Skip to content

በዓመት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አላቸው የተባሉ አምስት ኢትዮጵያውያን ይፋ ሆኑ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዋቂ ግለሰቦችንና የኩባንያ መሪዎችን የሀብት መጠንና ክንዋኔያቸውን በአኃዛዊ መረጃዎች አስደግፎ በመዝገብ የሚታወቀው ፎርብስ የተባለው መጽሔት፣ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ የአምስት ኢትዮጵያውያንን ይፋ አደረገ፡፡

ፎርብስ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን በመጥቀስ ይፋ ያደረጋቸው አምስቱ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች አቶ በላይነህ ክንዴ፣ አቶ ቴዎድሮስ አሸናፊ፣ አቶ ብዙአየሁ ታደለ፣ አቶ ከተማ ከበደና ወ/ሮ አኪኮ ሥዩም ናቸው፡፡

በመጽሔቱ ዘገባ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ተሰማርተው በሚሊዮን ዶላር የሚገመት ዓመታዊ ገቢ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ቢኖሩም፣ በቀዳሚነት ግን እነዚህ አምስት ባለሀብቶች ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡

ከሚሊየነሮቹ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ አሸናፊ በተለያዩ የቢዝነስ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ በዋናነት የሚታወቁት የአምቦ ውኃ አምራች ሆኖ የቆየውን አምቦ ውኃ ፋብሪካ ሳብ ሚለር ከተባለው የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ጋር ተጣምረው በመግዛትና ሥራውን በማንቀሳቀስ ነው፡፡ ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ የተባለ ኩባንያ በመመሥረትም በነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ ኩባንያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እየመሩ ናቸው፡፡

ፎርብስ እንዳመለከተው አቶ ቴዎድሮስ ለነዳጅና ጋዝ ፍለጋ የተረከቡት ምሥራቃዊው የአገሪቱ ክፍል በኢትዮጵያ ከፍተኛ የነዳጅና ጋዝ ክምችት አለው ተብሎ ይታመንበታል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ሳውዝ ዌስት ሆልዲንግ የተባለ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ቡድን መሥራች ናቸው፡፡ በሳውዝ ዌስት ሆልዲንግስ ሥር ከሚተዳደሩት በርካታ ኩባንያዎች መካከል ሳውዝ ዌስት ዴቨሎፕለመንትና ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሳውዝ ዌስት ዴቨሎፕመንት በአምቦ የማዕድን ውኃ አክሲዮን ማኅበር፣ በኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ (ኮካ ኮላ)፣ በኢትዮጵያ ትምባሆ ሞኖፖልና በሌሎች በርካታ ኩባንያዎች ላይ የአክሲዮን ባለድርሻ ሲሆኑ፣ በጋምቤላ የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤትም ናቸው፡፡

የሪፖርተር መረጃ እንደሚያመለክተው ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ በነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ የተሰማራ ኩባንያ ሲሆን፣ በሶማሌ ክልል በኦጋዴንና በጋምቤላ ክልል የነዳጅ ፍለጋ ፕሮጀክቶች በመምራት ላይ ይገኛል፡፡

እንደ አቶ ቴዎድሮስ ሁሉ ፎርብስ ሚሊየነር እንደሆኑ የጠቀሳቸው አቶ ብዙአየሁ ታደለ ደግሞ የተሳተፉበት ዋና ዋና ቢዝነስ ብሎ የተጠቀሰላቸው ደግሞ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግስ የተባለው ኩባንያ መሥራችና ከፍተኛ ባለድርሻ መሆናቸው ነው፡፡ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ብዙአየሁ፣ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ውጤቶች ላይ የተሰማራ ግንባር ቀድም የግል ኩባንያ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ በጋራና በተናጠል ወደ 30 የሚሆኑ ኩባንያዎች ውስጥም ባለቤት በመሆን ይታወቃሉ፡፡

ከ35 ዓመታት በላይ በንግድ ሥራ ላይ የቆዩት አቶ ብዙአየሁ 17 ኩባንያዎችን በግል በማቋቋም እየሠሩ ሲሆን፣ በዓመት አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ሽያጭ አላቸው፡፡ በየወሩ ለሠራተኞች 30 ሚሊዮን ብር ደመወዝ እንደሚከፍሉ ሪፖርተር ያሰባሰበው መረጃ ያስረዳል፡፡

በሻይ ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በቤቶች ልማት፣ በሲሚንቶ፣ በከሰል ማውጣት ሥራ ላይ መሰማራታቸው ይታወቃል፡፡ ሪፖርተር ባሰባሰበው ተጨማሪ መረጃ መሠረት አቶ ብዙአየሁ የመጀመሪያው የግል ኢንዱስትሪ ዞን መሥራች ናቸው፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ ውስጥ በተሰማሩባቸው የቢዝነስ ዘርፎችና በዚህም ባገኙት ውጤት ሊንከንና ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ በጋራ በመሆን የክብር ዶክትሬት እንደሰጡዋቸው አይዘነጋም፡፡

ፎርብስ ሌላው ያስተዋወቃቸው ባለሀብት ከሌሎቹ የተለየ ታሪክ አላቸው፡፡ እንደ ሌሎቹ ቢዝነሳቸው አጠገብ ሆነው በማንቀሳቀስ ላይ አይደሉም የሚገኙት፡፡ ኬኬ የሚባል መጠሪያ ያለው ኩባንያ ባለቤት የሆኑት አቶ ከተማ ከበደ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ናቸው፡፡ ከቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተከሰው በእስር ላይ ያሉት አቶ ከተማ፣ ኬኬ የተባለ ኤክስፖርት የሚያደርግ የብርድ ልብስ ፋብሪካ ያላቸው ሲሆን፣ ተመሳሳይ በሆነ የኩባንያ ስያሜ የተለያዩ ትልልቅ ማሽነሪዎችንና ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት የሚሠራ ኩባንያ ባለቤትም ናቸው፡፡

ኬኬ የተባለው የብርድ ልብስ ፋብሪካ መሥራችና ባለቤት የሆኑት አቶ ከበደ በአሁን ወቅት በእስር ላይ ቢሆኑም፣ በዓመት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ሽያጭ ያላቸው ኩባንያዎች አሉዋቸው፡፡

አቶ ከበደ ለእስር ከመዳረጋቸው በፊት በአዲስ አበባ በግለሰብ ደረጃ ትልቁ ነው የተባለውን ሕንፃ በመገንባት ላይም ነበሩ፡፡ ከ20 ፎቆች በላይ ያሉት ይህ ግዙፍ ሕንፃ ከብሔራዊ ቴአትር ትይዩ ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ፊት ለፊት እየተገነባ የነበረ ቢሆንም፣ የማጠናቀቂያ ሥራ እየቀረው ተቋርጧል፡፡

ወ/ሮ አኢኮ ሥዩም በፎርብስ መጽሔት ብቸኛዋ ሴት ባለሀብት ተብለው የቀረቡ የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤት ናቸው፡፡ እኝህ ኢትዮጵያዊት ሚሊየነር በሆቴል፣ በኮንስትራክሽን፣ በትራንስፖርትና በሎጂስቲክስ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ባለቤት ናቸው፡፡ የኮንስትራከሽን መሣሪያዎች በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን መጽሔቱ ይገልጻል፡፡

ሪፖርተር ባሰባሰበው መረጃ በወ/ሮ አኢኮ ባለቤትነት ከሚተዳደሩ ኩባንያዎች ውስጥ ከ90 በላይ ትልልቅ ተሽከርካሪዎችን የያዘው የከባድ ጭነት ማመላለሻ ኩባንያቸው ይጠቀሳል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንገድ ኮንስትራክሽን ግንባታ የተሸጋገረው የኮንስትራክሽን ኩባንያቸው ከ2.5 ቢሊዮን ብር ላይ ዋጋ ያላቸው ሁለት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችለውን የኮንስትራክሽን ስምምነት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመዋዋል ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በመሠረት ቁፋሮ ግንባታ ከሚታወቁ ጥቂት ኩባንያዎች መካከል የሆነ ኩባንያም አላቸው፡፡

ከሌሎች የመረጃ ምንጮች ማሰባሰብ እንደተቻለውም በቡና ወጪ ንግድ ላይም የተሰማሩ ሲሆን፣ ቡና በማገበያየት ከሚታወቁት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወንበሮች መካከል አንዱ የወ/ሮ አኢኮ ነው፡፡

በመጽሔቱ ዘገባ ሚሊየነር ተብለው የተጠቀሱት ሌላው ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አቶ በላይነህ ክንዴ ናቸው፡፡ አቶ በላይነህ ክንዴ ከስድስት በላይ በሚሆኑ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ በሆቴል፣ በአስመጪና ላኪነት፣ በኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርትና በግብርና ምርቶች ግብይት ተሳታፊ ናቸው፡፡ የሥራ መነሻቸው የእህል ንግድ እንደሆነም ይታወቃል፡፡

በሆቴል ዘርፍ የኢትዮጵያ ሆቴልን ከመንግሥት ላይ በመግዛት እያስተዳደሩ ነው፡፡ በኢንዱስትሪው  ደግሞ በኢትዮጵያ ቀዳሚ የተባለውን የቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ የገዛው እሳቸው ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑበት ፀሐይ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡

ከ110 በላይ የደረቅና የፍሳሽ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተዳድር ድርጅት ያላቸው ሲሆን፣ ጎልደን ባስ የተባለ ድንበር ተሻጋሪ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ድርጅት ባለቤትም ናቸው፡፡ በቡና እርሻ ላይም የተሰማሩት አቶ በላይነህ፣ እንደ ሰሊጥና ቡና ያሉ ምርቶችን በመላክም ይታወቃሉ፡፡

ከ3,000 በላይ ጊዜያዊና ቋሚ ሠራተኞች የያዙ ኩባንያዎችን የሚያስተዳድሩ አቶ በላይነህ፣ በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥም ከፍተኛ መጠን ያላቸው አክሲዮኖች ባለቤት ናቸው፡፡

Reporter Amahric

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
የባህል አብዮት በኢትዮጲያ

ሃይማኖትና ፍልስፍና በነፃነት የመስራትና ንብረት የማፍራት መብት፣ በምዕራብ አውሮፓ ሆነ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ ስረዓት ባላቸው ሀገራት በሕገ-መንግስት የተደነገገና የሕግ ጥበቃ የሚደረግለት...

Close