–    የይዞታ መብት ምን ማለት ነው?

law–    ባለ ይዞታነትን መደበቅ የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት ምን ይመስላል?

–    የአንድ ንብረት ይዞታ እንዴት ለሌላ ሰው ይተላለፋል?

–    ይዞታን ለማስከበር በጉልበት መጠቀምን ሕጉ ይፈቅዳል። በምን መልኩ?

–    የሁከት ይወገድልኝ ክስ ምንድንነው? እንዴትስ መቅረብ አለበት? በባህርዛፍ መሬት ይዞታ ከሰሜን ሸዋ ስድስትኪሎ የደረሰው የሁከት ይወገድልኝ ክርክር በምን ተቋጨ?

እንዴት ናችሁ ሠላም ነው? የዛሬው ወጋችን አንድ ሰው የራሱ ንብረት በሆነ ወይም በኪራይ በአደራ ጠባቂነት በይዞታው በሚገኝ ንብረት ላይ ሌሎች ሰዎች በንብረቱ የመጠቀም መብቱን የሚያሰናክሉ ድርጊቶች ሲፈፅሙበት በይዞታው ላይ ያለውን መብት ለማስጠበቅ ያለውን “የሁከት ይወገድልኝ ክስ” የማቅረብ መብት ጋር የተያያዙ ነጥቦችን የሚመለከት ነው። ሕጉን ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ የሁከት ይወገድልኝ ክስ መነሻዎችን እና የተደረገውን ክርክር የሚያሳይ እስከ ፌሬራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ደርሶ እንደ ክርክር የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜም እናያለን።

1.  የባህር ዛፎቹ ጉዳይ፡-

አቶ ሙሳ በሰሜን ሸዋ ዞን አሌልቱ ወረዳ በ1993 ከአቶ ደስታ እና ከወ/ሮ ሸዋዬ በሽያጭ አገኘሁት የሚሉት ይዞታ ላይ ባህር ዛፎች ተክለው ባህር ዛፎቹን እየተንከባከቡና እየጠበቁ ነበር። መስከረም 27 ቀን 2000 ዓ.ም የአቶ ደስታና የወ/ሮ ሸዋዬ ልጅ ጥላሁን ይዞታው ከነባህርዛፎቹ የኔ ነው ብሎ ይዞታዬ ላይ ድርሽ እንዳትል ስላላቸው ሁከት ፈጥሮ በይዞታዬ እንዳልጠቀም አድርጎኛልና ጥላሁን የፈጠረብኝ ሁከት ይወገድልኝ ሲሉ ለአሌልቱ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሰባተኛው ቀን አቤቱታ አቀረቡ።

አቶ ጥላሁንም ቀርቦ በሰጠው መልስ ይዞታው ከሟች አባቴ ከአቶ ደስታ በውርስ ያገኘሁት ይዞታ በመሁኑ አቶ ሙሳ እንዳይነካብኝ መከላከሌ መብቴን ማስከበሬ እንጂ ሁከት መፍጠር ስላልሆነ ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ ሲል ተከራከረ። ፍ/ቤቱም ጥላሁን በአቶ ሙሳ ባህር ዛፍ የተተከለበት መሬት ይዞታ ላይ ሁከት ፈጥሯልና ሁከቱን ያስወገድ ሲል ወሰነ።

አቶ ጥላሁን በውሳኔው ቅር ተሰኘና ይግባኝ ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቀረበ። ፍ/ቤቱም አቶ ሙሳ ከተከሳሽ አቶ ጥላሁን አባት ከአቶ ደስታ አያሌው ይዞታውን አግኝቼበታለሁ የሚሉት በ1993 የተደረገው የልዋጭ ውል ላይ የሰፈረው ፊርማ የሟች የአቶ አያሌው መሆኑ ተጣርቶ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥ በማለት ጉዳዩን ለአሌልቱ ወረዳ ፍ/ቤት መለሰለት።

የአሌሊቱ ወረዳ ፍ/ቤትም ፊርማው በፎረንሲክ ተመርምሮ የጥላሁን አባት የአቶ ደስታ ይሁን፣ አይሁን መለየት ስላልተቻለ አቶ ሙሳ በልዋጭ ውል ቦታውን አግኝቼበታለሁ የሚለው ሰነድ በአቶ ደስታ የተፈረመ አይደለም ብሎ በመደምደም ለሙሳ ወስኖት የነበረውን የሁከት ይወገድ ክስ ውድቅ አደረገው።

አሁን ደግሞ ይግባኝ የሙሳ ተራ ሆነ። በየደረጃው ለዞኑ ከ/ፍ/ቤት ቀጥሎም ለዞኑ ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት ስላላገኘ ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ስህተት ተፈፅሟል ይታረምልኝ ሲል አመለከተ። የክልሉ ሰበር ሰሚ ሙሳንና ጥላሁንን አከራክሮ ጥላሁን ሁከት ፈጥሮ ይዞታውን መያዝ፣ አለመያዙ በምስክሮች እና ከሚመለከታቸው የአስተዳደር አካላት ተጠይቆ ተገቢው ማጣሪያ ከተደረገ በኋላ የመሰለውን ውሳኔ ሰጥበት ሲል ለሁለተኛ ጊዜ ለአሌልቱ ወረዳ ፍ/ቤት መለሰለት።

የወረዳ ፍ/ቤት ከወረዳው አካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ጽ/ቤት ስለጉዳዩ ጠይቆ ካጣራ በኋላ አቶ ጥላሁን የፈፀመው ተግባር ሁከት አይደለም ሊል የሚችል ባለመሆኑ ሁከቱን አቁሞ ሙሳ በይዞታው ላይ ይጠቀም ሲል ወሰነ።

ጥላሁን በውሳኔው ባለመስማማት ይግባኝ ለዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ቢያቀርብም አልተሳካም። የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ጋርም ቢቀርብ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ፀና። በዚህ ሁሉ ያልታከተው ጥላሁን ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግራቀኙን አከራክሮና ማስረጃቸውን ሲመረምር ለክልሉ መነሻ የሆነው ይዞታ በመጀመሪያ የአቶ ጥላሁን አባት የአቶ ደስታ እንደነበረና ከ1993 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ግን በአቶ ሙሳ ስም ግብር እየተከፈለበት ባህር ዛፍ ተክለውበት ከይዞታቸው ስር መቆየቱን አረጋገጠ።

በ1998 አቶ ሙሳ በይዞታው ላይ የባለቤትነት የምስክር ወረቀትም አውጥተውበት ነበር። ይሄን ያወቀው አቶ ጥላሁን በ1999 እናቱን ወ/ሮ ሸዋዬን ከሶ ከአባቱ ከሟች አቶ ደስታ በውርስ የሚያገኘው ይዞታ ነው ተብሎ ተፈርዶበት በፍርድ አፈፃፀም ትዕዛዝ በ2001 ይዞታውን መቀበሉንና ከ2001 ጀምሮ በስሙ ግብር መገበሩን በ2002 የይዞታው ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በስሙ እንደተሰጠው አረጋገጠ። በተጨማሪ ጥላሁን እናቱን ሲከስ አቶ ሙሳ በመቃወሚያ አቅራቢነት ወደ ክርክሩ ገብቶ አቤቱታቸው ውድቅ እንደተደረገበት ስለተገነዘበ አቶ ጥላሁን በፍርድ ውሳኔ ያገኘውንና በእጁ አድርጎ የሚገብርበትን የዞታ ሁከት ፈጥረሃል ሊባልበት አይገባም በሚል የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ሻረው።

አቶ ሙሳ የመጨረሻ እድሉን ለመሞከር ለፌ/ጠ/ፍ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቅርቦ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጠበት። ውሳኔው ይቆየንና አንድ ሌላ ክርክር ልጨምር።

 

2.  ሕጋችን ምን ይላል?

የፍትህ ብሔር ሕጋችን በሶስተኛው መፅሐፍ ስለንብረቶች በጠቅላላውና ስለ ይዞታ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል። ስለንብረቶች አከፋፈል ከዘረዘረ በኋላ በሁለተኛው ምዕራፍ ስለይዞታ ምንነት ከቁጥር 1140-1150 የሕግ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል። ይህ የህግ ምዕራፍ ስለይዞታ ምንነት ትርጓሜ በመስጠት የሚጀምር ሲሆን ይዞታ ማለት “አንድ ሰው አንድንነገር በእጁ አድርጎ በእውነት የሚያዝበት ሆኖ ሲገኝ ነው” ብሎ ይተረጉመዋል። ይዞታ ከባለቤትነት ያነሰ መብት ሲሆን በቀጥታ ባለቤት በመሆን ወይም በጊዜያዊ ስምምነት በተሰጠ ውክልና ኪራይ፣ አደራ ወይም የመጠቀም መብትም ባለይዞታነት ሊፈጠር እንደሚችል የፍ/ብ/ሕ/ቁ/ 1141 ይደነግጋል። ይህ የባለ ይዞታነት መብት ጊዜያዊ በሆኑ ነገሮች መቋረጡ ወይም መገደቡ ብቻ የባለይዞታት መብት አያስቀርም።

አንድ ይዞታ ለሌላ ሰው በውል ተላልፏል የሚባለው ይዞታውን በመረከብ ነው። ይህ በተለይ የተለየ ምዝገባ የሚያስፈልጋቸውን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ለምሳሌ (ሞባይል፣ ላፕቶፕ የመሳሰሉትን በእጅ ማድረግ ወይም በይዞታችን ስር ማድረግ ብቻ በቂ ነው።

በሌላ በኩል አዲስ ባለይዞታ የሆነውን ሰው ባለይዞታነት የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በማስረከብ ለምሳሌ የይዞታ ወይም የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በመስጠት የሽያጭ ውል ወይም ደረሰኝ ወይም ስጦታ ሰጪው ለገዥ ወይም ለተቀባይ በመስጠት ይዞታን ማስተላለፍ ይቻላል:: ሆኖም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1144 መሰረት የዚህን ይዞታ የሚያስረዳ ሰነድ ባቀረበ ሰውና ንብረቴን በእጁ ባደረገ ሰው መካከል ክርክር ከተነሳ ንብረቱን በእጁ ሰው ተንኮል ወይም ክፉ ልቦና እንዳለበት ካልተገለፀ በስተቀር የባለ ይዞታነት አብላጫ ግምት የሚሰጠው ሰነድ ብቻ ካለው ይልቅ ንብረቱን በተጨባጭ ይዞ ለተገኘው ሰው ነው። የተለዩ እና የታወቁ እቃዎችን አዲሱ ባለይዞታ በእጅ ባያረገቸውም በእቃዎቹ የማዘዝ መብት ያለው ሰው እቃውን የያዝኩት ወደፊት አዲስ ባለይዞታ ለሚሆነው ሰው ነው ብሎ በሚፀና መልኩ ሲያሳውቅ የእቃው ይዞታ እንደተላለፈ ይቆጠራል።

የይዞታ ባለመብትነት በማያጠራጥር መልኩ በግልጽ መደረግ አለበት በእጅ የሚያገኘውን ንብረት ላይ አንዳችም መብት እንደሌለው ለማስመሰል የደበቀ ሰው በስውር የያዘው ይዞታ ነውና ምንም አይነት መብት በንብረቱ ላይ አይኖረውም። የሚያሻማ ይዞታ የሚባለው ደግሞ ንብረቱን ይዞ የሚጠቀመው ሰው የንብረቱ ባለቤት ነው ለማለት አካባቢው ሁኔታዎች የሚያጠራጥሩ ሲሆን ወይም ንብረቱ ለሌላ ሰው የያዘው ሲሆን ባለመብትነቱ አሻሚ በመሆኑ የባለይዞታነት መብት እንደማይኖረው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1146 ይደነግጋል። ስለሌላ ሰው ንብረቱን የያዘ ሰው ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ እንደ የንብረቱ ጠባቂ ተደርጎ ነው የሚገመተው።

ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን እንዳይጠቀም መሰናክል ወይም ንጥቂያ ሲፈጠርበት ይዞታውን ለማስከበር ሕጉ ሁለት አማራጮችን አስቀምጦለታል። የመጀመሪያው በኃይል ይዞታውን በመንጠቅ ወይም እንዳይጠቀምበት ለማድረግ የሚሞከረውን ሙከራ በኃይል መመለስ ነው። በተለይም በቀላሉ የሚንቀሳቀሱ ነገሮችን በንጥቂያ ወይም ወስዶ በመደበቅ ይዞታውን ሲቀጣ በግፍ ንብረቱን የሚወስደውን ወይም ይዞ የሚሸሸውን ነጣቂ ወዲያውኑ በጉልበት በማስለቀቅ ማስመለስ ይቻላል። የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሆነ በጉልበት ይዞታውን ነጣቂውን በማስወጣት ማስከበር አንዱ የሁከት ማስወገጃ አማራጭ ሲሆን ይህም ሕጋዊ ነው። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1148(3) ላይ አስገዳጅ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር ቀላል ህመም የሚያስከትሉ ጉዳዮችን ድብደባ (ቦክስ ጥፊ ካልቾ ቴስታ የመሳሰሉትን) የእጅ እልፊት የኃይል ተግባር ከመፈፀሙ በፊት ባለይዞታው መታገስ እንዳለበት ተደንግጓል።

ሁለተኛው አማራጭ የሁከት ይወገድልኝ ክስ ማቅረብ ሲሆን ይዞታው ላይ ሁከት የተነሳበት ሰው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1149(1) መሠረት የተወሰደው ነገር እንደመለሰለት ወይም የተፈጠረበት ሁከት እንዲወገድለት በተጨማሪም ይዞታውን እንዳይጠቀም በመከልከሉ ለደረሰበት ጉዳት ኪሳራ እንዲከፈለው ፍ/ቤት ክስ መጠየቅ አማራጭ  ነው።

ይህን የመክሰስ መብት ባለይዞታው ሁከት ከተነሳበት ቀን አንስቶ እስከ ሁለት አመት ክስ ካልጠቀየቀ ይዞታውን የማስመለስ መብቱ በይርጋ ይታገዳል። ሁከት በመፍጠር የተከሰሰው በፍጥነትና በማይስተባበል መልኩ ካላስረዳ ፍ/ቤቱ የተወሰደው ነገር እንደሚመለስ ወይም ይዞታው ላይ የተነሳው ሁከት እንዲወገድ 1149(3) መሰረት ያዛል።

የይዞታው ባለቤት የመሆን መብት ያለው ሰው ንብረቱን ያስተላለፈለትን ሰው የይዞታ ጊዜ ተደርቦ የሚቆጠርበት ንብረቱን ያስተላለፈው ሰው ከላይ በተቀመጠው የይርጋ ገደብ ይዞታውን ለራሱ የማስቀረት መብት ሲኖረው ሲሆን በ1150(2) መሠረት በአንድ ነባር ይዞታ ላይ ወይም በይዞታ የመጠቀም መብት ላይ ለሚነሳ ክርክር ይዞታውን እየተጠቀመበት የሚገኘው ሰው በስሙ የከፈለውን ግብር መከራከሪያ  ሊያደርገው ይችላል።

 

3.  ሰበር ምን አለ?

በመነሻችን ላይ ያነሳነው የአቶ ሙሳ እና የአቶ ጥላሁን ክርክር ላይ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ.መ.ቁ. በ4869 ሰኔ 19  ቀን 2006 በሰጠው ቅጽ 16 የሰበር ችሎቶች ውሳኔ ላይ ታትሞ በወጣው መጨረሻ ፍርዱ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎ የወሰነውን ውሳኔ በማጽናት አቶ ጥላሁን ይዞታውን ያገኙት በፍርድ ቤት ውሳኔ በመሆኑ ባለይዞታነታቸው ስለተረጋገጠ ሁከት አልፈጠሩም ሲል ወሰኗል።

ከኪዳኔ መካሻ    Kidane1983@yahoo.com

ሰንደቅ ጋዜጣ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *