አቶ አለማየሁ.pngፎቶ ሪፖርተር

የኢህአዴግ ፓርላማ ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳባቸው ሚኒስትር ዳኤታ አለማየሁ ጉጆ በስልጣን ዘመናቸው ህሊናቸውን የሚቆረቁር ተግባር እንዳልፈጸሙ ተናገሩ። የተጣለባቸውን ሃላፊነት ባገባቡ መወጣታቸውን ያስረዱት አቶ አለማየሁ፣መንግስት እያከናወነ ያለውን የፀረ ሙስና ትግል እደግፋለሁ ፤ ተፈፀመ የተባለው ጉዳይ እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቢታይ ጥሩ ነበር” ብለዋል። ሲል  አዲስ አድማስ  ዘግቧል።

አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹እውነቱ እንዲወጣ የተባለውን ዕርምጃ (ያለመያዝና ያለመከሰስ መብታቸው የመነሳቱን ጉዳይ) እደግፋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ባገለገልኩባቸው ዘጠኝ ዓመታት ሕዝብና መንግሥትን ለመበደል የሠራሁት ሥራ ህሊናዬን የሚቆረቁረኝ የለም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የቀረበባቸው ጉዳይ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መድረክ መጀመሪያ ቢታይ ይመርጡ እንደነበር፣ ይህ መሆኑም የተፋጠነ ፍትሕን ሊያስገኝ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሕግና የፍትሕ ሥርዓት እስካለ ድረስ‹ ሁሉም ሰው ፍትሕ እንደሚያገኝ አምናለሁ፡፡ ሥርዓታችንም ፍትሕ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ግን የእኔ እምነት ነው፤›› ማለታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል። ከታች ያለው የአዲስ አደማስ ዘገባ ነው።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር  አቶ ዛይድ ወ/ገብርኤል እና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ትናንት ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳባቸው የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚ/ደኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው መታሰራቸውን  ምንጮች ጠቆሙ፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን ለረጅም ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት የመሩት አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ስለተጠረጠሩበት የሙስና ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ማግኘት ባይቻልም በሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸውን አዲስ አድማስ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ማረጋገጥ ችሏል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በቀለ ንጉሴም ሰሞኑን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ሌላው ትናንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ፤ ለፓርላማ የተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀልም  በዝርዝር የተገለፀ ሲሆን ‹‹ፕሮጀክቶች ያለጨረታ በመስጠትና ስራው ሳይጠናቀቅ እንደተጠናቀቀ በማስመሰል ክፍያ በመፈፀም ለአንድ ድርጅት ውለታ ውለዋል›› የሚል ጥርጣሬ ቀርቦባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ሃላፊው ለዚሁ ስሙ ያልተገለፀ ድርጅት፤ ስምንት ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማስደረጋቸው እንዲሁም 2.2 ሚሊዮን  ዶላር የሚያወጣ ስራን በጥቅም በመተሳሰር ያለጨረታ መስጠታቸው ከጠቅላይ አቃቤ ህግ  ማብራሪያ መረዳት ተችሏል፡፡
ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት የግንባታ ቁሳቁሶች ከሚያስገባ አንድ ተቋም ግማሽ ሚሊዮን ብር ጉርሻ በመቀበል የተጠረጠሩት አቶ አለማየሁ ጉጆ፤ እንዲሁም ያለ ጨረታ ፕሮጀክት ካሰሩት የአሜሪካ ኩባንያ ማግኘታቸው ለፓርላማ በቀረበው ሪፖርት ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ የአሜሪካ ኩባንያ ከመላው ቤተሰባቸው ጋር አሜሪካ ለ1 ወር እንዲዝናኑና ልጆቻቸውም እዚያው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል ጥቅም ማግኘታቸውም ተጠቅሷል፡፡  በምክር ቤቱ የነበሩት ሚኒስቴር ዴኤታው በተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ህዝብንና መንግስትን በታማኝነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ገልፀው፤ ህሊናቸውን የሚቆረቁር ተግባር አለመፈፀማቸውንና በተፈጠረው ነገር በእጅጉ ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት እያከናወነ ያለውን የፀረ ሙስና ትግል እደግፋለሁ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “ተፈፀመ የተባለው ጉዳይ እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቢታይ ጥሩ ነበር” ብለዋል፡፡
የመንግስት የተለያዩ መንግስት ሃላፊዎችን በሙስና በመጠርጠር በቁጥጥር ሥር ማዋል ከጀመረ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን እስከ ትላንት የሙስና ተጠርጣሪዎች ቁጥር 50 መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ..

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “ትህነግ ከጁንታነትም ወርዶ በየጫካው ተሹለክላኪ የእህል ሌባ ሆኗል፣ ከያለበት እየታደነ ነው “ሜ/ጀ መሐመድ ተሰማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *