ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የተማሩት በዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ የደከሙት ለዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ ያገለገሉት ሀገራቸውን ኢትዮጵያን – እንዴት ባለ ሂሳብ ነው አዲስ አበባ ለቴአትሩ ንጉሥ ቦታ የላትም ተብሎ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ዐጽሙ ይሂድ የሚባለው? ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ መቀበርም የሚቻለው በክልላችሁ ነው ልትሉን ነው? ዮፍታሔ ንጉሤ የደብረ ኤልያስ ብቻ ናቸው? ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ያበረከትሺውን ሰው ጥቀሽ ስትባል ከምትጠቅሳቸው ተርታ አይደሉምን? ይህ ለትውልዱ እየሰጠነው ያለው ትምህርት የት የሚያደርስ ነው?

አራት ኪሎ ከቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አጠገብ የሚገኘው የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ‹ልማት ላለማ ነው› ብሎ በዚያ ያረፉ ክርስቲያኖችን ዐጽም አንሡልኝ እያለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የፕሮፌሰር ዐሥራት ወልደየስን፣ ቀጥሎ የመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን አሁን ደግሞ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ዐጽም አንሡ ብሏል፡፡ ለመሆኑ በዓለ ወልድ የማን ነው?

ለፕሮፌሰር ዐሥራት የማይሆን በዓለ ወልድ የማን ነው? ከልጅነታቸው ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ያደጉ፣ ቤተ መቅደሱን ያገለገሉ፣ በሕክምና ሞያቸው ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እስከ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያከሙ፣ አያሌ ጳጳሳትንና መነኮሳትን በየጊዜው እቤታቸው ድረስ እየመጡ ሲረዱ የነበሩትን የሕክምና ሰው እንደ ባዕድ ቆጥሮ ‹አንሥቼ ወደዚያ አደርጋቸዋለሁ› አለ፡፡ ገና ለገና ከዘመኑ ጋር አይስማሙም፣ በእርሳቸው ጉዳይ መንግሥት አይቆጣንም ብለው ካልሆነ በቀር የፕሮፌሰሩ ውለታ ጠፍቷቸው አልነበረም፡፡ ቀድሞውንም አቡነ ጳውሎስ ፖለቲካው ተጭኗቸው እንጂ ለጥላሁን ገሠሠ የሰጡትን የሥላሴ ቦታ ለፕሮፌሰር ዐሥራት መንፈግ አልነበረባቸውም፡፡ በርግጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዋሉባት እንጂ ለዋሉላት መሆን ካቆመች ቆየች፡፡

የፕሮፌሰር ዐሥራትን ጉዳይ ፓርቲዎቹ ጉዳየ ብለው በክብር አስፈጸሙት፡፡ ይመሰገናሉ፡፡ ፓርቲ አልባውን መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬንና ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ግን እንደ ተራ ነገር አንሡልኝ አለ አስተዳደሩ፡፡ ቤተ ክህነቱም አያገባኝም ብሎ ዝም አላቸው፡፡ ለመሆኑ በዓለ ወልድን የሊቀ ሥልጣናቱ ብቻ ያደረገው ማነው?እነዚህ ዛሬ ተነሡ የሚሏቸው ሰዎች እኮ ናቸው በዓለ ወልድን የሠሩት? ምእመኑን በእምነቱ አጽንተው እናንተ የሚከፈላችሁን ደመወዝ እንዳይቋረጥባችሁ ያደረጉት?ለመሆኑ አድማሱ ጀንበሬ የቤተሰቦቻቸው ናቸው? የደብሩ ካህናትና የሊቀ ሥልጣናቱ አይደሉም? ሲያስተምሩና ሲያገለግሉ የኖሩት፣ ሲጽፉና ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጋር ሲታገሉ የኖሩት ለቤተሰቦቻቸው ርስት ጉልት ለማሰጠት ነው? ኮኩሐ ሃይማኖት የተጻፈው ለቤተሰብ ነው? አድማሱ ጀንበሬ የቤተሰቦቻቸው ከሆኑ ነገ ያሬድም፣ አባ ጊዮርጊስም የቤተሰቦቻቸው ናቸው ልትሉን ነው?

እኒህ ሰውኮ የቤተክርስቲያን ከዚያም ሲያልፍ የሀገር ሀብት ናቸው፡፡ መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬኮ ሙት ያስነሡ ‹ቅዱስ› ናቸው፡፡ በሙት ዘመን ተፈጥረው ቅድስናቸውን የሚያውቅላቸውና የሚያውጅላቸው ጠፋ እንጂ፡፡ ታዋቂነት እንጂ ዐዋቂነት ክብር የማይሰጥበት ጊዜ ሆነ እንጂ ከአትናቴዎስና ከቄርሎስ የሚስተካከሉ ሊቅ ናቸው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን የሚነሡ አልነበሩም፤ ቤተ ክርስቲያን የሚሠራላቸው ነበሩ እንጂ፡፡ በምን ሂሳብ ነው ‹ቤተሰቦቻቸው መጥተው አጽሙን ያንሡልን› የሚባለው፡፡ ለመሆኑ ለመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬ ክብርና ፍቅር የሌለው ሰበካ ጉባኤ ሃይማኖቱ ምንድን ነው? ደብሩስ የማነው?

የእኒህ አባት ዐጽም የግድ ይፍለስ ከተባለኮ በቤተ ክርስቲያን የፍልሰተ ዐጽም ሥርዓት አለ፡፡ የነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የነ አቡነ ፊልጶስ፣ የነ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል፤ ከውጮቹም የነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዐጽም እንዴት እንደ ፈለሰ ከካቴድራሉ ዕቃ ቤት ያሉት መጻሕፍት በዝርዝር ያስረዱናል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ የት ሄዶ ነው የአንድ ደብር አስተዳዳሪ የኒህን ቅዱስ ሰው ዐጽም ‹አንሡ፣ ውሰዱ› የሚለው? ወይስ ዮሴፍን የማያውቅ አዲስ ፈርዖን መጣ?

ቤተ ክህነቱ መጽሐፋቸውን አሳትሞ ከመሸጥ ውጭ አያገባውምን? ዛሬ በመልአከ ብርሃናት አድማሱ ላይ እንዲህ ከተደረገ ነገ የየአንዳንዱ ጳጳስና ካህን ፋንታ ዕጣ ከዚህ የከፋ መሆኑን ረሳው? ዛሬ በበዓለ ወልድ የተጀመረው ነገር ሃይ የሚለው ካጣ ወደ ካቴድራሉ ተዛምቶ የማን ዐጽም እንደሚነሣ መንግሥትስ ጠፋው?

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የተማሩት በዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ የደከሙት ለዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ ያገለገሉት ሀገራቸውን ኢትዮጵያን – እንዴት ባለ ሂሳብ ነው አዲስ አበባ ለቴአትሩ ንጉሥ ቦታ የላትም ተብሎ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ዐጽሙ ይሂድ የሚባለው? ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ መቀበርም የሚቻለው በክልላችሁ ነው ልትሉን ነው? ዮፍታሔ ንጉሤ የደብረ ኤልያስ ብቻ ናቸው? ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ያበረከትሺውን ሰው ጥቀሽ ስትባል ከምትጠቅሳቸው ተርታ አይደሉምን? ይህ ለትውልዱ እየሰጠነው ያለው ትምህርት የት የሚያደርስ ነው?

መሐል ሠፋሪ ጦር ጃንሜዳ እየተሰበሰበ አንዴ እቴጌ ጣይቱ ከቤተ መንግሥት ይውጡ፣ አንዴ ሚኒስትሮቹ ይነሡ ሲል፣ መኳንንቱም እየተቀበሉ ሲያስፈጽሙ፣ እቴጌ ጣይቱ ‹ለዚህ ጦር ክፉ ትምህርት አታስተምሩት፣ ካልሆነ ሁላችሁንም ያወርዳችኋል› ብለው ነበር፡፤ ሰሚ አልተገኘም፡፡ ያው ጦር ግን በ66 ዓም ንጉሡንም መኳንንቱንም አወረደ፡፡ ያውም እንደ እቴጌ ጣይቱ ወደ እንጦጦ አልላካቸውም ፣ ወደ እንጦሮጦስ እንጂ፡፡ ዛሬም ለዚህ ትውልድ ክፉ ትምህርት ባታስተምሩት መልካም ነው፡፡ ዐጽም እያሽቀነጠሩ ሱቅና አዳራሽ መሥራት ነገ በዐጽመ ቅዱሳን መወጋትን ያመጣል፡፡ ሲሠራና ሲታደስ ገንዘብ ካላመጣችሁ የምትሉን ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲህ ደስ ሲላችሁ ዐጽማችንን የምትወረውሩበት ከሆነ በዓለ ወልድ የማነው? ብለን እንጠይቃለን፡፡

በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጽር ውስጥ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሕንጻ እየሠራ ነው፡፡ ከሕንጻው አጠገብ አንድ አምስት መቃብሮች አሉ፡፡ አንዱ የጣልያን ወታደር፣ ሌሎቹ የኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት እነዚህን ዐጽሞች እግር ከሚጠቀጥቃቸው በክብርና በሥርዓት አንሥተን በተገቢው ቦታ እናድርጋቸው፣ ብለው ጠየቁ፡፡ ቤተ ክህነቱ የሰጠው መልስ ግን አስገራሚ ነበር፡፡ ‹ከመቃብሮቹ መካከል የኢትዮጵያውያንን እንደፈለጋችሁ ማንሣት ትችላላችሁ፤ የጣልያኑን መቃብር ግን እኔ መፍቀድ አልችልም› አላቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለጣልያን ወታደር የምትሰጠውን ቦታ ያህል ለአድማሱ ጀንበሬና ለዮፍታሔ ንጉሤ የላትም?

ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ  – ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ – የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ – ይሉ ነበር፡፡

Posted by ዳንኤል ክብረት

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *