አበራ ገብሩ —Image may contain: 1 person, smiling

አበራ ገብሩ እባላለሁ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነኝ፡፡ ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ግንቦት 18ቀን 2009 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀው በፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ላይ ፓርቲዬን ወክዬ ተገኝቼ ስለነበርና በዕለቱ የፓርቲዬን አቋምና የራሴን ሐሳብና በውይይቱ የታዘብኩትን ዕይታ ለመግለጽ ፍላጎት የነበረኝ ቢሆንም የመናገር ዕድል ባለማግኘቴ በዚያ መግለጽ የፈለኩትን ሀሳብ በጽሁፍ ማቅረብ በመፈለጌ ነው፡፡በመሆኑም በዕለቱ እድሉን ባገኝ ኖሮ መግለጽ የምፈልገውን ሁሉ ለመግለጽና በተጨማሪ ሌሎች ዕድሉን አግኝተው ከተናገሩት በመነሳት የምገልጸው ነገር ይኖረኛል፡፡
በመጀመሪያ በዕለቱ ዝግጅቱን ያዘጋጁትን ሁለት የሚዲያ ተቋማትና ጽሁፉን ያቀረቡትን ባለሙያዎች ወይም ምሁራን በሚመለከት ማለት የምፈልገውን ላስቀድም ይኸውም የሚዲያ ተቋማቱ እንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶች በቀጣይነትም መዘጋጀት አለባቸው፡፡ መቀጠል አለበት፡፡ አንድ ጊዜ ወይም ለጥቂት ጊዜያቶች ብቻ ታይቶ የሚቆም ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ምሁራኑም በሀገራችሁ የፖለቲካ መድረክ ላይ ባይተዋር መሆን የለባችሁም፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍም ሆነ በማዘጋጀት ጽሁፎችን በየጊዜው በማቅረብና እውነትን በመጠቆም የዜግነት ግዴታችሁን ተወጡ ወይም ልትወጡ ይገባል ብዬ ስለማምን ሁለቱንም አካላት ማለትም የሚዲያ ተቋማቱንም ሆነ ምሁራኑን ይህ ጉዳይ ቀጣይ መሆን ስላለበት በርቱ ቀጥሉ ማለትን ነው የምመርጠው፡፡
በመቀጠል ወደዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት አንድ ትዝብቴን ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ይኸውም አንድ ተሳታፊ ከኦብኮ ይመስለኛል የተጠቀሙበትን ቃላት በሚመለከት ጥቂት ለማለት ነው፡፡ በመሠረቱ እንደዚህ ዓይነት የውይይት መደረረክ ሲዘጋጅ ለውይይት ሐሳብ ለመለዋወጥ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ማንኛውም ተሳታፊ የመሰለውን ሐሳብ ይዞ መቅረብ ይችላል፡፡ ሀሳቡ አሳማኝ መሆኑና አለመሆኑ ተቀባይነት ማግኘቱና አለማግኘቱ በውይይቱ ላይ የሚታይ ነው፡፡ በፌዴሬሽን መዋቀሩን አልፈልግም ማለትም እኮ መብት ነው፡፡ እንዳልኩት ሐሳቡ ተቀባይነት ማግኘቱና አለማግኘቱ ሆኖ ወሳኑ ነገር የትኛውንም ሐሳብ መሰንዘር ይችላል፡፡ ምናልባት ይህን ያልተረዳ ሊሆን ይችላል አንድ ተሳታፊ ተወደደም ተጠላ ፌዴሬሽን የግድ መሆኑን ነግሮናል ተወደደም ተጠላ የሚለው አባባል ለውይይት መልካም አነጋገር ስላልመሰለኝ ለውይይት የማይሆን አባባል ስለሆነ እንዲታረም ማሳሳብ ፈልጎ ነው፡፡
ይህን ካልኩ በኋላ ወደ ዋናው ጉዳይ ስገባ በመጀመሪያ የፓርቲያችንን አቋም መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓት ሥልጣኑ ሁሉ በማዕከላዊ መንግሥቱ ሥር እንዳይሆን ሥልጣንን መከፋፈል ስለሆነ ሰማያዊ ፓርቲ የሚደግፈው ጉዳይ ከመሆኑም በላይ በፕሮግራሙ ላይ የመንግስት አወቃቀር በፌዴራላዊ ሥርኣት እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ ከዚህም በላይ የፌዴራል መንግስት አወቃቀር መልክዐምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ ለልማትና አስተዳደር አመቺነትን፣ ቋንቋንና ባህልን፣ታሪክን፣የሕዝብ ፍላጎትን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስሮችንና የመሳሰሉትን ሁሉ ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት ይገልጻል፡፡ እንግዲህ ከኢህአዴግ ጋር ልዩነታችን ኢህአዴግ ሀገሪቱን በፌዴራል ስርዓት ለመከፋፈል የተጠቀመው ቋንቋን ወይም ብሔርን ብቻ መሠረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የኢህአዴግ ሰዎች በእውነት ላይ ተመርኩዘው መከራከር ሲያቅታቸው እንደሚሉት እኛ ፌዴራል ሥርዓትን ሳይሆን የምንቃወመው ኢህአዴግ የተከተለውን መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ፓርቲያችን የሚለው የፌዴራል ሥርዓቱ ከላይ ተገለጹትን እጅግ በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች ሁሉ ከግምት ባስገባ መንገድ መዋቀር አለበት ነው፡፡
በእለቱ ጥናቱን ያቀረቡት ምሁራኖች ብዙ ጉዳዮችን ያነሱ ቢሆንም ጽሁፋቸውን ባቀረቡበት ርእስ ማለትም የፌዴራል ሥርዓታችን ብዝሃነትና የጋራ ተጠቃሚነት የማስተናገድ አቅም በሚለው ርእስ ሥር ብዙ ሊነሱ የሚገባቸው አንኳር ነጥቦች አልተነሱም ወይም አልካተቱም፡፡ በእኔ እምነት ከዚህ በታች የተጠቀሱት ነጥቦች ሊነሱ ይገባቸው የነበሩ ግን ያልተነሱ ወይም ያልተካተቱ ነጥቦች ናቸው፡፡ ይኸውም፤
ምን ዓይነት የፌዴራል ሥርዓት ነው እየተጠቀምን ያለው? ምን አስገኘልን ምንስ አሳጣን? የሚሉት መነሳት ያለባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱ ካመጣው ውጤት አንጻር ተመዝኖ (ያስገኘውና ያመጣው ችግር ተነጻጽሮ) መቀጠል አለበት ወይስ የለበትም የሚል መደምደሚያ ላይ መደረስ ነበረበት፡፡
ሌሎች አማረጭ የፌዴራል ሥርዓት አሠራሮችና የእያንዳንዳቸው ጥቅምና ጉዳታቸው መመዘን ነበረበት፡፡
በአሁኑ ሰኣት በሀገራችን ያፈጠጡ ያገጠጡ በምንከተለው የፌዴራል ሥርኣት የተነሳ የተፈጠሩ ችግሮች አሉ እነዚህ ችግሮች መነሳት ነበረባቸው፣ ችግሮች የመፍትሔ ሐሳቦችና አማራጮች መቅረብ ነበረባቸው፡፡
ለምሳሌ በጥናቱ ያልተካተቱ ያፈጠጡና በገሃድ ከሚታዩት ችግሮች ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ማንሳት ይገባ ነበር፡፡

– በክልሎች ድንበር ላይ በየጊዜው የሚፈጠረውና እየተፈጠረ ያለው ግጭት
– ዜጎች ያለፍላጎታቸው የዚህኛው ወይም የዚያኛው ብሔር ናችሁ መባላቸው
– ጥቂት ቁጥር ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ተብለው በራሳቸው እንዲተዳደሩ ሲፈቀድላቸው በቁጥር ከእነዚህ በብዙ የሚበልጡ ሌሎች ይህን እድል መነፈጋቸው (አሠራሩ ለሁሉም ተመሳሳይ መሆን ሲገባው አለመሆኑ)፡፡
– ሀገራዊ ስሜት መሸርሸሩ
– ዜጎች በሀገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ቦታ እንደዜጋ መሥራት እንዳችይሉ ወይም ከቦታ ቦታ በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጉ
– በአንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች በጥረታቸው ያፈሩትን ንብረት ተቀምተውና ተነጥቀው ውጡ መባላቸው
– ዜጎች መንግሥታዊ አገልግሎት ለማግኘት ብዙ ርቀት እንዲጓዙ የሚያስገድድ ሁኔታ መፈጠሩ፡፡ ለምሳሌ የምንጃርና ሸንኮራ ነዋሪዎች አዳማና ናዝሬትን የመሳሰሉ ከተሞችንና አስተዳደሮችን እያለፉ ባህርዳር ድረስ እንዲጓዙ መገደዳቸው እንዲሁም የቤንች ማጅ ዞን ነዋሪዎች ጅማ በቅርባቸው እያለ አዋሳ እንዲጓዙ መገደዳቸው፡፡
– በአንድ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ተማሪዎች የአንድ ሀገር ልጅ እስከማይመስሉ ድረስ ተነጋግረው መግባባት አለመቻላቸው ማለትም በቋንቋ ችግር አለመግባባታቸው፡፡
– በቋንቋ የተነሣ የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ችግር መፈጠሩና ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች በቋንቋ ችግር የተነሳ የሥራ እድል ማጣታቸውና ሎሌች ብዙ ብዙ ችግሮችን መግለጽ ወይም ማንሳት ይቻላል፡፡
በዚህ የተነሳ የፌዴራል ሥርአታችን የጋራ ተጠቃሚነትን የማስተናገድ አቅም የለውም፤ ብዝሃነትንም ያስተናግዳል ብለን አናምንም፡፡ በመሆኑም ይህ ፌዴራል ሥርዓት ፈተናውን የወደቀ ሥርዓት ነው፡፡
ከዚህ በመቀጠል የኢህአዲግ አባላት ከቤቱ ለተነሱ ጉዳዮች የሰጡትን አስገራሚ መልስ በሚመለከት ጥቂት ልበል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ የኢህአዴግ ቱባ ባለሥልጣናት ተገኝተው ሐሳባቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ የተናገሯቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ጥቂቶቹን ብቻ በሚመለከት ጥቂት ልበል፡፡
የመጀመሪያው ተናጋሪ አቶ አባይ ፀሐይ ሲሆኑ የፌዴራል ሥርዓቱን በብሔር መከፋፈሉን ትተን በመልክዐ ምድር ብንከፋፍለው ወደቀድሞው ሥርአት መመለሳችን እንደሆነ ነግረውናል፡፡ አቶ አባይ ይህን ሲሉ ይህ ሥርአት ከቀድሞው የሚለየው ሀገሪቱን ቋንቋን ወይም ብሔርን መሠረት አድርጎ መከፋፈሉ ብቻ ነው ማለታቸው እንደሆነ አልተረዱ ይሆን፡፡ ነገር ግን ባለፈው ሥርአት ሀገሪቱ በክፍለሀገሮች መከፋፈሏ ብቻ ሳይሆን ዋናውና ትልቁ ልዩነት አሀዳዊ ሥርአት መሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት የክፍለ ሀገር አስተዳዳሪዎች በማእከላዊ መንግስት የሚሾሙ የማእከላዊ መንግስቱን ፍላጎትና ትእዛዝ የሚያስፈጽሙ እንጂ ለይስሙላም ቢሆን በህዝብ የሚመረጡ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ ሥልጣኑ ሙሉ በሙሉ በማእከላዊ መንግስት የተያዘ በመሆኑ ፌዴራላዊ ሥርአት አልነበረም፡፡ ስለዚህ ይህ የአቶ አባይ አባባል ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡
ሌላው ስለአውራ ፓርቲ ሲናገሩ የእነሱ ምኞት ጠንካራ ተሳታፊና ተፎካካሪ ፓርቲ እንዲኖር እንደሆነ የገለጹት ነው፡፡ ይህማ ቀላል አይደለም እንዴ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አለመኮርኮምና አለማሳደድ ብቻ ይበቃል እኮ ሌላ ከእናንተ የሚጠበቅ ነገር የለም፡፡
በመቀጠል የተናገሩት አቶ ስብሐት ነጋ ሲሆኑ አቶ ስብሐት ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር ለኢህአፓ፣ ለመኢሶንና ለኢሠፓ ሀገሪቱን ከመበታተን እናድናት ብለው ጥሪ አድርገውላቸው እንደነበርና ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ ኢህአዴግ ሀገሪቱን የተቆጣጠረበት ጊዜ እኮ ቅርብ ነው ሩቅ አይደለም፡፡ስለዚህ በጊዜው የነበረውን እውነት ብዙ ሰው የሚያውቀው ይመስለኛል፡፡ ኢሰፓ መጀመሪውኑ ፕሮግራም ኖሮት አባላት በፕሮግራሙና በአላማው ተማርከውና አምነውበት የገቡበት ድርጅት ባለመሆኑ ሥልጣን ሲያጡ ወይም ችግር ሲመጣ ችግሩን ተቋቁመው አብረውት ሊቆዩና መስዋእትነት ሊከፍሉ የሚችሉ አባላት ያሉት አይመስለኝምና በእንደዚህ አይነት ጊዜ ቀጣይ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከዚያ በኋላ በፍጹም ስለፓርቲው የሚሰማ ነገር የሌለው፡፡ ኢህአፓና መኢሶንን በሚመለከት ግን ትጥቅ ያነሱ ድርጅቶች ናቸው ተብለው እንደተገፉና እንኳንስ ሊጋበዙ እንዳይመጡ በር እንደተዘጋባቸው እየታወቀ በፍጹም ማቅረብ እንዳልተፈለገ ብዙዎች የሚያውቁት ጉዳይ ሆኖ ሳለ እንኳን አብሮ ለመስራት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ እንኳን ተከልክለው እያለና በብዙዎች እየታወቀ ለምን እንዲህ ማለት እንደተፈለገ ግልጽ አይደለም፡፡
ቀጣዩ ተናጋሪ አቶ ተፈራ ደርበው ተባሉ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነገረ አንድ ነገር የሰጡትን መልስ ልግለጽ ይኸውም ከተሳታፊዎች ፓርቲዎች ቢዝነስ ውስጥ መግባት የለባቸውም በሚል የቀረበውን ሐሳብ በሚመለከት ሲመልሱ፤ ቢዝነስ ውስጥ የገባ ፓርቲ የለም ቢኖርም በህግ ይጠየቃል አሉ፡፡ ቢሆንማ ጥሩ ነበር በእስር ቤትና በውጭ ያሉት ቦታ ሊለዋወጡ ይችሉ ነበር፡፡

ሌላኛው ተናጋሪ ስማቸውን የማላስታውሰው ሴት ተናጋሪ የተናገሩት ነው፡፡ እኚህኛውም ብዙ ያሉ ቢሆንም ከተነገሯቸው አንዷን ብቻ ላንሳ ዜጎች ከየክልሉ ውጡ እየተባሉ ይባረራሉ ተብሎ ለተነሳው ነጥብ የተናገሩትን አስገራሚ አባባል በሚመለከት ነው፡፡ ይኸውም ህዝባችን እንግዳ ተቀባይ መሆኑን ይገልጹና ነገር ግን ይህን እንዲያደርግ የሚገፋፋው አካል እንዳለ በል በል የሚለውና ለጥፋት የሚያበረታታው አካል እንዳለ የተናገሩት ነው፡፡ ውድ የኢህአዴግ ባለሥልጣን በመጀመሪያ እነዚህ ከመኖሪያ ቀያቸው የተባረሩ ወገኖች እንግዳ አይደሉም፡፡ ሀገራቸው ውስጥ ነው የነበሩት ይህ የሥርአቱ ችግር ነው እነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ እዚያው ተወልደው አድገው እነሱም በተራቸው ልጅ ወልደው አሳድገው ድረው ሰርተው ሀብት አፍርተው ለዘመናት የኖሩበት ነው እንግዶች አይደሉም እናንተ ናችሁ እንግዶች ያደረጋችኋቸው እንጂ ከሀገሬው ጋርማ ለዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡ አረ ለመሆኑ ይህን ያህል ጊዜ አብረው ሲኖሩ አብረው ሲሰሩና በጋብቻ ሲተሳሰሩ እንዲያባርሯቸው ያልገፋፋ አካል አሁን በኢህአዴግ ጊዜ ከየት መጥቶ ነው የሚገፋፋው?ይህ አካልስ ማነው?የፈጠረውስ ማነው?ተጠያቂውስ ማነው? ለምንስ ነበር የማይጠየቀው? ተጊጂዎቹ ለምን ጠያቂ ወገን አጡ? የሚሉት ጥቄዎች መልስ ይሻሉ፡፡
የኢህአዴግ ባለሥልጣናት አሁንም ለለውጥ ዝግጁ እንዳልሆኑ ነው በውይይቱ ላይ መገንዘብ የሚቻለው፡፡አሁንም የሚሉት የፌዴራል ሥርአቱ ጀማሪ ነው ነው፡፡ እንዴት 26 አመት ሙሉ ጀማሪ ነን ይባላል፡፡ እንዴት 26 አመት ሙሉ የአፈጻጸም ችግር ነው ይባላል፡፡ በአጠቃላይ ከላይ እንደተገለጸው ይህ ሥርአት ፈተናውን የወደቀ ሥርአት ነው፡፡
አመሰግናለሁ፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *