“Our true nationality is mankind.”H.G.

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ምስክሮችን የማወቅ መብት ስም ዝርዝርና አድራሻ ማግኘትን አይጨምርም አለ

የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ጥሰዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው ተከሳሾች ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የቆጠረባቸውን ምስክሮች የማወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለባቸው ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ጥያቄ፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል›› በማለት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የተላከ ቢሆንም ውድቅ ተደረገ፡፡ ይሁንና ምስክሮችን የማወቅ መብት የተከሰሱ ሰዎች የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ መብት የሚያረጋግጥ እንጂ፣ የምስክሮችን ስምና አድራሻ የማግኘት መብት እንደማይጨምር የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በግልጽ ሕገ መንግሥቱ ላይ መቀመጡን ገልጿል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን የተከሳሾች አቶ መሃዲ አሊይ፣ አቶ አህመድ አደምና አቶ ዓሊ ድልበቱና የከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ‹‹ምስክሮችን የማወቅ መብት አለኝና መታወቅ የለበትም›› ክርክር እልባት ለማሰጠት ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የላከው ቢሆንም፣ የክርክር መነሻውን አዋጅ ቁጥር 652/2001ን የመረመረው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም›› ብሏል፡፡

ተከሳሾች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) መሠረት ማለትም የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ፣ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት እንዳላቸው በተደነገገው መሠረት፣ ዓቃቤ ሕግ የቆጠረባቸውን ምስክሮች የማወቅ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ባቀረበው መቃወሚያ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 32(ሐ) ድንጋጌ መሠረት ለምስክሮች ጥበቃ ለማድረግ ማንነታቸውና አድራሻቸው እንዳይገለጽ መደንገጉን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 4(ሸ እና በ) ማንነታቸውና አድራሻቸው እንዳይገለጽ፣ ወይም እንዳስፈላጊነቱ በመጋረጃ በስተጀርባ ሆነውና ተሸፍነው ማንነታቸው ሳይገለጽ ምስክርነታቸውን እንዲያሰሙ መደንገጉን በመጠቆም፣ የተከሳሾች ‹‹ምስክሮች ይገለጹልን›› ጥያቄን ተቃውሟል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በዋናነት ተቃውሞውን የሚያቀርበው ምስክሮቹ ከመሰከሩ በኋላ በተከሳሾች ዘመዶችና ወገኖች ጥቃት ይደርስባቸዋል በማለት ነው፡፡

Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት

ተከሳሾቹ በበኩላቸው ባነሱት የመቃወሚያ ክርክር ለምስክሮች ደኅንነት ተብሎ ማንነታቸውና አድራሻቸው ለተከሳሽ እንዳይደርስ የሚደረገው፣ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት አመልክቶ ፍርድ ቤቱ ሲፈቅድ፣ ምስክሮቹ ለፍርድ ቤት አመልክተው ሲፈቀድላቸውና ፍርድ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት የምስክሮች ስም ዝርዝር ለተከሳሽ እንዳይደርስ ሲወስን ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በራሱ ጊዜ ፍርድ ቤቱን ሳያስፈቅድ የምስክሮቹን ማንነት አለመግለጹ የሕግ ድጋፍ እንደሌለው በማስረዳት ዝርዝራቸው እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ ተከሳሾች ያቀረቡት ‹‹የምስክሮች ዝርዝር ይሰጠን›› ጥያቄ፣ ከምስክሮች ጥበቃ አዋጅ አንፃር የምስክሮች ስም ዝርዝር ለተከሳሾች መድረስ በምስክሮች ሕይወት ላይ አደጋ ያደርሳል ወይስ አያደርስም የሚለውን ፍርድ ቤቱ በማስረጃ ከማጣራቱ በፊት፣ የተከሳሾቹ ጥያቄ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) መሠረት፣ የምስክሮች ዝርዝር ተገልጾ ቢሰጣቸው በምስክሮቹ ላይ አደጋ እንደሚደርስ ማረጋገጥ ቢቻል፣ ተከሳሾች ማንኛውንም ማስረጃ እንዳያውቁ መከልከል ይቻላል አይቻልም የሚለው የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው በመግለጽ ለምክር ቤቱ ልኮት ነበር፡፡

Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔም ከፍርድ ቤቱ የመጣን ትዕዛዝ መሠረት አድርጎ መመርመሩን በውሳኔው ገልጿል፡፡ ጉባዔው ፍርድ ቤቱ የላከለትን ትዕዛዝ ሲመረምር የተረዳው፣ ጥያቄያቸው የሕገ መንግሥት ትርጉም ሳይሆን የሕግ ትርጉም መሆኑን ገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ የሚሉት ፍርድ ቤት ሳይከለክላቸው ዓቃቤ ሕግ በራሱ ተነሳሽነት የሕግ ድጋፍ ሳይኖረው የምስክሮችን ዝርዝር ሊከለክል እንደማይችል የሚል መሆኑን አክሏል፡፡

ጉባዔውን ለማጠናከር፣ ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በድጋሚ በወጣው አዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ (4) መሠረት በፍርድ ቤት የሚላከው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ፣ በፍርድ ቤቱ በክርክር ላይ ያለውን ጉዳይ ለመወሰን የሚጠቅም በሚሆንበት ጊዜና በትርጉሙ መሠረት ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ እንደሆነ መደንገጉን አብራርቷል፡፡

በመሆኑም ተከሳሾች ያቀረቡት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሕጉን በመተርጎም የሚሰጠው ብይን ወይም ትዕዛዝ ለጉዳዩ ውሳኔ ለመስጠት ከሚጠቅም በስተቀር፣ ፍርድ ቤቱ ከሚሰጠው የሕግ ትርጉም የበለጠ ለጉዳዩ ውሳኔ አሰጣጥ የሚጠቅም አለመሆኑን ጉባዔው አስታውቋል፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ የምስክሮቹን ደኅንነት በሚመለከት ‹‹አደጋ ያመጣል ወይስ አያመጣም?›› የሚለውን አረጋግጦ ሊፈቅድ ወይም ሊከለክል እንደሚችልም ገልጿል፡፡

Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት

ፍርድ ቤቱ የላከውን የትርጉም ጥያቄ ጉባዔው መመርመሩን ጠቁሞ በተመሳሳይ ጥያቄ ላይ በመዝገብ ቁጥር 1365/2007 ውሳኔ መስጠቱን በማስታወስ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) ድንጋጌን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ጉባዔው በማብራሪያው እንደገለጸው፣ በአንቀጽ 20(4) ምስክሮችን በሚመለከት የተደነገገው የተከሰሱ ሰዎች የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ መብት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ እንጂ፣ የምስክሮችን ስም ዝርዝርና አድራሻ እንዲደርሳቸው መብት የሚሰጣቸው አለመሆኑን ወይም ግዴታ የሚጥል አለመሆኑን አሳውቋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 20(4) ላይ ለተከሳሾች መብት የሰጠበት ምክንያት፣ ፍትሐዊ የሙግት አካሄድ እንዲኖር መሆኑን አክሏል፡፡

ተከሳሽ የምስክሮችን ስምና አድራሻ ማወቁ ፍትሐዊ የሙግት አካሄድን ከማሳካት ይልቅ፣ ምስክሮችን ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እንዳይፈጸሙ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና በሕጎች አግባብ እንዲወሰን ለማድረግ መሆኑን ጉባዔው አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) መሠረት የተከሳሾች ስም ዝርዝር እንዳይደርስ ማድረግ፣ ከተገለጸው መብት ጋር የማይጋጭና የሕገ መንግሥቱን መርህ የተከተለ መሆኑን በመግለጽ፣ የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ በሙሉ ድምፅ ውድቅ ማድረጉን ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል፡፡

Reporter Amharic

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0