Skip to content

ያልከፈለ ስደት

 

የጠዋቷ ፀሐይ ፈንጥቃ ሙቀቷን ካጋራችው የሕንፃው በረንዳ አንዲት የተከናነበች ሴት ቡና ትቆላለች፡፡ ከፊት ለፊቷ የተወሰኑ መቀመጫዎች በክብ ተደርድረዋል፡፡ ዓረብ አገር ለሥራ ሄደው ገንዘብ ሳይሆን የአዕምሮ ሕመም ይዘው የተመለሱ ኢትዮጵያውያት የሚጠለሉበትን ሕንፃ ቃኝተን ወደበረንዳው ስንመለስ፣ የተወሰኑ ሴቶች ቡናውን ከበው ተቀምጠው ነበር፡፡ አንዷ ደግሞ የምትፈልገው ያለ ይመስል አንዴ ቤት ውስጥ አንዴ ውጭ ትንጎራደዳለች፡፡ ቤት በማፅዳት ላይ የነበሩት ስሟን ሲጠሩ ‹‹እ›› ከማለት ውጪ ብዙም ትኩረት አትሰጥም፡፡ ከክፍል ክፍል መዟዟር፣ በንግግር ጊዜ ዝም ማለት፣ መጨነቅ፣ ምንም አለመናገር ከመካከለኛው ምሥራቅ የአዕምሮ ሕመም ገጥሟቸው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ተቀብሎ የሚያስተናግደው የአጋር ኢትዮጵያ የዕለት ተዕለት ገጠመኝ መሆኑን በአጋር ኢትዮጵያ ኬዝ ማናጀሩ አቶ ፍሥሐ መለሰ ይናገራሉ፡፡

በማዕከሉ ከሚገቡት አንዳንዶቹ ስለመጡበት አካባቢና ስለኖሩበት የመካከለኛው ምሥራቅ አገር የሚናገሩ ቢኖሩም፣ ከአዕምሮ ሕመማቸው ከፍተኛነት የተነሳ ምንም የማያስታውሱ፣ ቤተሰቦቻቸውን ማወቅ የሚያዳግታቸውና ራሳቸውን እንኳን መግለጽ የማይችሉ ያጋጥማሉ፡፡ በማዕከሉ ገብተው ሕክምና ካገኙ በኋላ ደግሞ አገግመው ከቤተሰቦቻቸው የሚቀላቀሉ ወይም ለራሳቸው የሚሆን ሥራ የሚያገኙም አሉ፡፡ በማዕከሉ የአዕምሮና አካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሴቶችን መረጃ ከያዘው ማኅደር የአንዷ ይህንን ያሳያል፡፡

ወጣቷ ከነበረችበት ዱባይ ኢትዮጵያ ስትገባ የዘጠኝ ወር እርጉዝ ብትሆንም፣ የአዕምሮ ሕመሟ እርግዝናዋንም ሆነ ሌላ ነገር ከማስታወስ ጋርዷት ነበር፡፡ በሁለት እጆቿ ሆዷን እየደበደበች ሆዴ ውስጥ የተቀመጠ ነገር አለ በማለትም ትጮህ ነበር፡፡ እርጉዝ መሆኗ ሲነገራት እንኳን አላመነችም፡፡ አገሯ የገባችው ግን የዘጠኝ ወር ነፍሰጡር ሆና ነበር፡፡ አገሯ በገባች በሦስተኛው ቀን የተጠለለችበት አጋር ኢትዮጵያ ባመቻቸው የሕክምና ዕርዳታ የወለደች ሲሆን፣ በተከታታይ በተደረገላት የአዕምሮ ሕክምናም ራሷን ለማወቅ ትችላለች፡፡ ወደ ዱባይ የሄደችውም እናትና አባቷ በሕፃንነቷ በመሞታቸውና በተወለደችበት ቀዬ ከአምስተኛ ክፍል በላይ መማር ባለመቻሏ፣ በኋላም አጎቷ ጋር አዲስ አበባ ብትመጣም ትምህርቷን መግፋት ባለመቻሏ ዱባይ ሄዳ ሠርታ ገንዘብ ለማግኘት ነበር፡፡ አጎቷ ለደላላ ስምንት ሺሕ ብር ከፍሎ የላካት ሲሆን፣ የተመለሰችውም እንደወጠነችው ገንዘብ ይዛ ሳይሆን የአዕምሮ ሕመምና ልጅ ነበር፡፡

በአጋር ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የሚገኙት 30 ያህል ሴቶች የተለያየ ታሪክ ያላቸው ቢሆንም፣ አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ እንሠራለን ብለው ከሄዱባቸው መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የተመለሱት ገንዘብ ይዘው ሳይሆን የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸው፣ የአዕምሮ ሕምተኛ አሊያም አካል ጉዳተኛ ሆነው መምጣታቸው ነው፡፡

አቶ ፍስሃ እንደሚሉት፣ 100 ከዓረብ አገር ተመላሽ የአዕምሮና ሌላም ሕመም ያለባቸውን በአንዴ ተቀብሎ ምክር፣ ሕክምና፣ ሥልጠናና ከቤተሰብ ማገናኘት ላይ የሚሠራው አጋር ኢትዮጵያ፣ ራሱን መልሶ ካደራጀበት ከ2002 ዓ.ም. በኋላ የአዕምሮና ተጨማሪ የጤና እክል የነበረባቸውን 3,900 የዓረብ አገር ተመላሾች ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡

ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሄዱ ኢትዮጵያውያትን ሥነልቦናዊና ማኅበራዊ ችግሮቻቸው ምንድን ናቸው በሚለው ዙሪያ የሠሩትን ጥናት በአፍሪካን ኤንድ ብላክ ዳያስፖራ፡ አን ኢንተርናሽናል ጆርናል (African and Black Diaspora፡ An International Journal) ለማሳተም በመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚገኙት የቤዝና ካውንስሊንግና ሥልጠና ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አሰፋች ኃይለሥላሴ፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ሴቶች ላይ የሚታየው የአዕምሮና የሥነ ልቦና ችግር የከፋና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

Related stories   ሲሲሊ፥ ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን

ወ/ሮ አሰፋች ጥናታቸውን ጠቅሰው እንደነገሩን፣ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በሚሰጡት ተስፋና አማላይ ግፊት ተማርከው ወደ ዓረብ አገር የሚሰደዱ ሴቶች፣ የተነገራቸውና የሚገጥማቸው የተለያየ በመሆኑ ለሥነ ልቦና ብሎም ለአዕምሮ ሕመም ይጋለጣሉ፡፡

ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) መስፈርትን ተከትሎ ከአምስት ዓመት በፊት የተሠራው ጥናትም ያመለከተው፣ ሴቶቹ ወደ መካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ከመሄዳቸው በፊት ግንዛቤና ዝግጁነት እንደሌላቸው፣ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ሰንቀውና ቤተሰብ እንረዳለን ብለው በተጓዙበት ልክም ውጭ ሲደርሱ ያጋጠማቸው ፍጹም ያልጠበቁት መሆኑ ለአዕምሮ ችግር አጋልጧቸዋል፡፡

የሥራና የገንዘብ እጦት ለመሰደድ ምክንያት ከሆኑት ምክንያቶች ከቀዳሚዎቹ ሲመደቡ፣ እነዚህን ችግሮች ለመሙላት ከአገር ውስጥ የሚጀምረው የጉዞ ሒደትም በውጥረት የተሞላ ነው፡፡ ለመወሰን መጨነቅ፣ የሕገወጥ አዘዋዋሪዎችን ቃል ሰምቶ ስለጉዞዋቸው ለቤተሰብ በመንገርና ባለመንገር መሀል መብሰልሰል፣ ለደላላ ገንዘብ ለመክፈል መቸገርና በብዙ ውጣ ውረድ ማግኘት ከአገር ከሄዱ በኋላ ጥሩ አሠሪ፣ ምግብና ሕክምና አለማግኘት ለአካላዊ፣ ወሲባዊና ሥነ ነልቦናዊ ጥቃት መጋጥም ሴቶቹን ለሥነልቦናና ለአዕምሮ ሕመም ከዳረጉት ይጠቀሳሉ፡፡

በማያውቁት አገር፣ ባህልና ቋንቋ ውስጥ መገኘትም ለአዕምሮ ችግር ያጋልጣል፡፡ በጥናቱ የተሳተፉትም በቀላሉ መከፋት፣ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ የታየባቸው ሲሆን፣ ይህ የመጣውም የጠበቁትን ካለማግኘት ነው፡፡ ከአዕምሮ ጤና እክል ጎን ለጎንም የአካል ጉዳት የገጠማቸው አሉ፡፡

ወ/ሮ አሰፋች በጥናቱ ከተሳተፉት አንዷ ያለችውን እንዲህ ያስቀምጡታል፡፡ ‘ከመሄዴ በፊት ችግሬ ሥራ ማጣትና ገንዘብ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የጤና ችግር ታክሎልኛል፡፡ ከዚህ ስሄድ ቃል የተገባልኝ በታወቀ ሆቴል እንግዳ ተቀባይ እንደምሆን ነበር’ ብላለች፡፡

የመገለልና የብቸኝነት ስሜት በጥናቱ የታየ ሌላው የሥነ ልቦና ችግር ነው፡፡ ሰዎች አይረዱንም፣ ለቤተሰብ ገንዘብ ይዘን አልመጣንም በሚልም ከማኅበራዊ ግንኙነታቸው ራሳቸውን ያገለሉ አሉ፡፡ በዓረብ አገር ሁለት ቤተሰብ እያገለገለች የኖረች የጥናቱ ተሳታፊ የዚህ ችግር ሰለባ ነበረች፡፡ ወ/ሮ አሰፋች እንደሚሉት፣ አገሯ ስትመለስ ‘ማንም አይገነዘበኝም፣ ሴተኛ አዳሪነት ሠርታ ይሆናል ይሉኛል’ በሚል ራሷን ለጭንቀት አጋልጣለች፡፡

ነገሮች ከጠበቁት ውጪ መሆናቸውም የፀፀትና ግራ የመጋባት ስሜት የፈጠረባቸው ሲሆን፣ ተቀባይነት ያለማግኘት ሥጋትም ታይቶባቸዋል፡፡ ‘ማኅበረሰቡ እንደሌላው አያየንም፣ ዓረብ አገር ሄደን ገንዘብ ይዘን ባለመምጣታችን በቤተሰብም በኅብረተሰቡም ተቀባይነት አይኖረንም’ ብለው ጭንቀት የገቡ መኖራቸውም በጥናቱ ታይቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉት ልጆች አማካሪ አግኝተው ካልታከሙ ችግራቸው እየተባባሰ ሄዶ ከፍተኛ የአዕምሮ ሕመም ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ፣ ይህ እንዳይሆን የተሻለ ሕክምናና ክትትል እንዲሁም የቤተሰብ ድጋፍ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

Related stories   ሲሲሊ፥ ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን

የኢትዮጵያ አዕምሮ ሕክምና ማኅበር በየዓመቱ በሚያደርገው ሳይንሳዊ ጉባዔ በተመረጠ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፓናል ውይይት የሚያደርግ ሲሆን፣ ዘንድሮ የተመረጠውና ከሳምንታት በፊት ውይይት የተደረገበት ስደትና የአዕምሮ ጤና የሚል ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና ጥናት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሰለሞን ተፈራ፣ ኢትዮጵያውያን የአዕምሮ ሐኪሞች ወይም ሳይኪያትሪስቶች ከስደት ተመላሾች የገጠሟቸውን የአዕምሮ ጤና ችግሮቻቸውን በመለየት የሕክምና አገልግሎት የሚያደርጉ ሲሆን፣ እንደሙያ ማኅበርም አባላትን በማስተባበር ለከስደት ተመላሾች በሙያቸው የሚቻለውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ባላደጉ አገሮች እንዲሁም በአፍሪካና በሌሎችም አኅጉሮች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ስለአዕምሮ ሕመም የየራሳቸው አመለካከት ቢኖራቸውም እንደ ባለሙያ የአዕምሮ ጤና ችግር የሚመጣው ስሜታችንን፣ አስተሳሰባችንንና ባህሪያችንን ከሚቆጣጠረው አንጎል ነው፡፡ ይህ ክፍል ሲጎዳ የሚታዩ የአዕምሮ ጤና ችግሮችም እንደ ማንኛውም የጤና ችግር ሊታከሙ ይችላሉ ይላሉ፡፡

ከአጋር ኢትዮጵያ የሰማነውም ከየመን፣ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከሌሎች ዓረብ አገሮች ለሥራ ብለው ሄደው ጥሪት ሳይሆን የአዕምሮ ሕመም ይዘው የተመለሱ ሕሙማንን በመድኃኒትና በምክር አገልግሎት ከችግራቸው እንዲያገግሙ ብሎም ጤናቸው ተመልሶና ሥልጠና ወስደው ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግ መቻሉን ነው፡፡

ዶ/ር ሰለሞን እንደሚሉት፣ የአዕምሮ ሕሙማንን ሕክምና በመስጠት ችግራቸውን ከነበረበት መቀነስ ብሎም ሕመም ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ይቻላል፡፡ ሕክምናው በጊዜው ከተሰጠም ውጤታማነቱ ይጨምራል፡፡

እንደ  ዶ/ር ሰለሞን ስደት ለአዕምሮ ሕመም አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ ለስደት መሠረታዊ ምክንያቱም ሥነ ልቦናዊ ጫና የሚፈጥር ክስተት ነው፡፡ አንድ ሰው በሰላምና በፍቅር ከሚኖርበት ማኅበረሰብ ያለምክንያት ወጥቶ አይሰደድም፡፡ ኢኮኖሚያዊ፣ የደኅንነት ሥጋትና ሌሎችም ሁኔታዎች ለስደት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ከነበረበት ማኅበረሰብ መውጣቱ በራሱ ጫና ይፈጥራል፡፡ ወደ አዲስ ማኅበረሰብ ለመቀላቀልና ለመላመድ የሚያደርገው ትግልና የሚወስደው ጊዜ ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጫና የሚፈጥር ነው፡፡

በርካታ ዜጎችም የተመቹ በሚባሉት እንደ ምዕራብ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ ሄደው የኢኮኖሚ ችግር ባይኖርባቸውም በሚደርስባቸው የባህል ግጭትና አጠቃላይ ከነበሩበት አኗኗር መለየት ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጫና ውስጥ ከቷቸው ለበርካታ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ሲጋለጡ ይስተዋላሉ፡፡ ለዲፕረሽንና ከበድ ላለ የአዕምሮ ጤና ችግርም ይጋለጣሉ፡፡ ስደት ውስጥ ካሉትም ራሳቸውን የሚያጠፉት ቀላል አይደሉም፡፡

ስደተኞችና ስደተኛ ባልሆኑ ሰዎች መካከል እንግሊዝ አገር የተደረገ ጥናትን ጠቅሰው እንደገለጹትም፣ ስደተኞቹ ስደተኛ ካልሆኑት፣ ሳይኮሲስ ለተባለው ከፍተኛ የአዕምሮ መቃወስ የመጋለጥ ዕድላቸው በሁለት እጥፍና ከዚህ በላይ ይጨምራል፡፡ ይህ ማለት አዲሱ ነባራዊ ሁኔታ በአዕምሯቸው ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር እስከ ሳይኮሲስ የሚደርስ ከባድ የአዕምሮ መቃወስ አስከትሎባቸዋል፡፡ ይህም ስደት ለአዕምሮ ጤና ጠንቅ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡

Related stories   ሲሲሊ፥ ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን

በኢትዮጵያም ሲታይ ከመካከለኛው ምሥራቅ ተመልሰው የሚመጡ በርካታ ዜጎች ለበርካታ የአዕምሮ ጤና ቀውሶች ይጋለጣሉ፡፡ ራስን የማጥፋት ሁኔታም በስፋት በሴቶች ላይ ይታያል፡፡

ራስን ከማጥፋት ጋር ተያይዞ በአጋር ኢትዮጵያ የገቢ ማሰባሰቢያና የኮሙዩኒኬሽንስ ኦፊሰር የነበሩት አቶ ንጉሤ መኮንን በ2007 ዓ.ም. የገጠማቸውን እንዲህ ያስታውሱታል፡፡ ከወሎ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ተጉዛ ለሁለት ዓመታት ያገለገለች ወጣት፣ ኢትዮጵያ ስትመጣ ራሷን አታውቅም ነበር፡፡ ከፍተኛ የአዕምሮ ሕመም ስለነበረባትም ድርጅቱ እንደገባች አማኑኤል ሆስፒታል ነበር የተወሰደችው፡፡ የሕክምና ክትትል ሲደረግላት ከነበራት ሁኔታ እየተሻላት መጣ፡፡ ለውጡ የታየው በገባች በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ አንድ ቀን በየቢሮው እየገባች የጥፋተኝነት ስሜት እንዳለበት ሰው ‘ይቅርታ አድርጉልኝ’ እያለች ሠራተኛውን ሁሉ ጠየቀች፡፡ ይህ ሲሆን ግን እየተሰናበተች ስለመሆኑ የገባው አልነበረም፡፡ እሷ ግን የዛኑ ቀን ሌሊት በረንዳ ላይ ባለ የብረት ፍርግርግ ላይ ሻሿን ተጠቅማ ራሷን አንቃ ተገኝታለች፡፡

አቶ ንጉሤ እንደሚሉት፣ ራስን የማጥፋት ሁኔታ በተሰደዱበት ዓረብ አገር ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ከገቡ በኋላም ከአዕምሮ ሕመማቸው ጋር ተያይዞ ይከሰታል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሠርተን እናገኝበታለን ብለው ከተሰደዱበት አገር ባዶ እጃቸውን መምጣታቸው፣ ህልማቸው መጨንገፉ፣ እምነታቸውን፣ ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን ማጣታቸው ይገኝበታል፡፡

ከስደት ተመላሾች ላይ የሚታዩ የአዕምሮ ጤና እክሎችን ለማከም የማኅበሩ አባላት የሚሳተፉ ሲሆን፣ እንደ ዶ/ር ሰለሞን ገለጻም፣ ከስደት ተመላሾች ላይ በዋናነት ጎልቶ የሚታየው የአዕምሮ ጤና ችግር የድብርት (ድባቴ) በሽታ ነው፡፡ ልዩ ልዩ የጭንቀት ሕመሞች፣ ፖስት ትራውማቲክ ስትረስ ዲዝኦርደር ማለትም ሥነ ልቦናዊ ጥቃትን ተከትሎ የሚመጣ የጭንቀት ዓይነትም ይታያል፡፡ ሳይኮትራውማ የሚባለውና ከአዕምሮ ጥቃት፣ ስብዕናን ከመንቋሸሽ፣ ክብርን ከመነካት፣ ከመደፈር አደጋና ከመሳሰሉ ክብረነክ ጥቃቶች የሚከሰተው ችግርም በተለይ በሴቶች ላይ ይታያል፡፡ ሳይኮሲስ ማለትም ከባድ የአዕምሮ መቃወስ (እብደት) የሚታይባቸው ሴቶች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የስደት አሉታዊ ገፅታው ነው፡፡ ሆኖም ስደትን ማቆም ስለማይቻል በሕጋዊ መንገድ ማስተዳደር የሚቻልበትን አሠራር መዘርጋት ግለሰብን፣ ኅብረተሰብን ብሎም አገርን ይጠቅማል፡፡ ፊሊፒንስ ዜጎቿ በሕጋዊ መንገድ ውጪ ሄደው የሚሠሩበትን ሁኔታ በቅጡ በመዘርጋቷ ለዜጎቿ ጠበቃ መሆን፣ ለአገሪቷም ገቢ ማስገኘት ትችላለች፡፡ 20 በመቶ የአገሪቷ ገቢ ለሥራ ወደ ሌላ አገር ከሄዱ ዜጎቿ የሚገኝም ነው፡፡ ፊሊፒኖች ለሥራ ወደ ውጭ የሚሄዱትም ሠልጥነውና ሠርተፊኬት ይዘው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ይህንን ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲጠናከሩም ወ/ሮ አሰፋች ይመክራሉ፡፡

‹‹ከስደት ተመላሾችን ስናስብ ዓላማቸውን እናስብ›› የሚሉት ወ/ሮ አሰፋች፣ የሄዱበት ዓላማ ራሳቸውንና ቤተሰብን ለመለወጥ፣ እህትና ወንድምን ለማስተማር መሆኑን በማስታወስ፣ ስደቱ በሕገወጥ ድርጊት በመተብተቡ ብዙዎችን ለሥነ ልቦናዊና ለአዕምሯዊ ችግሮች እያጋለጠ ስለሆነ ሕገወጥነትን መግታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

0Shares
0
Read previous post:
ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የዘመናይ አምራችነት በር ከፋች

  በሳምንቱ መጀመሪያ የሐዋሳ ከተማ ከወትሮው ለየት ያለ ድባብ ታይቶባታል፡፡ የከተማዋ የንግድ ቤቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ደጃፎች፣ በከተማዋ ዋና...

Close