ድርቅ በሶማሌ ክልል የቤት እንስሳት ላይ አደጋ ደቅኗል

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ባለፈው ሁለት ዓመት ብቻ በድርቅ ምክንያት ሁለት ሚሊዮን የቤት እንስሳት መሞታቸውን አስታውቋል፡፡ የደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች አሁንም ተመሳሳይ አደጋ እንደተደቀነባቸዉ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

Image result for animals dying in ethiopia somali region

“በኢትዮጵያ በ2 ዓመት 2 ሚሊዮን የቤት እንስሳት ሞተዋል”

በ50 ዓመት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የከፋ ድርቅ ባለፈው ዓመት የተጋፈጠችው ኢትዮጵያ በዚህ ዓመትም ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ዜጎቿ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጋለች፡፡ በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመጋቢት እስከ ግንቦት ወር ይጠበቅ የነበረው ዝናብ ዝቅተኛ መሆኑ አሊያም ጭራሽ መቅረቱ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ከዚህ ቀደም ድርቅ ደጋግሞ የጎበኛቸው በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢ ያሉ አርብቶ አደሮች በተለይ የሕይወታቸው መደገፊያ አድርገው የሚቆጥሯቸው ከብቶቻቸው ህልውና አሰግቷቸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ በእነዚህ አካባቢዎች ዝናብ በመጥፋቱ ምክንያት የተከሰተው ድርቅ የነበረውን “ግጦሽ እና የውኃ ምንጮች አመናምኗል” ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ከብቶች ለህመም ተዳርገዋል አሊያም ሞተዋል ሲልም አስታውቋል፡፡ በተለይ ችግሩ በሶማሌ ክልል የጠና መሆኑንም ገልጿል፡፡ ሮም ጣሊያን በሚገኘው የ FAO ዋና መሥሪያ ቤት የድርቅ መቋቋሚያ ድጋፍ ክፍል ኃላፊ አቶ ሽኩሪ አህመድ በኢትዮጵያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን ብዛት በማነጻጸሪያነት በማንሳት ያብራራሉ፡፡

“ከዚህ 8.5 ሚሊዮን 3.3 ሚሊዩኑ አርብቶ አደሩ አካባቢ ነው፡፡ ይሄ ወደ 40 በመቶ የሚጠጋ ማለት ነው፡፡ ይሄ ካለው የህዝብ አሰፋፈር፣ ካለው የህዝብ ጥግግት ጋር ሲያያዝ በጣም ትልቅ ቁጥር ነው፡፡ ትልቁን እጅ እንዲይዝ ያደረገው በተለይ በመጋቢት እና [በቀጣይ ወራት] ባለመዝነቡ ምክንያት ነው፡፡ የእዚህ የአርብቶ አደሩ አካባቢ [ተረጂዎች] ቁጥር መጨመር የእዚህ የአሁኑ ዋናው ዝናብ አለመዝነብ ምክንያት የተከሰተ ነው” ይላሉ አቶ ሽኩሪ፡፡

የአርብቶ አደሩ አካባቢ ከጎርጎሮሳዊው 2015 መጨረሻ ጀምሮ በኢልኒኞ የአየር መዛባት ተከስቶ ከነበረው ድርቅ ሙሉ ለሙሉ አለማገገሙ ለችግሩ መባባስ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ “ሦስት ተከታታይ የዝናብ ጊዜ ነው ያልተከሰተው፡፡ የእነኚህ የሦስቱ የዝናብ ጊዜዎች በትክክል አለመዝነብ፣ መዛባት ወይም ጭርሱኑ አለመዝነቡ ያለውን የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ አናግቶታል፡፡ የተወሰኑ አካባቢዎች ከብቶቻቸውን አጥተዋል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች እንደውም ቦታዎቻቸውን ለቅቀው ቀድመው የወጡ ሰዎች አሉ” ሲሉ በአካባቢዎቹ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሽኩሪ እንደሚናገሩት በከብቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ወደ ሰውም እንዳይሻገር “ትልቅ ጥረት” እየተደረገ ነው፡፡ ሆኖም እስከ መጪው ጥቅምት ገፋ ሲልም እስከ ታኅሳስ ድረስ የሚዘልቅ እርዳታ ለአርብቶ አደሮቹ ካልቀረበ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል ይላሉ፡፡ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ በሶማሌ ክልል ቆራኼ አካባቢ የሚንቀሳቀስ የግብረሰናይ ድርጅት ሠራተኛ ለዶይቸ ቬለ እንደገለጸው አሁን የአካባቢው ሰዎች እርዳታ እያገኙ ቢሆንም የድርቁ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ግን አስጊ ነው፡፡

“አሁን በቅርብ ጊዜ ከአንድ ሁለት ወር በፊት የተወሰነ ዝናብ ዘንቦ ነበር ያ ዝናብ ለሰዎቹ ጠቃሚ አልነበረም፡፡ ዝናቡ እንደተጠበቀው አልሆነም፡፡ አሁን ከብቶቹ ያሉበት አካባቢ በዚህ አንድ ወር ሁለት ወር አካባቢ ካልዘነበ ከብቶቹ ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ዝናብ እጥረት በጣም አለ፡፡ ያሰጋል፤ በጣም ያሰጋል” ይላል የእርዳታ ሰራተኛው፡፡

በአሁኑ ወቅት ለFAO አሳሳቢ የሆነው ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የደረሰው የከብቶች እልቂት ድጋሚ በእነዚህ አካባቢዎች ማንዣባቡ ነው፡፡ እንደ FAO መግለጫ ከሆነ ባለፈው ሁለት ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ሁለት ሚሊዮን የቤት እንስሳትን አጥታለች፡፡ የእርዳታ ሠራተኛው በሶማሌ ክልል ያለውን የከብቶች ሁኔታ ሲገልጽ በቆራኼ፣ ጀረር፣ ዶሎ እና ነጎብ ዞኖች ድርቁ ከመበርታቱ የተነሳ ለከብቶች የማገገሚያ ማዕከላት ተዘጋጅቶላቸዋል ይላል፡፡ በእነዚህ ማዕከላት ውኃ በቦቴ እንደሚጓጓዝላቸው፣ መኖም እንደሚቀርብላቸው ይገልጻል፡፡ እንዲህ አይነት እርዳታ ያልደረሰላቸው በርካታ ከብቶች ግን ባለፉት ወራት መሞታቸውን አመልክቷል፡፡ FAO በቀጣዩቹ ሳምንታት በሚያደርገው ግምገማ በአሁኑ ድርቅ ምን ያህል ከብቶች እንደሞቱ እንደሚታወቅ አቶ ሽኩሪ ለዶይቨ ቬለ ተናግረዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ , ሸዋዬ ለገሠ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *