የአራጣ አበዳሪዎችና ተበዳሪዎች ዜና መስማት የተለመደ ሆኗል። በዜናዎቹ የተበዳሪዎች ስም ” ሰለባ” እየተባለ ይጠራል። በዜናዎች እንደሚሰማው አራጣ የሚበደሩት ሰዎች ባለሃብቶች፣ አስመጪዎች፣ ኮንትራክተሮች በጥቅሉ የተሻለ ህይወትና ኑሮ ያላቸው ናቸው። ታዲያ ዜናዎቹ ሰዎቹ ለስራቸው ማስኬጃ፣ ወደብ የተቀመጠ ንብረት ለማንሳት እና ለመሳሰሉት ተግባር ነው የሚበደሩት? እነኚህ ሰዎች ለምን ይሆን አራጣ አበዳሪዎች ጋር የሚሄዱት? ህጋዊ ብድር ማግኘት ስለማይችሉ? ወይስ?

አራጣ ወለዱ ብዙ ነው። አራጣ እጅግ ሰላም የሚነሳ መዘዝ ነው። አራጣ ቤታቸውን የዘጋባቸው፣ በውድቀታቸው ሃፍረት ይዟቸው ዝምታን የመረጡ፣ ትዳራቸው ፈርሶ ቤት የበተኑ ብዙ ናቸው። አራጣ ይባላል እንጂ በዝግ ቤቶች ቁማር ቤት ንብረት እያስያዙና እየተበደሩ በዜሮ የወጡ ብዛታቸውን የሚያውቀው የዚሁ ጉድ ሰለባ የሆነው ቤተሰብ እና ባለቤቱ ብቻ ነው።

ዝግ ቤቶች በቀጥታ አራጣ አበዳሪ ባይባሉም ፣ ንብረት እየያዙ ቁማር ያጫውታሉ። ቼክ እዚያም ይፈረማል።  መኪና እየነዳ ገብቶ ሲወጣ ባዶ እጁን እያጨበጨበ የሚሄድ እንዳለ አይካድም። እንዲህ ያለውን ማህበራዊ ቀውስ ከአራጣ ለይቶ ማየት ብዙም አግባብ አይሆንምና ፋና በነካ እጁ ቢዳሠውስ? የፋና የአምቦ አራታ አበዳሪዎች ዜና እንደሚከተለው ይነበባል

Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

በአራጣ አበዳሪዎች የተነሳ ስራችንም ንብረታችንም አጣን ይላሉ በአምቦ ከተማ በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋራጮች። አበዳሪዎቻችን በዋስትና በያዙት ደረቅ ቼክ ከሰው ተደብቀን ነው ያለነው ይላሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ።

አምቦ ከተማ ውስጥ ስማቸው ከሚነሳ ባለሃብቶች ተርታ የተሰለፉት አቶ ፍቃዱ ምትኩ፥ ከ10 አበዳሪዎቻቸው በ30 በመቶ ወለድ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ተበድረዋል።  አቶ ፍቃዱ ለብድራቸው በዋስትና ያስያዙት የተለያየ መጠን ገንዘብ የታዘዘበት ቼክ ነው።

ሂሳባቸው ውስጥ በቂ ገንዘብ ስለሌለ አበዳሪዎቻቸው ቀድሞ የተሰጣቸውን ቼክ እየመለሱ የገንዘብ መጠኑን ከፍ እያደረጉ ሌላ ቼክ ይቀበላሉ። ግለሰቡ አምስት ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቼን ትቼ ከምታሰር እያሉ ቼኩ ላይ ሲፈርሙ ቆይተዋል።

በዚህ መልኩ ለአስሩም አበዳሪዎቻቸው ከ4 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ በቼክ የሚከፈል ገንዘብ አዘዋል። ግለሰቡ ከአበዳሪዎቻቸው በቅያሪ የተመለሱ ለሶስት የተለያዩ ባንኮች የተጻፉ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ የታዘዘባቸው 25 ቼኮች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አቅርበዋል።

Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

ከዚህም በተጨማሪ አቶ ቡሽራ ሪሳ ከተባሉ ግለሰብ 50 ሺህ ብር ተበድረው 200 ሺህ ብር በንግድ ባንክ ሂሳባቸው (አካውንት) በኩል እንደገባላቸው የሚያሳይ ደረሰኝም ለጣቢያችን አሳይተዋል።

በአጠቃላይ በአራጣ አበዳሪዎች ምክንያት ከ200 በላይ ሰራተኞችን ያስተዳድሩ የነበሩት አቶ ፍቃዱ ምትኩ፥ እጅ አጥሯቸው ከስራ ውጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው የተከበሩ ሽማግሌዎችን ልከው ጉዳዩን ዕልባት ለማሰጠት ያደረጉት ሙከራም በርካታ ገንዘብ በመጠየቃቸው አለመሳካቱን ይገልፃሉ። ለዚህም ምክንያቱ በአበዳሪው በኩል የተላኩት ሽማግሌዎች በራሳቸው በአራጣ የሚያበድሩ መሆናቸው ነው ተብሏል። ግለሰቡ የፈረሙት ቼክ የሚያዝበት በቂ ገንዘብ ሳይኖረው ቼክ በመጻፍ አስከስሷቸዋል።

የአምቦ ከተማ ፍትህ ፅህፈት ቤትም ጉዳዩን ቢያውቀውም ማስረጃ በማጣቱ ብቻ አቶ ፍቃዱ በአራጣ አበድረውኛል ያሏቸውን ሰዎች እንዳላነጋገረ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዘምባባ ታደሰ ተናግረዋል።

በአራጣ ምክንያት ከፕሮጀክታቸውም ከሃብታቸውም ውጪ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ብቻ አይደሉም፤ አቶ አለሙ መገርሳም ተጠቃሽ ናቸው። አቶ አለሙ በስራቸው ለሚያስተዳድሯቸው ሰራተኞች የሚከፈል ገንዘብ ሲያጡ 180 ሺህ ብር ተበድረው 126 ሺህ ብር ወለድ ከፍለዋል። ግለሰቡ አሁን በ441 ሺህ ብር ቼክ ተፈላጊ ሆነዋል፤ ከአምቦ ከተማ ከወጡም አንድ ዓመት ሆኗቸዋል።

Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

በዚሁ ከተማ ከክልሉ ጋር ውል አስረው በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የተሰማሩ አሁን ከስራ ውጪ ሆነው ራሳቸውን ሸሽገው ያሉ አቶ አበራ ቢቂላ የተባሉ ግለሰብም የአራጣ አበዳሪዎች ሰለባ ሆነዋል። በርካታ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የስራ ተቋራጮች አበዳሪዎቻቸው በነጻነት እየተንቀሳቀሱ እነርሱ በወንጀል የሚፈለጉ ሆነዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ፍትህ ፅህፈት በቅሬታ አቅራቢዎቹ የተነሳውን ጉዳዩን አላውቀውም ብሏል። ፅህፈት ቤቱ ተበድለናል ያሉ ግለሰቦችን ፍትህ ለማሰጠት ግን የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ሀላፊው አቶ ጴጥሮስ ማሞ ገልፀዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ አስፈላጊ ከሆነ ጥበቃ ተደርጎላቸው ወደ አምቦ ተመልሰው ቃላቸውን ከሰጡ ጉዳያቸውን ለማየት ዝግጁ ነንም ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ በበኩሉ አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ በአራጣ አበዳሪዎች ምክንያት ከስራ እና ንብረታቸው ውጭ የሆኑ ሰዎችን ቅሬታ ለመፍታት እሰራለሁ ብሏል።

በባሃሩ ይድነቃቸው ፋና ብሮድካስቲን

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *