Skip to content

የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት ስድስት ዓመት ተፈረደባቸው

 

በቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የክስ መዝገብ ቁጥር 141352 ውስጥ ተካተው ክስ የተመሠረተባቸው፣ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት የስድስት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው፡፡ እንዲሁም ድርጅታቸው ጄኤች ሲሜክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላይ የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ተሰጠ፡፡

ከግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ በሚገኙት የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደና በድርጅታቸው ላይ የእስርና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ የሰጠው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ላለፉት አራት ዓመታት ሲመረምር በከረመው የክስ መዝገብ ላይ የቅጣት ውሳኔውን የሰጠው ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲሆን፣ አቶ ስማቸው ግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጥፋተኛ በተባሉባቸው ሁለት ክሶች በስድስት ዓመት እስራት እንዲቀጡ፣ ድርጅታቸውም በተመሳሳይ ጥፋተኛ በተባለባቸው ሁለት ክሶች በ100,000 ብር እንዲቀጣ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

በ2005 ዓ.ም. የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን በመገናኛ ብዙኋን ጭምር በመግለጽ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊዎች የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ፣ አቶ በላቸው በየነ፣ አቶ ማርክነህ ዓለማየሁ፣ እንዲሁም ከታዋቂ ነጋዴዎች አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ከተማ ከበደ (ኬኬ)፣ አቶ ገብረ ሥላሴ ኃይለ ማርያም በድምሩ ከ24 ተከሳሾች ጋር በሙስና ተጠርጥረው ታስረው የነበሩት አቶ ስማቸው፣ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን የሰነድና የሰው ማስረጃዎች አቅርቦና አሰምቶ ሲጨርስ በሰጠው ብይን ከሙስና ወንጀል ነፃ መሆናቸውን ማሳወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ፍርድ ቤቱ አቶ ስማቸው ከሙስና ወንጀሎች ነፃ መሆናቸውን በብይኑ የገለጸ ቢሆንም፣ እሳቸው ሥራ አስኪያጅ የሆኑበት ድርጅታቸው ጄኤች ሲሜክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ለመንግሥት አሳውቆ መክፈል የነበረበትን ተጨማሪ እሴት ታክስና የገቢ ግብር ታክስ አለመክፈሉን፣ ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች እንዳስረዳበት በመግለጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡ አቶ ስማቸው በወቅቱ ተከላከሉ የተባሉበት የወንጀል ድርጊት አዲስ ተሻሽሎ በወጣው የገቢ ግብር አዋጅ፣ ወንጀል መሆኑ ቀርቶ በአስተዳደር በኩል የሚታይ መሆኑን በመጠቆምና ያም ባይሆን፣ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ዋስትና እንደማይከለክላቸው ገልጸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

አቶ ስማቸው ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በመግለጽ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ የታክስ ጉዳዮች የተከሰሰ አካል የተከሰሰበት የሕግ አንቀጽ ዋስትና የማያስተካክለው ቢሆንም ዋስትና ሊሰጠው እንደማይገባ ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ መስጠቱን በመግለጽ፣ በሐሳብ ልዩነት አቤቱታቸው ውድቅ በመደረጉ የሥር ፍርድ ቤት ክርክሩን አስቀጥሏል፡፡

ክሳቸው ከእነ አቶ መላኩ ተለይቶ የመከላከያ ምስክሮቻቸውንና የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን ያሰሙት አቶ ስማቸው፣ ተከላከሉ ከተባሉባቸው አሥር ክሶች ስድስቱን በብቃት መከላከል መቻላቸውን ፍርድ ቤቱ በፍርድ መዝገቡ ላይ አስፍሯል፡፡ ጥፋተኛ የተባሉባቸው አራት ክሶች ቢሆኑም ሁለቱ እንደ አንድ ተጠቃለው በሁለት ክሶች ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ ድርጅቱ ለመንግሥት አሳውቆ መክፈል የነበረበትን 20,111,328 ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ አሳውቆ ባለመክፈሉ ጥፋተኛ ሲባል፣ አቶ ስማቸው ደግሞ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ዝም በማለታቸው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

ሌላው ድርጅቱ ከንግድ እንቅስቃሴዎች ካገኘው ገቢ ላይ ለመንግሥት አሳውቆ መክፈል የነበረበትን 29,433,211 ብር እና ከግዢ ዕቃ አቅርቦት ውል ከሚፈጸም ክፍያ 632,860 ብር ባለመክፈሉ ጥፋተኛ ሲባል፣ አቶ ስማቸውም ሥራ አስኪያጅ ሆነው ዝም በማለታቸው ጥፋተኛ መባላቸውን ፍርዱ ይገልጻል፡፡

ሁለቱ የጥፋተኝነት ውሳኔዎች ወደ አንድ ተጠቃለው፣ በአጠቃላይ በሁለት ክሶች ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ በመሆኑም ጄኤች ሲሜክስ በ100,000 ብር እንዲቀጣና አቶ ስማቸው በስድስት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡ አቶ ስማቸው ከአራት ዓመታት በላይ በእስር ላይ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

Reporter Amharic     ታምሩ ጽጌ’s blog  የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት የስድስት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

0Shares
0
Read previous post:
በዓመት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አላቸው የተባሉ አምስት ኢትዮጵያውያን ይፋ ሆኑ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዋቂ ግለሰቦችንና የኩባንያ መሪዎችን የሀብት መጠንና ክንዋኔያቸውን በአኃዛዊ መረጃዎች አስደግፎ በመዝገብ የሚታወቀው ፎርብስ የተባለው መጽሔት፣ ዓመታዊ ገቢያቸው...

Close