Skip to content

‹‹የጃማይካ ሙዚቃ የአፍሪካ ሙዚቃ ነው››

ድምፃዊ ፕሮቶዤ

በየአገሩ የተለያዩ ዘመናት ትውልዶች የሚገለጹባቸው እንቅስቃሴዎች ይካሄዳሉ፡፡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ግብ ያላቸው እነዚህ እንቅስቃሴዎች ከተነሱበት ዘመን በዘለለ በቀጣይ የሚመጣው ትውልድ በተሻለ ዓለም እንዲኖር መሠረት ይጥላሉ፡፡ የካረቢያኗ ጃማይካ ለጥቁሮች ነፃነት ከተደረገው ትግል አንስቶ በርካታ እንቅስቃሴዎችን በየዘመናቱ አስተናግዳለች፡፡ የሬጌ ሙዚቃ ትውልድ አገር የሆነችው ጃማይካ የበርካታ ጥበብ ተኮር ንቅናቄዎች መነሻም ናት፡፡ ባለፉት ዓመታት በመላው ጃማይካ እየገነነ የመጣው ‹‹ሬጌ ሪቫይቫል›› የቅርብ ጊዜ ማሳያ ነው፡፡

‹‹ሬጌ ሪቫይቫል›› መልዕክት አዘል ሙዚቃ በወጣቱ ዘንድ ተደማጭነት እንዲኖረው ከማድረግ በተጨማሪ፣ ሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎችም ከሙዚቃው ጎን ለጎን ነፃነትን፣ ፍትሕንና እኩልነትን እንዲያቀነቅኑ ከመፈለግ የመነጨ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በወጣት የጃማይካ የሬጌ ድምፃውያን የተጀመረው እንቅስቃሴው ዓላማውን የሚደግፉ ሁሉ እንዲቀላቀሉ ክፍት ሲሆን፣ ከአገሪቱ አልፎ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እያተረፈም ይገኛል፡፡

ፕሮቶዤ (ኦጄ ኬን ኦሊቨሬ)፣ ክሮኒክስ (ጃማር ማክናውተን)፣ ጃናይን (ጃኒኔ ከኒንግሀም) በእንቅስቃሴው ታዋቂ ከሆኑ ድምፃውያን መካከል ናቸው፡፡ በሙዚቃዎቻቸው ትውልዱን ለማንቃትና በትውልድ አገራቸው ለውጥ ለማምጣት ይጣጣራሉ፡፡ ከድምፃውያኑ አንዱ ክሮኒክስ አዲስ አበባ ውስጥ ትርዒቱን ካቀረበ ወደ ዓመት ገደማ አስቆጥሯል፡፡ ከክሮኒክስ ጋር በቅርበት የሚሠራው ፕሮቶዤ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ የተገለጸው ደግሞ ሌላው የጃማይካ አቀንቃኝ ዴሚያን ማርሌ ትርዒቱን በግዮን ሆቴል ባቀረበበት ምሽት ነበር፡፡

ፕሮቶዤ ወደ አዲስ አበባ የመጣበት ወቅት የራስተፈሪያን ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ መንግሥት መልካም ዜና የተሰማበት ወቅት ነው፡፡ ድምፃዊው ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በላፍቶ ሞል ሊያቀነቅን ሲሰናዳ፣ ከሁለት ቀናት ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ረዥም ዓመታት የኖሩ ራስተፈሪያኖችና ቤተ እስራኤላውያን የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ እንደሚያገኙ ተገልጾ ነበር፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 125ኛ ዓመት የልደት በዓል ሲከበር ደግሞ የንጉሡ ሐውልት በአፍሪካ አዳራሽ ፊት ለፊት እንዲቆም ተጠይቆ ነበር፡፡

በእነዚህ ሁነቶች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አህጉረ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ የመጣው ድምፃዊውን ኮንሰርት ለመታደም የጓጉ ታዳሚዎች ከአመሻሽ ጀምሮ ላፍቶ ሞል አካባቢ ይታዩ ነበር፡፡ በ300 ብር ሲሸጥ የሰነበተው መደበኛ ትኬት በ500 ብር እየተሸጠ ነበር፡፡ በር ላይ የኮንሰርቱ አዘጋጅ ኢኤምኤል ኢቨንትስ ካዘጋጀው ትክክለኛ መግቢያ ትኬት ውጪ በተመሳሳይ በተሠራ ሐሰተኛ ትኬት ለመግባት ይሞክሩ በነበሩ ሰዎችና በጥበቃዎች መካከል እሰጣ ገባ ተፈጥሮ ነበር፡፡

ላፍቶ ሞል ቅጥር ግቢ ውስጥ የፕሮቶዤ አልበሞችና በስሙ የተዘጋጁ ካናቴራዎች እየተሸጡ ነበር፡፡ መድረኩ የተሰናዳው ለሙዚቀኞቹ በሚመች መንገድ ቢሆንም ግቢው እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ የተመቸ አይደለም፡፡ በአገሪቱ ለኮንሰርቶችና ለፌስተቫሎች የተመቹ ቦታዎች በጣት የሚቆጠሩ ከመሆናቸው አንፃርም ሊታይ ይችላል፡፡ ፕሮቶዤ ወደ አምስት ሰዓት ገደማ መድረኩን ሲረከብ ታዳሚው ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገለት፡፡

ጃማይካዊው የኮንቴምፕረሪ ሬጌ አርቲስት ከሙሉ ባንዱ ጋር መድረኩን ግርማ ሞገሥ አላበሰው፡፡ ኢትዮጵያን፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የሚያወስዱ ዘፈኖቹን አብረው የሚያቀነቅኑ ወጣት አድናቂዎቹ ያጅቡት ጀመር፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከአልባሳቱ የማይታጣው ድምፃዊው፣ በዓለም ላይ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና ሰዎች ከማንኛውም ዓይነት ጭቆና ነፃ እንዲወጡ የሚያሳስቡ ዘፈኖቹን አስደምጧል፡፡

‹‹እኔ ሰላምን እደግፋለሁ!››፣ ‹‹በዓለም ላይ በሰዎች ጫንቃ የሚረማመዱ ጨቋኞችን እንቃወማለን!›› በየዘፈኖቹ መካከል ካስደመጣቸው መልዕክቶች መካከል ናቸው፡፡ የመጀመርያው በሆነው የአፍሪካ ጉዞው ኢትዮጵያን በቅድሚያ በመርገጡና ሙዚቃዎቹን በማቅረቡ የተሰማውን ደስታም ደጋግሞ ይገልጽ ነበር፡፡ ‹‹ራስታ ላቭ››፣ ‹‹አንሰር ቱ ዩር ኔም››፣ ‹‹ክሪሚናል››፣ ‹‹ሔል ራስ ታፋራይ››ን የመሰሉ ዕውቅ ዘፈኖቹ የምሽቱ ከፍታ ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሁም በመላው ዓለም ታዋቂ የሆኑ እንደ ‹‹ሁ ኖውስ›› እና ‹‹ኪንግስተን ቢ ዋይዝ›› ያሉ ዘፈኖቹም ሁለት ሰዓት በወሰደው የመድረክ ቆይታው ተደምጠዋል፡፡ በቅርቡ የለቀቀው ጃማይካን እንደ ማሳያ በመውሰድ ሕዝብን የሚበዘብዙ ባለሥልጣኖችን የተቸበት ‹‹ብለድ መኒ››ንም አቅርቧል፡፡ በዘፈኑ ስንኞች ኢትዮጵያን ደጋግሞ በመጥራት ሙዚቃውና ታዳሚው እንዲዋሃድም አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1972 ዕውቅና ካገኙት ድምፃዊት እናቱ ሎርና ቤኔትና ከካሊፕሶ ድምፃዊ አባቱ ሚካኤል ኦሊቨሬ የተወለደው ፕሮቴዤ፣ የሙዚቃ ዝንባሌ ያደረበት ታዳጊ ሳለ ሲሆን፣ የረዥም ርቀት ሯጭ የመሆንም ምኞት ነበረው፡፡ ‹‹በሙዚቀኛ ቤተሰብ ማደጌ ለሙዚቃ ሕይወቴ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሁሉም ጃማይካዊ ከሙዚቃ ጋር ትስስርም አለው፤›› ሲል ነበር ለሪፖርተር የገለጸው፡፡ የረዥም ርቀት ሯጭ የመሆን ህልሙ ዕውን እንዲሆን በወጣትነቱ ዘወትር ቢለማመድም የሙዚቃ ፍቅሩ አሸነፈ፡፡ ሆኖም ሩጫ ከመከታተል ወደ ኋላ አይልም፡፡ ኢትዮጵያውያኑን ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋር፣ ኃይለ ገብረሥላሴና ቀነኒሳ በቀለን ያደንቃል፡፡ ‹‹በተለይ ጥሩነሽ ስትሮጥ ሁሌ እከታተላለሁ፡፡ ብተዋወቃት ደስ ይለኛል፤›› ብሏል፡፡

ግጥምና ዜማ መጻፉን አጠናክሮ የቀጠለው የኮሌጅ ተማሪ ሳለ ነበር፡፡ ሙዚቃዎቹን ለሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲያጫውቱለት ሲሰጥ ‹‹ሙዚቃህ ገና ነው›› ይባል እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ሆኖም ዛሬ ላይ ሆኖ ሰዎች ማስተላለፍ የሚፈልገውን መልዕክት በተገነዘቡበት ወቅት ሙዚቃዎቹ ተደማጭነት በማግኘታቸው እንደሚደሰትም ይናገራል፡፡ ‹‹ከጊዜው በፊት የሚሆን ነበር የለም፡፡ ሙዚቃ የጀመርኩበትን ጊዜ ተምሬበታለሁ፤›› ይላል፡፡

ፕሮቶዤ ዕውቅና እያገኘ የመጣው እ.ኤ.አ. ከ2005 በኋላ ሲሆን፣ የመጀመርያ አልበሙ፣ ‹‹ሰቨን ይር ኢች›› ከለቀቀ በኋላ ከበርካታ ድምፃውያን ጋር በመጣመር ዕውቅ ሙዚቃዎች ለቋል፡፡ ዕውቅናው ሲጨምር፣ በመላው ዓለም እየተዘዋወረ ሙዚቃውን የማቅረብ ዕድልም አግኝቷል፡፡ ‹‹ዘ ኤይት ይር አፌር››፣ ‹‹ኤንሸንት ፊውቸር›› እና ‹‹ሮያሊቲ ፍሪ›› የተሰኙ አልበሞች የለቀቀ ሲሆን፣ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች የሰላ ትችት የሚሰነዝሩ ነጠላ ዜማዎቹም ተወዳጅነት አትርፈዋል፡፡ ‹‹ከአንዱ አልበም ወደ ሌላው ስሸጋገር አድጋለሁ፤ እለወጣለሁ፤›› ሲል ሒደቱን ይገልጻል፡፡

ሙዚቃ የሰዎችን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚውል መሣሪያ መሆን እንዳለበት ከሚያምኑ ድምፃውያን አንዱ ነው፡፡ ‹‹ድምፃውያን ለአድማጮች መንገድ ካሳዩ በኋላ አድማጮች በራሳቸው እውነታን የመፈተሽ እንዲሁም ትክክለኛውን ከስህተቱ የመለየት ኃላፊነት አለባቸው፤›› ይላል፡፡ ከቀደምቶቹ የሬጌ ከዋክብት ቦብ ማርሌ፣ ፒተር ቶሽ፣ በኒ ዊሊር፣ በርኒንግ ስፒርና ሌሎችም ድምፃውያን የተማረው በድፍረት እውነታን የሚጋፈጡ ሙዚቃዎች መሥራትን እንደሆነ ይገልጻል፡፡

የሬጌ ሙዚቃ መሠረቱ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መሆናቸውን ድምፃዊው ይናገራል፡፡ ‹‹የጃማይካ ሙዚቃ የአፍሪካ ሙዚቃ ነው፤›› ይላል፡፡ ጥቁሮች ለነፃነታቸው ያደረጉትን ትግል ያፋፋመው የሬጌ ሙዚቃ ከጃማይካ ቢፈልቅም የአፍሪካ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ለዚህም ነው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በማቀንቀኑ ደስተኛ የሆነው፡፡ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ስለመዝፈን ዘወትር አልም ነበር፡፡ በመምጣቴም ደስተኛ ነኝ፡፡ ዕድሉ ሙዚቃዬን የማቀርብበት ብቻ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃና ስለ አገሪቱ የበለጠ የማውቅበት እንዲሆን እፈልጋለሁ፤›› ሲልም ይናገራል፡፡ የራስተፈርያን ማኅበረሰብ የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ ማግኘታቸውን በተመለከተ ደስታውን ገልጾ፣ ‹‹የማኅበረሰቡ ጫና የሚሆኑ ሳይሆን አገሪቱ በምትፈልጋቸው ቦታ በዕውቀታቸውና በችሎታቸው አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆን አለባቸው፤›› ይላል፡፡

አብዛኞቹ የሬጌ ድምፃውያን የተስፋይቱ ምድር የሚሏት ኢትዮጵያን ደጋግመው በሙዚቃቸው ያወድሳሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሁም ወደ ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች በመምጣት ከሚያቀነቅኑለት ጥቁር ሕዝብ ጋር የመገናኘት ህልምም አላቸው፡፡ ድምፃዊው እንደሚለው፣ ህልማቸው ዕውን የሚሆነው ኃላፊነቱን መውሰድ የሚችሉ ፕሮሞተሮች ሲበራከቱ ነው፡፡ ‹‹እኛ የአፍሪካ ቅጣይ ነው፡፡ ሙዚቃችን ያነጣጠረው በአህጉሪቱ ላይ ነው፡፡ ሥራችንን እዚህ መጥተን እንድናስደምጥ ጥሩ ፕሮሞተሮች ያስፈልጉናል፤›› ይላል፡፡

‹‹ሙዚቃዬ ለእውነትና ለመብት የቆመ ነው፤›› የሚለው ድምፃዊው፣ በሙዚቃው ዓለም ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት ያምናል፡፡ እስካሁን ባለው ጉዞ፣ መልዕክቱን በጃማይካና ድንበር ተሻግሮ በሌሎች ዓለሞች በማስተላለፉ ደስታ እንደሚሰማው ይናገራል፡፡ በተለይም እንደ ‹‹ሬጌ ሪቫይቫል›› ባሉ ወጣት የሬጌ ድምፃውያንን ያማከሉ እንቅስቃሴዎች ጠንካራ መልዕክት ያላቸው ሙዚቃዎች ማሰራጨት በመቻላቸው ይኮራል፡፡

ፕሮቶዤ ሙዚቃዊ ጉዞውን እያከናወነ ያለው ብቻውን ሳይሆን ‹‹ቤተሰቦቼ ናቸው›› ከሚላቸው ኢንዲንግኔሸን ባንድ ጋር በመሆን ነው፡፡ እንደ ማርከስ ጋርቬይና ዋልተር ሮድኒ ያሉ የነፃነት ታጋዮች ለሙዚቃ ሥራዎቹ እንደሚያነሳሱት ይናገራል፡፡ ‹‹ዓለም ላይ ኢፍትሐዊነት በዝቷልና በሙዚቃዬ አንዳች መልዕክት ማስተላለፍ አለብኝ፤›› ሲል ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ በአሜሪካ ውስጥ ጥቁር አሜሪካውያን ለእኩልነት የሚያደርጉን ትግል እንደማሳያም ያነሳል፡፡

በእርግጥ መልዕክት አዘል ሙዚቃዎች እንዳይሰራጩ የሚፈልጉ አካሎች ድምፃቸውን ለማፈን ቢሞክሩም፣ እስከመጨረሻው ከመታገል ወደ ኋላ እንደማይሉ ይናገራል፡፡ ለሁሉም ነገር መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያን በየንግግሩ የሚያወድሰው ፕሮቶዤ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የጃማይካ እስከሚመስል ድረስ የሬጌ ሙዚቀኞች ኢትዮጵያን የሚገልጹ አልባሳት ይለብሳሉ፡፡ ጃማይካውያን ለዓመታት ለኢትዮጵያ ጥልቅ ፍቅር አላቸው፤›› ይላል፡፡

ከኮንሰርቱ በኋላ በሚኖረው ቆይታ ስለአገሪቱ እንዲሁም ስለሙዚቃው የበለጠ የማወቅ ዕድል እንደሚኖረው ተስፋ ያደርጋል፡፡ ስለኢትዮጵያ ሙዚቃ ያለው መረጃ ውስን ቢሆንም ከዚህ ቀደም የሰማቸው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ስልቶች ለውዝዋዜ ጋባዥ መሆናቸውን ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ መጠሪያ ስሙን ‹‹ፕሮዶዤ›› ከሚለው እንግሊዝኛ ቃልና ቤተሰቡ ካወጣለት ‹‹ኦጄ›› በማዳቀል ‹‹ፕሮቶዤ›› ያለው ድምፃዊው፣ ከሕይወት የሚማር መሆኑን በመድረክ ስሙ እንደሚገልጽ ያስረዳል፡፡ ሕይወት ከምትሰጠው ትምህርቶች መካከል በንባብ ስለ ኢትዮጵያ ካገኘው ዕውቀት ባሻገር በዕውን እየጎበኘ የሚገነዘበው እንደሚገኝበት ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

Reporter   ምሕረተሥላሴ መኰንን’s blog

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

0Shares
0
Read previous post:
መረጃ ጠቋሚዎች እስከ 30 ሚሊዮን ብር ሽልማት የሚያገኙበት መመርያ ወጣ

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለመረጃ ጠቋሚዎች እስከ 30 ሚሊዮን ብር ሽልማት መስጠት የሚያስችል መመርያ አወጣ፡፡ ከሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም....

Close