opinion 3 ሻ/ቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ሲያትል በሀገራዊ ንቅናቄው ስብሰባ ላይ የተናገሩትን አዳመጥኩት፣ ከዚህ ንግግር በመነሳት ከተጻፉት አንዳዶቹንም አነበብሁ  “የሻለቃ ዳዊት የዋሽንግተን ሲያትል ንግግር በሞረሽ ዕይታ!የሚለው ጽሁፍ በሁለት ምክንያት ቀልቤን ሳበው፡፡ የመጀመሪያውና እንዳነበው የገፋፋኝ በድርጅት ስም የተጻፈ መሆኑ ሲሆን ይህችን አስተያየት እንድጽፍ ያበቃኝ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በሻ/ቃ ዳዊት የተነሱና ሞረሽ ከጻፈ አይቀር ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገቡ የነበሩ አበይት ጉዳዩችን ወደ ጎን የተወ ሆኖ ማግኘቴ ነው፡፡

ሻለቃ ዳዊት በተናገሩት ውስጥ የማልስማማበት ክፍል ቢኖርም እስከ ዛሬ የሆነውን፣ ሊሆን ሲገባ መሆን ያልቻለውን፣ ለዚህም ምክንያት ማንና ምን እንደሆነ  ፍርጥ ፍርጥርጥ አድርገው እውነቱን ነው የተናገሩት፡፡ ፖለቲካ ድርጅቶችን ነው የኮነኑት፣ዲያስፖራውን ነው የወቀሱት፡፡ግና እውነት ትጎመዝዛለችና ብዙዎቻችን ስንናገር እንጂ ሲነገረን አንወድምና፣ራሳችንን በአቅመ መጠኑ ማየት አይሆንልንምና ወዘተ የሻ/ቃ ዳዊት ንግግርና አነጋገር ሊያስከፋ እንዲያም ሲል የተለመደውን እሽኮለሌና ዘለፋ ሊያስከትል ይችል ይሆናል፣ በተወሰነ ደረጃም ማየት ጀምረናል፡፡

“የሻ/ቃ ዳዊት ንግግር በሞረሽ ዕይታ” በሚል ርእስ የተጻፈው በርግጥ ከድርጅቱ ከሞረሽ ለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሆን ነገር ባይኖርም ድርጅቱ የእኔ አይደለም እስካላለ ድረስ በተጻፈበት ስም ልንቀበለው ግድ ይለናልና ይህ ሲሆን ደግሞ የድርጅቱ አቋምና እምነት ነውና ከጸደቁ ኤቀር ይንጋለሉ አንዲሉ መጻፉ ካልቀረ በዋናው ቁ ነገር ላይ ባተኮረ ይበጅ ነበርና  የዚህች አስተያየቴ መነሻ መድረሻም ምክንያት ይሄው ነው፡፡

የሞረሽ ጽሁፍ የሚጀምረው “ሰዎች መልካም ሢሠሩና ሲናገሩ ማመስገን፣ መጥፎ ሢሠሩና ሲናገሩ ደግሞ መምከርና መገሰጥ ተገቢ ነው፤” ብሎ ነው፡፡ ይህ ወደ ራስ ሲዞር መምከርና መገሰጥን ብቻ ሳይሆን መመከርና መገሰጥንም የሚያመለክት ነውና ሞረሾች አስተያየቴን በዚሁ በእነርሱ ስሜት ይቀበሉታል የሚል ተስፋ ሰንቄ ነው እጄን ከመክተቢያው መሳሪያ ጋር ማገናኘት የጀመርኩት፡፡እኔን ብቻ ስሙኝ- እናንተ ምን ታውቁና ነው የምትገስጡ የምትመክሩኝ የሚባል ከሆነ አልተገናኝቶም ይሆናል ነገሩ፡፡

በሞረሽ የቀረበው አብዛኛው የጽሁፉ ክፍል መሰከሩልን፣ ተናገሩልን፣ የሚልና ለዚህም ሽሙጥ በሚመስል አገላለጽ ምስጋና የሚያቀርብ ሲሆን በአጠቃላይ ይዘቱ እነ ሻ/ቃ ዳዊት እየደከሙበት ካለውና በዛም መድረክ በግልጽ ጥሪ ካስተላለፉበት ከልዩነት ወደ አንድነት መንፈስ ጋር በእጅጉ የተቃረነ ነው፡፡ ሞረሽ ልዩነት ሰብኮ፣ቁርሾ ቀስቅሶ፣በቀል አነሳስቶ ወዘተ  የሚያተርፈው አልገባኝም፣እነርሱም ማስረዳትና ማሳመን የሚችሉ አይመስለኝም፡፡  “ሞረሽ ወገኔዐማራ ድርጅት ለዐማራ ነገድ ድምፅ ለመሆን የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ያለ ድርጅት ነው።ስለዚህ ሻለቃውንበዚህ ንግግራቸው፣ ላለፉት 5 ዓመታት ሲጮኽባቸው የነበሩ አንኳር ጉዳዮችን እያነሱ፣ዐማራውን ሲያወግዙ፣በጠላትነት ፈርጀው የዘር ፍጅት በፈጸሙ ግለሰቦችና ስብስቦች ፊት በኩራት ቆመውበመናገራቸው ከልብልናመሰግናቸው እንወዳለን። የሚለው አገላለጽ በአዳራሹ የተገኙትን ሁሉ በጠላትነት የፈረጀ፣ ጸብ ያለሽ በዳቦ አይነት ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ይህ  አገላለጽ አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን የሚያቀነቅን፣ ወደ እርቅ ሳይሆን ወደ በቀል የሚያመራ፣ ዘላቂ ዓላማና ግብ ከሰነቀ  ሳይሆን በዛሬ ላይ ብቻ ከተመሰረተ አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው፡፡ ከጸብ የሚያተርፉ እርቅ፣ ከጦርነት የሚያተርፉ ሰላም፣ ከልዩነት የሚጠቀሙ አንድነት እንደማይፈልጉ ለማወቅ ጠንቋይ መጠየቅ ወይንም ሳይንሳዊ ምርምር ማድረግ አይሻም፡፡ሞረሾች የዚህ አስተሳሰብ ተጋሪዎች ናቸው እንበል ይሆን! የሞረሾች ጽሁፍ ሻ/ቃ ዳዊት «ኢትዮጵያዊ እንጂ፣ ዐማራ ሆኜ አስቤ አላውቅም» ያሏት አገላለጽ እንዳልተመቸቻውም  ያሳብቃል፡፡ ግን ለምን ኢትዮፕያዊነትን የሚያስጠላ አማራነት ከየት መቼና እንዴት? የመጣ ነው፡፡

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ሞረሾች ከጻፉ አይቀር ሊያተኩሩበት ሲገባ ወደ ጎን የተዉትን ነገር ለማስታወስና ከቻሉ ምላሽ እንዲሰጡበት(እሽኮለሌ አይፈቀድም) ለማበረታታ እንጂ ለጽሁፉ ምላሽ ለመስጠት አይደለምና ከዚህ በላይ ያነሳሁት ነገርን ነገር ያነሳዋል በሚል ይያዝልኝና ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ላዝግም፡፡ ሻ/ቃ ዳዊት በንግግራቸው ከሌሎች ባልደረባዎቻቸው ጋር በመሆን  ሀገራዊ ንቅናቄውን ለመፍጠር ያነሳሳቸውን ምክንያት፣ የፈጀባቸውን ግዜ፣ ያካሄዱዋቸውን ስብሰባዎች ብዛት፣ ዘርዝረው ይህም ሆኖ ትብብሩ ለተሰበለት ግዜ በተፈለገው መጠን መድረስ አለመቻሉን በቁጭት ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ግዜያት በአማራ ስም የተደራጀን የሚሉትን በሙሉ እንዳነጋገሩ (ሞረሽን በስም ጠቅሰው) ነገር ግን ሀገራዊ ንቅናቄው ውስጥ እንደ ድርጅት ለመካተት የሚችል ሀይል ለመገኘት ባለመቻሉ ጥረታቸው ለጊዜውም ቢሆን መምከኑንና ድካማቸው አለመሳካቱን  በሀዘን ተናግረዋል፡፡

በእኔ እምነት ሞረሾች በጽሁፋቸው ይህን እውነታ መጋፈጥ ነበረባቸው፡፡ ሆኖም ግን የተነገረው እውነት ነውና አምኖ መቀበሉም ሆነ ማስተባበሉ ይቸግራልና ሊነኩት አልደፈሩም፡፡እንደውም በተቃራኒው ከንግግሩ ያልሰማነውንና እነርሱ ከየት አንዳመጡት ያልገለጹትን  “ለተደራጁት ዕውቅና ሳይሰጡ «አዲስ እናደራጃለን» ማለት ውኃን ወቅጦ ለማላም እንደመጣር ይቆጠራል። ዐማራው ለመደራጀትና ያሻውን ለማድረግ የማንንም ድጋፍም ሆነ ፈቃድ አይጠይቅም። ስለሆነም ዕውቅናም በትግሉ የሚያገኘው ፀጋው እንጂ፣ ከሌሎች በችሮታ የሚያገኘው አይደለም፣ በማለት ጽፈዋል፡፡” እንዲህ ወደ ቀኝ ሲነገር ምላሹ ወደ ግራ እየሆነ፣ ያልተነገረ እየተባለ፣ ያልተጻፈ እየተነበበ ነው መግባባት ቀርቶ መተባበሩ ርቆ መከባበሩ እንኳን ጠፍቶ  ለወያኔ የተደላደለ የግዞት ዘመን መስጠት የተቻለው፡፡

ሁላችንም የምንሰማው እኩል በሁለት ጆሮአችን ቢሆንም  ህሊናችን ነጻ ሆኖ ስሜታችን ከግል ፍላጎትም ከጥላቻም ጸድቶ ካልሆነ፣ የምናዳምጠው እየመረጥን የምንተረጉመው እንደየፍላጎታችን ይሆንና አንድ ቋንቋ እየተነጋገሩ መግባባት የተሳናቸው የባቢሎን ሰዎች እንሆናለን፡፡ ደግሞም ሆነናል፡፡

እኔ አንደሰማሁት በሻ/ቃ ዳዊት ንግግር ውስጥ ለአማራ ድርጅቶች እውቅና የመስጠትም የመንሳትም ነገር የለም፡፡ በግልጽ የተነገረው በአማራ ስም ብዙ ድርጅቶች መኖራቸው ነገር ግን ከመሀከላቸው ለሀገራዊ ንቅናቄው አባል ለመሆን መጣኝ ቁመና ያለው አለመገኘቱ፣በዚህ መቀጠል ስለሌለበትም ብዙዎችን ወደ አንድነት የማምጣት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ነው፡፡ የፓርቲ ምስረታ ጥያቄ የቀረበው ለትግራይ ወንድም እህቶቻችን ነው፡፡

በመሆኑም እውቅና አልሰጡም፣አዲስ ፓርቲ ማሰብ ውኃን ወቅጦ እንደማላም ነው የተባለው መሰረታዊውን ጉዳይ መጋፈጥም  ዝም ብሎ ማፍም ለሞረሾች አልሆንላቸው ብሎ ለአቅጣጫ ማስቀየሪያ  የቀረበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መጽሀፈ ሲራክ ም/20/7 ላይ “ አዋቂ ሰው ጊዜውን እስኪያገኝ ድረስ ዝም ይላል፡፡ ሰነፍ ደፋር ሰው ግን እንዳገኘ ይናገራል፤” ተብሎ ተጽፏል፡፡ የሚገርመው ግን የተናጋሪዎቹ ወይንም የጸኃፊዎቹ አድራጎት ሳይሆን ደጋፊዎቻቸው ራሳቸው በቀጥታ ከተናጋሪው አንደበት ከሰሙት ይልቅ መሪዎቻችን የሚሉዋጀው ሰዎች ቱርጁማን ሆነው የተነገረውን አዛብተው ልተባለም አክለውበት  የሚነግሩዋቸውን መቀበላቸው ነው፡፡ የጎሰኝነት ዋናው ችግርም እዚህ ላይ ነው፡፡ በጎሳ ማሰብ ሲጀመር ሌላው እውነት ሁሉ አይታይም፡፡የእኔ ከሚሉት ሰው ውጪ ያለው የሚናገረው ሆነ የሚሰራው አይጥምም፡፡

ሞረሾች ሊደፍሩት የሚገባ ሀቅ፡፡

ሞረሾች እውነቱም ድፍረቱም ካላቸው ሻ/ቃ ዳዊት በገለጹት ሀገራዊ ንቅናቄውን ለመመስረት በተደረገ ረዥም ጉዞ ውስጥ መጠየቃቸው እውነት ነው ወይስ አይደለም? ከተጠየቁ ምላሻቸው ምን ነበር? ሀገራዊ ንቅናቄውን የሚመጥን ቁመና ያጡበት ምክንያትስ የፖለቲካ ድርጅት ባለመሆናቸው ወይንስ ድርጅታዊ ጥንካሬ በማጣታቸው? ሂደቱ ረዥም ግዜ የፈጀ ነበርና የጎደለውን አሟልቶ ለመሳተፍ ምን የተደረገ ጥረት ነበር ለምንስ አልተሳካም? ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡

በሌላም በኩል በአማራ ስም ከተደራጁት ካልተሳሳትኩ አንጋፋ ናችሁና የሌሎቹን ቁመና እንዴት ታዩታላች፣መደባበቁ መሞከሻሸቱ የትም አላደረሰም አያደርሰምም፡፡ አበው “ቂጥ ገልቦ ክንብንብ” እንደሚሉት በተግባር የሌለን ድርጅት በፌስ ቡክ ቢያገዝፉት፣ በፕሮፓጋንዳ ቢያተልቁት ሲገለጥ ባዶ ነውና  ከአጉል ጩኸትና የባዶ ቤት ፉከራ  የየራስን ማንነት የድርጅትን ቁመናና ብቃት በድፍረት ተነጋግሮ  አቅምን በግልጽ አውቆ ሆኖ ለመገኘት መስራቱ ነው የሚበጀው፡፡

እናም ሞረሽም ሆነ ሌሎች በአማራ ስም የተደራጀን የምትሉ ሻ/ቃ ዳዊት የተናገሩት ለሀገራዊ ንቅናቄው አባልነት የሚመጥን ቁመና የላቸውም የሚለው ሀሰት ከሆነ ለምን ተባለ ብሎ አካኪ ዘራፍ ሳይሆን እውነቱን በመረጃ አስደግፋችሁ በማስረጃ አረጋግጣችሁ ማቅረብ ነው፡፡አባል ያልሆናችሁበትንም ምክንያት በተራ የፕሮፓጋንዳ ዘየ ሳይሆን በሀቅ መግለጽ ነው፡፡ ርሳቸው ያሉት እውነት ከሆነ ደግሞ ቁመናችሁን ፈትሻችሁ፣ አቅማችሁን መዝናችሁ ምን አልባት ወደ አንድ ስትመጡ በየግል የምታጡት ነገር መኖሩ አይቀርምና  ያንን መስዋዕት አድርጋችሁ አስር አይነት አማራ የለምና አንድ ድርጅት ለመፍጠር ትጉ፣ እግዚአብሄርም ለዚህ የሚያበቃ ልቦና ይስጣችሁ፡፡ከመፎከር ወደ ተግባር ይምራችሁ፡፡

እኔ እስከገባኝ ድረስ ሻ/ቃ ዳዊት ስለ አማራ መደራጀት አጽንኦት ሰጥተው በቁጭት የተናገሩት በአማራነትም ሆነ በዞን ስም በመሰባሰብ (ጎጃም ጎንደር ወሎ) እንደ አሸን የፈሉትን ወደ አንድ በማምጣት አማራውን የሚመጥን ( የሚወክል ማለት አይቻልም) ድርጅት መፍጠር እንጂ ሞረሽ ለማለት እንደፈለገው አዲስ ድርጅት ለመመስረት አይደለም፡፡

እኛ የሌለንበት የሚል ትምክህት እንዳይዛችሁ፡

ሻ/ቃ ዳዊት አጽንኦት ለመስጠት ረገጥ አድርገው ከተናገሩት አንዱ አማራ የሌለበት ሀገራዊ ንቅናቄ ሊሆን አይችልም የሚለው አገላለጽ አጉል መታበይ ፈጥሮ ራስን አጠናክሮ አባል ለመሆን ከመስራት ይልቅ እኛ የሌለንበት እያሉ  እንቅፋት መሆን ላይ ማተኮር እንዳያመጣ በአማራ ስም የተደራጃችሁ መሪዎቻችሁን ሀይ ልትሉ ይገባል፡፡ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነውና ይህን የተቀደሰ መንገድ ለመከተል የማይፈልጉ ሰዎችን ( ድርጅቶችን አለማለቴ ልብ ይባልልኝ) በመጠበቅ ሀገራዊ ንቅናቄውን ለመመስረት ምክንያት የሆነው አጋጣሚ እንዳመለጠው ሁሉ ሌላ እድል ሌላ አጋጣሚ እንዲያመልጥ መፈቀድ የለበትም፡፡ይህ ደግሞ የሻ/ቃ ዳዊት የፕ/ር ጌታቸው ወዘተ ብቻ ሳይሆን ለውጥ እናፍቃለሁ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን አንዲሆን እሻለሁ ከሚል በአጭሩ ወያኔ ካልሆነ ዜጋ ሁሉ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡

መሪዎችም አባላትም ደጋፊዎችም መረዳት ያለብን ነገር፡

በሀገር ጉዳይ ጠሪና ተጠሪ፣ ጋባዥና ተጋባዥ መኖር የለበትም፣ ሊኖርም አይገባም፡፡ ይህን እንደ አምነት በመያዝ መነጋገር ሲጀመርም ሆነ ትብብር ሲፈጠር ጥያቄው መሆን ያለበት ለምን እኛ፣ ለምን ድርጅታችን አልተጠራም አልተጋበዘም ሳይሆን ለምን እኛ አልተካፈልንም፣ለምን ድርጅታችን አባል አልሆነም ብሎ ጥያቄውን ማንሳት መሪዎችን መሞገት ክርክር መግጠም በየራሳችን ቤት ነው፡፡ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ እንዲሉ እያለባበስንና እየተለባበስን ሀያ ስድስት የግዞት አመታት አስተናግደናል፡፡ አሁን ሁሉም በሻ/ቃ ዳዊት ልክ በድፍረት፣ በግልጽነት፣ በእውነት መናገር ይቻል፡፡ ግንዱ አይናችን ውስጥ ተጋድሞ ሌላው አይን ውስጥ ያየነውን ሰንጥር ለማሳየት አስር ጣታችንን መቀሰር ይብቃ፤ ራሳችንን ለመፈተሸ ለማወቅ ብሎም ለመሆን አንዷን ያቺን አመልካች የምትባለውን ጣት እንኳን ወደ ራሳችን ለማዞር ድፍረቱም ቅንነቱም ይኑረን፡፡ ይህን ማድረግ ከቻልን በሽታችንን በውል እናውቀዋለን መድሀኒቱም ይገኛል፡፡

– ይገረም አለሙ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *