Mohammed Ali Mohammed  መሐመድ አሊ መሐመድ የቀደሞው ፓርላማ አባል

mohamedየቀድሞው የፓርላማ ባልደረባዬ አብዱረህማን አህመድን የሙስናን ጉዳይ ከአሉባልታና የፈጠራ ወሬ ጋር ያያዙበት አቀራረብ ስለመሰጠኝ አንዲት ለስለስ ያለች አስተያየት/ጥቆማ በትህትና አቅርቤ ነበር:: አብዱረህማንን ጨምሮ የገፁ ታዳሚዎች የኔንም አስተያየት ከተራ አሉባልታ ከመፈረጅ አልፈው የህግ ባለሙያና ምክንያታዊ ሰው መሆኔን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት ሞከሩ:: በዚህም ሳያበቁ የሰጠሁት አስተያየት በአሉባልታ ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን ለማረጋጥ የሙሰኞችን ሥም እንድጠቅስና ማስረጃ እንዳቀርብ ወጥረው ያዙኝ:: በማስረጃ ዓይነት, ፋይዳና ሊቀርብ በሚችልበት አግባብ ዙሪያ መነጋገር ሌላ ሙያዊ እሰጥ-አገባ (technical debate) ውስጥ የሚያስገባ ከመሆኑም በላይ የራሱ ቦታና ጊዜ; እናም ባለቤት ስላለው ለጊዜው ለገፁ የሚመጥን የመሰለኝን ቀለል ያለ ምላሽ ሰጥቼ ገለል በማለት ጉዳዩን ወደራሴ ገፅ ላመጣው መረጥኩ::

እደግመዋለሁ – አገር በጠራራ ፀሐይ እየተዘረፈ ነው

ሙስና ከወያኔ/ኢህአደግ ሥርዓት መገለጫ ባህሪያት አንዱ ሲሆን ተቋማዊ መሠረት ያለው ነው:: ወያኔ/ኢህአደግ እንደተቋም ገና ጫካ ሳለ ጀምሮ ባንክና ሌሎች የመንግሥት ተቋማትን መዝረፍ የለመዴና ሀገር ሲቆጣጠርና የመንግሥት ሥልጣን ሲይዝም ይህንኑ ልምዱን በማስፋፋት አገር መመዝበርን ባህል አድርጎታል:: ዛሬ ከየጎጡ ተጠራርቶና ተቧድኖ ሀገርን መዝረፍ እንደነውር የማይታይበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: የሙስና ጉዳይ ከተራ አሉባልታና ሀሜት ባለፈ የህልውና አደጋ መሆኑ በራሱ በሥርዓቱ መሪዎች በአደባባይ ተረጋግጧል:: ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኪራይ ሰብሳቢ, ጥገኛ, አቀባባይ የሚሉና መሰል ቃላት በሥርዓቱ ሰዎች እጅግ የሚዘወተሩና የችግሩን ስፋት/ጥልቀት የሚያመለክቱ ናቸው:: ከዚህም በመነሳት አገርን በመዝረፍ አስነዋሪ ተግባር ውስጥ የተዘፈቁ የሙስና ተዋናዮችን ከሞላ ጎደል መጥቀስ ይቻላል::

1ኛ. የኢንዶውመንት ድርጅቶች ተብዬዋች:-
እነዚህ የሀብታቸው መነሻ/ምንጭ ዘረፋ ነው:: ገዥው ፓርቲ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ህጋዊ ሽፋን ተሰጥቷቸው በዘረፋ ባካበቱት ሀብት ላይ ፍትሓዊ ባልሆነና አግባብነት በጎደለው መንገድ እጅግ ግዙፍና ተገቢ ያልሆነ ትርፍ አጋብሰዋል:: እነዚህ ድርጅቶች ቁልፍ በሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲሰማሩ ከተደረገ በኋላ ከመንግሥት የሚያገኙት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውንም ሥራ በፈለጉት ዋጋ በግላጭ ያገኛሉ:: ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የባንክ ብድር, ሰፊ የቀረጥ ነፃ መብት, የግብር ቅነሳ, የሥልጠናና የተቋማዊ አቅም ግንባታ ድጋፎችና ሌሎች ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል:: የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብቶች እንዳሻቸው ቢዘርፉ ማንም ከልካይ የለባቸውም:: ድርጅቶቹ የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት መዝረፋቸው, ያላግባብ ትርፍ ማጋበሳቸውና መበልፀጋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ጥሮ ግሮ ሀብት የማፍራት እምነትንና የውድድር መንፈስን በመግደል ረገድ የፈፀሙት በደል ከቶም ይቅር የማይባል ነው::

2ኛ. የመንግሥት የልማት ድርጅቶች:-
እንደ ቴሌ, መብራት ኃይል, አውራ ጎዳና, የውሀ ሥራዎች ድርጅት, የማዕድን ልማት አ.ማ, የመንግሥት እርሻዎች, ፋብሪዎች … ወዘተረፈ በራሳቸው ለምዝበራ የተጋለጡ ከመሆናቸውም በላይ ከላይ ከተጠቀሱት የኢንዳውመንት ድርጅቶች ጋር ጤናማ ያልሆነ የሥራ ትስስርና ያልተገባ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር ለምዝበራና ለሀገር ሀብት ብክነት ሰፊ በር ይከፍታሉ:: አንዳንድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደግል ባለቤትነት የተዛወሩበት መንገድና የተሸጡበት ዋጋ ዛሬም ድረስ አነጋጋሪና ጥቂቶች በግላጭ እንደዋዛ የበለፀጉበት ነው።

3ኛ. ሜቴክ:-
የዳበረ ቴክኖሎጃዊ አቅምና ልምድ ሳይኖረው የሀገሪቱ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በሙሉ ለዚህ ተቋም መሰጠታቸው በራሱ እጅግ አነጋጋሪ ነው:: ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የተቋሙ አሠራር ተጠያቂነት የጎደለው, አፈፃፀሙ የወረደና ለከፍተኛ ምዝበራና ዘረፋ የተጋለጠ መሆኑ በህግ አውጭው አካል ፊት ተረጋግጧል:: ከዚህም ባለፈ ይህን ተቋም የኢንዳውመንት ድርጅቶች ከሚባሉት ጋር በማስተሳሰርና እርስ በርስ ተመጋጋቢ በማድረግ በሀገር ልማት ሽፋን ሌላ የዘረፋና ተገቢ ያልሆነ የብልፅግና መንገድ ተፈጥሯል::

4ኛ. ከፍተኛ የፓርቲ/መንግሥት ባለሥልጣናት:-
ከላይ የተጠቀሱትን ተቋማት በመምራትና በቀጥታ በመመዝበር, እንዲሁም የያዙትን የፓርቲ/የመንግሥት ሥልጣን በመጠቀምና ከጥገኛ ባለሀብቶች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ለምዝበራና ያላግባብ ለመበልፀግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት/በመፍጠር በአቋራጭ ከፍተኛ ሀብት ማፍራት ችለዋል:: በዚህ መንገድ ሀብት ሊያፈሩ የሚችሉት በተዘዋዋሪ ሲሆን በተለያዬ ጊዜ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ካገር መውጣቱንና በውጭ አገር ባንኮች መቀመጡን የተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት አጋልጠዋል::

5ኛ. የሥርዓቱ ቀኝ እጅ የሆኑ ባለሀብቶች:-
እንደሸህ መሐመድ አላሙዲን ያሉና ሌሎች ከሥርዓቱ ጋር እጅና ጓንት የሆኑ ባለሀብቶች ሰፋፊ መሬቶችን ከማጋበስ ጀምሮ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ተደርጎላቸው የሀገሪቷን አንጡራ ሀብት በሰፊው ዝቀዋል:: ለራሳቸው ይቅርና ከነሱ ጀርባ የተጠለለ ባለሥልጣን, እነሱን የተጠጋ ቢሮክራትና አቀባባይ ሁላ በአቋራጭና በአጭር ጊዜ የሀብት ማማ ላይ መንጠላጠል ችሏል::

6ኛ. ዝቅተኛው ቢሮክራት:-
በተለይ ከከፍተኛው የፓርቲ/መንግሥት አመራር ጋር መገናኘት በማይችሉ ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ ቢሮክራሲያዊ ጫናዎችን/ውጣ-ውረዶችን በመፍጠርና አማራጭ መንገዶችን በማጥበብ ከነሱ ጋር እንዲደራደሩና የጥቅም ትስስር እንዲፈጥሩ ያደርጋሉ:: በዚህ መንገድ የራሳቸውን አቋራጭ የሀብት ምንጭ የሚፈጥሩ ሲሆን ሰርቶ የማግኘት እምነትንና የውድድር መንፈስን በማቀጨጭ ጤናማ ዕድገት እንዳይኖር አድርገዋል::

7ኛ. ነጋዴዎችና አቀባባዮች:-
በዚህ ምድብ የሚካተቱት በተለይ ለሥርዓቱ ታማኝ የሆኑ ወይም በዝምድና, በአገር ልጅነትና በመሳሰሉት መንገዶች ከባለሥልጣናትና ቢሮክራቶች ጋር የመገናኘትና የጥቅም ትስስር የመፍጠር ዕድል ያላቸው ናቸው:: የነሱ ተልዕኮ በአቋራጭ ጥቅም የሚገኝባቸውን መንገዶች በማነፍነፍና አጋጣሚዎቹን በአግባቡ በመጠቀም በቀጥታ ወይም ለሌሎች ድልድይ ሆነው በማገልገል በአቋራጭና በፍጥነት መክበር ነው::

ከላይ የተመለከተው የሙስና አፈፃፀም ገፅታ ከሞላ ጎደል የችግሩን ስፋት, ጥልቀና ውስብስብነት; እንዲሁም የሥርዓቱን ባህሪ ፍንትው አድርጎ ያሳያል:: ሀገር ለመዝረፍ የተደራጁ የሙስና ተዋንያን ግንኙነት ከተፈለገው ዓላማ ስኬት አንፃር የተቃኘ, ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ,የተጠላለፈና (networked) በሂደት ተቋማዊ ባህሪ እየተላበሰ የመጣ ነው:: የአፈፃፀም ልምድና ክህሎቱ በሂደት እየዳበረና በተለይ ከነታምራት ላይኔና ከነስዬ አብርሃ መታሰር በኋላ እጅግ እየረቀቀ ሄዶ ችግሩን መቆጣጠርና ሂደቱን መቀልበስ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል:: መንግሥትም ችግሩን መሸፋፈን ከማይችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱም በላይ የህልውና አደጋ መጋረጡን በአደባባይ አምኗል::

ጠቅለል ባለ አነጋገር የሙስና ጉዳይ ከወያኔ/ኢህአደግ ህልውና ጋር በጥብቅ የተቆራኘና የሥርዓቱ ባህሪ ዓይነተኛ መገለጫ ነው:: ስለሆነም ሙስናን ከወያኔ/ኢህአደግ ህልውና ነጥሎ መዋጋትም ሆነ ማጥፋት አይቻልም:: ይህን እውነት ከማንም ይበልጥ ሥርዓቱ ራሱ ጠንቅቆ ያውቀዋል:: እውነቱ ይኸው ሆኖ ሳለ ሥርዓቱ ህልውናውን የሚፈትኑ ሌሎች ችግሮች ሲገጥሙት የፀረ-ሙስና ዘመቻ በሚል ትኩረት ለማስቀየርና ፋታ ለማግኘት የሚችልበትን መላ ዘይዷል:: ይሁን እንጅ ይህ ስልት ጊዜያዊ ግርግርና ጫጫታ ከመፍጠር ባለፈ ብዙ ርቀት ሊያስኬድ እንደማይችል ይታወቃል::

ስለሆነም ወያኔ/ኢህአደግ ከበሮ በጎሸመ ቁጥር አብረን እስክስታ የምንወርድ የዋሆች አይደለንም:: የተደራጀ ዘራፊ ቡድን ተቋማዊ በሆነ መንገድ በጠራራ ፀሐይ የሀገርን አንጡራ ሀብት በገሀድ መዝረፉን ሳይክድና በአደባባይ እየተናዘዘ ባለበት ሁኔታ ማስረጃ ይቅረብ የሚል ሙግት ይዞ መነሳት አስተዛዛቢ ነው:: ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ማስረጃ ማሰባሰብና ማደራጀት ያለባቸው የሚመለከታቸው የፍትህ አካላት መሆናቸው ይታወቃል:: ይሁን እንጅ ሥርዓቱ ይህን ማድረግ በሚችልበት ቁመና ላይ አይደለም, መቼም ቢሆን ሊያደርገው አይችልም:: ወያኔ/ኢህአደግ ባለበት ሁኔታ ሙስናን የምር መዋጋት ማለት ሥርዓቱ ከጭንቅላቱ ተመትቶ እንዲወድቅ ማድረግ ማለት ነው:: ወያኔ/ኢህአደግ ደግሞ በራሱ ህልውና ላይ ሊዘምትና ይህን ኃላፊነት (risk) ሊወስድ አይችልም:: ሥርዓቱ በዚህ አጣብቂኝ ውሰጥ በገባበት ሁኔታ ማስረጃ አቅርቡ በሚል አጉል መራቀቅ ዜጎች በአንገብጋቢ ጉዳዮች ዙሪያ በግልፅ እንዳይወያዩ ለማድረግ መሞከር “ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ” ተፈጥሯዊና መሠረታዊ መብትን ማጣብ ተገቢ አይደለም::
ወያኔ/ኢህአደግ ሊክድ በማይችልበት ሁኔታ ሀገር በጠራራ ፀሐይ እየተዘረፈ ነው – እናም እንጮሃለን!

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *