አቻምየለህ ታምሩ

old addis

ዛሬ የማቀርባቸው ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃዎች የኦነግ የጥላቻ ዶክተሮች ላለፉት አርባ አመታት ሲደርቱት የኖሩትን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ከራሳቸዉ የመከራከሪያ ሀሳብ ብቻ በመነሳት ከስር መሰረቱ የሚንዱ ናቸው። ለምን ቢባል የማቀርባቸው የታሪክ ማስረጃዎች የማያከራክሩ ብቻ ሳይሆኑ ዛሬም ድረስ ቦታው ላይ የሚገኙ ቋሚ ምስክሮች ስለሆኑ ነው።

የኦነግ ፖለቲካ ላለፉት አርባ አመታት ስንሰማው የኖርነው የጥላቻና የቢላዋ መሳል ዘመቻ ነው። የሚሳለው ቢላዋም የአማራንና የኢትዮጵያን አንገት ለመባረክ ነው። ኦነጎች ለትግል አነሳሳን የሚሉት ዋነኛ ፕሮፓጋንዳቸው አጼ ምኒልክ ቅኝ ገዝተውናል የሚለው የሀጢዓት ክሳቸው ነው። የኦነግ «የታሪክ ፕሮፌሰሮች» ተረት ተረታቸውን ቀጠል ያደርጉና «አጼ ምኒልክ ወደ ኦሮምያ ዘምቶ የፊንፊኔን ስም ወደ አዲስ አበባ በመቀየር በኦሮሞ አጥንት ላይ አማራን አስፍሮ ዋና ከተማውን አዲስ አበባ ላይ ከመሰረተ በኋላ የተቀረውን ኦሮምያ ደግሞ በመውረር ቅኝ ግዛቱ አደረጋት» ይሉናል። ሌላው የኦነግ ክስ የአማራ ሀይማኖት አራማጅ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዋቄ ፈታ ተከታዩን ኦሮሞ በማጥመቅ ከማንነቱ አፋታዋለች በማለት የሚነዛው ፉርሽ አስተምህሮው ነው። የጽሁፌ ዋና መከራከሪያም [main argument] ኦነግ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ባለቤትና ዋና የኦርቶዶክስ ክርስትና አስፋፊ አማራ ነው የሚለውን ፕሮፓጋንዳ ቅቡል ያደረገ ነው።

እንግዲህ ጨዋታው በብሔረሰብ ከሆነ፣ ዛሬ የማቀርባቸው ማስረጃዎች ከሁሉ አስቀድሞ አዲስ አበባና አካባቢዋ የማንኛው ብሔረሰብ እንደነበረች የሚያሳዩ ናቸው። የማቀርባቸው ማስረጃዎች ሁለት ናቸው። እነዚህም ማስረጃዎች አዲስ አበባ ውስጥና በዙሪያዋ የሚገኙ ጥንታዊ ቤተክርስቲያናት ናቸው። ቤተክርስቲያኖቹ በዋናነት አማሮችና ሌሎች የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኞች የሆኑ ምንመናን መንፈሳዊ ተግባሮቻቸውን ይፈጽሙባቸው የነበሩ የእግዚያብሔር ቤቶች ናቸው።

እነዚህን ጥንታዊ የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚከተለው ላቅርብ፤
1. አዲስ አበባ ውስጥ እነማን ይኖሩ እንደነበር የመጀመሪያው ማስረጃ ዋሻ ሚካኤል የሚባል 1600 አመት እድሜ ያስቆጠረ የአለት ውቅር ቤተክርስቲያን ሲሆን የሚገኘውም አዲስ አበባ የካ አምባ ላይ ነው። ይህ ቤተክርስቲያን የላሊበላ ውቅር ቤተክርስቲያን አይነት ስልት የያዘ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የአለት ውቅር ቤተክርስቲያኖች በትልቅነቱ ሁለተኛ እንደሆነ ተመራማሪዎች ዘግበዋል።

[ STRACHAN/PANKHURST, Dr. Richard, The Semi-monolithic Church in Yeka – Heritage Site in Danger, Annales d’Ethiopie]

2. አዲስ አበባ ውስጥ እነማን ይኖሩ እንደነበር ሁለተኛው ማስረጃዬ የአንፋር ወይንም የአዳዲ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ቤተ ክርስቲያኗ የምትገኘው ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ወደቡታጅራ በሚወስደው መንገድ ከዋሻ ሚካኤል 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሌመን ወረዳ ውስጥ ነው። ይቺ ቤተ ክርስቲያንም እንደ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ከወጥ ድንጋይ ተፈልፍላ የተሠራች ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሰረተችና ዛሬ 740 አመት እድሜዋን ያከበረች ጥንታዊ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ናት። [ Ibid]

እነዚህ ቤተ ክርትስቲያኖች ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በየዘመናቱ የገጠማቸውን መከራ አልፈው ጸንተው ይኖራሉ።

ለኔ ኦሮሞ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር የነበረ ህዝብ ነው። ስለዚህ ለኔ ኦሮሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ከደቡብ ወደ ሰሜን ያደረገው እንቅስቃሴ ከአንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ያደረገው መስፋፋት ነው። ስለዚህ ኦነግ እንደሚነግረን የኦሮሞ ህዝብ እስከ አጼ ቴዎድሮስና አጼ ምኒልክ ዘመን ድረስ የዋቄ ፈታ እምነት ተከታይ ከነበር፤ ኦሮሞዎች ወደ ሰሜን [በኢትዮጵያ ውስጥ] ከመስፋፋታቸው በፊት ከፍ ብዬ የጠቀስኋቸው ቤተክርስቲያኖች የሚገኙበት መሬትና በቤተ ክርስቲያኖቹ ዙሪያ ይኖር የነበረው ህዝበ ክርስቲያን ይኖርበት የነበረው መሬት [ዛሬ አዲስ አበባ የሆነው መሬት ማለቴ ነው] የማን ነበር? ካልን የዚህ ጥያቄ መልስ ቀላል ነው። በኦነጎቹ መከራከሪያ መሰረት በሁለቱ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኖች ዙሪያና በቤተ ክርስቲያኖቹ አጥቢያ ይኖር የነበረው ባለአገር ዋቄ ፈታ አራማጁ ኦሮሞ ሳይሆን ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይና እንደ ማህበረሰብ ባካባቢው ይኖር የነበረው አማራው ነው። ታዲያ እውነታው ይህ ከሆነ የቤተ ክርስቲያኖቹ አጥቢያ፣ የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ቅኝ ገዢ ማነው? ኋላ የመጣው ኦሮሞው ነው? ወይንስ ከጥንት ጀምሮ በአጥቢያ ቤተክርስቲያኖች ሲኖር የነበረው አማራው?

በቤተክርስቲያኖቹ ዙሪያ ይኖር የነበረው አማራም ይሁን ቤተክርስቲያኖቹ የተመሰረቱት ከምኒልክ «ወረራ» በኋላ ነው እንዳይባል የዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያንም ይሁን የአንፋር ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የተቆረቆሩት በቅደም ተከተል ምንሊክ ከመወለዱ ከ1414 እና 554 ዓመታት በፊት ነው። በነገራችን ላይ እንጦጦ ማሪያምም የተሰራችው ቦታው ላይ ይኖር የነበረው ቤተ ክርስቲያን ወድሞ ሲኖር ከጊዜ በኋላ የወደመው ቤተክርስቲያን ፍርስራሽ በመገኝቱ ድሮ የፈረሰው ቤተክርስቲያን አሻራ እንዳይጠፋ በሚል እሳቤ የቀደመው ቤተክርስቲያን ይገኝ በነበረበት ቦታ ላይ እንደ ገና ተተክላ ነው። ይሄም የሚያመላክተን የእጦጦ አካባቢ የአዲስ አበባ መሬትና የዙሪያ ገጠሙ ኗሪዎች የአማራ የክርስቲያኖች እንደነበሩ ነው። ባጠቃላይ ኦሮሞ የዋቄ ፈታ ተከታይ ነበር ከተባለና አዲስ አበባ ኦነግ እንደሚለው የኦሮሞ ብቻ ከነበረች ጥንታዊነት ያላቸው ቤተክርስቲያኖች በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ከሆነ፤ እነዚያ ቤተከርስቲያኖችች በእርግጠኝነት የኦሮሞ ቤተ እምነቶች አይደሉም። እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያኖቹ ደግሞ የግዴታ ተገልጋይ ይኖራቸዋል ። ኦሮሞው ደግሞ የዋቄ ፈታ እምነት ተከታይ ነው። ከዚህ ተነስተን የምንደርሰው ድምዳሜ አዲስ አበባ ኦነግ እንደሚለው የኦሮሞ መሬት ሳትሆን የአማራ ነባር እርስት እንደሆነች ነው። አሁን ኦነግና ተከታይ ጀሌዎቹ በቤተክርስቲያን ለምን እንደዘመቱ ግልጽ ነው። የቤተ ክርስቲያን እድሜና በቤተክርስቲያን ዙሪያ ያለው መሬት የማን እንደነበር የነሱን ቡትቶ ፕሮፓጋንዳ አፈር ድሜ የሚያስግጥ ማስረጃ ስለሚሆን ቤተ ክርስቲያን እንድትጠፋ ይሻሉ! በገቢርም ቤተክርስቲያን ላይ ዘምተው ኖረዋል፤ ወደፊትም ይቀጥላሉ። መሬት ላይ ያለው እውነታው ይህ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የኦነግን ፕሮፓጋንዳ ወደ ጎን ትተን ሺ ዘመናት ያስቆጠሩ ቤቴክርስትያንችን ሌሎችንም ተመሳሳይ አሻራዎችን ወስደን ብናጤን ኦሮሞ አዲስ አበባ አካባቢው ለዘመናት ኖረ እንኳ ብለን ብንወስድ ኦሮሞ አዲስ አበባ ውስት ከክርስቲያኑ ወይንም ከአማራው ጋር አብሮ ኖረ ወይንም co-exist አደረገ ልንል እንችል ይሆናል እንጂ ዛሬ በኦነግና በወያኔ እንደሚደሰኮረው የብቻው አዲስ አበባ ባለቤት ሊሆን አይችልም።

እንግዲህ ምን ይደረግ! «ተው ማነህ ተው ማነህ የተኛውን ልቤን ትቀሰቅሳለህ። መንደርተኛው ሁሉ እሳት ጫሪ ነው፣ ያንን ገል አደራ ሰው እንዳይነካው፤» ስትል እንሰማለን ዘፋኟ። አይ ግጥም! አይ ጥበብ! እኔምለው ለምንድነው ውስጠ ወይራ ጥበብም እንደ ተማሪዎች ንቅናቄ አንድ ዘመን ላይ ብልጭ ብሎ የጠፋብን? ግን መቼ ጠፉብን እነሱ? ታይተው ቢጠፉ ኖሮማ አርባ አመት ውቅያኖስ ውስጥ ገብተው ቁልቁል ተዘቅዝቀው ኖረው ዋና መማር ሳይችሉ አድሮ ቃሪያ እየሆኑ ዛሬም ያኔ ከአርባ አመት በፊት እንደነበረው የተማሪው ንቅናቄ ግብታዊ በሆነ አካሄድ የእውር ድንብታቸውን አይሄዱም ነበር። እኛ ግን ነገሩ ሁሉ ሲጨማለቅ እያየን አቃለነው ጠፍተናል።

የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ እስካለች ድረስ አዲስ አበባ የመላው አትዮጵያዊያን፣ የአፍሪካዊያንና የዓለም ከተማ ነች። ኦነግ እንደ ጉም ተኖ እንደ አቧራ በኖ ይቀራል። አዲስ አበባም ከኦሮሞ ጀምሮ የመላው አትዮጵያዊ ከተማ ሆና ትኖራለች::

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *