኀንን ጩኸት ሳይፈሩ በነጻነት መንሸራሸር መቻላቸው ነው፡፡ እርሱ የሚቀኝላት ሀገር የእርሱን ሥራዎች ጥንካሬ ብቻ እንድዘምር ለምትፈልግ፣ ድክመቶቹን ግን ትንፍሽ ለማልልባት፣ የሐሳቤን፣ የልቤን፣ ታየኝ የምለውን እንድናገር ለማትፈቅደዋ ኢትዮጵያ አይመስለኝም፡፡ ከኾነግን፣ ኢትዮጵያው ከእኔ ኢትዮጵያ በእጅጉ ትለያለች፡፡ እኔ የምናፍቃትና የማፈቅራት ኢትዮጵያ፣ ኹሉ የልቡን እውነት መንግስትንም ኾነ ፍቅር ያሸንፋል እያሉ ጎራዴ የሚወዘውዙ አንዳንድ ቁጡ አድናቂዎችን ሳይሰጋ እንዳሻው ተናግሮ፣ ስለደኅንነቱ የማያሰላስልባት፣ ፍርድ በማያውቅ ፍርድቤትም ኾነ በኢንተርኔት አደባባይ ላይ የማይቸነከርባት ኢትዮጵያን ነው፡፡

ሐ፣ ጥበብ ሊቃውንቱን የሚያግባቡ መሰረታዊ መርኾዎችና መለኪያዎች እንዳሉት ባይታበልም፣ ግለሰባዊ (subjective) የኾነ፣ የድምጫና የጣዕም ልዩነቶች በሚገባ የሚስተናገዱበት ነውና፣ በሥራው ላይ ወጥ የኾነ አመለካከት እንዲኖር መፈለግ ሰብዓዊ ተፈጥሮን የሚጻረር ከባድ ስህተት ነው፡፡ በመኾኑም፣ የማቀርበው ዐተያይ እንጂ የምደነግገው ህግ የለምና በአስተያየቴ የማይስማማ ማንም ስድብ ፍለጋ ብዕሩንና አንደበቱን ከሚያሳድፍ አመክንዮዎቹን ቢሞግት ይበጀዋል፡፡

7.5 ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይጠበቃል ብዬም አምናለሁ፡፡ መጽሐፉም ይላል፡፡ አንድ ጥበብ ሠሪ የሚያደንቀው ሲጨምር፣ በእርሱ ላይ የሚደረገው ትኩረት እጅጉን ዝርዝር (Microscopic)  መኾኑ፣ ኃላፊነቱ ማደጉና ከእርሱ የሚጠበቀው ከፍታ መላቁ አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎች ለጣሉበት አደራ በንባብ፣ በተዋስኦና በልምምድ ይበልጥ እራሱን ሊያበቃ የሚገባው፡፡ ለዚህም ብዙ ፍቅር ምላሽ እንዲኾን ነው የተሻሉና የታሰበባቸው የፈጠራ ሥራዎች በማቅረብ ለአፍቃሪዎቹና አድማጮቹ ያለውን ክብር እንዲገልጽ የምሻው፡፡

8 ዐይነ ሥውርነትስ? (ሌላኛው የብርሀን መልክ”

ሰው መኾን አገሩ እሩቅ ነው፡፡ የሰውም ልብ ስፋት ከህዋ ይበልጥ ይመስለኛል፡፡ ምነው ቢሉ፣ የሰው ልብ ፈጣሪ እንኳ የሚኖርበት ማኅደር ነውና፡፡ ሰውነት የኅሊናው ስውርነትና የስጋው ግልጥነት ድምር፣ ከረቂቃንም ከግዙፋንም የሚዛመድ፣ በማናቸውም ግን ሙሉ በሙሉ የማይገለጽ፣   በህዋው ላይ ማንም እንዳይመስለው፣ ማንንም እንዳይመስል ኾኖ የተበጀ ልዑል፡፡

መለኮት እንኳ ሊኾነው የፈቀደውና የለበሰው፣ ከከፍታው በላይ ሊከብር፣ ከእንስሳም በታች ሊዘቅጥ ልቀቱም እንጦሮጦሱም  መጨረሻ የሌለው የነፍስና የሥጋ ግጥም፡፡ ትርጓሜውም እንዲሁ ሰው መኾንን የሚሻ፡፡

ታድያ፣ ይህ ሰብዓዊ ክብርና ልዕልናን Inherent Dignity የመረዳት እርከን እንዲያው መናገር፣ ማየት፣ ማሽተት፣ መስማት፣ መዳሰስ፣ መራመድ፣ ኧረ እንዲያውም ማሰብ የቻለ ሁሉ የሚወጣው ሰገነት አይደለም፡፡ ሰው ሰው በመኾኑ ብቻ ከምንም የማይናጸር፣ ፍጹም የኾነና ቅድመ ኹኔታ የሌለው ክብር ይገባዋል ይላል ጀርመናዊው ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት፡፡ ይህም ክብር ሰው ከመኾን በቀር፣ በሚሰጠው ጥቅም ወይም አገልግሎት፣ በማኅበራዊ ሥፍራው፣ በዐተያዩ፣ በቆዳው ቀለም፣ በአካላዊ ኹኔታው፣ በሞራል ቁመናው ሰበብነት ከፍ ዝቅ የማይል ሰው በመኾኑ የሚያገኘው ክብር ነው፡፡  ኢማኑኤል ካንት የሰው ልጅ ዕሴትና ዋጋ ከዚያው ሰው ከመኾኑ የሚመነጭ እንጂ፤ ሰው ባልኾኑ ሕይወት ባላቸው ወይም በሌላቸው ነገሮች ላይ እንደሚደረገው ከወደውጪ የሚወሰንና የሚለጠፍ አለመኾኑን ያብራራል፡፡

እናም፣ እንደሰው ድቅል ተፈጥሮ ሰዎችም ቢያንስ ከሁለት ምድብ ናቸው፡፡

1 ይህንን ረቂቅነትና ግዙፍነት፣ ይህንን መለኮት እንኳ ሊዋሃደው የፈቀደውን ማንነት፣ ይህንን ጥንትነትና አዲስነት አስተቃቅፈው፣ አስተሳስረው የሚገነዘቡ፣ የሰውነትን ክብር በማናቸውም ቅርጽ፣ መልክ፣ ኹኔታ፣ ደረጃ ግርዶሽነት የማይስቱ ብርሀናት በአንድ ወገን አሉ፡፡ ይህ ቀዳሚ ምድብ፤ የሰውን በፈጣሪ ፊት እኩልነት  ኅሊናቸው ነግሯቸውም ኾነ ከመንፈሳዊ አባቶቻቸው ተምረው ያንኑ በተግባር የኖሩ ሚሊዮኖች ጨዋና ባለደጋግ ልብ ኢትዮጵያውያንን ያካትታል፡፡

2 በራቁት እይታቸው በሚያዩት ወይም ያዩ በመሰላቸው ግልብ ሐቅ ተመርኩዘው የራሳቸውንም ኾነ የሌሎችን ሰብዓዊ ክብር በራሳቸው ትንሽነት ልክ የሚከረክሙ፣ እብርሀናቸውና ሰብአዊ ክብራቸው  ላይ የተጋደሙ ጥቂት ጨለማዎች በሌላ ወገን ነው ሰልፉ፡፡ ስለጥቂቶቹ ጥቂት ልበል፡፡ እነኚህ ሁለተኞቹ፣ በቆዳ ቀለም ወይም በመገኛ ሥፍራ፣ በአካላዊ ኹኔታ፣ በኑሮ፣ በብሔር፣ በጎሳ፣ ወዘተ እነርሱን ካልመሰልክ፣ ቁልቁል ሊያዩህ የማይሸማቀቁ ቁልቁሎች ናቸው፡፡ ድክመት በሚመስላቸው ማናቸውም ግለሰባዊ መገለጫ ከማሽሟጠጥና ከመሳለቅ የሚገታ የኅሊና ልጓምም ኾነ ነውሩን ከክቡሩ የሚለዩበት የልቦና ምላስ የላቸውም፡፡ እንደትንሽነታቸው ቁልቁል ያዩ ይምሰላቸው እንጂ በእርግጥ የሚያዩት ሽቅብ ነው፡፡ እንዴት? እነርሱ ሰው የመኾን ወለል ናቸውና፡፡ ገብረ ክርስቶስ ደስታን ያክል የብዕርና የብሩሽ አድባር ሲያዩ፣ ሰው ከመኾን ልዕልናውና ከልዩ ሥነ ጥበባዊና ሥነ ጽሑፋዊ በረከቱ ይልቅ ከዐይናቸው የሚገባው የቆዳው ቀለም ለውጥ ነው፡፡ ምክንያቱም የዐተያያቸው ጥልቀት ግልብ (skin deep) ብቻ ነውና፡፡  ደበበ ሰይፉን ያህል ገጣሚ፣ እጹብ መምኅርና የስነጽሁፍ ዋርካ ሲያዩ፣ ሰው ከመኾኑ ዋጋ፣ ከድንቅ ግጥሞቹ፣ ከልዩ የማስተማር ስጦታውና ከስነጽኁፍ ሊቅነቱ ይልቅ ከዐይናቸው የሚገባው የጀርባው መጉበጥና የአካሄዱ እክል ነው፡፡ ምክንያት፣ ምልከታቸው እንጭጭና የጎበጠ ነውና፡፡ እንዲያው እንደአብነት እነኚህን ጠቀስኩ እንጂ በሀገሬ በተለያየ ዘመን የኖሩ፤ በልዩ ልዩ ሞያዎች ተሰማርተው ኢትዮጵያን ያገለገሉ፤ አካላዊ ኹናቴያቸው ከብዙሀኑ በመለየቱ ምክንያት የዚህ ዝቅጠትና ግልብነት ሰለባ የኾኑ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ እነኚህ ትንንሽ ተሳላቂዎች የቱንም ግለሰብ የሚመለከቱት በእራሳቸው ልክ ቀንሰውና አሳንሰው ነው፡፡

“ከሰብአዊነት አንሼ ላለማስተዋል የሰገድኩ፣

እንደምሽት ጥላ ቅናሽ ቁልቁል እንደግቻ ያደግሁ…”

ሲል እንዲገልጻቸው ጸጋዬ ገብረመድህን፡፡

ከብዕራቸውና አንደበታቸው የሚወጣውም ጉድፍ ከዚሁ ወለልነታቸው ይመነጫል፡፡ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፡፤ ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላም በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያፈራል፤ መልካምም ዛፍ ክፉ ፍሬን ማፍራት፣ ክፉ ዛፍም መልካም ፍሬን ማፍራት አይችልም፤… እንግዲህ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፡፡” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ፡፡ ማቴ. 7፣16-20፡፡

ዐይነሥውርነት እንደውፍረትና ቅጥነት ኹሉ፣ እንደጥቁረትና ቅላት፣ እንደእጥረትና ርዝመት ኹሉ አንድ ሰው የመሆን መልክ ነው፡፡ ዐይነ ሥውርነት አለማየት ሳይሆን በሌላ መንገድ ማየት ነው፡፡ እናም፣ ለአመታት የኖርኩትን፣ ያጌጥኩትን፣ የግስጋሴዬ የሀይል ምንጭና በረከት ያደረግሁትን፣ የጥልቅ ፍለጋና ሀሰሳ ሌላኛው የብርሀን መልክ የኾነልኝን ዐይነ ሥውርነት፣ በተለያየ አጋጣሚ እንደአዲስ ግኝት በተሳልቆ መልሰው ከነገሩኝና እኔን ቁልቁል መጎተቻ ገመድ ከመሰላቸው ተሳላቂ ወለሎች ጋር የመግባቢያ ቋንቋ የለኝም፡፡

ታድያ፣ ሐሳብ ቋንቋቸው ወደታች ክፉኛ ቢርቀኝም፣ በምግባራቸው ባፍርም፣ ነውራቸውን ብጸየፈውም፣ ሰዎች ናቸውና ሰው መኾናቸውን አከብረዋለሁ፡፡ ሊያድጉ ተስፋ እንዳላቸውም አውቃለሁ፡፡ ለከፍታ አይረፍድም፡፡

በመጨረሻም፣ የማይቻለውን የቻለውና ሳይኖረው ሲሰጥ የኖረው  የሀገሬ ሕዝብ በልጆቹ እንዲካስ፤ መከራው እንዲቀልለት፣ ብርሃን እንዲወጣለት፣ በጎ ቀን እንዲመጣለት የዘውትር ጸሎቴም ምኞቴም ነው፡፡

ኢትዮጵያ ምንጊዜም በክብር ትኑር፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *