“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ለመንግስት ስራ ብዙ አትልፋ – ከወንበርህ ግን አትጥፋ”

ገብረህይወት ካህሳይ (ኢዜአ)

የኢፌዴሪ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ወስጥ የሚገኙ ሰራተኞችና አመራሮች በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት ባሉባቸው ችግሮች ላይ አገራዊ ጥናት አካሔዶ ግኝቶቹን ይፋ አድርጓል ።

በጥናቱ ግኝት ክፍል ሁለት ላይ “ ለመንግስት ስራ ብዙ አትልፋ ከወንበርህ ግን አትጥፋ “ የሚል አባባል አገኘሁኝና ትኩረቴን ሳበው ። ወዲያውኑ ትውስ ያለኝ አንድ ወዳጄ ያጫወተኝ እውነተኛ ገጠመኝ ነበር ።

ግደይ አሰፋ ይባላል ። ነዋሪነቱ በአዳማ ከተማ ቀበሌ 05 ውስጥ ነው ። የመኖሪያ ቤት ሰራና የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እንዲገባለት ያመለክታል ። በነገ ዛሬ ቆጣሪው ሳይገባ አንድ ዓመት አለፈው ።

“ አማራጭ ሳጣ ቆጣሪ ከግለሰብ በ10 ሺህ ብር ገዛሁ” አለኝ ። እንዴት ቆጣሪ በግለሰብ ይሸጣል እንዴ? ስል ጠየቅኩት ። “አዎን ! ቤት ሳይኖራቸውና ቋሚ አድራሻ ሳያስመዘግቡ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት አንዳንድ ሰራተኞች ጋር ተመሳጥረው ቆጣሪ ለመውሰድ ይመዘገቡና ወረፋ ደረሳችሁ እየተባለ ይሰጣቸዋል ። ቆጣሪውን አውጥተውም በውድ ዋጋ ይሸጡታል “ አለኝ ።

“አስገራሚው ነገር ግን ከግለሰብ የተገዛውን ቆጣሪ ድርሻቸውን የበሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች ወዲያውኑ ህጋዊ በማድረግ ከመስመር ጋር ማያያዛቸው ነው” በማለት ነበር በቅሬታ መንፈስ ያጫወተኝ ። እነዚህ ሰዎች የህዝብ አገልጋዮች ወይስ ተገልጋዮች ?

ከአገልጋይነት ይልቅ የተገልጋይነት መንፈስ ያዳበረ ሲቪል ሰርቪስ ከተንሰራፋ  በየትኛውንም መልኩ የተሟላ ልማትና አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ አስቸጋሪ መሆኑን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች ያመላክታሉ ።

በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምክንያት የሚያለቅስ ተገልጋይ ካለ አስለቃሽ አካል መኖሩ የማይታበል ሀቅ ነው ። ከህዝብ ከተሰበሰበው ግብር ደመወዝ እየበላ ህዝብን መልሶ የሚያስለቅሰው ወገን በህግ አግባብ የሚቀጣበት “ የተጠያቂነት “ አሰራር መፍጠር ደግሞ ይዋል ይደር የማይባል አጀንዳ መሆን አለበት ።

አደጉ በሚባሉ አገሮች የሲቪል ሰርቪስ ስርዓት 72 በመቶ የሚሆነውን የሰራተኛ ቅጥር ውድድርን (Competition) መሰረት አድርጎ የሚፈፀም ነው ።የተወሰኑ የአመራር ቦታዎች ግን ከውድድር ነፃ በሆነ መልኩ በፖለቲካ ሹመት የሚያዙ ናቸው ።

ሲቪል ሰርቪሱ ከግል ዘርፉ በአንፃራዊ መልኩ የተሻለ ክፍያ የሚያገኝ ሲሆን ከ1 እስከ 15 ባለው ደረጃ እየተመዘነ ያልፋል ። ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ የሚያገኝበት ፍትሃዊ አሰራርም ተዘርግቷል ። በዚህ ሂደት አልፈው ውጤታማ ሲቪል ሰርቪስ ከገነቡ አገራት መካከል ሩሲያና ሀንጋሪ መጥቀስ ይቻላል ።

በልማታዊ መንግስት የሚመሩና (Asian tigers) ተብለው የሚጠሩ ሲንጋፖር ፣ደቡብ ኮሪያ ፣ ታይዋን ፣ ሆንግኮንግ፣ ቻይና የመሳሰሉት አገራት ባለፉት 60 ዓመታት ቀልጣፋና ውጤታማ የህዝብ አስተዳደር ፣ አስገራሚ ኢኮኖሚያዊ እድገትና የተረጋጋ ሰላም መፍጠር የቻሉት  ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት  ነው ። የእነዚህ አገራት እድገትና ብልፅግና የአንድ ትውልድ ጉዞ ነው ብሎ መውሰድም ይቻላል ።

በተለይ ሲንጋፖር በሲቪል ሰርቪሱ  ቀዳሚ አገር ስትሆን በእድገት ከዓለም 5ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አስችሎአታል ። ታይዋን 11ኛ ፣ሆንግኮንግ 13ኛ ፣ ደቡብ ኮሪያ 24ኛና ቻይና ደግሞ ከመሪዎች ጎራ እንድትቀላቀል አድርጎአታል ።

በአህጉራችን አፍሪካም ቢሆንም የተሳካ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በማካሔድ አመርቂ ውጤት ካመጡ አገራት መካከል ታንዛኒያ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች ። ዛምቢያም በፕሬዚዳንቷ ቁርጠኛ አመራር በመስኩ ጥሩ ውጤት ያመጣች ሲሆን በጎረቤታችን ኬኒያ ግን ለውጡ አልተሳካም ።

የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚደረግ ለውጥ (Reform) ስድስት ምሰሶዎች (Pillars) ሊኖሩት ይገባል ።

የዓለም አገራት በ2008 በኒዮርክ  የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ለውጥን አስመልክተው ባካሄዱት ስብሰባ ላይ በርካታ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ሁሉንም አገሮች የተስማሙባቸው ግን ስድስቱ የለውጥ ምሰሶዎች ናቸው ።

ቀዳሚው የለውጥ ምሰሶ የአመራር ቁርጠኝነት ነው ። አመራሩ ለውጡን በቁርጠኝነት ከመራው እንደ ታንዛኒያና ዛምቢያ ይሳካል ። አመራሩ ከተልፈሰፈሰ ግን እንደ ኬኒያ ተሰናክሎ ይቀራል ።

ሁለተኛው የለውጥ ምሰሶ አድሎአዊ አሰራር ማስወገድ ነው ። በአገልጋዩም ሆነ በተገልጋዩ የሚደርስ አድሎአዊ አሰራር ካለ በለውጡ ላይ  እምነት አይኖርም ። እምነት ያልተጣለበት ለውጥ ደግሞ ከውስጡ  ተቀብሎ የሚፈፅመው ሃይል አይኖርም ።

ሶስተኛው የለውጥ ምሰሶ የመዋቅር መስፋት ነው ። አገሪቷ የደረሰችበት የእድገት ደረጃ ታሳቢ ያደረገና በጥናት ላይ የተመሰረተ የመዋቅር መስፋት ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ።ነገር ግን ያለበቂ ጥናት ወደ ጎንና ወደ ታች የሚለጠጥ መዋቅር ለውጡን ከመደገፍ ይልቅ አደናቃፊ ይሆናል ።

አራተኛው ምሰሶ የሲቪክ ማህበራት መጠናከር ነው ። ለውጡን የሚተገብረው አካል ሃላፊነቱን በአግባቡ እያከናወነ መሆኑን የሚከታተል ፣ ጥንካሬውን የሚያበረታታና ድክመቱን የሚተች ሃይል (Push factor) ያስፈልገዋል ። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ሁነኛ መሳሪያ ነው ።

Related stories   ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያራመዱት ያለው አቋም የዴሞክራሲ መርህን የጣሰ ነው

አምስተኛው ምሰሶ በጀት ሲሆን በእርዳታ በጀት የተጀመረ የለውጥ ስራ እርዳታው የቆመ ጊዜ አብሮ ቀጥ ይላል ። ስለሆነም ለውጡ በራስ በጀት እንዲከናወን ይመከራል ።

የመጨረሻው ምሰሶ ጊዜ ነው ። ሪፎርም በቂ ጊዜ ተቀምጦለት በቅርብ ክትትልና በጠንካራ ግምገማ ካልተመራ  ጥሩ ውጤት መጠበቅ ያልዘሩትን የማጨድ ያክል ነው ።

የኬኒያ የለውጥ ጉዞ የተደናቀፈውም እነዚህ የለውጥ ምሰሶዎች በአግባቡ ተግባራዊ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ነው ።

ከላይ የተጠቀሱትን መልካም ተሞክሮዎች ፣ መሰረታዊ ሃሳቦችንና መንደርደሪያዎችን መነሻ በማድረግ የአገራችን ሲቪል ሰርቪስ ያለበት ደረጃና በመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞችና አመራሮች የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ የፈተሸ አገራዊ ጥናት ተካሄዷል ።

የጥናቱ ባለቤት የኢፌዴሪ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ነው ።በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምክንያት እየፈሰሰ ያለውን የህዝብ እንባ ለማበስ የተካሄደ ጥናት ነውና 15 ግኝቶችን ይዞ ብቅ ብሏል ።

በተቋሙ የቁጥጥርና ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አዱኛ ሙሉነህ እንዳሉት ጥናቱ ችግሮቹን ፣ መንስኤዎቻቸውና መፍትሔዎቻቸው ያካተተ ባለ 110 ገፅ ሰነድ ነው ።

በፌዴራል ፣ በአዲስ አበባ ፣ በኦሮሚያ ፣ በደቡብ ፣ በአማራ ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በአፋር የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞችና አመራሮች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር አያይዞ የፈተሸበት ጥናት ነው ።

ጥናቱ 3ሺህ 441 የፅሁፍ መጠይቆችን ፣ 198 የቡድን ውይይቶችን ፣ 434 ቃለ መጠይቆችንና 73 ምልከታዎችን በማካሄድ በርካታ መረጃዎችን የሰበሰበ ነው ።

የጥናቱ ግኝቶችን የያዘው ሰነድ “ ለመንግስት ስራ ብዙ አትልፋ – ከወንበርህ አትጥፋ “ የሚለውን የተሳሳተ አባባል ስር የሰደደ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል ።

አጠቃላይ የጥናቱ ግኝቶች ከመመልከታችን በፊት ግን በጥናቱ የቀረበው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ብልሹ አሰራር እንመልከት ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች የትምህርት ደረጃ 18 በመቶውን ብቻ የመጀመሪያ ድግሪና ከዚያ በላይ ሲሆኑ የተቀሩት ግን ዲፕሎማና ከዚያ በታች ናቸው ። የበርካቶቹ ኑሮ ግን ከማንም የመንግስት ሰራተኛ በላይ ነው ።

በየጊዜው የሚፈጠረው የሃይል መቆራረጥ እድገቱን ያመጣውና የሃይል አቅርቦት ማነስ ብቻ አይደለም ። እንዲያውም ዋነኛው ሰው ሰራሽ ችግር ነው ይለናል የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጥናት ።

የኢፌዴሪ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የቁጥጥርና ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አዱኛ ሙሉነህ የጥናቱን ግኝት ይፋ ሲያደርጉ እንደገለፁት “ አብዛኛው የመስመር ሰራተኛ አኗኗር ከሚከፈለው ደመወዝ በላይ ነው ።”

“ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ሃይል እየጠለፉ ቆጣሪ ላይ ሳይገባ ለእንጀራ ጋጋሪዎችና ለሌሎች ተጠቃሚዎች በጎን ይሰጣሉ ።”

“  በሶስት ቤቶች መሀከል ሲፈልጉ የመሀከለኛውን ነጥለው መብራት ያቋርጣሉ ። ካልተከፈላቸው መስመሩን አይቀጥሉትም “ ይላሉ ።

“በውሃና ፍሳሽ ዘርፍም በተለይ ከቦቴ የፍሳሽ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ አገልግሎቱን ለማግኘት ለመንግስት ተገቢውን ክፍያ ፈፅሞና ህጋዊ ደረሰኝ ቆርጦ ይጠባበቃል ። ሲመጡ ግን ግማሽ ቦቴ ብቻ አንስተው በመሄድ ግማሹን ቦቴ መንገድ ላይ ለግል ጥቅም የሌላ ሰው ፍሳሽ ሞልተው ይሄዳሉ።”

ስርቆቱ ፣ ሙሱናውና ብልሹ አሰራሩ የሰፋ በመሆኑ ኑሮአቸው ከሌላው የመንግስት ሰራተኛ በላይ እንዲሆን አድርጎአቸዋል ። መንግስትም ከአገልግሎቱ ማግኘት የሚገባው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያጣ መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል።

በጥናቱ የተለዩ ዋነኛ ችግሮች ከአመለካከት ፣ ከክህሎትና ከተጠያቂነት ማነስ የሚመነጩ ቢሆኑም ሌሎች ምክንያቶችም ተካትተዋል ።

ጥናቱ ብዙ ጉድ ጎልጉሎ ያወጣ ነውና በዝርዝር መመልከቱ አይከፋም ። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሰራተኛውና የአመራሩ ጉዶች ከህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እነሆ —– ።

ግኝት 1. ምቹ የስራ ሁኔታ ካለመኖርና ከግብአት አቅርቦት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች አሉ ። የአብዛኛዎቹ መስሪያ ቤቶች ህንፃ ለሰራተኛውም ሆነ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ በተለይም ደግሞ ለአረጋዊያን ፣ ለነፍሰጡር እናቶችና ለአካል ጉዳተኞች የተመቹ አይደሉም ።

መንስኤው በየደረጃው የሚገኝ አመራር ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ፣ ህንፃዎቹ ሲሰሩ የተጠቀሱት የህብተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያላደረጉ መሆናቸውና ችግሩን በአሰራርና በአደረጃጀት ለይቶ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አናሳ መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል ።

ግኝት 2. ከአመለካከት ፣ ከአገልጋይነት መንፈስ መጓደል ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች ናቸው ። የመንግስት ሰራተኛው በተቀጠረበት የስራ መደብ በቅንነት ህብረተሰቡን የማገልገል ስሜቱ በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን ፣ እራሱን በአገልጋይነት መንፈስ በስነ ምግባር ያለማነፅ ፣ የህዝብ አገልጋይ ነኝ ብሎ በእምነት ያለመቀበልና ይህን ለመቀየር የሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በእጅጉ አናሳ መሆን ነው ተብሏል ።

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

መንስኤውም የስራ ባህል ያለመዳበር ፣ በመብት ላይ ብቻ በማተኮር ግዴታዎችን አለመወጣት ፣ ያልተገባ ጥቅም መፈለግ ፣ ሙሉ ጊዜን በስራ ላይ አውሎ በጥረት ከማደግ ይልቅ ጥቂት ሰርቶ በአቋራጭ ለማደግ የሚደረግ እንቅስቃሴ መሆኑን በጥናቱ ላይ ተቀምጧል ።

ግኝት 3. ከውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር ተያይዞ በየቢሮዎቹ አሁንም ድረስ ያልተቀረፈ የውስጥ መልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ በጥናቱ ተረጋግጧል ።ለአብነት ያክልም ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ፣ ከፍትሃዊነት ፣ በዘመድ አዝማድ በመሳሳብ (Networking) ላይ የተመሰረተ ሹመት ፣ የደረጃ እድገት ፣ የትምህርት ዕድል አሰጣጥ ላይ አድሎአዊ አሰራር በመኖሩ ሰራተኛው ተስፋ የመቁረጥና በሙሉ ልቡ ስራውን እንዳያከናውን አድርጎታል ።የዚህ ነፀብራቅም በአገልግሎት ፈላጊው ህብረተሰብ ላይ አገልግሎቱን በጊዜና በጥራት እንዳያገኝ እያደረገው ይገኛል ።

ግኝት 4. ከአደረጃጀትና የመዋቅር ችግር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች አሉ ። አብዛኛው ሰራተኛ በተማረበትና ልምድ ባካበተበት የስራ መደብ ላይ ያለመስራቱ ፣ መዋቅሮች ሲታጠፉም ሆኑ ሲጨምሩ በቂ ጥናት የማይካሔድባቸው መሆኑ ነው ። አመራሩ ከስር ከስር ችግሮችን እየለየ ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት አናሳ መሆኑ ደግሞ ችግሩ እንዳይፈታ አድርጎታል ።

ግኝት 5. ከአቅም ግንባታ ፣ ከእውቀትና ፣ ክህሎትና ልምድ ማነስ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችም በጥናቱ ተፈትሸዋል ። አመራሩም ሆነ ሰራተኛው ቀደም ሲል በአገኘው የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ላይ በመመስረት ወደ ስራ ከገባ በኋላ ከስራው ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ራሱን ያለማብቃት  ችግር በስፋት ይታያል ።

አልፎ አልፎ በየተቋማቱ የሚሰጡ ስልጠናዎች ቢኖሩም በስልጠናው የሚካፈለው ሰው የሚመለከተው ሳይሆን ከስራው ጋር ምንም ግንኝነት  የሌለውና አመራሩ ለራሱ ቅድሚያ በመስጠት ነው ። ይህም በስራ ቅልጥፍና ፣ ጥራትና ውጤት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩን በጥናቱ ተረጋግጧል ።

በየደረጃው ያለ የአመራር ምደባ በእውቀት ፣ ክህሎትና ስነ ምግባር ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በኔትወርክና በጥቅም ትስስር ላይ የተመሰረተ መሆኑ ፣ የአመራሩ ቶሎ ቶሎ መቀያየርና አመራሩ በትርፍ ጊዜው ራሱን ለማብቃት ዝግጁ ያለመሆን ከችግሮቹ መንስኤዎች መካከል ከፊሎቹ ናቸው ።

ግኝት 6.ከአሰራር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች በርካቶች ናቸው ። ስራውን አክብሮ የሚሰራውም ሆነ በስራው ላይ ትኩረት የማያደርገው  ስለሚመዘን እና የተሻለ ስራ ለሚያስመዘግበው ከሌላ በተለየ ሁኔታ የማትጊያ ስርዓት ስለማይተገበር በውጤታማነትና ቅልጥፍና ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን በጥናቱ የተረጋገጠ ነው ።

በፌዴራልና በአዲስ አበባ ስር ከሚገኙ መስሪያ ቤቶች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት የራሳቸው ህንፃ የሌላቸው ናቸው ። ከሚመደብላቸው በጀት አብዛኛው ወጪ ለቤት ኪራይ ያውሉታል ። ለአብነት በ2008 ዓም 500 ሚሊዮን ዘንድሮ ደግሞ 800 ሚሊዮን ብር ለኪራይ ከፍለዋል ። ይህም በእቅድ የያዙዋቸውን ስራዎች ለማስፈፀም ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸዋል ።

በዚህ ገንዘብ ስንት የራሳቸው የሆነ ህንፃዎች መገንባት እንደሚችሉ ሲታሰብ ደግሞ ምን እየተሰራ ነው ? የሚል ጥያቄ ሆኖ ተገኝቷል ።

አንዳንድ መመሪያዎች ከፌዴራልና ከክልል አልፈው እስከ ታች ድረስ አለመውረዳቸውና ተንጠልጥለው መቅረታቸው በጥናቱ ሲገለፅ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ደግሞ የደንቦችና መመሪያዎች መብዛት ተስተውሏል ።

ለምሳሌ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን 80 የሚሆኑ መመሪያዎች መኖራቸውን በጥናቱ ተረጋግጧል ። እነዚህ መመሪያዎች ከብዛታቸው አንፃር ተገልጋዩ ቀርቶ ፈፃሚው አካልስ ያውቃቸዋል ወይ ? የሚል ጥያቄ የሚያስከትሉ ሆነው ተገኝተዋል ።

የእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች መንስኤ የህዝባዊ ወገንተኝነት ማነስ፣የተጠያቂነት ስርዓት የላላ መሆን ፣ በየደረጃው ለሚገኝ የአመራር ቦታ በግልፅና አግባብነት ባለው መመዘኛ ላይ ተመስርቶ አለመመደብ …. እያለ የጥናቱ ውጤት ዘርዝሮአቸዋል ።

ግኝት 7. ከቅንጅታዊ አሰራርና ከህዝብ አሳታፊነት መጓደል ጋር ተያይዘው የተነሱ ችግሮች የተዳሰሱበት ነው ።በአመራሩም ሆነ በፈፃሚ ባለሙያው ዘንድ በህዝብ ተሳትፎ ውጤታማነት ላይ በእምነት ያለ መያዝ ችግር አለ ።

መመሪያዎችና የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃዎች ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር ሳይወያዩ የሚያወጡ በመሆናቸው በስራ አፈፃፀም ላይ ውጤቱ አናሳ መሆኑ ተረጋግጧል።

 ግኝት 8.  ደግሞ ከቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ ጋር የተያያዙ ችግሮች ላይ ያተኮረ ነው ።ሰራተኛው በተመደበበት የስራ ሃላፊነት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ሳይሰጥ ሲቀር ፣ በእቅዱ መሰረት ተቋማቱ ባወጡት የአገልግሎት ጥራት ደረጃ ሳይፈፀሙ ሲቀሩ የበላይ አመራሩ የሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር የላላ ነው ።

Related stories   ሰላም፣እርጋታና የዜጎች ደህንነት ለኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ እድገት ወሳኝ ናቸው – በአሜሪካ የህዝብ ዲፕሎማሲ አማካሪ ምክር ቤት

መንስኤዎቹ ስራዎችን በለውጥ ሰራዊት አግባብ ለመምራት በአመራሩ ያለው ውስጣዊ ተነሳሽነት ደካማ መሆን ፣ የተገልጋይ ቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓት የተጠሪነት ችግር መኖር ፣ የተገልጋይ የአገልግሎት እርካታ ደረጃ ጥናት በየጊዜው አለማድረግና ስራዎችን በእቅድና በፕሮግራም ወቅቱን በጠበቀ አግባብ አድምቶ ከመስራት ይልቅ በዘመቻ መልክ የመስራት ልምድ የሰፋ መሆኑን ይጠቀሳሉ ።

ግኝት 9.ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የተያያዙችግሮች አሉ ። አንዳንዱ በዘመድ አዝማድ የመስራት ፣ሌላው በስልጣን በመጠቀም በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ጉቦ የመቀበል ፣ ሌላው ደግሞ በእጅ አዙር የመጠቃቀም ሁኔታዎች በመንግስት መስሪያ ቤቶች በስፋት የሚስተዋሉና ያሉ ችግሮች እንደሆኑ ጥናቱ አመላክቷል ።

በተለይ የእጅ አዙር መጠቃቀም በወረዳዎች ጎልቶ የሚታይ ሲሆን አንዱ ሃላፊ የራሱ  ዘመድና የሚፈልገው ሰው በሌላ መስሪያ ቤት ማስቀጠርና ማሳደግ በግልባጩ ደግሞ ውለታ የዋለለትን ሃላፊ ዘመድ እሱ በሚመራው ተቋም ላይ በመቅጠር ብድር መመለስን ያካተተ ነው ።

ይህ ብልሹ አሰራር መንስኤው የግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር ደካማ መሆን ፣ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የራስን ጥቅም ማስቀደም ፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ጋር ሳይታገሉ በአድርባይነት በስልጣን ላይ ለመቆየት መፈለግ ፣የአመራሩ በራስ የመተማመን መንፈስ መጓደል የመሳሰሉትን ያካትታል ።

ግኝት 10 .ከሰራተኛ የፍልሰት ሁኔታ ጋር የተያያዙ ችግሮችም በጥናቱ ተዳስሷል ።የሰራተኛ ፍልሰት በፐብሊክ ሰርቪሱ የተሳለጠ አገልግሎት እንዳይኖርና ለመልካም አስተዳደር እጦት አንዱ ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል ።

ምክንያቶቹ በርካታ ቢሆኑም በጥናቱ የተስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ሁለት ናቸው ። 85 በመቶ የሚሆኑት የተሻለ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ፍለጋ የሚለቁ ናቸው ። 15 በመቶ የሚሆኑትን ደግሞ በውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግርና ምቹ የስራ አካባቢ ያለመኖር ምክንያት መስሪያ ቤታቸውን ለቀው እንደሚሄዱ በጥናቱ ተረጋግጧል ።

የችግሩ መንስኤ በመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል ለተመሳሳይ የትምህርት ዝግጅት ፣ የስራ ልምድና የስራ መደብ የተለያየና ሰፊ የሆነ የደመወዝ ክፍያ መኖር ፣ ሙያና ሙያተኛ  ያለመገጣጠምና የምደባ ስርዓቱ መዛበት ፣ በውስጥ የአመራሩ ኢዴሞክሲያዊ መሆን ፣የአድሎና የኔትወርክ ስራ በስፋት መንፀባረቅ ተጠቃሾች ናቸው ።

የአገልጋይነት መንፈስ መጥፋትና በአቋራጭ የመክበር አባዜ በሰራተኛው ላይ መኖር ፣ሰራተኛውን አስመልክተው የወጡ ህጎች በአግባቡ ያለመተግበር ደግሞ ተጨማሪ መንስኤዎቸ ናቸው ።

የተቀሩት አምስቱ ግኝቶች ከተጠያቂነት መጓደል ፣ ከለውጥ (Reform) ስራዎች መቀዛቀዝ ፣ከሰራተኛው የህክምና ሁኔታ ጋር ፣ ከአመራሩ የአሿሿም ስርዓት ክፍተትና ከመንግስት መዋቅር መስፋት ጋር የተያያዙ ችግሮች ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው ።

ጥናቱ በእያንዳንዱ ግኝት ለተነሱ ችግሮች የመፍትሔ ሃሳብ ያስቀመጠ ሲሆን ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ክፍተቶቹን ለመሙላት ከተሰራ የመንግስት ሰራተኛውን ተስፋ በማለምለምና ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን በማረጋገጥ በስራው ላይ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላል የሚል መደምደሚያ አስቀምጧል ።

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ሰኔ 3 ቀን 2009 ይፋ ያደረገው ይኽው ጥናት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፣ የተመረጡ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የስራ ሃላፊዎችና የክልል ተወካዮች በስፋት መክረውበታል ።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የምክር ቤት ውሳኔዎች አፈፃፀምና የህዝብ ማስተናገጃ ዳይሬክተር አቶ ሸዋንግዛው ማሞ በሰጡት አስተያየት “በአግባቡ መብቱን ተጠቅሞ አገልግሎት ለማግኘት ሔዶ ተሸማቆ የሚመለስ ሰው ብዙ ነው “ ብለዋል ።

ጥናቱ ብዙ ቁም ነገሮች የያዘና የመፍትሔ ሃሳቦችን ያስቀመጠ በመሆኑ በመልካም ጎኑ የሚታይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በቅንጅት የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የቅሬታ ማስተናገጃ ዘርፍ መደራጀቱን ተናግረዋል ።

የኢፌዴሪ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን የጥናቱ ግኝት በውይይት ከዳበረ በኋላ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ ለመልካም አስተዳደር ችግር የመፍትሔ አማራጭ ሆኖ እንዲያገለግል ይደረጋል ብለዋል ።

“ ለመንግስት ስራ ብዙ አትልፋ – ከወንበርህ አትጥፋ “ የሚል አባባልና አስተሳሰብ አሁንም እንዳልተወገደ ሰነዱ አስቀምጦታል ። ሰራተኛውና አመራሩ ከህዝቡና ከአገሩ በላይ ማን አለው ? ሳትሰራ ባዶ ወንበር ታቅፈህ መዋልስ ምን ይፈይዳል ?

ችግሩ የሁላችን መፍትሔውም በእጃችን ነውና ለአገራችን እድገትና ብልፅግናና ለህዝባችን እርካታ በተሰማራንበት መስክ ሁሉ የአቅማችንን ማበርከት ይጠበቅብናል ። በስራዬ አገልጋይ እንጂ ተገልጋይ አይደለሁም የሚል ወኔ ከውስጣችን መመንጨት አለበት ።

ENA

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0