በሳዲቅ አህመድ

 

sadidue

የቀጠር ጾመኞች የሌሊት ገበታን (ሱህርን) ተቋድሰዉ የጠዋት ሰላትን (ስግደት) አከናዉነዉ የሚተኝዉ ሲተኛ ወደ ስራ የሚሰማራዉ ሲሰማራ ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ።በጁን 5/2017 ባህሬን ማለዳ ከቀጠር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማቋረጧን አወጀች። ከ10ደቂቃ በሗላ ሳኡዲ ተከተለች።ከ10 ደቂቃ በሗላ ግብጽና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቀጠርን ማግለላቸዉን አሳወቁ። ምስራቃዊ ሊቢያና የመን ተከተሉ። የአየር፣የባህርና የምድር ግንኙነቱ ተቋረጠ። ወዲያዉኑ ኢትሃድ፣ ኢምሬትና የሳዑዲ የአየር መንገዶች ወደ ዶሃና ከዶሃ ዉጪ የሚያደርጉትን በረራቸዉን ሰረዙ። ድንገተኛዉ ዲፕሎማሲያዊ መዋከብ ጸና። ግራ የተጋባቸዋ ቀጠር ለአለም ስሞታን ማሰማት ቀጠለች። «አገራቱ እኔን ለማግለ ምንም አይነት ህጋዊ ሽፋን የላቸዉም፣አለም አቀፋዊ ህጎች ተጥሰዋል ብላ ወቀሰች። ሳዑዲ አረቢያ ጉዳይዋን ለማስረዳት በመሞከር «ቀጠር ሽብር ፈጠራን ትረዳለች፣በኢራን የሚደገፉትንየየመን የሁቲ አማጽያን ደግፋ ሉዓላዊነቴን አደጋ ላይ እንዲኖር አድርጋለች» የሚል ማመካኛ ሰጠች። ቀጠር ክሱን አጣጥላ ሽብር ፈጠራን እንደማትደግፍ አሳዉቃ ዲፕሎማሲያዊ ምቱን ለመከላከል ጥረቷን ቀጠለች።ዉጥረቱ እንደነገሰ ባለበት ወቅት ታሪካዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን በወፍ በረር በመዳሰስ በግጭቱን እንመልከት።

አልሱዑድ እና አብድልወሃብ

የተለያዩ ነገስታትና መሪዎች በሚፎካከሩባት አረቢያ ዉስጥ የአልሱዑድ ቤተሰቦች ተጽእኖ መፍጠር ከጀመሩ ቆይቷል። የአሁኗ ሳዑዲ አረቢያ ከመፈጠሯ በፊት የአልሱዑድ ቤተሰቦች የደራኢያ አሚርነትን ተጎናጽፈዉ ነጅድ የሚባለዉ ሰፋ ያለ ግዛትን ለማስተዳደር በቅተዋል። የአልሱዑድ ቤተሰቦች ሙሐመድ አብድልወሃብ ከሚባሉት የሐይማኖት አስተማሪ ጋር ቃል ኪዳንን ፈጽመዉ በጋብቻ ተቆራኝተዉ ሐይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሐይልን ተቀዳጅተዉ መስፋፋታቸዉን ቀጠሉ። አሃዳዊ አምልኮን (ተውሒድ) የሚያስተምሩት መሐመድ አብድልወሃብ ባእድ አምልኮን (ቢደዓ) ከአካባቢዉ ሊያጠፉ የጀመሩትን ስርነቀል ለዉጥ እንዲያጠናክሩ የአልሱዑድን ድጋፍና ጥበቃ ይሹ ነበር። ባንጻሩ በአረብ በድዉያን መካከል የፖለቲካ ስልጣንን ተጎናጽፈዉ ባካባቢዉ  የሐይል መሰረት መሆን የሚሹት መሐመድ ቢን ሱዑድ ህዝብን በአንድ ማእቀፍ ዉስጥ የሚያስገባላቸዉን ሐማኖታዊ አስተሳሰብን ይሹ ነበር። ፈላጊና ተፈላላጊ ተጋጥመዉ ያከናወኑት ጥምረት በዘመንና በትዉልድ ሳይገታ ቀጥሏል። የአብድል ወሃብ ትምርት ተስፋፍቶ የህዝቡን አስተሳሰብ በስነ ሐይምኖት ተቆጣጠረ።በጦርነት ክንዱን ያደነደነዉ የአልሱዑድ ቤተሰቦች የጦር ጥምረት ህዝቡን በሐይል አርበድብዶ የገዢ ሐይል በመሆን በአረብ ጎሳዎች ዘንድ ገናና ሆኖ ወጣ። አልሱዑድ ቤተሰቦች የእንግሊዝ ቀልብ አረፈባቸው። መስፋፋቱ ሳይገታ ከ10ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሐሺሚት ስርወ-መንግስት ስር የነበረችዋን መካን ተቆጣጠሩ መላዉንም የሒጃዝ መሬት  በጃቸዉ አስገቡ። የአልሱዑድ ቤተሰብ ከየመን ግዛቶች ለም መሬትን ሸራርፎ  በመዉሰድ በእንግሊዞች ድጋፍ  የዛሬይቱን ሳዑዲ አረቢያ በ1932 እ.ኤ.አ በስሙ መሰረተ። ጅማሮዉ አሃዳዊ አምልኮን (ተዉሒድን) ማስረጽ የነበረው የመሐመድ አብድልወሃብ አስተምሮ «ወሃቢ» የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት መስፋፋቱን ቀጠለ። መካና መዲና በአልሱዑድ ቤተሰቦች እጅ ወደቁ። የንጉሳዉያን ቤተሰቦቹ እራሳቸዉን የሁለቱ ቅዱሳን መስጊዶች አገልጋይ የሚል መጠሪያን ቸሩ።

የኦትማን ኢማፓየር መመናመን

የአብድል ወሃብና የአልሱዑድ ጥምረት ከመካከለኛዉ ምስራቅ እስከ አዉሮፓና አፍሪካ የደረሰዉን ማእከላዊ የኦትማን ኢምፓየር መንግስት (1299-1922 ..) ከእንግሊዝ ጋር በመተባበር እንዲመናመን አደረገ። እስከ 1922 .. የዘለቀዉ የቱርኩ የኦትስማን ኢምፓየር በስሩ በከፊል አዉሮፓንን ፣ግሪኮችን፣በርበሮችን፣አረቦችን፣ቱርኮችንና ኩርዶችን ያካተተ ነበር። ሙስሊሞች፣ክርስቲያኖችና አይሁዳዉያን በጥምረት ይኖሩበት የነበረዉ የኦትማን ኢምፓየር መኮማተሩ ይፋ ሲሆን በቦታዉ የተተኩት የአረብ የጦር አበጋዞች ገናና ይሆኑ ጀመር።በከርሰ ምድሩ ዉድ ማእድንና የነዳጅ ዘይት ያመቀዉ የባህረ ሰላጤዉ በርሃ የጦር አበጋዞች ንግስናን ወይም አሚርነትን ከእንግሊዞች የሚቀበሉበት ቦታ ሆነ።ያያኔዎቹ የጎሳ የጦር አበጋዞች ያሁኖቹ ንጉስና አሚሮች የሐብትን ጣእም እያጣጣሙ ተስማማተዉ ሳይስማሙ፤ተጣልተዉ ሲታረቁ፤ያበቅየለሹን ንትርካቸዉንና መናቆራቸዉን እንደ ሸቀጥ ወደ አለም እየላኩ ይገኛሉ። ከሐያላን አገራት ጋር በእከከኝ ልከክህ‘ የጥቅም ቁርኝት ያደርጋሉ።አገር ሆነው  ድንበር ተሰምሮላቸዉ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መቀመጫን ይዘዉ እስከዛሬ ዘልቀዋል። የአንደኛዉን አለም ጦርነት ተከትሎ የእንግሊዝ የቀኝ እጅ የሆኑት የአልሱዑድ ቤተሰቦች የሙስሊሞችማእከላዊ አስተዳደር እንዲፈርስና የኦትማን ኢምፓየር እንዲኮማተር በማድረግ ሚናቸዉን በታሪክ መዛግብት ላይአስፈረዋል።

የሳኡዲና የቀጠር ዲፕሎማሲያዊ ግርግር 

ጉዳዩ የአገራት መናቆር ነዉ። ጉዳዩ የሳዑዲዎቹ የአል ሱዑድ ቤተሰብና የቀጠሮቹ የአል ሳኒ ቤተሰብ ፉክክር ነዉ። ጉዳዩ በሳዑዲዉ ንጉስ አስተዳደር ዉስጥ የጎላ ድምጽ ያለዉ ተለዋጭ አልጋ ወራሹ መሐመድ ቢን ሰልማን ቢን አብዱል አዚዝ አል  ሱዑድ በችኮላ የሚፈጥራቸዉ  አስተዳደራዊ ወከባዎች አካል ነዉ። ጉዳዩ የአል ሱዑድ ቤተሰብ የስልጣን ምርኩዝ የሆነዉ የበደዉያን ባህላዊ እሴት ላይ መሰረት ያደረገዉ ጥብቁ አሃዳዊ  አስተምሮት ላይ የተንተራሰዉ የመሐመድ አብድል ወሃብ አስተምሮት የሚያደርገዉ ስነ ሐይማኖታዊ ፉክክር ነዉ።ጉዳዩ በሳይንስ፣ በምርምር፣ በስፖርት፣በኢኮኖሚ፣በፖለቲካ፣በጤናና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሁለገብ መዋቅር ካለዉ የሙስሊም ወንድማቾች ጋር የሚደረግ የሐሳብ ፍልሚያ ነዉ።ጉዳዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለዉጥን ለማስረጽ በመምህር ሐሰን አል በና እ.ኤ.አ በ1928  የተመሰረተዉ የሙስሊም ወንድማማቾች መጠለያን ቀጠር ዉስጥ በማግኘቱ የተፈጠረ ዉጥረት ነዉ። የሙስሊም ወንድማማቾች በቀጣናናዉ በመስፋፋቱ ሳቢያ ከሳዑዲዉ የአብድልወሃብ አስተምሮት ጋር የተፈጠረዉ ዉጥረት በመፈንዳቱ የተከሰተ ክስተት ነው።

የአረቡ አለም መንግስታት ሙስሊም ወንድማቾችን ይፈራሉ ቀጠር ስትቀር

ሰንሰለታማ የሆነ መዋቅርን በመሬት ላይ በመዘርጋት ይታወቃሉ።ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑት የግብጾቹ ሙስሊም ወንድማቾች በ1952 እ.ኤ.አ ያገሪቱን አብዮታዊ ወታደራዊ ክንፍ በመደገፍ በወቅቱ ያስተዳድሩ የነበሩትን ንጉስ ፋሩቅን በመጣሉ ሒደት ዉስጥ ተሳትፈዋል።የህዝቡን ንቃተ ህሊናን  በማዳበሩ ረገድ የነበራቸዉ ሚና የላቀ ነበር። የፕሬዝዳንት ጀማል አብድል ናስር ሴኩልራዊ አስተሳሰብ በጽኑ የተቃወሙት የሙስሊም ወንድማቾች  በፕሬዝዳንቱ ላይ ግድያ ሙስከራ አድርገዋል ከተባለ በሗላ ከግብጽ መንግስት ጋር ፍጥጫ ዉስጥ ገበተዋል።

ፕሬዝዳንት ሁስኒ ሙባረክ በህዝባዊ አብዮት ከስልጣን እስኪወርዱ ድረስ የሙስሊም ወንድማቾች ላይ ከፍተኛ ጫና ከፍተኛ ነበር። በርካታ የሙስሊም ወንድማማቾች ምሁራን ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት ተሰደዋል።በየአገራቱ የመማርና ማስተማር ሒደት ዉስጥ ዘለቀዉ በመግባትና ከትንሽ እስከ ትላላቅ ባሉ ኩባንያዎች ዉስጥ ገብተዉ በመስራት የግልጽና የህቡእ  ለዉጦች ባለቤት ሆነዋል። ወንድማማቾች (ኢኽዋን) በየአገራቱ የአስተሳሰብ ለዉጥ በማምጣትና የኢኮኖሚ አቅምን በማጎልበት ያላቸዉ ሚና የሰፋ ነዉ።ይህ የነጅድ ዘይት ሐብት ባደነደናት ሳዑዲ አረቢያ ላይ የተሰየመዉ ንጉሳዊ ቤተሰብ መስማት የሚፈልገዉ ጉዳይ ባለመሆኑ ቤተሰቡ በዙፋኑ ላይ ተደላድሎ ለመግዛትና የሳዑዲን ህዝብ የለዉጥ ፍላጎት ለማምከን የተቻለዉን ሁሉ ያደርጋል።

የግብጽ ሙስሊም ወንድማቾች ሁከትን ትተዉ የማህበራዊና የእዉቀት ዘርፎችን አጥብቀዉ ይዘዋል።የዘረጉትን የርዮተ-አለም ሰንሰለት የግብጹ የሁስኒ ሙባረክ መንግስት ሊቆርጠዉ አልቻለም። በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አገሪቱን ለ30 አመት የጠፈረዉ የሁስኒ ሙባረክ አመራር በሙስሊም ወንድማቾች አመራር ላይ ብዙ ጫናዎችን አሳድሯል።በርካቶች ሲታሰሩ፣የስቃይ አያያዝ ሲያዙና ሲገደሉ፤ ከዚሁ መከራና ስቃይ ለመዳንም በሺዎች የሚቆጠሩ ሸሽተዉ ወደ ተለያዩ አገራት ተሰደዋል። ትንሿ ቀጠር የሙስሊም ወንድማማቾችን በማስጠጋትና ከአገራቸዉ ዉጪ መዋቅራቸዉን ዘርግተዉ ይስፋፉ ዘንድ በመፍቀዷ ሳዑዲ የምትሰጋዉ የአረቡ አለምና የባህረሰላጤዉ ሒደት ሆኗል። ታዋቂዉ ግብጻዊዉ የሐይኖት ሊቅ ዶክተር ዩሱፍ አልቀርዳዊ ቀጠር ዉስጥ በጥገኝነት ተቀምጠዉ ሐይማኖታዊ አስተምሮታቸዉን በመላዉ አለም ቀጥለዋል።ቀርዳዊ የሳዑዲ ዜጎችን ቀልብ እየሳቡ መምጣታቸዉ በጋብቻ፣በሐይምኖታዊ አስተምሮትና በፖለቲካዊ ርዮተ-አለም ከአብድልወሃብ ጋር ተሳስረዉ ሳዑዲን አንቀጥቅጠዉ ለሚገዙት የአልሱዑድ ቤተሰቦች ስጋት ሆነዋል።

የግብጽ ምሁራን ቀጠር ዉስጥ በብዛት ሰፍረዋል። የዛሬይቱ ቀጠር በሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች ሳትታነጽ፣ የቴክኖሎጂ ማማ ላይ ከፍ ብላ ሳትወጣ በፊት አያቶቻቸዉ የጦር አበጋዝ የነበሩት የቀጠር አሚሮችና የአል ሳኒ ቤተሰቦች ከግብጻዉያኑ የሙስሊም ወንድማማቾች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸዉ። ትንሿ አገርም ለስላሳ ሐይልን ተጎናጸፍ ዘንድ ከወንድማቾቹ ምክር ያገኛሉ። አረቡ አለም ዉስጥ ከሚመጡት ለዉጦች በስተጀርባ ሆነዉ በግልጽም በህቡእም የሚሰሩት የግብጽ ምሁራን በሒደት በአሱዑድ ቤተሰብ ጭቆና ያለ አማራጭ የሚኖረዉ የሳዑዲ ህዝብ ከወደ ቀጠር የሚፈነጠቀዉን ለዉጥ በነቂስ አሻግሮ ሳይመለከት በፊት መስተጓገል ስለነበረበት ሳዑዲ ዲፕሎማሲያዊ መናቆርን ለኮሰች።

ከአልጀዚራ በስተጀርባ

ከትንሿ የዶሃ ከተማ በመላዉ አለም ላይ የገነነ የሚዲያ ሐይልን ቀጠሮቹ ተጎናጽፈዋል።ከአሜሪካዉ የጆርጅ ቡሽ (ልጅየው) አመራር ጀምሮ አሜሪካ በአልጀዚራ ላይ ቅሬታ ታሰማለች።እንደተለመደው ከጆርጅ ቡሽ (ልጅየው) ጋር የበደውያን ባህላዊ ዳንስ የደነሱት ሟቹ የሳዑዲ ንጉስ አብደላህ ቢን አብድል አዚዝ አል ሱዑድ በአልጀዚራ ላይ የነበራቸዉ ቅሬታ የሚዘነጋ አይደለም።የግብጾቹ የሙስሊም ወንድማማቾች ልሒቃን በቀጠሩ አልጀዚራ ላይ እንደልብ መቅረባቸዉ በአረቡ አለም ዉስጥ ጽኑ የሆነ አስተሳሰብ ለዉጥ ይመጣ ዘንድ መንስኤ ሆኗል። ከአምላክ በታች አስተዳዳሪ  የሚባሉልትን የሳዑዲ የንጉሳዉያን ቤተሰቦች የሚሰጉበት ንቃተህሊና በአገራቸዉ ዉስጥ እየጎለበተ ነው።

አልጀዚራ ሚዲያ በኩል በተፈጠረዉ ወጋገን ግብጽ ባንድ ወቅት ፈክታ ነበር።የሙስሊም ወንድማቾች በግብጽ መሬት ላይ የፈጠሩት ሰንሰለታዊ መዋቅር የግብጽ ሙስሊም ሊበራሎችን፣የግብጽ ሴኩላሮችንና የግብጽ ካፕቲክ ክርስቲያኖችን አዋህዶ የግብጹ የጸደይ አብዮት እንዲከሰት አልጀዚራ ታላቅ ሚና ተጫዉቷል።ሱፍና ከረባት የገደገደዉ የሁስኒ ሙባረክ ወታደራዊ አገዛዝ በጃንዋሪ 25/2011 ሲወድቅ በለዉጡ ላይ የቀጠር አሻራ የለበትም ለማለት አይቻልም።

 የምእራቡ አለም ምጸታዊ ዲሞክራሲ

ከቆዳዋ ስፋት በላይ የተፈጥሮ ሐብትን ከመሬት በታች ያካበተቸዉ ቀጠር በአልጀዚራ የሚዲያ የማንቂያ ደወል ብቻ ሳይሆን ገንዘቧንም ለግብጹ አብዮት አንቆርቁራበታለች። የግብጹ ወንድማማቾች ከ80 አመታት የማህበራዊ፣የመማርና ማስተተማር፣ የእጅ አዙር ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በሗላ የምእራቡ አለም የሚያቆላምጠዉን ዲሞክራሲ ተገብራለሁ ብሎ በግብጽ ምርጫ ዉስጥ ገባ። በምርጫም አሸንፎ ዶክተር መሐመድ ሙርሲ የተባሉን የሙስሊም ወንድማማቾች ምሁር ያገሪቱ ፕሬዝዳንት አደረገ። ድሮ በቅኝ አገዛዝ አሁን በዲሞክራሲ ሽፋን ሶስተኛው አለም ብለዉ የሚጠሯቸዉን አገራት በከፋፍለህ ግዛዉ የቆለፉት ምእራባዉያን ሒደቱን በጥርጣሬ ተመለከቱት።

ባንድ ወቅት አሸባሪ የሚል መጠሪያ ተደርቦለት የነበረው ሙስሊም ወንድማቾች ስልጣን ላይ መዉጣቱ ለምእራቡ አገራት አልተዋጠላቸዉም። የሙስሊም ወንግማማቾች 80 አመታትን ታግሶ በ20 አመት ሊመጣ የሚችልን ለዉጥ በአንድ አመት ዉስጥ ለማምጣት መሞከሩ አተርፍ ባይ አጉዳይ አደረገዉ።በግብጽ የጦር ሐይል ዉስጥ የሰረጸዉን ሙስና ለማጽዳት ስራዎችን ጀመረ።እስከ ግማሽ የሚደርሰዉ የግብጽ ኢኮኖሚ በጁ የሆነዉ  የግብጽ የጦር ሐይል የሙርሲ አስተዳደር ለመናጥ ጥረቱን ቀጠለ። ፕሬዝዳንት ሙርሲ የታማዦር ሹሙን ፊልድ ማርሻል ጠንጣዊ በጁን 30/2012 ከስልጣን አስወገዱ። ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የስልጣንን እርከንን ተጎናጸፉና የታማዦር ሹም ሆኑ። ይህ ድንገተኛ የለዉጥ ለዉጥ  ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ወደ ተለያዩ  አረብ አገራት አገራት መዝለቁን ቀጠለ።

የሳዑዲ ሺዓዎች በሱኒዉ የአገሪቱ አገዛዝ እንጨቆናለን ለዉጥን እንሻለን ሲሉ ንቅናቄ ጀመሩ። ሳዑዲ ዉስጥ ተደርጎ የማያዉቅ ህዝባዊ ተቃዉሞ ተሰማ። ሺዓዎቹ አደባባይ ወጡ ። አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ሚዲያዎች የሺዓዎቹን ንቅናቄ አጎሉት። ቀስ በቀስ ሳዑዲ የሺዓዎቹን ንቅናቄ መሰባበር ጀመረች። ሼህ ንምር አል ንምር የሚባሉ የንቅናቄዉ መሪ አሰረች።

ቀጠር ቀንዘቧን በግብጽ ላይ ብታንቆረቁርም የሙርሲን መንግስት ለመጣል ሳዑዲና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አደቡ።አብደላህ ቢን አብዱል አዚዝ አል ሱዑድ በሳዑዲ ዙፋን ላይ የተሰየሙ ቢሆኑም የጤና መቃወስ ነበረባቸዉ።ያሁኑ ንጉስ የያነእዉ አልጋ ወራሽ ሰልማን ቢን አብዱል አዚዝ አል ሱዑድ የታማሚ ወንድማቸዉን ቦታ በአደራ ይዘዉ ያስተዳድሩ ነበር። የቀጠሩ መዋእለ ነዋይ ግብጽ ላይ ቢንቆረቆርም ሳዑዲ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በመተባበር የገንዘብ ጎርፍ ግብጽ ላይ ለቀቁ።ዲሞክራሲ በሚባለዉ የምእራቡ አለም እንቁልልጭ ስልጣን የያዙት ፕሬዝዳንት ሙርሲ በጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በጁላይ 3/2013 የመፈንቅለ መንግስት ተደረገባቸዉና ዘብጥያ ወረዱ። ወታደራዊ መለዮአቸዉን በሱፍና በከረባት በቀየሩት ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በሳኡዲ፣በተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ባንዳንድ የምእራብ አገራት ታግዘዉ ዲሞክራሲን አገቱት። የሙስሊም ወንድማቾች ህገ ወጥ ሆነ። መሪዎቹ ታድነዉ መያዝ ጀመሩ። ብዙዎች በጄኔራል አል ሲሲ መንግስት ተገደሉ።ሳዑዲና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በጨዋታው አጥቂ ሆኑና ቀጠር ወደ መከላከል ገባች።

የንምር አልንምር የሞት ቅጣትና ዲፕሎማሲያዊው ጣጣ

ለሳዑዲ ሺዓዎች የመንፈስ አባት በመሆን የለዉጥ ጥሪ ያደርጉ የነበሩት ሼህ ንምር አልንምር  ጃኑዋሪ 2/2016 በሞት ተቀጡ። ጉዳዩ ሺዓ የሆነችዋን ኢራንን በጣም አስቆጣ። ህዝቧ አደባባይ ላይ ወጣ። ቀደም ሲል ከኖቨምበር 4/1979 የአሜሪካ ኤምባሲን ወረዉ 52 ዲፕሎማቶችን ለ444 ቀናት በማገት ልምድ የነበራቸዉ ኢራናዉያን ተመሳሳይ ስምሪትን አደረጉ። ቀደም ሲል ኢራናዉያን አሜሪካን ኤምባሲ በማገታቸዉ አሜሪካ ዉስጥበተፈጠረዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ ሳቢያ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በምርጫ እንዲሸነፉና ሮናልድ ሬገን ስልጣልን ላይእንዲወጡ ያደረጉ መሆናቸዉ በታሪክ መዝግብት ላይ ላይ የሰፈረ ነዉ። ኢራኖቹ ያንን ተሞክሮ በሳዑዲ ላይ ደገሙት።በጃንዋሪ 2/2016 በቴህራኑ ኤምባሲና ቆንስላ ጽፈት ቤት ላይ ጥቃት አደረሱ።የሳዑዲና የኢራን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተቋረጠ። ቀጠር ከኢራን ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተመጣጣኝ (ያል በዛና ያላነሰ) በመሆኑ ለሳዑዲ ስጋት ሆኖባታል። ይህች በሳዑዲ ተክለ ሰዉነት ላይ የእምብርት ያህል ስፋት ያላት ቀጠር፤ የሳዑዲን የበላይነትና ተሰሚነት የምትፈታተን በመሆኗ ሳዑዲ ክንዷን አፈርጥማ በዲፕሎማሲ ቅጣት ልትደቁሳት ፈለገች። ሳዑዲ ባህሬንን፣ግብጽን፣የመንንና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን አስከትላ  በሰማይ፣በምድርና በባህር ያላትን በር በቀጠር ላይ ቆለፈቸዉ። የሳዑዲ እርምጃ ሰብዐዊነት የጎደለዉ ነዉ ተብሎ በሰፊዉ መተቸቱ ቀጥሏል።

ከትራምፕ ጋር በበድዊያን ባህላዊ ዳንስ የተዉረገረጉት የአልሱዑድ ቤተሰቦች ‘ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ዉጪ ታሳድራች’ እስኪያስመስል ድረስ ደንታ ቢስ ሆኑ።ዲፕሎማሲ ሚዛናዊ በሆነ እይታ እንጂ በስሜት መመራት እንደሌለበት የሚገልጹት ሐያሲያን የሳዑዲን ዉሳኔ ኮነኑት። ቱርክና ኢራን የቀጠርን ህዝብ ለመታደግና ለመመገብ ተረባረቡ። ከቱርኩ የጁላይ 16/2016  የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በሗላ ዲፕሎማሲያዊ ማርን እየቆረጡ ያሉት ቱርክና ቀጠር ወታደርዊ ትብብር እንደሚያደርጉ ይፋ አደረጉ።

ሳዑዲ የባህረ ሰላጤዉ ሐያል መንግስት?

ቀደም ሲል አሜሪካና ሌሎች ሐያላን አገራት እየተመለከቱ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በገሃድ እያስተዋለዉ የአረቡ የጸደይ አብዮት ማናማ ባህሬን ደርሶ በመንታ ባህሮች መካከል ያለችዉ ባህሬን  ለዉጥ አፋፍ ላይ ደርሳ ነበር።የጎረቤትን አገር ህዝባዊ ለዉጥን የሰጋቸዉና በአሜሪካን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ቂቅ ያለቸዉ ሳዑዲ አረቢያ የጦር ሐይሏን ወደ ባህሬን ልካ ባህሬንን ወረረች። ሳዑዲ ህዝባዊ አመጹን ከስክሳ  የባህሬኑን ንጉስ አል ኸሊፋ በስልጣን ላይ አቆየች። ይህ ሲክሰት የበራክ ኦባማ አስተዳደር እጁን አጣጥፎ ነበር የተቀመጠዉ።

ልክ እንደ ባህሬን  በቆዳ ስፋት የሳዑዲ እምብርት የምታክለዋን ቀጠር ዉስጥ ችግር እንዳይፈጠር በመስጋት ይመስላል ቱርክ እጇን የዘረጋቸዉ። በተግባር ሳይሆን የኔቶ አባላትን ቁጥር ለመጭመርና አንድ ሙስሊም አገርናን ለማቀላቀል እስኪያስመስል ድረስ ቱርክ የኔቶ አባል ናት።በአነስተኛ ሚና የኔቶ አባል የሆነችዋ ቱርክ የጦር ሐይሏን ወደ ቀጠር ልካ ሳዑዲ አረቢያን ” ለማለት የፈለገች ይመስላል።ሳዑዲ ሁለት ግዜ በቀጠር ዉስጥ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት ያደረገቸዉ ሙከራ በአል ሳኒ ቤተሰብ «እኛም አዉቀናል ጉድጓድ ምሰናል ብልሃት ከሽፏል።

ሳዑዲና ቀጠር ይፎካከራሉ 

በቆዳ ስፋት ሳዑዲ ከቀጠር 186 ግዜ ትበልጣታለች። በቀጠር ዉስጥ60% የአገሪቱ ነዋሪ በመዲናዋ ዶሃ  ዉስጥ ነዉ የሚኖር ሲሆን በሳዑዲ ደግሞ በተለያዩ ከተማማዎች ተበታትኖ ነዉ የሚኖረው። የቀጠር የህዝብ ብዛት 2.5 ሚሊዮን ሲሆን፤ የሳኡዲ ደግሞ 30.8 ሚሊዮን ነው። በነዳጅ ዘይትና በተፈጥሮ ሐብት የምትምነሸነሸዋ ቀጠር የዜጎቿ አማካይ የገቢ መጥን 13 622 ዶላር በወር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ ። የሳኡዲ ዜጎች አማካይ የገቢ መጠን 4266 ዶላር በወር አካባቢ መሆኑን ተመሳሳይ መረጃዎች ያሳያሉ።

የቀጠርና ሳዑዲ በዲፕሎማሲ መናቆር ከጀመረ ቆይቷል። እ ኤ አ በ1995 የባህረ ሰላጤዉ አገራት መሪነትን ሳዑዲ አረቢያ ስትወስድ ቀጠሮች ተቃዉሞ አሰምተዋል። ስብሰባን ረግጠዉ በመዉጣታቸዉ የአልሱዑድ በተሰቦች ጥርሳቸዉን ነክሰዋል። ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ሳዑዲ፣ባህሬንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እ.ኤ.አ በ2014 ዲፕሎማሲያኢ ግንኙነታቸዉን ማቋረጣቸዉ የሚታወስ  ሲሆን ግንኙነቱን ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ ዘጠኝ ወር እንደፈጀባቸዉ ይታወሳል።

ቀጠር አልጀዚራን በመክፈት ተሰሚነቷን አልቃለች። ሳዑዲ አረቢያ የአልጅዚራን መስፋፋት ለመግታት አል አረቢያ የሚባል ሚዲያ ብትከፍትም አልጀዚራን መብለጥ አልቻለችም። ሳዑዲ ወታደራዊ አቅሟን ለማጎልበት ገንዘቧን ከመጠን በላይ ታፈሳለች። ግሎባል ፋየር ፓወር (www.globalfirepower.com) የተባለዉ ተቋም የሳዑዲን ወታደራዊ አቅም ከ128 አገራት መካከል ከአለም 24ኛ አርጎ ሲያስቀምጠዉ ትንሿን  ቀጠር 90ኛ  አድርጎ አስቀምጦታል። በወታደራዊ አቅሟ ከአለም 8ኛ የሆነቸዉ ቱርክ ለቀጠር በወታደራዊ ሀይል ሞግዚት ለመሆን ወደ መድረኩ ብቅ ብላለች። በተመሳሳይ መልኩ በወታደራዊ ሐይሏ ከአለም አንደኛ የሆነችዉ አሜሪካ 11ሺ ወታደሮቿን ቀጠር ዉስጥ ማስፈሯ ይታወቃል። ከቀጠር መዲና ዶሃ 20 ማይል ርቀት ላይ የሚገኘዉ ቀጠር የገነባቸዉ አል ኡዴይድ የተሰኘዉ ዘመናዊው  የአየር ሐይል አሜሪካ በመካከለኛዉ ምስራቅና በደቡብ ምስራቅ ኤስያ ሽብር ፈጠራን መዋጋት በሚል ስም ለምታደርገዉ የጦር ቅኝት ማእከላዊ የሆነ ወሳኝ ተቋም ነዉ።ይህን የመሰለ የአሜሪካ ጥቅም ባለበት ቦታ ሳዑዲ አረቢያ ቀደም ሲል የባህሬንን ድንበር ጥሳ እንደገባቸዉ ሁሉ ወደ ቀጠር የሚያስገባት ምክንያት የለም።በአገራቱ ድንበር አካባቢ የሚኖረዉን የበደዉያን (ዘላኖች) ግጭት መሰረት አርጋ ቀጠርን ለመዉረር ሳዑዲ ብትሞክር የአሜሪካንን ጥቅም የሚነካ በመሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ቁርሾ ለሳዑዲ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ አማራጭ ነበር።

ሐማስና ቀጠር

ቀጠር የፍልስጤምን ነጻነት ትደግፋለች። ይህ በአረቡና በሙስሊሙ አለም ጎዳኖች ላይ አድናቆትን አትርፎላታል። በምእራብ አገራት አሸባሪ የተባለዉን የጋዛ ሰርጡን ሐማስ ቀጠር መደገፏ እራሷም የማትክደዉ የአደባባይ ምስጢር ነዉ። ሳዑዲ በበኩሏ ፍልስጤማዉያን ጥቃት ሲደርስባቸዉ የገንዘብ ድጎማ ታደርጋለች። ሳዑዲ እስራኤል በሐይል የያዘቻቸዉን የፍልስጤም ይዞታዎች አስመልክቶ በእስራኤል ላይ የምታቀርበዉ ትችትና ዲፕሎማሲያዊ ጫና የተላዘበ ነው ወይም ማድረግ ከሚገባት በታች ነዉ የሚል ወቀሳ ይቀርብባታል። ትንሿ ቀጠር አቅሟ ከሚፈቅደዉ በላይ ተለጥጣና ሁሉም ቦታ ደርሳ «አለሁ አለሁ» ማለቷና ተጽእኖ ፈጥራ ተሞጋሽ መሆኗ ለሳዑዲ ስነ-ልቦናዊ ቅናትን ይፈጥራል ።

ሳዑዲ በሐማኖት አስተማሪዎች በኩል ወደ አረቡ አለምና ወደ ሙስሊሙ አለም ልታዘልቀዉ የምትሻዉ የመሐመድ ቢን አብድል ወሃብ አስተምሮት በቀጠር በሚደገፉት የሙስሊም ወንድማቾች (ኢኽዋነል ሙስሊሚን) ይመከታል።ሳዑዲ በእንግሊዞች ድጋፍ ከተቋቋመች በሗላ ለግማሽ ምእተ አመት የዘረጋቸዉ ሐይማኖታዊ አስተምሮ የአልሱዑድ ቤተሰብ ምንጭ ከሆነዉ፣ 28% የሳዑዲ ህዝብ ከሚኖርበት የነጅድ ግዛት ጥንታዊ የበደዉያን (የገጠር ሰዎች) ጋር የተቆራኘ ነዉ። የሳዑዲ ጥብቅ የበደዉያን ባህል የሙስሊሙ አለም ካለበት ነባራዊ ሁናቴ ጋር አብሮ መጓዝ አልቻለም። በሙስሊሙ አለም ያሉ ምእምናንን ከሳዑዲ አሃዳዊ አምልኮ አስተምሮት (ተዉሒድ) ዉስጥ የበደዉያንን ባህል ነጥለዉ በማዉጣት ነባር የሚሉትን መመሪያና ደንቦች ተግባሪ እየሆኑ ነዉ።ለምሳሌ፦ሳዑዲ ዉስጥ ሴቶች መኪና አይነዱም።ቀጠር ዉስጥም ሆነ በሌሎች ሙስሊም አገራት (ጣሊባን በሚቆጣጠራቸዉ የአፍጋኒስታን ይዞታዎች ካልሆነ በስተቀር) የሴቶች መኪና መንዳት ችግር አይደለም።

የትራምፕ ጉዞንና ዉጤቱ

ሳዑዲ  አረቢያ ባላት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር ሳቢያ የኦባማ አስተዳደር ትፈልግ የነበረዉን የመሳሪያ ግዢ እንኪ ብሎ አልዘረገፈላትም። ኦባማ ሳዑዲ አረቢያን በተደጋጋሚ ቢጎበኙም ላገራቸዉ ወፈር ያለ ገንዘብን የሚያስገኝ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት አላደረጉም። በኢራን እየተደገፉ በየመን በኩል ሳዑዲ አረቢያ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙትን የሁቲ የሺአ አማጽያንን ለማጥቃት ሳዑዲ አረቢያ ከመጠን ያለፈ እርምጅን በመዉስድ በንጽሗን ላይ ከፍተኛ ጥቃት ታደሳለች ሲሉ አለምቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ይከሳሉ።

አቡ ኢቫንካ አል አሜሪኪ፦ (የትምፕ የአረቡ አለም የቁልምጫ ስም ነዉ) ሙስሊሞች አሜሪካ እንዳይገቡ እንዲታገድ ለማድረግ ጥረዋል።በጸረ ሙስሊም የምርጫ ዘመቻና ቅስቀሳ ድጋፍን ሰብስበዋል።ኢስላም ይጠላናል ሲሉ ተዛልፈዋል። የሴፕተምበር 11/2001 የኒዮርክ የሽብር ጥቃትን ተከትሎ ሙስሊሞች ከኒዉ ዮርክ አቅራቢያ ከሆነችዉ የኒዉጀርሲ ግዛት ዉስጥ በደስታ ሲጨፍሩ አየሁ ብለዉ ዋሽተዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቃላቸዉ ሳይጸኑ የመጀመሪያ የዉጭ ዲፕሎማሲያዊ ጉዞአቸዉን  ወደ ሙስሊም አገር ነበር ያደረጉት።

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ ነበር በሜይ 20/2017 ሪያድ የገቡት አቡ ኢቫንካ አል አሜሪኪ (ትራምፕ) ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።የሪያድ ጎዳኖች በሁለቱ አገራት ሰንደቅ አላማዎችና  በመሪዎቻቸዉ ፎቶግራፎች ደምቀዉ ነበር።ተለዋዋጩ ትራምፕ የሳዑዲ የበደዉያንን ባህላዊ ዳንስ ከንጉስ ሰልማንና ከሌሎች ደናሾች ጋር ጋር በመሆን ደነሱ። ለሙስሊም አገራት ንግግር አደረጉ። ኢስላም ይጠላናል እንዳላሉት ሁላ ሐሳባቸዉን ቀይረዉ ኢስላምን አቆላመጡ። በምላሹም የ400 መቶ ቢሊየን ዶላር የቢዝነስ ዉልን አገኙ።

ሳዑዲ ሽብር ፈጠራን እዋጋለሁ ብላ 34 የሙስሊም አገራትን አሰባስባለች። የኔቶን ቃልኪዳን አገራት የመሰለ የሙስሊም አገራትን ህብረ ጦር ጦር ለማቋቋም ሳዑዲ ደፋ ቀና እያለች ነዉ።ባንጻሩ  ትራምፕን በትከሽዉ ተሸክሞ ለስልጣን ያበቃዉ የቀኝ ክንፍ የወግ አጥባቂያን የፖለቲካ ስብስብ በእጅጉ ጸረ ሳዑዲና (ጸረ ወሃብይ) አቋም  ያለዉ ቢሆንም ጣፋጭ የቢዝነስ ዉል ከሳዑዲ በመምጣቱ ያለማጉረምረም ዝም ጭጭ ያለ ይመስላል። የዚሁ የ34 የሙስሊም አገራት ህብረጦር አባል የሆነችዋ ቀጠር በትራምፓዉያንና በአልሱዑድ ቤተሰቦች  የሪያዱ ፈንጠዚያ ላይ ተገኝታለች። የቀጠሩ ኢሚር ሽህ ተሚም ቢን-አል-ሳኒ ሳኡዲ አረቢያ ተጉዘዉ ከትራምፕ ሲገናኙ ነገሮች ሰላም ነበሩ። ከትራምፕ የሳዑዲ ጉዞ በሗላ ምን ተፈጠረ? ሽብር ፈጠራን ለመዋጋት ቀጠር የአሜሪካ አጋር ናት። ቀጠር የ34 የሙስሊም አገራት ህብረ ጦር አባል ናት። ቀጠር ሽብር ፈጠራን መዋጋት በሚል ሰበብ 11ሺ የአሜርካ ወታደር የሰፈረባትና የአየር ሐይል ቤዝ ሰርታ ለአሜሪካ የሰጠች ናት። ግን በድንገት ሽብር ፈጠራን ትረዳለች ተብሎ ዲፕሎማሲ ግንኙነቷ  ከሳዑዲና ከሌሎች አገራት ጋር በጁን 5/2017 መቋረጡ ከአቡ ኢቫንካ አል አሜሪኪ ጋር የሚያገናኘዉ ነገር እንዳለ የሚተነብዩ ብዙ ናቸዉ።

የ400 ቢሊየን ዶላር የቢዝነስ ዉልን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያደረጉት ትራምፕ ሳዑዲን በመደገፍ ተግባር ላይ የተሰማሩ ይመስላል።የሳዑዲና የቀጠር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጥ ተከትሎ  ለሳዑዲ ምስለኔ የሆኑ እስኪያስመስልባቸዉ ድረስ ትራምፕ ዉስኔዉን በትዊተር ገጻቸዉ እያዳነቁ “ቀጠር ሽበር ፈጣሪዎችን መርዳቷን ማቆም አለበባት!” በማለት ሐሳባቸዉን ገልጸዋል። ከእርሳቸዉ ሐሳብ በሚጻረር መልኩ የአሜሪካዉ የመከላከያ ተቋም ፔንታጎን ቀጠርን “ሸጋ አጋር” ሲል በጁን 6/2017 አዳንቋል።ትራምፕ ቀጠርን ባብጠለጠሉ ሳምንት የመከላከያ ሚኒስቴራቸዉ የ12 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ከቀጠር ጋር  ተስማምተዋል። ጉዳዩ ዲፕሎማሲያዊ ስላቅ እስኪባል ድረስ ብዝዎችን አስገርሟል። ሳዑዲ የሚተገበር የ110 ቢሊዮን ዶላር የመሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ዉል ስትፈጽም ቀጥር ደግሞ ባቋራጭ ዳጋጎስ ያለ ገንዘብ ይዛ ወደ ዋሽንግተን አቅንታ መሳሪያ ለመግዛት ተስማምታለች።

ሐምሳ ዘጠኝ አሸባሪዎች?

ሳዑዲ አረቢያ  ቀጠር ዉስጥ ያሉ 59 ሰዎችን አሸባሪ ናቸዉ ስትል ፈረጀች።አሸባሪ የሚለዉ ስያሜ ለታዋቂዉ የኢስላማዊ መምህርና ሊቅ ዶክተር ዩስፍ አልቀርዳዊ አልቀረላቸዉም።ይህ ‘የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳዉ ሰንበሌጥ’ የሆነዉ የሳዑዲ ዉስኔ መሰረተቢስ ነዉ የሚል ወቀሳ በአረቡና በሙስሊሙ አለም ዉስጥ በስፋት ቀርቦበታል። ሳዑዲ በዚህም ሳትገታ የዶክተር ዩሱፍ አል ቀርዳዊ መጽሃፍትና የምርርምር ስራዎች ከሁለተኛ ደረጃ ትምርት ቤትና ከዩንቨርስቲዎቿ ይወጣ ዘንድ አዛለች።  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሳዑዲ ፍረጃ እንደማይገደብ በማስረዳት ተቃዉሞዉን አሰምቷል። ቀጠር በሶሪያ፣በሶማሊያና በፍልስጤም ዉስጥ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የምታደርገዉን ሰብዓዊ እርዳታን የ.ተ.መ.ድ ማዳነቁ በጁን 9/2017 በተለያዩ የመገናኛ ብዙሗን ተዘግቧል።

ቀጠር ታስራለች ሳዑዲ ቀረርቶ ታሰማለች

ሳዑዲ አረቢያ፣የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣የምስራቃዊ ሊቢያ መንግስት፣ሞሪታኒያ፣ሴኔጋልና ማልዳይቭስ ከቀጠር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸዉን አቋርጠዋል። ዮርዳኖስና ጅቡቲ ከቀጠር ጋር ያለዉን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቀንሰዋል።የቀጠር ህዝብ ህልዉና ከሳዑዲ ጋር የተያየዘ ቢሆንም ሳዑዲ ድንበሯን ያለ ርህራሄ ጥርቅም አርጋ ዘግታለች። የባህር በሯንና የአየር ቀጣናዋን ሳዑዲ በቀጠር ላይ ቆልፋለች።ሳዑዲና ሌሎች ያደሙ አገራት በተመሳሳይ መልኩ በቀጠር ላይ የባህርና ያየር መስመራቸዉን ከርችመዋል። ጉዳዩ አለም አቀፍ ህግን የጣሰነዉ!” በማለት የቀጠር መንግስት እሮሮ እያሰማ ነዉ። የ2022 አለም ኳስ ዋንጫ ዉድድር ለማዘጋጀት እያዳከረች ያለቸዉ ቀጠር ግማሽ ሚሊዮን ዜጎቿንና 2ሚሊዮን ከዉጭ የመጡ ሰራተኞችን ለመመገብ የመሬቱ ግንኙነት ከሳዑዲ የጋር በመቋረጡ የነፍስ ያለህ!” ስትል ስንቅን ይዘዉ በአዉሮፕላን የደረሱላት ቱርክና ኢራን ናቸዉ።ተሰሚነቷን በመላዉ አለም በሐይኖት፣በዲፕሎማሲ፣በእርዳታና የምእራቡን ሐይልን በመጠቀም ለማዝለግ የምይፈልገዋ ሳዑዲ አረቢያ የወሰደችዉ እርምጃ ከመጠን ያለፈ ነዉ የሚል ተቃዉሞ እየቀረበባት ነው። ፍትጫው ቀጥሏል። ዉጤት የለሹ መፋተግ የሚያመጥዉ ወዴት እንደሚደርስ በሒደት የሚታይ ይሆናል።

የህሊና ጥያቄ

አለማችን ላይ ያሉት ሙስሊሞች  የህሊና ጥያቄን እያነሱ “እስከዛሬ ድረስ ስንናቆር የኖርነዉ በሳዑዲ ምክንያት ነዉ ወይስ…በቀጠር?” ጥያቄዉ ይቀጥላል… “አብድልወሃብና አል ሱዑድ ተጣመሩና በፖለቲካና በሐይማኖት የሱዑድ ግዛትን መሰረቱና ድንበር ዘለል መስፋፋትን እያደረጉ ነው። አብድልወሃብ የተነሱበት አሃዳዊ አስተምሮት ድሮም አለ፣ አሁንም ሆነ ወደፊት ይኖራል…ግን ዉሉ ያልታወቅ የሳዑዲ አረቢያ ንጉሳዉያን ቤተሰቦች የአመለካከት ሸቀጥ ማራገፊያ ለምን እንሆናለን?” ጥያቄዉ ይቀጥላል…”ለጦር መሳሪያ 110 ቢሊዮን ዶላር ሳዑዲዎች ከሚያወጡ ለምን ሰላማቸዉንና ሉዐላዊነታቸዉን በበጎ አድራጎት ማስጠበቅ አይችሉምን? በርግጥ ሙስሊም ወገኖቻቸዉ በየን፣በሶማሊያና በሌሎችም አገራት በራብ ሲንገላቱ ለአቡ ኢቫንካ አል-አሜሪኪ እጅ መንሻ 400 ቢሊየን ዶላር ማዉጣት ነበረባቸዉን?” በሙስሊም አገራት ጎዳኖች የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸዉ። ደጋፊ አገራትን በገንዘብ ለመግዛት የምትሞክረዋ ሳዑዲ አረቢያ ለሶማሊያ 80 ሚሊዮን ዶላር እከፍልሻለሁ ከጎኔ ሁኚ ብትልም፤ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ-ፈርማጆ ዲፕሎማሲያዊ ጉቦውን እምቢኝ ብለዉ ከዉዝግቡ ገለልተኛ ሆነዋል። የሳዑዲና የቀጠር መናቆር የኢትዮጵያ አጎራባች አገራትን አካሏል። ሱዳን፣ኤርትራ፣ጅቡቲና ሶማሊያ ገብተዉበታል። ኢትዮጵያንም የሚመለከት በመሆኑ ልብ ያለዉ ልብ ይበል ማለቱን መረጥን።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *