ዛጎል ዜና – የኦሮሚያ ጉዳይ የሁሉንም ቀልብ የሚስብ ነው። ከዓመት በፊት በትንሿ ከተማ ጊንጪ የተጀመረ ተቃውሞ እንደ ሰደድ እሳት ዙሪያ ገባዋን አግሟት ነበር። በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መነሻነት የተነሳው ተቃውሞ ሕዝባዊ ማዕበል እስከመሆን ደርሶ የቁጥር ጸብ ቢኖርም ሲጠሩት የሚከበድ ቁጥር ዜጎች ህይወት አልፏል። በሺህ የሚቆጠሩ ታስረዋል። አሁንም እስር ላይ ያሉት ቁጥራቸው በውል ባይታወቅም ቀላል አይደለም።

በተመሳሳይ ኢህአዴግ አንድ ነገር ጀምሮ ህዝብ ሲነሳና ሲቃወም ለማስታገስ የሚፈልገውን መንገድ ሄዶ ሲያበቃ ” ያሰብኩትን ትቼዋለሁ” አለያም ” ከፍተኛ በጀት በድንገት በመመደብ ቀውሱን የሚገታ የሚመስል፣ ነገር ግን ነገ ሌላ ጥያቄ የሚይሳነሳ ውሳኔ ያሳልፋል” በሚል ትችት ታጅቦ ኦሮሚያን ያባረደ ቢመስልም ” ተዳፈነ እንጂ አለበረደም” በሚል ሃሳብ የሚሰጡ አሉ። ከሃሳብም በላይ አልፈው በመሄድ የመንግስትን የመፍትሄ እቅዶች እየበተኑ የሚተቹ በርካታ ናቸው።

በቅርቡ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም የሚወስን ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ መላኩ ይፋ ሲሆን ” ሞኝህን ፈልግ” ሲሉ ያጣጣሉ ጥቂት አይደሉም። አዲስ አበባ ያሉ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ” መንግስት ህገ መንግስቱን ጨፈለቀው” ሲሉ የሚምልበትን ” የማዕዘን ደንጋይ” የወረወረ ያህል ሙያዊ ትንተና በመስጠት ” ህዝብ ሊመክርበት ይገባል ሲሉ አስተያየት የሰጡ አሉ። በሸገር ካፌ ፐሮግራም ቡናው እየሸተተን አቶ አብዱ አሊ ያጫወቱን ጨዋታም ክግርምትና ከመደመም ጋር ተላውሶ የመንግስትን ሬት ሬት የሚል አካሄድ የነቀሰ ነበር። ማጋነን ካልሆነ ማብራሪያውን ሲሰሙ እንዲህ ያሉ ሰዎች ለምን ምክር እንዲሰጡ በር አይከፈትላቸውም? የሚሉም አይታጡም። ኢህአዴግ በብቃት ማነስና በግምገማ ባለስልጣናቱን ሲያሳንስ ” አማካሪ” እያለ ” የማያማክሩትን” ከሚሰብስባቸው ለማለት ነው።

Related stories   PM Abiy, U.S Senator Inhofe Hold Encouraging Conversation about Tigray

ኦሮሚያ በየትኛውም አገላለጽ ሃዘን ወድቆባት ነበር። ሃዘኑ ቢበርድም ቁስሉ ግን እንዳልጠገገ ብዙ አመላካች ጉዳዮች አሉ። ሃዘን በጉያቸው ላቀፉት የክልሉ ነዋሪዎች ማንኛውም ጉዳይ የታቀፉትን ሃዘን ቀስቃሽ ነው። ለዚህም ይመስላል ሰሞኑን የቀን ገቢ ግምትን ተንተርሶ ከወደ ምዕራብ ሸዋ አምቦ፣ ጉደር፣ ጊንጪ እና ካባቢው ያሉ ከተሞች የአመጽ ድምጽ የተሰማው። ላለፉት ሁለት ቀናት በተለይ አምቦና ወሊሶ በዚሁ አመጽ ሳቢያ ጸጥ እረጭ ማለታቸው ተሰምቷል።

የከተሞቹ ነዋሪዎች አስተያየት ሲሰጡ እንደሚደመጠው በከተሞቹ የንግድ ቤቶች ተከርችመዋል። የትራንስፖርት አቅርቦት ተስተጓጉሏል። የንግድ ሂደቱ ተፋልሷል። ቆየት ብለውም ጊንቢና ደንቢ ዶሎ ይህንኑ አመጽ መቀላቀላቸውን የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊም ሊሸሽጉት አልቻሉም። ነገ ይህ ተቃውሞ ላለመቀጠሉ ማረጋገጫ የለም።

Related stories   Speaking Truth to Power, Samantha: Stop Defending Ethiopia’s “Proud Boys”!

አሳሳቢ የሚሆነው የአዲስ አበባ አካባቢ ያሉ ከተሞች ይህንን ተቃውሞ ከተቀላቀሉ አዲስ አበባ ተጠቂ የመሆኗ ጉዳይ ነው። ዘይት በወጉ ማከፋፈል የማይችለው መዋቅር የኦሮሚያ አርሶ አደርና ነጋዴዎች ካመረሩ ችግሩን እንዴት ይፈታል? ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባም የዚሁ የቀን ገቢ ግምት ለቅሶ ስለሚሰማ ነጋዴው ተባባሪ ሊሆን የሚችልበት አግባብ መኖሩ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ችግሩ የከተማዋን ድሆች ከደቆሳቸው ድህነት ጋር ተዳምሮ ችግሩን እንዳያባብሰው ነው።

የቀን ገቢ ግምቱ እንደገደላቸው ከሚናገሩ ወገኖች ድምጽ መካከል አንዳንዱ አስዛኝም ጭምር ነው። አንድ ጸጉር ቆራጭን 12 ሽህ ብር የቀነ ገቢ እንዳለው የሚገምት ባለሙያ ” ህዝብን ለአመጽ የሚያነሳሳ ” ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል?ተመሳሳይ ” አመጽ አነሳሽ” ሊባሉ የሚችሉ ግምቶች አሉ። በዚህ ሁኔታ የተበደሉ ቢያምጽ፣ ለማመጽ ቢዶልቱ፣ አመጽ ላይ ቢሆኑ… የሚገርም እንዳልሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ። እንደውም ራሱ መንግስት ” በአመጽ አነሳሽነትና አስተባባሪነት ይከሰስ” የሚሉም እየተደመጡ ነው።

Related stories   Ethiopia: Lies, Damn Lies, Axum and the West – by Jeff Pearce

ግብር መክፈል ግዴታ ነው። ግብር ለማስከፈል ግብር አስከፋዩና ሰብሳቢው አካል የሚገባውን ተግባር ለመፈጸም መነሳቱም አግባብ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ግብር መክፈል ግዴታ በመህኑ ሰዎች መብታቸው ይገፈፍ፣ ቆዳቸው ይላጥ፣ ህልውናቸው ይናድ ሊባል አይችልም። መንግስት የራሱ ከፈተኛ ሃላፊዎች የሚዋኙበት የኮነትሮባንድ ንግድ አገሪቱን እንደወረራት በራሱ ሚኒስትር ተነግሮታል። በከፍተኛ ደረጃ የሚነገዱ፣ የሚያስነገዱ፣ እንዲሁም የፓርቲ ንብረት ሆነው የመንግስትንና የህዝብን ማጅራት የሚመቱ ተቋምት ላይ ተለሳልሶ አንድ ሱቅ በደረቴ ላይ ጉለበቱን ማሳየቱ በማናቸውም መስፈርት ፍትሃዊ ሊሆን እንደማይችል መከራከሪያ የሚያቀርቡ፣ ግብር ሰብሳቢው አካል የቀን ጉሮሯቸውን ለመዝጋት በሚተጉት ላይ የሚያሳድረውን ቻና እንዲያቆም ይምክራሉ።

በይፋ ስም ዝርዝራቸው ባይጠቀስም የትጀመረውን ተቃውሞ የሚቀላቀሉ ከተሞች ቁጥር ጨምሯል። ያልተቀላቀሉትም እያጉረመረሙ መህናቸው ተሰምቷል። ከዚያም ከዚህም የሚባለው ” ሰከን በል” ነው። የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ጽፈት ቤት ውይይት እንደሚደረግና መሻሻል ያለበት ነገር እንደሚሻሻል፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ ስራው የሚሰራው በሰዎች ስለ ሆነ ስህተት ሊሰራ እንደሚችልም ተናገረዋል።

ምስል – ሱሉልታ የወሃ ችግር –

ቪኦኤ ይህንን ዘግቧል

 

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *