Written by  በሀብታሙ ግርማ – 

 መንደርደርያ

በጥበብ ተሰጥኦውና በተክለ-ሰብዕናው የማደንቀው እና የምወደው ድምጻ ቴዎድሮስ ካሳሁን አምስተኛው የሙዚቃ አልበም ‹ኢትዮጵያ›ን ላለፉት በርካታ ሳምንታት በጥሞና አጣጥሜዋለሁ፡፡  አልበሙ የወጣ ሰሞን በጻፍኩትና በሪፖርተር እንግሊዝኛው ጋዜጣ ላይ ለንባብ በበቃው ጽሁፌ፤ ስራው የቴዲን የግጥም  ችሎታ ብቻ ሳይሆን የአማርኛ ቋንቋ ነገሮችን የመግለፅ አቅምና ብቃት ልክ ያስገነዘበ መሆኑን፣ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባልተናነሰ ለአማርኛ ቋንቋና ስነጽሁፍ ዘርፍ ዕድገትም አንድ ነገር ይጨምራል ብዬ እንደማምን ጠቅሼአለሁ፡፡ ከ600 ገጽ በላይ የሚሆነውንና በእኔ እምነት የአለም ስነ ጽሁፍ ቅርስ የሆነው የሃዲስ አለማየሁን ‹ፍቅር እስከ መቃብር›ን በስድስት ደቂቃ ገደማ በ ‹ማር እስከ ጣፍ› ሙዚቃው በጥበብ ሃይል አስክሮናል፤ አስፈንድቆናል፡፡ በ‹ኢትዮጵያ› አልበም ውስጥ፤ ልክ እንደ ‹ማር እስከ ጣፍ› ሁሉ ‹ሰምበሬ› የሚለው የሙዚቃ ሥራውም፣ ያለንበትን ዘመን ገጽታ አጠር አድርጎ ይነግረናል፡፡ የዚሁ ሙዚቃ አዝማች ‹ጉራ ብቻ›፤ ቸል ብለን እያየነው ያለውን፣ ነገር ግን ሊያጠፋን ቋፍ የደረሰውን የአገራችንን ወቅታዊ ችግር በአራት ፊደላት አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡ በግሌ የሙዚቃው (የአልበሙ አላልኩም) ርዕስ “ጉራ ብቻ” መሆን ነበረበት እላለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የጥበብ ስራዎች ዋጋቸው የሚተመነውና ለደራሲው አድናቆት መለገስ ቢያስፈልግ የምንሰጥበት አግባብ መሆን ያለበት ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት አስቦበት ነው አይደለም  በሚለው ጉዳይ ሳይሆን፣ ሃሳቡ ምን ያህል ገዢ ነው በሚለው መሆን አለበት፡፡ የመልዕክቱ ገዢ ሃሳብ መሆን ማለት ደግሞ በተለያየ ቅርፅና አውድ የተለያዩ ነገሮችን ለማሳየትና (ወይም) ለመግለጽ የመቻል አቅሙ ነው፡፡ ጥበብን ጥበብ የሚደርገውም  ስራውን እንደፈለግነው መመንዘራችን ነው፡፡ በእርግጥም ‹ኢትዮጵያ› አልበም እንደ ልብ የመመንዘር አቅም ባላቸው የሙዚቃ ሥራዎች  የተሞላ ነው፡፡ በመሆኑም እኔ የ‹ሰምበሬ› ሙዚቃን መልዕክት የመነዘርኩት ራሴ በተረዳሁበት ልክ እንጂ አረዳዴን  ቴዲ አፍሮ ይጋራው አይጋራው አላውቅም፡፡
‹ሰምበሬ› ሙዚቃ ላይ አዝማች የሆነው “ጉራ ብቻ” ትልቅ ጽንሰ-ሃሳብ (concept) ነው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ይህን ስል በምክንያት እንጂ እንዲያው በጉራ መንፈስ አይደለም፤ ጽንሰ ሃሳብ የሚለው ቃል ትርጉሙ በውስጡ ብዙ ሃሳቦችን ጸንሶ ያለና የሚገልጽ ጉዳይ ማለት ስለሆነ ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ አብይ አላማም ‘‹ጉራ ብቻ› ውስጥ ምን ምን አለ?’ እና (ወይም) ‘‘‹ጉራ ብቻ› ምን ያህል የምንኖርበትን ዘመን ይገልጻል?’ የሚል ነው፡፡ ሀተታዬን ሳብራራ በሁለት ማዕቀፎች (domain) መገደብ መርጫለሁ- በግለሰባዊ ወይም በማህበራዊ ተራክቧችን (social transactions) እንዲሁም በፖለቲካዊና በመንግስት አስተዳደራችን (political system and governance)
‹ጉራ ብቻ› ማነው?
‹ጉራ ብቻ› በመንፈስም በቁስም ሰንካላ የሚያደርግ፣ ራሱን ቀስ እያለ የሚያሰፋ መርዝ ነው፡፡ ይህ መርዝ የነካው ሰው መርዙን በደረሰበት ሁሉ ያዛምታል፡፡ በግል መጎረር እንዳለ ሁሉ ተደራጅቶም ይቻላል፤ እናም ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊ መልክ ሊይዝ ይችላል፡፡ ቡድናዊ ስል የመንግስት (የግል) ተቋም፣ የፖለቲካ ቡድን፣ ስልጣን ያለው አስተዳደር ወይም መንግስት ለማለት ነው፡፡ በግለሰብም ይሁን በቡድን ወይም ተቋማት አሊያም  በመንግስት ደረጃ ‹ጉራ ብቻ› መገለጫዎቹ ተመሳሳይ ናቸው፤ በሌሎች ዘንድ የሌለን ምስል ለመሳል የሚደረግ ከንቱ ጥረት ነው፤ የጮሌነት ወይም የእወደድ ባይነት ጠባይ ነው፤ እኔ ብቻ አዋቂ ባይነት ነው፤ ለቃል አለመታመን ማለት ነው፡፡
በመሰረቱ ‹ጉራ ብቻ› ን ስንተዋወቀው ፈልገነው እንጂ ፈልጎን አይደለም፡፡ ከመኖሪያው ጎራ ስንል ለሁለት ጉዳይ ነው፤ ወይ የምንፈልገውን ነገር ለማሳካት፤ አልያም የጉራ ሱስ የለከፈን እንደሆነ ሱሳችንን ለማስታገስ ነው፡፡ የጉራ መነሾዎች መልካቸው ሁለት ቢመስልም በግብር ግን አንድ ናቸው፤ ሁለቱም የግል ጥቅምን (self-interest) ወይም ግለኝነትን (individualism) በተሳሳተ ሁኔታ በመረዳት የመነጩ ናቸው፡፡ ጉራ ብቻ የምንፈልገውን ካሳካን በኋላ ብንተወው እንኳ እርሱ አይተወንም፤ አመል ሆኖ እላያችን ላይ ተጣብቆ ይኖራል፡፡ ከተመቻቸንለት ደግሞ ጠባይና ባህሪያችን ይሆናል፤ እናም በዙሪያችን ላሉ፣ ለልጆቻችን፣ ለምናስተምራቸው ተማሪዎች፣ ለምንመራቸው ሰራተኞች፣ በሽርክና ለምንሰራ የቢዝነስ አጋሮቻችን፣ ለምንመራው ፖለቲካና ህዝብ ወዘተ እናስተላልፋለን፡፡ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች፣ ተቋማት ሁሉ ጠባይ ይሆናል፡፡ አልፈልግም ያለ ሳይቀር የግድ የጨዋታው አካል እንዲሆን፣አለበለዚያ  ከጨዋታ ውጪ እንደሚሆን በማስፈራራት (bullying) ተከታዩ እንድንሆን የማድረግ ዘዴ ይጠቀማል፡፡ በዚህ ደረጃ ሲደርስ ‹ጉራ ብቻ› ሁለት መልክ ይይዛል – ዝቅ ሲል ቃል አባይነት፣ ከፍ ሲል ደግሞ ማጭበርበር፤ ህብረተሰቡና አገር የሚመራበት መርህ ይሆናል፤ መርዙንም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ መስክም ይሁን በሌላ ዘርፍ ያሉ ግንኙነቶች መሰረት በሆኑት መተማመንና መከባበር ላይ ይረጫል፤ በውጤቱም የግለሰቦችን፣ ማህበራዊም ይሁን መንግስታዊ ተቋማትን ተአማኒነት ይሸረሽራል፤ የእርስ በርስ ግንኙነታችንንም ያሻክራል፤ እንደ ሀገርና ህዝብ ህልውናችንን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡
‹ጉራ ብቻ›፣ እኛ እና ማህበራዊ መስተጋብራችን
የልጅነት አመል ከላዬ ላይ እየተቀረፈ ከመጣበትና የማህበራዊ ተሳትፎ ጀመርኩ ከምልበት፤ የአገሬን ጉዳይ በንቃትም ባይሆን እንኳ በርቀት መቃኘት ከጀመርኩበት ካለፉት አስር ዓመታት በላይ በግለሰባዊና ማህበራዊ ህይወት እንዲሁም ካነበብኩትና ከሰማሁት መንግስታዊ ጉዳዮች እንደምታዘበው፤ ጉራ ብቻ ስር እየሰደደ ያለ፣ የህዝባችንና የአገራችን መጋኛ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡
በጥልቀት ለተመለከተ እያበቡ ያሉ (emerging) ግለሰባዊም ሆነ ማህበረሰባዊ ችግሮቻችን መነሻቸው በአንድም ይሁን በሌላ ጉራ ብቻ ነው፤ የግል ጥቅምን አለአግባብ መረዳት፡፡ የግል ጥቅምን ጽንሰ ሃሳብ አለማወቃችን በያለንበት መስክና ግንኙነት የዛሬን የዛሬን ብቻ እንድናስብ ሆነናል፤ ድርጊታችን ሁሉ ለመጪው ትውልድ ይቅርና ለራሳችን እንኳ ነገ ላይ ስለሚያመጣብን መዘዝ ደንታ ቢስ አድርጎናል፡፡ እንዲህ ባደርግ እንዲህ ልሆን እችላለሁ፤ በምናውቀውም ይሁን በማናውቀው አለማዊም ይሁን ሰማያዊ (ሃይማኖታዊ) ህግ ልዳኝና ልቀጣበት እችላለሁ ብሎ ማለት የፌዝ ሆኗል፡፡ በውጤቱም በቃል አባይነት፤ በሙስና፤ በብዝበዛ፤ በሃጢአት አድፈናል፡፡ ዛሬ ዛሬ የአጭር ግዜ እቅዱንና ፍላጎቱን ለማሳካት ሲል እኔ ይህን ያህል ሃብት (ዕውቀት)አለኝ፣ እንዲህ አደርግልሃለሁ (አደርግልሻለሁ) በሚል መደለያ የሚኖር በዝቷል፤ ጉዳዩን ሲጨርስ ግን አዲዮስ!
አንዳንዱ ደግሞ  እንዲያው ጉራ ሱስ ሆኖበት ቃል ሲገባና ባዶ ተስፋ ሲሰጥ መታዘብ ከተለመዱ የዕለት ውሎአችን አንዱ ሆኗል፡፡ በተግባር ግን ዜሮ ነው፡፡ በግሌም በርካታ ጊዜ የጉራ ሰለባ ሆኛለሁ፤ እኔም ሌሎችን የጉራ ሰለባ ያደረኩበት አጋጣሚ ቢፈለግ አይጠፋም። ነገር ግን የአገሬ ሰው ‹‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም›› ይላልና ይበልጥ የማስታውሰው የደረሰብኝን ነው፡፡ በመሰረቱ ጉራ ብቻ ተክለ ሰብዕናችንን ይበክላል፡፡ እንደ ጮሌነት፣ አታላይነት፣ውሸታም፤ ክህደት የመሳሰሉ ከራስ ጋር እንኳ የሚያጣሉ ጠንቅ ጠባያትን ያለማምደናል። በግለሰብ ደረጃ ጉራ ብቻ ከራሳችን ጋር እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያቀያይመናል፡፡ በውጤቱም መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥቅማችንን ይነካል፡፡ ከራስ ጋር በሚኖረው መስተጋብር ከንቱነት እንዲሰማን ያደርገናል፡፡ ነገሩ በእርግጥም አንድ ጤነኛ የሆነ፣ በሳል ሰው እንደሚሰማው ነው። ይህ ሰው ከራሱ ጋር ተማከሮ፣ቃል ገብቶ ሳያደርገው ሲቀር የሚሰማው ስሜት የርካሽነት፣ የከሃዲነት፣ በራሱ እምነት ማጣት ነው፡፡ በማህበራዊ ግንኙነት መስኩም መተማመንና መከባበርን ያጠፋና፣ማህበራዊ ግንኙነቶቻችንን ያበላሻል፤ በየግንኙነታችን ሁሉ ጉራ ብቻ ከሆንን ዘላቂ ጥቅማችንን እናጣለን፡፡ በሌሎች ዘንድ እምነት ስለማናገኝ በማህበራዊ ኑራችን መገለል ይደርስብናል፡፡ በኢኮኖሚ ህይወታችንም እንዲሁ ነው። በዘመናችን ከዕለት ወደ ዕለት  የካፒታሊዝም ተፅዕኖ እየበረታ መሆኑ ሃቅ ነው፤ ካፒታሊዝም በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚ ገፁ የሚፈልገው ዋና ምግብ ስነ ምግባር ነው- የነቃና ዘላቂ ጥቅሙን ያገናዘበ ውሳኔ የሚወስን የኢኮኖሚ ሰው፤ መብቱና ግዴታውን የሚያውቅ ህዝብ ይፈልጋል፡፡ ይህ የጉራ ብቻ ጠባያችን ደግሞ ስርዓቱ ከሚፈልገው ጋር አምርሮ የሚጣላ ነው፡፡ እንግዲህ የጉራ ብቻ ጠባይ የማይለቀን ከሆነ የኢኮኖሚው መርህ መበላላት ወይም ብዝበዛ በማድረግ በነጋዴና በሸማቾች መካከል የማይታረቅ ቅራኔን ይፈጥራል፤ የኢኮኖሚ መላሸቅ (economic paralyse) ያስከትላል፡፡
‹ጉራ ብቻ›፣ ፖለቲካችን እና መንግስታችን
‹ጉራ ብቻ› ኢትዮጵያን አንካሳ እያደረገ ያለ ክፉ ደዌ ነው፡፡ በሃገር ጉዳይም  ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡  በየጊዜው ሃሳቦች ይመከራሉ፣ ይዳብራሉ፣ ይነገራሉ፤ቃል ይገባል፣ ዕቅድ ይታቀዳል፣ ህግ፣ አዋጅ፣ መመሪያ ወ.ዘ.ተ ይወጣል ግን ተግባር ላይ ዜሮ ነው፡፡ ፍላጎታቸውን ተራ ዝና፣ ኢኮኖሚ፣ ፕሮፓጋንዳ፣ ፖለቲካ፣ መንፈሳዊ ወዘተ በማድረግ የተቧደኑ በርካቶች በ‹ጉራ ብቻ› ከበሮ እያደነቆሩን ነው፡፡ ታዲያ ህዝብ አምኖ እንዲከተላቸው ካደረጉ በኋላ ጥቅማቸውን ሲያሳኩ፣ በጓሮ በር ዞር ማለታቸውን |ሳያፍሩበት፣ በአደባባይ አንገታቸውን ሰበር እንኳ ሳያደርጉ በማናለብኝነት ሲንጎዳጎዱ መታዘብ አዲስ አይደለም፡፡
“ጉራ ብቻ” በመሰረቱ ህዝብ በፖለቲካ ስርዓቱና በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ በማድረግ፣ የህዝቡን ሰላም እንዲሁም የአገሪቱን ስትራቴጂያዊ ጥቅሞችን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡  የመንግስት አስተዳደርና ተቋማዊ ተዓማኒነትን ይሸረሽራል፡፡ በዚህም ህዝብ በመንግስት ላይ ዓመኔታ እንዲያጣ መንገድ ያመቻቻል፡፡
የ‹ጉራ ብቻ› መሰረቱ ግለኝነትን በተሳሳተ ሁኔታ መገንዘብ እንደሆነ ቀደም ብሎ ተብራርቷል፤ ‹ፖለቲካ ደግሞ ለህዝብ ጥቅም ሲባል መስዋዕት መሆን ማለት ነው፤ የ‹ጉራ ብቻ› መርዝ ግን ይህን ትክክለኛ የፖለቲካ ምንነት (ተክለ ቁመና) በማዛባት፣እንዲያውም ተቃራኒ መልክ በመስጠት፣ ፖለቲካ የእርስ በርስ (በግል ወይም በቡድን ተደራጅቶ) ቂም በቀል መወጫ፣ የኢኮኖሚ ፍላጎት ማሳኪያ እየሆነ መምጣቱ  የፖለቲካ ስርዓቱ ዋና ስንክሳር ሆኗል፡፡
ዘመናዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ተጀመረ ከሚባልበት ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ያለውን ብንቃኝ የሚነግረን፤ በፖለቲካ ቡድኖች መካከል አንድነትን ወይም ልዩነትን የሚፈጥረውና እርስ በርስ የሚያተጋግለው  የርዕዮተ ዓለም ልዩነት አይደለም፤ የተሳሳተው የግለኝነት አረዳድ፣ ‹ጉራ ብቻ› እንጂ፡፡ ‹ጉራ ብቻ› በፖለቲካ ቡድኖች መካከል “እኔ እበልጥ እኔ” በሚል መንፈስ እንዲመሩ አድርጓል፡፡ ዛሬም ቢሆን ገዢውም ሆነ ተቃዋሚዎች (ሰላማዊም ሆኑ ነፍጥ ያነሱ) ከ‹ጉራ ብቻ› አዙሪት አልወጡም፡፡ የቅርብ ሳምንታት የፖለቲከኞቻችን ሁኔታም ከዚሁ የመነጨ ነው፡፡ “ከእኔ ውጭ ትክክል የለም” ከሚል አባዜ ተላቀው፣ ሰጥቶ መቀበል የሚለውን መርህ ከልብ መቀበል ካልቻሉ፣ ከፖለቲከኞቻችን ከ‹ጉራ ብቻ› ውጭ ምንም አንጠብቅም፡፡ የአለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት የ10.5 አማካይ ዓመታዊ የተጣራ (real) የጠቅላላ አገራዊ ምርት (Gross Domestic Product-GDP) እድገት እንዳስመዘገበች አስታውቋል፡፡ በርካታ አለማቀፍ የዴሞክራሲ፣ የነጻ ሚዲያና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም፤ ይህን የአገሪቱን ዕድገት ተቀብለው ነገር ግን የፖለቲካውና የሰብዓዊው መብት ጉዳይ ግን ወርዷል ሲሉ ከርመዋል፡፡ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞችም፤ ይህ ሁኔታ የአገሪቱን ዕድገት ወደ ኋላ ይጎትተዋል፣ ዲሞክራሲው ላይም መሰራት አለበት ሲሉ ደጋግመው ወትውተዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ግን ይህን ችላ ብሎ ቆይቷል፤ ፓርቲው “ሙያ በልብ ነው” የሚል የሚመስለውን የቀደመ ባህሉን ትቶ፣ ጉረኞችን ከተቀላቀለ ብዙ ዓመታት ተቆጠሩ። እዚህ ጋ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ፤ ‹ኢህአዴግ ኪሎው ስንት ነው?› ብሎ ያጠየቀበት አንድ መጣጥፉ ትዝ አለኝ። በ‹ጉራ ብቻ› መርዝ ተለክፎ ሚናቸውና ተፅዕኖአቸው እምብዛም ከሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር እልህ እየተጋባና እየተበሻሸቀ፣ በመሃል ዋና ሥራውን ዘንግቶታል፤ የዲሞክራሲውን ጉዳይ፣ የህዝብን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች፡፡ በቅርቡ ለገጠመው አይቶት የማያውቀው ፈተናም  ምክንያቱም ይህ ነው፡፡
በመንግስታችን ውስጥ በየጊዜው “ጉራ ብቻ” የሆኑ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ችግሩ የማስፈጸም  እንጂ የፖሊሲ  አይደለም እያለ የፕሮፓጋንዳ ያህል ደጋግሞ ሲነግረን ይኸው ሩብ ክፍለ ዘመን አለፈው፡፡ በእርግጥም ችግሩ “ጉራ ብቻ” መሆኑ ራሱ መንግስት ተቀብሏል፡፡ “ጉራ ብቻ” በመንግስት መዋቅር መርዙን የሚያዛምትባቸው መንገዶች ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ናቸው፡፡
በመንግስታዊ ማዕቀፍ “ጉራ ብቻ” ራሱን የሚገልጽበት አንዱና ዋነኛው መልክ ራሱ ላወጣቸው ህጎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ አሰራሮች ቸልተኛ መሆን፣ ከፍ ሲልም አለመገዛት ነው፡፡ ለአብነትም የቅርቡን የአገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ  መነሾዎች ለመረመረ፣ የፖለቲካ ትኩሳቱ ምንጭ የህዝብ ለህዝብ ግጭት፣ የማንነት ጥያቄ ወይም የማስተርፕላን ጉዳይ ሳይሆን መንግስት “ጉራ ብቻ” ሆኖ ሰንብቶ፣ ቃል  የገባውን ሳይፈጽም መቅረቱ፣ ላወጣው ህግና አዋጅ መፈጸም ቸልተኝነት ማሳየቱ ነበር፡፡ ለአብነትም የአዲስ አበባ ዙሪያ (ፊንፊኔ) የኦሮሚያ ልዩ ዞን እና አዲስ አበባ ከተማን የሚያስተሳስረው መሪ ዕቅድ ወይም ማስተር ፕላን ጉዳይ አወዛጋቢ ሆኖ የተነሳው ያለፉትን ሁለት አስርት ዓመታት በ‹ጉራ ብቻ› ዳንኪራ በማሳለፋችን ነው እንጂ የችግሩ መፍትሄ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ላይ በግልጽ ተቀምጦ ነበር፡፡ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ እንደተቀመጠው፤ የአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የኦሮሚያ ዙሪያ ህዝብ ከአዲስ አበባ ማግኘት የሚገባው ጥቅሞች በህግ እንደሚዘረዘር ይጠቅሳል፡፡ ህገ መንግስቱ ከጸደቀበት ካለፉት 22  ዓመታት ወዲህ  ግን ይህ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቶ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖር የኦሮሚያ አርሶ አደር ከመሬቱ መፈናቀል ዕጣ ፈንታው ሆነ፡፡ የኦሮሚያ ህዝብ ቀድሞውኑ በህገ መንግስቱ የተደነገገለት መብት ሳይከበርለት ሲቀር  በመንግስት ላይ አመኔታ አጣ፡፡ እናም የማስተር ፕላኑ ተቃውሞ መልዕክት፤ “በመንግስት ላይ አመኔታ አጥተናል፤ የኦሮሚያ አርሶ አደር እስከ ዛሬ የተበዘበዘው ይበቃል፤ በማስተር ፕላን ሰበብ ደግሞ ሌላ ብዝበዛ አናስተናግድም” ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት የህገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ቀደም ባሉት ዓመታት ተግባራዊ ቢደረግ ኖሮ፣ የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ዞንን የሚያስተሳስረውና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሀይል እምብርት ይሆናል የተባለው  የከተማ መሪ ዕቅድ ከተቃውሞ ይልቅ  ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ያገኝ ነበር፡፡ ከዚህ ‹ጉራ ብቻ› አባዜ መላቀቅ እስካልቻልን  ድረስ እንደዚህ ያሉ የአገርና ህዝብ ስትራቴጂያዊ ጥቅሞች እክል ይገጥማቸዋል፡፡
በመንግስታዊ አሰራር ውስጥ “ጉራ ብቻ” ራሱን የሚገልጽበት ሌላ መልክና ገጽታ አለው፤ ይህም ልክ ያልሆነ ዕቅድ ማቀድ በቢሮክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ በማላመድ ነው፡፡ ልክ ያልሆነ ዕቅድ ሲባል ከአቅም በታች አውርዶ ወይም ከአቅም በላይ ለጥጦ ማቀድ ማለት ነው፡፡ በዚህ መልኩ የታቀደ ዕቅድ፣ ዓላማው ሃብትን በአግባቡ አቀናጅቶ ተጠቅሞ ስራን ለመከወን ሳይሆን “ጉራ ብቻ” የተጠናወታቸውን ሹመኞች ወይም የበላይ አካላትን ትኩረት  ለመሳብ ወይም ለማሳመንና ሰፋ ያለ የስራ ማስኬጃ  ገንዘብ (budget) ለማሳካት አሊያም ተጨማሪ ሥልጣንና ሹመት ለማግኘት ነው፡፡ ዕቅዱ ተፈጻሚ መሆኑን ሪፖርት ሲዘጋጅም፤ እንዲሁ ‹ጉራ ብቻ› ሌላ ልብስ ለብሶ ይታያል፤ ያልተሰራ ስራ ወይም ያለውን አጋንኖ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ይዘጋጃል፤ በወረቀት የቀረበው በተጨባጭ ካለው ገዝፎ የሚታይ፣ አንዳንዴም ጨርሶ የሌለ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚም ይኖራል፡፡ በዚህ መልኩ የመንግስት መዋቅሩ አቅምና ችሎታ ያላቸውን ገሸሽ አድርጎ ‹ጉራ ብቻ›፣ ‹ወሬ ብቻ› በሆኑ ቢሮክራቶች ሲወላገድ መቆየቱ፣ በየመስሪያ ቤቱ ያሉ ወንበዴዎችን ሲታደግ የኖረ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፈልፈያ የሆነ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ህዝብ በመንግስት ተቋማትና በቢሮክራሲያዊ አስተዳደር (Bureaucratic Goverance) ስርዓቱ ላይ አመኔታን እንዲያጣ ሆኗል፡፡ የዚህ አንዱ መገለጫም መንግስት በቅርቡ የገጠመው አይነት ፈተና፣ ማለትም ህዝቡ ለመንግስት ያለው ተዓማኒነት መዝቀጥ (legitimacy of Government) ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢህአዴግ መራሹ መንግስታችን፤ “እኔ ብቻ አዋቂ” በሚል አደገኛ ደዌ ክፉኛ ተጠቅቶ ከርሟል፡፡ በፖሊሲ ጥራት አንደኛ፣ በአፈጻጸም ግን  ውራ ያስቀረንም ይኸው ‹ጉራ ብቻ› አባዜ ነው፡፡
አሁን ያለፈው ስህተትና ችግር ሁሉ አልፏል፤ ዋናው ቁምነገር በቀጣይ ከዚያ ስህተት ምን ተማርን ወይም  ምን እንማር የሚለው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከጥቂት ወራት በፊት ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌአለሁ፣ የስርዓቱ ችግሮች ሁሉ መሰረት በፖለቲካም ይሁን በቢሮክራሲያዊ አስተዳደር ያሉ አመራሮቼ ላይ ያለው የተንሸዋረረ የስልጣን አረዳድ ነው፤ አመራሮች ስልጣንን  የህዝብ ማገልገያ መሳሪያ ሳይሆን የግል ፍላጎታቸው መጠቀሚያ አድርገው ወስደውታል ነበር ያለው፡፡ እንደ ማስረጃ የቀረቡትም  ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ነበሩ፡፡ (በነገራችን ላይ መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲው በፖለቲካ ችግሮቹ ላይ ጥልቅ ጥናት አድርገዋል የሚል ዕምነት የለኝም) ይሁንና ይህን የመንግስት የዳሰሳ ውጤት ብንቀበል እንኳን የጥልቅ ተሃድሶው ውጤት የሚነግረን ሌላ ሳይሆን ‹ጉራ ብቻ› ራሱን አጎልብቶ መንግስትና ህዝብ የሚመራበት መርህ ሆኖ እንደከረመ ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ “ጉራ ብቻ” ዋነኛ ችግሩን እንደሆነ መለየቱ አንድ ነገር ቢሆንም ምን ያህል ተረድቶታል፣ ለመታገልስ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው የሚለው ደግሞ ሌላ ነው፡፡ በቅርብ ወራት፣ ማለትም ከተሃድሶ በኋላ ባሉት ወራት እንኳ የ”ጉራ ብቻ” ምልክቶች የመደብዘዝ ምልክት አላሳዩም፡፡ በነዚህ ጊዜያት በተለያዩ አካላት ይነሱ የነበሩ ችግሮችና የህዝብ ቅሬታዎች ቀጥለዋል፡፡ መንግስት ከሰባት ዓመት በፊት፣ ማለትም በምርጫ 2002 ሰሞን ይዞት ከተፍ ያለውና ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ያማለለው የ10/90፣ የ20/80 እንዲሁም የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት እነሆ ከስድስት ዓመታት በኋላ መንግስት፤  “የፋይናንስ ችግር ገጥሞኛል፣ ሌላ አማራጭ እስከምፈልግ ታገሱ” ማለቱን በሚዲያ ላይ አንብቤአለሁ፡፡ ስድስት ዓመት ሙሉ ከዕለት ጉርሱ ሲቆጥብ የከረመ ተመዝጋቢን ምን ሊሰማው እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡  ተጽዕኖው ቀላል አይደለም፤ ዜጎች በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጡ ያደርጋል፡፡  በቅርብ ወራት ቆሼ በተባለው የአዲስ አበባ ክፍል ዜጎች ለደረሰባቸው አደጋ ቃል የተገባው የመልሶ ማቋቋም ጉዳይም  ተመሳሳይ መልክ አለው፡፡ ተጎጂዎች ከከንቲባ ድሪባ ኩማ እጅ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቁልፍ ከተቀበሉ ጊዜያት ቢያልፉም፣ ቤቱን ግን እንዳልተረከቡ ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር፤ መንግስት ቤቶቹን ለማስረከብ የቱንም ያህል የአጭር ጊዜ ችግር ቢገጥመው እንኳ ተጎጂዎች የነበሩበት ሁኔታ አንድም ቀን ሊያስታግስ የማይችል ነበርና መንግስት ለገባው ቃል አፋጣኝ መልስ መስጠት ነበረበት፡፡ በአጠቃላይ በማህበራዊው፣ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው እየበረቱብን የመጡ አገራዊ ችግሮች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የ”ጉራ ብቻ” ውጤቶች ወይም ነጸብራቆች ናቸው፡፡
ከ‹ጉራ ብቻ› መርዝ
የሚፈውሰን ምን ይሆን?
በግለሰብም ይሁን በቡድን ተደራጅተን ለምንገኝ  የ›ጉራ ብቻ› ክፉ  መንፈስ ሰለባዎች ከደዌው ለመፈወስ ቀላል ነው፡፡ ለፈውስ ራስን ዝግጁ ማድረግን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ ዋናው ነገር “ጉራ ብቻ”ን ከላይ ከላይ ሳይሆን ከውስጣችን አምርረን መጥላት ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ህይወታችንን በምክንያት መምራት፤ ለህገ-ህሊና (Moral law) ራስን ማስገዛት ከ”ጉራ ብቻ” ለመንጻት ፍቱን መድሃኒት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በእኔ ዕይታ፤ የህይወታችን መርሆች ሊሆኑ የሚችሉና የሚገቡ፣ ከ”ጉራ ብቻ” የሚያስጥሉን መልእክቶች በሥነቃሎቻችን ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በእኔ ትውስታ፣ በአማርኛ ከማውቃቸው ‹ሙያ በልብ ነው›፤ ‹ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›፤ ‹ለወሬ የለውም ፍሬ› ወ.ዘ.ተ ተጠቃሽ ናቻ፡፡ ሌላው “ጉራ ብቻ” የተጠናወታቸው በዙሪያችን ካሉ፣ ይህን ጠባያቸውን በዝምታ አለማለፍ፤ እንደየቅርበታችን ተገቢውን እርምት እንዲወስዱ፤ቢያንስ በማናለብኝነት ነገም እንዳይደግሙ ማድረግ፡፡ ታዝቦ ዝም አለማለት፤ “ለመሆኑ እንዲያ ያልከኝ ነገር ምን ደረሰ?”፤“ጉዳዬን ምን አደረግክልኝ?“፤ ቃል የገባህልኝስ ነገር?” ብለን ማፋጠጥ፡፡ ደዌው ያልበረታበት ከሆነ ራሱ ያፍርበታል፣ ይሸማቀቅበታል፤ አለበለዚያ የሌባ አይነ ደረቅ አይነት ጠባይ ሊያሳይ የሚችል ካለ ጠንከር ያለ መልስ መስጠት፤ “ወሬ ሩዝ አይቀቅልም” የሚለውን የቻይናዎቹን አባባል ማስታወስ፡፡
መንግስትና የፖለቲካ ቡድኖች ከ”ጉራ ብቻ” በሽታ ይፈወሱ ዘንድ መፍትሄው፣ የህዝብን ጉዳዮች ለፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ከማዋል  መታቀብ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲና የሚመራው መንግስት የሚሰራው ለአገርና ለህዝብ እስከሆነ ድረስ አገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮችን ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን (ህዝቡን፣ ምሁራንን፣ ተቃዋሚውን፤ ዳያስፖራውን) በማቅረብና በማሰባሰብ “የአገራችሁ ጉዳይ ነውና እንማከር፤ እንከራከር፤ እናዳብረው” የማለት ፖለቲካዊ ብስለትና ባህል ማዳበር ይጠበቅበታል፡፡ ስርዓቱ ራሱን ከምር ሊያድስ የሚሻ ከሆነ፣ ብቸኛው መንገድ ከ ‹ጉራ ብቻ› አዙሪት መውጣትና መራቅ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ለተቃዋሚውም ጎራ ይሰራል፡፡ ሁላችንም ከ‹ጉራ ብቻ› ክፉ መንፈስ እንፈወስ ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን!!
(ከአዘጋጁ፡- የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ  ሀብታሙ ግርማ፤ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ከፍል መምህር ሲሆኑ፤ ለአስተያየት ወይም ከጸሃፊው ጋር ለመገናኘት በሚከተሉት የኢሜይል አድራሻዎቹ መጠቀም ይቻላል፡- ruhe215@gmail.com orhab200517@yahoo.com)

Related stories   እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እቅዷን ይፋ አደረገች፤ ዶክተር ዳንኤል የማይካድራን ጂኖሳይድ ዝም ማለቱ ክህደት ነው

አዲስ አድማስ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *