charityፈረንጆች “Charity begins at home.” ይላሉ፡፡ እንዲህ ሲሉ መልካምነት ወይም በጎነት ከቤት እንደሚጀምር ለመግለጽ ነው፡፡ እኔም ከዚህ አባባል ኮርጄ “መንግሥትነት ከቤት ይጀምራል” አልሁ፡፡ በመሠረቱ ከቤት የማይጀምር ነገር የለም፡፡ ከቤት የሚጀምር ነገር በጎም ሆነ ክፉ በውጭም ይታያል፡፡ ከቤት ያልጀመረ ከውጭ አይመጣም፡፡ ስለዚህ የብዙ ነገሮች መሠረት ቤት ነው፡፡ የሰው ዕድገት የሚጀምረው ከቤት በመሆኑ ቤታችን በኛነታችን ላይ ያለው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ “እናቷን አይተህ ልጅቷን አግባ” መባሉም ለዚህ ነው፡፡

እናትና አባት መልካም ሰዎች ከሆኑ በአብዛኛው ልጆችና የልጅ ልጆችም መልካም የመሆናቸው ዕድል የሰፋ ነው፡፡ በተቃራኒው እናት ክፉ ብትሆን ሴት ልጆቿ የእርሷን መጥፎ አርአያ ተከትለው ክፉ የመሆን መጥፎ ዕድል ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ለአብነት ባሏን የምታታልል ሚስት ማታለል የፅድቅ ሥራ እንደሆነ ያህል የምታምን ልጃገረድ ነው ለማኅበረሰቧ የምታበረክተው፡፡ ባል ሰካራምና አምሽቶ የሚገባ በድራቦሹም በሥራ ስትደክም የዋለችዋን ባለቤቱን የሚያንገላታና በስካር መንፈስ በመነዳት ቤተሰቡን የሚያምስ ከሆነ ወንዶች ልጆቹም ሲያድጉ የርሱን ባሕርይ በመያዝ ቤታቸውን የሚበጠብጡ ይሆናሉ፤  ዕድል ከዚህ ካልሰወራቸው፡፡

መግቢያየ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ለአንድ ሀገር አመራርም እንበለው አስተዳደር ከጥሩ ቤተሰብ መውጣት ወሳኝ ነው፡፡ ቀደም ካለ ጊዜ ጀምሮ የሀገራችንን የአስተዳደር ልጓም የሚይዙ ዜጎቻችንን አስተዳደግና የልጅነት ባሕርይ ብናጤን ምናልባትም ብዙዎቹ ለተቆናጠጡት ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት የሚያበቃ የኋላ ታሪክ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ወደ እገሌና እገሌ አልገባም፡፡

ይህችን መጣጥፍ ለመክተብ ያነሳሳኝ አንድ አሳዛኝ ታሪክ ሰምቼ ነው፡፡ እባካችሁን ወደየአእምሮኣችን እንመለስ፡፡ የኛን የተጣመመ ባሕርይ ከማቃናትና ከመግራት በተጓዳኝ የልጆቻችንን የወደፊት ሕይወት የተበላሸ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥረት እናድርግ፡፡ የሰማሁት ነገር በጣም አደገኛና ሀገርን የሚያጠፋ ነው፡፡ ከዚህ ጠማማ መንገድ በአፋጣኝ  ካልተመለስን በየጓዳችን የተጠመደው ፍንጅ ጊዜ እየጠበቀ የሚፈነዳና ማንንም ከማንም ለይቶ የማይምር ነው፡፡ ሕወሓት በከፈተልን የጥፋት ጎዳና እየተመምን ዘር እንኳ እንዳይተርፍ በጣም አደገኛ አቅጣጫ እየተከተልን ነው፡፡ በዛሬ ውስጥ ሆነን በየቤታችን የምነሠራው ነገር ነገ በግልጽ የሀገራችንን መፃዒ ዕድል እንደሚወስን መጠራጠር የለብንም፡፡ ስለዚህ ከዚህ በታች ከምነግራችሁ አሳዛኝ ተሞክሮ ብዙ መማር እንደሚገባን ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡

አንድ የወያኔ ሚኒስትር ነው፡፡ ለሰዎች ደኅንነት ስል የማንንም ስም አልጠቅስም፡፡ ሚኒስትሩ ዘመድ ይሞትበታል፡፡ ከረምረም ብሎ ጓደኞቹ ሊጠይቁት ሰብሰብ ብለው ወደቤቱ ይሄዳሉ፡፡ ልቅሶው ስለሰነበተ ቴሌቪዥን ተከፍቶ እንግዶቹም ቤተሰቡም ይመለከቱ ነበር፡፡ በዘመናዊ ቤተሰብ ውስጥ እንደዱሮው የመረጃ ምንጭን ለረጂም ጊዜ መዝጋት ተገቢ አለመሆኑ መረሳት እንደሌለበትና ሚኒስትሩም ያደረገው ከዚህ አኳያ መጥፎ እንዳልሆነ ይታሰብልኝና በዚህ የቴሌቪዥን ሥርጭት ሳቢያ የተከሰተው ነገር ግና ሁላችንንም የሚያስተምር፣ ከተኛንበትም የሚያነቃ አቢይ ቁም ነገር ነው፡፡

ሚኒስትሩና ጓደኞቹ የደራ ጨዋታ ይዘዋል፡፡ በነገራችን ላይ በወያኔው የዘር ፖለቲካ አገላለጽ መሠረት ሰዎቹ ሳይወዱ በግዳቸውና ባጋጣሚ ከሦስቱም “በጥባጭ” ነገዶች የሚወለዱ ናቸው፡፡ ሚኒስትር ተብዬው ደግሞ ኦሮሞ ነው፡፡ ‹ተብዬው› ማለቴ በዚህ ሥርዓት አእምሯዊ የጤንነት ደረጃውንና ትምህርታዊ የብቃት መሥፈርቱን አሟልቶ የሚሾም ሰው እንደሌለ በሚገባ ስለምረዳ ነው፡፡ በስህተት ተሹመህ “ሰው” መሆንህ ቢደረስበት ተዋርደህና አለሥራህ ሥራና አለስምህ ስም ወጥቶልህ በአናቱም ላይ “ሙሰኛ” የምትለዋን የነሱን የሠርክ ስም ተሸልመህ ወደ ዘብጥያ ልትወርድ ትችላለህ፡፡ ወያኔ ጋ ቀልድ የለም፡፡ ጤናማ አስተሳሰብና አመለካከት እንዲሁም ብሔራዊ የሀገር ፍቅር ስሜት ካለህ በምንም ዓይነት የኃላፊነት ቦታ ላይ አትሾምም፤ ሰው መሆንህ እስኪያጠራጥር ድረስ እጅግ የዘቀጠ ስብዕና እንዳለህ በአደባባይ ካልተመሰከረልህ የወያኔን ሹመት አታገኛትም (ሹመት ከፈለግህ ማሟላት ስለሚገባህ መሥፈርት ፍንጭ ልስጥህ – ሰካራምነት፣ ውሸታምነት፣ ዘሟችነት፣ ሙሰኝነት፣ ጎጠኝነት፣ አጨብጫቢነት፣ አላዋቂነት….)፡፡ ባለሥልጣናቱ “ሰው” መሆን ከፈለጉ በድብቅ ነው ሰው መሆን የሚችሉት፡፡ ዐዋቂና ምሁር መሆን ካማራቸው እነዚህንም መሆን የሚችሉት በሥውር ነው፤ ከተነቃባቸው ይባረራሉ፡፡ አሃ፣ ሰው ከሆኑማ “እንዴት”ንና “ለምን”ን ዐወቁ ማለት እኮ ነው፡፡ “ለምን?” ብለህ መጠየቅ ጀመርክ ማለት ደግሞ ጤናማ ሰው መሆን ጀመርክ ማለት ነውና ወያኔ አለቀለት ማለት ነው፡፡ ወያኔ ጋ ለመኖር ጭንቅላትህን ቦርጭ ካለህ እዚያ ውስጥ ወትፈህ አለበለዚያም ዘመድ ካለህ በአደራ መልክ አስቀምጠህ ባዶ ቀፎህን ነው መግባት ያለብህና የምትችለውም፡፡ በዚህ ዘመን ለትልቅ ሥልጣን የሚታጩትና የሚሾሙትም ፀረ-አማራና ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ በመብራት እየተፈለጉና ሥይጠናም(ሥልጠና) እየተሰጣቸው ነው፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ደቡቦች በከፍተኛ ደረጃና በብዛት እየተሾሙ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አማራ ጠሉ ኃይለማርያም በቀደደው የአሻንጉሊትነት የሥራ መደብ ደቡባውያኑ አልተቻሉም አሉ፡፡ ኧረ ደቡብ ከተነሳስ አይቀር ብዙ መዘዝ መጥቶብናል እናንተዬ! (በጨለማ ሰውን የሚደፉ ወጣቶች ከደቡብ እየፈለሱ አዲስ አበባን እየሞሉና ዜጎች እንደደሮ በ12 ሰዓት ወደ ቆጣቸው እንዲከቱ በመገደድ ላይ ናቸው ይባላል፡፡ በቆንጨራና በኮብል ስቶን ማጅር ማጅሩን እያሉ በተለይ “ንዑስ ከበርቴ”ውን የኔ ቢጤ  ድሃ እየፈጁት እንደሆነ በስፋት ይነገራል፤ ወይ ዕዳችን! “አንበሣን ፈርቼ ዛፍ ላይ ብወጣ ነብር ጠበቀኝ” አሉ? የዘንድሮ ዘንድሮስ ከምንጊዜውም ዘንድሮዎች ለዬት አለች፡፡) ስንክሳሩ ብዙ ነው ወንድሜ፡፡….

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

የዚያን ጣጠኛ ቲቪ ነገር ቀጠልኩ፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ ይተላለፍ የነበረው ዝግጅት ተጠናቅቆ የአማርኛው ሊቀጥል ሲል ይሉኝታንና መደባበቅን የማያውቀው የሚኒስትሩ ትንሽዬ ልጅ “እነዚህ ጭራቆች ደግሞ መጡ!” ይልና ቴሌቪዥኑን ጥርቅም ያደርገዋል፡፡ ሚኒስትሩም ጓደኞቹም ባለቤቱም ክው አሉ፡፡ አያ ሚኒስትር አፉ እየተሳሰረ የሞት ሞቱን “ሕጻን እኮ ነው፤ ም….ምን ያ’ቃል? ብላችሁ ነው፡፡” ይላል፡፡ የኦሮሞም የአማራም ደም የነበረው አንዱ የተማረ ጓደኛው “አይ፣ የእናንተን ይዞ እንጂ ይህ ሕጻን ከራሱ ምን አለውና እንዲህ ይላል?” በማለት በአማርኛ ይናገራል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በእኩልነትና በፍትህ ሊያስተዳድር በሚኒስትርነት ማዕረግ በወያኔ የተሾመው ሚኒስትር በኦሮምኛ “አንተ! በነዚህ መሃል እንዲህ ትለኛለህ?…” በማለት በትግሬዎችና በአማራዎች ፊት ሊያሳጣው እንደማይገባ በወቀሳ መልክ ጠቆም ያደርገዋል፡፡ ያ ሰው ከልቡ ሰው ነውና ቋንቋ ሳይቀይር (ኮድ ሳይለውጥ) በአማርኛ “አዎ፣ ችግሩ የኛ የአሳዳጊዎች ነው፡፡ ጥላቻን እየጋትን እናሳድጋቸዋለን፤ ሲያድጉም ያን ተግባራዊ እያደረጉ እርስ በርስ ከመጋጨትና ከመነታረክ ውጭ ሌላ የሚጠቅም በጎ ነገር አይሠሩም፡፡…” ይለዋል፡፡ የጨዋታ አጀንዳ ይለወጥና ሰላምም ይወርድና በቤቱ ውስጥ ሕይወት እንደአዲስ ትቀጥላለች፡፡

ቴሌቪዥኑ ግን አልተዘጋም ነበር፡፡ ተራውን ጠብቆ የባሰው መጣ፡፡ አማርኛው አለቀ – (ያው የነበረውም እንደነገሩ ለወጉ ያህል እንጂ አማርኛ እንኳን አሁን አሁን እየሞተች ነው)፡፡ ትግርኛው ሊቀጥል “ጥእና ሃበለይ ዝተፈተውኩም ተኣዘብትና…” የሚል አስገምጋሚ የትግርኛ ጋዜጠኛ የቲቪው መስኮት ላይ ድቅን ይላል፡፡ ያ ሕጻን ያ ትግራዋይ ጋዜጠኛ የጀመረውን የእንኳን ዋላችሁ/አመሻችሁ ዐረፍተ ነገር እንኳን እስኪጨረስ አልጠበቀውም፡፡ “ምናባታቸው እነዚህ ዐውሬዎች!” ይልና አሁንም ድርግም ያደርገዋል፡፡ ሚኒስትሩና ባለቤቱ የሚገቡበትን አጡ፡፡ በየቤቱ ይህን መሰል ጉድ ሞልቷል፡፡ ገመና ሸፋኙ ቤት ይሸፍነዋል እንጂ፡፡

ኢትዮጵያ ማለት እንዲህ ሆነች፡፡ ከዚህ ገፋ አድርጌ ብናገር ደስ ባለኝ ፡፡ ነገር ግን ሰዎችን ላላስፈላጊ መስዋዕትነት መዳረግ ነው፡፡

ምን አይታችሁ – ወያኔዎች የዘሩትን ገና በብዛትና በዓይነት ያጭዳሉ፡፡ የዘራውን የማያጭድ ገበሬ የለምና፡፡ ማን ተጠቃሚ ማን ተጎጂ እንደሚሆን የወደፊቱ ታሪካችን በግልጽ ይመሰክረዋል፡፡ ወያኔዎችን ስታዘባቸው ባሏን የጎዳች መስሏት የገዛ ገላዋን በጋሬጣ የተለተለችውን ጅላጅል ሚስት ይመስሉኛል፡፡ የዘሩት የጥላቻ መርዝ ወደነሱ እንደማይዞር ያሰቡት አይመስሉም፡፡ በአማራ ላይ ያላቸው ጭፍን ጥላቻ እነሱንም ሀገሪቱንም ወደማይወጡት አዘቅት እየከተታቸው ነው፡፡ የሚሾሙት ሆድ አደር ሁሉ አማራንና ኢትዮጵያን የሚጠላ ይምሰላቸው እንጂ እነሱን እንደሚወድና እንደማይወድ እንኳን ለማወቅ ግድ ያላቸው አይመስሉም፡፡ እናም ለአማራ የጣዱት የወጥ መቀቀያ ጎላ ውስጥ እነሱም ገብተው ሊንፈቀፈቁ  እንደሚችሉ አልተገለጠላቸውም – እንደወያኔ ልበ ሥውርና አእምሮ-ድፍን መቼም የትም የለም –  በዘወትር ጸሎታችን “እጅግ ቸርና ሩህሩህ አምላክ” ብለን የምንጠራው እግዚአብሔር እነዚህን ወያኔዎች እንዲህ የጨከነባቸውና ባልጩት ራስ አድርጎ የፈጠራቸው ለምን ዓላማና በመጨረሻው ምን ሊያደርጋቸው ዐቅዶ እንደሆነ ሳስበው ሁል ጊዜም ይገርመኛል፡፡ ሌላውን ሁሉ ተውት፡- ከትግራይ ሕዝብ በግርድፍ ግምት ከ60 እስከ 70 በመቶው በአሁኑ ሰዓት የሚኖረው የት ነው? ይህ ሕዝብ ደላውም አልደላውም በስማቸው አተረፍም አላተረፈም እየኖረ ያለው ግን ከቀሪ ወንድምና እህቶቹ  ጋር ከትግራይ ክልል ውጭ ነው – ውጭ ሀገራትን ጨምሮ፡፡ ታዲያ ወያኔዎች ለሌላዋ ኢትዮጵያ ከሚያጠምዱት ቦምብና ፈንጅ ይህን ብዙ ትግራዋይ እንዴት ሊያድኑት ይችላሉ? እነዚህ ሰዎች ሁል ጊዜ የሚያቅዱት ዕቅድ “ሀ”ን ብቻ እንጂ ዕቅድ “ለ” የሚባል ከችግር መውጫ ብልኃት ኖሯቸው የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ያው “ደፋርና ጭስ… “ እንደሚባለው በብላኔ የሚገቡበትን ጣጣ ሁሉ በብላኔ ይወጡታል፤ ይህ የዕውር ድምብር አካሄዳቸው እስካሁን ብዙም ያከሰራቸው አይመስልም፤ እንጂ ለሠርገኛ ጤፍ የተዘጋጀ ብረት ምጣድ ቀይና ነጭ ጤፍን መርጦ ሳይቆላቸው እንደሚቀር ለሕወሓት ብቻ እንዴት ተገለጸለት? ሁል ጊዜ የሚገርመኝ ጥያቄ ስለሆነብኝ ነው አሁን እዚህ አለቦታው የደነቀርኩባችሁ፡፡ ወደጀመርኩት –  እያንዳዱ የአሁን ዘመን ባለሥልጣን – አማራም ቢሆን – ፀረ-አማራና ፀረ-ኢትዮጵያ መሆን እንዳለበት የሕወሓት ፅኑ እምነት ነው፤ መለስም “ሥልጣን የምንሰጠው በታማኝነት እንጂ በትምህርት ብቃትና በችሎታ አይደለም” ብሏል በግልጽ፡፡ ስለዚህም ነው አለምነው መኮንንን የመሰለ የወያኔ ዕንባ ጠባቂ ባሕር ዳር ላይ አማሮችን ጠፍንጎ ለማሰር በወያኔ ተሹሞ የምናየው፡፡ ስለዚህም ነው ገነት ዘውዴን የመሰለች ከወያኔ በልጣ ስለወያኔ የምትብከነከንና የምትጨነቅ ሲሞቱባትም ከሚስቶቻቸው በበለጠ ሙሾ የምታወርድ የአማራ ዮዲት ጉዲት “ወላድ አትይሽ”ን ልንመለከት የቻልነው፡፡ ብዙ ምሣሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አትታዛቡኝና ይሄ ነገር የድግምት ይመስለኛል፡፡ የመረገምም ጣጣ ሳይኖርበት አይቀርምም እላለሁ፡፡ አንድ ለሂትለር ያደረ ይሁዲ ሌላ ምሥኪን ይሁዲን ይዞ በኦሽትዊዝ የጋዝ ቼምበር አስገብቶ በይሁዲነቱ ምክንያት ሲያቀልጠው ይታያችሁ – ከዚህ በላይ ዕንቆቅልሽ ደግሞ ሊኖር አይችልም፡፡ በመሠረቱ አማራ ሆኖ ትግሬ መሆን ወይም ትግሬ ሆኖ አማራ መሆን በራሱ ምንም ማለት አይደለም፤ የምርጫ ጉዳይም ነው፡፡ ነገር ግን አልተፈጠርኩበትም ብለህ የካድከው ነገደም ቢሆን የመኖር መብት እንዳለው ማመን ይገባል እንጂ ገና ለገና ለሆድህም ይሁን አንዳች ነገር ተዙሮብህ ክደህ የወጣህበትን ማኅበረሰብ ሊያጠፉት ከተሰለፉ ወገኖች ጋር ተደርበህና ተባበብረህ ለማጥፋት መነሳት በዕብድነት ብቻም አይገለጽም፡፡ ከዕብደትም በላይ ነውና እንዲህ ዓይነት ሰው መመርመር አለበት፡፡ የዲኤንኤው ስብጥር (ኮምፖሲዚሽን) ተመርምሮ መታወቅና ህመሙ እንዳይዛመት ክትባት ሊፈጠርለት ይገባል፡፡  ለወደፊቱ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ምሁራን አንድ በሉን፡፡

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

ለማንኛውም በዚያ ከእህልና ግፋ ቢል ከፊደል ዘር መለየት ያላለፈ ችሎታና ዕውቀት ሊኖረው ከማይጠበቅ ሳይወድ በግዱ ጃዋር ሞሀመድን እንዲሆን ከተፈረደበት ኢትዮጵያዊ ሕጻን ብዙ የምንማረው ነገር አለ፡፡ አባትና እናቱ አጥፍተዋል፡፡ ማንንም ማሳበብ አይችሉም በትልቁ ነው ያጠፉት፡፡ እነሱ ንስሃ ይግቡ፤ ይጸጸቱና ወደደጉ መንገድ ይመለሱ፡፡ ለነሱ ከዚህ በላይ ምክር የለኝም፡፡

ወደኛ ልመለስ፡፡ እኔም ልጆች አሉኝ፡፡ አንቺም ልጆች አሉሽ፡፡ አንተም ልጆች አሉህ፡፡ እናተም ልጆች አሏችሁ፤ ባይኖሯችሁም እንኳን የኛ ልጆች የናንተም ናቸው፡፡ ሀገር የምትገነባው ወይም የምትፈርሰው  ከሕጻናቷ ጀምሮ ነው፡፡ ከታች የጠፋ ከላይ ቢፈልጉት አይገኝም፡፡ እባካችሁን የኛን ስሜት በልጆቻችን ላይ ለመጫን አንሞክር፤ ልጆቻችንን የእምነቶቻችንና የጥላቻ ማቆያ ማኅደሮቻችን ከማድረግ እንቆጠብ፡፡ የራሳቸው ስብዕና እንዲኖራቸው እንጂ የኛ ጥላዎች ወይም ሲዲና ዲቪዲዎቻችን አድርገን አንጠቀምባቸው፡፡ ታሪክ እንሥራ፡፡ ቢያንስ ነገን ለነሱ እንተውላቸው፡፡ የኛን ዘመን አበላሽተን የነሱንም አናበላሽባቸው፡፡ በጥላቻ አናሳድጋቸው፡፡ ፍቅርንና መዋደድን እናሳያቸው፡፡ የኛ ስህተት የኛን ሕይወት አጨለመ፡፡ በዚያም ምክንያት የረባ ሕይወት ሳንኖር እንደአባ መሸ በከንቱ እንዲሁ ጊዜያችን ተቃጠለ፡፡አንድ ጊዜ ተፈጥረን አንድ ጊዜ ብቻ በምንኖርባት ምድር ብዙ ዕድሎችን አበላሸን፡፡  የልጆቻችን ጊዜስ ለምን በከንቱ ይቃጠላል? በዚህ ጉዳይ ላይ በግልጽ እንነጋገር፡፡ በተለይ ሰለጠነ በሚባለው ዓለም ውስጥ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እስካሁን የገነባችሁትን የልዩነት አጥር አሁኑኑ አፈራርሱና ቢያንስ ልጆቻችሁ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖሩባትን የጋራ ሀገር ለመፍጠር ሞክሩ – ሰው እንዴት በቤተ አምልኮትና በጽላት ሳይቀር ይጣላል?(አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ አባ ኪሮስ… እያለ ታቦታትንም በጎሣና በነገድ የሚከፋፍል ምን ዓይነት ትውልድ ላይ ደረስን?)፡፡

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

የሰው ወርቅ አያደምቅም፡፡ ዝንታለሙን በሰው ሀገር መኖርም የሚቻል አይደለም፤ ቢቻልም የማንነት ጥያቄያችንን በአግባና ዘለቄታ ባለው መልክ አይመልስልንም፡፡ በጥቅሉ ሲታይ  አካሄዳችን አያምርምና በአፋጣኝ እንለውጠው፡፡ ከሁሉም የነሣን ሆነን በኋላ ቀርነት አለንጋ ተገሽልጠናል፡፡ ሀገራችንን ከተጠመዱባት ፈንጂዎች ነፃ እናውጣት፡፡ አንዱ ዘዴ ልጆቻችንን በፍቅርና በመተሳሰብ እንዲኖሩ መምከርና በተግባርም ማሣየት ነው፡፡ በየቤታችን ይህን ዘመቻ ብናጧጡፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እናመጣለን፡፡ ወያኔ የዘራውን መርዝ የምናረክስበት በርሱ መንገድ በመጓዝ ሳይሆን በተቃራኒው ፍቅርን በመዝራት ነው፡፡ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አማራ፣… የእግዜር ፍጡራን እንጂ አንዳቸው አንዳቸውን እንደድብኝት ጠፍጥፈው የሠሩዋቸው የሸክላ ውጤቶች አይደሉም፡፡ ያለፈ ችግር መኖሩ ብዙዎችንን ሊያሳምን ይችላል፤ እንኳንስ በማኅበረሰብና በሀገር ግንባታ በቤተሰብ ደረጃ እንኳን ብዙ ችግሮች እየደረሱ በዕርቅና በስምምነት ግን ቤትና ትዳር እየታደሰ ከቀድሞው ወደተሻለ ትልቅ ደረጃ ይደረሳል፡፡ የኛ ባልሆነ ጊዜ በተፈጠሩ ችግሮች የኛ የሆነን ጊዜ በከንቱ ማበላሸትና ማባከን ብልኅነት አይደለም – ሞኝነት እንጂ፡፡ በማንትስ ጊዜ የደነቆረ ማንትስ ይሙት እያለ ይኖራል እንደሚባለው አንድ ወቅት በተፈጸመ ስህተት ዝንታለሙን ማሞስካትና ሕዝብን ሆድ ማስባስ ጤነኛነትን ካለማሳየቱም በላይ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ቅኝታችን ከሰላምና ከዕርቅ ውጭ ሆኖ ባለፈ ነገር ብቻ መብከንከን ከሆነ በዚህች ሀገር ማንም በሰላም አይኖርም፡፡ በሰላም ለመኖር የሚከፈል መስዋዕትነት ደግሞ በግድ በደም ብቻ የሚሰላ ሊሆን አይገባም፡፡ በፍቅርም ጠላት ተብሎ የተፈረጀን ወገን ማንበርከክ ይቻላል፡፡ በይቅርታም ወዳጅ ማፍራትና የተቀያየሙትን ኃይል ማቅረብ ይቻላል፡፡ በእልህና በቂም በቀል የትም መድረስ እንደማይቻል እኛ ኢትዮጵያውያን ኅያው ምሥክሮች ነን፡፡ የከረረ ይበጠሳል፤ ከተውት ግን ይመለሳል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ጫፍ ወደመሀል ሲሰባሰቡ ይታየኛል፡፡ ሀገራችንን ፈጣሪ ይባርክልን፡፡ ከሃይማኖት ጽንፈኞች፣ ከወያኔ ወጥመዶች፣ ከሙስና አሜከላዎች፣ ከሞራላዊ ዕሤቶቻችን ቀበኞች፣ ከማይምነት ጥቁር ግርዶሽ፣ … እግዚአብሔር ሀገራችንን በቶሎ ነፃ ያውጣልን፡፡ ደግሞም በርትተን እንጸልይ፡፡ ከ2000 ዓመታት በላይ በዓለም ዙሪያ ተበታትነው የነበሩ እስራኤላውያንን እንኳ ቃል ኪዳኑን ጠብቆ  የታፈረችና የበለጸገች የአንዲት ሀገር ባለቤት አድርጓቸዋል፡፡ እኛ ደግሞ ለርሱ ከነርሱ እንበልጥበታለን፤ ሀሰት አይደለም፡፡ “እናንተስ ለኔ እንደኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?” ብሎ ፈጣሪ ስለኛ ለነሱ የተናገረው ስለሚወደን ነው፡፡ እኛ አምነነዋል፤ እነሱ ግን ገና አላመኑትም፡፡ ስለዚህ ተስፋችን እርሱም ነው፡፡ የኛ የኃላፊነት ድርሻ ግን ትልቁ ነው፡፡ ምክንያቱም “አዳም ሆይ! በላብህና በወዝህ ጥረህ ግረህ ብላ” ተብሎ ወደ ምድር ወርዷልና ቢያንስ አሻሮ እንኳን ሳንይዝ ወዳለው – ወደፈጣሪ – መጠጋት ስንፍና መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

Mz23602@gmail.com

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *