ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተጨማሪ የሙስና ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ደላሎች እና ነጋዴዎች ቁጥር 42 ደረሰ። የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ዛሬ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በዛሬው እለት ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት፥ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው ያመለከቱት።

እነዚህም ተጠርጣሪዎች ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የመሬት ዝግጅት እና መሰረተ ልማት ዲዛይን ረዳት ሀላፊ የነበሩት ወይዘሮ ሳባ መኮንን ፣ የቤቶች ማስተባበሪያ ምክትል ሀላፊ የነበሩት አቶ ሽመልስ ዓለማየሁ እና የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት ስራ አስኪያጅ የነበሩት ወይዘሮ ፀዳለ ማሞ ናቸው።

ይህን ተከትሎም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር የዋሉት የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ደላሎች እና ነጋዴዎች ቁጥር 42 ደርሷል።

በምርመራ ሂደት ህጉ ከሚፈቅደው የፋይናንስ አሰራር ወጪ ግዥ እና ክፍያ የተፈጸመ ከ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱንም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

በአምስት ተቋማት ላይ የተጀመረው የጸረ ሙስና ትግልም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።  አቶ ጌታቸው በየዘርፉ ከአሰራር ውጪ በተካሄደ ክፍያ በመንግስት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በዝርዝር አስቀምጠዋል።

በዚህም መሰረት፦

ከፌደራል መንገዶች ባለስልጣን 1 ቢሊየን 358 ሚሊየን ብር፣

ከስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከመተሃራ፣ ተንዳሆ እና ኦሞ ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች 1 ቢሊየን 21 ሚሊየን ብር፣

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር፣

ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከ198 ሚሊየን ብር በላይ እና

ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከ41 ሚሊየን ብር በላይ መመሪያው ከሚያዘው ውጪ ክፍያ እና ግዢ በመፈፀሙ በመንግስት ላይ ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት።

ከፍርድ ቤት በወጣ የፍተሻ ፍቃድ መሰረት ብርበራ መደረጉን የገለጹት አቶ ጌታቸው፥ በዚህም ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በአንዱ ቤት ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ተገኝቷል ብለዋል። በሺዎች የሚቆጠር የእንግሊዝ ፖውንድ፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠር ዩሮ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላርን ጨምሮ የተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ እና የቻይና ገንዝብ መገኘቱንም አብራርተዋል።

መንግስት በተጠናቀቀው በጀት አመት መጀመሪያ ላይ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ተልዕኮውን ብቁ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት ጠቅላይ አቃቢ ህጉ፥ ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ እና በሙስና ወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦችን ለማጥራት በገባው ቃል መሰረት የተለያዩ የመረጃ ምንጮች አማካኝነት ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱ ተናግረዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በዛሬው መግለጫቸው መንግስት በሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ከተማ የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ሪፖርትን፣ በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን እና የሀብረተሰቡን ጥቆማን ጨምሮ መንግስት በራሱ ባደረጋቸው ከፍተኛ ጥናቶች ያገኘውን መረጃ እና ማስረጃ መሰረት በማድረግ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ኦፕሬሽን እንደሚቀጥል አረጋገጠዋል።

ህብረተሰቡ ለሚመለከተው አካል የሚያደርገውን ጥቆማን አሁንም እንዲቀጥል ነው የጠየቁት።  ሰሞኑን በመስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉትን ጨምሮ 32 የመንግስት ሰራተኞች፣ ሶስት ጉዳይ አስፈጻሚ(ደላሎች ) እና 7 ባለሀብቶች በድምሩ 42 ግለሰቦች የተያዙ ሲሆን፥ ከሰባቱ ባለሀብቶች መካከል ሁለቱ የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው።

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 22፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰርካለም ጌታቸው

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *