ከሰሞኑ የአማራው በአማራነት መደራጀት ጉዳይ እንደገና ተቀስቅሶ የውውይት አጀንዳ የሆነ ይመስላል። ገራሚው ነገር የአማራውን በአማራነት መደራጀት አጀንዳ እያደረጉ ያሉት ሰዎች በዘውግ ከተደራጁት ቡድኖች ጋር አብሮ ለመስራት ደፋ ቀና እያሉ ያሉ ግለሰቦች ጭምር መሆናቸው ነው። የአማራው በአማራነት መደራጀት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ሆኖም ግን የአማራውን በአማራነት መደራጀትና «የአማራ ብሔርተኛነት» የሚባለውን የሌለ ነገር መለየት ያስፈልጋል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የአማራ ብሔርተኝነት የሚባል ነገር የለም። የአማራ ብሔርተኛነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ያለበትና ሊኖር የሚገባው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነት ብቻ ነው። ብሔር የግዕዝ ቃል ነው። ትርጉሙም አገር ማለት ነው። ብሔር የሚለው የግዕዝ ቃል ከህዝብ ጋር የሚያገናኝው ነገር የለም። ብሔር የሚገልጸው ምድሩን ነው። በእንግሊዝኛም ብሔር ማለት Nation ማለት ነው። United Nations የአገራት ህብረት ማለት ነው።

ያ ትውልድ ነገድን ብሔር ወይንም Nation የሚል ስያሜ ሰጥቶ ፖለቲካ ያካሄደው «ዳግማዊ ምኒልክ የተባለ የአማራ ንጉስ የተለያዩ አማራ ያልሆኑ «የአፍሪካ አገሮችን» ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር በመመሳጠር ወርሮ በቅኝ ግዛትነት ይዟል» የሚለውን የትውልዱን የትግል መነሻ ጽንሰ ኃሳባዊ መሰረት ለመስጠት ነበር። በያ ትልውድ ፍልስፍና አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ወዘተ ብሔሮች ወይንም Nations ስለሆኑ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የአገራት ህብረት ወይንም United Nations ናት ማለት ነው። በያ ትውልድ የፖለቲካ ትርጓሜ ኒዮርክ ባለው አለማቀፉ United Nations እና በUnited Nations [of Ethiopia] መካከል ልዩነት የለም።

ማንም ያድርገው ማን ብሔሮች ወይንም ብሔረሰቦች የሚባሉት ስብስቦች በነገዳቸው ዙሪያ የሚያደርጉት የብሔርተኛነት ትግል ጸረ ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህ ጸረ ኢትዮጵያዊነት ትግል ወያኔ፣ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ወዘተ የታገሉለት አይነት ትግል ነው። ወያኔ፣ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ወዘተ የታገሉት ዋለልኝ በፈጠረው እስር ቤት ውስጥ የታጎሩት «ብሔር፣ ብሔረሰቦች»፤ ምኒልክ ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር ተባብሮ አፍሪካን ሲቀራመት ከጠቀለለበት ኢትዮጵያ የምትባል እስር ቤት «ነጻ ወጥተው» ኦሮምያ፣ ትግራይ፣ ኦጋዴን፣ አፋር፣ሲዳማ፣ ወዘተ የሚባሉ አዳዲስ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች እንዲመሰረቱ ነበር። የዚህ ትግል ግብ ነጻነት ወይንም እኩልነት አይደለም። እንዴውም ይህ ትግል ከነጻነትና እኩልነት ጋር አንዳች የሚያገናኘው ነገር የለም። በአካባቢያችን የተካሄደ የነገድ ብሔረኛነት እንግስቃሴ ግብ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ የሚሻ የወያኔ፣ የኢሕአፓ፣ የኦነግና የሻዕብያ ትግል ፍሬ ውጤት የሆነችዋን የኢሳያስ አፈወርቁዋን ኤርትራ ማየት ይችላል።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

የያ ትውልድ ድርጅቶች እነ ወያኔ፣ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ወዘተ የታገሉት የራሳቸውን ባንዲራ ፈጥረው፤ የክብር ዘብ አሰልፈው የህይወት ዘመን ፕሬዝደንት ሆነው የሚገዘግዙት አገር መፍጠር ነው እንጂ ትክክኛ የህዝብን የመብት፣ የመናገር፣ የመወከልና የንብረት መብት ነጻነት ለማምጣት አይደለም። ለዚህ ቢሆን ኖሮ የታገሉት በየለቱ ንግግራቸውና ተግባራቸው ሁሉ በራስ ሀብት ስለማዘዝ፣ ስለመናገር፣ ስለመወከልና ስለንብረት ማፍራት መብት ነጻነቶች ሲሰብኩ ይሰማና ይታይ ነበር።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን «የኃሳብ ልዩነት የማያስተናግዱ ጨቋኝ» ብሎ ለነጻነት የታገለው ኦነግ ፋኖዎቹ የሚያነሱትን የኃሳብ ልዩነቶች መቀበል ተስኖት በቅድሚያ እነ ባሮ ቱምሳን ገደለ፤ ሲቀጥል ደግሞ እነ ሌንጮ ለታ አለን ያሉትን የሀሳብ ልዩነት ማስተናገድ አልችል ብሎ ሌንጮና በዙሪያው ያሉ ግለሰቦች ድርጅታቸውን ለማሻሻል ሀሳብ በማቅረባቸው የተነሳ ጠራርጎ በማባረር እነ ሌንጮ ለታ የኦነግ መሪዎች በነበሩበት ጊዜ እንደነ ጀኔራል ጃገማ ኬሎ አይነት ሀውልት ሊቀምላቸው የሚገባ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን «ጎበናዎች» እያሉ ሲያሸማቅቁበት የነበረውን የኦነግ ስድብ ወደራሳቸው አዞሮ ትናንትና እነ ሌንጮ እነ ጀኔራል አበራ አበበንና መርዕድ መንገሻን «ጎበናዎች» እያሉ ሲያሸማቅቁበት በነበረው የኦነግ ስድብ ዛሬ በተራቸው እነሱን «ጎበናዎች» እያለ ሲሰድብ የሚውለው፤ አንድ የነበረው ኦነግ ግለሰቦች የተለየ ሀሳብ ባነሱ ቁጥር እየተሰነጠቀ ዛሬ ላይ ለስምንት ተከፍሎ በየሳምንቱ ጥምረት ሲመሠርትና ሽር ብትን ሲል የሚውለው፣ የኦሮሞን ገበሬ ከመሬቱ ሲያፈናቅል ከሚውለው የትግሬ አገዛዝ ጋር ምርጫ በደረሰ ቁጥር «እንደራደር እያሉ» አገር ቤት ለመግባት የወያኔን ደጅ የሚጠኑት እድሜ ልካቸውን የታገሉት፤ እንደ መለስ ዜናዊ ጮሌ የሆነ አንዱ ኦነጋዊ የህይወት ዘመን ፕሬዝደንት ሆኖ የሚገዘገዘው የኦሮሞ አገር ለመመስረት እንጂ የሀሳብ ልዩነት ለሚከበርበት ነጻነትና የኦሮሞ ገበሬ የመሬት ባለቤት የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር ስላልነበረ ነው።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የሀሳብ ልዩነት አልተከበረም ብለው የሀሳብ ልዩነት እንዲከበር ለመታገል ጫካ ገባን ያሉት ወያኔና ኢሕአፓም ልክ እንደ ኦነግ የታገሉት የራስ አገር ለመፍጠር እንጂ የሀሳብ ልዩነት እንዲከበር ወይንም ለነጻነት[for freedom] ቢሆን ኖሮ ወያኔ በየ አሥር ዓመቱ ለሁለት እየተከፈለ TAND, TPDM, ARENA, ወዘተ እያለ አይባዛም ነገር፤ ኢሕአፓም እንደ አሜባ ራሱን እየቆረጠ «ኢሕአፓ D» ምንትሴ እያለ እየተራበ እድሜ ልኩን ርስ በርስ ሲጫረስ አይኖርም ነበር።

ኢሕአፓ ከምስረታው ጀምሮ የታገለው ኢትዮጵያን በመበታተብ የዋለልኝ መኮነንን እስረኞች «ነጻ አውጥቶ» ከሰማኒያ በላይ የሚሆኑ አዳዲስ የአካባቢ አገራትን ለመመስረት ነበር። የኢሕአፓ አስተሳሰብ ውሉድ የሆነው ወያኔ ደግሞ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ኢሕአፓ ሊመሰርታቸው የታገለላቸውን ከሰማኒያ በላይ በየነ መንግስታት ወደ ዘጠኝ ክልሎች በማጠፍ የትግራይን የበላይነት በሌሎችን ኢትዮጵያውያን ፍዳና መከራ ላይ ማደላደል እስከቻለ ድረስ እንዳሻው የሚያስገብራት፤ ነገር ግን በማንኛውም ጊዜ ዘጠኝ አገር ልትሆን የምትችል የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስብስብ ፈጠረ። የኦሮሞ፣ የትግሬ፣ ወዘተ ብሔርተኛነት የወለደው ትግል አሁን ያጋመስነው እንደ ሕዝብ የመኖር እጣችን ለጊዜውም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት አሊያም የሚያቆምበት ደረጃ ላይ አድርሶናል። አማራው በታሪኩና በባህሉ ጥላቻ ስለሌለው የነ ኦነግ፣ ወያኔ፣ኢሕአፓና ወዘተ አይነት ደም የተጠሙ ድርጅቶች ትግል አያደርግም።

ከዚህ በፊት እንደተናገርሁት የአማራ ክልል ኢትዮጵያ ነች። የኦሮሞም ሆነ የሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶች ክልላቸው ኢትዮጵያ ናት። አማራው የሚያደርገው ትግል በዚች በክልሉ በኢትዮጵያ ከሌሎች እኩል በጋራ ለመኖር ነው። የአማራ ብሔርተኛነት የመፍጠር ሕልም ይዞ ወያኔና ኦነግን መውቀስ ግብዝነት ነው። ትክክለኛው የፖለቲካ ትግል ሁሉም ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውና ኃይማኖታቸው ተከብሮ፤ ቋንቋቸውን እየተናገሩ በዜግነት እኩል ሆነው የሚኖሩበትን አገር የመፍጠር እንቅስቅሴ ነው። ይህ አይነት ትግል ከነገድ ብሔርተኛነትጋር የሚያገናኝው ነገር የለም።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

የሆነው ሆኖ አማራ እያካሄደው ያለው ትግል በሰፊዋ አገሩ በዜግነት እኩል ሆኖ ለመኖር የሚያካሄድ ተጋድሎ ወይንም የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ትግል እንጂ የአማራ ብሔር ወይንም Amhara nation ለመፍጠር አይደለም። የአማራ ብሔር ኢትዮጵያ ነች። የአማራ ወይንም የኦሮሞ ብሔርተኝነት የሚባለው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን አፍርሶ በሸምበቆ አጥር ተከልለው ርስ በርስ የሚተረማመሱ የአካባቢ መንግስታትን የመመስረት ጸረ ኢትዮጵያ ትግል ነው። ባጭሩ አማራ ከፍ ብለን እንዳየነው አይነት የከሰረ ትውልድ የነገድ ብሔርተኛነትን የትግል መመሪያው አድርጎ ትግል አያካሂድም።

ማንበብ ከብዙ ስህተት ያድናል። ባሌ ከጥንት ጀምሮ የአማራ ጭምር ርስተ ምድር የነበረ፤ ግራኝ አህመድ «የባሌ አበሾች ሰይጣኖች ናቸው» ሲል የመከሰረላቸው የባሌ ነጋሹ የራስ ተክለ ሃይማኖት ግዛትና ከግራኝ አህመድ ጋር ሲዋጉ ለአገራቸውና ለኃይማኖታቸው የወደቁት የባሌ ተወላጆች የነ ራስ ነብያንትና የነ አዛዥ ፋኑኤል መቃብር ነው። ደዋሮ [የዛሬው ምዕራብ ሐረርጌ] የልብነ ድንግል የጦር አዝማች የነበረው የቢትወደድ በድል ሰገድ ርስት ነው። ዳሞትና ቢዛሞ[የዛሬው ወለጋ] በሽምግልና እድሜው ግራኝን ለመፋለም ዘምቶ አስደማሚ ተጋድሎ ያደረገው የልብነ ድንግል የጦር አዛዥ የአዛውንቱ የራስ ወሰን ሰገድና የጀግናው ልጁ የባህር ሰገድ እትብት የተቀበረበት አገራችን ነው። ፈጠጋር[ የዛሬው አርሲ] እነ ነጋሽ ተክለ ሐዋርያት ከግራኝ ጋር ሲፋለሙ የወደቁበት ያያቶቻችን ርስት ነው።

ስለዚህ አማራው የሚጋደለው በአባቶቹ አገር በኢትዮጵያ እኩል ዜጋ ሆኖ ለመኖር እንጂ እንደ ወያኔና ኦነግ ለብሔርተኛነት አይደለም። ብዙ ሰው የአማራው በአማራነት መደራጀት ለወያኔ ስኬት ነው ብሎ ያስባል። ይህ በጣም የተሳሳተ ነው። አማራው በኢትዮጵያ ለመኖር የሚያደርገው ትግል የወያኔ ስኬት ሊሆን አይችልም። የአማራው በአማራነቱ መደራጀቱ የወያኔ ስኬት የሚሆነው የአማራው ትግል የአማራ ብሔርተኛነት ከሆነ ነው። አማራው ለብሔርተኛነት ከታገለ የሚታገለው ለኢትዮጵያ ብሔርተኛነት ነው።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *