“ኢህአዴግ ትክክለኛውን በሽታ ፈፅሞ አላወቀውም”

“ኢህአዴግ ትክክለኛውን በሽታ ፈፅሞ አላወቀውም”

 Written by  አለማየሁ አንበሴ

 

   · ኢህአዴግ ወደ እግሩ ተኩሶም ቢሆን ራሱንና ሀገርን ማዳን አለበት
                 · አሁን ያለው የፌደራል ሥርአት የማይታጠፍበት ደረጃ የደረሰ ይመስላል
                 · ኢትዮጵያ ውስጥ እየተጠየቀ ያለው መሰረታዊ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው
                 · በኛ አገር ሁኔታ ፖለቲካዊ ስርአቱ ህገ መንግሥቱን አይመስልም
                 · ሥራ አስፈፃሚው የመንግሥት አካል ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሮታል
                 · ሁሉንም እኔ ልቆጣጠር የሚል አንድ ፓርቲ ነው የተፈጠረው

አቶ ናሁሰናይ በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ፌደራሊዝም መምህር ሲሆኑ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካ ሳይንስና አለማቀፍ ግንኙነት፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፌደራል ስርአት ጥናት ያገኙ ሲሆን አሁን በፌደራሊዝም፣ በሰላምና በሰብአዊ መብት የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በማገባደድ ላይ ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖች ለወደፊት አገሪቱን ሊበታትናት ይችላል በሚል ስጋታቸውን የሚገልጹበት ቋንቋና ማንነትን መሰረት ያደረገው የፌደራል ስርአቱ የ26 ዓመታት ጉዞ ምን ይመስላል፣ብሄርተኝነትና ኢትዮጵያዊነት ምንና ምን ናቸው፣የቅርብ ጊዜው
ህዝባዊ ተቃውሞና ግጭቶች መንስኤያቸው ምንድን ነው በሚሉና ተያያዥ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ዙሪያ
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ አቶናሁሰናይ በላይን አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

አሁን አገራችን የምትከተለው ቋንቋና ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ብዙ ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ሌላ ሁሉንም የሚያስማማ አማራጭ የለም እንዴ?
በመጀመሪያ ፌደራላዊ ስርአት ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ብናይ፣ በሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ አንዱ የብሔር ጉዳይ ነው፤ ሌላው የመሬት ጥያቄ ነው፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በተለያየ መንገድ አዩት እንጂ ወሳኝ ተቃርኖዎቹ በብሔርና በመሬት ዙሪያ እንደሆኑ ነው የዘመናዊ የፖለቲካ ታሪካችን የሚያሳየን። ይሄ ደግሞ ዝም ብሎ የመጣ ነገር አይደለም፡፡ ከሀገሪቱ አመሰራረት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው፡፡ ልክ እንደ ሌሎች ሀገሮች የኢትዮጵያ የሀገር ግንባታም በጉልበት፣ በእልቂት፣ በፍጅት የመጣ ነው፡፡ ይሄም የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው፡፡ አሁን ያለውን ቅርፅ መያዝ የጀመረው ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ከምንለው ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ የማንነት፣ የቋንቋና የመደብ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጎ በተለይ በዋናነት በተደራጀ መልኩ በተማሪዎች ሲቀርብ ነበር፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የነበረው “መሬት ላራሹ” እና “የብሔር መብት ይከበር” የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት መሰረታዊ መነሻውም ይኸው ጥያቄ ነው፡፡ በወቅቱም ብዙ የብሔር ነፃ አውጪ ግንባሮች የነበሩበት መሆኑም ይታወሳል፡፡
የብዙኃኑ ህዝብ ፍላጎት ሳይሆን የጥቂት ብሔርተኞች አስተሳሰብ ገኖ በመውጣት ነው ሌላው ላይ የተጫነው —- የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ምንድነው የእርስዎ አስተያየት?
ብሔርተኝነት ብዙ ጊዜ በኛ ሀገር ሁኔታ በተመሳሳይ መንገድ ነው የሚተረጎመው፡፡ ብሔርተኝነት ዲሞክራሲዊ እስከሆነ ድረስ በራሱ ችግር የለውም፡፡ አንድ ብሔር ለራሱ መብት መታገሉ ችግር የለውም። ኢትዮጵያ ላይ ህዝቡ በግ ሆኖ፣ ልሂቃኑ ነድተውት ነው ዛሬ ላይ የደረሰው ማለት ህዝቡን መስደብ ይመስለኛል፡፡ የብሔር ጭቆናው መወገድ ስላለበት ነው ሂደቱ የመጣው፡፡ አንድ ብሔር ለመብቱ መታገሉ መጥፎ ነው የሚል አመለካከት የለኝም፡፡ መጥፎ የሚሆነው የኔ መብት የሚከበረው ሌሎችን ረግጬ ነው ሲባል ነው፡፡
በወቅቱ ለሰዎች ስሜት በእጅጉ ቅርብ የሆነውን የብሔር ጉዳይ ማታገያ ከማድረግ ይልቅ ሌላ አማራጭ አልነበረም?
አንድ ህዝብ የሚደራጀው ባለው ነገር ነው፤ኢትዮጵያ ላይ የመደብ አደረጃጀት ለማድረግ በወቅቱ ምን ሰራተኛ ነበር? ምን ፋብሪካ አለ? ሲጀመር በብሔር መደራጀት ሀጢያት አይደለም። ብሄር እንደ ፆታ አንድ ማንነት ነው፡፡ ሰው ባለው ነው የሚደራጀው፡፡ ተፈጥሮአዊም ነው፡፡ በመደብ ወይም በሰራተኛ መደራጀት የሚቻለው ሰፋፊ ኢንዱስትሪ ሲኖር ነው፡፡ አሁንም ድረስ ፈረንሳይን የሚያንቀጠቅጠው የመደብ ጥያቄ ነው፡፡ ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት ግን የሰፈር ጥያቄዎች ነበሯቸው፡፡ ስለዚህ ሰው ባለው ነገር ነው የሚራጀው፡፡ ማንነት ብዙ መልክ ነው ያለው። ኢትዮጵያዊነት ራሱን የቻለ ማንነት ነው፡፡ ብሄር፣ ፆታ፣ ሥራ ራሳቸውን የቻሉ አደረጃጀቶች ናቸው። በእነዚህ መደራጀት አደገኛ የሚሆነው ሌላውን ለመጨፍለቅ በማሰብ ሲሆን ነው፡፡
በአሁኑ የፌደራሊዝም ስርአት ላይ ከሚቀርቡ ትችቶች አንዱ ኢትዮጵያዊነትን አላልቷል የሚል ነው  …
የትኛው ኢትዮጵያዊነት? እነዚያ ህዝቦች እኮ ኢትዮጵያዊነት መረረን ብለው ነው የታገሉት። ኢትዮጵያዊነት ላልቷል ማለት ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያዊነት በድሎናል በሚል አይደል እንዴ ትግል የተጀመረው? ሀገር ሰውን መምሰል ሲያቅተው ነው ሰው ሀገር ላይ የሚያምፀው፡፡  እዚህ ሀገር የብሔርም የመደብም ጭቆና ነበረ፡፡ ይሄ የነበረ ሃቅ ነው፡፡ ትግሉ የነበረው ኢትዮጵያ የሁላችንም ትምሰል የሚል ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰብ መብት ይከበር የሚለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ደግሞ የግራ ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ የነበረ ነው። ስለዚህ በሚያዋጣቸው መንገድ ተደራጅተዋል፡፡ የህውሓት ማሸነፍ ሌላ ሚስጥር የለውም፤የተከተለው መስመር ነው አሸናፊ ያደረገው እንጂ ደርግ የማይተኩስ ወይም ህውሓት ጎበዝ ተኳሽ ሆኖ አይደለም፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአክራሪ ብሔርተኝነት ውጤት ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ። አክራሪ ብሔርተኝነት ደግሞ የፌደራሊዝም ሥርዓቱ ያመጣው ነው ማለት አይቻልም?
በመጀመሪያ ጦርነቱን አስቁሟል፡፡ ሰላም አንፃራዊ ነው፡፡ አንፃራዊ መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ ዜጎች በቋንቋቸው መጠቀም፣ በማንነታቸው መስራት ችለዋል፡፡ የመተዋወቅ እድልም ፈጥሮልናል፡፡ መሰረታዊ ቅራኔዎችን የፈታ ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው ግጭቶች ይኖራሉ፤ ግን ያን ያህል አይደለም፤ ይሄ አይነቱ እንኳን በጀማሪዎቹ በሌሎቹም ዘንድ አለ፡፡ ስዊዘርላንድ በዘመናት ግጭት ነው ዛሬ ያላት ፌደራሊዝም ላይ የደረሰችው፡፡ በናይጄሪያ እዚህ እንደሚታየው “አካባቢዬን ለቀህ ውጣልኝ”፣ “የኔ ንብረት ነው” —- በሚል ብዙ ተጋጭተዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ እኛም መደንገጥ የለብንም፡፡ የሂደቱ አካል መሆኑን ማመን አለብን፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ የፖለቲካ ነጋዴዎች እንደሚኖሩም መዘንጋት አይገባም፡፡ ስርቆታቸውን ለመደበቅ ሲሉ ግጭት የሚፈጥሩ አሉ፡፡ እነዚህም ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡
ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ብሔርተኝነት እየቀደመ መምጣቱ ለአገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ አስጊ አይሆንም?
በአንድነት ውስጥ ልዩነት፤ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ማየት የተሳነው ሰው በዝቷል፡፡ ልዩነት ብቻውን ትርጉም አይኖረውም፤ አንድነትን ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ አንድነትም ብቻውን ትርጉም የለውም፤ ልዩነትን ማክበር አለበት፤ ስለዚህ ያለው የብሔርተኝነት አይነት ይወስነዋል፡፡ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ የሆነ ብሔርተኝነት ፌደራሊዝሙ በዚህ መንገድ ተዋቀረም አልተዋቀረ አደገኛ መሆኑ አይቀርም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ችግር የለውም፡፡ ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊነት፣ አማራነት ኢትዮጵያዊነት፣ ትግሬነት ኢትዮጵያዊነት ነው፤ይሄ ነው ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ማለት፡፡ አማራነት ተሰበከ ማለት ኢትዮጵያዊነት አልተሰበከም ማለት አይደለም፡፡ ችግሩ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ የሆነ አማራነት ወይም ኦሮሞነት አሊያም ትግራዋይነት ሲሰበክ ነው፡፡ ያ አደገኛ ነው፡፡ አሁን የምናስተውለው አንድነት ብቻ የሚለው ኃይል፤ ብዝኃነትን የጨፈለቀ አስተሳሰብ ነው፡፡ ጫፍ የረገጠው ብዝኃነት ባዩ፣ አንድነትን ታሳቢ አያደርግም፡፡ ስለዚህ ሁለቱንም ታሳቢ አድርጎ የሚሄድ ሀገር ነው መስራት ያለብን፡፡ አንዱ አንዱን ረግጦ የሚሄድበት እድል ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በኋላ የፌደራል ስርአቱ አንድ ኢንች ወደ ኋላ ይመለስ ቢባል፣ ከብጥብጥና ጦርነት ውጪ ምንም ምርጫ የለውም። ይሄን በግልፅ እያየነው ነው፡፡ ገና ለገና የአንድን ክልል ይነካል በሚል ነው የታሰቡ ህጎች ጭምር ግጭትና ቅሬታ እየፈጠሩ ያሉት፡፡ ስለዚህ የትኛውም አካል ይሄን ካልተቀበለ ለሀገሪቱ አደገኛ ነው፡፡ አሁን ያለው የፌደራል ስርአት የማይታጠፍበት ደረጃ የደረሰ ይመስላል፡፡ በአንድነት ስም መጨፍለቅ የሚታሰብ አይመስልም፡፡ ይሄን አለማክበር ነው ከዚህ በኋላ አደገኛ የሚሆነው፡፡
በዚያው ልክ አደገኛ ብሔርተኝነትም እየተንፀባረቀ ነው፡፡ በተለይ ከአንዳንድ የዳያስፖራው ወገን  የሚነሳው ብሔርተኝነት አደገኛ ነው። እኔ የማልገዛት ኢትዮጵያ ትበተን የሚለው ኃይል አደገኛ ነው፡፡ የህዝቦች መቀራረብና ዲሞክራሲያዊ አንድነት ለእነዚህ ኃይሎች ስጋት ነው፡፡
ይሄን አደገኛ ብሔርተኝነት ያመጣው ምንድን ነው? ስጋቱስ ምን ያህል ነው?
ስጋቱ ያን ያህል ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ይሄን አይቀበልም፤ የአማራ ህዝብም እንዲህ አይነቱን አይቀበልም፡፡ ቆሻሻ ሲከመር ባለቤት የሌለው ውሻ የመጣል፡፡ ይሄም እንደዚያው ነው፡፡ ቆሻሻው ሲፀዳ ውሻውም አይኖርም፡፡ ይሄን አደገኛ ብሔርተኝነት ያመጣው በስርአቱ ላይ የተፈጠረው የፖለቲካ ቆሻሻ ነው፡፡ ያ ቆሻሻ ሲፀዳ ሁሉም ይስተካከላል። ተወደደም ተጠላ አንድ ሀገር ነው ያለን፡፡ እጣ ፈንታችን በአንድነት መኖር ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ቆሻሻውን ማስወገድ ወደ መፍትሄው የሚወስደን መንገድ ነው፡፡ መንግስት ችግሬ የመልካም አስተዳደር ነው ይላል፡፡ ግን ይሄ ብቻ አይደለም ቆሻሻው፡፡ ይሄ አንዱ መገለጫ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየተጠየቀ ያለው መሰረታዊ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው።
አንዲት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አሉ፡፡ የሚሳካላቸው ይመስልዎታል?
ከንቱ ልፋት ነው፡፡ ፖለቲካ ማረፊያ ያስፈልገዋል። ሀሳቡን የሚፈልግ ህዝብ ያስፈልገዋል። ይሄ አስተሳሰብ አሁን የት ሊያርፍ ነው። ሶማሌው አንድ ቋንቋ፣ አንዲት ኢትዮጵያ የሚለውን ይቀበለዋል? ኦሮሞው፣ ትግራዋዩ ይቀበለዋል? በነቃ ማህበረሰብ ላይ እኔን ምሰል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ቅኝታቸውን ካላስተካከሉ ከንቱ ልፋት ነው የሚለፉት፡፡ ፖለቲካችን አዲስ አበባ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ክልል ላይ ሄዶ የህዝቡን ስነ ልቦና ማጥናት ይገባል፡፡
ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰው ተቃውሞና ግጭት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞትና እስራት ምክንያት ሆኗል…. ለዚህ ፖለቲካዊ ቀውስ የምንከተለው የፌደራል ስርአት አስተዋፅኦ አድርጓል ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አተያይ ምንድን ነው?
ዋናው የተቃውሞና ግጭቱ መነሻ በሃገሪቱ ያለው የፖለቲካ ችግር ነው፡፡ ፖለቲካው ህገ መንግስቱን ማስተናገድ ስላልቻለ ነው ችግሩ የተፈጠረው። ፖለቲካው ሌላ፣ ህገ መንግስቱ ሌላ ሆኖ ነው ያ ሁሉ ሁኔታ ያጋጠመው፡፡ መሠረታዊ ችግሩ ላይ ደግሞ ገዥው ፓርቲ የሚያነሳው መከራከሪያ ለኔ አስቂኝም ነው፡፡ ችግሩ የጥቂት ሰዎች ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል ወይም የመልካም አስተዳደር ችግር ነው በሚል ነው የወሰደው፡፡ ይሄን ሲል ደግሞ ለምን የስልጣን ብልግናው ተፈጠረ የሚለውን ወደ ኋላ ተመልሶ አይጠይቅም፡፡ ዝም ብሎ ግለሰብን በግለሰብ መቀየርን ነው የተያያዘው፤ ይሄ በጭራሽ መፍትሄ አይሆንም፡፡
የአሜሪካ መስራች አባት ማዲሰን ስለ “Check and Balance” ሲናገር፤ ሶስቱ የመንግስት አካላት እርስ በእርስ መቆጣጠር አለባቸው ይላል፡፡ አሁን ደግሞ ሚዲያውም 4ኛው የመንግስት አካል ሆኗል። ይህ ሰው ምን ይላል? ሰዎች የመላዕክት ስብስብ ቢሆኑ መንግስት ባላስፈለጋቸው፣ መንግስትም የመላዕክት ስብስብ ቢሆን ቁጥጥር ባላስፈለገው ነበር ይላል፡፡ ከዚህ መረዳት የምንችለው፣ ስልጣን ሃይ ባይ ካጣ ያባልጋል የሚለውን ነው፤ተቆጣጣሪ ከሌለ ስልጣን ያባልጋል። አሁን በኛ ሃገር ሁኔታ ፖለቲካዊ ስርአቱ ህገ መንግስቱን አይመስልም። ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መንቀሳቀስ ያለበት ፍ/ቤት፣ በተግባር እንደዚያ አይደለም፡፡ ስራ አስፈፃሚው የሚባለው የመንግስት አካል ከሁሉም በላይ ሆኖ ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሮታል፡፡ ነገሮች ተገላብጠዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ህዝብ መንግስትን የሚቆጣጠርባቸው መዋቅሮች ተዳክመው ሥራ አስፈፃሚው ጡንቸኛ ሆኗል፡፡ ፓርላማ፣ ማህበራት፣ ተቃዋሚ ፓርቲ የመሣሠሉት ተዳክመዋል፡፡ ህዝብ፤ መንግስትን የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎቹ እነዚህ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ከቀበሌ እስከ ማህበራት ሁሉንም ነገር እኔ ልቆጣጠር የሚል አንድ ፓርቲ ነው የተፈጠረው። ፓርቲው ልቆጣጠር ብሎ ሲንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መዋቅሮቹ ሽባ ሆነዋል፡፡ የዚህ ሁሉ መዝረክረክ ወይም በድሃ ህይወት መቀለድ ዋና መንስኤው ተቆጣጣሪ አካል አለመኖሩ ነው፡፡ ራሱን በራሱ መቆጣጠር የማይችል፣ ከውጪም ተቆጣጣሪ የሌለው የመንግስት አካል መኖሩ ነው፣ መሠረታዊ የሃገሪቱ ችግር መንስኤ፡፡
ለምን ሥራ አስፈፃሚው ከፓርላማው በላይ ሆነ? ወይም ተቆጣጣሪ አልባ ሆነ?
ሃገሪቱን የሚመራው ግንባር የተማከለ የውሳኔ አሰጣጥ የሚል መርህ አለው፡፡ የመወያየት ነፃነት ቢኖርም በውሳኔ አንድ መሆን የሚለውን የሌኒን መርህን ነው የሚከተለው፡፡ ይሄ ወዴት ያመራል? ህዝብን የሚወክሉ ሰዎች ተሰብስበው ወደ ፓርላማው ሲገቡ በዲሞክራሲ ማዕከላዊነት በሚለው የገዥው ፓርቲ አስተሳሰብ ተጠርንፈው ይመስለኛል፡፡ ታማኝነታቸው ለገዥው ፓርቲ ነው ማለት ነው፡፡ እስካሁን የተመለሰ ረቂቅ አዋጅ መኖሩን አላውቅም፡፡ ይሄ ምን ያህል የዲሞክራሲ ማዕከላዊነት የሚለው አስተሳሰብ ሰዎቹን እንደተጫናቸው ያሣያል፡፡ ምናልባት በረሃ በነበሩበት ጊዜ ይሄ አሠራር አዋጪ የነበረ ይመስለኛል፡፡ ለድል እንዲበቁ ያደረጋቸውም ይመስለኛል፡፡ ግን መንግስት ሲሆኑና ያልተማከለ አስተዳደር ሲገነቡ፣ተቆጣጣሪ አካል እንዲኖር የሚፈቅድ ህገ መንግስት ሲዘረጉ፣ፓርቲው አሠራሩን ለዚህ በሚመጥን መልኩ ፈትሿል ወይ? የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ ያለመፈተሹ ምክንያትም ነው ተጠቃሎ እየመጣ አሁን ላለንበት ሁኔታ ያበቃን፡፡ ነገሮች ሲለወጡ ግንባሩ አመለካከቱንና አደረጃጀቱን እየለወጠ አልመጣም፡፡ ስለዚህ የስራ አስፈፃሚው የበላይነት የመነጨው ከዚህ መርህ ነው፡፡ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እጃቸው ላይ ብዙ ነገር የነበረ ይመስለኛል፡፡ ያ የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡
ለምሳሌ ምን…?
የተፅዕኖ መጠናቸው ሠፊ ነበር፡፡ ያ የራሱን አሻራ አሳርፎ ይሄዳል፡፡ የተለያየ አካል ሆኖ መንቀሳቀስ የነበረበት የመንግስት ሃይል ልክ ጸረ ደርግ በነበረው ትግል ጊዜ እንደነበረው አይነት አካሄድ ነው የነበረው። መንግስት ከተሆነ በኋላ ለመንግስት በሚመጥን አሠራር ላይ መሆን አልቻለም ነበር ድርጅቱ፡፡ ፓርላማውም፣ ፍ/ቤቱም የሚገባውን ቦታ አላገኘም፡፡ ዝም ብለን ስናይ እንኳ ክቡር የሚሰጠው ለፓርላማ አባል ሣይሆን ለስራ አስፈፃሚው አባላት ነው፡፡ ይሄ መሆን የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ የመጨረሻው የስልጣን ሉአላዊ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ካልን፣ ሌላ አካል አይደለም፤ፓርላማው ነው ማለታችን ነው፡፡ ምክር ቤቱ የመጨረሻው የስልጣን ባለቤት ነው፡፡ ፍትህ የሌለው ሀገር አያግድም፤ ስለዚህ የፍትህ ተቋማት መጠናት አለባቸው፡፡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋምም ጉዳዩን አምባገነንነት ነው ብሏል፡፡ እኔም የምለው ይሄንኑ ነው፡፡ ፀረ-ዲሞክራሲያዊነት ጎልብቷል፤ በዚህ ደግሞ ህዝቦች ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡
ታዲያ ለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው?
የማይስተካከል ችግር የለም፡፡ የሰው ልጅ የፈጠረውን ችግር የሚፈታው ራሱ የሰው ልጅ ነው፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ሀገር ብዙ እድል አለን። ለዘመናት ዲሞክራሲ ፈልጎ ሲታገል የኖረ ህዝብ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቅንጦት አይደለም፡፡ እዚህ ሀገር ለዲሞክራሲ ያልተደረገ ትግል የለም፡፡ በሌላ በኩል በርካታ የተማረ ኢትዮጵያዊ ወጣት እየተፈጠረ ነው። ይሄ ትውልድ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አመለካከትን የሚሸከምበት እድል የለውም፡፡ ህዝቡም ለነፃነቱ ቀናኢ ነው፡፡ ነገሮችን ለማስተካከል የሚያስችል ጠንካራ ህገ መንግሥት አለን፡፡ በህገ መንግሥቱ መርህ ማስተካከል ይችላል። ስልጣን ላይ ያለው አካል የኃላፊነቱን መጠን በደንብ መገንዘብ አለበት። የህዝብ ግፊትም ይሄ እንዲሆን ነው፡፡ የህዝቡ እውነተኛ ምክንያት ምንድን ነው የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ አሁን በመንግስትም ሆነ በሌሎች እየተነገረ ያለው ከመሃል የተቆረጠ ምክንያት ነው፡፡ ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል የሚለው ቁንፅል ነው፡፡
በድፍረት የችግሩን ምንጭ ለማወቅ መጣር ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ መተኮስ ካለበት፣ ወደ እግሩም ቢሆን ተኩሶ ራሱንና ሀገሩን ማዳን አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ ለራሱም ለሀገርም ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢህአዴግ ትክክለኛውን በሽታ ፈፅሞ አላወቀውም፡፡ እየሄደበት ያለው አቅጣጫም የእሳት ማጥፋት እንጂ ሌላ ስር ነቀል መፍትሄ የሚያመጣ አይደለም፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር መሆን የሚያኮራ ሳይሆን አሳፋሪ ነው፡፡ ይሄ መለወጥ አለበት፡፡ አለበለዚያ ቀጣዩ ሁኔታ አደገኛ ነው፡፡
ዋነኛ የአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ምንድን ናቸው ይላሉ ?
ሀገር ውስጥ ያለው የተለየ ሀሳብ የሚያንፀባርቀው አካል ታፍኖ፣ ተቀጥቅጦ፣ አሁን ላይ ሞቷል ማለት ይቻላል፡፡ መንግሰት ከሚያቀነቅነው አስተሳሰብ የተለየ አስተሳሰብ ያለው አካል የሚተነፍስበት መድረክ የለም፡፡ ሚዲያ የለውም፡፡ ሲንቀሳቀስ ይዋከባል፡፡ የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኝ ተፅዕኖ ተደርጎበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ፖለቲካው ተሰዶ ወደ ዲያስፖራው ሄደ፡፡ የረጅም ርቀት ብሔርተኝነት ፖለቲካ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይሄ ደግሞ አደገኛ ነው በባህሪው፡፡ ከውጭ የሚመጣ አካል ኃላፊነት አይወስድም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ መንግስት ሆን ብሎ አቅዶ መስራት አለበት፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ችግሮች ላለመፈጠራቸው እርግጠኛ መሆን ይቻላል?
እኔ በአጠቃላይ ተሃድሶ በሚለው ላይ ጥያቄ አለኝ፡፡ “ተሃድሶ ነው ወይስ ተደባብሶ?” ይሄን ለይተን ማወቅ አለብን፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ለምሳሌ በኦሮሚያ አካባቢ ያለው እንቅስቃሴ የሚያበረታታ ነው፤ በርቱ መባል አለባቸው፡፡ ኦሮሚያ ላይ ከምናየው ተስፋ ውጪ ይሄ ነው የሚባል ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የችግሩን ምክንያት የተነተኑበት አመክንዮ የላቸውም፡፡ የተሳሳተ ትንተና ላይ መሰረት ተደርጎ ትክክለኛ መፍትሄ ሊመጣ አይችልም፡፡
ኦሮሚያ ላይ ተስፋ አለ፤ ለራሳቸው ልዕልና ዘብ እየቆሙ ይመስለኛል፡፡ ሌሎች ክልሎች ላይ ተስፋ የማጣት ነገር ይታያል፡፡ “ቤተ አማራ”፣ “አግአዚያን” የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎችም የዚህ ተስፋ ማጣት ውጤቶች ናቸው፡፡ የበሽታውን ምንጭ አግኝቶ ትክክለኛ ህክምና እስካልተደረገ ድረስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብዙ ርቀት ይኬዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡

addisadmass

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “በአጣዬ እና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ለፍርድ ይቀርባሉ” ኮማንድ ፖስቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *