Image may contain: 1 person
By – Tibebu Belete

 

ታላቁ ባለቅኔ፣ ጸሐፌ-ተውኔት፣ አርበኛ፣ የመዝሙርና የታሪክ ጸሐፊው ዮፍታሔ ንጉሴ፣ ከ70 አመታት በኋላ አጽሙ ካረፈበት ከባለወልድ ቤተክርስትያን ተነስቶ ወደ ትውልድ ቦታው ጎጃም እየተጓዘ ነው፡፡ ዮፍታሔ ኢትዮጵያ የጥበብ ሊቆችዋን ስትጠራ አንድ… ብላ መጀመሪያ ላይ ከምታስቀምጣቸው ከዋክብቶችዋ አንዱ ነው፡፡ ዋና ከተማዋ በስሙ ትልቅ ሐውልት መገንባት ሲገባት ጭራሽ የዮፍታሔን አጽም ሸኘችው፡፡ እውነት ለመናገር እጅግ ያበሽቃል! ለመሆኑ ባሕል ሚኒስቴርስ ስራው ምንድን ነው? ግን ይህ ብርቅ ኢትዮጵያዊ ጀግና ማን ነው?
ባለቅኔውና ሃያሲው ዮሐንስ አድማሱ ሰኔ 25 ቀን 1961 ዓ.ም ላይ መነን ተብሎ ይታወቅ በነበረው መጽሔት፣ “ተወርዋሪ ኰከብ” የሚል ረጅም ግጥም ፅፏል። ግጥሙን የፃፈው ደግሞ ለዮፍታሔ ንጉሴ ነው። አንዴ ብልጭ ብሎ በሚጠፋው ተወርዋሪ ኰከብ /Shooting Star/ ጋር አመሳስሎት ነው የገለፀው። በትውልድ ውስጥ እንደ ዮፍታሔ አይነት ሰው ብርሃን ሆኖ ወዲያው መጥፋቱን ያስነብበናል።

ብሩሕ ነፀብራቁ 
ውበትና ድምፁ አንድነት ተሰምተው 
አንድነት ቢቦርቁ
የሚያውቅለት ጠፍቶ
ምስጢሩን አካቶ
ተወርዋሪ ኰከብ በራሱ ነበልባል
በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ
ተወርዋሪ ኰከብ በምናየው ሰማይ ነበረ በይፋ


እያለ በቅኔና በውበት የደማመቀ የግጥም ለዛ ለዮፍታሔ ንጉሴ አውርዶለታል። ዮሐንስ አድማሱ እንዲህ ስሜቱ የተነካለት ዮፍታሔ ንጉሴ በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበባት ዓለም ውስጥ ደማቅ አሻራ አሳርፈው ካለፉ ባለውለተኞች አንዱ ስለሆነ ነው። እናም ዛሬ ከዮፍታሔ ንጉሴ መንፈስና ተግባራት ጋር አብረን እንቆያለን።
የዮፍታሔ የአባቱ ስም ቄስ ገበዝ ንጉሴ ወልደየሱስ ሲባል፤ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ ማዘንጊያ ወልደሔር ተድላ ይባላሉ። ሁለቱም ባልና ሚስቶች ጐጃም ውስጥ ካሉ ባለጠጋ ቤተሰቦች የተወለዱ እንደነበር ታሪካቸው ያወሳል። በትዳራቸውም ምክንያት ሁለት ወንዶችና ሦስት ሴቶችን ወልደዋል። የበኩር ልጃቸው ሴት ነች። ስሟም ትበርህ ንጉሴ ይባላል። ጡት ያስጣላት ዮፍታሔ ንጉሴ ነው። አስቀጣይ ሞሲት ንጉሴ፣ አራተኛዋ ጠጅቱ ንጉሴ፣ መቁረጫው ደግሞ አያሌው ንጉሴ ይባላል።
ዮፍታሔ የተወለደው ጐጃም ውስጥ ደብረኤልያስ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በ1887 ዓ.ም እንደነበር ሐምሌ 9 ቀን 1939 ዓ.ም የታተመው “ሰንደቅ አላማችን” የተሰኘው ጋዜጣ ያስታውሳል። ስሙንም “ዮፍታሔ” ያሉት በደብረኤልያስ የታወቁ የቅኔና የመጽሐፍ ትርጓሜ መምህር የኔታ ገብረስላሴ እንደሆኑ ታሪኩ ያወሳል። ዮፍታሔ የተወለደባት መንደር ደብረኤልያስ ውስጥ “አመደ ጉባ” ትባላላች።
ትምህርት የጀመረው መምህር አደላ፤ ንጉሴ ዘንድ ነው። ፊደልን፣ ንባብን፣ መዝሙረ ዳዊትን ከተማረ በኋላ የዜማ ትምህርት ቀጠለ። ከዚያም ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍን ቀጥሎም ድጓ፣ ከዚያም ቅኔ ቤት ገባ። በወቅቱ በጣም ወጣት ነበር። ትምህርቱን ሲጨርስ መምህር ሆኖ ተመረቀ። በሙያውም ለአምስት ዓመታት ካገለገለ በኋላ የሽማግሌዎችን ሹመት “ቀኝ ጌታ” ተባለ።
ዮፍታሔ እንዴት ወደ አዲስ አበባ መጣ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። እርሱ የመጣበት ምክንያት ሁለት ነገሮች በዋቢነት ይጠቀሳሉ። አንደኛው ንጉስ ሚካኤል ዘንድ መልዕክት ለማድረስ እንደነበር ይወሳል። ንጉስ ሚካኤለ በ1907 ዓ.ም ግንቦት 23 ቀን “ዘ ስልጣኑ ፅሁፍ ዲበ መትከፍቱ ሚካኤል ንጉስ ፅዮን” ተብለው በወሎ፣ በትግራይ፣ በጐጃም ነገሡ። የንጉስ ሚካኤል እናት የትውልድ ሐረግ ደብረኤልያስ ልዩ ስሙ ደልዳል የሚባል ቦታ ስለበር ይሄን ታሪክ ይዞ ዮፍታሔ ወደ ወሎ ሄደ። ዮፍታሔ የሄደው የደብረኤልያስ ሰዎች ኰሚቴ አቋቁመው መልዕክተኞችን ሲልኩ አንዱ በመሆን ተመርጦ ነው። እርሱ ደግሞ የተመረጠው ተናጋሪ (ሪፖርት አቅራቢ) ሆኖ ነው። አልበርት ጀራልድ የተባለው የኢትዮጵያን ሥነ-ፅሁፍ የተመራመረው ፀሐፊ እ.ኤ.አ በ1968 ዓ.ም Amharic Creative Literature በሚል ርዕስ ፅፎታል።
እነ ዮፍታሔ ወደ ንጉስ ሚካኤል ዘንድ ሲሄዱ ቀለብ አልቆባቸው ተቸግረው ነበር። ገንዘብ ማግኛም የሚሆናቸውን ዘዴ ፈጥረው ነበር። ጠንቋይ ሆኑ፣ መፃፍ ገላጭ በመሆን በየአካባቢው ሲደርሱ ሰው “አዋቂዎች” ናቸው እያለ ገንዘብ እየለገሳቸው ቆይተዋል።
ከዚህ ሁሉ በኋላም ደሴ ደርሰው ከንጉስ ሚካኤል ዘንድ መልዕክቱን አቀረቡ። ንጉስ ሚካኤልም ለደብረ ኤልያስ ታቦት መጐናፀፊያ ልዩ ልዩ ንዋየ ቅዱሳትንና መቶ ብር ለገሱ።
ከዚህ በኋላ የዮፍታሔ ህይወት መቀየር ይጀምራል። በ1908 ዓ.ም ወደ ራስ ኃይሉ (የጐጃም ገዢ) ዘንድ ማለትም ደብረማርቆስ ሄዶ ስራ ለመቀጠር ችሎታውን አሳየ። በችሎታውና ባለው የቀለም እውቀት ተደንቆ ተቀጠረ።
ዮፍታሔ ንጉሴ ወደ አዲስ አበባም የመጣበት ምክንያትም ተፈጠረ። ይህም አባቱ ቄሰ ገበዝ ንጉሴ ሲሞቱ እናቱ ወ/ሮ ማዘንጊያ ገና አንዲት ፍሬ ነበሩ። ሥጋወ ደሙ ተቀብለው ነበር የተጋቡት። መመንኰስ ነበረባቸው። ግን አልመነኩሱም። እንደውም አፈረሱ ተባለ። ዮፍታሔም የህዝቡን አሽሙርና አግቦ መቋቋም ተስኖት ወደ አዲስ አበባ ኰበለለ ይባላል። ሌሎች ደግሞ ወደ አዲስ አበባ የመጣው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው ብለው የፃፉም አሉ።
ግንቦት ወር 1910 ዓ.ም ዮፍታሔ ንጉሴ አዲስ አበባ መጣ። በቤተ-ክህነት ትምህርት እጅግ በሳል የተባለ አዋቂ በመሆኑ ስራ ለመያዝ ምንም አልተቸገረም። አቦ ደብር ውስጥ ስራ አገኘ። አዲስ አበባ አንድ የጐጃም ሊቅ አገኘች እየተባለ ተወራ። ወዲያው ዝነኛ ሆነ። ቤት ተሰጠው – ያውም ከብላታ መርሴሃዘን ወልደቂርቆስ አዋሳኝ ላይ። ከዚህ ሌላ መተዳደሪያ የሚሆነው አርሲ ውስጥ አንድ ጋሻ መሬት ተሰጠው። ንግስት ዘውዲቱም በ1910 ዓ.ም ካባ ሸልመውታል።
በ1911 ዓ.ም በየካቲት ወር ባየር የሚባል የፈረንሣይ ኩባንያ የወርቅና የብር ማዕድን ለመፈለግ ሲዘጋጅ ስራውን ለመጀመር ካሰለጠናቸው ውስጥ ዮፍታሔና መርሰኤሃዘን (ብላታ) ተመረጡ። የወር ደመወዙም ሰባት ብር ነበር። ከዚያም በሊጋባ ወዳጆ ስር በሊጋባ ጽ/ቤት በ1911 ዓ.ም የጽህፈት ሥራ አገኘ። ደመወዙም በወር 10 ብር ነበር።
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ አንድ አዲስ ነገር መጣ። ነሐሴ 29 ቀን 1916 ዓ.ም ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን አውሮፓን ጐበኙ። ከአውሮፓ ሲመለሱ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ወሰኑ። በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተጨማሪ መምህራን ሲቀጠሩ እሱና መላኩ በጐሰው በወር 30 ብር ተመደበላቸው። በ1918 ዓ.ም ዮፍታሔና መላኩ በጐሰው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በአማርኛ መምህርነት ስራ ጀመሩ።
እዚህ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ማስተማር ከጀመረ በኋላ ግጥሞችን እና መዝሙሮችን እንዲሁም ቴአትሮችን “ማምረት” ጀመረ።
ወላድ ኢትዮጵያ ለልጆቿ ብላ
እጅግ ሳይጥሩላት ሳይዘሯት አብቅላ
ስንዴውን ጠብቃ እንክርዳዱን ነቅላ
ስትመግበን አየን በፀሐይ አብቅላ
እያለ መቀኘት የየእለት ተግባሩ ሆነ።
ባለቅኔውና ሐያሲው ምሁር ዮሐንስ አድማሱ፣ መነን መጽሔት ላይ እንደፃፈው ዮፍታሔ ብዙ ዘፈኖችን እራሱ አውጥቶ ነበር። ሙናዬ ሙናዬ፣ የኛማ ሙሽራ፣ አንተ ባላጐዛ ወዘተ የሚሰኙ መዝሙሮችን ደርሷል።
በቴአትር ፀሐፊነትና አዘጋጅነትም የተዋጣለት ሆነ። አፋጀሽኝ የተሰኘችው ቴአትሩና ሌሎችም ስመ ገናና እያደረጉት መጡ። ታላቁ ደራሲ ሃዲስ አለማየሁ በአንድ ወቅት ሲናገሩ “አንድ ጊዜ ጃንሆይ በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ ከልዑል አልጋ ወራሽ አንገት ወርቅ አውልቀው ለዮፍታሔ አንገት አጥልቀውለታል” ብለዋል። “የሆድ አምላኩ ቅጣት” የተሰኘው ቴአትር ሲታይ 300 ብር ጉርሻ እና ቴአትሩን ላቀረቡት ተማሪዎች የወርቅና የብር ሰዓት ተሰጥቷቸዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ቴአትር በማስፋፋትና በማሳደግ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀሰው ዮፍታሔ፣ በ1919 ዓ.ም ሐምሌ 14 ቀን ከብላታ በቀለ ጋር ሆኖ በፈረንጅ አንተማመን የሚል ኀሳብ ያለው ቴአትር ሰርቶ ከብዙ ሳንሱር በኋላ ታይቶለታል።
ቴአትሮቹ ብዙ የመገለጫ ገፅታዎች አሏቸው። አንዳንዶቹን ኀሳቦች የሚወስደው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ለዚህም ምስክር የተሰኘው ቴአትሩ ይጠቀሳል። ከዚህ ሌላ ቴአትሮችን ከመዝሙር እና ከህብረ ዝማሬ ጋር ቀላቅሎም የማቅረብ ጥበብ አስፋፍቷል። ከነባራዊው እውነታም እየተነሳ የሚፅፋቸው ቴአትሮች ፖለቲካዊ ጉነጣ ያካሂድባቸው ነበር። ለምሳሌ በ1921 ዓ.ም የፃፈው ቴአትር ኢትዮጵያ ወደኋላ እየቀረች ነው በማለት ምስክር በተሰኘው ቴአትሩ አሳይቷል።
“የኛማ ሀገር የእኛማ ሀገር
ምትሐት ፈጣሪ መልዕክተ ፍጡር
ምን ያለሽ ሞኝ ነሽ ምን ያለሽ ተላላ
ወርቅ ተሸክመሽ መቅረት ወደኋላ”
በኢትዮጵያ ውስጥ ቴአትር በደንብ ተዘጋጅቶ የታየው በ1923 ዓ.ም ጃንሆይ ሲነግሱ ነው። “ጥቅም ያለበት ጨዋታ” የሚለው ይሄው ቴአትሩ በሃይማኖትና በምግባር መካከል ጋብቻ ፈጥሮ የፃፈው እንደሆነ ኤኔሪኰ ቹሪሊ የተባለ የጣሊያን ተመራማሪ ፅፏል።
በ1924 ዓ.ም ሐምሌ 11 ቀን ደግሞ ልዕልት ዘነበወርቅ ከባለቤታቸው ከደጃዝማች ኃይለስላሴ ጉግሣ ጋር ሲመለሱ “ያማረ ምላሽ” የተባለ ቴአትር አሳየ። “የኛማ ሙሽራ” የተባለ እጅግ የደመቀ ዘፈንም አቅርቧል።
በዚሁ ዓመት ለጃንሆይ ልደት “የሆድ አምላኩ ቅጣት” ቴአትር አሳይቷል። የቴአትሩ ሁለት መሪ ገፀ-ባህርያት “በጐ ሰው” እና “ሆድ አምላኩ” ናቸው። በጐ ሰው በንጉሠ ነገስቱ ተመስሎ፣ “ሆድ አምላኩ” በልዑል ራስ ኃይሉ ተመስሎ ነበር የቀረበው።
ንግድ ሚኒስቴር ውስጥ ይሰሩ የነበሩት መሐሪ ካሣ የተባሉ ጓደኛው ስለ ዮፍታሔ ሲመሰክሩ ማስታወሻ ደብተርና እስክሪብቶ ከእጁ አይጠፋም ብለዋል። ዮፍታሔ በ1925 ዓ.ም የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ።
ይህ ፀሐፌ-ተውኔት በ1925 ዓ.ም ህዳር 11 ቀን በኦሮምኛ ቋንቋ “ዳዲ ቱራ” የሚል ቴአትር ፅፏል። ቴአትሩ በኦሮሞ ባህል ላይ የሚያተኩር ነው። ሐምሌ 16 ቀን 1926 ዓ.ም ደግሞ “የህዝብ ፀፀት የእመት በልዩ ጉዳት” የተባለ ቴአትር በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት አሳየ። ቴአትሩ በሽታ ያለባቸው ሀብታሞች ህመማቸው በሌላ ሰው ላይ ሆን ብለው ሲያሰራጩት የሚያሳይ ነው። ይህን የቴአትር ፅሁፍ ግን እስካሁን አግኝቼው አላነበብኩትም። የት እንዳለም ላገኘው አልቻልኩም።
ዮፍታሔ ንጉሴ ስለ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያንም አርበኝነትና ተጋድሎ በመፃፍ የሚታወቅ ባለቅኔ ነው። ከንጉስ ኃይለስላሴና ቤተሰቦቻቸው በተጨማሪ ለታላላቅ ኢትዮጵያውያን ተቀኝቷል። ለምሳሌ ህዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም ወልወል ላይ በተደረገው ጦርነት ፊታውራሪ አለማየሁ መሞታቸውን ሲሰማ የሚከተለውን ቅኔ አቅርቧል።
አለማየሁ ጐሹ እንደቀድሞው ካሣ
አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍስሶ
ደጃዝማች አፈወርቅ ምድሩን አሳርሶ
አጥንቱን ተከለው፤ ደሙን አለስልሶ
የውጋዴን ዳኛ የውጋዳን ዳኛ
ደከመው መሰለኝ ተሸፋፍኖ ተኛ።
ዮሐንስ አድማሱ ሲገልፅ ጐበዝ ደራሲ ነብይ ነው ይላል። የሚመጣውን ነገር አሻግሮ ማየት የሚችል። ዮፍታሔም ልክ እንደ ደራሲ ተመስገን ገብሬ አይነት ነብይ ነበር። ምክንያቱም ጣሊያን ኢትዮጵያን እንደምትወር ቀደም ሲል ከታያቸው ጠቢባን መካከል አንዱ እርሱ ነው። የጠላትን መምጣት በሚከተለው መልኩ ቀደም ብሎ ጽፎታል።

አትርሱኝ እዘኑ ዘመዶቼ ሁሉ
እኔም ታምሜያለሁ ባሌም ታሟል አሉ።
እንጃ መዳኑን እንጃ መዳኑን
እየቆራረጠ አሞታል ባሌን
ዘወትር ይስቃል አወይ ጥርሴ ሞኙ
ጐፈሬዋን አይተው ዙረው የተመኙ
ዳሩን እንጋባ እያሉ ሲመኙ
የዮፍታሔ ንጉሴን ነብይነት ከመሰከሩት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን መካከል ንጉስ ኃይለስላሴ እና ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ይገኙበታል። ፋሽስቶች ኢትዮጵያን ሲወሩ ከንጉስ ኃይለስላሴ ጋር በመሆን ወደ እንግሊዝ የተጓዙት ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ሰኔ 16 ቀን 1929 ዓ.ም ለዮፍታሔ ንጉሴ የሚከተለውን ደብዳቤ ፅፈውለታል።
“ወንድሜ ሆይ፤ ምስጢራዊ ንግግርህና ፅህፈትህ ዛሬ አደባባይ ወጣ። መስጢር የለውም። ጊዜ ይገልጠዋል። ይኸውልህ ሁላችንንም የድካማችንን ፍሬ እግዚአብሔር እንዲህ አደረገው” ብለውታል።
ዮፍታሔ ንጉሴ በዘመኑ ልክ እንደ ደራሲ ተመስገን ገብሬ ሁሉ ንግግር አዋቂ ነበር። በ1927 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ማኅበር ሲመሰረት በበጅሮንድ ተ/ሐዋርያት እና በሌሎችም አሳሳቢነት ስለ ኢትዮጵያ ፍቅርና አንድነት ንግግር እንዲያደርጉ “ዲስኩረኞች” ተመረጡ። እነዚህም፤ ዮፍታሔ ንጉሴ፣ ተመስገን ገብሬ፣ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ፣ ደምስ ወ/አማኑኤል፣ መላኩ በጐሰው፣ አስፋው አንዳርጌ፣ መርስኤ ሀዘን ወ/ቂርቆስ፣ አበበ ገመዳ፣ መንገሻ ከፈለ፣ ኃይለገብርኤል ነገሮ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የኢጣሊያ ወረራ ከመምጣቱ በፊት ህዝቡ ነቅቶ ሀገሩ ኢትዮጵያን እንዲጠብቅ ያስተማሩ የታሪክ ባለውለተኞች ናቸው። ዮፍታሔም ከነርሱ መካከል አንዱ ነው።
ይህ የኪነ-ጥበብ ሰው፣ ኢትዮጵያን በጀግኖቿ ተመሳሌነት በአንድነት ለማስተሳሰር ሲል እጅግ ውብ የሆነ ግጥምም ፅፏል። ይህ ግጥም ርዕሱ “አጥንቱን ልልቀመው” የሚል ነው።
አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፈሬ
ጐበናን ተሸዋ አሉላን ከትግሬ
ስመኝ አድሬያለሁ ትናንትና ዛሬ
አሉላን ለጥይት ጐበናን ለጭሬ
ጐበና ሴት ልጁን ሊያስተምር ፈረስ
አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሊያስተኩስ
አገሬ ተባብራ ታልረገጠች እርካብ
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ።
የሀገር ፍቅር ስሜትን በኢትዮጵያዊያን ደም ውስጥ በማስረግ ከሚታወቁት የኢትዮጵያ ጠቢባን መካከል አንዱ የሆነው ዮፍታሔ ንጉሴ በ1928 ዓ.ም ጐበዝ አየን የምትሰኝ መጽሐፍ አሳትሟል። በዚህች መፅሐፍ ውስጥ፤ ሰው ለሀገሩ፣ ለነፃነቱ፣ ለክብሩ ቢሞት እንደሞተ አይቆጠርም ይላል።
“ሕይወቱን ጠብቆ የሞተ ላገሩ
በሕይወት ይኖራል ነፃነቱ ክብሩ”
የኢጣሊያ ወረራ
ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር በመጀመሪያ ያደረገችው ለሀገርና ለወገን ተቆርቋሪ የሆኑ እንደ ዮፍታሔ ንጉሴ ያሉትን ሰዎች ማጥፋት ነበር። ቤት ለቤት እየዞሩም አሰሳቸውን ቀጠሉ። ሐምሌ 10 ቀን 1928 ዮፍታሔን ፍለጋ ቤቱ መጡ። ቤቱን በርብረው በርካታ ሠነዶቹን ወሰዱበት። እሱ ግን በአጋጣሚ አልነበረም። በብሽቀት ጐረቤቱን አለቃ መርሻን ገድለው ሄዱ።
ዮፍታሔ በወቅቱ ያስቸገሩት ለጣሊያን ያደሩ ባንዳዎች ነበሩ። “እኔ የምሸሸው ከኢጣሊያኖች ሳይሆን ከእኛው ዜጐች ነው” በማለት በወቅቱ ዮፍታሔ ተናግሯል። በዚህም የተነሳ ራሱን ቀያይሮ በማይታወቅበት ሁኔታ ከተማው ውስጥ ይዘዋወር ነበር።
ጢሙን አሳድጐ፣ የቄስ ልብስ ለብሶ፣ ጢሙም ገረጃጅፎ አድጐ ከተደበቀበት ወጥቶ ሲሄድ በፍፁም አይታወቅም ነበር። ብላታ መርሴሃዘን መንገድ ላይ አግኝተውት አላወቁትም ነበር። እሱ ግን ዮፍታሔ ነኝ ብሎ ነገራቸው።
አንድ ቀን ደግሞ የቄስ ልብስ ለብሶና ጠምጥሞ፣ መስቀል እያሳለመ፣ ማንነቱ ሳይታወቅበት አዲስ አበባን ለቅቆ በአቃቂ በኩል ወደ አዋሽ ሄደ። አመለጠ። አዋሽም ደጃች ባልቻን አገኘ። አብረው ሆነው ጣሊያንን ወጉ። ባንዳው ግን አስቸገራቸው።
በኋላ ወደ ጎሬ መጓዝ ጀመረ። ጉዞው አደጋ ያለው መሆኑን ሲያውቅ የባህታዊ ልብስ ለብሶ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተጠግቶ መቃብር ቤት ውስጥ ማደር ጀመረ። በኋላም ማስወራት ጀመረ። “አዋቂ ነው፤ ጥንቆላውም መሬት ጠብ አይልም፤ የተናገረው ሁሉ እውነት ነው” ተባለለት። እናም ጆቴ የተባለው እዚያ አካባቢ የነበረውን የኢጣሊያን የጦር አዛዥን “ነብይ” ሆኖለት ጠነቆለለት። “ጆቴ፤ በኢትዮጵያ ላይ ትነግሳለህ፤ ይቀናሃል” አለው። ጆቶም እጅግ ደስ ብሎት ለዮፍታሔ የሚፈልገውን ሁሉ እንዲደረግለት አደረገ። ዮፍታሔ ደግሞ ዋናው አላማው ወደ ጐሬ መሄድና የትግል ስልቱን መቀየር ነበር። እናም ጐሬ ደርሶ ለመምጣት ፈቃድ አግኝቶ አመለጠ። ከዚያም ሱዳን ገባ።
ካርቱም ከገባ በኋላ በርካታ ተግባራትን ማከናወን ጀመረ። በተለይ ደግሞ ልዩ ልዩ ድርሰቶችን እየፃፈ ወደ ለንደን ይልካል። እዚያም የነበሩት ጃንሆይ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ እና ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ያነቡለት ነበር። እንደውም በአንድ ወቅት ጃንሆይ የሚከተለውን ደብዳቤ ወደ ዮፍታሔ ፃፉ።
“በየጊዜው የምትልከው ደብዳቤ እየቀረበልን ተመልክተነዋል። ባጭር ባጭሩ እያዘጋጀህ ላከው። የትካዜ መዝሙር ልብ ይነካል” /መጋቢት 19 ቀን 1930 ዓ.ም/
ዮፍታሔ ንጉሴ የልቦለድ ድርሰት እንደፃፈ ቢናገርም፤ እስከ ዛሬ ድረስ የት እንዳለ አይታወቅም። ካርቱም ላይ “አፋጀሽኝ” የተሰኘውን ድንቅዬ ቴአትሩን ፅፏል። ቴአትሩ ኢትዮጵያ እንዴት በጠላት እጅ እንደወደቀችና እንዴትስ እንዳዳነች ከአንዲት የታመመች ሴት ጋር አመሳስሎ ፅፎታል። በመታመሟ እና በመዳኗ መካከል ያለውን ድርጊት በማሳየት የጊዜውን የፖለቲካ ሁኔታ የሚገልፅ ቴአትር ነው።
ከዚህ ሌላ “ደብረጽዮን” የተባለ መጽሐፍ ፅፎ ነበር። ግን የት እንዳለ አይታወቅም። “ዐመተ ምህረት” የሚለው መጽሐፉም ፀሐፌ ትዕዛዝ ወ/ጊዮርጊስ ዘንድ ተቀምጦ ነበር ይባላል። እሱም አልተገኘም። ስደተኞች ተስፋ እንዳይቆርጡም “በለስ ለመለመች” እና “ጐሀ ፅባህ” የተባሉ መዝሙሮች ደርሷል።
ዮፍታሔ አደገኛ ሰላይ ሆኖ ለሀገሩ ኢትዮጵያ አገልግሏል። ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ራሱን በልዩ ልዩ መልክ እየቀየረ በመምጣት ከአርበኞች ጋር ተገናኝቶ እና የሚፈልገውን መልዕክት አድርሶና ተቀብሎ ወደ ሱዳን ይመለስ ነበር። ለጃንሆይም መልዕክት ያስተላልፍ ነበር።
ይሄ ሁሉ መከራ አልፎ የጣሊያኖች ግብዐተ መሬት ይፈፀም ጀመር። አርበኞች ድል በድል ሆኑ። የጣሊያኖች ምሰሶ ሲናድ የተሰደደው የኢትዮጵያ መንግስት ተመልሶ መምጣት ጀመረ። ጃንሆይ ከእንግሊዝ ወደ ካርቱም ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ዮፍታሔ የጉዞ ማስታወሻ ፀሐፊ ሆኖ አብሮ መጣ።
በዚህም ጉዞ ወቅት “ደሙን ያፈሰሰ” እና “ተጣማጅ አርበኛ” የተሰኙ የሰንደቅ ዓላማ መዝሙሮች ደረሰ። ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ በድል ማግስት “አፋጀሽኝ” ቴአትሩን አሳየ። በዚያን ጊዜ ተዋናዮቹ 30 ነበሩ። 10 አረንጓዴ፣ 10 ቢጫ፣ 10 ቀይ ልብስ ለብሰው መስከረም 3 ቀን 1934 ዓ.ም አሳዩ። ቴአትሩ የኢትዮጵያ የነፃነት መንፈስ መገለጫ ሆኖ ናኘ።
ለሀገሩ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለው ዮፍታሔ ከነፃነት በኋላ ስራ እንኳን ሳያገኝ ከአንድ ዓመት በላይ ቁጭ አለ። ባንዳዎች እንኳን ሳይቀሩ ስራ ተሰጥቷቸው ነበር። ያ ሁሉ ተስፋው ከንቱ ሆነ። ሀዘን ገባው። እውቀቴ ችሎታዬ አንሶ ነው? ብሎም አሰበ። አገልግሎቴስ አጥጋቢ አልነበረም ማለት ነው? ይል ጀመር። የባንዳዎችን ሹመት ሲያይ የሚከተለውን ገጠመ።
ለጌሾ ወቀጣ
ማንም አልወጣ
ለመጠጡ ለመጠጡ
ከየጓዳው ወጡ
ከዚህ በኋላ ሥነ-ጥበብ ሚኒስቴር ውስጥ ስራ ተሰጠው፤ በወር ከ150 ብር ደመወዝ ጋር። ግን አልሰራም አለ። ሐምሌ 16 ቀን 1934 ዓ.ም “እያዩ ማዘን” የተባለ ቴአትር ፃፈ። ቴአትሩ ደግሞ ከፍተኛ ብስጭቱን የገለፀበት ነበር።
ጌታዬ የኔ ጌታ ጌታዬ
በመስቀልህ ባርከኝ
በስልጣንህ ባርከኝ
ዕድሌንም ባርከው
ተመለጠ ራሴ እየቆጨኝ ባከው።
ይህን ቴአትር የተገነዘቡት አፄ ኃይለስላሴ ውሣኔ ሰጡ። ወዲያው ጥቅምት 18 ቀን 1935 ዓ.ም ዮፍታሔ ንጉሴ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው ሾሙት። ከዚህ በኋላም “ዕርበተ ፀሐይ” የተሰኘውን ቴአትሩን ፅፏል። ቴአትሩ የልዕልት ፀሐይ ኃይለስላሴን ሞት ምክንያት በማድረግ የተፃፈ ነው።
ዮፍታሔ ንጉሴ ሦስት ትዳሮችን በየጊዜው መስርቷል። ወ/ሮ ጥሩነሽ ደባን፣ ወ/ሮ ሙሉወርቅ ጠናን እና የመጀመሪያዋ የሴት ጋዜጠኛ የነበሩትን ደራሲ ሮማንወርቅ ካሳሁንን አግብቷል። ትዳር የቀያየረ ባለቅኔ ነበር።
ዮፍታሔ በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ አጭር የሆነ ጊዜ ቢቆይም፤ አብርቶ ያለፈው ብርሃን እጅግ ደማቅ ነበር። በርካታ ጉዳዮች ላይ ፅፏል። ለምሳሌ “ከማይጨው እስከ ደብረማርቆስ” የተሰኘ የታሪክ መጽሐፍ አበርክቶልናል። “ጐበዝ አየን”፣ “አመተ ምህረት”፣ “ደብረ ጽዮን”፣ የተሰኙ አራት መፃህፍትን አሳትሟል። በቴአትር ዘርፉ ደግሞ 17 ቴአትሮችን ፅፎ እና አዘጋጅቶ እንዲሁም አሳይቶ አልፏል። ከ20 የሚበልጡ መዝሙሮችን ደርሷል። የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ደራሲም ነበር። በቅኔ፣ በዜማ፣ በመድረክ ንግግር ወዘተ ከፍተኛ ተሰጥኦውን አሳይቷል። አያሌ ደብዳቤዎችና የጉዞ ማስታወሻዎችን ፅፏል። እነዚህ ቀሪ ስራዎቹ ዛሬም ስለ እሱ ይመሰክራሉ።
ይህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም ድንገት አሞት ሐኪም ቤት ሄዶ መርፌ ተወግቶ ተመልሷል። ህመሙ ከባድ ስላልነበር ከስራው አልቀረም። ማታም ከጓደኛው ከአቶ መሐሪ ካሣ ቤት ደህና ሲጫወት አምሽቶ ወደ ቤቱ ገብቶ ተኝቷል። ሆኖም ጧት ሰራተኛው ቁርስ ሰርታ ብትጠብቀው አልመጣም። ታላቁ የኪነ-ጥበብ ሰው ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም በ52 ዓመቱ እስከወዲያኛው ተሰናብቶናል። አንዳንዶች የተመረዘ ነገር ተሰጥቶት ነው የሞተው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ የከሰል ጭስ አፍኖት በማለት ይገልፃሉ። ሞቱ ግን ምስጢር ነው!
ሰውን ሰው ቢወደው አይሆንም
እንደራስ
ታመህ ሳልጠይቅህ መቅረቴን
አትውቀስ
ባውቀው ነው ተመጣሁ
እንደማልመለስ
ይማርህ መሐሪው እስክመጣ
ድረስ።
ይህን የዮፍታሔን ታሪክ ለመፃፍ ያገለገሉኝ ሰነዶች፤ ዮሐንስ አድማሱ፣ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት የፃፏቸው መፅሀፍት፣ ሙሉጌታ ስዩም 1964 ዓ.ም የፃፈው ታሪክ፣ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ 1976 ዓ.ም ያዘጋጁት፣ ተስፋዬ ገሠሠ የፃፈው የቴአትር ታሪክና ራሱ ዮፍታሔ የፃፋቸው ታሪኮች ናቸው።

ምስጋና ስንዱ ፌስ ቡክ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *