ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ደረጃ ባይኖረኝም … በግብር ከፋይነቴ እኮራለሁ፤ እኮራና ደግሞ አፍራለሁ …

ተሜ

እኮራና ደግሞ አፍራለሁ፡፡ ኮርቼ ሳላበቃ እንደገና አንገቴን እደፋለሁ፡፡ግብር መክፈል ክብር ከመክፈል አቻ ሆኖብኝ ተቸግሬአለሁ፡፡ክብሬን ከግብሬ ጋር ስለምከፍል አፍራለሁ፡፡
በስታዲየም በኩል አድርጌ ቀና ብዬ የባቡሩን መንገድ ሳይ እኮራለሁ… ጎንበስ ብዬ ደግሞ መንገድ ላይ እንደ ተረፈ ምርት፡ ውሃው እንደተጠጣ የፕላስቲክ ኮዳ ወገኔ ወድቆ ሳይ አፍራለሁ፡፡ያ ኮርቼበት ያላበቃሁት ባቡር በመብራት እጦት ባለበት መቆሙን ሰሰማ እንደገና አፍራለሁ፡፡
.
የመደበኛ ስራዬ ገቢ መሰረታዊ ፍላጎቴን ለሟሟላት ስለማይበቃኝ (በርግጥ ግብር ባይቀነስብኝ ኖሮ ይበቃኝ ነበር)ትርፍ ሰኣት ስራ ለመስራት እገደዳለሁ፡፡ ቤቴ እንደደረስኩ ፋይሌን አገላብጬ ኮምፒውተሬን ስዘረጋ መብራት አለመኖሩን ሳይ ደግሞ አፍራለሁ… “እኛስ እንደዚህ ነን ለመሆኑ የተቀረው አለም እንዴት ዋለ?” ብዬ ዜና ለመስማት በሞባይሌ ራዲዮ ከፈትኩ፡፡ ማንትስ ቁ.3 ኃይል ማመንጫ መመረቁን ስሰማ ደግሞ በግብር ከፋይነቴ እኮራለሁ… መብራት ባለመኖሩ እራትም፤ የነገ ቁርስ እና ምሳም ሳልሰራ እየኮራሁ እተኛለሁ፡፡ኩራት እራት አይሆንም ብላችሁ እንዳትሞኙ… ጠዋት ተነስቼ ፊቴን ለመታጠብ የዘወርኩት ቧንቧ ውርጩን ከማለዳው ተውሶ ቀዝቅዟል ፤ አፉ አካባቢ ጠብታ ውሃ ናፍቆት እንደ መዛግ ጀምሮታል፤ ከዘንጉ እስከ ቆጣሪው ሸረሪት አድርቷል … ይህን ያዩ ወፎች የልብ ልብ ተሰምቷቸው ጎጇቸውን እንዳይቀልሱ የሸረሪቱን ድር እንደ ሪቫን በጣጥሼ ከቤቴ ወጣሁ፡፡
(እና ለዚህ በጀብዱ የተሞላ የአኗኗር ዘዬ ሜዳሊያ አያስፈልገውም?)
እንደ አለቤ ሾው አይኔን በጣቴ አባብሼ … በየመንገዱ ልብሴን እየለበስኩ… ጫማዬን እያሰርኩ… ተንደርድሬ ታክሲ ሰልፍ መጨረሻኛ ራሴን ሳገኘው ደግሞ አፍራለሁ፡፡ ጀርባዬን ለፀሐይ ሰጥቼ ስገተር …እንደማረፍድ አውቄ ለአለቃዬ ለመደወል ስሞክር የስልኬ ገንዘብ ማለቁን ስረዳ… እንደገና አፍራለሁ ትናንት ነበር 50 ብር የሞላሁት…የደወልኩባቸውን ቦታዎች Log history ውስጥ ገብቼ ሳጠና ፤ text messag እንኳ ስልክ ለአንድ መልእክት የተመደበችውን የ35 ሳንቲም ገደብ ላለማለፍ ተጠንቅቄ… ሁለት እና ከዛ በላይ የሆነ ትርጉም ያላት አንድ ቃል ዲክሽነሬ አገላብጬ ፈልጌ ነው… ታዲያ በዚህ ሁሉ አልፌ ለ50 ብር ያገኘሁነትን ተመጣጣኝ አገልግሎት ማስታወስ ያቅተኛል፡፡ እንግዲህ እሱም ግብር አለው አሉ…አሁንስ መፋቁም ሰለቸኝ፡፡ ደሞ ምንድነው የሚለድፉበት?
.
እዛው ከፀሐይ እየታገልኩ በቆምኩበት “የስኬታማ ሰዎች ምስጢር” የሚል መፅሐፍ ለማንበብ ስሞክር… “ጊዜን በአግባቡ መጠቀም” ከሚል ንኡስ-ርዕስ ስር እንዲህ የምትል አረፍተ ነገር ለቀምኩ “…ስኬታማ ሰዎች የመጠበቅ ጊዜአቸውን ይጠቀማሉ… ረጃጅም ሰልፎች እና ወረፋ ያለበት ቦታ ሲቆሙ ወይም ሲቀመጡ ምርታማ የሆነ ጠቃሚ ስራ ያከናውናሉ እንጂ ጊዜውን በከንቱ አያሳልፉትም …” ድንቅ ምክር…እዚህም እዚያም ሰልፍ በበዛበት ከተማ ከዚህ የተሻለ ምክር ከየት ሊመጣ?… ግን የታክሲ ስልፍ ላይ ቆሞ አንድ ሰው ምን ሊሰራ ይችላል?… አወጣሁ አወረድኩ… በመጨረሻም ደረስኩበት!!!
ከነገ ጀምሮ ታክሲ ሰልፍ ላይ ጥጥ መፍተል እጀምራለሁ፡፡ በልቃቂት ተቆጥሮ ይሸጥ የለም?… ገንዘብ የሚያስገኝ ስራ … ሹራብ ስራ …ወይም ሙዳይ ነገር መስፋት ያው ከታክሲ የሚተራርፈውን ሳንቲም ለማጠራቀሚያ (ከተረፈ ነው ለዛውም)…ድሮ የሆነች ሳጥን ቢጤ ነበረችን : ኪኒን በምታክል ጓጉንቸር የምትቆለፍ…ሳንቲም ማጠራቀሚያ… ሰው ቢሰጠን…ወድቆ ስናገኝ… (ልጆች…በድሮ ዘመን መሬት ላይ ሳንቲም ወድቆ ይገኝ ነበር …) ዛሬ ሳንቲምም መሬት ላይ የሚጥል ጠፋ!!! ሰው ሁሉ 5 ሳንቲም የማታሾልክ ቀዳዳ ኪሱን በ25 ሳንቲም መርፌ ሰፋ!!! የዛሬ ልጆችም ሳንቲም አያጠራቅሙም ለነገሩ ብሩን ማን ከልክሏቸው?
ይህንን እና ያንን ሳስብ ሰልፍ ደርሶኝ የገባሁበት ታክሲ ረዳት ጠጋ በሉ በሚል ምክንያት ከፍ ዝቅ አድርጎ ሲያመነጫጭቀን ደግሞ አፍራለሁ፡፡
እንዲያውም ለስራ ፈጣሪዎች የሚሆን አንድ ሃሳብ አለኝ፡፡ የታክሲ ረዳቶች ማሰልጠኛ ቢኖርስ? ስለ ደንበኛ እና ገንዘብ አያያዝ፤ስለ አጠራር አይነቶች፤የሰፈር ስሞችን በቀላሉ የማወቅ ዘዴ፤ስለ መልስ አሰጣጣጥ እና ሂሳብ ስሌት፤ንፅህና አጠባበቅ ፤ የረዳቶች የልምድ ልውውጥ…እንደ ሞያ የተወሰነ ስልጠና ቢኖረው ደግ ይመስለኛል፡፡ መቼም አንድ ሰው ስራዬ ብሎ ከቤት ከወጣ እና ገቢ አግኝቶ ከተዳደረበት ወንጀል እስካልሆነ ድረስ ሙያው ነውና የሚያዳብርበት መንገድ ቢያገኝ አይጠላም፡፡ጥያቄ አለኝ… የእነሱ ገቢ ግን ግብር ይቀነስበታል እንዴ? አይመስለኝም! ለዛ ይሆን እንዲህ በማን አለብኝነት እና በኩራት የሚናገሩት? ሁሉ ነገር የተገላቢጦሽ ሆኖብናል መቼም… ግብር ከፋዩ እየኮራ ያፍራል፡፡ ግብር ከፍሎ የማያውቀው… ሀፍረት የሚባል ነገር የለው.. ኩራቱና ትእቢቱ ሀገር ያስለቅቃል…
.
ያው መብራት ባለመኖሩ ምክንያት እራቴን ኩራት በልቼ ፡ኩራት ጠጠጥቼ፡ ኩራት አግስቼ ማደሬ ይታወቃል፡፡ ለክፋቱ ኩራት እራት እንጂ ምሳ አይሆንም… ስለዚህ ምሳ ሰኣት ላይ አንዱ ምግብ ቤት ለመግባት ተገደድኩ ፡፡ ሂሳቡም ይቀንሳል በሚል ግምት ሽሮ አዘዝኩ (ለወትሮም ምክርና ምግብ ከቤት !!!)እዚህ ግባ የማይባል መናኛ ሽሮ 50 ብር የሚሸጥበት ሰፈር እንደምውል እስከዛሬ አላውቅም ነበር፡፡ እሱ አልበቃ ብሎ ከምሳው ቢል ጋር ያልበላሁበትን 15 በመቶ ጭማሪ እከፍላለሁ ፡፡ በዛ ሳቢያ ማኪያቶ መጠጣቴን እተውና “የስኬታማ ሰዎች ምስጢር”ን ካቆምኩበት እቀጥላለሁ፡፡ ሰዓት ሳይመርጡ በየ ካፌው እግራቸውን አጣምረው … ሞባይላቸውን በናፕኪን እየወለወሉ…ቻፕስቲካቸውን እያለቡ እየተቀቡ… ማኪያቶ የሚጠጡ ወንዶች እና ሴቶች …ይህንን ነገር ግን ልብ ብለውታል?
በህትመት ጥራቷ ከፍተኛነት እጠፉኝ፡ ጠርዙኝ የማትለዋን ሚጢጢ የግብር ከፋይ መታወቂያ ጥሩ እልባት ማደረጊያ ሆና አግኝቻታለሁና ያቆምኩበትን አልሳትኩም….ሲያይዋት ያን ሁሉ ዜሮ ፤ ያን ሁሉ የቁጥር ድርድር የተሸከመች አትመስልም… የኔን ፎቶ አሳንሳ ቁጥር አብዝታለች፡፡
ከመፅሀፉ ላይ “አላስፈላጊ ወጪዎችን ያስወግዳሉ” የምትለዋን አረፍተ-ነገር ሳይ ማኪያቶ ባለመጠጣት ውሳኔዬ እደሰታለሁ፡፡
በዚሁ ከቀጠልኩ ስኬታማ የመሆኛዬ ጊዜ ቅርብ መሆኑን እየገመትኩ እፅናናለሁ፡፡ከደረጃ አልባ ግብር ከፋይነት ወደ ‘ባለደረጃ’ግብር ከፋይነት መሸጋገሬም አይቀርም…
.
በከተማ መሃል እና ዳርቻ ላይ የሚገነቡትን 40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የገጠጠ ብሎኬት ሳይ በነገ ቤቶቼ እኮራለሁ… አንዳንዴ አንዱ ሳይት ጎራ ብዬ… “እናንተ ልጆች…በተወደደ ሲሚንቶ… በተወደደ ብረት ምንድነው ይሄ ሁሉ ብክነት… በል አንሳ እና በስርአት አስቀምጥ…” ማለት ሁሉ ያምረኛል (እዚህ ጋ በግብር ከፋይነቴ ብቻ ሳይሆን በቆጣቢነቴም እኮራለሁ!)ለዓመታት ጠብቄ ‘ዕጣው’ ሲወጣ ስሜ አለመኖሩን ሳውቅ ደግሞ አፍራለሁ፡፡አዝናለሁም፡፡
.
የስራዬ ባህሪ ሆኖ ድርጅቱ ከእኔ እና ከመሰሎቼ የቀነሰውን የደመወዝ ግብር ለመክፈል አንዱ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት በየወሩ እሄድና እሰለፋለሁ ያኔ አፍራለሁ፡፡ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክፍያዎችን ይዘን በ “ሲስተም የለም” ፡ በ “ስብሰባ ገቡ” … ስንጉላላ የበለጠ አፍራለሁ::
ለስራ ቅጥር ስወዳደር… ከዛም ስደራደር የደመወዜን መጠን በፍጥነት ግብሩን ቀንሼ ሳሰላ አፍራለሁ፡፡ ከስራ ልምድ እና ከደመወዝ መጠን ቀጥሎ “በየወሩ ከደመወዟ የስራ ግብር እየተቀነሰ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ገቢ የተደረገ መሆኑን እናረጋግጣለን::” የሚለው አረፍተ ነገር በደማቅ (CAPITAL LETTER, Bold & Underline) እንዲፃፍልኝ በኩራት እጠይቃለሁ:: ይህ የተቀነሰው ብር ግን የት ሄዶ የትኛውን የሀገር ቀዳዳ እንደደፈነ ለማወቅ ብጥርም ተሳክቶልኝ አያውቅም፡፡ ምን ምን ላይ እንደሚውል ብቻ የሚያስረዳኝ ባገኘሁ….
ስለ ምጣኔ ሃብት ያለኝ እውቀት ዜሮ መሆኑን ቢያሳብቅብኝም አንዳንድ ጊዜ እንዲህም አስባለሁ… “ከደመወዜ ላይ የሚቆረጠውን ታክስ ከቤት እስከ መስሪያቤት ለሚያመላልሰኝ ታክሲ ኮንትራት ብከፍለውስ?” እላለሁ፡፡ “በየወሩ ለመንግስት የምከፍለው ግብር ቦርሳዬ ውስጥ ቢገኝ… ለህክምና አገልግሎታቸው ከሚያማርር የመንግስት ጤና ጣቢያ እና ሆስፒታሎች መሄዴን ትቼ አንዱ የግል ከፍተኛ ክሊኒክ በከፍተኛ እንክብካቤ ብታከምበትስ?” እላለሁ፡፡ መቼም ከመተማ ሱዳን ገዳሪፍ አስፋልት መንገድ፤ ወይም የህዳሴው ግድብ ምናምን በመቶ በእኔ የግብር ክፍያ እንዳልተሰራ ይገባኛል … በየገጠሩ ንፁሕ የመጠጥ ውሃ ማስገቢያ ጤና ጣቢያ ማሰሪያ ውሎ ይሆን? አሁንም ግን ማን ስንት ሊትር ውሃ አገኘ? ማንስ ከበሽታ ዳነ? የሚለውን እንደ ግብር ከፋይ ‘ኩሩ’ ዜጋ ማወቅ እሻለሁ፡፡
እስከዛው ግን በኩራት እና ሀፍረት መሃል እየዋለልኩ አለሁ፡፡
(ከጥቂት ማስተካከያ ጋር-የተደገመ)

Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?
Teym Tsigereda Gonfa  ከፌስ ቡክ የተወሰደ