(የአባታችን መካነ መቃብር መፍረሱን ስሰማ በ2008 ዓም የቅድስት ሥላሴ መቃብርን ጉብኝቼ የጻፍኩትን የጉዞ ማስታዎሻ ደግሜ ማካፈል እንዳለብኝ አሰብኩ)

እናቴ ዛሬ በጣም አዝኛለሁ፡፡ ‹ሲከፋህ ቤተ ክርስቲያን ሂድ!› ባልሽኝ ምክር መሠረት እስከዛሬ አድባር ላድባር ስዞር ኖርኩ፡፡ ዛሬ ግን ቤተ ክርስቲያን ሂጄ ‹ምክርሽን ባልሰማ ኖሮ› እያልኩ ተጸጽቻለሁ፡፡ ይህች ከርሳም መሬት ይህን ሁሉ ሕዝብ በልታ አለመጠርቃቷን አወቅኩ፡፡ ይኸዉ አዲስ አበባ ከመጣሁ ጀምሮ አንድም ቀን ደስ ብሎኝ አያዉቅም፡፡ ከአድባር አድባር ሰንከራተት ዛሬ ‹ቅድስ ሥላሴ ካቴደራል› እምባለዉ ቤተ ክርስቲያን ዘንዳ ሄድኩ፡፡
ቤተ ክርስቲያን በላይኛዉ በር ሥገባ የታጠቁ ወታደሮች የተቀመጡበት አንድ በእምነ በረድ የተንቆጠቆጠ ዛኒጋባ ቤት አየሁ፡፡ ወታደሮቹን ስመለከት በስህተት አጠገቡ ካለው ፓርላማ የገባሁ መስሎኝ ደነገጥኩ፡፡ ፊት ለፊት በቅርጻ ቅርጽ የተንቆጠቆጠ የሚያምር ህንጻ ስመለከት ቤተ ክርስቲያን መሆኑን እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ ‹ታዲያ ለምንድን ነው ወታደሮቹ የሚጠብቁ?› እያልኩ ብዙ አሰብኩ፡፡
‹አንድም እንኳ ጻድቅ ሰው ጠፍቷልና› እንዳለው መጻፉ ጸሎተኛ ሰዉ ጠፍቶ ወታደሮቹ ሰይጣንን የሚጠብቁ ይሆኑ? መቼም አዲስ አበባ ብዙ ነገሯ ግራ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ የልማታዊ መንግሥታችን የወታደራዊ ጥበብ እድገት አሳይቷል ማለት ነዉም አልኩ፡፡ ‹ሊማሊሞ ገደል ያለውን ሰይጣን ጣሊያኖቹ አስረውታል› ስላልሽኝ ነዉ ይህን ማሰቤ፡፡
እማዬ፡ የቤተ ክርስቲያኑ ስፋት ትልቅ ሁዳድ ነው፤ በዚያ ላይ አሰራሩ ሲምር፡፡ ግና ከኛ አገር የክርስትና አስተምሮት ጋር የሚቃረን ነገርም አይቻለሁ፡፡ በህንጻው ዙሪያ፣ አናት ላይ፣ ግድግዳ ላይና መሬትም ላይ የብዙ ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ሥእል ተቀርጧል፡፡ ሰው ደግሞ ያን ቅርጻ ቅርጽ እየመጣ ይሳለመዋል፡፡ በእኛ ሀገር ቅርጻ ቅርጽ ቤተ ክርስቲያን አይፈቀድም፡፡ አዲስ አበባ ግን ቤተ ክርስቲያኑ ሁሉ በቅርጽ የተሞላ ነው፡፡ እንዲያዉ ለምሳሌ መጥመቁ ዮሐንስ ጌታን ሲያጠምቅ የተቀረጸውን ብታየው እኔ ራሴ የማውቀው የማውቀው እስቲመስለኝ ድረስ ተገርሜ አየሁት፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ በር ብዙ ሰዎች ተቀምጠዉና ቆመዉ ተቀርጸዋል፡፡ ተቀምጦ መጽሐፍ የሚያነበው ራሰ በራ ግን ‹ጴጥሮስ› ሳይሆን አይቀርም፡፡
እና እልሽ እናታለም! ቤተ ክርስቲያኑ ተሳልሜ ወደ ዛፎቹ ገባሁ፡፡ ዛፎቹ ውስጥ የሚያለቅስ፣ የሚያነብ፣ የሚያወራ፣ ስልክ የሚነካካ ሰዉ.. ብዙ ነው፡፡ ብቻውን ያለ ሰው ጎን ሂጄ ተቀመጥኩ፡፡ ‹‹ጌታው እንዚያ ወታደሮች ምን እያደረጉ ነዉ?›› ብዬ ስፋራ ስቸር ጠየቅኩት፡፡
‹‹የጠቅላያችን መቃብር እየጠበቁ›› አለኝ፡፡ አሁን ሁሉ ነገር ተገለጠልኝ፡፡ የቀድሞው ጠቅላያችንን አስከሬን እንዳይጠፋ ወታደሮቹ በሁሉም አቅጣጫ እስከ አፍንጫቸው ታጥቀው ይጠብቃሉ፡፡ የሮም ወታደሮች ትዝ አሉኝ፡፡ የሮም ወታደሮች እደለኛ ስለሆኑ ከሦስት ቀን በላይ መቃብር አልጠበቁም፡፡ የጌታን መቃብር ሥለነበር የሚጠብቁት በሦስተኛው ቀን ድንጋዩ ተንከባሎ አስከሬኑም ጠፋቸው፡፡ ‹የልማታዊው ሀይማኖት› መሥራች ጌታ አስከሬን እስካሁን አልተነሳም፤ እንደተኛ ነው፡፡ ትንሳኤው መቼ እንደሆነም ያወቁ አይመስለኝም፡፡
ተኛ አገር አስከሬንን የሚፈልግ አራዊት ‹አውጭ› የሚባለው አይደለም እማዬ? አውጭ አዲስ አበባ የለም፡፡ ጉድጓድ አጥቶ አይመስለኝም፡፡ ጉድጓድማ በየቦታው ሽህ ተሚሊዮን አውጭ መደበቅ የሚችል ሥርቻ መልቷል፡፡ አዲስ አበባ በየቦታው ጉድጓድ ብቻ ነው፡፡ አውጩም ቢሆን መቆፈር ሳያስፈልገው መብላት የሚችለው ብዙ አስከሬን አያጣም ነበር፡፡ እንዴው አወራዉሽ እንጅ የጠቅላያችንን አስከሬን የተቀበረበት ቤት እንኳን በአውጭ ጥፍር መንገድ የሚሰራው የቻይናዎቹ ቆፋሪ መኪናም የሚንደው አይመስለኝም፡፡ ልማታው መንግሥታችን መካሪ አጥቶ ነውጅ አውጭም አያወጣውም ነበር፡፡ ‹የእነርሱ ጌታም› ተመችቶት አንቀላፍቷል፤ ተዚህ በኋላ አይነቃም አይነሳም፡፡ ሮማዉያን ወታደሮች ጎን ወዳለው ፓርላማ ቤት ሂደው ቢጠብቅ የተሻለ ነበር፡፡

መቶ በመቶ ‹የልማታውያን ሀይማኖተኞች› የጸሎት ቦታ በሆነው ፓርላማ በኩል ልወጣ ስሄድ እኒያ ስማቸው ረጅም የሆነው ከጠቅላያችን ጋር በአንድ ሰሞን የሞቱት ፓትሪያርክ ‹ዙፋን› ላይ ተቀምጠው ተቀርጸዋል፡፡ ተግራቸው ሥር ስማቸው በአምስት መስመር ተጽፏል፡፡ ረጅም በመሆኑ ጊዜና ወረቀት ለመቆጠብ ዘልየዋለሁ፡፡ ከተቀመጡበት ወንበር ላይ ደግሞ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ‹መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል› የሚል ጥቅስ አነበብኩ፡፡ እሳቸው ግን አቀማመጣቸውን ያዬ ሰው እንኳንስ ሮጠው የተጋደሉ ከተቀመጡበት ወንበርም ተነስተው የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ የጽድቅ አክሊል ወደ ፊት የተዘጋጀ ሳይሆን ትተውት የሄዱ ነው የሚመስለው፡፡ አቤት እንዴት ያለ የሚያምር ‹ዙፋን› የመሰለ የሚመች ወንበር አምልጧቸዋል እናቴ! የእሳቸውን ሳይ ‹የጠቅላይ ጌታችን› ሐውልት አለመቀረጹ አናዶኛል፡፡ ግነ እዚሁ አዲስ አበባ አንድ ወረዳ የእሳቸውን ቀረጽን ብለው ኃይሉ ሻውልን አስመስለውት አዲስ አበቤ ሁላ ስላማቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡

በስመ ረጅሙ ፓትሪያርክ ጎን ‹አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘጎንደር› የሚባሉ አባት ተቀርጸዋል፡፡ አይናቸው በእርጅና የሞጨሞጨ ምስኪን ቢጤ ይመስላሉ፡፡ ይቁሙ ይቀመጡ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ቅርጻቸው ጉርድ ስለሆነ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ ከእኚሁ ጳጳስ ጎን ደግሞ ማስጠንቀቂያ የተጻፈበት ሐውልት አለ፡፡
‹የማነው ብላችሁ እንዳትጠይቁ፣
የጀግናው ሠፈር ነው እንግዲህ እወቁ፡፡
ስታልፉ በተራ ሥትመላለሱ፣
መርድ ታክቶት አርፏል እንዳትቀሰቅሱ፡፡› የሚለው ጽሁፍ የተጻፈው ሌ. ጄኔራል መርድ መንገሻ ተሚባል ሎጋ ሰው ሐውልት ላይ ነው፡፡ ሲያዩት ገና ሎጋ ወጣት ነው፤ ባይታክተው እንዴት ጥሩ ነበር፡፡ ማስጠንቀቂያውን ገቢራዊ አድርጌ ቀስ ብዬ በእግሬ ጥፍር አለፍኩ፤ እንዳለው ከተነሳ!
ተነዚህ ሰዎች ሐውልት ፊት ለፊት ያለውን የሐውልት ብዛት ስመለከት ‹አይ ይህች መሬት ስንቱን ሰው በልተዋለች?› ብዬ ተቆጨው፡፡ እመቤቴን የእኛ ሀገር መሬት የማትጠግብ ከርሳም ናት፡፡ ስንቱ ልማታዊ፣ ስንቱ አርቲስት፣ ስንቱ ጋዜጠኛ፣ ስንቱ ደራሲ፣ ስንቱ ታዋቂ ሰው ‹ድፍት ብሎ› ቀርቷል በማርያም!

ደሞ እኮ እማ ተዚህ ቤተ ክርስቲያን የማይታወቅ ሰው አይቀበርም አሉ፡፡ መቼም አንቺ ሞኝ ስለሆንሽ እግዜር ታወቀውስ? ትኛለሽ፡፡ በዚህ አገር በሰው እንጅ በእግዜር መታወቅ ጭንቅ አይደለም፡፡ በልማታዊው ስብስብ እንጅ አንቺ ቅዱሳን በምትያቸው ቅርበት ምንም አይፈይድም፡፡ ልማታዊው ክምችት ካወቀሽ ሰማያዊው አምላክ ያውቀዋል ብለው ነዉ የሚያስቡት፡፡ ተኛ ሀገር ካህን የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ አለው እንደምንለው አዲስ አበባ ደግሞ የመንግሥተ ሠማያት በር ‹በልማታዊ ወታደር› ትጠበቃለች፡፡ የኪሩቤልና የሱራፌልን ግብር ለመተካት እንችላለን የሚሉ ይመስላል፡፡ የኪሩቤል ሱራፌል የምትገለባበጥ ሰይፍ በአጋዚ ክላሽንኮቭ ሳትቀየር አልቀረም፡፡
ይህ የታዋቂ ሰዎች የመቃብር ሰፈር ብዙ ገራሚ ነገሮች አሉት፡፡ እያንዳንዱ ሰው ሐውልት ላይ ‹ሟቹን› የሚገልጽ ጽሁፍ ወይም ቅርጽ ተሰርቷል፡፡ ፖለቲከኞቹ ፊት ለፊት ሠፊ ቦታ ይዘው ይታያሉ፡፡ እኔ እንዴውም እነዚህ ሰዎች ሞተውም መሬት ይነግዳሉ እንዴ? ብየ ነበር፤ መልስ አጣሁ እንጅ፡፡
በጥር 2002 ዓ.ም. ሊባኖስ ተሚባል ሀገር ተነስተው ሲመጡ አየሩ ውቅያኖስ ውስጥ ገብቶ የሞቱት ሰዎች ያለአስከሬን በጅምላ ሐውልት ተሰርቶላቸዋል፡፡ እንዲያውም ሐውልቱ የሚመስለው አዋሳ ከተማ ገብሬል ፊት ለፊት የቆመውን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሐውልት ነው፡፡ የጥቂት ሰዎች ፎቶና ስም ከሐውልቱ ላይ ተለጥፎበታል፡፡ ያው ከሞቱት ሰዎች ውስጥ ክርስቲያንም፣ እስላምም፣ ፕሮቴስታንትም፣ የማያምንም … ቢኖርም ሥላሴ አርባ ቀጽር ውስጥ ሐውልታቸው ተሰርቷል፡፡
ያው ሥላሴ ለመቀበር መታወቅ እንጅ እምነት መሥፈርት አይመስለኝም፡፡ በፕሮቴስታንትነቱ የሚታወቀው ልማታዊው የክልል ርዕሰ መስተዳደር አለማየሁ አቶምሳ ለሥላሴ መንበር ከእሱ የቀረበ የለም፡፡ ፊቱ ግን አልተፈታም- እየጸለየ ነው መሰል፡፡ እንግዲህ በቁሙ የተዋቸውን ሲሞት ለማካካስ ይሆናል፡፡

ጥላን ገሠሠ ቆሞ እየዘፈነ አለ፡፡ ከጥላሁን ሐውልት ላይ ሙዚቀኞቹ በፈረንጅኛ ‹ጂ ክሌፍ› የሚሉት ምልክት፣ መስቀልና የዳዊት ኮከብ አብሮ አለ፡፡ መስቀሉ ክርስቲያን ነበርኩ ለማለት ሲሆን የዳዊት ኮከቡ ግን ምን እንደሆነ አላወቅኩም፡፡ መቼም በአይሁዳዊነትና በክርስትና መካከል ያለ እምነት የለም፡፡ ጥልሽ ሞቶም ‹‹ትንፋሼ ተቀርጾ ይሁን ማስታዎሻ›› ይላል፡፡ ቀርቤ በስልኬ ልቀዳው ብሞክር ዝም ጭጭ ያለ ነው፡፡
ሰሞኑን ‹የታሪክ ማስታዎሻ› የሚለውን መጽሐፋቸውን ሳነብ ሰንብቼ ከዚህ ደግሞ ሐውልታቸው ሥር የሚነበብ ትተውልን ሳይ ጊዜ ‹የማይደክማቸው ብርቱ ሰው ናቸው› ብዬ ተገረምኩ፡፡ ‹ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ከ1894- 1997፤ የኢትዮጵያዊነት ግዳጆቼን ሁሉ በንጽህና ስለፈጸምኩ ተወድጄ ተከብሬና ታምኜ አልፌያለሁ› ይላል፡፡ መቶ ሦስት አመት መቀመጥ መታደል ነው፡፡ የደጃዝማች ገሞራው በላይ የጥጥ ፍልቃቂ የመሰለ ጥርሱን እያሳዬ የተነሳው ፎቶ ብቻ ነው ያለው፡፡ በአይን የሚገባው በትልቁ የተጻፈው ገሞራው የሚለው ብቻ ነው፡፡ ወደ ውስጥ ገባ ሥል ሀዲስ አለማየሁን አየዋቸው፡፡ ሰብለወንጌልና በዛብህን ‹ጎሓ ጽዮን› ቀብረው ከዚህ ከመንጋው ጋር ሳገናቸው በመገረም ፈገግ አልኩ፡፡
የዋጉ ርእሰ መኳንንት ‹ክቡር ዘዋግ ሥዩም ወሰን ኃይሉ› በእርሳቸው ምስል ፈንታ መቃብራቸው ላይ ላሊበላን ቤተ ክርስቲያን አሰርተዋል፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ› እያሉ የተማጽኖ ጦማራቸውን ከፎቷቸው ስር ከተብውታል፡፡ ወደ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን ስንቃረብ አይኔን ዘወር አደረግኩት፡፡ አርቲስት አስናቀች ወርቁ ክራሯን አሁንም እንደተሸከመች ነው፡፡ የክራር ፍቅር እስከሞት ድረስ ይኸ ነው፡፡ ከያነዉ አብርሐም አስመላሽም በዚያው አካባቢ አርፏል፡፡ ከሥር የተጻፈው ብዙ ስለሆነ ላልፈው ግድ ብሎኛል፡፡ የተከበሩት ገጣሚ የዓለም እውቅ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን መጽሐፍ በእጁ እንዳንጠለጠለ ነው፡፡ ‹አፈር ሥሆን አንድ ቅኔ ተቀኝልኝ› ብለው ዝም ጭጭ፤ አይናገር አይጋገር፡፡

ወደ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን መንገድ በፎቅ ተነባብረው የተቀበሩ ሰዎች የትየለሌ ናቸው፡፡ ቀብር በኮንዶሚንዬም ይመስላል፡፡ ዝነኞቹና ሐብታሞቹ መሬቱን ስለተቀራመቱት ሰባት ክንድ መሬት ጠፍቶ ነዉ መሰል ከሰው ላይ ሰው ተነባብሮ የተኛበት አስከሬን ብዙ ነው፡፡ ጀሞ ኮንዶሚንየም የሚኖረውን ሕዘብ ያክል እዚህም አለ፡፡

ባለወልድ ቤተ ክርስቲያንን ስመለከት ለሥላሴ ጀርባዉን የሰጠ ብቸኛ ሐውልት አየሁ፡፡ ደሞ ማነው በሥላሴ ያኮረፈ? እያልኩ ሐውልቱን ቀርቤ አየሁት፡፡ የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ነው፡፡ ፕሮፌሰር አስራት ሥላሴ እንዳይቀበሩ ሲከለከሉ ጀርባቸውን ሰጥተው ባለወልድ በብቸኛነት ከተሙ፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ ሲታገሉ ሕይታቸው እንዳለፈ የተጻፈው ገድላቸው ያስረዳል፡፡ ከቅራቅንቦ ስብስብ ብቻን መሆን የመረጡ ይመስላል፡፡ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያንን ዞርኩት፤ ከርሳም መሬት የበላቻቸውን ሰዎች ታሪክ አነበብኩ፡፡ ወደ ሥላሴ ተመልሼ በሌላ አቅጣጫ ሄድኩ፡፡ የጳጳሳት የተለየ የቀብር ቦታ አለ፡፡ ባለ ስመ ረጅሙ ፓትሪያርክ ከጳጳሳት ጋር ለምን እንዳልተጨመሩ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ግን ጳጳሳት በህብረት ‹‹አንፈልግዎትም›› ብለው ያባረሩዋቸው ነው የሚመስል፡፡ እኔማ ‹ዘመድ ከዘመዱ አህያ ታመዱ. እንደሚባለው ‹አባታችን!› ከጳጳሳት ይልቅ ለፖለቲከኞች ቀረብ ብለው የከተሙት ፖለቲከኛ ነበሩ እንዴ ብዬ አማዋቸው፡፡
ከዚያ ቀጥሎ የሌሎች ሰዎች መካነ መቃብር ደግሞ አለ፡፡ ደምሴ ዳምጤ ኤርፎን ጆሮው ላይ ሰክቶ ሲመለከቱት አሁንም ዜና ለማንበብ የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ እሱን ጨርሼ ወደ በር ልሄድ ስል ‹የአጋዚ ወታደሮችን› አየዋቸው፡፡ ልጸልይ አልኩና በጀርባዬ የደገነ መሳሪያ እንዳለ ሳሰብ ቀልቤን መሰብሰብ ተሳነኝ፡፡ የጠቅላያችን ጠባቂዎች በታችኛው በር ልወጣ ስሄድ ፓትርያርኩ አሁን እንደተቀመጡ ናቸው፡፡
የሥላሴ አንደኛው በር በፓትርያርኩ ሌላኛው ደግሞ በጠቅላዩ ይጠበቃሉ፤ ወይ ሀጣንን አሊም ጻድቃንን ሊያባርሩ፡፡

Muluken Tesfaw

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *