Skip to content

ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የዘመናይ አምራችነት በር ከፋች

 

በሳምንቱ መጀመሪያ የሐዋሳ ከተማ ከወትሮው ለየት ያለ ድባብ ታይቶባታል፡፡ የከተማዋ የንግድ ቤቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ደጃፎች፣ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ዙሪያ የተለያየዩ መልዕክቶችን ያነገቡ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችና ማሳያዎች ተሰቅለዋል፡፡ የሲዳማን ባህላዊ አልባሳት የተጎናፀፉ ወጣቶችና ጎልማሶች በከተማው ወዲህ ወዲያ እያሉ ሲንጎማለሉ ማየት የሰሞኑ የሐዋሳ ከተማ አክራሞት ነበር፡፡

የንግድ ድርጅቶች ትላልቅ የድምፅ ማስተጋቢያ ሳጥኖችን ከደጆቻቸው አስቀምጠው የሲዳማን ባህላዊ ዝማሬዎችና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን ጨዋታዎች አጉልተው ሲያሰሙ የተመለከተ ከተማዋ ውስጥ የተለየ ነገር መኖሩን እየተከናወነ እንዳለ ያሳብቃል፡፡

ይህ ሁሉ የሲዳማ ዘመን መለወጫ የሚከበርበትን የፍቼ ጫምባላላ ክብረ በዓል ለመቀበል ከዋዜማው ጀምሮ ሲደረግ የነበረው ዝግጅት የፈጠረው ነበር፡፡ ከዚህ በዓል የዋዜማ ዕለት ጎን ለጎን ሐዋሳን ሊያጎላ የሚችል ሌላ ትልቅ ዝግጅት እየተደገሰ ስለነበር ከተማዋ እንቅስቃሴ የበዛባት ሆና እንድትሰንብት አድርጎታል፡፡

ይህም በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እየተገነቡ ካሉና ግንባታቸው ከተጠናቀቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ የሆነው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ ሥራ መጀመሩን በማስመልከት የተዘጋጀው ክብረ በዓል አንዱ የድምቀቷ ምክንያት ነበር፡፡

የጫምባላላ በዓል ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ መጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ጋር በመገጣጠሙ፣ ፓርኩን ለመመረቅ ሐዋሳ የሔዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስለፓርኩ ምርቃት ንግግራቸውን የጀመሩት እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን በማለት ነበር፡፡

የግዙፉ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገፅታዎች

የኢንዱስትሪ ፓርኩ አጠቃላይ ይዞታ ሦስት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የፓርኩ የመጀመርያው ምዕራፍ የሸፈነው ቦታ 1.4 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ነው፡፡ ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ እየተገነቡ ካሉና ይገነባሉ ተብለው ከሚጠበቁት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ትልቁ ሆኗል፡፡

35 የማምረቻ ፋብሪካዎች ያሉት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ከመግቢያው ጀምሮ ዓይነ ገብ ነው፡፡ ምድረ ግቢው ባማረ ዲዛይን የተሠራ፣ የሥራ ፍላጎትን የሚያነሳሳ ነው፡፡ ከ50 ሺሕ በላይ የተለያዩ ዛፎችና ዕፅዋት የተተከሉበት ከመሆኑም ባሻገር፣ የመኖሪያ ቤት ሕንፃዎችም አሉት፡፡ የሁለተኛው ምዕራፍ የፓርኩን ግንባታ ለማካሔድ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. መሠረት ተቀምጦለታል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩን የገነባው ሲሲአርሲ የተባለው የቻይና ተቋራጭ ከመሆኑም ባሻገር ከዚህ ግንባታ በተጨማሪ ከ14ቱ ፓርኮች የሦስቱን ሥራ ተረክቧል፡፡ የዚህን ፓርክ የግንባታ ወጪ ለየት የሚያደርገው ልዩ ሒደት ያለው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ  በሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቦንድ ሽያጭ አማካይነት ከተገኘ ገንዘብ የድርሻውን ተመድቦለት መገንባቱ ነው፡፡

የፓርኩን ግንባታ የኋላ ታሪክ በተመለከተ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሊቀመንበር ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የገለጹት ነጠብ ይጠቀሳል፡፡ ፓርኩን  ለየት የሚያደርገው አንዱ ነጥብ ግንባታው በዘጠኝ ወራት ውስጥ መጠናቀቁ ነው፡፡ ቀጥሎም በፓርኩ ውስጥ ወደ ተገነቡት ማምረቻዎች የሚገቡ በዓለም የታወቁ ኩባንያዎች እንዲመጡ ለማድረግ ብዙ አድካሚ ሥራዎች መሠራታቸውንም ዶ/ር አርከበ ጠቅሰዋል፡፡ ጥያቄ ከቀረበላቸው ታዋቂ ኩባንያዎች ውስጥ 18ቱ በመምጣት ሥራ ጀምረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ወደ ፓርኩ የገቡት ኩባንያዎች የማምረት ሥራቸውን የጀመሩት ዘግይተው ነበር፡፡

ዶ/ር አርከበ እንደገለጹት ይህ የሆነው በመስከረምና ጥቅምት ወራት በተፈጠረው የፖለቲካ ግርግር ሳቢያ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ምርት በጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንዳንዶቹ ወደ ውጭ ለመላክ በቅተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በፓርኩ ውስጥ የተገነቡት ሁሉም ማምረቻዎች ኩባንያዎች አልገቡባቸውም፡፡ ለዚህ የቀረበው ምክንያትም ምርጥ ኩባንያዎች ተመልምለው እንዲገቡ መንግሥት ከመለፈጉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ሐዋሳን ያነጋገረው የፓርኩ ፍሳሽ ማስወገጃ

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአካባቢ ብክለትን እንዳያስከትል ከዲዛይን ጀምሮ ታስቦበታል፡፡ የፓርኩ ዲዛይን ብክለትን የሚከላከለው ልዩ መሠረተ ልማትም አስተማማኝነቱ በተነገረለት ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የጠየቀ ሥርዓት ያለው ነው፡፡ ከፓርኩ የሚወጣውን ፍሳሽ በመቀበል አጣርቶ መልሶ ለፋብሪካ ሥራ ለማዋል የሚያስችለው ቴክኖሎጂ የሚያስፈልጉት መሠረተ ልማቶች ተሟልተውለት በተንጣለለ ቦታ ላይ ታንጿል፡፡ በቀን ከፋብሪካዎቹ ሊመነጭ የሚችለውን 11 ሚሊዮን ሊትር ፍሳሽ ይማጥራት አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ለብክለት የሚያጋልጥ ሥጋት እንደሚኖር ቴክኖሎጂውንና ተዛማጅ መሠረተ ልማቶችን የገነባው የህንዱ ኩባንያ ኦርቪንድ ኤንቪሶል ኩባንያ አስታውቋል፡፡

ይህ ይባል እንጂ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረገጾች በቅርቡ ሲስተጋባ እንደታየው ከፓርኩ የሚለቀቅ ፍሳሽ ወደ ሐዋሳ ሐይቅ እንዲገባ የሚያመቻች ግንባታና የቦይ ቁፋሮ እየተካሄደ እንደሚገኝ የሚገልጹ ትችቶች የበርካቶችን ቀልብ በመሳብ ሲያነጋግሩ ከርመዋል፡፡ እንዴት እንዲህ ይደረጋል? የሚለው ጥያቄም ተስተጋብቷል፡፡ ይሁንና የተባለው ሁሉ ሐሰት እንደሆነ የፍሳሽ ማጣሪያው ይመስክር ተብሏል፡፡ በፓርኩ ሥራ መጀመሪያ ዕለትም በርካቶች ይህንኑ መሠረተ ልማት እንዲጎበኙት ተደርጓል፡፡ ከፓርኩ የሚወጣው ፍሳሽ ኢንዱስትሪዎች የሚያመነጩት ሳይሆን፣ ከእያንዳንዶቹ ማምረቻ የሚወርደውን የዝናብ ውኃ የሚከማችበትና በአግባቡ የሚስተናገድበት ሥርዓት ስለመሆኑ ማበራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም ሆነ ከዚህ በኋላ የሚገነቡት ፓርኮች የሥራ ሒደት ሲነደፍ፣ የበርካታ አገሮችን ልምድ ለማየት ተሞክሯል ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ ልምድ ከተቀሰመባቸው ዋና ዋና አገሮች መካከል ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ቬትናምና ቻይና ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከተጠቀሱት የሩቅ ምሥራቅ አገሮች በተጨማሪ ከአፍሪካ የሞሪሺየስና የናይጄሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ታይተዋል፡፡ ይህ ቅኝት የፓርኮች ልማት፣ የሚታዩ ችግሮችንና ምርጥ ልምዶችን ለመመልከት ያስቻለ ነበር ብለዋል፡፡ በእስያም ሆነ በአፍሪካ በተመረጡ አገሮች ልምድ ለመቅሰም በተደረገው ቅኝት፣ ኢትዮጵያ የምትገነባቸው ፓርኮች ምን መምሰል እንዳለባቸው ለመገንዘብ እንደተቻለ ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ በአብዛኛዎቹ የእስያ አገሮች የተሳካ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልምድ ስለመኖሩ መረዳት ቢቻልም ከአካባቢ ጥበቃ ረገድ ጥሩ የሚባል ልምድ እንደሌላቸው ያስረዱት ዶ/ር አርከበ፣ እነዚህ አገሮች ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት ቢያሳዩም አካባቢን ሲጎዱ በመቆየታቸው አሁን ላይ የጎዱትን አካባቢ በማከም ሥራ መጠመዳቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነቶቹን ጉዳዮች በመመልከታችን የኢትዮጵያ ምርጫ አካባቢን እየጠበቅን በሺዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎችን ማስፋት የሚለውን አማራጭ ለመከተል የመወሰን ዕድል ሰጥቷታል፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ብከላ የሚያስከትሉ መሆን እንደሌለባቸው ታምኖ ከአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከብከላ ነፃ በሆነ መንገድ የተገነባ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚገነቡ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የወጪ ንግድና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሚና

የፓርኮች ግንባታ አስፈላጊነትና ጠቃሚ የሚሆንበት ሌላው አንኳር ጉዳይ፣ ከወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ጋር ስለሚያያዝ ነው፡፡

የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለማሳደግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚኖራቸው ጠቀሜታ የላቀ ስለመሆኑ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ሲጀምር ከዚህ ፓርክ ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ይገኛል ተብሏክል፡፡ ይህ ውጥን ምን ያህል ይሳካል የሚለው አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ ዶ/ር አርከበም እንዲህ ያለው ጥያቄ ብዙ ጊዜ እንደሚነሳ አልሸሸጉም፡፡ ፓርኩ አንድ ቢሊዮን ዶላር ስለማስገኘቱ ለማስረገጥ ወደ ፓርኩ የገቡት የውጭ ኩባንያዎች አቅም ማሳያ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር እነዚህ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኩባንያዎችን ከነባር የአገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጋር በማነፃፀር ልዩነቱን ለማሳየት ተሞክሯል፡፡

ዶ/ር አርከበ እንደሚጠቅሱት፣ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው የፈጠረው የሥራ ብዛት ለ53 ሺሕ ሰዎች ብቻ እንደነበር በማስታወስ፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግን 60 ሺሕ ሠራተኞች መቅጠር መቻሉ ከብልጫዎቹ አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ 60 ሺሕ ሰዎችን መቅጠር መቻል በራሱ በፓርኩ ያሉ ፋብሪካዎችን አቅም ያሳያል ብለዋል፡፡ አያይዘውም የወጪ ንግዱን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ የነባሮቹ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢ 180 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር ብለዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ግን የኢንዱስትሪ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ሲያመርት የጨርቃጨርቅን የወጪ ንግድ ገቢ በአሥር እጥፍ በማሳደግ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያደርሰው ተናግረዋል፡፡

በሌሎች ፓርኮች የሚመረቱት ሲታከሉበት የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ መጠን ስለሚያድግ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአገሪቱ የወጪ ንግድ ማደግ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ድርሻ ከአምስት በመቶ በታች በመሆኑ፣ በአሥር ዓመት ውስጥ በአራት እጥፍ ማደግ እንዲችል ታቅዷል፡፡

ከ12 በመቶ ያልበለጠውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በአራት እጥፍ ለማሳደግ ይፈለጋል፡፡ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንግድ ሚኒስቴር የ11 ወራት ሪፖርትም የወጪ ንግዱ አፈጻጸም 41 በመቶ ጉድለት አሳይቷል፡፡ ዶ/ር አርከበ ግን እነዚህ ፓርኮች ይህንን መለወጥ ይችላሉ እያሉ ነው፡፡

‹‹በወጪ ንግድ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ሰብረን ላለመግባታችን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሚገባ አለማደጉ የፈጠረው ማነቆ ነው፤›› ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ ዘርፉ ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ከመሆኑም በተጨማሪ አምራቾች አሉባቸው ያሉቸውንም ጉድለቶችና ችግሮችም አብራርተዋል፡፡ አንድ አምራች የንግድና የኢንቨስትመንት የምዝገባ ሠርተፍኬት ወስዶ፣ ቦታ አግኝቶ፣ ግንባታ ጀምሮ ወደ ማምረቱ ሥራ እስኪገባ ድረስ በትንሹ አምስት ዓመት እንደሚወሰድበት ገልጸዋል፡፡ የምዝገባ ሠርተፍኬት ካገኙ በኋላ መሬት ለማግኘት ቢያንስ ሁለት ዓመት እንደሚፈጅ፣ መሬት ለማግኘት ያለው ሒደትም ሙስና እንዳለበት አስታውሰዋል፡፡

‹‹መሬት ካገኙ በኋላ ፋይናንስ ማፈላለግ ስለሚኖርባቸው፣ ለሕንፃ ግንባታውና ለማሽነሪ ጭምር የሚፈልጉትን ገንዘብ አግኝተው ወደ ግንባታ ለመግባት ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ይፈጅባቸዋል፤›› በማለት አንድ አምራች ከምዝገባ እስከ ማምረት ሥራ ድረስ የሚገጥሙትን ውጣ ውረዶች አስቀምጠዋል፡፡

ግንባታው ከተጠናቀቀም በኋላ ቢሆን የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አገልግሎት ለማግኘት፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ለማስተካከል ተጨማሪ ጊዜ ይጠይቀዋል ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ አንድ አምራች ወደ ምርት ሥራ ለመግባት አምስት ዓመት ይፈጅበታል ብለዋል፡፡ መንግሥት ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እንዲገባ ውሳኔ ላይ ከደረሰባቸው ምክንያቶች አንዱም ይህ ችግር ነው ተብሏል፡፡ ስለዚህ አምራቾች እንደ ሐዋሳ ባሉ ፓርኮች ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ከሆኑ፣ ሁሉም ነገር ተመቻችቶ ስለሚጠብቃቸው፣  ስለመሠረተ ልማት ግንባታ ወጪ ሳያስቡ፣ ማሽነሪ ተክለው በአምስት ወይም በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ምርት ሥራ መግባት ያስቻለቸዋል፡፡

በፓርኩ ውስጥ መሬት በነፃ የሚሰጥ መሆኑም አንዱ ማበረታቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያለ ምንም ውጣ ውረድና ከሙስና በነፃ ሁኔታ ሥራቸውን እንዲሠሩ ያስችላቸዋል፡፡ በሐዋሳና በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚያመርቱ ኩባንያዎች ሌላ ልዩ ዕድል መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡ ይኸውም ያመረቱትን ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ለማስገባት ሲጥሩ ይገጥሟቸው የነበሩ ማነቆዎችን ለማስቀረት የሚያስችሉ አሠራሮች በፓርኮቹ ውስጥ ይዘረጋሉ፡፡

በዚህ ረገድ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡ እንደ ምሳሌ የተነሳው ደግሞ በአንድ ማዕከል ለውጭ ዜጎች በፓርኩ ውስጥ ቪዛ መስጠት ማስቻሉ ነው፡፡ በፓርኩ ውስጥ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎችና ባለሀብቶች ረዘም ላለ ጊዜ የሚገለገሉበት ቪዛ ይሰጣቸዋል፡፡ ለሙያተኞችና ለማኔጅመንት አባላት የሦስት ዓመት፣ ለባለሀብቶች ደግሞ እስከ አምስት ዓመት የሚያገለግል ቪዛ ይሰጣል ተብሏል፡፡ ከሎጂስቲክስና ከፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት አንፃርም የታሰበበት አካሔድም ተወጥኗል፡፡ በምን መልኩ የሚለውን በግልጽ ባያብራሩም፣ በመንግሥት አገልግሎቶች ላይ መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ በሎጂስቲክስ፣ በጉምሩክና በብሔራዊ ባንክ አሠራሮች ላይ ለውጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡

‹‹ያለ ተደራሽ የፋይናንስ አገልግሎት ኢትዮጵያ ተመራጭና ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ልትሆን አትችልም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ባንኮች ራሳቸውን በአዲስ መልክ በማደራጀት፣ ዓለም ከደረሰበት ዘመናዊ አገልግሎት ጋር ማስተዋወቅ አለባቸው በማለት አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በእነዚህ ዘርፎች አሠራር ላይ ያሰበውን ለውጥንና የተመቻቸ የቢዝነስ ኢንቨስትመንት የመፍጠር ዓላማ እንደያዘና ከዋናው የመንግሥት ዓላማ ጋር ማስተሳሰር እንደሚኖርበት የጠቀሱት ዶ/ር አርከበ ሲሆኑ፣ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2025 ኢትዮጵያ ዋነኛ የአፍሪካ ማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚሻም ተናግረዋል፡፡

የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ፓርኮቹ

መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የንግድ ኅብረተሰብ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በእጅጉ በመራቁና ፍላጎቱ የተቀዛቀዘ በመሆኑ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ብቻ የተተወ አስመስሎታል፡፡ የዕውቀትና የፋይናንስ እጥረት እንደምክንያት ቢጠቀስም፣ አቅሙም ኖሯቸው ወደ ማኑፋክቸሪንግ መስክ ለመግባት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች አቅማምተዋል፡፡ መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ በሚፈለገው ደረጃ እገዛ አላደረገም የሚለው ወቀሳም ይሰነዘራል፡፡

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የገቡት በሙሉ የውጭ ኩባንያዎች ብቻ መሆናቸው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ በምን ደረጃ እንደሚገኝ ያሳየ ነው ቢባልም ዶ/ር አርከበ ግን ኢትዮጵያውያን ወደዚህ ሥራ ዘርፍ እንዲገቡ ለማድረግ  የተለያዩ አቅጣጫዎች መታሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ወደ ማኑፋክቸሪንግ የማይገቡበት ዋነኛ ምክንያት ግን ማኑፋክቸሪንግ አክሳሪ በመሆኑ ነው በማለት ያከሉት ዶ/ር አርከበ፣ አክሳሪ የሚሆኑበትም ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው ብለው ካስቀመጡት ውስጥ የፋብሪካ ምርት ሲጀምሩ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚያጋጥማቸው መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ከባንክ በቀላሉ ብድር ማግኘት የማይቻል መሆኑም ወደ ኪሳራ ከሚገፋቸው ምክንያቶች ውስጥ ተካቷል፡፡ የሚፈልጓቸውን መሠረተ ልማቶች የሚያገኙ በመሆኑም እኚህ ኢትዮጵያውያን የምርት ሒደታቸውን አስፋፍተው በማኑፋክቸሪንግ ሊያድጉ አይችሉም በማለት አብራርተዋል፡፡

ሆኖም የቀደሙት ልምዶችን በማየት እንዲህ ያለውን ሒደት ለመፍታት አንዱ ዘዴ ነባሮቹም ሆኑ አዳዲሶቹ አምራቾች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እንዲገቡ ማድረግ ተብሏል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ከገቡ የኤሌክትሪክ ችግር አያጋጥምም፡፡ የጉምሩክ መጓተትና ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥማቸው ወደ ፓርኩ መግባት አንድ መፍትሔ ይሆናል ተብሏል፡፡ ስለዚህ ከ15 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቦታ ለኢትዮጵያውያን እንዲሆን ስለመታሰቡ ተገልጿል፡፡

ለአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ተጨማሪ ልዩ ድጋፍ በማድረግ በፓርኩ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደ ዋነኛ ማነቆ ሆኖ የቆየውን የፋይናንስ፣ የክህሎትና የቴክኒክ አቅም እንዲሁም የገበያ ልማት ናቸው፡፡ እነዚህን ሦስት ጉዳዮች ለመፍታት መንግሥት በሁለት መንገድ ችግሩን ለማቃለል እንዲያስብ ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህም በአንድ በኩል መሠረተ ልማት የተሟላለት ማምረቻ ሕንፃ ስለሚያገኙ እስከ ስልሳ በመቶ የሚሆነው ካፒታል ኢንቨስትመንት ይቀንስላቸዋል፡፡ ለማሽነሪና ለሥራ ማስኬጃ የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ እስከ 85 በመቶ በብድር ተመቻችቶላቸዋል፡፡

ይህ አዲስ ፖሊሲ እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር አርከበ፣ ሌሎች አገሮች በዚህን ያህል ደረጃ ድጋፍ እንደማያደርጉም ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይህንኑ ሐሳብ በማጠናከር በዘርፉ ለሚሳተፉ ባለሀብቶች ያልተለመደ ልዩ ዕድል ማመቻቸቱን  ተናግረዋል፡፡ የቴክኒክና የክህሎት ችግሮቻቸውን እንዲፈቱም ሥልጠና ወሳኝ በመሆኑ፣ መንግሥት ውሳኔ ላይ ከደረሰባቸው አበረታች ዕርምጃዎች መካከል በማኑፋክቸሪንግ ወደ ፓርኩ የሚገቡ አገር በቀል ኩባንያዎች ለሥራቸው የሚያስፈልጓቸውን ብቁ የሰው ኃይል እንዲያገኙ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለማሠልጠን ከፈለጉ የሚያስፈልጋቸው ወጪ፣ (የውጭ ምንዛሪን ጨምሮ) በመጀመሪያው ዓመት 85 በመቶን መንግሥት ለመሸፈን የተዘጋጀ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ዓመት ላይ 75፣ በሦስተኛው ዓመት 50 በመቶ በአራተኛው ዓመት 25 በመቶ የሚሆነውን ወጪ መንግሥት እንዲሸፍንላቸው ተወስኗል ተብሏል፡፡ በአምስተኛው ዓመት ግን አምራቾቹ ለሠልጣኞቻቸው የሚያወጡትን ወጪ ሙሉ በሙሉ ይሸፍናሉ፡፡ እንደ ሥልጠና ወጪው ሁሉ ኢትዮጵያውያን አምራቾች የውጭ ባለሙያ ሲቀጥሩ በተመሳሳይ ለአራት ዓመታት ከ25 እስከ 85 በመቶ የሚደርሰውን ወጪያቸውን ይሸፍናል፡፡

18ቱ ጀማሪዎች

ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ኢትዮጵያ አግኝታዋለች ያሉን ከፍተኛ ውጤት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ዕድገትን በማሳካት ረገድ የውጭ ኢንቨስትመንት የማይተካ ሚና ያለው ዓይነተኛ መሣሪያ እንደሆነ፣ ይህም የመንግሥታችን ጽኑ ቅኝት መሆኑን ላስገነዝብ እወዳለሁ፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ላይ ምንም ብዥታ ሊኖር እንደማይገባ ያስመዘገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይ በእነዚህ ፓርኮች ውስጥ ምርጥ የሚባሉ የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ ማድረግ ላይ መንግሥት ብዙ መልፋቱንና ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ወደ ሥራ የገቡት ከ18ቱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መረጣ ምርጥ የሚባሉ ኩባንያዎችን ከማግኘት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በእርግጥም በፓርኩ ውስጥ የገቡት ኩባንያዎች በዓለም ደረጃ የሚታወቁ ምርቶችን የሚያቀርቡ ናቸው፡፡

እንደ ዶ/ር አርከበ ገለጻ ፒቪኤች የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከ130 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ፒቪኤች ኩባንያ፣ በዓለም ምርጥ አልባሳት ከሚያመርቱ ትልልቅ ኩባንያዎች አንዱ ነው፡፡ በ40 አገሮች ውስጥ ከ30,000 በላይ አምራቾች ጋር ይሠራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ከ8.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስመዘገበ ኩባንያም ነው፡፡ ፒቪኤች ታዋቂ የሆኑት ካልቪን ክሌን፣ የቶሚ ሃልፊገር፣ የቫን ሂውን፣ የአሮው፣ የስፒድ፣ የዋርነርስና ኦልጋ ብራንዶችን ጨምሮ የበርካታ ምርቶች ባለቤት ስለመሆኑ የኩባንያው ታሪክ ያሳያል፡፡

ፒቪኤች በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሥራት ዘርፉን ለማገዝና ወደፊት ለማራመድ ስለመነሳቱ የኩባንያው ማኔጅመንት አባል፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ባለንብረቶች ማኅበር ሊቀ መንበር ሚኒስትር ቢል ማክሬን ተናግረዋል፡፡ ፒቪኤች በፓርኩ የተመረተውን የመጀመሪያውን ምርቱን በግንቦት ወር ለውጭ ገበያ አቅርቧል፡፡

የሐዋሳ ፓርክን የተቀላቀለው ሌላው ስመ ጥር ኩባንያ ደግሞ ሬይመንድ ሲልቨርስፓርክ አፓረል ኩባንያ የተባለው ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1925 በሕንድ የተመሠረተው ይህ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ከ25,000 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ የህንድ ምርጥ ኩባንያ በመባል በተደጋጋሚ ለመመረጥ የበቃው ሬይመንድ፣ በእስያም ምርጥ የሥራ ቦታ አላቸው ተብለው ከተመረጡ ኩባንያዎች አንዱ ነው፡፡ ራይመንድ፣ ራይመንድ ፕሪምየም፣ ፓርክ አቬኑ፣ ፓርክ አቬኑ ከለር ፕላስ፣ ፓርክስና በመሳሰሉት ብራንዶች ይታወቃል፡፡

ዉሺ የተባለው የቻይና ኩባንያ በጨርቃ ጨርቅ፣ በስፌትና በመሳሰሉት ይታወቃል፡፡ ከኩባንያው ደንበኞች መካከል ፒቪኤች፣ ጋፕ፣ ጃክ ፔነር፣ ታርጌት የተባሉት በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡

ሃይድራማኒ ጋርመንት ኩባንያ ዋና መሥሪያ ቤቱ በሲሪላንካ ሲሆን፣ ከ100 ዓመት በላይ ልምድ አለው፡፡ በስድስት አኅጉራት ውስጥ ግንባር ቀደም ልብስ አምራች ሲሆን፣ ለትልልቅ ብራንዶችም ያቀርባል፡፡ በተለይ የሴቶችን ፖሎ ቲሸርቶችና የውስጥ አልባሳት እያመረተ ይገኛል፡፡ እስካሁንም ከፓርኩ 25 ኮንቴነር ምርትን ኤክስፖርት አድርጓል፡፡

ኢንዱስትሪ ፓርኩና የሰው ኃይል

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለሰው ኃይል ቅጥር ሰፊ ዕድል ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ ዶ/ር አርከበ እንደገለጹትም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አስተማማኝ የሆነ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሥራ ዕድል እንዳለውም የሚታመንበት በመሆኑ እየተሠራበት ነው፡፡

ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ዕድገት የሚኖራት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እያደገ የሚመጣውን የሥራ ፍላጎት ለማሟላት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ አስፈላጊነት ጎልቶ ይታያል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በየዓመቱ 100 ሺሕ የሚሆኑ ምሩቃን የሚያወጡ ሆነዋል፡፡ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የ12ኛ የቴክኒክ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ይመረቃሉ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የሥራ ዕድል መፈጠር ካለበት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ዶ/ር አርከበ አስረድተዋል፡፡ በግብርና ብቻ ይህንን የሥራ ፍላጎት መሸፈን የማይቻል ስለሆነ በማኑፋክቸሪንግ በአሥር ዓመት ለሁለት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር 60 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ አሁን እስከ አሥር ሺሕ የሚደርሱ ሠራተኞችን ይዟል፡፡ ሠራተኞችን ለመቅጠር የተቋቋመ አላክም ወደ 30 ሺሕ የሚጠጉ ዜጎችን መዝግቦ እየጠበቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስመ ጥር ኩባንያዎች የከተሙበት ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ ከሠራተኞች ደመወዝ ጋር ተያይዞ ከሠራተኞች አንዳንድ ጥያቄዎች እየተሰሙ ነው፡፡

ብዙ ወጣቶች በተለይም ሴቶች በዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሥራ በጀመሩ ኩባንያዎች ውስጥ እየሠሩ ቢሆንም ለሠራተኞች ዝቅተኛ እየተባለ ነው፡፡ ስሟን ያልገለጸችው የ19 ዓመት ወጣት በህንዱ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥራ እየሠራች ነው፡፡ ሥራውን ከጀመረች ሁለተኛ ወሯ ነው፡፡ ሥራዋ አድካሚ ቢሆንም ሥራ በመገኘቱ መደሰቷን ትገልጻለች፡፡ ነገር ግን የሚከፈላት ደመወዝ ሕይወቷን ለመምራት የሚያስችል ስለመሆኑ ያሳስባታል፡፡

እንደ እሷ ገለጻ ደመወዟ 650 ብር ነው፡፡ ከአንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞች ጋር ተደምሮ በወር 1,002 ብር ይደርሳታል፡፡ ገንዘቡ እጅግ በጣም ትንሽ በመሆኑ በዚህ ደመወዝ እንዴት መቀጠል እንዳለባትና ምን ማድረግ እንደሚኖርባት ግራ ስለመጋባቷም ጠቅሳለች፡፡ ነዋሪነቷ ሐዋሳ ከተማ ውስጥ ባለመሆኑ ቤት መከራየት ስላለባትና በዚህ ደመወዝ ደግሞ ለብቻዋ መከራየት ስላልቻላት እሷ ጋር በተመሳሳይ ሥራ ላይ ከሚኖሩ ሁለት ጓደኞቿ ጋር በ600 ብር በጋራ በተከራዩት ቤት እየኖሩ ነው፡፡ የተከራዩት ቤት ከፓርኩ የሚርቅ በመሆኑ ረዥም ጉዞ ይጠብቃቸዋል፡፡ ጉዞውም ወጪ እንዳለው የጠቀሰችው ይቺ ወጣት ክፍያው ሊስተካከል ይገባል ትላለች፡፡ በአብዛኛው ዝቅተኛ የሥራ መደብ ላይ ያሉ ሠራተኞች ተመሳሳይ አስተያየት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ 650፣ 750፣ 1,002 እና 1,200 ብር የሚከፈላቸው ሠራተኞችም አሉ፡፡ ይህ ክፍያ ለምንም አሁን ካለው የመኖር ዋጋ ጋር አልተጣጣመላቸውም፡፡ ሰርቪስ የሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች የመኖራቸውን ያህል ለሠራተኞች ማጓጓዣ ያላዘጋጁም እንዳሉ ካነጋገርናቸው የፓርኩ ሠራተኞች ለመረዳት ተችሏል፡፡ በእርግጥ የትራንስፖርት የሚከፍሉም አጋጥመውናል፡፡ ደመወዙ በቂ ባለመሆኑ ኢንዱስትሪው በተገነባበትና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አጥር ይዘው በላስቲክ የተሠሩ ምግብ ቤቶች ከዚያ ያማረ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚወጡ ደንበኞቻቸውን በአቅማቸው ያስተናግዳሉ፡፡

ቀጣዮቹ ፓርኮች

እነዚህም ከሁለት ዓመት በፊት ለአገልግሎት የበቃው ቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን፣ ወደ አገልግሎት የገባ ሁለተኛው የኢንዱስትሪ ፓርክ ሆኗል፡፡ የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው የተጠናቀቁ በመሆኑ በዚህ ወር መጨረሻ ይመረቃሉ፡፡ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ መስከረም 2010 ግንባታቸው እንደሚጠናቀቁ ዶ/ር አርከበ ተናግረዋል፡፡ በፋርማቲውካል ዘርፍ ላይ የሚሠራው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጥር 2010 ዓ.ም. ለምርት ዝግጁ ይሆናል ተብሏል፡፡

የቦሌ ለሚ (ሁለት) በግንባታ ላይ ሲሆን፣ በጥር 2010 ወደ ምርት ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በጅማና ባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ግንባታ የገቡ ሲሆን፣ በሚያዚያ 2010 ይጠናቀቃሉ፡፡ የአራርቲ የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ በቅርቡ የግንባታቸው ኮንትራት ይፈረማል፡፡ አላጌ (ዝዋይ) አይሻ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም ደግሞ ሁናን የተባለውና በአዳማ የታሰበው ሌላ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በቀጣዩ የበጀት ዓመት ግንባታቸው ይጀመራል፡፡ ከእነዚህ ውጭ በሰመራ አካባቢ ይገነባል ተብሎ የሚጠበቀው አዲስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ጥናት እንደሚጀመር ከዶ/ር አርከበ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ረፖርተር አማርኛ -ችዳዊት ታዬ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
የ26 ዓመት ወጣት መንገድ በመጣሱ ተደብድቦ ለሞት ተዳረገ፤ ፖሊሶቹ ታስረዋል ተብሏል

የ26 ዓመት ወጣት በፖሊሶች ድብደባ ምክንያት ሀየወቱ ማለፉ ታወቀ፤ አምስት የሚጠጉ ፖሊሶች ነወጣቱ ህይወት ማለፍ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር እንደዋ...

Close