ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ ለመላክ የምታደርገው ጉዞ ሲፈተሽ…

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ለውጭ ለመላክ የሚያስችሏትን አምስት ስምምነቶች ተፈራርማለች።

በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በካሉብና ሂላላ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰባት ጉድጓዶች ተቆፍረዋል።

በእነዚህ ስፍራዎች ያለውን የጋዝ ክምችት ጥቅም ላይ ለማዋል ከቻይናው ፖሊ ሲ ጂ ኤል ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

በ2009 መጨረሻ አልያም በ2010 ዓ.ም መጀመሪያ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ የተፈጥሮ ጋዙ በ2009 አልያም 2010 መጀመሪያ ወደ ምርት ይገባል የሚል እቅድ የለም ብለዋል የማዕድን፣ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ቴድሮስ ገብረ እግዚአብሄር።

በ2007 ዓመተ ምህረት መጋቢት ወር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጉዳዩ ዙሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባቀረበው ጥያቄ፥ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱ በ2009 አልያም 2010 ዓ.ም ወደ ምርት ይገባል ማለታቸው አይዘነጋም። ሚኒስተር መስሪያ ቤቱ አሁን ላይ ያስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ቀደም ሲል መንግስት ይፋ ካደረገው ጋር ሲነፃፀር በሁለት ዓመት የዘገየ ነው።

ለምን ዘገየ ለሚለው ጥያቄ ከሚኒስቴሩ የተገኘው ምላሽ “እየተዘጋጀን ያለነው በፈረንጆቹ 2019 ማለትም ከሁለት ዓመት በኋላ ምርቱን ለመላክ ታሳቢ በማድረግ ስለሆነ አልዘገየም” የሚል ሆኗል። መንግስት ይፋ ባደረገው ወቅት ቢሆን አሁን የተፈጥሮ ጋዙ ለምርት መዘጋጀት የሚገባው ምዕራፍ ላይ መድረስ ነበረበት።

ሚኒስቴሩ በተባለው ጊዜ ወደ ምርት ባይገባም ሰባት ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፤ አራት ስምምነቶችንም ከቻይናው ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል።

በቅርቡም የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ጂቡቲ ወደብ ለማድረስ የሚያስችል የማስተላለፊያ ቱቦ ዝርጋታ እንዲካሄድ አምስተኛ ስምምነት ተደርሷል ነው ያሉት አቶ ቴድሮስ። ስምምነቱ ይጸደቅ ዘንድም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ውሳኔ አሳልፏል። የማስተላለፍያ ቱቦ ዝርጋታው በሚቀጥለው አመት መጨረሻ እንደሚጀመር የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ዝርጋታው በአንድ አመት የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ ግንባታ ሲከናወን ከጅቡቲ መንግስት ጋር የሚቀሩ ተጨማሪ ድርድሮችም ይጠናቀቃሉ ብለዋል። የማስተላለፊያ ቱቦው ዝርጋታ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ተጠናቆ የተፈጥሮ ጋዝ ምርት መላክ ሲጀመር በመጀመሪያው አመት እስከ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ተብሏል። በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ካሉብና ሂላላ ተብለው በሚጠሩ ስፍራዎች 4 ነጥብ 7 ትሪሊየን ኪዩቢክ ፊት የተፈጥሮ ጋዝ መኖሩ ተረጋግጦ ወደ ስራ እንደተገባ የተገለጸው ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበር ይታወሳል።

 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *