“Our true nationality is mankind.”H.G.

የመንገድ ላይ ሕጻናት ፈተና

በኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሕፃናትን ይዘው በልመና የሚተዳደሩ ሴቶችና እናቶች ውሎና አዳራቸው የተመሠረተው በጎዳና ላይ ነው፡፡ ዋና ዋና የክልል ከተሞች ቀርተው፣ አዲስ አበባን ብቻ ብናነሳ፤ ጎዳና ላይ የሚለምኑ፣ የሚመገቡ፣ የሚውሉ፣ የሚያድሩና እዛው የሚፀዳዱ በርካታ ናቸው፡፡  አብዛኞቹም ለፆታ ጥቃት ይጋለጣሉ፣ ይደፈራሉ፡፡ ጎዳና ላይ የሚያድጉ ሕፃናትን ማየቱም ለአዲስ አበባ አዲስ አይደለም፡፡ ይልቁንም ስር የሰደደና ከተማዋም ልትመክተው ያልቻለችው ችግር ነው፡፡ ሕፃናቱ ጎዳና መዋል ማደራቸው ብቻ ሳይሆን ከ‹‹ትምህርት ለሁሉም›› የትምህርት መሪ ቃል ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ በሥነ ምግባር ታንፆ የማደግ ጉዳይም እንዲሁ፡፡

በእግረኛ መተላለፊያዎችና በመንገድ አካፋዮች ላይ ልብሳቸውን አጥበው የሚያሰጡ፣ የሚያበስሉ የሚፀዳዱን ለማየት ፒያሳ አያሌው ሙዚቃ ፊት ለፊት ያለውን ጎዳናና የመንገድ አካፋዮች ማየቱ በቂ ነው፡፡ እልፍም ከተባለ የዳግማዊ ምኒልክና የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልቶች ጥግ ስር የተከማቸው እዳሪ ‹‹ወይ አዲስ አበባ?›› የሚያስብል ነው፡፡

ከቀን ቀን ዋና ዋና ጎዳናዎችን የሚያፀዱ ሠራተኞችን ማየት የተለመደ ቢሆንም፣ የከተማዋ ፅዳት ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ዓይነት ሆኗል፡፡ ለዚህም ከዓመት ዓመት፣ ከዕለት ዕለት እየበዙና የአዲስ አበባን ዋና ጎዳናዎች እያጨናነቁ የሚገኙት ለማኞችና ጎዳና ተዳዳሪዎች አንድ ምክንያት ናቸው፡፡

የአፍሪካ ሕብረትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ፣ በአጠቃላይ በዓለም ውስጥ ከኒውዮርክና ከጄኔቭ ቀጥሎ ሁለተኛዋ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መናኸሪያ በሆነችው አዲስ አበባ፣ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ቢያስነውርም፣ እውነቱ ግን ይህ ነው፡፡

Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”

ከሁሉም በላይ ሕፃናቱና አዋቂዎቹ ጎዳና ተዳዳሪዎች  በችግር ላይ የሚገኙ መሆናቸው ዋናው ችግር ነው፡፡ መንግሥት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሕፃናትንና ሕፃናትን ይዘው በልመና ላይ የተሰማሩ እናቶችን ለመታደግና ማኅበረሰቡን መሠረት ያደረገ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሠራ ቢሆንም፣ ሥራው በተደራጀ፣ በተጠናከረ፣ ቀጣይነትና ወጥነት ባለው መልኩ ባለመከናወኑ የተገኘው ውጤት አመርቂ ሆኖ አለመገኘቱን የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በ2009 ዓ.ም. ያወጣውን ትንበያ ዋቢ በማድረግ እንዳመለከተው፣ በመላ አገሪቱ ከሚገኙ ሕዝቦች መካከል 52 ከመቶ ወይም 47,837,094 ሕፃናት ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ 7,000,000 ያህሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙና ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው፡፡

ወላጆቻቸውን በሞት በመነጠቅ፣ ተጥለው በመገኘት፣ በየጎዳናው ላይ በመታየት፣ በከፍተኛ ሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ችግሮች በመጠቃት፣ ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ለፆታዊ ጥቃት በመጋለጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሕፃናትን ለመታደግ በመንግሥት የተጀመረውን ጥረት በተደራጀ፣ በዘላቂነትና በወጥነት ለማከናወን የሚያስችል ሕዝባዊ ንቅናቄ ከወራት በፊት መጀመሩ ይታወቃል፡፡ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና አባገዳዎችን ያቀፈውና ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፍሪካ ደረጃ የሚከናወነውን የሕፃናት ቀን ምክንያት በማድረግ የተጀመረው ሕዝባዊ ንቅናቄ፣ አራት መሠረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን ይዟል፡፡

ጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ ሕፃናትንና ሕፃናትን ይዘው በልመና የተሰማሩ እናቶችን መረጃ የመለየት፣ የማደራጀትና በማዕከላት ገብተው ተገቢውን የተሃድሶ ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቤተሰብ ያላቸውን ከቤተሰቦቻቸውና ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉና እንዲዋሃዱ ማድረግ ነው፡፡

Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”

ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ ሕፃናት ተገቢውን ሥልጠና እንዲወስዱና ከዕድሜያቸው ጋር ተመጣጣኝ ሥራ እንዲያገኙ ለማስቻል እንዲሁም ቤተሰብ የሌላቸውን ሕፃናት አማራጭ እስከሚገኝላቸው ድረስ በማዕከላት ወይም በሕፃናት ማሳደጊያ ገብተው በጊዜያዊነት እንዲቆዩ ቀሪዎቹ አቅጣጫዎች ናቸው፡፡

ሕዝባዊ ንቅናቄው በከፊል አዲስ አበባን ጨምሮ ከክልሎች በተመረጡ 60 ከተሞች ባካሄደው እንቅስቃሴ፣ 12,416 ሕፃናትና ሕፃናትን ይዘው በልመና ላይ የነበሩ እናቶችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማቀላቀልና የማዋሃድ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ 2,776 ሕፃናትንና ሕናቶችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ያደረገ ሲሆን፣ የ858 ቤተሰቦች እስከሚገኙ ድረስ በማዕከል እንዲቆዩ አድርጓል፡፡

ሕዝባዊ ንቅናቄው በተደራጀ አግባብ እንዲመራ በፌዴራል ደረጃ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞለታል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ሮ ደሚቱ ሃምቢሳ ምክትል ሰብሳቢ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ ፀሐፊ ናቸው፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው በርካታ ሚኒስቴሮችና ሌሎች መንግሥታዊ ድርጅቶች በአባልነት ታቅፈው ተገቢውን እገዛና አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

በየክልሉ ምክትል ርዕሳነ መስተዳድር፣ በዞንና በወረዳ በምክትል አስተዳዳሪዎች ሰብሳቢነት የሚመራ አስተባባሪ ኮሚቴ የሚቋቋም ሲሆን፣ የፌዴራል አስተባባሪ ኮሚቴ መቋቋሙ፣ ሥራ አስፈጻሚዎችም መመደባቸውን እንዲሁም በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ተመሳሳይ ኮሚቴ የሚቋቋም መሆኑ የተገለጸው፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትንና ሕፃናትን ይዘው በልመና የተሰማሩ እናቶችን ከቤተሰቦቻቸውና ከማኅበረሰቡ ጋር ለማቀላቀልና ለማዋሃድ፣ እንዲሁም ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ለመወያየት ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”

ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥት አካላትና የሃይማኖት ተቋማት ተሳታፊ በሆኑበትና በካፒታል ሆቴል በተካሄደው በዚሁ የምክክር መድረክ፣ የኮሚቴውን የንቅናቄው ሥራ የሚያጠናክሩ ሐሳቦች ከታዳሚዎች ተንፀባርቀዋል፡፡ ከተንፀባረቁትም ሐሳቦች መካከል በሕፃናት ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ከግሉ ዘርፍ የንቅናቄው አካል እንዲሆኑ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡

የሕፃናትን ፍልሰት ለመከላከል በአጎራባች ክልሎች መካከል ግንኙነት መፍጠር፣ ለንቅናቄው ግብ መምታት የሚረዱ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን ማጎልበት፣ መገናኛ ብዙኃን በአገር ውስጥ የሚካሄደውን ጉዲፈቻ የማበረታታትና የማነቃቃት ሥራ እንዲያከናውኑ ማድረግ ከተንፀባረቁት ሐሳቦች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ሮ ደሚቱ ሃምቢሳ ‹‹መንግሥት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትን በአገራቸው ለመደገፍ በቀረፃቸው አማራጭ ፕሮግራሞች አበረታች ውጤት ማስመዝገብ የተቻለ ቢሆንም አሁንም፣ መብትና ደህንነታቸውን ለሚያስጠብቁ መሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽ ያልሆኑ በርካታ ሕፃናት ውስብስብ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፣ በተለይም የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትን ይዘው በልመና ላይ የተሰማሩ ወላጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሕፃናትንና ሕፃናትን ይዘው ለልመና የተዳረጉ እናቶችን ለመታደግና ከድርጊቱ እንዲላቀቁ ለማድረግ በመከናወን ላይ ባለው ሕዝባዊ ንቅናቄ ውስጥ የቤተሰብና የማኅበረሰብ እገዛ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ታደሰ ገብረማርያም Reporter Amharic

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0