“ዘመናዊ ፋብሪካ ገንብተን፤  የአገዳ አቅርቦት እጥረት ገጥሞናል” አቶ ተገኑ ገነሞ  የከሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ

ባሳለፍነው ሳምንት በከሰም ስኳር ፋብሪካ በመገኘት የሶስት ቀን የሥራ ጉብኝት አድርገን ነበር። ጉብኝታችን በፋብሪካ፣ በከሰም እና በአሚባራ የሚገኙትን በአገዳ የተሸፈኑ እርሻዎችን፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻዎችን እና የከሰም ወንዝ ግድብን ተመልክተናል።

ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ የከሰም ግድብን በተሰረሰሩ ቀዳዳዎች ዘልቀው እየፈሰሱ ስንመለከት አስደንግጦናል። ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ለመገመት ሁሉ ከብዶናል። ሌላው የፋብሪካው ዘመናዊነት አስደምሞን ሳለ፣ የአገዳ አቅርቦት ክፍተት ቁጭት ጭሮብናል። በከሰም ጋራዥ ያለው የመለዋወጫ እጥረት ደግሞ ምን ያህል የድርጅቱን ሥራዎች እንደበደለ ለመረዳት ችለናል።

በማኔጅመንቱ እና በሠራተኛው መካከል ያለውን ግንኙነት ለመፈተሽ ሞክረናል። ከሰራተኛ ማሕበር መሪዎች እና በተለያየ የሥራ ዘርፍ ውስጥ ካሉ ቅሬታ ሰሚዎች ጋር ባደረግነው ውይይት በከሰም ፋብሪካ የተፈጠሩ ችግሮች በአብዛኛው በስኳር ኮርፖሬሽን እና በመንግስት አቅም የሚመለሱ መሆናቸውን እንደሚገነዘቡ ነግረውናል። ማኔጅመንቱ ከሠራተኛው ጋር አብሮ የችግሩ ተጠቂ መሆኑ ገልጸውልናል፤ በተቻላቸው መጠን ግን ሠራተኛውን ለመደገፍ እንደሚሰሩ ነግረውናል። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅም በዓል ሳይቀር አብሯቸው በፋብሪካ እና በእርሻ ውስጥ ያሳልፋል ሲሉ ምስክርነታቸውን የሠጡ ሠራተኞችም አሉ። 

ለዛሬ ከከሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራአስኪያጅ ከአቶ ተገኑ ገነሞ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በዚህ መልክ አቅርበናል። በቀጣይ ከፋብሪካ፣ ከእርሻ ዘርፍ ሥራ አስኪያጆች ጋር የነበረን ቆይታ እናቀርባለን። 

 

ቁጥሮች በከሰም ስኳር ፋብሪካ

በከሠም ስኳር ፋብሪካ በአሁኑ ሠዓት በአጠቃላይ 5ሺ 574 (አምስት ሺ አምስት መቶ ሰባ አራት) ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ከአጠቃላይ ሠራተኞቹ፣ በቋሚነት 1ሺ 587፣ በኮንትራት 196 እና በጊዜያዊነት 3ሺ 791 ናቸው።

ከፋብሪካው የሰው ኃብት፣ አምራች ኃይሉ 82 በመቶ ሲሆን ድጋፍ ሰጪው 18 በመቶ ነው። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር 2ሺ 939 ቋሚ ሠራተኞች የመያዝ አቅም አለው ተብሎ ይገመታል። በአሁኑ ጊዜ የያዘው ቋሚ ሠራተኛ 1ሺ 587 ሲሆኑ በመቶኛ ሲቀመጥም 54 በመቶ ነው።

የአካባቢው ሕብረተሰብ ተሳትፎ በቋሚ ቅጥር 505 ሲሆን በኮንትራት 44 እንዲሁም በጊዜያዊነት (ወርሃዊ) 2ሺ 808 ናቸው። በአካባቢው የሚገኙ የከሰም ስኳር ፋብሪካ አገዳ አብቃዮች ሕብረት ሠራ ማሕበር አሉ። ከዳ ድሆ፣ ቦንቲ ጎና፣ አዳ ጉርቶ ፣ሚራህቶ እና ሀመዳስ የተባሉ አምስት የሸንኮራ አገዳ አብቃይ ህብረት ስራ ማህበርት ለፋብሪካው በኩንታል 423ሺ 262.4 ምርት አቅርበው ብር 9 ሚሊዮን 630ሺ 907.84 ገቢ አግኝተዋል።

 

ሰንደቅ፡- በከሰም ወንዝ ላይ የተሰራው የውሃ ግድብ ባለቤቱ ማነው? ግድብ ሰርስሮ የሚወጣው ውሃ ከስጋት አንፃር እንዴት ይታያል?

 አቶ ተገኑ፡- ግድቡን በባለቤትነት ያስተዳድር የነበረው የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ነበር። በአዲሱ አደረጃጀት የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ነው። በእነዚህ ተቋማት መካከል በአሁን ሰዓት ርክብክብ እየተደረገ ነው።

ግድቡን በተመለከተ ባለቤቱ ምላሽ ቢሰጥበት መልካም ነው። ስለግድቡ እንደከሰም ስኳር ፋብሪካ ማኔጅመንት ለማስረዳት፣ በዋናነት ችግር ብለን የምንወስደው ከኦፕሬሽን ጋር የተገናኘ ነው። ይኸውም የግድቡ በር መከፈት እና መዘጋት ባለመቻሉ ውሃውን በተገቢው ሁኔታ ማስተዳደር አልተቻለም። ይህም በመሆኑ ለአገዳ የሚበቃ ውሃ በፈለግን ሰዓት እያገኘን አይደለም። ውሃ ሲያንስም ሆነ የበዛ ውሃ ሲመጣ መመጠን አልተቻለም። ችግሩን ተቋቁመን እየሰራን ነው።

ከግድቡ የሚወጣው ፍሳሽን (እዣት) በተመለከተ በጣም ቴክኒካል በመሆኑ ተቋሙ ቢመልሰው ይሻላል። የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ከከርሰ ምድሩ ፍል ውሃ ተገኝቷል። ይህንን ፍልውሃ ለማስተካከል ማስተንፈሻ ተሰርቶለት በአሁን ሰዓት ሥርዓቱን ጠብቆ እየወጣ ነው። ሌላው ግድቡን እያለፉ የሚወጡት ፍሳሾችን በተመለከተ ችግሩን ለመቅረፍ ሥራዎች መሰራታቸውን እና ውጤት መገኘቱንም ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጋር በሚደረጉ ስብሰባዎች ሲገለፁ ሰምተናል። ይኸውም፣ የግራውቲንግ ሥራዎች ተሰርተው የተወሰነ መሻሻል ቢኖርም፣ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከፍሳሽ የጸዳ ነው ለማለት አይቻልም። በአካልም ከአንተ ጋር አብረን የተመለከትነው ግድቡን ሰርስሮ የሚወጣ ፍሳሽ መኖሩን ሲሆን፤ በቀጣይም ሥጋት መሆኑ አይቀርም።

ሰንደቅ፡- በአካል ተገኝቼ የተመለከትኩት ግድቡን አቋርጦ የሚወጣው ፍሳሽ ተብሎ በቀላል አገላለጽ የሚቀመጥ አይደለም። ከፍተኛ ፍጥነትና የውሃ መጠን ያለው ቢያንስ አምስት የሚሆኑ ጅረቶችን ነው የተመለከትኩት። ከዚህ አንፃር በቀጣይ ሥጋት ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ነው እንዴ? ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሥጋቶችስ በእናንተ በኩል ምንድን ናቸው?

አቶ ተገኑ፡- እንደ ስጋት ከተነሳ ግድቡ የተገነባበት ቦታ ፍልውሃ መገኘቱ በራሱ ያለውን ሥጋት ከፍ ያደርገዋል። ሆኖም በኮንክሪት ሙሌት ቱቦ ፍልውሃው እንዲፈስ በመደረጉ ለመቆጣጠር ተችሏል። አሁን ያለው ችግር ግድቡን ሰርስሮ የሚወጣው ፍሳሽ በእኔ በኩል እንደ ከፍተኛ ሥጋት አድርጌ የምወስደው ነው። ከዚህ ውጪ ግድቡን አቋርጦ የሚወጣው ውሃ ከተያዘው ውሃ ይውጣ ወይም ከፍልውሃ ውስጥ ይውጣ ባለሙያዎች የሚያረጋግጡት በመሆኑ በዚህ ላይ የምሰጠው አስተያየት የለም። እንደሚታወቀው ግድቡ የተጀመረው በ1996 ዓ.ም. ሲሆን እየተጠናቀቀ ያለው አሁን ላይ ነው። በተቀመጠለት ጊዜ የተጠናቀቀ የውሃ ግድብ አይደለም።

ሰንደቅ፡-በጠጠር ከተጠቀጠቀው ግድብ ጎን፣ በተፈጥሮ በቆሙ መለስተኛ ተራራዎች ውሃ ተገድቦ ነው ያለው። በእነዚህ ተራራዎች መካከል ከተያዘው የከሰም ወንዝ እየሾለኩ የሚፈሱት ጅረቶች የውሃ መጠናቸው በጣም ከፍተኛ ነው። በግድቡ የተያዘው የውሃ መጠን 500 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በመሆኑ፣ የሚፈሰው ውሃ ተራሮቹን እያላላ እንዲደረመሱ ቢያደርግ ጥፋቱ ምን ሊሆን ይችላል? የሳቡሬን ወረዳ እና የከሰም ፋብሪካና የእርሻ ቦታዎችን ማግኘት ይቻል ይሆን?

አቶ ተገኑ፡- በጋራ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ የክልሉ መንግስት እና ስኳር ኮርፖሬሽን ያለንን ሥጋቶች በተደጋጋሚ እናሳውቃለን። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ አዲስ የግራውቲንግ ቴክኖሎጂሥራዎች እንዲሰሩ ተደርጎ ለውጥ ማምጣት የተቻለው። ፍሳሹ በፊት ከነበረበት አሁን ላይ በጣም ቀንሷል። ሆኖም ፍሳሹ ሙሉ ለሙሉ አልቆመም። በቅርብ ጊዜም የጋራ መድረኮች ስላላካሄድን በቀጣይ ያለውን ሁኔታ ለማስቀመጥ አልችልም። ለውጦች ግን አሉ፤ የምዘና ሥራዎች ግን በጋራ አልሰራንም።

ሰንደቅ፡- የጎበኘሁት የከሰም ስኳር ፋብሪካ እጅግ ዘመናዊ ነው። በቀን አስር ሺ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም አለው። ለፋብሪካ ከሚያስፈልገው 20ሺ ሔክታር የሸንኮራ አገዳ ማሳ ወደ 3ሺ ሔክታር የሚጠጋ ማሳ ነው ያላችሁ። ይህ ምን ማለት ነው? የአቅርቦቱ ክፍተት እንዴት ተፈጠረ?

አቶ ተገኑ፡- የፋብሪካው ግንባታ ሲታቀድ፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ ፋብሪካው 6ሺ ቶን አገዳ በቀን የመፍጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ በዓመት 153ሺ ቶን ስኳር ያመርታል፡፡ እንዲሁም በሰዓት 26 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም አለው፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ፋብሪካው 10ሺ ቶን አገዳ በቀን የመፍጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ በዓመት 250ሺ ቶን ስኳር ማምረት የሚያመርት ነው፡፡ በተጨማሪም በሰዓት 39 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ፋብሪካ ነው፡፡

ወደ እርሻው ስንመጣ ሰባ በመቶ የሚሆነው አገዳ የምናመጣው ከአሚባራ ነው። ወደ አሚባራ ለምን ሄዳችሁ ለሚለው ጥያቄ፣ በከሰም በቂ አገዳ ባለመኖሩ ነው። በአሁን ሰዓት 288ሺ ሔክታር በአገዳ የተሸፈነ ማሳ በከስም ስኳር ፋብሪካ አለ። በአሚባራ 5ሺ 997 ሔክታር በአገዳ የተሸፈነ ማሳ አለን። በድምሩ ወደ 8ሺ 386 ሔክታር በአገዳ የተሸፈነ ማሳ አለን። ፋብሪካ አሁን ባለበት ቲሲዲ የሚያስፈልገው 12ሺ ሔክታር በአገዳ የተሸፈነ መሬት ይፈልጋል።

ወደ አሚባራ ለምን ሄድን? የአሰራር ሥርዓቱስ ምን ይመስላል? በመጀመሪያ ፋብሪካው ለመገንባት በተደረገው የአዋጪነት ጥናት የግድቡን ሥራ ይሰራ የነበረው የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር ነው። የውሃ ገብ መሬት ዝግጅት ሥራም ሲሰራ የነበረው ይኸው ሚኒስቴር መስሪቤት መሆኑ ይታወቃል። እነሱ መሬቱን አዘጋጅተው ውሃ ገብ አድርገው ሲሰጡን ነው፣ እኛ ተረክበን ቀሪ ሥራዎችን የምንሰራው። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ለአስር አመታት በሥራው ላይ ቆይቶ፣ በግሮስ 4ሺ ሔክታር መሬት አስረክቦ ነው ከመሬት ዝግጅት የወጣው። ይህ ማለት 20ሺ ሔክታር መሬት ለማዘጋጀት አቅዶ ወደ ስራ የገባው ሚኒስቴር መስሪያቤቱ። በመጨረሻ 4ሺ ሔክታር ነው ማስረከብ የቻለው። ስለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በከሰም ውሃ ገብ የሆነ መሬት አዘጋጅቶ ባለማቅረቡ፣ አሁን በከሰም ፋብሪካ ለተፈጠረው የአገዳ አቅርቦት ክፍተት ምክንያት ሊሆን ችሏል። ከዚህ አንፃር ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ውጤታማ ስራ አልሰራም ብሎ ማናገር ይቻላል።

ከዚህም በላይ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የፈጠረው ችግር፣ በአገዳ አቅርቦት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ምክንያቱም ፕሮጀክቱ ሲጀመር የነበረው እሳቤ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ለእያንዳንዱ ለአካባቢው አባወራ አንድ ሔክታር ውሃ ገብ መሬት አዘጋጅቶ እንደሚያቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። ከዚህ ውስጥ 0 ነጥብ 25 ሔክታር ለጓሮ አትክልት እና 0 ነጥብ 75 ሔክታር በአገዳ የተሸፈነ በ“out grower” የሚከናወን ሥራም ይሰጣል። ይህ የስምምነት ጊዜ በአካባቢው ሲታለም 775 አባወራዎች ብቻ ነበሩ። አሁን ላይ ፕሮጀክቱ አልተጠናቀቀም፤ ዛሬ ላይ ደግሞ የአባወራዎቹ ቁጥር ወደ 1ሺ 300 ከፍ ብሏል። በወቅቱ እድሜያቸው ለትዳር ያልደረሱ የአካባቢው ሰዎች አሁን አባወራ ለመሆን በቅተዋል። እንዲሁም በጊዜው በቀበሌ ውስጥ የነበረው የመሬት መጠን አሁን ካለው የአባወራ ብዛት ጋር የሚመጣጠን አይደለም። ስለዚህም እንደከሰም ስንመለከተው፣ ቀጣይ ሥጋታችን ውሃ ገብ የሆነ መሬት አለማግኘት እንዲሁም አዘጋጅቶ አለማቅረብ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ፕሮጀክቱ ሳይጠናቀቅ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሥራውን አቋርጦ ሲወጣ፣ በእኛ በኩል ትክክለኛ መረጃ አልደረሰንም። ከሌሎች አካላት ጋር ውል አስረን እንኳን የምንሰራበት አጋጣሚ አልነበረንም። የዘንድሮ አፈፃጸማችንም የሚጠበቀውን ያህል አይደለም። ምክንያቱም ድርጅታችን አገዳ ለመትከል የተዘጋጀነው፤ የእነሱን ዕቅድ መሰረት አድርጎ ነበር፣  ሆኖም ግን ውሃ ገብ የሆነ መሬት አዘጋጅተው አላቀረቡልንም፤ ዘንድሮ ደግሞ በጀት አልተመደበልንም ብለው ለቀው ወጥተዋል። በሁለታችን መካከል ግን እስካሁን የተደረገ ርክብክብ የለም። በእኛ በኩል ሥራዎችን ለማስጀመር እንኳን ከእነሱ ጋር ዶክመንቶችን አልተለዋወጥንም። እጃችን አጣጥፈን ከመቀመጥ ብለን ኪስ ቦታዎችን እያለማን ወደ ሥራ እያስገባን ነው። እንዲሁም በማሕበራዊ ችግሮች የቆመ መሬትን በራሳችን ጥረት እያስተካከልን ወደ ሥራ አስገብተናል። በርግጥ በማክሮ ደረጃ ያለውን የመሬት አቅርቦት ችግር በዚህ መልኩ በዘላቂነት መፍታት አይቻልም።

 ሌላው ከአሚባራ የሚመጣውም አገዳ በግለሰብ ማሳ ላይ የሚለማ በመሆኑ ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም። ባለሃብቱ ነገ ተነስቶ ፋብሪካ እተክላለሁ ቢለን፣ በያዝነው 3ሺ ሔክታር መሬት በመጠቀም ብቻ ኬን ሳይክሉን ጠብቆ በየአመቱ ኦፕሬት እያደረጉ ለመሄድ ትልቅ ስጋት ነው። ይህንን ችግር ለኮርፖሬሽን ለሚኒስቴሩም ያሳወቅንበት ሁኔታ ነው ያለው። በእነሱ በኩል ችግሩን ለመቅረፍ እየሄዱበት መሆኑን ብንገነዘብም፣ እንደመንግስት ግን ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት ያለበት መሆኑን እናምናለን።

እንደሚታወቀው በከሰም ዘመናዊ ፋብሪካ ነው ያለው። በሌሎች እርሻዎች እንዳየነው አገዳ ለምርት ደርሶ ፋብሪካ ተከላ የዘገየበት ሁኔታ ነው። በከሰም ደግሞ እጅግ ዘመናዊ ፋብሪካ ገንብተን፣ የአገዳ አቅርቦት ችግር ገጥሞናል።

ሰንደቅ፡- ከአሚባራ ከሰም ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ ሲሆን፣ የአገዳው እድሜም 35 ወር የሚጠጋ ነው። ከዚህ አንፃር አንድ ኪሎ ግራም ስኳር የምታመርቱበትን ወጪ አያንረውም ወይ? ዘላቂ አማራጮችስ ምንድን ናቸው?

አቶ ተገኑ፡- ከአሚባራ እርሻ የምናነሳው አገዳ በኩንታል ሃምሳ ብር ነው የምንገዛው። ከማምረቻ ዋጋ አንፃር አገዳውን በራስ አቅም አልምቶና ምርታማነቱን ጨምሮ የተከናወነ ቢሆን ትርጉም ባለው ሁኔታ የማምረቻ ወጪውን መቀነስ ይቻላል። ከአሚባራ የምናነሳው አገዳ በብዛት የሚመረት ሲሆን፤ የሚመዘነው በብዛቱ መጠን ነው። አሁን ላይ የውል ስምምነታችን አብቅቶ በአዲስ ድርድር ላይ ስለምንገኝ ወደ አዲስ ስምምነት ውስጥ እንገባለን የሚል እቅድ ይዘናል። በሌሎች ሀገሮች የሚደረገው የአገዳ አቅርቦት ድርድር የሚወሰነው፣ በአገዳው ይዘት ነው። ይህ ማለት አገዳው በሚይዘው የስኳር መጠን ብቻ የሚደረግ ድርድር ነው።

እስካሁን ባለው አሰራር ከአሚባራ የሚቀርበው አገዳ የሚመዘነው፣ በኪሎ ግራም ክብደት ነው። በኪሎ ግራም ሲቀርብ ቆሻሻውም ሌላም ባዕድ ነገሮችም አብረው ተመዝነው ነው የሚቀርቡት። ይህ ማለት የማምረቻ ወጪ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ አለ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- የአሚባራን የመጀመሪያ የአገዳ ማሳ ማግኘት የሚያስችል የ7 ኪሎ ሜትር አቋራጭ መንገድ አለ። ለምን ይህንን መንገድ ወደ አስፋልት ደረጃ ከፍ አድርጋችሁ መጠቀም አልቻላችሁም?

አቶ ተገኑ፡- የአሚባራ እርሻ ልማትን ለመጠቀም ሲታቀድ ወደ 6 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ አስፋልት በመስራት ማሳውን ለማግኘት ነበር። በ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ኤጀንሲ መንገዱን ለመስራት ኃላፊነት ወስዶ ነበር። ሆኖም በዚህ ዓመት በስምንተኛው ወር ላይ “መንገድን መስራት አልችልም፣ እራሳችሁ መንገድን ስሩ ሲል አስታውቆ፤ እስካሁን የሄድኩበትን ሰነዶች ከደብዳቤው ጋር አባሪ አድርጊያለሁ” ብሎ ከአመታት በኋላ መልሷል። ባለስልጣኑ መንገዱን ሳይሰራ ሰነድ ብቻ ለእኛ አስረክቧል። ኮርፖሬሽኑ ጉዳዩን ተመልክቶ በራሳችን አቅም ለመስራት ዲዛይኑን ተቀብለን ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን መንገዱን እንዲሰራ በማድረግ ዘላቂ የሆነ መፍትሄም አስቀምጠናል።

መንገዶች ባለስልጣን ሥራውን አልሰራም ብለን ግን እጃችንን አጣጥፈን አልተቀመጥንም። እስከ 2008 ዓ.ም. መንገዱ ይሰራል በሚል ተስፋ አድርገን ነበር፤ አልተሰራም። ስለዚህ በ2009 ዓ.ም. ባለፈው መልኩ መቀጠል አይገባም ብለን፣ በድርጅታችን አቅም አዋሽ ወንዝ ላይ ድልድይ ገንብተን አገዳ ለማመላለስ በቅተናል። በተወሰኑ ጊዜያት ግን ከፍተኛ የውሃ መጠን ያለው ጎርፍ ከአዋሽ በመነሳቱ በድልድዩ ላይ አገዳ ለማስተላለፍ የገጠም ችግር ነበር።

ከአሚባራ የሚመጣው አገዳ 70 ኪሎ ሜትር መርዘሙ ብቻ ሳይሆን ለተጨማሪ ወጪዎችም የሚዳርጉ ነገሮችን የያዘ መሆኑ መታወቅ አለበት። ይኸውም፣ ረጅም ርቀት በመሄዳችን በትራክተሮች እና በሚጎተቱ ጋሪዎች ላይ ያሉ ማሽኖችና ቁሶች ይሰበራሉ። ማሽኖቹ ሲሰበሩ የመለዋወጫ አቅርቦት በቀላሉ አናገኝም። ማሽኖቹ የመጡት ከቻይና በመሆናቸው በሀገር ውስጥ እቃቸውን የሚያቀርብ ድርጅት የለም። ሌሎቹ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት የሜቴክ ማሽኖች ናቸው። ዋይቲኦ እና ቤቢኤን ትራኮች ናቸው። ዋይቲኦ የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ናቸው የሚያስመጣቸው ምንም አይነት መለዋወጫ ማግኘት አይቻልም። ቤቢኤን ትራክም ቢሾፍቱ ኦቶሞቲቨ ነው የሚያስመጣቸው። ምንም አይነት መለዋወጫ የላቸውም።

ስለዚህም እነዚህ ማሽኖች ሲሰበሩ ጠግኖ ለማውጣት ከፍተኛ ችግር ነው ያለው። በፋብሪካ ሥራዎች ላይ የሚያስከትለው “down time” ከፍተኛ በመሆኑ፣ በፋብሪካ ውስጥ የሚፈጠሩ የአፈፃፀም ችግሮች ለእነዚህ ማሽኖች ጥገና ከሚጠፋው ጊዜ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው።

ሰንደቅ፡- 70 በመቶ አገዳው በግለሰቦች የሚተዳደር ነው። ከአሰራር አንፃር እንዴት የሚገለጽ ነው?

አቶ ተገኑ፡- ይህ ማለት እኛ በፈለግነው አቅምና መጠን በማሳው ውስጥ ገብተን መስራት አንችልም። ምክንያቱም ስለባለሃብት ስናወራ፣ ስለሃብት ማውራታችን አይቀርም። የሃብቱ ባለቤት፣ የይዞታውም ባለቤት ነው። ስለዚህም ይህንን ይዞታ ለመጠቀም፣ የባለሃብቱ ፈቃድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ 70 ኪሎ ሜትር ተጉዘን አገዳ ስናመጣ የትራንስፖርት ወጪ አለብን። በማሳ ውስጥ ገብተን እንድንሰራ ባለሃብቱ ካልፈቀደ ምንም ልናደርግ አንችልም። በማሳ ውስጥ ያለውን መንገድ ጠግኑልን የሚል ጥያቄ ባለሃብቱ ካላቀረበ በእኛ በኩል ምንም ማድረግ አንችልም።

የአሚባራ እርሻ ተዘጋጀው ለጥጥ በመሆኑ አገዳውን ለማውጣት የውስጥ ለውስጥ መንገድ የለውም። ከአንድ ማሳ አገዳ ለማውጣት፣ አራት ማሳዎች አቋርጠን ነው የምንሄደው። ማሳው ለአገዳ የተዘጋጀ በመሆኑ ለቅሞ አንስቶ ለመጫን በሚደረገው ሒደት የሚፈጠር “down time” አለ። በሌሎች ፋብሪካዎች የተዘጋጀ መንገድ በመኖሩ የተቆረጠውን አገዳ በቀጥታ ከማሳው ላይ ነው የሚያነሱት። ይህ ማለት ግን ባለሃብቱ ምንም አልሰራም የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ አይደለም። ባላቸው መጠን የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል።

ሰንደቅ፡- በከሰም ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ያሉ ችግሮች ባለቤታቸው በርካታ ናቸው። ለምሳሌ የከሰም ግድብ፣ የውሃ ገብ መሬት ዝግጅት፣ የአገዳ አቅርቦት፣ የማሽነሪ መለዋወጫዎች፣ መሰረተ ልማት እና ሌሎችም ችግሮች አሉ። የከስም ስኳር ፋብሪካ ማኔጅመንት እነዚህ ችግሮች ተቋቁሞ ተወዳዳሪ ፋብሪካ ለመሆን ምን አይነት እቅዶች ይዟል?

አቶ ተገኑ፡- ስለከሰም ስኳር ፋብሪካ ስናወራ ከሌሎች ስኳር ፋብሪካዎች አንፃር መመልከቱ ጥሩ ነው። በሌሎች አካባቢ የሆነው የአገዳ ምርት ይደርሳል፤ የመኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተሟልተው ለሠራተኞች ይቀርባል። ከሰም ላይ ደግሞ የተገላቢጦሽ ነው። በአሁን ሰዓት 5ሺ 500 የሚጠጉ ሠራተኞች ናቸው ያሉት። ከሁለት ዓመት በፊት ግን ወደ 200 የሚጠጋ ሠራተኞች ብቻ ይዘን ነበር የምንሰራው። ይህ አሃዝ የሚያሳይህ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሰሩ ውጤታማ ሥራዎች ናቸው፣ በሠራተኞች ላይ እምነት በማሳደር በርካታ የሰው ኃይል ማግኘት የተቻለው።

ስለሠራተኞች መኖሪያ ቤቶች ብትወስድ ፋብሪካ ተከላ ስንጀምር እና ሠራተኞች ስንቀጥር አንድም የመኖሪያ ቤት በከሰም አልነበረም። ሠራተኞውን ቀጥረን በእርሻ መንደሮች በአሊቤቴ በደሆ ሳይጠናቀቁ ወስደን ነው ያሰፈርናቸው፤ መብራትና ውሃ አልነበራቸውም። አሁን ላይ ግን፣ በ219 ሚሊዮን ብር ወጪ 571 የሚሆኑ መኖሪያ እና መኖሪያ ያልሆኑ ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 529 የመኖሪያ ቤት ቤቶች ሲሆኑ 42 ደግሞ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የማሕራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ናቸው።

ማሽነሪዎቹንም በተመለከተ የፋብሪካ ተከላ ኮንትራት የወሰደው ድርጅት የሆሌጅ ማሽነሪዎችን በተወሰ ደረጃ ያቀርብ ነበር። ከቻይና ዳም ትራኮች መጥተዋል፤ የሆሌጅ ማሽነሪዎችም ገብተዋል። በቻይና አምራች አላቸው። በሀገራችን ግን አቅራቢ የላቸውም። ችግሩን ለመፍታት ከአምራቾቹ ጋር ትስስር በመፍጠር በቂ መለዋወጫዎችን ለማግኘት እንደማኔጅመንት እየሰራ እንገኛለን። ኮርፖሬሽኑም በዚህ ሥራ በጣም እያገዘን ነው።

 ለሠራተኛው የሚቀርብ የመጠጥ ውሃ የለም። ችግሩን ለመቅረፍ ከአዋሽ አርባ በቦቴ በማመላለስ የውሃ አቅርቦት እደላዎች እያደርግን ነው። ይህንን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ኮርፖሬሽኑ እና ማኔጅመንቱ በሁለት የእርሻ ቦታዎች ላይ ለአንድ ኮንትራክተር ሥራዎችን አስረክቦ ነበር። ሆኖም ኮንትራክተሩ የተሰጠውን ሥራ ሳይጨረስ አቋርጦ ጥሎ ሄዷል። ኮንትራክተሩ ሥራውን ሳይሰራ በመቅረቱ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል። በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ለውሃ ኮንስትራክሽን ድርጅት ባቀረብነው ጥያቄ መሰረት የውሃ ማጣሪያ ግንባታ ውል ስምምነት እንፈራረማለን።

የመብራት ኃይል አቅርቦትን በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ2012፤ ወደ 14 ሚሊዮን ብር ለመብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ከፍያ ፈጽመናል። እስካሁን የገባ መብራት ግን የለም። በራሳችን አቅም ባመነጨነው የመብራት ኃይል እራሳችንን ችለን እየተጠቀምን እንገኛለን። ከፋብሪካው የሚመነጨውን የመብራት ኃይል ወደ ናሽናል ግሪድ ለማስገባት የ66ሺ ኪሎቮልት ትራንስሚሽን መስመር የሚያስፈልግ ቢሆንም፤ እስከሁን የመጣ ነገር የለም።

ሰንደቅ፡- የከሰም ስኳር ፋብሪካ እንደእቅዱ መጓዝ እንዳይችል ያደረጉ በርካታ ባለድርሻ አካላት እንዳሉ ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም። ይህም በመሆኑ፣ እንደማኔጅመንት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን የመለየት ሥራዎች ትሰራላችሁ?

አቶ ተገኑ፡- በድርጅታችን ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች ማንም ይፍጠራቸው ማንም፣ ከእነችግሮቻቸው ወስደን ፋብሪካችን ውጤታማ ለማድረግ ጠንክረን እየሰራን ነው። እንደተቋምም ችግሮችን እየቀረፍን ውጤታማ የምንሆንበትን መንገዶች እያመቻቸን መቀጠል እንጂ፤ ሒሳብ ለማወራረድ የተቀመጠ ማኔጅመንት የለም። ለውጤታማነት እንጂ ለመጠቋቆር ኃላፊነት አልተቀበልንም፤ ችግሮች በየትም ቦታና ስፍራ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ግንዛቤ መውሰዱ ተገቢ ነው።¾

“ከሰም ዛሬ በከፊል ለብሷል፤   ነገ በርግጠኛነት ሙሉ ልብስ ይለብሳል”  የከሰም ሠራተኞች

ከሠራተኛ መሪዎች እና ከሠራተኛ ቅሬታ ሰሚዎች ጋር ባደረግነው የጋራ ውይይት በመድረኩ ላይ የቀረበው አጠቃላይ ጭብጥ፣ በሰንደቅ ጋዜጣ ከሰም ስኳር ፋብሪካን በተመለከተ ተደጋግሞ የተዘገበው መረጃ እኛን ሙሉ ለሙሉ የሚገልጽ አይደለም። የሚገልጸን የተካተተውን ያህል የማይገልጸንም ተፅፏል። ስለዚህም አሁን በአካል ከአዘጋጆቹ ጋር መገናኘታችን ለመተራረም ያስችለናል ብለዋል።

በመድረኩ ከተዘገቡት መረጃዎች አንፃር ብዙ ነገሮች ተነስተው ተወያይተናል። እንደጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የወሰድነው አለ፤ እነሱም በዘገባው ላይ የቀረቡ ነጥቦችን በተመለከተ በመተማመን የወሰዷቸው ነጥቦ አሉ። አጋጣሚው ግን ለሁላችንም ትምህርት የሰጠን ነበር።

ከመድረኩ የተንፀባረቁ በርካታ ሃሳቦች ቢኖሩም በአንድ ሠራተኛ የተሰጠው አስተያየት ግን በጣም አስገራሚ ነበር። ከፍተኛ የሞራል ደረጃ ላይ የደረሱ ሠራተኞች በከሰም ፋብሪካ ውስጥ መኖራቸውን አመላካችም ነው። በተለይ ማጅመንቱ ምን ያድርግ ከአቅሙ በላይ ነው ብለው ችግሮችን መረዳት የሚችሉ ሠራተኞችን ማዳመጥ መታደል ነው። ጣት እየተቀሳሰሩ ለሚውሉ አሰሪዎች እና ሠራተኞች ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ በመሆኑ በዚህ መልክ ቀረበ።

ወጣት ምስጋናው ከፍያለው በፋብሪካ በቴክኒካል ክፍል ውስጥ ነው የሚሰራው። በመድረኩ በመገኘት በከሰም ፋብሪካ ያሉት ችግሮች የተረዳበትን መንገድ በዚህ መልኩ ነበር ያቀረበው።

“የሠራተኞች ፍልሰት በዋናነት የመልካም አስተዳደር ችግር አይደለም። ምክንያቱም የሰው ልጅ አንድ አካባቢ ለመልመድ አስራ አምስት ቀናቶች ቢያንስ ይበቁታል ተብሎ ነው የሚወሰደው። በእነዚህ ቀናቶች ውስጥ አካባቢውን ለመልመድ ካልቻለ ሥራውን ለቆ ይሄዳል። በከሰም በአብዛኛው የገጠመን የሠራተኞች ፍልሰት ምክንያት ከአካባቢው ጋር የተያያዘ ነው፤ አካባቢው በቀላሉ የሚለመድ አይደለም።” ብሏል።

ምስጋናው አያይዞም፣ “እንደመተሐራ የተደራጀ የሥራ አካባቢ አንጠብቅም። ተንዳሆን ብትወስደው ኮንዶሚኒየም የመኖሪያ ቤቶች ገንብቶ ለሠራተኞቹ አቅርቧል። በከሰም መብራት፣ ውሃ፣ የመኖሪያ ቤት ችግሮች አሉ። ይህንን የሚክድ የለም። የገጠሙንን ችግሮች ተቋቁመን እየሰራ፣ ነገን ዛሬ ላይ ሆነን መስራት እንችላለን። ነገ ቤት ይኖረናል፣ ቤተሰብ እንመሰርታለን፣ የተሻለ ገቢም ይኖረናል፣ ምክንያቱም እየሰራን በመሆኑ ነው። ሌላው በዚህ በከሰም ፋብሪካ ውስጥ ከተወሰኑ ቻይናዎች ውጪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ከተመለከትነው ለመጪው ትውልድ እኛ ካልሰራንላቸው ማን ሊሰራላቸው ነው? በሰለጠነው ዓለም ለመጪው ትውልድ ተብሎ የሚሰሩ በርካታ ሥራዎች አሉ። እኔም ወደፊት በእርጅና ዘመኔ ለመጪው ትውልድ አንድ ነገር ማስቀመጥ እንደቻልኩ ይሰማኛል። በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ከሰም ስኳር ፋብሪካን ለማልማት ሰው ያስፈልጋል፤ እኛ እናስፈልጋለን። ከዚህ ውጪ ማን ከየት መጥቶ ሀገር ሊያለማ ይችላል? ወላጆቻችን ለዚህች ሀገር የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ እኛ የሕይወት ዋጋ አይደለም እየከፈልን ያለነው፤ በጣም ትንሽ ዋጋ ነው እየከፈልን ያለነው። ለዚህም ነው የገጠሙንን ችግሮች አግዝፈን ያላየናቸው። በእኛ ማኔጅመንት የሚፈቱ ችግሮችን ሲገጥሙን እዚሁ ተጋግዘን ለመፍታት እንሞክራለን። ከማኔጅመንቱ በላይ የሆኑ ችግሮች በመንግስት የሚፈቱ በመሆናቸው ከመጠበቅ ውጪ ምን ማድረግ አንችልም” ሲል ሠራተኛው ያለበትን ሐላፊነት ለመድረኩ አካፍሏል።

በከሰም ስኳር ፋብሪካ ላይ ያለውን ተስፋና መተማመን ሲያስቀምጥ ምስጋናው እንዲህ ነበር ያለው፤ “ሁሉም ባለድርሻ አካል ሊገነዘበው የሚገባው እኔ ከሰም ስቀጠር፤ ከሰም ራቁቱን የቆመ ሰው ነበር የሚመስለው። ዛሬ ግን በከፊል ለብሷል፣ ቢያንስ ቁምጣ ለብሷል። ነገ ደግሞ በርግጠኝነት፣ ሙሉ ልብስ ይለብሳል። አሁን የተሰበሰብንበት ክፍል ቦታ በጣም በአቧራ የተሞላ በመሆኑ መቀመጥ እንኳን አይቻልም ነበር። ዛሬ ግን፤ ግንባታ አርፎበት ለመሰብሰብ ችለናል። ይህ የሚያሳይህ ነገ የመለወጥ ተስፋ እንዳለን ነው። በዚህ አስተሳሰብ ነው እየሰራን ያለነው። ይህ ማለት ግን ችግር የለብንም ተብሎ መወሰድ የለበትም” ብሏል።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ ዘርፍ ሠራተኛ ማሕበር ሊቀመንበር አቶ ጌታሁን አርፊጮ በበኩላቸው “የከሰም ስኳር ፋብሪካ ያለቀው ለሠራተኞች መሰረተ ልማቶች ሳይሟሉ ነው። ከአመት አመት በጣም ለውጦች እየተመለከትን በመሆኑ የተሻለ ነገር እንጠብቃለን። በሰንደቅ ጋዜጣ ችግር ተደርጎ የወጣው በጣም የተጋነነ ነው። የሥራ አስኪያጁ ችግር አይደለም። የፋብሪካው ችግር አይደለም። የኮርፖሬሽኑ ችግር አይደለም። የመኖሪያ ቤት ለመገንባት ገንዘብ ይጠይቃል። ሌሎችም መሰረተ ልማቶችም ይሟላሉ። አሁን ላይ ግን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው ብለን አንወስድም። ፋብሪካው ማምረት የጀመረው በ2008 ነው። ከዚህ በኋላ አስፈላጊ ነገሮች ይሟላሉ ብለን እጠብቃለን። በአንድ ጊዜ ሁሉም ሊሟላ እንደማይችል እንገነዛባለን” ብለዋል።

ሰንደቅ ጋዜጣ ፋኑኤል ክንፉ 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *