የፕሮቴስታንትነት እና ኢትዮጵያዊነት ፀብ (በያሬድ ይልማ)

የኢትዮጵያዊነትን ብሄራዊ ስሜት ካጎለበቱት ዋነኛ ቅመሞች አንዱ የኢትዮጵያዊያን ሃይማኖት ነው ቢባል ብዙ ማጋነን የለውም፡፡ ይህን ስል ታዲያ የኦርቶዶክስ ክርስትናም ሆነ እስልምና ባላቸው፣ ማህበረሰባዊ ፣ አገራዊ፣ እንዲሁም ግብረገባዊ ግብአታቸው፣ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት በነዚህ ሁሉ ወሳኝ የህዝብ ለህዝብ ግንኚነትን የሚያስተሳስሩ ናቸው፡፡

ጥንታዊያኑ የገዳ ስርአቶች፣ በሲዳማ እና በደቡብ ክልሎች በተለያዩ መንገድ እንደ እምነት ምርኩዝ ሆነው ህዝቡን ያገለገሉ፣ በባሌ ድሬ እና አርሲ እንዲሁም በምእራብ ኢትዮጵያ ጥግ ብዙ ቁጥር ያለውን የኢትዮጵን ህዝብ የስነምግባር ግድግዳ አበጅተው፣ ህዝቦችን እንደየአስተምህሮቶቻቸው ህዝቡን አብሮ እራሱንና አከባቢውን ከጠላት እንዲጠብቅ፣ እንዲሁም እርስ በእርሱም እንደሃገር መቀጠል የሚያስችል ፍትህ እየለገሱ የኖሩ፣ ከላይ የተገለፁት የመጀመሪያ ምንጫቸው እና መነሻ መሰረታቸው የትም ይሁን የትም የእምነቶቹ እድገት ከአገር ውስጥ አፈር ጋር አብሮ እየተለወሰ የሚያድግ በመሆኑ፣ አበቃቀላቸውም ሆነ አጠቃላይ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ህዝብ አኗኗር ጋር የሚፈጥሩትን ወይም ፈጥረው ያለፉትን ዝብ መስተጋብር በማየት መመስከር ይቻላል፡፡

ለዚህ ምሳሌ ለመስጠት ያክል፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት በኢትዮጵያዊያን ፈረሃ እግዚአብሄር ላይ ፣ በኢትዮጵያ ስነጥበብ፣ የስራ ባህል፣ በግለሰብ ደረጃ ሊስተዋሉ የሚችሉ ሞራላዊ ልእልናዎችንና የሚያሳድራቸውን አዎንታዊ ተፅእኖ ለአንባቢያን ትቼ፣ የእስልምና ሃይማኖት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚኖሩት ማህበረሰቦች ባበረከተው እጅግ የሚማርክ እሴት ለብዙ አገራት ምሳሌ መሆን የቻለች እንደ ሃረር አይነት ከተማን አፍርቷል፡፡ እንዲሁም በወሎ እና በባሌ አካባቢዎች ያሉትን ከእምነት በተጨማሪ ለረቂቅ የስነግጥም እና ዜማ ጥበብ ብልፅግናዎች (መንዙማንና የገሪዎችን ልዩ አዚያዜም ) የወለደ ሌሎች አያሌ ምሳሌዎችን ልናነሳ የሚያስችሉን ከኢትዮጵያ አፈር ተለውሰው ከባህሉ ተዋድደው የኖሩ በጎ እሴቶችን ለማህበረሰቡ ያበረከቱ ናቸው፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እና እስልምና፡፡

እነዚህ እድሜ ጠገብ የኢትዮጵያዊያን እምነቶች ባለፉት ቅርብ አመታት የሚያመሳስላቸው ሁለት እውነተኛ ክስተቶችን አስተናግደዋል፡፡እነዚህ ሁለት እውነታዎች የኢትዮጵያን ዋነኛ ሃይማኖቶች የነኩ፣ የነቀነቁ የቅርብ ጊዜ ተውስታዎች ነበሩ፡፡ የትኛውን ክስተት ለሚል አጥብቆ ጠያቂ፣ ገሃዱን ክስተት በወፍበረር እነሆ፣

ከልደታ ቤተክርስቲያን እስከ የተሃድሶ መስፋፋት፣ በኋላም እስከ ቤተክህነት ድረስ የዘለቀ የንዋይ እና የስልጣን ሰጣገባ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች፣ እዚም እዚያም መንግስት በከፈተው በር ገብተው፣ ህዝቡን በአመፅ ያነሳሱ የጣልቃገብነት ጋሬጣዎች ጋር ምእመናን ፊትለፊት ሲላተሙ እንደነበር ሁሉም ያውቃል፡፡

ከመጅሊሶች ጋር በተያያዘና ፣ እንዲሁም በአወሊያ እስልምና አስተምህሮት ሰበብ፣ እንደፈለገው በእምነት ስፍራዎች የፖለቲካ ታማኝነትን ከእምነት የሚያስቀድሙ ሎሌዎችን መንግስት ቀይሮ ፣ ለእስልምና አማኝ ምእመኖች ፣ እምነታቸውን በማያምናቸው የፖለቲካ ምልምል መሪዎች እንዲመራ ሊደረግባቸው ሲልና በሌሎችም ከጊዜ ወዲህ በእስልምና ውስጥ እየተቀየሩ በመጡ ያልተፈለጉ ለውጦች አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታዮች እምቢታቸውን በገለፁባቸው ባለፉት ተከታታይ አመታት፣ ድምፃቸው እንዲሰማ አገራዊ ተቃውሞ እና ንቅናቄ ሲደረግ መቆየቱንም እንዲሁ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በደንብ ያውቃል፡፡

ታዲያ በዚህ ሁሉ ሁለቱ ዋነኛ የኢትዮጵያዊያን ሃይማኖቶች እና አማኞቻቸው ነውጥ ሲያጋጥማቸው እና ከፍ ዝቅ የሚል ስሜት ሲያስተናግዱ፣ ከፍታን ብቻ ሲያጣጥም የነበረው የኢትዮጵያዊያን እምነት የትኛው ነው ካላችሁ ፕሮቴስታንት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት እምነታቸውን እንደሰደድ በመላ ኢትዮጵያ እያሰራጩ ያሉት የኢትዮጵያ ፕሮቴስታንት መሪዎች፣ ወንጌላዊያንና ጉባኤዎች፣ ያልጠበቁትን ብልፅግና በኢትዮጵ ምድር ያመጣላቸውን ፣ ለፕሮቴስታንቶች፣ “ገደኛው” ህወሃት መራሹ መንግስት በመንበሩ ፀንቶ እንዲቆይ ተግተው ይፀልዩ ነበር፡፡ ለዚህም አሳማኝ ምከንያት አላቸው፡፡
እምነቱ እና ተከታዮቹ በኢትዮጵያ ውስጥ በነበራቸው አጭር እድሜ ኢትዮጵያም ለእምነቱ፣ ምቹ ስፍረ ስላልነበረች፣ ለዚህም በንጉሱም ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እስተ ስርአተ መንግስት ድረስ በነበራት ጉልህ ተፅእኖ እና የፕሮቴስታንት እምነት ጥቂት አማኞች ከነ እምነታቸው ስፍራ ስላልነበራቸው፣ በደርግ ዘመነ መንግስት እንኳን ከቁጥር የማይገባ ተከታይ ለነበራቸው ለነርሱ ይቅርና፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትም ፣ የኮሚኒዝም ርእዮተ አለም መርሆ የሚያራምደው ወታደራዊ አገዛዝ ቀላል የማይባል ወቅት በመሆኑ ፣ እንዲሁም በራሱ በፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ላይe በደረሱ ችግሮች ፕሮቴስታንት በኢትዮጵያ ጥሩ ቆይታ አልነበረውም ማለት ይቻላል፡፡
እንደ ታላቋ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ሪታ ፓንክረስት የ1966 የኦብዘርቨር እትም መሰረት፣ “ሚካኤል አረጋዊ” ከተባለው ከመጀመሪያው የፕሮቴስታንት ሚሽነሪ እስከ አፄ ኀይለሥላሤ ዘመነ መንግሰት ብሎም እስከ ደርግ ፍፃሜ ድረስ ለቁጥር የሚበቃ እድገት ያልነበረው የኢትዮጵያ ፕሮቴስታንት ሃይማኖት እና የተከታዮች እድገት ጉዞ በ2007 በብሄራዊ የሰታስቲክስ ኤጀነንሲ በተደረገው ቆጠራ መሰረት የአገሪቱ 43.5% ወይም ከሰላሳ አምስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚሆነው ህዝብ የኦርቶደክስ ክርስትና እምነት ተከታይ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ እንዲሀ ደግሞ 33.9% የሚሆኑትን የአስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው ሲል፣ የፕረሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ከአገሪቱ ህዝብ 13,7 ሚሊዮን, አሊያም በመቶኛ ሲሰላ 12.6%, በሚያስገርም መልኩ በአሁኑ ሰአት ባለው የኢትዮጵያ ህዝብ አሃዛዊ ሃይማኖታዊ የክፍፍል ድርሻ መጠን ይዘዋል፡፡

በ2007 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ በሆነው አቶ ተፈሪ አቡሃይ ፣ የአንትሮፖሎጂካል ማስተርስ የድህረ ምረቃ ጥናታዊ ፅሁፍ ማጠቃለያ መሰረት፣ የፕሮቴስታንት እምነት የእምነቱ ተከታይ በሆኑት ባብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን ላይ አንድ እጅግ የሚያስገርም እና መሰረታዊ የማንነት ለውጥ (cultural discontinuity) ሂደትን ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የመንግስት ፖለቲካዊ እይታ እና ምሪት ምክንያት ፣ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ህዝቧን አንድ በሚያደርጉት እሴቶቹ ላይ ተግቶ በመስራት ፣ ከልዩነቱ ይልቅ ህብረቱ እንዲጎላ መደረግ ሲገባው፣ በዘር እና ቋንቋው እየተለየ የተዛመደበት፣ የተሳሰረበት ብልት ጅማቱ ላይ እንዲበጠስ ፣ መንግስት ከሚተዳደርበት ህገ መንግስት እስከ ቀበሌ መታወቂያ ድረስ ፣ ጠባብነትን በብዙ መንገድ እያበረታታ፣ የሚበጀውን የኢትዮጵያዊነት አገራዊ ስሜት ወይም ለብዙ ዘመናት የዳበረ አሻራ የነበረው ብሄራዊ ወገንተኝነት መጥፋት ላይ ፣ የፕሮቴስታንት እምነት የራሱን ፣ አሉታዊ የሆነ ጉልህ ሚና የሚጫወት የኢትዮጵያ ሃቀ ሆኗል፡፡ ይህ በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያድግ እና የሚያብብ አሉታዊ የማህበረሰብ ክፍል በቁጥር ይገለፅ ከተባለ፣ ለኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት የማይገዳቸው ዜጎች፣ በየአመቱ በ6.7% የዚህ መሰረታዊ የማንነት ለውጥ (cultural discontinuity) ሂደትን ይቀላቀላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሲፀድቅ ከብሄር ብሄረሰቦች በፊት ቀድመው በደስታ ደረት የደቁት ሌሎች ሳይሆኑ፣ ትንሽ ቁጥር የነበራቸው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ነበሩ፡፡ባህላዊ እና ትውፊታዊ መበጠስን በፅኑ የሚያበረታታው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት፣ በኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት ላይ በፖለቲካው መስክ ከተጋረጡት ዘረኝነት፣ ሙስና እና መከፋፈል እኩል ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ቁመናዋን ጠብቃ እንዳትራመድ የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡

የዚህ አጭር ፅሁፍ አላማ እውነቱን በማሳወቅ ፣ ኢጥዮጵዊነት የሚገደው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች አዎንታዊ እርምጃን በመውሰድ ፣ ከኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ ውስጥ ለተምሳሌትነት የሚበቃ ሚና እንዲጫወቱ ለማነሳሳት እንጂ፣ ብዙ ሰው በቀላሉ እንደሚገምተው፣ ከጥላቻ አሊያም በእምነቱ ላይ ካለ ግላዊ ተቃርኖ የተነሳ እንዳልሆነ አንባቢዎች እንዲገነዘቡልኝ እሻለሁ፡፡
ይህንንም ቅን ኢትዮጵያዊ ወገንተኝነት በተጨባጭ ለማሳየት ማንም ሊያረጋግጣቸው የሚችላቸውን እና የዚህ ፅሁፍ ትኩት የሆነውን የፕሮቴስታንት እምነት እውነታን ብቻ የተከተሉ አመክንዮዎችን ፣ ከአቶ ተፈሪ አቡሃይ ፣ የአንትሮፖሎጂካል ማስተርስ ጥናት በምሳሌነት ለማካተት ሞክሪያለሁ፡፡

እነዚህ ማሳያዎች በጥቂቱ ኢትዮጵያዊነት እና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይነት ከላይ በጥናቱ መሰረት እንደተደረሰው ድምዳሜ፣ የእምነቱ ተከታዮች መሰረታዊ የማንነት ለውጥ (cultural discontinuity) ሂደት ውስጥ ይገባሉ ወይም አዲስ ፣ በእምነቱ የዳበረ ፣ እንደ ደሴት እራሱን ያገለለ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አካል እና ባህል ውስጥ እራሳቸውን ያገኙታል የሚለውን ብይን፣ እንደ አስረጂ እንዲሆኑ የመረጥኳቸው ሲሆኑ እነዚህም፣ ማህበረሰባዊ ህብረት፣ መሰባሰብ፤ ቤተሰባዊ ፍቅር ፤ አገራዊ እሴቶችን በተመለከተ ፤ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ፤ እና አለባበስ ጥቂቶቹ ማሳያዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

1- መሰባሰብ እና ህብረት፣ ይህ ሲባል ብዙ አይነት ማህበረሰባዊ መሰባሰብን የሚመለከት ነው፡፡ በሃዘን በደስታ እና በበአል መሰባሰብን፣ አንድ ኢትዮጵያ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በሆነበት ማግስት በከፍተኛ መጠን ተሳትፎው ለዜሮ የሚቀርብበት የባህል ለውጡ ነው፡፡

2- ቤተሰባዊ ፍቅር ፤ አንድ ሰው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ሲሆን ከሚያደርጋቸው አስገራሚ ለውጦች አንዱ፣ ከወላጅ ቤተሰብ ጋር የሚኖረው ግንኙነት የይመናመናል በብዙዎች እንደሚታየው እንደውም ይቋረጣል፡፡ በተለይ ቤተሰብ እናት አባትን ጨምሮ፣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ካልሆኑ ሙሉ ለሙሉ መቋረጡ እና ከአዲሱ እምነቱ ተከታዮች ጋር አዲስ መተኪያ የሚሆን ግንኙነት መመስረቱ አይቀሬ ነው፡፡

3- አገራዊ እሴቶችን ፣ ቅርሶችንና ትውፊቶችን በተመለከተ ያለው አተያይ፤ የአድዋ በአል፣ የአርበኞች ቀን፣ እንዲሁም ቋሚ የትውልድ ውርስ ስለሆኑት ላሊበላ፣ አክሱም፣ የፋሲል ግንብ፣ ሀረር፣ ሼክ ሁሴን፣ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ ሌሎች ቅርሶች ፣ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ያደጉ አገራዊ ቅርስ እና ትውፊቶች ፣ ፈፅሞ እንደማይመለከታቸው እና እንደውም እስከ መጠየፍ ድረስ የሚደርስ አተያይ ፣ ለገዛ አገሩ ቅርስና ሃብቶች ያለው ካለ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የፕሮቴስታንት አማኝ ሲሆን ነው፡፡

4- የማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በተመለከተ፤ ከእድር ምርጫ አንስቶ እስከ ሱቅና ሌሎች ከፍ ያሉ የንግድ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ውስጥ፣ የትኛውም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነ አማኝ፣ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ በአገልግሎትም ሆነ በግዢ ሲፈልግ ምርጫው የሚያደርገው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነ ሌላ መሰሉን ፈልጎ እንጂ በዘፈቀደ አይራመድም ለዚህም በአማኞች ዘንድ ከሚቀርቡት ምክንያቶች አንዱ ፕሮቴስታንት ከሆነ “ለእግዚአብሄር አስራት ይከፍላል” በሚል ማስረጃ ነው፡፡

5- አለባበስን በተመለከተ፤ የሁሉም እምነት ተከታዮች የሚያመሳስላቸው የጋራ ነገራቸው ምእመናቸው የሚለብሷቸው ልብሶቻቸው በሃይማኖታቸው መመሪያ ዶግማ እና ቀኖና መሰረት የሚቃኙ እንደሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ግን ሁሉም የኢትዮጵያ እምነት ተከታዮች በጋራ የሚለዩት ደግሞ ባላቸው ደርዙን ያልሳተ፣ የቆየ ባህላዊ አልባሳቱ ላይ የተመሰረተው ጥንካሬው እና እደጥበባዊ ውበቱ ነው፡፡ የዚህ ፈፅሞ ተቃራኒ፣ በአንፃሩ ግን ለምእራቡ አለም ባህል የቀረበ ዝንባሌን ፣ በተለይ ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የጋራ በሆኑ የዘመን መለወጫ አይነት በአላት እና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተንቆጠቆጡ ቀለመቀት ተውቦ አገሩን በሚያደምቅባቸው አመታዊ በአላት ወቅት፣ ከዚህ በሚገባ አማኞቹ ተለይተው እንዲታዩ የሚያበረታታው ደግሞ የፕሮቴስታንት እምነት ነው፡፡ ታላላቆቹ ፣ በስታዲየም እና በሚሊኒየም አዳራሽ የሚደረጉ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በብዙ ሺዎች ወጥተው ይህንን ኢትዮጵያዊ ውበት እንዲቀይጡ እምነቱ ፣ ከአመት አመት ሲተጋ ይታያል፡፡
እነኚህ ሁሉ ተቃርኖዎች፣ ተደምረው የሚሸረሽሩት በብዙ ጋሬጣዎች ፣ ወደንድፈሃሳባዊ ህልውናነት እየወረደ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊነትን፣ ብሄራዊ ስሜትን ነው፡፡ ይህ ፅሁፍም እነዚህን ነጥቦች ለማሳያነት ያቀረባቀቸው፣ ወደፊት ኢትዮጵያዊነት እንዲለመልም የምትቀኑ ብዙ የምትቆጠሩ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች፣ ለዚህች አገር አንድነት ከማስተዋል የመነጨ፣ ከራስ ፈቃደኝነት የተነሳ የዜግነት ቅንአት ተነስታችሁ በሚያድገው የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር ልክ፣ ኢትዮጵዊነት እንዲለመልም የየራሳችሁን ሚና እነድትጫወቱ ሲባል ነውና ይህንን እወቁና ወደ በጎው ህብረት በርትታችሁ ተራመዱ ለማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም፡፡

ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው አቋም ብቻ ነው፤ መልስ ለምስጠት የምትፈልጉ ክፍሎች ካላችሁ በዝግጅት ክፍሉ አድራሻ zaggolenews2016@gmail.com ብትልኩ እናስተናግዳለን

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *