በቶላ ሊካሳ

    ……የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ጥፋት ፈልጎ ማጥመድና ማሸት፣ ወዘተ፣ ወዘተ የማያሳፍሩ የአብዮታዊ/የልማታዊ ዴሞክራሲ የመታገያ መንገዶች ሆነው ቆይተዋል፡፡ ዕድገት፣ ሹመት፣ የጥቅማ ጥቅም ዕድሎችም እንዲሁ ‹‹ደጋፊ›› የማብዣ መሣሪያዎች ሆነው አገልግለዋል፡፡ ሹመትና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማ ጥቅሞች የፖለቲካ አገልጋይ መግዣ አድርጎ መጠቀም ከልካይ ከሌለው፣ የአገርና የመንግሥት ንብረት ለፓርቲ ሥራ መዋሉ ወግና ሕግ ከሆነ ሥርዓት ይናጋል፡፡ የኅብረተሰቡ የሕግና ሥርዓት እንዲሁም የሥነ ምግባር ውቅራቶች ፍልስልሳቸው ይወጣል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፖለቲካዊ ሎሌነትን በጥቅም የመግዛት፣ ሙሰኝነትን አሠራሩና ባህሪው ያደረገ መንገድ የሙስና አባዢ እንጂ ለሙስና ፀር መሆን አይችልም…

ከአምስት ዓመት በፊት የክረምቱ ወራት ከመግባቱ በፊት ጀምሮ እንደ ተለመደው ድንገት፣ ውስጥ ለውጥና በሹክሹክታ የተሰማው የአቶ መለስ ዜናዊ መታመም ወሬ መንግሥት፣ ፓርቲው፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤትና ባለሥልጣኖቻቸው ዕቅድ ይዘው ግዳጅ አድርገው ቀርቅረው ይዘው የሚጠብቁት፣ የሚከላከሉትና የሚያስተባብሉት ሚስጥር ነበር፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆኗ በምታስተናግደው ዓመታዊ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ግን የአቶ መለስ አለመገኘትና አለመታየት ሊደብቁት የማይችሉት በመሆኑ ምክንያት ብቻ ሳይሆን፣ በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ሊቀመንበር በይፋ ተነገረ፡፡

አገር ውስጥ አለመኖራቸው መታመማቸው ብቻ እየተወራ የፓርቲው ጫካ ውስጥ የተገኘና የዳበረ ባህልና ‹‹ግለሰባዊ›› አነስተኛ ቦታ መማኸኛ እየሆነ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የማወቅ መብት እዚህ ውስጥ የሚያገባው ጉዳይ የለም ተባለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይም እንደተለመደው ከሕገ መንግሥቱ በላይ ከመንግሥት የአስተዳደር ሕግና ወግ ይበልጥ የፓርቲ ወግና ባህል የአገር ጉዳይ መግዛት ያዘ፡፡ በዚህ ውስጥ እያለንና ስለአቶ መለስ ሕመም፣ አድራሻና ሁኔታ ‹‹አትጠይቅ አትመልስ›› ሠፍኖ እያለ መንግሥት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ሕልፈታቸውን በይፋ ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ አነሰም በዛም፣ ከፋም ለማም በጭምጭምታ ሰምቶ የጨረሰው ቢሆንም ብሶቱን ውጦ የአሁኑን ከወደፊቱ አገናዝቦና የአቶ መለስ ዜናዊን ደግ ደጉን አስተውሎ ያዘነው ማዘን ደግሞ ለማንም አስደማሚ ነበር፡፡ ለእኔ ደግሞ ትምህርትም ነበር፡፡ አስደማሚ ትምህርት፡፡ የኢትዮጵያ የጠብ ፖለቲካ ለዚህ ሕዝብ ምን ያህል እንደጠበበው እንድገነዘብና አንገቴን እንድሰብር አደረገኝ፡፡ ዓይናችንን ካልጨፈንን ልቦናችንን ካልደፈንን፣ በስተቀር ትምህርቱና ኃፍረቱ ከላይና ከሥር ያሉትን፣ መታመማቸውን ደብቀው የራሳቸው ብቻ ‹‹የቤተሰብ›› ጉዳይ ያደረጉትን ፖለቲከኞችና መሪዎቻችን ሁሉ የሚመለከት ነበር፡፡ ከ1968 ዓ.ም. አንስቶ የፍጥጫ ፖለቲካ ውስጥ ከገባን እስከዚያው ድረስ 37 ዓመታት ሆነን፡፡ አሁንም እነሆ ለ42 ዓመታት እዚያው የጥላቻና የፍጥጫ ፖለቲካ ውስጥ ነን፡፡ ሕዝብ ግን በእኛ ፖለቲካ እንደማይመዘንና ከፖለቲከኞች ፍጥጫ በላይ እንደሆነ አስመስከረ፡፡ ለሟቹ አዘነ ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ሳይሆን መተማመኛ ለሌለው ለራሱ ኑሮም አዘነ የባሰ እንዳይመጣ ሠጋ፡፡

የምናወራለት ሐዘን ከአስከሬን አቀባበል እስከ ቀብር በመንግሥት ስለተቀናበረው ተራ በተራ ቤተ መንግሥት የመድረስ፣ ሠልፍ የመውጣትና በአደባባይ ሻማ የማብራት ምደባ ስለተካሄደበት፣ ፎቶ ያለው ካነቴራ ግዙ እየተባለ ስለታዘዘበት፣ ቅን ሐዘን በፕሮፓጋንዳ ተጎሳቁሎ ለታለ አይሰጥ ኑሮ ከዚህ በላይ እንባ ሲበዛ ተብሎ ስለተተረተበት የሰሜን ኮሪያን የመሰለ የሐዘን ትርዒት አይደለም የማወራው፡፡ በየደረስንበት የተመለከትነውንና የመሰከርነውን ቀደም ብሎ እህል እየሸመተ እንዴት እንሆን ይሆን እያለ ሲጨነቅ የነበረ ሰው በየቤቱና በየመንደሩ ከልቡ ይገልጽ ስለነበረው የምር ስሜት ነው፡፡ በጣም መራር ብሶት የነበራቸው ሰዎች እንኳን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ደንግጠው ከእሱ የተሻለ ሰው ከቀሪዎቹም፣ ከተቃዋሚዎቹም ማን አለ ብለው ሲጨነቁ መስከረናል፡፡ የአቶ መለስ ያልተጠበቀ ሞት በኋላ እንዴት እንሆናለን የሚል ጭንቀት የፈጠረው በሕዝብ ውስጥ ብቻ አልነበረም፡፡ ድንጋጤውና ጭንቀቱ በመንግሥት (በፓርቲ) ውስጥ ያሉት ሰዎች ጭምር ነበረ፡፡ እነሱም ጭንቅ ጥብ ውስጥ እንደነበሩ አመላካቾችን ዓይተናል፡፡ የሞቱን አለዚያም የሕመሙን ተደብቆ መሰንበትና ሌላ ሌላውን ትተን የሕዝብ በጎ ምላሽ የፈጠረባቸው ግርምታና ዕፎይታ ብቻውን ለማሳያ ያህል በቂ ነው፡፡

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ያኔም በወቅቱ እንደሚታወቀውና አሁንም ከአምስት ዓመት በኋላ እንደተረጋገጠው፣ የሕዝቡም ሆነ ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ጭንቀት አልፎ ሂያጅ ንፋስ አልሆነም፡፡ እውነታዊ መሠረት ያለውና ያላበቃለት መፍትሔ ያልተገኘለት ችግር አለው፡፡ ከዝምታችን፣ ከሰላማችንና ከመቻቻላችን ሥር በቁጥጥርና በፕሮፓጋንዳ እየተድበሰበሰና እየ‹‹ታከመ›› የቆየ ሕመምና ረመጥ አለ፡፡ ያኔም ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለታዘነ ሐዘኑ ለፕሮፓጋንዳ ሽመና ውሎ የስም ግንባታ ሐውልት ኅብረተሰቡ ህሊና ውስጥ ለማነፅ፣ ወይም በእሳቸው የመሐንዲስነት ውዳሴ ውስጥ ለመጠለል ስለተሞከረ፣ የዚህም ልምድ ስለዳበረ ከ10 እና ከ12 ዓመት ወዲህ የመጣ ልማት የ26 ዓመት እንዲመስል ተደርጎ ስለቀረበና ልማቱን የማፋጠን ተግባር ለራሳችን ሳይሆን የሟቹ ራዕይ ከንቱ እንዳይቀር ብለን የምንሠራው እስኪመስል የተጠናከረ፣ ቃል ኪዳን ያጎረፈ፣ ፕሮፓጋንዳ የአገር ወግ ስለሆነ ከሥር ያለው ረመጥና ከውስጥ ያለው ምሬት አልጠፋም፡፡

በ2008 ዓ.ም. ከኅዳር አንስቶ እስከ 2009 ዓ.ም. መባቻ ድረስ የዘለቀውና የፈነዳው ተቃውሞ ድፍን አሥር ወር የፀናው አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም የዚህ ምስክር ነው፡፡ ዛሬም እንደ በፊቱ ብሶቶችን ማስተባበል ማፈን ወይም እንዳይወጡ ፕሮፓጋንዳ ማልበስ በተንሠራፋ ቁጥጥርና በእሳት ማጥፋ የዘመቻ ሥራ ሽንቆሮቹን እየተከታተሉ ‹‹መድፈን›› ከቀጠለ ሄዶ ሄዶ ጋን እንዳይፈነዳ፣ ቤት እንዳይቃጠል ያሳስባል፡፡ ድንገቴዎች መቼ እንደሚከሰቱና ምን ይዘው እንደሚመጡ እንደማይታወቅ መጀመርያ የአቶ መለስ ሞት ማሳሰቢያ፣ የ2008/09 ዓ.ም. የሕዝብ ተቃውሞና የተቃውሞው አስተዳደግ ደግሞ በቂ ማስጠንቀቂያ ነበር፡፡ አሁንም ‹‹ጨዋታው›› አልፈረሰም፡፡ የገዢው ፓርቲ ወገንና መንግሥት የመንግሥትና የፓርቲን ሚና ሳያምታቱ፣ በፀጥታ መረባቸውና በፕሮፓጋንዳ ምርታቸው ሳይዋጡ፣ ተቃዋሚዎችም እርስ በርስ ካብ ለካብ መተያየታቸውን ትተው ከመንግሥትም ይምጣ ሳይሉ ለትግግዝና ለአገር ጥቅም ሊሠሩ ይገባል፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ መንግሥት ከዓመታዊ የ‹‹ሌጋሲ ማስቀጠል›› ክብረ በዓል፣ ከፀረ ሙስናው የዘመቻ እንቅስቃሴ የፕሮፓጋንዳ ሥጋጃ ሥር የሕዝብ ብሶት ልዩ ልዩ ምክንያቶችና ምንጮች እንዳሉ፣ እውነተኛው የአገር ሕመም የትኛው እንደሆነ መፍትሔውና መድኃኒቱም የቱ ስለመሆኑ ሙሉ ምርመራና አጥጋቢ ሕክምና እንዲያገኝ ማድረግ አለበት፡፡ የአገራችን ችግር ከአንድ ቡድንና ፓርቲ በላይ ነው፡፡ አንድ ወይም ሌላ ቡድን ብቻውን የሚፈታው አይደለም፡፡ የዥጉርጉር ብዙኃን አገር የሁሉንም መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ እኔ ብቻ ባይነት የኢሕአዴግ የችግሮች ሁሉ ችግር ነው፡፡

ኢሕአዴግ እኔ ብቻ ካልገዛሁ ሁሉን እንቅስቃሴ ተቀጥላዬ ካላደረግሁ ባይ ነው፡፡ ሕዝቦች ከደርግ ወታደራዊ አገዛዝ የተላቀቁበት ለውጥና የተገኘው ሥልጣን የመስዋዕትነቴ ውጤት ነው፡፡ የሕዝቦችን ጥቅም የምወክልና የማራምድም እኔው ብቻ ነኝ፡፡ እኔንና መስመሬን የተቃረነ ጠላት፣ (መጀመርያ የኢሠፓ ርዝራዥ፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ አሸባሪ) ነው የሚል ወፍራም የብረት ጡሩር የተላበሰ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ትምክህተኛን የሚንቀው ኢሕአዴግ አውራ ትምክህተኛ ሆኖ አርፎታል፡፡

ነፃ ገበያ፣ የብዙ ፓርቲ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ የሕግ የበላይነት ባይነት ድሮውንም ቢሆን በስተኋላ የመጡና ከተለወጡ የዓለም ሁኔታዎች ጋር ራስን የማስማሚያ ዘይቤዎች የነበሩ ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የመሰለ ሰነድ ውስጥ ገብተውም ትርጉም የሚኖራቸው የኢሕአዴግ የበላይነት እስከተከበረ ድረስ ብቻ ነው፡፡ የኢሕአዴግ የበላይነት የግድ መሆን አለበት፡፡ ይህ ከሸፈ ማለት ስንቶች የተሰውለት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማ ተሸነፈ፣ ከሸፈ ማለት ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን በሚቻለው ሥልት ሁሉ (በጉልበትና በሸፍጥ መንገዶች ሁሉ ጭምር) መዋደቅ የታጋይ ግዴታ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የተገራው በዚህ አመለካከትና አካሄድ ነው፡፡

ስለነፃ ምርጫና ስለነፃ ፍርድ ቤት እያወሩ በተግባር ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መቆጣጠር፣ የወጡትን ሕግና ደንብ በግልጽና በሥውር መጣስ፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ጥፋት ፈልጎ ማጥመድና ማሸት፣ ወዘተ፣ ወዘተ የማያሳፍሩ የአብዮታዊ/የልማታዊ ዴሞክራሲ የመታገያ መንገዶች ሆነው ቆይተዋል፡፡ ዕድገት፣ ሹመት፣ የጥቅማ ጥቅም ዕድሎችም እንዲሁ ‹‹ደጋፊ›› የማብዣ መሣሪያዎች ሆነው አገልግለዋል፡፡ ሹመትና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማ ጥቅሞች የፖለቲካ አገልጋይ መግዣ አድርጎ መጠቀም ከልካይ ከሌለው፣ የአገርና የመንግሥት ንብረት ለፓርቲ ሥራ መዋሉ ወግና ሕግ ከሆነ ሥርዓት ይናጋል፡፡ የኅብረተሰቡ የሕግና ሥርዓት እንዲሁም የሥነ ምግባር ውቅራቶች ፍልስልሳቸው ይወጣል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፖለቲካዊ ሎሌነትን በጥቅም የመግዛት፣ ሙሰኝነትን አሠራሩና ባህሪው ያደረገ መንገድ የሙስና አባዢ እንጂ ለሙስና ፀር መሆን አይችልም፡፡

Related stories   “ትህነግ ከጁንታነትም ወርዶ በየጫካው ተሹለክላኪ የእህል ሌባ ሆኗል፣ ከያለበት እየታደነ ነው “ሜ/ጀ መሐመድ ተሰማ

ኢሕአዴግ ከመንግሥት ተቀጥላነት ውጪ የሆነ ነፃ የሕዝብ እንቅስቃሴን አይፈቅደም፡፡ ነፃ የብዙኃን መድረኮችን እንኳንስ ማበረታታት ፊት መስጠት እርም ነው ብሎ የጀመረው ገና ሲጀመር አንስቶ፣ በግል ጋዜጦችና በኢሰመጉ የሚወጡ ዘገባዎችን ጉድፍ መመልከቻ አድርጎ ከመጠቀም ይልቅ የጠላት ጥቃት እንደተፈጸመበት አድርጎ ሲያይ የቆየውና ይህም አሁን ድረስ ቀጥሎ የአገር ፖሊሲ የሆነው ከዚሁ እኔ ብቻ ልክ ነኝ ችግሩ የተነሳ ነው፡፡ የሙያና የብዙኃን ማኅበራትን ተቆጣጥሮ የራሱ ፖለቲካ ማስፈጸሚያ ማድረግ ሲቻለው ከፖለቲካ ነፃ የሚሆን የለም ብሎ ይከራከራል፡፡ አልጠመድ ያለውን ማኅበር ደግሞ ከበስተጀርባው የፖለቲካ ዓላማ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ሥራ የሚሠራ ብሎ እየፈረጀ እየሰረሰረ ሌላ ተለጣፊ ፈጥሮ ንትርክ ውስጥ ከቶ፣ አግዶና አዳክሞ በመልቀቅ ፋይዳ ቢስ ያደርጋል፡፡ ያለቀላቸው ዕቅዶችና ውሳኔዎቹን በስብሰባና በጭብጨባ የሕዝብ ውሳኔ በማድረግ ይህንንም ለሕዝባዊ አሠራር ማረጋገጫነት በመጠቀም የተለመዱት ጥበቦች ውስጥ እየተትረከረከ፣ ዴሞክራሲን ገነባሁ ሊልና ዴሞክራሲን የመገንባት ሚናም ሊጫወት አይችልም፡፡

ሥልጣንና ትክክለኛነት የእኔ ብቻ ከሚል አመለካከት እስካልተገላገለ ድረስ፣ ሕገወጥ መሰሪ መንገዶችንና በሥልጣን መማገጥን ጭምር እንደ ትግል መሣሪያ የመጠቀም ዘይቤውን እርግፍ አድርጎ የሚያስጥለው ሥርዓት እስካልተዘረጋ ድረስ፣ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን የመገንባትና ሙስናን የመዋጋት ሚና ሊጫወት አይቻለውም፡፡ ኢሕአዴግ ነጋ ጠባ በየመድረኩና በየተሃድሶው ፌርማታ ላይ እንደሚለው ዴሞክራሲ በአንድ ድርጅት በጎ ፈቃድ ላይ የሚንጠለጠል ሰጥቶ ሊከለክለው የሚችለው መሆን የለበትም፡፡ ዴሞክራሲ፣ መብቶቻችንና ነፃነቶቻችንም ከማንም የቁርጠኝነት መሀላ ውጪ የሚኖሩ ሆነው መገንባት አለባቸው፡፡

በገሃዱ ዓለም ውስጥ ግን እንደህ ያለ ነገር የለንም፡፡ የአገር ህልውና ከኢሕአዴግ ጋር የተጣበቀ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ በጎ ፈቃድ የወጣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊደራጅ አልቻለም፡፡

ዴሞክራሲው የሌለው በፓርቲው ውስጥ ጭምር ነው፡፡ የኢሕአዴግ (አባል ድርጅቶች) አባላት የድርጅቱ የገደል ማሚቱዎች ናቸው፡፡ የፓርቲው አቋምና መስመር አድራጊ ፈጣሪ የድርጅቱ አመራር ነው፡፡ የድርጅቱ ጉልላትና አመራር የመንግሥታዊ ሥልጣኑም ጉልላት ወይም ቁንጮ ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ተጠሪነቱም ለአገሪቱ ሕዝብ ነው፡፡ ይህንን የሚለው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ በተግባር ግን ሕግ የማውጣት፣ አስፈጻሚውን የመመርመርና የመጠየቅ፣ ሕግ ተርጓሚውን የመሾምና ሌላው ቀርቶ መንግሥታዊ የብዙኃን መገናኛዎችን የመምራት ሥልጣን አለው የሚባለውና በኢሕአዴግ ተመራጮች የተሞላው የተወካዮች ምክር ቤት ግን ዞሮ ዞሮ በፓርቲው የበላይ አመራር ምናልባትም መሪ መዳፍ ውስጥ ነው፡፡ ኢሕአዴግን የሚመሩት ጥቂት ግለሰቦች ናቸው፡፡ ቅድመ 2004 ዓ.ም. ነሐሴማ እሳቸው ብቻ ነበሩም ይባላል፡፡

ለማንኛውም ኢሕአዴግን የሚመሩት የመንግሥቱንም ሥራ አስፈጻሚ አካል ይመራሉ፡፡ በኢሕአዴግ የፓርቲ የመስመር ግንኙነት በኩል ደግሞ በፓርላማው ውስጥ ያሉትን ተወካዮች ያዛሉ፡፡ መናገር፣ መደገፍና መቃወም ያለባቸውን ይሰፍሩላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በመንግሥት ተጠሪዎች አማካይነት ተቋማዊ ህልውና አለው፡፡ የመንግሥት ተጠሪዎች ማለት በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አብላጫ መቀመጫ ያገኘው ፓርቲ በዚያው ምክር ቤት ውስጥ የፓርቲውን ሥራዎች እንዲያስተባብሩ የሚወክላቸው የምክር ቤቱ አባል የሆኑ የፓርቲ አባሎች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር በሕግ (አዋጅ ቁጥር 916/2008) የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ነው፡፡ በአጭሩ ሥራ የማስፈጸም፣ ሥራ አስፈጻሚውን የመቆጣጠር፣ የመመርመርና የመጠየቅ፣ ሕግ የማውጣትና ዳኛ የመሾሙ ሥራ ሁሉ በአንድ ቡድን/ግለሰብ ውስጥ ነው፡፡ ወይም ነበር፡፡

ከ2008 ዓ.ም. በኋላ ይህን ሁኔታ አጋልጦና አሳጥቶ ያወጣ አንድ ድንገተኛ ጥናትና ምርምር ነበር፡፡ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል መግለጫ አቋም በአስፈጻሚው አካል ላይ የቀረበ ከባድ ክስና ‹‹ፍርድ›› ጭምር ነበር፡፡ ከመጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ መሰማት የጀመረውና እንደየሁኔታው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ውይይት የተስተጋባው ይህ እንቅስቃሴ ግን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ‹‹ደነገጠ››፡፡ የደነገጠውም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጥናቱን እንደማያውቁት፣ ጥናት ማለት የመንግሥት ፖሊሲ ማለት እንዳልሆነ፣ እንዲያውም ‹‹የተሃድሶ እንቅስቃሴው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በዚህች ባለች አጭር ጊዜ ውስጥ ምን ዓይነት ጥናት ሊጠና እንደሚችልም… ግራ ይገባል፣ ጥናት ጊዜ ይወስዳል፤›› ብለው ውድቅ ሲያደርጉት ነው እንጂ፣ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናት (ጥናት አይደለም ተባለ እንጂ) የአስፈጻሚውን አካል ‹‹በደል›› እና ‹‹ግፍ›› መቁጠርና ማስቆጠር ጀምሮ ነበር፡፡

Related stories   Egypt-Sudan alliance shifting in row with Ethiopia over Nile dam

የ2007 ዓ.ም. ምርጫ አቶ መለስ የሌሉበት የመጀመርያው ምርጫ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ውጤት መሠረት ሥልጣን የያዘው አምስተኛው ፓርላማ ከአጋሮች ጋር መቀመጫውን በሙሉ አሟጦ የያዘ ነበር፡፡ በዚህ ምርጫ የተቋቋመውን መንግሥት ተቃውሞ መናጥ የጀመረው ገና ከኅዳር ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር፡፡ ከ2009 ዓ.ም. ከመስከረም ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አውጀን አሥር ወራት እዚያው ውስጥ ቆየን፡፡ የተሃድሶው አካል አድርገን የአፈጻጸም ብቃታችንን ለማሻሻል ሹምሽርም እያደረግን ነው፡፡ የፀረ ሙስና ዘመቻም ጀምረናል፡፡

ተሃድሶው በኢሕአዴግ በረዥሙ ሥልጣን ላይ የመቆየት መዋቅር አኳያ ከተቃኘ፣ ትግሉ ዴሞክራሲን የመገንባትና ሙስናን የመዋጋት ሚና አይኖረውም፡፡ ኢሕአዴግ ካለታማኝ ጭፍራ በቀር ማንንም ሳያስጠጋ ሥልጣን ለብቻው ይዞ ረዥም ዘመን ለመቆየት የቆረጠና የኢትዮጵያ ልማት ያለ ኢሕአዴግ አይቀጥልም ብሎ የሚያምን ነው፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ ‹‹የልማታዊ መንግሥት›› ሐሳብና ትምህርት “African Development: Dead Ends and New Beginnings” የሚል የረዥም ሥራ ቅንጭብጭብ ውስጥ የሚከተሉት ነጥቦች ቁልፍ ቦታ ይዘዋል፡፡

– ዛሬ በኒዮሊበራሊዝም ውስጥ ማደግ የተዘጋ መንገድ ነው፡፡ ማደግ የሚቻለው በልማታዊ መንግሥት ነው፡፡

– ልማት የፖሊሲ መቀጠልን ይጠይቃል፡፡ በአንድ የምርጫ ዘመን ልማት አይሟላም፡፡ በዴሞክራሲ ምርጫ (በገዢ ፓርቲ መቀየር) ፖሊሲ ሊቀየር ይችላል፡፡ ይህ እንዳይሆን ኢዴሞክራሲያዊ ከመሆን አማራጭ ውጪ የረዥም ዘመን ጥምረት የመፍጠር መንገድ አለ፡፡ መንግሥት ለመቅጣትም ሆነ ለመሸለም ነፃ መሆን ስላለበት በዚህ ጥምረት ውስጥ የግል ባለሀብቱ አይካተትም፡፡

– ይህ ጥምረት ከገጠሩ ኅብረተሰብ ጋር ነው፡፡ ለተረጋጋ ልማታዊ አጋርነት ጠንካራው መሠረት የገጠሩ ኅብረተሰብ ነውና፡፡ የዚህ ዓይነት ጥምረት “Dominant Party/Dominant Coalition Democracy” ይባላል፡፡

– በመሠረታዊ የልማት ፖሊሲ ላይ ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት በፖለቲከኞቹና በሕዝቡ መካከል እስከተፈጠረ ድረስ የፓርቲዎች የሥልጣን ቅይይርም ባለበት ሁኔታ፣ የልማት ፖሊሲ ፅናትና ቀጣይነት ሊያገኝ ይችላል፡፡ ይህ ግን በታዳጊ አገሮች ውስጥ የማይሆን ነው፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲ ነው፡፡

እነዚህን ነጥቦች በደንብ ያስተዋለ ኢትዮጵያዊ የመለስን ‹‹አዲስ መንገድ›› እንደ ማንኛውም የጥናት ሥራ ወይም የዕድገት ንድፈ ሐሳብ ሙከራ አድርጎ ሊወስድ አይችልም፡፡ የመለስ ‹‹አዲስ መንገድ›› ብቸኛ ገዢ በመሆን ዓላማ የተነደፈና በምሁራዊ ወዘና የቀረበ በሥልጣን ላይ የመቆየት አዋጅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውም የዚህን ንድፍ ክንዋኔ ይመስለኛል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ህልውናና ዕጣ ከአንድ ፓርቲ የሥልጣን ጥቅም በላይ ነው፡፡ ዴሞክራሲም መልካም አስተዳደርም ከማንም ፈቃድና ከወረት የዘለለ ዕድሜ ሊኖራቸው የሚችለው፣ ህልውናቸው ከሥራ አስፈጻሚው በጎ ፈቃድ ውጪ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ማለትም የሥልጣነ መንግሥቱ ወታደራዊውም፣ ሲቪሉም ዓምዶች ከቡድናዊ ቅኝትና መረባዊ ውጦሽ ሲፀዱና ሲጠበቁ፣ የሕግ ተርጓሚው፣ የሕግ አውጪውና የአስፈጻሚው የሥልጣን አካላት አላስፈላጊ ዝንባሌዎችን ለመቆጣጠር በሚያስችል ተገናዛቢነት ሲደራጁ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የጎደላት ይኸው ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Reporter Amharic

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *