የሀረማያ ሃይቅ ሙሉ በሙሉ ለመድረቅ ተቃርቧል

ከዚህ ቀደም እንዳገገመ የተነገረለት የሀረማያ ሃይቅ በአሁኑ ወቅት ችግሩ ተባብሶ ሙሉ በሙሉ የመድረቅ አደጋ ተጋርጦበታል። የውሃ ምስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቻው አካላት እስካሁን ሃይቁን ለማዳን የሚያስችል እንቅስቀሴ ኣላደረጉም።

የሃረማያ ሃይቅ ለዘጠኝ ተከታታይ አመታት ከ1 ሜትር እስከ 1 ነጥብ 5 ሜትር እየቀነሰ እንደመጣና የውሃ አጠቃቀሙ በዚህ ከቀጠለ ከ21 አመታት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሊደርቅ እንደሚችል በጥናት ተረጋግጧል።

ጥናቱ ይህንን ቢያሳይም ሃይቁ የሚገኝበት የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን እስካሁን ሃይቁን ስለማዳን ያቀዱት የሰሩትም የለም።የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቦና ይህንን ያረጋገጡ ሲሆን፥ ከዚህ በፊት ለችግሩ ታቅዶ የተሰራ ስራ የለም ሲሉም ይናገራሉ።

በችግሩ ላይ ያገባኛል የሚል እያንዳንዱ ሴክተር አስካሁን ለይቶ ያመጣው ነገር የለም፤ ለዚህም በቂ ስራ አልተሰራም ብለዋል። የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ምን ሰርቷል ለሚለው ጥያቄ በሚኒስቴሩ ተፋሰስ ዳይሬክቶሬት የኢኮ ሃይድሮሎጂ ፕሮጄክት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮሃንስ ዘርይሁን፥ ሀይቁ እስኪደርቅ መጠበቅ የለብንም ነበር ይላሉ።ከዚህ በኋላ ጉዳዩን እንዳዲስ በማንቀሳቀስ መሆን ያለበትን ስራዎች እንሰራለን ሲሉም አቶ ዮሃንስ ተናግረዋል።

በሃረማያ ዩኒቨርስቲ የሃረማያ ሃይቅ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ ዶክተር አብዱልለጢፍ አህመድ፥ የሀረማያ ሃይቅ ከቦታው መሸሹና መድረቁ ከዚህ ቀደም መነገሩ እና አገግሟልም ተብሎ እንደነበር ያስታውሳሉ። እውነታው ግን ያ እንዳልነበረ ነው ዶክተር አብዱልለጢፍ የሚናገሩት።

ከዛሬ አምስት አመት በፊት ሃይቁን ለማዳን በሃረማያ ዩኒቨርስቲ፣ በ14 ቀበሌ ገበሬ ማህበራትና 3 የከተማ ቀበሌ ማህበራትን ባቀፈ ከሃረሪ ክልልና ከሃረር ቢራ ጋር የተያዘው እቅድ ወደ ተግባር አልተለወጠም። በዚህ ምክንያት የሀረማያ ሃይቅ የሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኝ ዶክተር አብዱልለጢፍ አህመድ ተናግረዋል።

የከርሰ ምድር ባለሙያና ተመራማሪው አቶ ሃይሌ አረፋይኔ በበኩላቸው፥ ሀይቁን የማዳን ስራ በፍጥነት ካልተሰራ ሙሉ ሙሉ ሊጠፋ እንደሚችል ይናገራሉ።

ሃይቁን ለማዳን አሁንም አልረፈደም ያሉት አቶ ሀይሌ፥ ሃይቁ እንዲያገግምና እንዲመለስ ካስፈለገ የከርሰ ምድር ውሃው ላይ መሰራት አለበት ይላሉ።

የሃረማያ ሃይቅ ከሚችለው በላይ ጥቅም ላይ መዋሉ፣ ከተራራ ወደ ሃይቁ የሚገባ ደለልና በአለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተከሰተ የዝናብ አጥረት ችግሩ እንደደረሰበት ይነገራል። ሃይቁ አሁን ለገጠመው ፈተና ሌላው ምክንያት ተገቢ ጥበቃ እና እንክብካቤ አለማግኘቱ ነው።

ከዚህ ቀደም ሃይቁን ለማዳን ወደ ስራ ገባን ያሉ አካላት ቃል ከመግባት ባለፈ በሚፈለገው መጠን ያለመሳተፍም ሃይቁን ሙሉ በሙሉ የመድረቅ አደጋን ጋርጦበታል።

F.BC

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *