ዶ/ር ዋባና ኩንደር ይባላሉ፡፡ በጋናውያን ዘንድ ሚኒስትር ዱምሶር (Dumsor) በሚባል ቅፅል ስማቸው ይታወቃሉ፡፡ ዶ/ር ዋባና እ.ኤ.አ. በ2014 የጋና የኤሌክትሪክ ሚኒስትር ሆነው በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሾሙ ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ጋናን በወቅቱ ከነበረችበት የኃይል አቅርቦት ችግር ማውጣት ዋና ተልዕኳቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ ከ2012 ወዲህ ተባብሶ የቀጠለው የኃይል አቅርቦት መቆራረጥና ጭለማ፣ የጋናውያን በተለይም የዋና ከተማዋ አክራ ሕይወት ነበር፡፡ ፋብሪካዎች ሠራተኞቻቸውን የመቀነስ ሒደት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ተስፋ የተጣለባቸው ሚኒስትር ልፋትም ተስፋን መፈንጠቅ አልቻለም፡፡ ይልቁንም ‘ሚኒስትር ዱምሶር’ በሚባል ቅጥያ ስም እንዲጠሩ ምክንያት ሆነባቸው፡፡ ጋናውያን ዱምሶር የሚሉት ሁለት የእንግሊዝኛ ቃላትን ‘Dum’ እና ‘Sor’ ገጣጥመው ነው፡፡ ትርጓሜውም ብልጭ ድርግም እንደ ማለት ነው፡፡

ፋታ የማይሰጥ ችግርን በአጭር ጊዜ እንዲፈቱ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሚኒስትሩ ግን፣ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እየሸነገሉ መኖርን አልመረጡም፡፡ አ.ኤ.አ በዲሴምበር 2015 ከተሾሙ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡

ከላይ የተገለጸው በአፍሪካ ዘመናዊ የዴሞክራሲ ታሪክ ተጠቃሽ ከሆነችው ጋና የተገኘ ነው፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር በእንግሊዝ ለንደን ግሪንፌል የመኖርያ አፓርትመንት ላይ በደረሰው ቃጠሎ፣ ከ80 በላይ ሰዎች ተቃጥለው ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡

በዚህ አደጋ የተቆጡ እንግሊዛውያንና የአገሪቱ የሚዲያ ተቋማት በፈጠሩት ጫና፣ አደጋው የተከሰተበት የኬንሲንግተንና የቼልሲ ዲስትሪክት ካውንስል መሪ ሚስተር ኒክ ፓጌት ብራውን በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀዋል፡፡ ‹‹በደረሰው አደጋ ከፊል ኃላፊነት እወስዳለሁ፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በተለያዩ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው፣ እንዲሁም ጥፋት በመፈጸማቸው ራሳቸውን ከኃላፊነት በማንሳት ሞራላዊ ግዴታቸውን ሲወጡ በአገሪቱ የፍትሕ አካላትም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋሉ፡፡

በኢትዮጵያ ግን ይህ ሲሆን አይታይም፡፡ በሥራ አፈጻጸሙ የተተቸ አመራር ወደ ሌላ ኃላፊነት ሲዘዋወር ወይም በዲፕሎማሲ የሥራ ዘርፍ በአምባሳደርነት ሲመደብ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሕግን የተላለፉ ከፍተኛ አመራሮችም ፖለቲካዊ ከለላ ሲሰጣቸው እንጂ በሕግ ሲጠየቁ አይታይም፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የአገሪቱ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባካሄደው የፀረ ሙስና ዘመቻ 50 የሚሆኑ መካከለኛ አመራሮችንና ባለሀብቶችን በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በአገሪቱ ላይ የአራት ቢሊዮን ብር ጉዳት እንዳደረሱ መንግሥት የሰጠው መግለጫ ያመለክታል፡፡

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

ይህንን ዕርምጃ በርካታ ኢትዮጵያውያን ያደነቁት ቢሆንም፣ ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለሙስና መንሰራፋት በር የከፈቱ ከፍተኛ አመራሮች በሕግ የማይጠየቁበት የፀረ ሙስና ዘመቻ የትም አይደርስም ሲሉ ይተቻሉ፡፡

መንግሥት ስለወሰደው የፀረ ሙስና ዘመቻና በቁጥጥር ሥር ስላዋላቸው አመራሮች፣ ቅዳሜ ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ አማካይነት መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በዚህ መግለጫ ላይ ከፍተኛ አመራሩ ለምን በሕግ ተጠያቂ እንደማይሆን ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ተጠይቀው ነበር፡፡ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ብለን የምናስበው በሚኒስትርና በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ብቻ ያሉትን ከሆነ ስህተት ይሆናል፡፡ ለእኔ እስከሚገባኝ ድረስ የመንግሥት ኃላፊነት ደረጃ ላይ ከፍተኛ የመወሰን ድርሻ ያለው በዳይሬክተርነት ደረጃ ያለው ኃይል ነው፤›› ብለዋል፡፡

በማከልም፣ ‹‹አንዳንድ ወገኖች መንግሥት ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታ ካልተጠየቀ ራሱን አላየም የሚሉት ጉዳይ የዋህነት ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ሀብትና ገንዘብ በስፋት የማንቀሳቀስና የማሰማራት ኃላፊነት የተሰጠው ኃይል በዳይሬክተርነት ደረጃ ያለው ኃይል ነው፡፡ ጉዳዮችን የሚያመቻቸውና የሚፈጽመው ይኼ ኃይል ነው፡፡ ይህ ኃይል በሚያቀርባቸው የውሳኔ ሐሳቦችና ሙያዊ አስተያየቶች ላይ ተመሥርቶ ሚኒስትሩ ወይም ሚኒስትር ዴኤታው ሊወስን ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን ኃላፊነት የለበትም አይደለም፡፡ ኔትወርክ ውስጥ ገብተው ከተገኙ ተጠያቂ ከመሆን አያመልጡም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከፍተኛ አመራሩ ማነው?

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በሰጡት መግለጫ በመንግሥት የኃላፊነት ደረጃ ላይ ከፍተኛ የመወሰን ድርሻ ያለው በዳይሬክተር ደረጃ ያለው መሆኑንና የከፍተኛ አመራሩ ሚና ተቋምን የመምራትና የማንቀሳቀስ ኃላፊነት ነው ቢሉም፣ የአገሪቱ የተለያዩ ሕጎች ግን በተቃራኒው ነው የሚደነግጉት፡፡

ሀብትን ለማሳወቅና ለማስመዝገብ የወጣው አዋጅ 668/2002 የመንግሥትን አሠራር በግልጽነትና በተጠያቂነት መመሥረት አስፈላጊ በመሆኑ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የግል ጥቅማቸውንና ኃላፊነታቸውን ሳይቀላቅሉ መሥራት እንዲችሉ ሀብትና ንብረታቸውን ማስመዝገብ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

በዚህ አዋጅ መሠረት የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ተሿሚዎች የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል፡፡ በትርጉሙም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ማኒስትር፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ምክትል ሚኒስትሮች፣ ኮሚሽነሮች፣ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ ዋና ዳይሬክተሮችና ምክትሎች መሆናቸውን ያስቀምጣል፡፡

በተመሳሳይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ለመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ወይም የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተመሳሳይ ትርጓሜ ይሰጣል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በሚለው ትርጓሜ ሥር ደግሞ በተቋማት ውስጥ የሚገኙ ዳይሬክቶሬት ኃላፊዎና ከዚያ በታች ያሉ ሠራተኞች መሆናቸውን ይገልጻል፡፡

በሌላ በኩል ከፍተኛ የልማት ሥራዎችን የሚያንቀሳቅሱ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1992 ድንጋጌ መሠረት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ለሚፈጸሙ ጥፋቶች ሥራ አስፈጻሚዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የቦርድ አመራሮች ጭምር ሕጋዊ ተጠያቂነት እንደሚወድቅባቸው ይደነግጋል፡፡

ከአዋጁ ድንጋጌዎች መካከል የአንድ የልማት ድርጅት ቦርድ የተቋሙን የሥራ አመራር እንደሚሾምና ከሥራ እንደሚያሰናብት ይደነግጋል፡፡ የቦርድ አመራሮች የሥራ ኃላፊነታቸውን በጥንቃቄ እንደሚወጡ፣ ሥራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው በተቋሙ ላይ ለደረሰው ጉዳት በቡድንና በተናጠል ተጠያቂ እንደሚሆኑ ይደነግጋል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የሥራ አመራሮች (ማኔጀሮች) ተጠሪነት ለቦርድ መሆኑን፣ በቸልተኝነትም ይሁን ሆን ተብሎ ለደረሰ ጉዳት በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ይደነግጋል፡፡

በመሆኑም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የሰጡት አስተያየት ሕጋዊ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ያመለክታል፡፡

ፖለቲካዊ አንድምታ

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌታቸው አምባዬ በሰጡት መግለጫ ከፍተኛ አመራሩን ከተጠያቂነት ያገለለ አስተያየት መስጠታቸው፣ የፖለቲካ ስህተት መሆኑንና ከአገሪቱ ዓቃቤ ሕግ የማይጠበቅ ሲሉ የተለያዩ ባለሙያዎች እየተቹት ይገኛሉ፡፡

አቶ ውብሸት ሙላት የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ የሚኒስትሮችና የሚኒስትር ዴኤታዎች ሚና የፖለቲካ አቅጣጫ መስጠት ነው የተባለው አስገራሚ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ለአብነት የአገሪቱን የፋይናንስ አስተዳደር ሕግ የሚጠቅሱት አቶ ውብሸት፣ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ግዥ ያለ ሚኒስትሩ ይሁንታ (ውሳኔ) ሊፈጸም እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

በመንግሥት ተቋማት ከከፍተኛ አመራሩ በታች ያለው የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ ከ500 ሺሕ ብር በታች የተመለከቱ ወጪዎች ላይ ብቻ የመወሰን ሥልጣን እንዳለው በሕጉ መደንገጉን ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም አንድ ግለሰብ በሚኒስትርነት ሲሾም ዝም ብሎ ፊርማውን እንዲያስቀምጥ ሳይሆን፣ እያንዳንዱን የተቋሙን እንቅስቃሴዎች ለመከታተል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል መምህር የሆኑት አቶ ናሁሰናይ በላይ በበኩላቸው፣ ‹‹ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ያላገናዘቡት ለሙስና ምቹ የሆነ ሁኔታ የፈጠረው አመራር ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለሙስና ምቹ ሁኔታን የፈጠረ፣ እያየ እንዳላየ የሆነና በሰዓቱ እንዲቀጣ ያላደረገ በሙሉ ተጠያቂነት ሊኖርበት እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ሙስና ሠረቀ አልሠረቀም ብቻ አይደለም፡፡ በአንድ ጊዜ ውጊያ ወይም እሳት ለማጥፋት በሚደረግ እንቅስቃሴ የማይፈታ  ውስብስብ ተግባር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በዓቃቤ ሕግነት ያገለገሉት የሕግ ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በሰጡት መግለጫ ተጠርጥረው የተያዙት አመራሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት መሆናቸውን ለመግለጽ የተጠቀሙበት መንገድ፣ የታሰሩትን ግለሰቦች በፍርድ ቤቶችና በዓቃቢያነ ሕጎች ዘንድ ጥፋተኛ ሆነው እንዲገመቱ ያደርጋል ሲሉ ተችተዋል፡፡

‹‹እንደምናውቀው ዓቃቤ ሕግ ከፖሊስ የተቀበለውን መረጃና ማስረጃ መርምሮ አልጨረሰም፡፡ በመሆኑም ገና ክስ አልተመሠረተም፡፡ ታዲያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ዋነኛ ሙሰኞች እነማን እንደሆኑ ቀድመው ተናግረው፣ ዓቃቢያነ ሕጎች እንዴት አድርገው ነው በነፃነት ክስ የሚመሠርቱት?›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

በዚህ አገር ላለፉት ዓመታት ሙስና በዘመቻና በዙር በተመሳሳይ መንገድ ሲካሄድ እንደቆየና በዚያው መንገድ መቀጠሉን አቶ ዮሐንስ ያምናሉ፡፡ ‹‹ከአቶ ታምራት ላይኔ ጀምሮ ይኼኛው ዘጠነኛ ዙር ዘመቻ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች በጋራ የሚስማሙት ግን፣ ሙስና በዙር የሚካሄድ ወይም የፖለቲካ ትኩሳት በተነሳ ቁጥር ለማብረድ የሚዘመትበት ሳይሆን፣ ንቁ ሥርዓት መፍጠር የሚጠይቅ የማያቋርጥ ዘመቻን የግድ የሚል መሆኑን ያሳስባሉ፡፡ (ሰለሞን ጎሹ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል)

ዮሐንስ አምበርብር ሪፖርተር

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *