“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኢንተርኔት መቋረጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እያወከ ነው

ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ኢንተርኔት በመቋረጡ፣ በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

ከአሁን ቀደም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ በነበረው ቀውስ፣ መንግሥት ኢንተርኔት እንዲቋረጥ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ በየዓመቱ ከሚደረገው የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ሥጋት መንግሥት ኢንተርኔት አቋርጧል፡፡

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ፈተና በመሰረቁ ኢንተርኔት መቋረጡ ይታወሳል፡፡ ፈተናው ተሰርቆ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ቀድሞ መለቀቁ ለኢንተርኔት መዘጋት ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ 246,452 የሚሆኑ የ12ኛ እና 1,029,782 የሚሆኑ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና መቀመጣቸው አይዘነጋም፡፡

ዓምና መንግሥት ለፈተና ዝግጅት 250 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ ፈተናው ተሰርቆ ከወጣ በኋላ ሌላ ፈተና ለማዘጋጀት ተገዶ ነበር፡፡ እስካሁን ከፈተናው መሰረቅ ጋር ተያይዞ ተጠያቂ የሆነ አካል የለም፡፡

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በመንግሥት በተወሰደ ዕርምጃ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ የተደረገ በመሆኑ፣ በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ችግር መፍጠሩ ታውቋል፡፡

‹‹እኛ የምናውቀው ኢንተርኔቱ ሙሉ በሙሉ አለመቋረጡንና የተወሰደውም ዕርምጃ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ነው፤›› ሲሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሰይድ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የኢንተርኔት መቋረጡ ከማኅበራዊ ድረ ገጾች አልፎ የኮምፒዩተርና የሞባይል ስልክ ተገልጋዮች ዘንድ ደርሷል፡፡

Related stories   መንግስት ከግብርናው ዘርፍ ስኬት ቆንጥሮ በዳታ የተደገፈ መረጃ ይፋ አደረገ - አቡካዶ ቀጣዩ ወርቅ !

የንግድ ተቋማት፣ ባንኮች፣ የመረጃና ቴክኖሎጂ ተቋማትና የጉዞ ወኪሎች በዚህ የኢንተርኔት መቋረጥ ተጠቂ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ለአብነት ያህል ሞደርን ኢትዮጵያ የተባለ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ከሳይበር ጋር በተያያዙ ሥራዎች  የሚታወቀው ድርጅት ይገኝበታል፡፡

ይህ ድርጅት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጀቶች ጋር የሚሠራ ሲሆን፣ በኢንተርኔት መቋረጥ ሳቢያ አጋር ድርጅቶቹ ባለፈው ሳምንት ያከናውኑት የነበረውን ሥራ አቋርጠው ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እንደሄዱ፣ የድርጅቱ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡

‹‹ይኼ ለእኛ በጣም የሚያናድድ ነገር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሆቴሎች በዚህ የኢንተርኔት መቋረጥ ተጠቂ ሲሆኑ፣ በችግሩ ምክንያት በኢንተርኔት የሚደረግ የመኝታ አገልግሎት ቡኪንግ ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ወደ 25 በመቶ የሚጠጋው የሆቴል ቡኪንግ በኢንተርኔት የሚከናወን ነው፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሆቴላቸውም ሆነ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሆቴል አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡

‹‹ነገር ግን በመረጃ ፍሰቱ ላይ በተፈጠረው መቋረጥ እነዚህን ሁሉ ነገሮች መሥራት አልቻልንም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በክሬዲት ካርድ የሚደረጉ ክፍያዎችን፣ የሆቴሉን የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ክፍያዎችን፣ እንዲሁም  በተለያዩ የሥራ ክፍሎች መካከል የሚደረጉ የመረጃ ልውውጦችን ማከናወን እንደተቸገሩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህ ለአገሪቱ ገጽታ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፤›› ሲሉም ይከራከራሉ፡፡

Related stories   መንግስት ከግብርናው ዘርፍ ስኬት ቆንጥሮ በዳታ የተደገፈ መረጃ ይፋ አደረገ - አቡካዶ ቀጣዩ ወርቅ !

ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንዳየው ኢንተርኔት ከተቋረጠ ጀምሮ ከሒልተን ሆቴል በስተቀር በአብዛኞቹ ሆቴሎች ኢንተርኔት ተቋርጦ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሒልተን ሆቴል ኢንተርኔት መጠቀም በሚፈልጉ ደንበኞች ተጨናንቆ ተስተውሏል፡፡

ይህ የኢንተርኔት መቋረጥ የተከሰተው ሆቴሎች በአስቸኳይ አዋጁና በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ወደ 380 ሚሊዮን ብር ገቢ እንዳጡ በገለጸ በሳምንታት ውስጥ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተቋረጠው ኢንተርኔት እንደ ራማዳና ካፒታል የመሳሰሉ ሆቴሎች ላይ ከሁለት ቀናት በኋላ መሥራት እንደጀመረ ሪፖርተር ማረጋገጥ ችሏል፡፡

 ከዚሁ ከሆቴል ሥራ ጋር በተያያዘ የጉዞ ወኪሎች የችግሩ ተጠቂ ሲሆኑ፣ በአብዛኛው በኢንተርኔት የሚሰጡ አገልግሎቶች ተቋርጠውባቸዋል፡፡

ከተመሠረተ ሁለት ዓመት የሆነው ጁመያ የጉዞ ወኪል 26 ሠራተኞች ቀጥሮ የሚያሠራ ድርጅት ሲሆን፣ በዚሁ ችግር በሳምንት በአማካይ የሚደረጉ ከ60 እስከ 80 የሆቴል ይያዝልን ጥያቄዎች ቆመዋል ይላል፡፡ ‹‹አሁን ምን ያህል እያጣን ነው የሚለውን መግለጽ ቢከብድም፣ ነገር ግን እየሠራን እንዳልሆነ ማረጋገጥ ይቻላል፤›› ሲሉ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ኤደን ሳህሌ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እንደ ባንክ ያሉ የገንዘብ ተቋማት ሥራቸው እየተስተጓጎለባቸው ነው፡፡ የገንዘብ ማስተላላፊያ ስዊፍት፣ ከወጪና ከገቢ ንግድ ጋር የተያያዙ የባንክ ሥራዎች መስተጓጎላቸውን የባንክ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ከገንዘብ ማስተላለፍ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የግል ባንኮች የሎተሪ ወይም የሽልማት ዘመቻ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡

Related stories   መንግስት ከግብርናው ዘርፍ ስኬት ቆንጥሮ በዳታ የተደገፈ መረጃ ይፋ አደረገ - አቡካዶ ቀጣዩ ወርቅ !

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ኃላፊዎች በአጠቃላይ የሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ መቋረጡን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ደንበኞች ገንዘብ ሲላክላቸው በእኛ ባንክ በኩል እንዲጠቀሙ ለማበረታታት ሽልማት ብናዘጋጅም፣ ሰሞኑን ግን ይህን ማድረግ አልቻልንም፤›› ሲሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የባንክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

‹‹ብሔራዊ ሎተሪ ይኼን የሽልማት ዘመቻ እንድናደርግ ውስን የጊዜ ፈቃድ ቢሰጥንም፣ በቀጣይ ሳምንታት ግን ምንም ማድረግ እንደማንችል ተገንዝበናል፡፡ ለዚህ ዘመቻ ብዙ ወጪ ብናወጣም የኢንተርኔት መቋረጥ ልፋታችንን መና አስቀርቶታል፤›› ሲሉ እኝሁ ኃላፊ አክለዋል፡፡

በኢንተርኔት ሳቢያ መቋረጥ ከገቢና ከወጪ ንግድ ጋር በተያያዘ ባንኮች ሥራቸውን ማከናወን እንደተሳናቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኃላፊዎች ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ይኼ ማለት በቀላል አማርኛ  ገቢና ወጪ ንግድ ቆመ ማለት ነው፤›› ሲሉ አንድ የግል ባንክ የመረጃና የቴክኖሎጂ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

‹‹ማኅበራዊ ድረ ገጽን ስንዘጋ ተማሪዎችን ከሚፈጠረው አለመረጋጋት ለመጠበቅና ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲወስዱ ነው፤›› ሲሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡

በዳዊት እንደሻው Reporter Amharic

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0