ነብዩ ዳንኤል – የእስራኤልን መውደቅ ባየ ጊዜ ማቅ ለብሶ አምላኩ እግር ስር ተደፋ። ሳይበላ፣ ሳይጠጣ አነባ፣ አምላኩን ተማጸነ …… ከዚህ በሁዋላ ታሪክ ተለወጠ። ነብዩ አሻግሮ ስለሚመለከት፣ የወደፊቱን አስቀደሞ አየና አምላኩ እግር ስር ተደፋ። አሻግሮ ማይት ከመሪዎች የሚጠበቅ ነው። አሻግሮ የማያይ መሪ፣ መሪ ሊሆን አይችልም።ቢሆንም መሪ አይባልም። ራሱን መሪ ብሎ ይጠራል እንጂ፣ እሱ መሪ አይደልም። አሁን አገራችን የገጠማት ችግር አሻግሮ አለማየት ነው። “አማራና ኦሮሞ የተስማሙት በእኛ ችግር ነው” በሚል የሚጸጸቱ መሪዎች ራእይ አልባ፣ የክፋት ምንጮች፣ የበቀል አስተማሪዎች ናቸው። እየሆነ ያለውም ይህ ነው። ብራቮ ኢህአዴግ!!

 

… በሌሎች ወገኖች ላይ የሚደርስን በደል አለመቃወም ግብዝነት ነው። ሌሎች ላይ የሚደርስን ግፍ በዝምታ ማየት ግብዝነት ነው። ሌሎች እናቶች ወልደው መካን ሲሆን መሳለቅ ግብዝነት ነው። ሌሎች ህጻናት ወላጆቻቸውን በጥይት ሲነጠቁ ማሽካካት ግብዝነት ነው። ሌሎች እየተነጠቁ ሲራቆቱ ድጋፍ መስጠት ግብዝነት ነው። ሌሎች ፍትህ ሲዛባባቸው በጥጋብ መስከር የውድቀት አፋፍ ላይ የመድረስ ምልክት ነው…

ይህንን ጽሁፍ ሳዘጋጅ እንባዬ እያስቸገረኝ ሊያሰራኝ አልቻለም ነበር። አንድ መስመር ስጀምር እንባዬ ይጀምራል። አቁሜው ተረጋግቼ መጻፍ ስጀምር እንባዬ ይወረዳል። ያለምንም ማጋነን የሞት ስሜት ነው የሚሰማኝ የነበረው። የሃዘኔ ዋና መነሻ በጥቅሉ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ማሰብና መገንዘብ አለመረዳታችን ነው። ይህንን ጽሁፍ የምታነቡ ይህ ስሜት አይሰማችሁም? የአገራችን ፖለቲካ ከመከርፋት አልፎ አልሄደባችሁም? ቂምና ጥላቻ እንደ ኩይሳ ተከምረው በየቦታው አይታዩዋችሁም? ሰው ሁሉ ሲያልፍ ሲያገደም ጥርሱን እየነከሰ ሲዝትና በንዴት ሲንተከተክ … ማንነታችሁን ለማወቅ ሲሰልላችሁ አይሰማችሁም?
እኔ ትውልዴ ባቢች ከተማ ሲሆን የተማርኩት አምቦ ነው። ከዛም ስድስት ኪሎ ገብቻለሁ። አሁን የምኖረው አዲስ አበባ፣ መምህር ነኝ። በትውልድ የአማራና የኦሮሞ ደም አለኝ። አያቴ ደግሞ ሌላ ደም አላቸው። እድገቴም ውልደቴም ኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ በመሆኑ ከኦሮሞነት ውጪ የሚሰማኝ ስሜት የለም። ወደፊትም ሊኖር አይችልም። ኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ የተወለድኩና ያደኩ የአገሬ ጉዳይ የሚያሳስበኝ ኢትዮጵያዊ ነኝ

በእውነቱ …እንዴት እየታሰበ እንደሆነ ማወቅ ተስኖኛል

በአጭሩ አገራችን ወዴት እየሄደች እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። አጋነንክ ካልተባልኩ ምን እየሆነ እንደሆነም መረዳት አልቻልኩም። እንዴት እየታሰበ እንደሆነ ማወቅ ተስኖኛል። ጤነኛ እንደሆንኩ እርግጠኛ ብሆንም አገሪቱ አሳፍረው የሚጋልቡበት ባቡር ለመደፋት ከሚያደርገው ሽምጥ ፍጥነት አንጻር ላየው አልቻልኩም። በንፋስ ፍጥነት ሲበርና ንፋሱ ሲገርፈኝ ግን እሰማለሁ።
በአገራችን የሚቀንስ፣ የሚሳሳ፣ የሚረግብ ነገር አልታይህም ብሎኛል። በተቃራኒው ነገሮች እየከረሩ፣ እየተበላሹ፣ እየተጨመላለቁ፣ እየተወሳሰቡ፣ መረን ለመውጣት የተቃረቡበት ደረጃ የደረሱበት ወቅት ላይ ነው የሚሰማኝ። ይህ ሟርት ወይም ክፉ ምኞት አይደለም። በትክክል የሚሰማኝ ስሜት ነው። ወደ አንድ የማይታውቅ መድረሻ አገሪቱ ስትከንፍ ይታየኛል። ሁሌም የማየው ይህንን በረራ ነው። በረራው የሚቆም አይመስልም። የዘር ፖለቲካ በሚባለው ነዳጅ የሞት ጉዞን አውጀን፣ ከትንንሾች ጋር እኩል ለመሆን ትንንሽ ተደርገን እየበረርን!!
ብሄርተኝነት የሰውን ልጅ ወደ አውሬነት የሚቀይር ተውሳክ ነው። ገለጻዬን ለማጉላት አጭር ምሳሌ ላንሳ። ፍልስጤማውያን ገና ከህጻንነታቸው ስለ እስራኤል ክፉ እየተነግራቸው፣ አሻኑሊት መጫውቻዎች ሳይቀሩ የእስራኤልን ጨካኝነት በሚያሳይ መልኩ እየተሰራ እየተሰጣቸው ስለሚያድጉ የያዙት አጠቃላይ ምስል አንድ እስራኤላዊ አውሬ፣ ጨካኝ፣ ነበሰ በላ… እንደሆነ ነው። በዚህ ስሜት ያደጉት ህጻናቶች መጨረሻ ምን ድረስ እነደሆነ አይተነዋል። እያየን ነው። ገና እናያለን።
ዛሬም በአገራችን ካለፉት 26 ዓመታት ጀመሮ ልጆች ምን እያዩና እየሰሙ፣ ምን እየተማሩና እየተጋቱ እንዳደጉ ማሰብ ከባድ አይመስለኝም። የትግራይ ህጻናት አማራን አውሬ አድረገው፣ ጠላት አድርገው እንዲስሉ መደረጉን ከራሳቸው ከህወሃት ሰዎች ሰምተናል። ሌሎች ባይፈልጉትም አሁን እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ አንድን የህብረተሰብ ክፍል አውሬ አድርገው፣ ገዳይ አድርገው፣ ጨፍጫፊ አድርገው፣ ነብሰ በላ አድርገው እንዲስሉና በበቀል እንዲያድጉ የሚያደርግ ነው። ይህ አልሆነም የሚሉ ካሉ ለመማርና ለመታረም ዝግጁ ነኝ። ግን ይህ አልሆነም በሚል እኔን እንደቅዠታም ቆጥሮ የሚሞግተኝ ያለ አይመስለኝም። ራሳቸው ህወሃቶችም ቢሆኑ!! ምክንያቱም በሚዲያቸው ነጋ ጠባ የሚዘምሩት መዝሙር ነውና!!
የጅምላ እስር፣ ቶርቸር፣ ግድያ / ህጻናት ሳይቀሩ ተገለዋል፣ እናት የልጇ አስከሬን ላይ ተቀምጣ ተገርፋለች…/ እጅግ ከልክ ያለፈ ደም ፈሷል። እናቶች ያለ ጧሪ፣ ልጆች ያለ ወላጅ ቀርተዋል። በሚገርም ሁኔታ ከተለያዩ አገር በቀልና ዓለም ዓቀፍ የዜና ማሰራጫዎች በተጨማሪ የሶሻል ሚዲያው ሁሉንም ግፍ አሰራጭቶታል። ታሪክና ትውልድ ይህንን ጉድ ማን ፈጸመው በሚል በየትኛውም ዘመን የበቀል እጁን እንደ አቅሙ ለማንሳት ከበቂ በላይ እልህ ውስጥ የሚከቱ መረጃዎች አሉ። ማስተባበል በማይቻልበት ደረጃ ቂም የንግስና ካባውን ለብሶ ቀን እየቆጠረ ነው። ይህ ሁሉ እየሆነ የማለዘብና ነገሮችን ወደ መስመራቸው ለመመለስ ከመስራት ይልቅ ይበልጥ ቤንዚን የማርከፍከፍ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። አንዳንዴም ሆን ተብሎ የሚከናወን እስኪመስል ደረስ!! ሆን ተብሎ ላለመከናወኑ ማስረጃ የለምም።
ይህንን ካልኩ ወደ መነሻውና ህሊናዬን ወዳራደው ጉዳይ ላምራ። በሳምንቱ መጀመሪያ መረራ ጉዲና ወደ ሚታደምበት ፍርድ ቤት አቅንቼ ነበር። ያቀናሁት ቢያንስ ፊቱን ለማየት በሚል ነበር። ወዳጄን አየሁት። ብርክ ያዘኝ። እንደ ህጻን በቆምኩበት ተዝረበረብኩ። እንባዬንና ስሜቲን መቆጣጠር አቅቶን ሳግ ወደላይ ፈነቀለኝ። የማደርገው ጠፋኝ። እረፍት አጣሁ። ሁለመናዬ ሲበላሽ ተሰማኝ። ጎዶሎነት ወረረኝ። “አይ ጊዜ'” አልኩና እንደምንም አካባቢውን ለቀኩ። በቃ ሄድኩ!!
ዶክተር መረራ ጉዲናን ጠንቀቄ አውቀዋለሁ። አስተምሮኛል። እቀርበዋለሁ። ስለ ኦሮሞና ኦሮሚያ ጉዳይ አንስተን በወጉ በተደጋጋሚ ተጫውተናል። አንድም ቀን በስህተት ሌሎችን በሚጎዳና በሚያስቀይ መልኩ ስለፖለቲካ ትግል ስልት አንስቶልኝ አያውቅም። ማክረር የሚባለውን ፖለቲካ የሚጠየፍ ሰው ነው። እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ዜጋ እንደሚረዳው ጽንፈኛ አመለካከቶችን የተዋጋና ፊት ለፊት የተጋፈጠ ጅግናም ነው።

…ማስተባበል በማይቻልበት ደረጃ ቂም የንግስና ካባውን ለብሶ ቀን እየቆጠረ ነው። ይህ ሁሉ እየሆነ የማለዘብና ነገሮችን ወደ መስመራቸው ለመመለስ ከመስራት ይልቅ ይበልጥ ቤንዚን የማርከፍከፍ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል…

ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን ማንንም በግልጽ የሚወቅስ፣ የሚተች፣ ቀልደኛ፣ እንደመጣለት ሳይጨነቅ የሚናገር የኢትዮጵያዊያንን ቀልብና ልብ የገዛ አንጋፋ ፖለቲከኛ፣ መምህር፣ ተመራማሪ፣ አዋቂ ሰው ነው። በዚህም ላይ ሩህሩህ፣ የተቸገሩትን የሚረዳ፣ ምንም ዓይነት የወንጀል ሪኮርድ የሌለበት፣ ስብዕናውን የጠበቀ፣ ያልረከሰ፣ የማይደለል፣ ቆፍጣናና ኩሩ ሰው ነው። ከሁሉም በላይ የሚያውቀውን እውነት ለመናገር የማይፈራና የማይሸማቀቅ ስልጡን ነው። የበቃ ምስጉን መምህር ነው።
በነጻነት ማሰብና መናገር፣ ብሎም ባመኑት መንገድ የመሄድ የሰው ልጆች መብት ከማንም በችሮታ የማይሰጥ መሆኑንን ያምናል። በዚህ እምነቱ ሳቢያ በቀድሞው ስርዓት ታስሯል። ተሰቃይቷል። ዛሬም፣ አሁንም እየተሰቃየ ይገኛል።
ስለ ውድ ባልደረባዬ ይህንን ለማለት ያነሳሳኝ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ፍርድ ቤት ሲቀርብ በአይኔ ብረት የተመለከትኩት ጉዳይ ጤና ነስቶኝ ነው። እርፍት ከልክሎኝ፣ መተንፈስ እስኪያቅተኝ አሞኝ ነው። ስለ ህግና ህግ ጉዳዮች ምንም የምለው የለም። ነገር ግን እንደ አንድ ዜጋና ሰው በወቅቱ መረራ በብረት ወደ ሁዋላ ታስሮ ፣ ክላሽ ከፊትና ከሁዋላ ተወድሮበት፣ በዛ መካከል ተጎሳቁሎ ስመልከተው የተሰማኝን ስሜት የሚሰማ ካለ ለማጋራት ነው።
አንድን “እስረኛ” በብረት ጠፍሮ ማያዝ የ”ሰዎቹ” የህግ አግባብ ሊሆን ይችላል። እዚህ ነጥብ ላይ ለመከራከር አልወድም። በእስር ቤት እንደሚፈጸም ከምንሰማው ግፍ አንጻር በአደባባይ በብረት ማሰር ምንም ነውና። ግን መረራ ለዚህ ” ወግ” መብቃቱ ያሳፍረኛል፣ ያመኛል፣ ህሊናዬን ያርደዋል። ስለዚህም ነው “ሰሚ ካለ” በሚል ከርህራሄ አንጻር፣ የወደፊት ኪሳራን ከማሰብ አንጻር እንደ ማሳሰቢያ ይህንን የሳፍኩት።
እናንተ ግብዞች – ስሙ
በሌሎች ወገኖች ላይ የሚደርስን በደል አለመቃወም ግብዝነት ነው። ሌሎች ላይ የሚደርስን ግፍ በዝምታ ማየት ግብዝነት ነው። ሌሎች እናቶች ወልደው መካን ሲሆን መሳለቅ ግብዝነት ነው። ሌሎች ህጻናት ወላጆቻቸውን በጥይት ሲነጠቁ ማሽካካት ግብዝነት ነው። ሌሎች እየተነጠቁ ሲራቆቱ ድጋፍ መስጠት ግብዝነት ነው። ሌሎች ፍትህ ሲዛባባቸው በጥጋብ መስከር የውድቀት አፋፍ ላይ የመድረስ ምልክት ነው።
መተዛዘን፣ መተሳሰብ፣ መራራት፣ መቆርቆር፣ ማካፈል… ከጥንት የነበረው እሴታችን፣ ምንም እንኳ በዘር ፖለቲካ ተሸርሽሮ ወደ አውሬነት እየቀየረን ቢሆንም ፣ ሙሉ በሙሉ አውሬ ከመሆናቸን በፊት አውሬ የሆነውን አካላችንን የማዳን ስራ ልንሰራ እንችላለን። ሙሉ ሰው ወደ መሆን ለመመለስ ፍላጎቱ ካለ ማለቴ ነው። ይህ የየዋሆችና ጅሎች አስተሳሰብ ተደርጎ ከተወሰደ ….
ግን የመረራ እንደዚህ ሆኖ “ፍርድ ቤት” መቅረብ ማንን ያስደስታል? አሁን የህወሃት ሰዎች በዚህ ትኮራላችሁ? የህወሃት ደጋፊዎች በዚህ ትደሰታላችሁ? የትግራይን ህዝብ ያስከበረዋል? አንድን ሽማግሌ በብረት ጠፍሮና መሳሪያ ደግኖ ማንገላታት ድል ነው? አዋቂነት ነው? ጀብድ ነው? ዝና ነው? ምንድን ነው? በዋስ እንዲፈታ አድርጎ የፍርድ ሂደቱን እንዲከታተል ማድረግ ቢቀር ማሰቃየት ለምን? ይህንን ያዩ የእኔ አይነት ሰዎች እንዲፈጠሩ፣ የቂም መጥን እንዲጨምር…. ለምን ይደረጋል።
አንድ እጅግ የምቀርበው የነበር የኢህአዴግ ሹመኛ ደውዬለት አወራን። ቃል በቃል እንዲህ አለኝ ” ተወኝ፣ ማልቀስ ለራስ ነው” አዎ !! ማልቀስ ለራስ ነው። መረራን አልኩ እንጂ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ያለው እስርና እንግልት ቀንና ቤት ይቁጠረው። ሁሉም በየፊናው ያለቅሳል። አስለቃሾቹ ይሳለቃሉ። ለቅሶ ብስላቅ ተሸንፏል!! ለጊዜው!!
ለማ ሁንዴ ስም የተቀየረ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *