“Our true nationality is mankind.”H.G.

ጣራው ለሚያፈስ ቤት -የወለል እድሳት!

– ይገረም አለሙ  

missing the target

 

መላ አከላቷን ዝንጀሮ እሾህ ወግቷት
መቆም መራድ መቀመጥ ተስኖአት
የትኛውን እንንቀልልሽ ብለው ቢጠይቋት፣
ብታስቀድሙልኝ የመቀመጫየን
እኔ እነቅለዋለሁ ቁጭ ብዬ ሌላውን ፣  በማለት መለሰች  ቅድሚያ የሚሰጠውን ነገር ስላወቀች ፡፡

ጣሪያው በሚያፈስ ቤት ውስት እየኖሩ ክረምት በመጣ ቁጥር እየተሰቃዩ በጋ  ሲሆን የወቅት መለዋወጥ የተፈጥሮ ባህርይ መሆኑ ተዘንግቶ ነገር አለሙን በመርሳት ወለሉን ቢያድሱት ግድግዳውን ቀለም ቢያብሱት አይቀሬ ነውና ክረምት ሲመጣ የሚሆነውን አስቡት፤ከንቱ ልፋት አጉል ብክነት፡፡

የቤቱ ወለል እድሳት ቢሻ፣ ግድግዳው ቀለም ቢያምረው፣ ጣራው ደህና እስከሆነ ድረስ መኖር አይከለክልምና ቅድሚያ መቀመጫየን እንዳለችው ዝንጀሮ መቀመጫን አስተካክሎ ሌላ ሌላውን በሂደት ቀን ሲፈቅድ አቅም ሲጎለብት ማደስ ይቻላል፡፡ ጣሪያው የሚያፈስ ቤት ውስጥ እየኖሩ ክረምቱ አልፏል ብሎ ወለል ማደስ ቅድግዳ ቀለም መቀባት ግን አንድም ሞኝነት ሁለትም አጭበርባሪነት ነው፡፡እንዲያም ሲል ከዛሬ ያለፈ አለማሰብ ይሆናል፡፡በአን ጎራ ካለነው እኛ ከምንባለው እነማን ከየትኛው ጎራ እንደሆኑ  እናንተው አስቡት፡፡

ሀገራችን ቤታችን ናት፤ ጣራዋ በብልሽትም በእርጅናም ተበለሻሽቶ በበጋ ለጸሀይ ሀሩር፣ በክረምት ለዝናም ዶፍ ብንዳረግም  ለምደን ተላማምደነው  እንኖራለን፡፡ገዢዎቻንም የእኛ ቻይነት፣ የፈረንጆቹም ጩኸት እንዴትነት ገብቷቸው ወለሉን እያደሱ፣ ግድገዳውን ቀለም እየቀባቡ  ለአላፊ አግዳሚውም ሆነ ለደርሶ ሀጅ ጎብኝው ችግሩ አንዳይታወቅ አንደውም ያማረ የሰመረ መስሎ አንዲታይ በማድረግና መኖሩን ችለውበታል፡፡ ያማረው ቤታችን ሞንዳላው ኑሮአችን እያሉ በሚያሰሙት ፕሮፓጋንዳም እኛን እያደነቆሩም አቀጣጫ እያሳቱም ከፈረንጆቹ ጋር እየተሞዳሞዱ ረብጣው ሳይነጥፍባቸው፣ ዲፕሎማሲያዊው ድጋፍ ሳይቋረጥባቸው፣ሲገድሉና ሲያስሩ የሚሰማው ተቃውሞም ከቃል ወደ ተግባር ሳይሸጋገርባቸው ሀያ ስድስት ዓመት እንደዋዛ ገዙን፡፡ ሁሉንም ነገር አይተው ገምተው ጠብ- መንጅቸውንም ተማምነው ገና አርባ አመት አንገዛችኋለን እያሉ ነው፡፡ ይበሉ! የታገሉት ለምንና ለማን ሆነና፡፡ ጥያቄው እኛ የምንባለው ከተቃውሞው ጎራ ያለነው ብዙ እኛዎች ያለፈውን የሰሩትን እያየን የወደፊት ምኞት ዝግጅታቸውን እየሰማን ምን አልን ምንስ አደረግን ነው ? ብዙዎቻችን ካለንበት ነቅነቅ ያላልነው  ከመማረር ወደ ማምረር ተሸጋግረን  ራሳችንን ከሰቀልንበት ከፍታ አውርደን ከመጯጫህ ወጥተን  አገዛዝ በቃን በማለት  የምንችለውን ጠጠርም ቢሆን ለማስቀመጥ ዝግጁ ነን ወይ? ነው ጥያቄው ይህ ካልሆነ ወያኔ ከምኞት ፍላጎቱም በላ ይገዛናል፡፡ አንደ አያያዛችን ከሆነ ብዙዎቻችን በአፋችን እንጮሀለን እንጂ በወያኔ የተፈጸመው ነገር ሁሉ ውስጣችን ዘልቆ አልተሰማንም ለዚህም ነው ከመማር ወደ ማምረር መሸጋገር ያልቻልነው፡፡ ይህ ባይሆንማ ኖሮ ወቅት እየጠበቀ ወያኔ በሚሰጠን መጫወቻ ከአንልፋችን እየባነንን በምናሰማው ውግዘት ጩኸት  ጣሪያው ለሚያፈስ ቤት የወለል እድሳት የምንጠይቅ ባልሆነ ነበር፡፡ በእኔ እምነት ጣራው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡ እንደ አብርሀም ሊንከን አባባል የህዝብ፣ በህዝብ፣  ለህዝብ፣  የሆነ መንግሥት ፡፡ ስለሆነም ይህ በሌለበት/በተነፈግንበት/ ሀገራችን  ሌሎች የህግም በሉት የሰብአዊ መብት፣ የቋንቋም በሉት የሀይማኖት ጥያቄዎችን ማንሳት  ታሰርን ተሰደድን ተገደልን እያሉ መጮህ ከሂደቱ ለማትረፍ እንጂ ከግቡ ለመድረስ የማንታገል ያስመስላል፡፡

Related stories   የተላላኪው ጠበቃዎች

ዴሞክራሲ ቅንጦት ተደርጎ በሚታይበት አገዛዝ ውስጥ እየኖሩ ስለ ቋንቋ፣ስለ ሀይማኖት፣ስለ ብሄር ብሄረሰብ፤ስለ ህግ በላይነት፣ስለ ሰብአዊ መብት መከበር ስለ ነጻ ምርጫ ወዘተ ማሰብ፣  መጠየቅ፣ መጮህ ጣራው በሚያፈስ ቤት እየኖሩ ወለል ለመቀየር ግድግዳ ለማደስ የመንደፋደፍ ያህል ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ሲሆን ምላሽ የሚያገኙ ናቸው፡ ብቻ ሳይሆን ያለ እነዚህ ተግባራዊነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊኖር ስለማይችል ወያኔ በሥልጣን ለመቆየት ጠመንጃውን እንደሚተማመን ሁሉ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለሥልጣን የሚበቃ ግለሰብም ይሁን ፓርቲ እነዚህን ነገሮች ማክበርና ማስከበር የህልውናው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከፈረሱ ጋሪው የሆነውን መያዣ መጨበጫ ያጣውን ነገራችንን በማስወገድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ በሚያስችለው መንገድ አንደየአቅማችን እንራመድ፡፡ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው ነገር ራስን መለወጥ ነው ፡፡ እዚህ ላይ አንድ ዘመን ተሸጋሪ አባባል ብጠቅስ ማለት የፈለኩትን ይበልጥ የሚያሳይልኝ መሰለኝና እነሆ!

የአሜሪካፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሀም ሊንከን ለኮንግረስ ያስተላለፉት ሁለተኛው መልዕክታቸው ተብሎ በሚጠቀሰው ንግግራቸው «አንድ ትውልድ ያልፍና ሌላ ትወልድ ይተካል፣ ዓለም/መሬት ግን ለዘለአለም ትኖራለች፡፡ ጸጥ ረጭ ያለው ያለፈው ግዜ ፍልሰፍናዎች (ዶግማስ) አውሎ ነፋሳዊ ለሆነው ለዛሬው ችግር ለመፍትሄነት አይመጥኑም፡፡ ጊዜያችን ችግር ያዘለ ስለሆነ በአዲስ ሁኔታ ማሰብና በአዲስ ሁኔታም መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ራሳችንን ከሰቀልንበት ከፍታ ማውረድ ይገባል፡፡ ያን ግዜ አገራችንን ለማዳን እንችላለን፡፡ ታሪክን ልናመልጥ አንችልም፣ልንሸሸው አይሆንልንም፣ ክፉም ሰራን ደግ እንዘከራለን፣ (እንታወሳለን) ግለሰባዊ መታወቅ ወይም አለመታወቅ አንዳችንንም ሆነ ሁላችንን አያተርፈንም፣የምናልፍበት እሳታዊ ፈተና (ፍርድ) በክብር ወይንም በውርደት ማለፋችንን ይመሰክራል»

ብዙዎች እኛ ፤ እነርሱ ወያኔዎች ምንም በሉዋቸው ምን ባነገቡት ዓላማ ሊደርሱበት በሚያስቡት ግብ አንድ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ አይደለም ሰው ነፋስ አያስገቡም፡፡እንዲህም በመሆናቸው ነው ታግለው ያሸነፉት፣ ሀያ ስድስት ዓመታትም በዙፋኑ ለመዝለቅ የበቁት፡፡ በተቃውሞው ሰፈር ያለነው እኛ ግን ብዙ እኛዎች ነን፡፡ ሰንደቅ ኣላማ ለብሶ ከሚፎክረው፣ ኢትዮጵያ እያለ ከሚዘምረው፣ የብሄር ኩታ ለብሶ ከሚያቀነቅነው ፖለቲከና አይደለሁም እያለ ከሚሸውደው  ወዘተ ብዙ እኛዎች መካከል  የቤታችን ጣራ ተቀይሮ ሁላችንም የጸሀዩ ሀሩር ሳጠብሰን፤ የክረምቱ ዝናም ሳያበሰብሰን መኖር የምችልበት ቤት እንዲኖረን ምን ያህሉ ነን ከምር የምንሻው ተብሎ ቢጠየቅ  ከብዙዎቹ ተግባር በማየት የምናገኘው ምላሽ አሉታዊ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ለወያኔ ግዞት ያመቻቸን መሰረት አልባው ልዩነታችን መሰረት የለሽ በመሆኑ ለገላጋይ ዳኛ ለመካሪ ሽማግሌም የሚመች አይደለም፡፡ ብዙዎች በቤታችን ጣራ መቀየር በየግላቸው ያምናሉ፣ነገር ግን ይህን እምነት የጋራ ለማድረግ ይቸገራሉ፣ለምክንያትነት የማይበቃው ሰበባቸው የሚያሳብቅባቸው ደግሞ ጣራው እኔ በምለውና በምፈልገው መንገድ ካልሆነ በስተቀር ባይለወጥ ይቅር የሚሉ ከራስ በላይ የማያስቡ መሆናቸው ነው፡፡ በግልጽ ቋንቋ ለመናገር እኔ አባዋራ የማልሆንበት ቤት አንኳን ጣራው ግድግዳውም ይደርመስ የሚሉ ነው የሚመስሉት፡፡

Related stories   "አንድ ሰዉ መላ አካላቱን ሰውቶ እምብርቱን ብቻ በማዳን እንዴት ህልውናን ያረጋግጣል" Taye Dendea

አንዳንዶቹ ደግሞ ለስሙ ከተቃውሞው ጎራ ከትመዋል እንጂ አድራጎት ንግግራቸው የተቃውሞ አይደለም፡፡ ጣራው እያፈሰሰም ለጸሀይ እየዳረገም ቢሆን ወለሉ ከታደሰ ግድጋዳው ቀለም ከተቀባ ርካታ የሚሰጣቸው አይነት ናቸው፡፡ ያ ባይሆን  ከሀያ ስድስት አመታት አገዛዝ በኋላ ዛሬ ስለ ህግ በላይነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት መከበር፣ ስለ ሀብት እኩል ተጠቃሚነት፣ ስለ ፍትህ ወዘተ ለወያኔ  ማላዘኑ በቆመ ነበር፡፡ እነዚህ ከእባብ እንቁላል እርግብ የሚጠብቁ ሊባሉ የሚበቁ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀርና ቢረሳን  የህዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው፣ የሰጡትን ዝም ብሎ የማይቀበል ጠያቂ ትውልድ ፈጥረናል ወዘተ ብለው ተመጻድቀውና ተሳልቀው ለተቃውሞ መውጣቱም ሆነ ያነሳው ጥያቄ ትክክል ነው ያሉትን ህዝብ በገፍና በግፍ አስረው እያስተማርነው ነው ተሀድሶ እየሰጠነው ነው ከሚሉ ሰዎች ምን ሊገኝ ጥያቄ እንደሚቀርብ ጩኸት እንደሚሰማ አይገባኝም፡፡

እያዩያ አለማስተዋሉ፣እየሰሙ አለማዳመጡ፣ እያነበቡ አለመገንዘቡ በእኛ ሰፈር በመብዛቱ እንጂ ወያኔዎች ከጅምሩ በመቃብራችን ላይ ሲሉ በግልጽ ነግረውናል፡፡ጽፈው አስነብበውናል፣ በተለያየ መንገድ በዘፈንም በፊልም አሳይተውናል፡፡እኛ ሰፈር ግን በምኒልክ ዘመን የደነቆረ ምንይልክ ይሙት እንዳለ ይኖራል እንደሚባለው ሆነን በወያኔ ድል ማግስት የተጀመረው ጩኸት፣ልመና ተማጽኖ፣ ስድብ ዘለፋ የመግለጫ ተቃውሞ  ወይ መሻሻል ሳይሳይ ወይ አርጅቶ ገለል ሳይል እስካሁን አለ፡፡

ሎሬት ጸጋየ  ገብረ መድህን የአባቶቻችን ነገር ሳስታውሰው ትዝ የሚለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ እንዳለው  እስከ ዛሬ የመጣንበት የፖለቲካ ጨዋታ አላዋጣም፣ የያዝነውም ተለይይቶ ጉዞ  ከምንለው ቦታ የሚያደርስ አልሆነም ስለዚህ ራሳችንን ፈትሸን፣ አመጣጣችንን ገምግምን ድክት ጥንካሬአችንን ለይተን፣ለዘመኑ የሚስማማውን አስተሳሰብ እንያዝ፣ ለትግሉ የሚመጥነው መንገድ እንከተል በማለት የሚታትሩ ብቅ ሲሉ ከወያኔ ሰፈር ባልተናነሰ ጩኸቱ የሚበዛውም ሆነ  ትንሽ ትንሽ መሰናክል ማስቀመጥ የሚጀመረው እኛ ከምንባለው ብዙዎቹ እኛዎች በኩል ነው፡፡

ቤቱ ጣራው ዝናብ ቢያፈስም፣ ጸሀይ ቢያስመታም ወለሉ ካማረ፣ ግድግዳው ቀለም ከተቀባባ ለእኔ ይመቸኛል፤ የጣራው ነገር አያስጨንቀኝም ማለት መብት ነው ምርጫ ነው፡፡ ለዴሞክራሲ ነው የምታገለው የሚል ሁሉ ይህን ምርጫ መቀበል የሰዎቹን መብት ማክበር ይገባዋል፡፡እነርሱ ደግሞ ጣራው መቀየር አለበት ብቻ ሳይሆን ካልተቀየረ በቤቱ ውስጥ መኖር አንችልም በሚለው ወገን እየተከለሉም እየተመሳሰሉም እያደናገሩም መኖሩን አቁመው አቋማቸው ጥቅም የሚያገኙበት ሳይሆን ከልብ የሚያምኑበት ከሆነ   መብታቸውን በይፋ መጠቀም እምነታቸውን በግልጽ ማራመድ ይኖርባቸዋል፡፡መሸፋፈን ለመኝታ ግዜ ብቻ ይሁን፡፡ ማለባበስ ይቁም!

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

በጣም አስቸጋሪው መፍትሄ አጥቶ የግዞት ዘመናችንን እያራዘመው ያለው በጣራው መቀየር ላይ ልዩነት ሳይኖር መቀየር ያለበት እኔ በምለው መንገድ ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡የነገሩ ክፋት የሚብሰው ደግሞ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች በሚሉት መንገድ ለመቀየር ስንዝር የተግባር እንቅስቃሴ የማያደርጉ መሆናቸው ነው፡፡ተግባሩ ቀርቶ እንዴት በምን ሁኔታ በማን ጣራው መለወጥ እንደሚችል ግልጽ አቋም የላቸውም፡፡ አቋማቸውን ገልጸው መንገዳቸውን አሳይተው ሊደርሱበት የሚያልሙትን ግብ ነግረው ደፋ ቀና በሚሉት ላይ ለመዝመት ግን እንቅልፍ የላቸውም ፡፡እንዲህ መሆን የለበትም፣ አንደዚህ ለምን ይደረጋል፣ በዚህ መንገድ ለምን ይኬዳል ከማለት በስተቀር እንዲህ ይሁን በዚህ መንገድ መሄድ ያዋጣል ወዘተ በተግባር ቀርቶ በቃል ደረጃ እንኳን አይናገሩም፡፡

ግልጽ አቋም በጣራው መለወጥ ላይ፣ የቤታችን ጣራ ከተለያየ አቅጣጫ ብዙ ስም የወጣለት ገዢዎቻችንም ሊያደናብሩንና አቅጣጫ ሊያስቱን በከጀሉ ቁጥር አዳዲስ ስም እያወጡ  በአንድ ያልረጉበት ሲሆን የምንሻው ግን ግልጽ ነው፡፡ዴሞክራሲያዊ ጣራ፡፡ ወራጅና ማገሩ ቆርቆሮና ምስማሩ በህዝብ ለህዝብ የህዝብ ሆኖ የሚሰራ ጣራ፡፡ይህን የሚጠላ ወይንም የማይፈልግ በአንደበቱ ባይናገረውም በተግባሩ እንለየዋልን፡፡የመጀመሪያው ወያኔና በዙሪያው ተኮልኩለው ተጠቃሚ የሆኑት ናቸው፡፡ለጥቆ የምናገኛቸው ሀያ ስድስት አመት ሙሉ ተቀዋሚ መባል ያልሰለቻቸው ምን አልባትም የሚያኖራቸው ወያኔ ተሰናብቶ ዴሞክራሲያዊ ሥርኣት ቢሰፍን ወለሉ ይታደስ ግድግዳው ቀለም ይቀባ አይነት የይስሙላ ተቃውሞ እያሰሙ መኖር አይችሉምና የጣራውን ለውጥ አይፈልጉትም፡፡ ሲስልስ ወያኔን ከማውገዝና ከማጥላላት ባለፈ የተጀመረም ሆነ የተሰነቀ ነገር የማይታይባቸው ነገር ግን ይህንኑ መኖሪያቸው ያደረጉ እናት ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ብሉኮ ብትከናነብ ህዝባችን ተገደለ ታሰረ በዘራችን ብቻ ተጠቃን  እያሉ ነሸጥ ሲያደርጋቸውም በመገንጠል እያስፈራሩ፣ ሰከን ያሉ እለት ደግሞ ስለ አንድነት እየዘመሩ ያሉ፣ የሚኖሩ ወገኖች ያኔ ይህን ማድረግ አይችሉምና በአፋቸው የሚናገሩት/የሚነግዱበት  ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተግባር እውን ሲሆን ለማየት ይሻሉ ብሎ ማሰብ ይቸግራል፡፡

በድርድርም በሉት በግርግር፤በሰላማዊ ሰለፍም በሉት በጩኸት፣በጽሁፍም ይሁን በንግግር የሚቀርቡ ጣራውን በመለወጥ ላይ የማያተኩሩ ነሮች ሁሉ ጣራው ለሚያፈስ ቤት የወለል እድሳት የመፈልግ ያህል ነውና ሲብስም እቅጣጫ የሚያስት ትግል የሚያዘናጋ ለገዢዎች እፎይታ የሚሰጥ ወዘተ ነውና ይታሰብብት፡፡ በሁሉም መንገድ በየትኛውም መስመር ትግል ጣራውን ለመቀየር፡

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0