በአዲስ አበባ አራጣ በማበደር የተጠረጠሩት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ አብይ አበራ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ። ተጠርጣሪው ዛሬ ቤፈደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው የቀረቡት። መርማሪ ፖሊስም ከተጠርጣሪው ጋር ተያይዞ እስካሁን የሰራቸውን ስራዎችና ያከናወናቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል። 

መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ የጀመርኩትን ጉዳይ አልጨረስኩም በማለት ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። በዚህም እየመጡ ያሉ ተጨማሪ ተበዳዮችን ማስተናገድ፣ ተጠርጣሪው ላይ ያሉ ሰነዶችን የማሰባሰብና ምስክሮችን የመለየት ስራ እየሰራ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፤

ከዚህ ጋር ተያይዞም እስካሁን ሁለት ምስክሮችን መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል። ከዚህ ባለፈም ተጠርጣሪው ከተገኘባቸው ሰነድ ውጭ በአራጣ አበድረው በያዟቸው ቸኮች መሰረት የተበዳዮች የሆነን 18 ሚሊየን ብር ያሳገዱበትን የሰነድ ማስረጃ ማግኘቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

Related stories   እነ ጃዋር " በዛሬው ቀጠሮ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁ አይደለንም" ሲሉ የመማከሪያ ጊዜ ጠየቁ

ግለሰቡ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፈጽመዋል ከተባለበት 19 97 ዓ.ም በኋላ ባፈሯቸው ሃብትና ንብረቶች ውስጥ ከወንጀሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሃብትና ንብረቶች ማሳገዱንም ጠቅሷል። በመሆኑም እስካሁን የተሰራው ስራ ሌሎች ተጨማሪ ማስረጃዎች ሊያስገኙ የሚያስችሉ በመሆናቸው ተጨማሪ ምስክሮችና ሰነዶችን በመለየት ላይ መሆኑንን በመጥቀስም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪው በዋስ ከወጡ ሰነዶችን ሊያሸሹና ምስክሮች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ሊያደርሱ ይችላሉ በማለት የዋስትና መብታቸው እንዳይፈቀድም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ለዚህም ከዚህ ቀደም በሁለት ምስክሮች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ አድርሰዋል በማለት አስረድቷል።

Related stories   እጃቸውን የሰጡ ከፍተኛ መኮንኖች ተገደው ሚኒሻ ሲያደራጁ እንደነበር ለችሎት አስረዱ

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ቀደም ብሎ ምርመራ ጀምሬያለሁ በማለቱ እስከዛሬ የተጠቀመው ጊዜ ይበቃዋል በማለት ተጨማሪ ቀን ሊፈቀድ አይገባም በማለት ተከራክረዋል። ተጨማሪ ጊዜ ከተሰጠም ደንበኛችን በቁጥጥር ስር የሚውሉበት ምክንያት አይኖርም በማለት ደንበኛቸው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉና የዋስትና መብታቸው ይከበር ዘንድ ጠይቀዋል።

ለዚህም ፖሊስ ጨረስኩ ብሎ ያቀረበው ስራ ተመሳሳይ በመሆኑ ደንበኛችንን በቁጥጥር ስር እንዲውል ሊያደርጋቸው የሚችል ምክንያት የለም በማለት ምክንያታቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል። ፖሊስ በበኩሉ ተከሳሽ የተጠረጠሩበት ወንጀል በአራጣ ብድር እና ሃሰተኛ ሰነድ በመጠቀም የተለያዩ ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረሳቸው መሆኑን በመጥቀስ ዋስትናው ውድቅ ይደረግልኝ ብሏል።

Related stories   ህገወጥ ሰው አዘዋዋሪ ወንጀለኞችን ለመመርመርና ማስቀጣት የሚያስችል አዲስ የሰነድ ርክክብ ተደረገ

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱም መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውስጥ 12 ቀን በመፍቀድ፥ ለተጠርጣሪው ዋስትና ይፈቀድ አይፈቀድ በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለነሃሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። አቶ አብይ አበራ አራጣ በማበደር ተጠርጥረው ባለፈው ሃምሌ 13 ቀን በፖሊስ በቁጥጥር ሰር መዋላቸው ይታወሳል።

ፋና ብሮድካስቲንግ በሃይለኢየሱስ ስዩም

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *