Skip to content

ፖሊስ ሙሉ በሙሉ ማስረጃዎቹን ሰብስቦ ሳይጨርስ “በጥርጣሬ መነሻ አሰሬያለሁ” ማለቱን ጠበቆች ተቃወሙ፤ ከፍተኛ ባለስልጣን ማለት ሚኒስትር ማለት አይደለም

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ሙሉ በሙሉ መረጃ ተሰብስቦ ሳይሆን በጥርጣሬ እንደሆነ ጠቅሶ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቁን ተዘገበ። የተጠርጣሪ ጠበቆች ፓሊስ መረጃውን ሰብስቦ ሳይጨርስ በጥርጣሬ መነሻ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩ አግባብ አለመሆኑ ጠቅሰው ተቃወሙ። በቁትጥር ስር የዋሉት ክፍተኛ ባለስልጣናት አይደሉም በሚል የሚሰማው አስተያየት ትክክል አለመሆኑ ተገለጸ።
ፎቶ ሪፖርተር ጋዜጣ 
ሪፖርተር የችሎት ውሎውን አመላክቶ እንደዘገበው ፖሊስ በያዛቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ሙሉ በሙሉ መረጃ የለውም። በቁጥጥር ስር ሲያውል የጥርጣሬ መነሻዎችን በመያዝ ነው። በዚሁ መነሻ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል። የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው ተቃውሞ ሲያቀርቡ ” ፖሊስ የሚጠረጥረውን አካል በቁጥጥር ሥር ማዋል ያለበት ማስረጃዎቹን ሰብስቦ ከጨረሰ በኋላ መሆኑን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓቱ ተቀምጧል ” ማለታቸውን፣ ከዚህም በተጨማሪ ይህንኑ በተመለከተ የመንግስት የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤትም ይህንኑ ማረጋገጡን አስረደተዋል። ፖሊስ ደንበኞቻቸውን ያሰረው ምንም ሳያሰራ በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ለችሎቱ ተናገረዋል።
በሌላ ተመሳሳይ ዜና የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚባሉት በሚኒስትርና በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ ብቻ ያሉት አለመሆናቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ አመልክተዋል። ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች የፖለቲካ አቅጣጫ ከመስጠት ባሻገር ብዙ ሚና እንደሌላቸው፣ ይልቁንም በዳይሬክተር ደረጃ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በአጠቃላይ በገንዘብ እንቅስቃሴዎችና በቢሮክራሲያዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ከፍተኛ ሥልጣን እንዳላቸው በመግለጽ፣ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በሙስና ጠርጥሮ አላሰረም ተብሎ የቀረበውን ትችት ማስተባበላቸውን ቅዳሜ ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ የተከታተለው የሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል።

አቶ ጌታቸው ሲያብራሩም ‹‹የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ብለን የምናስባቸው በሚኒስትርና በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ብቻ ያሉትን ከሆነ ስህተት ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በመንግሥት ኃላፊነት ከፍተኛውን የመወሰን ድርሻ ያለው በዳይሬክተር ደረጃ ያለው ኃይል ነው፡፡ አጠቃላይ የገንዘብ እንቅስቃሴውንና በቢሮክራሲው ላይ የመወሰን ሥልጣን በእነዚህ ጫንቃ ላይ የወደቀ ነው፡፡ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች የፖለቲካ ተሿሚዎች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በዚህ ጉዳይ የሉበትም ባይባልም እንኳን፣ ዋነኛ ሥራቸው ፖለቲካዊ አቅጣጫ መስጠት ነው፡፡ ነገር ግን በምርመራው የሚገኘው መረጃና ማስረጃ ተሳትፎ እንዳላቸው ካረጋገጠ፣ በእነሱም ላይ ዕርምጃ መወሰዱና መጠየቃቸው አይቀርም፤›› ማለታቸውን ሪፖርተር ጨመሮ ዘግቧል። ሙሉ ዘገባውን ማሰፈንጠሪያውን በመጫን እዚህ ላይ  ያንብቡ ። ከታች ያለው ሙሉ የሪፖርተር የፍርድ ቤት ውሎ ዜና ነው

ከሐምሌ 18 ቀን ጀምሮ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ነጋዴዎች ላይ የተጠየቀው የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ፡፡ መንግሥት ተጠርጣሪዎቹን የለየው ከሕዝብ በደረሰው ጥቆማና ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትና ከአዲስ አበባ ኦዲተር መሥሪያ ቤት በደረሱት ሪፖርቶች መሠረት መሆኑን ገልጿል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ በቅንጅት ባደረጉት ኦፕሬሽን 37 ተጠርጣሪዎችን (የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን፣ ነጋዴዎችንና ደላሎችን) በቁጥጥር ሥር አውለው፣ በ48 ሰዓታት ውስጥ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አቅርበዋል፡፡ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀናት እንዲፈቀድላቸውም፣ ፍርድ ቤቱን ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል፡፡

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ቡድን 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ የጠየቀው ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ያዋለው ሙሉ በሙሉ ማስረጃዎችን ሰብስቦ ሳይሆን የጥርጣሬ መነሻዎች ከያዘ በኋላ መሆኑን በማስረዳት፣ እጅግ በጣም ብዙ የሚሠራቸው ሥራዎች እንዳሉ በመጠቆም የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸውና በራሳቸው የመርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት፣ ፖሊስ የሚጠረጥረውን አካል በቁጥጥር ሥር ማዋል ያለበት ማስረጃዎቹን ሰብስቦ ከጨረሰ በኋላ መሆኑን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓቱ ተቀምጧል፡፡ እነሱን በሚመለከትም መንግሥት በኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አማካይነትም ይህንኑ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ እነሱን በእስር ሊያቆይ አይገባም ብለዋል፡፡ ወይም በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ምንም ሳይሠራ መሆኑ ታውቆ ፍርድ ቤቱ እንዲለቃቸው፣ ወይም ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ፣ ሙስና በባህሪው ውስብስብ በመሆኑ እስካሁን በሰበሰበው ማስረጃ ብቻ የተፈጸመውን ወንጀል አጠቃሎ ማቅረብ እንደማይችል አስታውቋል፡፡ ከእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ጋር የወንጀሉ ንክኪ አላቸው የሚባሉ ተጠርጣሪዎችን መያዝ እንደሚቀረው፣ የታሰሩት ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ ምስክሮችን የማባበል፣ ሰነዶችን የማጥፋትና የማስጠፋት አቅም ስላላቸው ዋስትናቸው ተነፍጎ የተጠየቀው የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜያት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ብይን፣ ተጠርጣሪዎች ፈጽመውታል በማለት መርማሪ ቡድኑ ካቀረበው የወንጀል ድርጊትና ዓይነት አንፃር ውስብስብነት ያለው መሆኑን መረዳቱን ገልጾ፣ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜውን እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ፈቅዷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቆ የተፈቀደለት፣ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ከማዕድን ሚኒስቴር እስከ ውኃ ሀብት ሚኒስቴር ድረስ ያለውን መንገድ ለማስገንባት ትድሃር ኧርዝ ሙቪንግ ኤንድ ኤክስካቬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት ሚስተር ሚናሽ ሌቪ ጋር ውል በመፈጸሙ 198,872,730 ብር በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ጉዳት በማድረስ በተጠረጠሩ ሦስት የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ላይ ነው፡፡ ኃላፊዎቹ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ፣ ኢንጂነር አህመዲን ቡሴር፣ ኢንጂነር ዋስይሁን ሽፈራውና ኮንትራክተሩ ሚስተር ሚናሽ ሌቪ (ከመንገድ ሥራው ጋር በተገናኘ ተከሰው ማረሚያ ቤት ናቸው) ናቸው፡፡

ከመንገድ ግንባታ ጋር በተገናኘ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ደግሞ አቶ አብዶ መሐመድ፣ አቶ በቀለ ንጉሤ፣ አቶ ገላስ ቦሬ፣ አቶ የኔነህ አሰፋ፣ አቶ አሰፋ ባራኪ፣ አቶ ገብረ አናንያ ጻድቅና አቶ በቀለ ባልቻ ናቸው፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ 646,980,626 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ባለሥልጣኑ በኮምቦልቻ፣ በሐረር፣ በጅግጅጋና ከጋምቤላ ጐሬ በሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ አስፈላጊ የሆነ የዲዛይን ለውጥ ሳይደረግና ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውል ሳይኖር ኃላፊዎቹ ሆን ብለው ዋጋ በመጨመር፣ ከአሠራር ውጪ ኮንትራቱ እንዲዘገይ በማድረግ ጉዳቱ እንዲደርስ ማድረጋቸውን ቡድኑ አስረድቷል፡፡

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

የፌዴራል ፖሊስ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ የ31,379,985 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቅሶ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ተክል ምክትል ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋዬና የፋብሪካው ጠቅላላ ሒሳብ ያዥ አቶ ቢልልኝ ጣሰው ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በጋራ በመመሳጠር ከአንድ ኩባንያ ጋር የአርማታ ብረትና ሲሚንቶ በዓይነት መረከብ ሲገባቸው፣ ሳይረከቡና ተቀናሽ ሳያደርጉ በመቀበላቸው ጉዳቱ ሊደርስ እንደቻለ አስረድቷል፡፡

የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የግዢ ቡድን መሪ፣ የውጭ የዕቃ ግዢ ኃላፊዎች ነበሩ የተባሉት አቶ እንዳልካቸው ግርማ፣ ወ/ሮ ሰናይት ወርቁ፣ አቶ አየነው ከበደና አቶ በለጠ ዘለለው ናቸው፡፡ ለዕቃ አቅራቢዎች ያላግባብ 13,104,049 ብር እንዲከፈል በማድረግ፣ እንዲሁም ዕቃ አቅራቢዎቹ በአግባቡ ዕቃውን ባለማቅረባቸው 0.1 በመቶ ቅጣት መቅጣት ሲገባቸው ባለማድረጋቸው፣ 2,743,035 ብር በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ አቶ በለጠ የፋብሪካው የፋይናንስ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ለፋብሪካው መሣሪያ ዕድሳት ያልተሠራ መሆኑን እያወቁ፣ 1,164,465 ብር ክፍያ በመፈጸም ጉዳት ማድረሳቸውን አክሏል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በሕዝብና በመንግሥት ላይ የ184,408,000 ብር ጉዳት አድርሰዋል በማለት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው አምስት ተጠርጣሪዎች ከኦሞ ኩራዝ አምስት የስኳር ፋብሪካ ጋር በተገናኘ ነው፡፡ የፋብሪካው ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መልካሙ፣ ወ/ሮ ሳሌም ከበደ፣ ፋብሪካውን የሚገነባው ጄጄአይኢሲ ተቋራጭ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጂ ዮኦን፣ አቶ ፀጋዬ ገብረ እግዚአብሔርና አቶ ፍሬው ብርሃኔ ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ እርስ በርሳቸው በመመሳጠር በፕሮጀክቱ ላይ አግባብ ያልሆነ ውል በመስጠት ጉዳቱ እንዲደርስ ማድረጋቸውን ቡድኑ አስረድቷል፡፡

ወ/ሮ ሳሌም ባለቤታቸው ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ የአልጋ ቁራኛ መሆናቸውንና በፍርድ ቤት አስወስነው እሳቸው ሞግዚት እንደሆኑ፣ ሌላ ረዳት እንደሌላቸውና እንዲሁም ሁለት ሕፃናት ልጆች እንዳሉዋቸው በማስረዳት ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

ሚስተር ጂ ዮአንም በጠበቃቸውና አልፎ አልፎ እሳቸው ጣልቃ እየገቡ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፋብሪካ እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ከቻይና መንግሥት ባገኘው 550 ሚሊዮን ዶላር ብድር ነው፡፡ እሳቸው በተያዙበት ወቅት አንድ ሚሊዮን ብር የሠራተኛ ደመወዝና 8,000 ዶላር በፀጥታ ኃይሎች በመወሰዱ ለሠራተኛ የሚከፈል ስለሌለ ሥራው እንደሚቆም አስረድተዋል፡፡ እሳቸው በእስር ላይ ከቆዩ፣ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም እያየና በቻይና ላለው ባንክ እያሳወቀ ገንዘብ የሚያስለቅቅ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ በቻይናው ባንክና በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መካከል ያሉት እሳቸው በመሆናቸውና ፕሮጀክቱ ሊስተጓጎል ስለማይገባ፣ በበቂ ዋስ ተለቀው በውጭ ሆነው ሥራቸውን እያሠሩ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀው ነበር፡፡

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ተጠርጥረው የታሰሩት ደግሞ የተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የቤቶች ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አበበ፣ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋዬና የማነ ግርማይ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ የማነ ግርማይ ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በመመሳጠር፣ የተለያዩ ሰነዶችን በመሰረዝና በመደለዝ ለአቶ የማነ ግርማይ 20 ሚሊዮን ብር ያላግባብ ክፍያ በመፈጸም ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ አቶ የማነ የልብ ሕመምተኛ መሆናቸውንና እንኳን ገንዘብ ሊወስዱ ቀርቶ የተጠቀሰውን ሁለት እጥፍ የሚሆን ቀሪ ክፍያ እንዳላቸው ገልጸው፣ ከይቅርታ ጋር ገንዘቡ እንደሚከፈላቸው በቅርቡ ደብዳቤ እንደተጻፈላቸው ተናግረዋል፡፡ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

አቶ የማነ ከአቶ አበበ ተስፋዬና ከአቶ ኤፍሬም ዓለማየሁ ከሚባሉ ተጠርጣሪዎች ጋር በሌላ መዝገብ በቀረበባቸው ክስ ደግሞ፣ ለባቱ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰጥቶ የነበረ 2,000 ሔክታር መሬት ምንጣሮ ለእሳቸው ስለተሰጠ እንደሆነ መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ምንጣሮውን ባቱ ኮንስትራክሽን በካሬ ሜትር በ25,000 ብር ተዋውሎ የነበረ ቢሆንም፣ ለአቶ የማነ ሔክታሩን በ72,150 ብር በመስጠት የ42 ሚሊዮን ብር ልዩነት ያለምንም ጨረታ መሰጠቱን አስረድቷል፡፡

አቶ ፈለቀ ታደሰና አቶ ኤፍሬም ደሳለኝ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የግዢና ንብረት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ፣ 1,000 ካሬ ሜትር መሬት ለማስመንጠር ለባቱ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰጥቶ ተገቢው ሥራ ሳይከናወን አሥር ሚሊዮን ብር ክፍያ በመፈጸማቸው ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ሰባት ባልደረቦች ተጠርጥረው ተይዘዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማሠራት የስድስት ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት እየሠራ እንደሚገኝ፣ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

የቴክኖሎጂው አቅም ላላቸው በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለሚገኙ ባለሙያዎች መሰጠት ሲገባው፣ ዓለም አቀፍ ጨረታ ሕግን ሳይከተሉ በማሠራት በመንግሥት ላይ የ2.2 ሚሊዮን ዶላር ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ጉዳቱን አድርሰዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎችም የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሳ መሐመድ፣ የፕሮጀክት ባለሙያ አቶ መስፍን ወርቅነህ፣ የሚኒስቴሩ የሕግ ክፍል ኃላፊ አቶ ዋስይሁን አባተ፣ ባለሙያዎች አቶ ታምራት አማረ፣ አቶ ሰሙ ጐበና፣ የሕግ ባለሙያ አቶ አክሎግ ደምሴና ሌላ ባለሙያ አቶ ጌታቸው ነገራ ናቸው፡፡ አብረው ተጠርጥረው የታሰሩት ደግሞ ቴክኖሎጂውን ይሠራሉ የተባሉት ወርቁ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ አቶ ዮናስ መርአዊና አቶ ታጠቅ ደባልቄ ናቸው፡፡ ድርጊቱን የፈጸሙት በመመሳጠር መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን አስረድቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የመነሻ ማስረጃዎችን በመያዝ በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድ ቤት ካቀረባቸው 37 ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ፣ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በመያዝ እያሰረ መሆኑ ቢሰማም ሪፖርተር ለኅትመት እስከገባበት ዓርብ ሌሊት ድረስ የተጠርጣሪዎች ቁጥር 39 መድረሱ ታውቋል፡፡ የሁለቱ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን ማንነት ለማጣራት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
ከአንድ ቤት ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ በብርበራ ተገኘ፤ የውጪ ምንዛሬም በብዛት የተገኘባቸው አሉ፤ መንግስት ዘመቻው ይቀጥላል ብሏል

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ደላሎች እና ነጋዴዎች ቁጥር 42 ደረሰ። የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ...

Close