በዓፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ከአንድ መቶ አስር ዓመት በፊት መኪና ወደ አገራችን ሲገባ የመጀመሪያው አሸከርካሪ ራሳቸው እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፡፡

በዚያን ወቅት ንጉሱ መኪናዋን እያሽከረከሩ ሲጓዙ በነበረው ማህበረሰብ ዘንድ ሰይጣን እንደተጠናወታቸው በማየት የሚሸሸው ሰው በርከት ያለ እንደነበርም ፈገግ የሚያደርገው ታሪካችን ያወሳናል!!

ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በህጋዊ መንገድ መንጃ ፈቃድ አውጥቶ በማሽከርከር ረገድ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ደግሞ አሽከርካሪ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ መሆናቸውን የሚገልጹ መዛግብትም አሉ፡፡ በአጼ ሚኒሊክ  ዘመነ-መንግስት ወደሃገራችን የገባቸው አንድ መኪና አንድ ሁለት እያለች ዛሬ ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ደርሳለች፡፡

ለመነሻ ያህል ስለመኪና ስርወ አመጣጥ በጥቂቱ አወጋን እንጂ አንኩዋር ነጥባችን ታሪክ አይደለም፡፡ ከታሪኩ ጀርባ ስላለው አስደንጋጩ የትራፊክ አደጋ ነው እንጂ!! ኢትዮጵያ በአፍሪካ አነስተኛ መኪና ካላቸው ሀገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ ለአብነት እንኩዋን ከጎረቤት አገር ጋር ብናወዳድራት ኬንያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተሸከርከካሪዎች የምታስተናግድ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ሰባት መቶ ሺህ !!!

አደጋ በመድረስ ከኛ በላት ላሳር ይመስላል የትራንስፖርት ባለስልጣን እንደሚጠቁመው ከሆነ በሀገራችን በአማካይ በቀን አስር ንጹሀን ህይወታቸውን በዚሁ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ይገልፃል፡፡ ይህ ስሌት ደግሞ በአመት ወደ አራት ሺህ አምስት መቶ ያደርሰዋል፡፡ አጀብ አያሰኝም !!!

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፈው 2007 ዓ.ም ብቻ በትራፊክ አደጋ ከአራት ሺሀ አምስት መቶ በላይ ዜጎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ያወጣው ሪፖርት አሳውቆን ነበር ዘንድሮ ደግሞ ገና በዘጠኝ ወሩ ከአራት ሺህ በላይ ዜጎቻችንን ህይወታቸውን ማጣታቸው ተጠቁማል፡፡

እስቲ አንድ ሁለት በመንገድ ላይ በተፈጸሙ የትራፊክ አደጋ ሳቢያ የተሰጡ የቅጣት ውሳኔዎችን እንመልከት የዘገባችን ትኩረት ፍትህ አይደል የሚለው!! ከሳሽ የፌደራሉ ዓቃቤ ህግ ሲሆን ተከሳሽ ደግሞ ገዛህኝ ሲሳይ ይባላል፡፡

ተከሳሽ የሰውን ህይወት እና ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ሃላፊነት እያለበት ጥር 26 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ሲሆን ላዳ ታክሲ እያሽከረከረ ከላምበረት ወደ መገናኛ  ሲጓዝ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው  ላምበረት ወተት ሀብት አካባቢ የቀኝ መንገዱን ይዞ በመጓዝ ላይ የነበረውን ሟች ዋቱማ ዋቅፉላን በመግጨት በቸልተኝነት ሰው መግደል ወንጀል መከሰሱን ያትታል፡፡

የዓቃቤ ህግን የክስ መዝገብ የመረመረው የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት በስምንት ወር ቀላል እስራትና በብር ሁለት ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ሌላው መዝገብ እንደሚያስረዳው ደግሞ ተከሳሽ ጥጋቡ በለጠ የሰውን ህይወት እና ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ሃላፊነት እያለበት የካቲት 1 ቀን 2009 በሸጎሌ አካባቢ ሟች ሰለሞን ዛሎ የተባለውን ግለሰብ በሚያሽከረክረው የሚኒባስ መኪና ገጭቶ መግደሉ ዓቃቤ ህግ ባቀረበው መረጃ በመረጋገጡ በሶስት ዓመት ፅኑ እስራትና በአምስት ሺህ ብር እንዲቀጣ ይህው ችሎት ወስኗል፡፡

እንግዲህ የአደጋው ውጤት ሞት ሆኖ ውሳኔው ደግሞ ሁለትና  ሶስት አመት ሲሆን ለምን የሚል ጥያቄ ያጭር ይሆናል፡፡ የራሱ ምክንያት ይኖረው ይሆን? የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 572 የትራፊክ ደንብን በመጣስ ለአደጋ ማጋለጥ በሚለው ላይ ያስቀመጠው ድንጋጌ እንደሚያወሳው፣

ማንም አሽከርካሪ ወይም እግረኛ በቸልተኝነት የትራፊክ ደንብን በመጣስ የሌላውን ሰው ህይወት ፣ አካል ፣ ጤና ወይም ንብረት አደጋ ያጋለጠ እንደሆነ ከአንድ ወር እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት  ወይም ከመቶ ብር በማያንስ ወይም በሁለቱም መቀጫ ይቀጣል ይላል፡፡

ለፍርዱ ማነስ ምክንያቱ ይህ ከሆነ ደግሞ ልብ ሊባል የሚገባ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከችሎቱ ወጣ ስንል በአብዛኛው  የትራፊክ አደጋ እየደረሰ ያለው በአሽከርካሪዎች ምክንያት መሆኑን በሚወጡ ጥናቶች በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡

አንዳንዶቹ ምንም ጥናትና ምርምር ሳይጠይቁ የሚገለጹ ናቸው፡፡ ለአብነት አሁን በቅርቡ ግንቦት 13 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ከወደ አዳማ የተዘገበውን የትራፊክ አደጋን እንመልከተው፡፡ ዜናዋ እንደሚከተለው ቀርባለች እነሆ!!

ዶልፊኑ 14 መንገደኞችን አሳፍሮ   ከጭሮ ወደ አዳማ ይጓዝ እንደነበር ነው የተገለፀው፡፡  አነስተኛው የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው ታድያ ከተነሳበት ወደሚፈልግበት አልደረሰም፡፡ በዝናብ ውስጥ በፍጥነት የሚጓዘው የዶልፊን ቅርጽ ያለው አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ  ተገልብጦ የስምንት ሰዎች  ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን ነው  ፖሊስ የጠቆመው፡፡

አደጋው የደረሰው ተሽከርካሪው ከቀኑ 7 ሰዓት ከሩብ አካባቢ ፈንታሌ ወረዳ ሲደርስ ኢላላ በተባለው ቀበሌ አካባቢ ነው።  በአደጋው አሽከርካሪውን ጨምሮ ህይወታቸው ካለፈው ሌላ  በሰባት ሰዎች ላይ  ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱም ተጠቁማል፡፡ የሚያሳዝነው ህይወታቸው ካለፈው ሰዎች መካከል ስድስቱ ሴቶች ሲሆኑ እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ በዚሁ አደጋ እናቱ የሞተችበት  አንድ የአምስት ዓመት ህፃን እንዳለና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶበት ህክምና በመከታተል ላይ እንደሚገኝም መገለጹ ነው።

የአደጋው መንስኤ በዝናብ ውስጥ ከትራፊክ ቁጥጥር ለማምለጥ ከልክ በላይ እየበረረ በተቦረቦረ መንገድ ውስጥ ገብቶ በመገልበጡ  መሆኑን ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡ የጥንቃቄ ጉድለት የሚባለው ይህ ነው፣ አንድ አሸከርካሪ በማብረሩ የሚያተርፈው ነገር ሳይኖር ለራስም ለወገንም የሚተርፍ አሳዛኝ ነገር ይፈጠራል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡን አናግረን በሰጡን ምላሽ አደጋው ምን ያህል ጨመረ የሚለው ብቻ መያዝ የለበትም ባይ ናቸው፡፡

በሀገሪቱ በየዓመቱ ከመቶ ሺህ በላይ ተሸከርካሪዎች በጎዳና ላይ እንደሚሰማሩና እነዚህ እድገቶች በመንገዱ ላይ ሰፊ መጨናነቅ በመፍጠር አደጋው ሊጨምር ይችላል፡፡

ነገር ግን የአደጋው መጨመር ከልክ በላይ ሲሆን አሳሳቢ ስለሚሆን ነው በተለያዩ መንገዶች ንቅናቄዎችና ቅስቀሳዎችን በመፍጠር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ጥረት የሚደረገው ብለዋል፡፡

በ2007 ዓመተ ምህረት ሶስት ሺህ ያህል የነበረው የሞት አደጋ በ2008 ዓመተ ምህረት ከአንድ ሺህ በላይ ብልጫ በማሳየት አራት ሺህ ሶስት መቶ ሀምሳ ሁለት ደርሷል ነው ያሉት፡፡

የአለም ጤና ጥበቃ በየዓመቱ የሚያወጣውን ሪፖርት እንከታተላለን ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ የሀገራችን የአደጋ መጠን ከሌሎች አገራት ላቅ ብሎ እንደሚታይ ነው የገለጹት፡፡

አንዱና ዋናው የአደጋው መንስዔ የአሽከርካሪዎች  ችሎታ ማነስ ፣ የስነምግባር ችግር ፣ በትክክል ህጉን ጠብቆ አለማሽከርከር ዋና ዋናዎቹ ቢሆኑም የተሸከርካሪ ብልሽትም በዚሁ እንደሚካተት ገልጸዋል፡፡

እንግዲህ ይህን አስከፊ አደጋ ለመከላከል በትራንስፖርት ባለስልጣንም ሆነ በትራፊክ ጽህፈት ቤቶች አማካይነት የግንዛቤ ትምህርቶች ከመስጠት በዘለለ በ1996 ዓመተ ምህረት የወጣው የኢፌዴሪ ወንጀለኛ መቅጫ ህግን መሰረት ያደረገ የቅጣት ውሳኔዎችን በማውጣት ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡

በቅርቡም በተሸሻለው የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 ተግባራዊ መሆን የአደጋውን መጠን ይቀንሰው ይሆን ?!

ይህ ደንብ ታድያ በአምስት እርከኖች የተከፋፈሉ የቅጣት ውሳኔዎችን የያዘ ሲሆን የገንዘብ ቅጣቱ እስከ ሰባት ሺህ ብር የሚደርስና እንደ እርከኑ ጥፋት የመንጃ ፍቃድን የሚያግድ መሆኑን ያሳያል፡፡

በአንዳንድ የፍትህ ተቋማት የሚሰጡ የአደጋ ቅጣቶች ውሳኔዎች አርኪና ፍትሃዊ አለመሆን እንዲሁም የህጉ ጠንከር አለማለት ለአደጋው መባባስ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ሊታሰብበት ይገባል መልዕክታችን ነው፡፡

ENA   ሚስባህ አወል /ኢዜአ/

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *