ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

“አውራ ዘለሉ” መሪ ማን ነው? ሕወሃት በወደብ አልባነት ህመም ከ40 ዓመት በሁዋላ !!

President Isaias Afwerki with Meles Zenawiኢትዮጵያ ዳግም የባህር በር እንዲኖራት የሚሆነው እንዴት ነው? ከሶማሌ በመከራየት? ከኬናያ ወይም ከሱዳን በመወዳጀት?  ወይስ አሰብን መልሶ በመያዝ? ለሚለው ጥያቄ መልስ የለም።  ኢሳያስን ማስወገድ የሚል የቆየ ሃሳብ አለ። ኢሳያስ ከወደቁ በሁዋላ ምን ሊሆን? አዲሱ የኤርትራ መንግስት ከህወሃት ጋር ሆኖ ትልቅ ሊሆን? የኤርትራና የትግራይ ህዝብ ተዋዶና ተስማምቶ የቀጠናው ታላቅ ሃይል ሊሆኑ? ሰሞኑንን ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ አገር መሆን የለባትም በሚል የተነሳው ሃሳብ አዲስ ነው? ለምን ዛሬ? ለመሆኑ ኢሳያስን ማውረድ ዛሬ ቀላል ነው?

ኢህአዴግ እጅግ በሸተተ መንገድ ላይ እየዳከረ መሆኑንን የሚገልጹ ወገኖች በርካታ ናቸው። ኢህአዴግ በመከላከያ አመራሮቹ ታማኝነትና ደህንነቱ ሙሉ በሙሉ ከአንድ ባህር የተቀዳ በመሆኑ እንጂ እንደ ድርጅት ከሽፏልም እየተባለ ነው። ራሱ ኢህአዴግም ” ጥልቅ” የሚባል ተሃድሶ ብቸኛ የመዳኛ መፍትሄ ነው ሲል ያወጀው የሚነገረው ሁሉ ትክክል መሆኑንን አምኖ እንደሆነ በተደጋጋሚ በአደባባይ ራሱን በራሱ እየዘለፈ ማረጋገጫ አቅርቧል።

ኢህአዴግ – አስመራ ላይ ምን አሰበ? ” ጥልቅ ጥናት እየተደረገ ነው፤ ተግባራዊ የሚያደርገው ሕዝብ ስለሆነ ሲጠናቀቅ ይፋ ይደረጋል” ሃይለማሪያም ደሳለኝ

ህወሃት በረሃ እያለ ጀምሮ ሲያቀነቅነው የነበረውን የብሄር ፖለቲካ እንዲያረግብ ሲጠይቅና ሲመከር፣ አገሪቱን በቋንቋና በብሄር ሲከፋፍል አድሮ ችግር እንደሚፈጥር ሲነገረው፣ አገሪቱን ወደብ አልባ ማድረግ ዞሮ ጣጣው ብዙ ነው በሚል እንዲያስብ አቅጣጫ ሲጠቆም፣ በተለይም የምስራቅ አፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካና የቀይ ባህር ፖለቲካ አደጋው ሊጥብሰን እንደሚችል ባለሙያዎች ሲወተውቱ፣ የግብርና ፖሊሲው ችግር እንዳለበት መርጃ ሲቀርብለት፣ የብቃት ሳይሆን የፖለቲካ ሹመት የአገሪቱን ተቋማት እንዳሽመደመዳቸው ሲጠቆም … አልሰማ ያለው ኢህአዴግ ዛሬ ከሶስት አስርት ዓመት በሁዋል በራሱ ሰዎች ውድቀቱን እየመሰከረ እንደሆነ ራሳቸው የመንግስት መገናኛዎች ዋቢ ናቸው።
በቅርቡ አገሪቱ ውስጥ አክራሪ ብሄርተኛነት አስጊ ደረጃ መድረሱን አምነዋል። የትምህርት ፖሊሲው ዋጋ ቢስ እንደሆነ አምነዋል። ቢሮክራሲው የከሸፈ መሆኑን አምነዋል። ሙስና የአገሪቱ ዋና አደጋ መሆኑን አምነዋል። በአጋር ፓርቲዎችና በአቻ ድርጅቶች መካከል መተማመን አለምኖሩን አምነዋል። የምስራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ ኢትዮጵያን የባህር በር አልባ አገር ስለሆነች ሊያገላት እንደሚችል አደባባይ ወጥተው አምነዋል። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ስለሆነች እና ትልቅ ኢኮኖሚ ስላላት ከቀይ ባህር ፖለቲካ ልትገለል አይገባም በሚል ድሮ ሆን ብለው ለሰሩት ጥፋት ይቅርታ እንኳ ሳይጥይቁ እየወተወቱ ናቸው። በዚህ ሁሉ ላይ አሁን አገሪቱ በወታደራዊ እዝ ስር መውደቋና ህዝባዊ አመጹን ተከትሎ የደረሰው ሰብአዊ ቀውስ፣ እስር እና ተመሳሳይ ጉዳቶች አሁን ያለውን የሸተተ መስመር አመላካች ሆነው ይወሰዳሉ።
አንዴ “እብድ” ሌላ ጊዜ “አጉራ ዘለል” እየተባሉ ሲሰደቡ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የቀይ ባህርን እየከፋፈሉ ለታላላቅ የአረብ አገራት ማከራየታቸው ዛሬ ላይ እብደና አጉራ ዘለል የሚያስብላቸው አልሆነም። ጓዳዩን የሚከታተሉ እንደሚሉት ” እብድና አጉራ ዘለሎቹ የኢህአዴግ በተለይም የህወሃት መሪዎች ናቸው” ምክንያቱም አሰብን የሚያክል ወደብ ሆን ብለው አስረክበው ” አስብን እኛ ካልተጠቀምንበት የግመል መፈንጫ ይሆናል” እያሉ በፓርላማ ገልፍጠው ያስገለፍጡ ነበርና!!

Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

Image result for ethio eritrea war
” በጤናችሁ ነው” በሚል አሰብን ኢትዮጵያ መወስድ እንደምትችል የተባበሩት መንግስታት ሲወተውት ” የለም አንፈልግም ፤ ወደብ አያስፈልገንም “ በሚል መልስ ይሰጥ እንደነበር የሚያስታውሱ፣ እብድና አጉራ ዘለል ማን ነበር? ሲሉ ይጠይቃሉ። ሲገለፈጥለት የሚገልፍጥ የነበረውን ፓርላማም ከአጉራ ዘለልነት ደረጃ ያወርዱታል። የባህር በርን በሚያክል ታላቅ ጉዳይ ገልፍጦ ማስገልፈጥ ታሪክና ጀግንነት ሆኖ ዛሬ ድረስ ይማልበታል። እንደ ውቃቢ ይማተብበታል።
ሰሞኑንን የቀድሞው የመከላከያ ኤታማጆር ጀነራል ጻድቃን ቀይ ባህርን አስመልክቶና ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ አገር መሆኗን አንተርሰው ያቀረቡት ትንተና፣ ስጋት፣ አደጋ… ማንም ዜጋ ሊጋራው እንደሚገባ ስምምነት አለ። ጻድቃን የበሰለ ሙያዊ አስተምህሮት አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ይህንን ሁሉ ያወቁት ዛሬ ከ30 ዓመታት በሁዋላ ነው እንዴ? የሚል ጥያቄም ተነስቶባቸዋል። ለምንስ ዛሬ አነሱት? ድሮ የጋረዳቸው የትኛው ስራቴጂ ተበላሸ? የትኛው ህልም በነነ?
ሰባ ሺህ በላይ ወገኖቻችንን በአጭር ቀን ውስጥ እምሽክ ያደረገው የባድመ ጦረንት እንደ ጎርፍ በፈሰሰው የጀግኖች ደምና፣ በተከሰከሰው አጥንት ወደ ድል ሲቀየር አሰብ በቁጥጥር ስር እንድትሆን ኮማንድ ፓስቱ ትዕዛዝ ቢሰጥም ” ባለ ራዕዩ” መሪ መከልከላቸውን ስዬ አብርሃ መናገራቸው ይታወሳል። በወቅቱ ጻድቃን ይህንን እርምጃ እና ውሳኔ ስለመቃወማቸው መረጃ የለም። ዛሬ ከሁለት አስርት ዓመታት በሁዋላ ኢትዮጵያ የባህር አልባ አገር መሆኗ የሚያስከትለውን አደጋ ሲናገሩ ስለዚህ ጉዳይም አልተጠየቁም። በወቅቱ የዛሬው አደጋ እንዴት ያዩት እንደነበር እንዲናዘዙም አልተጋበዙም።
በሎንደን የሚኖር አንድ አስተያየት ሰጪ እንዳለው ጻድቃን ዛሬ በውብ ገለጻ ያሰቀመጡት የባህር በር አልባነት ጉዳይ ደሮ ጀምሮ ደምና አጥንት ሲገበርበት የነበረ፣ ትውልድ ዋጋ የከፈለበት፣ የባህር በርን ማጣት ከአንገት መቆረጥ ጋር በማያያዝ ዜጎች በሙሉ የሚምሉበት የኢትዮጵያዊነት ማህተም ነበር። ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረን ማህተም አውልቀውና አንቋሸው የጣሉ ክፍሎች ዛሬ ተመልሰው ለዚህ ዋጋ ሲከፍል ለኖረ ህዝብ ስለ ባህር በር ለማስረዳት መሞከራቸው አስፋሪ ነው።
ጻድቃን በማንኛውም አግባብ ኢሳያስ አፉወርቂ መወገድ እንዳለባቸው በሚጠይቁበት ማብራሪያቸው ዙሪያ የተነሱ ሃሳቦችና ክርክሮች መጨረሻሸው ” ትንታኔው እጅግ የዘገየ፣ የመሸበት ነው” የሚል ነው። ከሁሉም በላይ አሁን በሃይል ኢሳያስን የማንበርከክ ዘመቻ ቢታቀድ ውስጥ ያለው ችግርስ? የሚሉት እና የቀይ ባህር ላይ ስምምነት ያደረጉ ሃብታም አገሮችን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ሲታሰብ ጉዳይ ከመዘግየትም በላይ የተወሳሰበ ያደርገዋል።
ጻድቃን እንዳሉት፣ ዓለምም እንደሚያውቀው ኢሳያስ የቀይ ባህር ላይ ባካሄዱት ስምምነት ከፍተኛ የሚባል ገቢ አግኝተዋል። የጦር የጋራ መከላከል ስምምነትም ፈርመዋል። በስምምነቱ መሰረትም በመሳሪያ ሃይል ፈርጥመዋል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ወገን አሁን በረሃብ፣ በውስጥ የፖለቲካ ችግር፣ በተቃውሞና፣ በጥላቻ ፖለቲካ ሳቢያ ጦርነት መሸከም የሚችል ደጀንና ሎጂስቲክ እንደማይኖር የሚናገሩም አሉ። በተለይም የአማራ ብሄርተኛነት እንቀስቃሴና በኦሮሚያ ዝም ያለ የሚመስለው ነገር ግን ቁርሾና ቂም ያዘለው “የነጻነት” ጥያቄ ኢህአዴግ ከውስጥ አልፎ ወደ ውጭ ለማየት የተጋረጠበት ችግር እንደሆነ የሚያምኑ ጥቂት አይደሉም። ራሱ ኢህአዴግም ቢሆን ” አስቸኳይ አዋጁን በተመለከት ጥሪ አይቀበልም” ማለቱን የችግሩን ግዝፈት ሊክድ እንደማይችል እንደ ምስክር ይጠቅሱበታል።
ዛሬ ድረስ የበረሃ ስሙን ያልቀየረው ህወሃት፣ በተገንጣይ ስም / የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ/ እየተባለ አገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ ሁሉ እንደ ዛሬ አሳሳቢ ፈተና ውስጥ ገብቶ አያውቅም። ችግሩ ከውስጥና ከውጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ሊፈታ የሚችል አለመሆኑ አድሮ ወዴት እያሰኘና እያስጨነቀ ነው። በሃይል ችግሮችን ለመቀልበስ የተኬደበት መንገድ ለጊዜው አንጻራዊ ሰላም የሰፈነ ቢመስልም፣ ሰፈነ ከሚባለው አንጻራዊ ሰላም በላይ ጠባሳው የሚያበራ፣ የሚታይ፣ በቀላሉ ሊጠግ የማይችል፣ በደም የታጀለ መሆኑ ብሄራዊ እርቅ ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ይታመናል።
የውስጡን ችግር በብሄራዊ እርቅ ዘግቶ ወደ ውጭ ማየት ካልተቻለ ኢትዮጵያን እየበላት ያለው የብሄረተኛንት ብልና የፖለቲካው ዝግነት፣ የህዝቦች ትክክለኛ የስልጣን ውክልና ጥያቄና የታሪካዊ ጠላቶቿ ደባ አንድ ላይ ተዳምርው መጨረሻውን እንዳያበላሹት አገር ወዳዶች ስጋት አላቸው።
በቀይ ባህር ላይ የአረብ አገራት እንዲፈነጩ መደረጉ እስራኤልን ጨምሮ አሜሪካንና ምዕራብ አገራትን የሚያስደስት ባለመሆኑ፣ የሚፈጥረው የተለየ እድል ካለ ወደፊት የሚታይ እንደሚሆን ከማስብ በተለየ ለጊዜው አስተያየት መስጠት እንደሚያስቸግር የለንደኑ ነዋሪ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ 1000 ኪ/ ሜትር ታሪካዊ የባህር በሯን አስከበረው የኖሩ ጅግኖች ያሉዋትን ያህል፣ ወደው፣ ፈቅደው፣ አያስፈልግም፣ የባህር በር አይጠቅመንም በሚል ገልፍጠዋና አስገልፍጠው ባህር አልባ ያደርጓት መሪዎች መርተዋታል። የባህር በሯን አስከብረው የኖሩ ” ወራሪዎች ” እየተባሉ በራሳቸው አገር ሚዲያ ሲዘለፉ፣ ባህር አልባ አድርገው ያነጠፏት እየተወደሱ ናቸው። ራዕያቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሰፋ ከቋሚው በላይ በጀት እያሻመዱ ነው።

ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ ……………….የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ …………..ይሏል ይህ ነው

” አሰብን መልሰን የኢትዮጵያ እናደርጋለን የሚሉ ይችላሉ፤ ኢህአዴግ ግን አንድም እርዳታ አያደርግላቸውም። ጉዳዩ በህዝብ ድምጽ የተወሰነና የተዘጋ ፋይል ነው” ሃይለማሪያም ደሳለኝ የኢህአዴግ የምርጫ ሹምና ቃል አቀባይ በነበሩበት ወቅት ስለ አሰብ ወደብ ተጠይቀው የመለሱት ነበር። በወቅቱ ምላሻቸውን የመለስን ንግግር ቃል በቃል በመድገማቸው ” ኮራጅ” ተብለው ተተችተው ነበር።

በመጨረሻ የሚነሱት ጥያቄዎች ግን — ኢትዮጵያ ዳግም የባህር በር እንዲኖራት የሚሆነው እንዴት ነው። ከሶማሌ በመከራየት፣ ከኬናያ ወይም ከሱዳን በመወዳጀት?  ወይስ አሰብን መልሶ በመያዝ? ለሚለው ጥያቄ መልስ የለም።  ኢሳያስን ማስወገድ የሚል የቆየ ሃሳብ አለ። ኢሳያስ ከወደቁ በሁዋላ ምን ሊሆን? አዲሱ የኤርትራ መንግስት ከህወሃት ጋር ሆኖ ትልቅ ሊሆን? የኤርትራና የትግራይ ህዝብ ተዋዶና ተስማምቶ የቀጠናው ታላቅ ሃይል ሊሆኑ? ሰሞኑንን ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ አገር መሆን የለባትም በሚል የተነሳው ሃሳብ አዲስ ነው? ለምን ዛሬ? ለመሆኑ ኢሳያስን ማውረድ ዛሬ ቀላል ነው?

 

Related stories   የፌደራልና የክልል ፖሊስ አዲስ የአደረጃጀት ሰነድ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ቀረበ