አቶ በቀለ ገርባ ክሳቸው በሽብር ወንጀል ስር ሊታይ አይችልም በሚል ውድቅ የተደረገ የክስ ሃሳብ እንደገና ተጠቅሶባቸው የዋስትና መባታቸውን እንደተከለከሉ ጠበቃቸው አስታወቁ። ጠበቃቸው ይህንን ያስታወቁት አምስት ጊዜ ሲንከባለል የቆየውን የዋስትና ጥያቄ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ፍርድ ቤት ውድቅ ካደረገው በሁዋላ ነው።
ቀደም ሲል ውጪ ካሉ የተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸውና ኦሳ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል በሚል በተራ ቁጥር 2 እና 3 ተመስርቶባቸው የነበረው ክስ ማስረጃ አልቀረበበትም በሚል በሽብርተኛ ወንጀል ሊያስከስሳቸው እንደማይችል፣ በዚሁም አግባብ በተራ የወንጀል ህግ ጉዳያቸው ሊታይ እንደሚገባ ውሳኔ ተሰጥቶ ነበር።
በዚሁ መሰረት የአገሪቱን ህገ መንግስት ጠቅሰው የዋስትና መብታቸውን እንዲከበርላቸው የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቆች ጠይቀው ነበር። ለአምስት ጊዜ የተለያየ ምክንይት እየተሰጠ ሲንከባለል የቆየው ብይን በመጨረሻ ውድቅ ተደርጓል። ለዋስትናው መብት መከልከል ዋና ምክንያት የሆነው ” ቢፈቱ ከአገር ይወጣሉ ፣ ከተፈቱ ዳግም የማነሳሳት ስራ ይሰራሉ ” የሚል ነው።
ይህ አቃቤ ህግ ያቀረበው መከራከሪያ ቀደም ሲል ማስረጃ ያልቀረበበት ተብሎ ውድቅ የተደረገ ሲሆን፤ አቶ በቀለ ገርባ ቀደም ሲል ታስረው ሲፈቱ ከአገር ውጥተው ተመልሰዋል በሚል ጠበቃቸው ተከራክረዋል። አቶ በቀለ በበኩላቸው ” ደሮም ፍትህን አገኛልሁ ብዬ አላስብም” ማለታቸው ተሰምቷል።
” ፍትህ አገኛለሁ ብዬ አስቀድሜም አላስብም እዚህ የምንመላለሰው ጉዳዩን የዓለም ህብረተሰብ እንዲያውቀው ነው” ያሉት አቶ በቀለ ገርባ ቀደም ሲል ጉዳዩን የኦሮሚያ ፍርድ ቤት በውክልና የሚያየው ሆኖ ሳለ፣ መከልከሉ ቀድሞውም የፍርድ አካሄዱን መዝመም እንደሚያሳይ ተባግረዋል። ውሳኔውም ምንም እንዳላስደነቃቸውና የሚጠብቁት እንደሆነ አመልክተዋል።
አቶ በቀለ በቃሬዛ ያምጡኝ እንጂ በራሴ ፈቃድ ወደ ችሎት አልመጣም በሚል መናገራቸው አይዘነጋም