ገለታው ዘለቀ

የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮችም ሆኑ ዜጎች በጋራ ከመሰረቱት ሃገር ልዩ ጥቅም ፈላጊዎች አይደሉም። ኢትዮጵያውያን በመሬት ዙሪያ በኢኮኖሚ ዙሪያ ለየቡድናቸው ልዩ ጥቅም ( special interest)  ይዘው በአንድ የፓለቲካ ጠገግ ዘንድ ለማረፍ አይስማሙም። አልተስማሙም። ኢትዮጵያውያን ለእንደዚህ ዓይነት ራስ ወዳድ ስምምነት ሃይማኖታዊም ባህላዊም መሰረት የላቸውም። ለእንግዳ እንኳን ቅድሚያ የሚሰጥ ባህል ነው ያላቸው።  ለነገሩ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን እጅግ ብዙ የዓለም ሃገራትም ቢሆኑ በመሬትና በኢኮኖሚ አካባቢ “ልዩ ጥቅም” የሚል ስምምነት በህገ-መንግስታቸው ላይ አያሰፍሩም። ልዩ ጥቅም የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ራሱ ከፍትህ ምንጭ አይቀዳም። ራስን ያስቀደመ ስግብግብ ፍልስፍና በመሆኑ የሰው ልጆች ፓለቲካዊ ጠገግ ሲሰሩ  “በልዩ ጥቅም” አይስማሙም። ቡድኖች አገር ሲመሰርቱና ጠገጉን ሲሰሩ አንዱ ትልቁ ኪዳናቸው የጋራ እኩልነት፣ ፍትህ ነፃነት ናቸው። በጋራ የሚያቆሙት ይህንን ነው።  መንግስትም ዘብ ቆሞ ይህንን እሴት  እንዲጠብቅላቸው ይሻሉ። ይሁን እንጂ በታሪክ አጋጣሚ ብሄርን ለይቶ በኢኮኖሚ ወይም በማህበራዊ ጉዳይ ያልተመጣጠነ እድገት ካለ እነዚህ በአንድ ላይ የሚኖሩት ህዝባች ቀደም ብለው ለፍትህና ለእኩልነት በህገ መንግስታቸው ላይ ቃል በገቡት ጠቅላላ የፍትህ ሥርዓት መሰረት እንደየ ሁኔታው የተለያዩ ካሳዎች (affirmative actions) እየተጠቀሙ ለእኩልነት ሊሮጡ ይችላሉ።  ይህ ማለት ግን ልዩ ጥቅም በሚል ሃብትን መሬትን ለመቀራመት ሳይሆን  እኩልነትን በፍጥነት ለማረጋገጥ የሚወሰድ የማስተካከያ ርምጃ  ነው።

አሁን በቅርቡ በኢትዮጵያ ሚንስትሮች ምክር ቤት የወጣው መግለጫ ይዘት ካሳ ወይም afirmative action ሳይሆን ከብሄር ፌደራሊዝሙ አስተሳሰብ የመነጨ ከተፈጥሮ ሃብትና የመሬት የብሄሮች ቅርምት የመጣ ዶክትሪን ነው። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ አደገኛ ነው። ይህ የብሄር ፓለቲካን መሰረት ያደረገ ፓሊሲ በሃገሪቱ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም በኢኮኖሚ ክፍፍል ላይ ብዙ የሚያተራምሱ ችግሮችን የያዘ ነው። ለምሳሌ ህገ-መንግስቱ አዲስ አበባ አካባቢ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ያነሳል። ይህ ስሜት ግን ብዙ ጥያቄዎችን ይለምናል። ራስን በራስ ማስተዳደርና የራስን እድል በራስ መወሰን ዋና መመሪያችን ከሆነ ቡድኖች ሰብሰብ ብለው በሚኖሩባቸው ከተማዎች ሁሉ የልዩ ጥቅም ጉዳይ ይነሳባቸዋል።  ለምሳሌ አዋሳን እናንሳ። አዋሳ የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ስትሆን ነገር ግን የሲዳማ ህዝብ በአዋሳ ላይ ልዩ ጥቅም ሊጠይቅ ይችላል ማለት ነው። ምክንያቱም የክልሉ ርእሰ ከተማ ሲዳማ እምብርት ላይ ስለምትገኝ።  አዋሳ ብቻ ሳትሆን አሶሳም፣ ጋምቤላም ይህንን ጥያቄ ያነሳሉ። የሚገርመው ይህ ችግር እስከ ዞን ከተሞችም ሊወርድ ይችላል። ብሄሮች ሰብሰብ ብለው  በሚገኙበት ከተማ አካባቢ የልዩ ጥቅም ጉዳይ ሊነሳ ይችላል። ውሎ እያደር ማለት ነው።  ይህ የሚያሳየው ልዩ ጥቅም የሚባለው ነገር  እንዴት የፍትህ ስርዓታችንን እስከ ታች እንደሚያበላሽብን ነው።  ይህ ጥይቄ ከፍ ሲል እንዳልኩት የተበደለን ለመካስ ሳይሆን የመሬትና የተፈጥሮ ሃብት ቅርምትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከፍትህ የተጣላ እርስ በርስ የሚያናቁር ነገር ነው። በመርህ ደረጃ ያለውን ችግር ማንሳቴ ነው። ወደ  ተግባራዊ ጉዳዮች እንግባ ካልን ደግሞ በርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት ለኦሮሞ ህዝብ ልዩ ጥቅም በዚህ አዋጅ አምጥቷል ወይ? ብለን መገምገምም አለብን።   በመግለጫው ላይ የተጠቀሰውን አንዳንዱን እናንሳ። የትምህርትን ጉዳይ እናንሳ። አንዱ የኦሮምያ ልዩ ጥቅም ማሳያ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይከፈታል የሚል ነው። ይሄ ልዩ ጥቅም ሳይሆን መብት ነው። ኦሮሞው ብቻ ሳይሆን ጉራጌም፣ ትግሬም ሊፈቀድላቸው ይገባል። የንፁህ መጠጥ ውሃ ጉዳይም እንደ ልዩ ጥቅም አይታይም። የግድ በማናቸውም መልኩ ይህ ህዝብ ንፁህ ውሃ ማግኘት አለበት። እስካሁን አለማግኘቱም ይገርማል። የቋንቋ ጉዳይ ሲነሳ መታየት ያለበት ጉዳይ ዲሞ ግራፊው ነው። በዛ ያለ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ባለበት ወረዳ ወይም የታችኛው የስልጣን ርከን አካባቢ የዚያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቋንቌቸው ኦፊሽያል ሊሆን ይገባል።  ሁሉንም  ቋንቋዎችም በዚህ መንገድ ኦፊሺያል በማድረግ ፍትህን ማውረድ ይቻላል። ኦሮምኛ የስራ ቋንቋ መሆኑ ሲነገር መልካም ነው። ታዲያ ከኦሮሞ ቀጥሎ በቁጥር ብዙም የማያንሰው የጉራጌ ብሄርስ? ስለዚህ ዓላማው  የተጎዳን የመካስ ጉዳይ ከሆነ ቋንቋዎች ሁሉ አሰራራቸው ተቀይሮ ለተጠቃሚው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረግ አለበት። መግለጫው ፊንፊኔ የሚለውን ስያሜ ህጋዊ አድርጎታል። መልካም ነው። ሸገር፣ ፊንፊኔ፣ አዲስ አበባ እየተባለች ብትጠራ የሚከፋ አይኖርም። በተለይ ፊንፊኔ የሚለውን መጠሪያ ብዙ ሰው ከወደደው ይህ ስም እውቅና ቢሰጠው የሚደገፍ ነው።  ይልቅ ሌላው በመግለጫው ውስጥ የተቀመጠው አስገራሚ ነገር የመሬት አቅርቦትን የሚመለከተው ነው። የኦሮምያ መንግስት ለህዝብ ጥቅም የሚሆኑ ህንፃዎችን ለመስራት ሲያስብ ከሊዝ ነፃ ይሆናል ይላል። ይሄ በውነት ያሳዝናል።ይሄ አይደለም እኮ የኦሮሞ ጥያቄ። ለመሆኑ የኦሮምያ መንግስት የሊዝ ክፍያ የማይከፍል ከሆነ ማን ነው እንዲከፍል የተፈረደበት? ለምሳሌ የአማራ መንግስት ለህዝብ ጥቅም የሚሆን የሙዚየም ህንፃ አዲስ አበባ ለመገንባት ቢያስብ ይከፍላል ማለት ነው? ትግራዩ ቢያስብ ይከፍላል ማለት ነው? ጋምቤላ ቢያስብ ይከፍላል ማለት ነው? ለመሆኑ ኦሮሞስ በዚህ ይደሰታል? ይሄ አይሰራም። ወይ ሁሉም ይከፍላል። ወይ ሁሉም አይከፍልም። አለቀ። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ አዲስ አበባ ውስጥ መሬት ለእኔ በነፃ ይሰጥ ሌላው ይክፈል አይደለም። የእኩልነት ጥያቄ ነው ያነሳው። ከተማዋ ስትስፋፋ ለሚፈናቀለው ገበሬ ተገቢ ካሳ ይሰጥ ነው እንጂ መሬት በነፃ ይሰጠኝ አይደለም።  ሌላው ጉዳይ የሥራ እድል ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው  በቡድኖች መካከል ያለን የኢኮኖሚ እድሎች  የትምህርት እድሎች መራራቅ ለማስተካከል ካሳ (affirmative action ) በርግጥ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ አዲስ አበባ ከተማ አቅም አግኝታ ካሳ ካሰበች የተጎዱትን ሁሉ ማሰብ አለባት። ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባን የማያውቁ ብሄሮች አሉ። እነዚህ ብሄሮች ባህላቸውን በከተማዋ እንዲያስተዋውቁ ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ እድሎችን ማስፋት ተገቢ ሊሆን ይችላል። የአካባቢ ስሞችን በሚመለከት እንደየ ሁኔታው በቀድሞ የኦሮምኛ ስም እንዲጠራ ይደረጋል ይላል የሚንስትሮች ምክር ቤት መግለጫ።  ይህ በውነት ሚዛን አይደፋም። ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ሥልቻ ነው ነገሩ። አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ የሚለው ስም ተቀይሮ በአንድ የኦሮምኛ ስም ቢተካ ለኦሮሞ ህዝብም ቢሆን ትርጉም ያለው አይመስለኝም። ከተማይቱ ፊንፍኔ እንድትባል ሰዎች አሳብ ሲሰጡ እሰማለሁ። የየሰፈሩ ስም በኦሮምኛ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ ግን አይሰማም። የኦሮሞ ህዝብ ስንት ግዙፍ ችግር እያለበት በስም ለውጥ ልቡን ማድረቅ በደል ነው። ይልቅ አንዳንድ አዳዲስ መንገዶች ሲሰሩ መንደሮች ሲሰሩ ስማቸውን በኦሮምኛ ብቻም ሳይሆን በሌሎችም ቋንቋዎች ቢሰየም ደስ ይላል። በአማርኛ በእንግሊዘኛ በጣሊያንኛ የተሰየሙ ቦታዎች እንደገና ቢቀየሩ የሚሰራው ያጣ መንግስት ሥራ ይሆናል ሥራው።  በአማራ ክልል አንዳንድ የኦሮሞ ስያሜ ያላቸው ቦታዎች አሉ፣ በደቡብ አንዳንድ የአማርኛ ስም ያላቸው ቦታዎች አሉ፣ በደቡብ የኦሮምኛ ስም ያላቸው ቦታዎች አሉ ወዘተ. ሃገሪቱ በቦታ ስም ለውጥ መታወክ የለባትም። ይህን ሁሉ እንዴውም የህብረታችን ጌጥ አድርገን ልናይ ነው የሚገባን። ይህን ካልኩ በሁዋላ ትንሽ ስለ ካሳ (Affirmative. Action ) ውይይት ልቀጥል።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ እኩልነትን ለማምጣት የተጎዳን መካስ በጣም ጥሩ መንገድ ነው። ይህ ጉዳይ ለብሄራዊ እርቅም መሰረት ነው። በርግጥ ሁሉም ቡድን ባለፉት ሥርዓቶች ተጎድቷል። ሁሉንም እንደየ ጉዳቱ መካስ ደግሞ ይቻላል። በአሁኑ ሰዓት ሃገራችን አፌርማቲቭ አክሽንን ተግባራዊ ማድረግ ከሚገባት መስክ አንዱ በኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎት አካባቢ ነው። እውነተኛ የአፌርማቲቭ አክሽን ከፈለግን የኢኮኖሚውን ያልተመጣጠነ የቡድን ሃብት ክምችት ነው ማየት ያለብን። እውን ይህ መንግስት ካሳ  ከፈለገ በህወሃት ሃብትና በኦህዴድ ሃብት መካከል ያለውን ልዩነት መመልከት ያስፈልጋል። የኦህዴድ ሃብትና የኤፈርት ሃብት ሲወዳደር ልክ አላሙዲንን አንድ በተለምዶ ሸምሱ ከሚባል ትንሽ ባለ ሱቅ ጋር የማወዳደር ያህል ነው። ግዙፍ የሃብት ልዩነት አለ። ደቡብ ደሞ በጣም ያንሳል፣ አፋር ጋምቤላ ሌሎች ብሄሮች ደግሞ ጨርሶ የላቸውም መሰለኝ።   አልማ ከህወሃት አይወዳደርም።  ይሄ ነው ማስተካከያ የሚሻው። ህወሃት ኦሮሞን ሊክሰው ካሰበ የአዲስ አበባ የሰፈር ስም በኦሮምኛ ሊሆንልህ ነው አይልም። ህወሃት ሌሎቹን ብሄሮች በመጫን ያከማቸውን ሃብት ወደ ብሄራዊ ሃብት ካዛወረ ነው ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ካሳ። ኢትዮጵያን ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ አንዱ ትልቁ ርምጃ  ኢትዮጵያን ወደ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብነት መለወጥ ነው። ይህ በራሱ ብዙ ነገር የሚለውጥ ሲሆን በሂደት የተመጣጠነ የማህበራዊ አገልግሎት ማቅረብ ተገቢ ነው። መንግስት የያዝከው የተከፋፈለ ኢኮኖሚ የሃገርን አንድነት እያናጋ ለግጭት መንስኤ እየሆነ ነው ሲሉት ሽንጡን ገትሮ አንድ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየሰራሁ ነው ይላል። አስቸጋሪ ነገር ነው የገጠመን በውነት። በሌላ በኩል    በህገ መንግስቱ ላይ መብታችን እስከመገንጠል ነው ይላል። ልክ የኢትዮጵያ ብሄሮች  እቃቸውን ሸክፈው  አንድ ቀን ብሽ ሲላቸው ለመበተን የተዘጋጁ አድርጎ ያሳያቸዋል። ኧረ ይሄ ነገር ጥሩ አይደለም ዲክተተር ብትሆኑ ይሻላል ይህን እስከ ሃቹ የሚጎዳንን ነገር እባካችሁ ሰርዙ  ሲባሉ አፍጠው መጥተው የአንድነታችን ዋስትና ነው ይላሉ። በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

ምን ይሻላል?

አሁን ያለንበት የፓለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ የኢትዮጵያን መስዋእቶች ሁሉ አጭዶ የበላ ነው። አንድ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ማህበረሰብ ይፈጠር ዘንድ መሰረታዊው ነገር ቡድኖች ያሏቸውን የተፈጥሮ ሃብትና መሬት ኢኮኖሚ እውቀት ሁሉ ለኢትዮጵያዊነት መስዋእት ማድረግ አለባቸው። ይህን መስዋእት ማድረጋቸውን የሚያሳይ ለትውልድ የሚያሳልፉት አንድ አዲስ ኪዳን መግባትም አለባቸው። ይህ ኪዳን የሚይዘው ዋና ነገር የመስዋእትነት ጉዳይን ሆኖ ይህ ኪዳናቸው አንድ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ማህበረሰብ ሆነው ጠንካራ የመኖሪያ አገራዊ ጠገግ እንዲመሰርቱ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም የሚነሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን የሃገርን የመስዋእት ጉዳይ ከፍ አድርገው ማሳየት አለባቸው። የአሁኑ የብሄር ፌደራሊዝም የሃገርን መስዋእቶች ሁሉ የዘረፈ ነው። የወሰድነውን መስዋእት እንመልስ። የተከፋፈለ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ እየፈጠርን እንደገና ለአንድነት እንሰራለን ማለቱን ትተን በጋራ ለአዲሲቱ የተባበረች ኢትዮጵያ መስራት አለብን። ኢትዮጵያውያን ሁሉ ነፍስ ሳይቀርላቸው ለሃገራቸው ያላቸውን መስዋእት አድርገው ጠንካራ አንድ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር መነቃነቅ ወጣቶች መመካከር አለባቸው። ይህን ስናደርግ ሁላችንን የሚክስ ስርዓት እንፈጥራለን።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ

geletawzeleke@gmail.com

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *