…የሐሰት ክሱን ያነሳችው የቀድሞ ባለቤቴ የክብር እንግዳ ሆና በዚያው ሴኔት ውስጥ ንግግር አድርጋ ነበር፡፡ ኒውዮርክ ውስጥ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የታወቁ ድርጅቶች ሴኔቱን በመርዳት የኔ ክስ በአሜሪካ ታሪክ ትልቅ ምሳሌ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ናይሮቢ ይካሄድ የነበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ስብሰባ ሳይቀር በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እንዲደረግ፣ የአሜሪካ ሚዲያም ሙሉ ለሙሉ ሽፋን እንዲሰጠው አድርገዋል፡፡ የተሰጠው የፖለቲካ ክብደት በቃላት የምገልፀው አይደለም…

photo reporter

አቶ ካሊድ አደም   

አቶ ካሊድ አደም ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1991 የ16 ዓመት ልጅ ሳሉ ነበር፡፡ አሜሪካ ትኖር የነበረችው አክስታቸው ባመቻቸችላቸው ዕድል አሜሪካ ሄዱ፡፡ በወቅቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የጨረሱበት ወቅት ነበርና የኮሌጅ ትምህርታቸውን እዚያው መከታተል ችለዋል፡፡ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በተለያዩ ሬስቶራንቶችና በኤሌክትሮኒክስ መሸጫ ሱቆች ተቀጥረው ሠርተዋል፡፡ በአንድ የገበያ ማዕከልም በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ የሕክምና ትምህርት (ፕሪ ሜድስን)፣ አካውንቲንግና ማኔጅመንት መማራቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሁንና የጀመሩትን የሕክምና ትምህርት ሳያገባድዱ ነበር ሴት ልጃቸውን ገርዘዋል በሚል ክስ የቀረበባቸውና 15 ዓመታት እስር የተፈረደባቸው፡፡ የአካውንቲንግና የማኔጅመንት ትምህርታቸውን የተከታተሉት በእስር ላይ ሳሉ ነው፡፡ በወቅቱ አቶ ካሊድ የተከሰሱበትና የተሰጠው ፍርድ ኢፍትሃዊ እንደሆነ በመግለፅ እሳቸውን ጨምሮ ብዙዎች ቅሬታቸውን አሰምተው ነበር፡፡ ‹‹ድርጊቱን አልፈፀምኩም፡፡ ወንጀለኛ አይደለሁም፤›› የሚሉትን አቶ ካሊድ ወንጀለኛ አይደለሁም የሚሉበትን ምክንያት፣ በእስር ቤትና በግል ሕይወታቸው ዙሪያ ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- መቼ ነበር ትዳር የያዙት? ባለቤትዎስ የምን አገር ዜጋ ነበሩ?

አቶ ካሊድ፡- ትዳር የያዝኩት እ.ኤ.አ በ1997 ነበር፡፡ እዚያው አሜሪካ ውስጥ በፍርድ ቤት ነበር የተጋባነው፡፡ እዚህም መጥተን ሠርግ ደግሰን ነበር፡፡ በትውልድ ደቡብ አፍሪካ ዜጋ ነች፡፡ ነገር ግን ከተጋባን በኋላ የአሜሪካ ዜግነት አግኝታለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1999 መስከረም ወር ላይም አሚራ ካሊድ የምትባል ልጅ አፍርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ወንጀሉ ተፈፀመ ተብሎ እስር ቤት ከመግባትዎ አስቀድሞ ከባለቤትዎ ጋር የነበርዎት ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ ካሊድ፡- በመካከላችን ከፍተኛ ጥላቻ ያዘለ ንትርክ ነበር፡፡ ችግራችንን በተለያዩ መንገዶች በቤተሰብ ሽምግልና፣ በትዳር አማካሪዎች ለመፍታት ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ ነገር ግን በቀላሉ ሊፈታ አልቻለም፡፡ ጉዳዩ የግድ ፍርድ ቤት መድረስ ነበረበት፡፡ ባለቤቴ በጣም ኃይለኛ ነች፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጋር መገናኘትም ሆነ የኢትጵያውያን ስብሰባ፣ ኮንሰርት ላይ መገኘት አልችልም፡፡ እንዲህ ባሉ ፕሮግራሞች ከተገኘሁኝ ትጣላኛለች፡፡ ኑሮዬ የቤት እስረኛ የመሆን ያህል ሲሆን፣ አብረን መኖር እንደማንችል ተገነዘብኩኝ፡፡ ለዚህም በፍቺ ለመለያየት ወሰንኩ፡፡ ከዚያም እኔም ጠበቃ ቀጥሬ እሷም ቀጥራ በንብረት ክፍፍልና በልጅ ማሳደግ መብት ላይ ክርክር ማድረግ ጀመርን፡፡ የፍርድ ቤቱ ሒደት ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት ሲቀረው ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሰዓት ከሁለት ዓመት በፊት ልጁን ገርዟል እኔ ያየሁት አሁን ነው፡፡ የሚል የሐሰት ክስ አመጣች፡፡ ክሱን አሸነፈች፡፡ ለአሥር ዓመታት ያህልም በእስር እንድቆይ ተደረገ፡፡

ሪፖርተር፡- በእርግጥ ግን ልጅቷ ተገርዛ ነበር?

አቶ ካሊድ፡- የዓቃቢ ሕግ ምስክር ሆነው የቀረቡት ሁለት የሕክምና ባለሙያዎች አዎ ተገርዛለች፣ የተገረዘችውም ልምድ ባለው ሰው በመቀስ ነው ብለው ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ ይህንን የሕክምና ማስረጃ ስላልተቀበልን ጠበቃዬና በሌሎች ኤክስፐርቶች ምርመራ እንዲደረግና ምስክርነት ይሰጥ የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- ውድቅ የተደረገበት ምክንያት ምን ነበር?

አቶ ካሊድ፡- አንድ ተከሳሽ የዓቃቢ ሕጉን ክስ የመፈተን መብት አለው፡፡ እነሱ ያቀረቡት የሕክምና ባለሙያ ማስረጃ አለ እኛም የራሳችንን እናቅርብ የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ዳኛው ልጅቱን በተደጋጋሚ ጊዜ እንድትመረመር ማድረግ የሥነ ልቦና ጫና ያሳድርባታል፡፡ ስለዚህም አንዴ የተደረገው ምርመራ በቂ ነው በማለት ነበር ጥያቄውን ውድቅ ያደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ ልጅቱ ስንት ዓመቷ ነበር?

አቶ ካሊድ፡- ልጅቱ ክሱ ሲነሳ የሦስት ዓመት ከስድስት ወር ልጅ ነበረች፡፡ ተገረዘች የተባለው ግን የ21 ወር ልጅ እያለች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በክስ ሒደቱ ቀርቦብኛል ከሚሉት የሐሰት ማስረጃ ውጪ የፍርድ ሒደቱን ሚዛናዊ እንዳይሆን አድርገዋል የሚሏቸው ሌሎች ነገሮች ነበሩ?

አቶ ካሊድ፡- በጣም ከፍተኛ የሆነ ችግር ነበር፡፡ በመጀመሪያ ጉዳዩ በፍትሐ ብሔር የሚታይ የፍቺ ኬዝ ነበር፡፡ ይህንን የልቦለድ ክስ ስታመጣ ወደ ወንጀል ሄደ፡፡ ከወንጀል ደግሞ አለፈና ነገሩ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው የሴት ልጅ ግርዛት በመሆኑ የፖለቲካ ድባብ ፈጠረ፡፡ የጆርጂያ ሴኔት በዚህ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል፡፡ በልጄ ስም አሚራ አክት የሚል ሕግም አውጥተዋል፡፡ ሕጉም ሙሉ ለሙሉ በተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ፀድቋል፡፡ የሐሰት ክሱን ያነሳችው የቀድሞ ባለቤቴ የክብር እንግዳ ሆና በዚያው ሴኔት ውስጥ ንግግር አድርጋ ነበር፡፡ ኒውዮርክ ውስጥ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የታወቁ ድርጅቶች ሴኔቱን በመርዳት የኔ ክስ በአሜሪካ ታሪክ ትልቅ ምሳሌ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ናይሮቢ ይካሄድ የነበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ስብሰባ ሳይቀር በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እንዲደረግ፣ የአሜሪካ ሚዲያም ሙሉ ለሙሉ ሽፋን እንዲሰጠው አድርገዋል፡፡ የተሰጠው የፖለቲካ ክብደት በቃላት የምገልፀው አይደለም፡፡ ጠበቆቼም ይህንን አንስተው ነበር፡፡ ዳኞችና ዓቃቢ ሕጎችም ሕገ መንግሥታዊ መብቴ እንዳይጠበቅ አድርገዋል፡፡ አንደኛ እኔ ያመጣሁዋቸውን ምስክሮች እንዳይቀርቡ በማድረግ፣ ልጅቱ ዳግም እንድትመረመር ያቀረብኩትን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴት ልጅ ግርዛት በኢትዮጵያ በሚል ከ30 ዓመታት በፊት ያወጣውን ሪፖርት ያለምንም ጥያቄ በመጠቀም ወንጀለኛ ብለውኛል፡፡ ጠበቆቼም እነዚህን ነጥቦች በመጥቀስ ይግባኝ ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን የሚሰማን አጥተናል፡፡

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

ሪፖርተር፡- በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች እርሶን በመደገፍ ቅሬታቸውን ሲገልፁ ነበር፡፡ በዚህ ምን ይሰማዎት ነበር?

አቶ ካሊድ፡- የክሱ ሒደት በተለያዩ ሚዲያዎች በቀጥታ ስርጭት ይታይ ነበር፡፡ አጠቃላይ ሒደቱ አሥር ቀናት የፈጀ ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ በቀጥታ ስርጭት ለሕዝቡ ይተላለፍ ነበር፡፡ በአትላንታ፣ በዋሽንግተን፣ በሎሳንጀለስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ነገሩን በመቃወም፣ ወንድ ሴትን አይገርዝም በታሪክም የሚታወቅ አይደለም አውቃችሁ እስር ቤት ልትከቱት ብላችሁ እንጂ ይህ በፍፁም የማይሆን ነው በማለት ተቃውሟቸውን ሲገልፁ ነበር፡፡ ጉዳዩን የሰሙ በአዲስ አበባ የሚኖሩ 2000 ሰዎችም ሠልፍ ወጥተው ነበር፡፡ በአትላንታ የሚኖሩም ገንዘብ በመሰብሰብ ሊረዱኝ ጥረት አድርገዋል፡፡ ከአቅማቸው በላይ ሲሆንም ሼሕ መሐመድ ዓሊ አልአሙዲ እንዲረዷቸው በመጠየቅ፣ በአሜሪካ ታዋቂ የሆኑ ሦስት ጠበቆችን ቀጥረው ከእስር እንድፈታ ሐቁ እንዲታወቅ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በመግረዝ ወንጀል ተከሰው ከመታሰርዎ በፊት ለሴት ልጅ ግርዛት የነበርዎት አመለካከት ምን ይመስላል?

አቶ ካሊድ፡- ግርዛት ሲካሄድ በዓይኔ አይቼ እንኳን አላውቅም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አውርቼም አላውቅም፡፡ ስሄድም ልጅ ነበርኩኝ፡፡ ብዙ የማውቀው ነገር አልነበረኝም፡፡ በየመገናኛ ብዙሃን እሰማ የነበረውም የሴት ልጅ ግርዛት መቅረት ያለበት ጎጂ ልማድ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ መከሰሴ በጣም ነበር ያስደነገጠኝ፡፡ ራስህ በመቀስ ነው የገረዝካት ብለው ነው የከሰሱኝ፡፡ ሌላም ነጭ ሰው እግር በመያዝ እንደተባበረኝ በክሳቸው ጠቅሰዋል፡፡ በሕይወቴ አስቤው በማላውቀው ጉዳይ ተከስሼ መገናኛ ብዙሀን ፊት ሲያቆሙኝ ቅዠት ነበር የመሰለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ተባባሪ ነበር የተባለው ነጭስ ከእርስዎ ጋር ተከሶ ነበር?

አቶ ካሊድ፡- ተባባሪ የተባለው ሰው ልብ ወለድ ነው፡፡ ስሙንም አያውቁትም፡፡ ጠበቆቼ ሲጠይቁ የነበሩት ነገርም ይህንኑ ነበር፡፡ የታለ? ካሊድን ረድቼዋለሁ ልጁ ስትገረዝ እግሯን ይዤለታለሁ ብሎ ለምን አይናገርም? እናትስ ድርጊቱ ሲፈፀም የት ነበረች? ልጅቱስ አትቆስልም አትደማም ወይ? ሁለት ዓመት ድረስ የት ነበረች? በማለት ጠይቀዋል፡፡ የሚሰማ ግን  አላገኘንም፡፡ ክሱንም ልዩ የሚያደርገው ይኼ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞ ባለቤትዎ ደቡብ አፍሪካዊ ሆና ሳለ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚከናወነው የሴት ልጅ ግርዛት ምን ያህል ግንዛቤው ቢኖራት ነው ሕፃን ልጁን ገረዘ ብላ ክስ የመሠረተችው? ወይስ በጉዳዩ ትወያዩ ነበር?

አቶ ካሊድ፡– ይሄ ጥያቄ ፍርድ ቤት ውስጥ ተነስቶ ብዙ ያወያየና ያከራከረ ነበር፡፡ እሷ የደቡብ አፍሪክ ተወላጅ ነች፡፡ እናቷ ደግሞ የሕፃናት ነርስ ነች፡፡ ወደ አሜሪካ ከመምጣቷ በፊት በሕክምና ለአሥር ዓመታት ያህል ሠርታለች፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሴት ልጅ ግርዛት መኖሩንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርትም ያሳያል፡፡ ስለዚህም የባለቤቴ እናት ችሎታው ሊኖራት እንደሚችል ነው የተገነዘብነው፡፡ ከዚህም ሌላ ክሱ ከመምጣቱ ሁለት ዓመታት በፊት ባለቤቴ በኢንተርኔት ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴት ልጅ ግርዛት ሪፖርት፣ በአትላንታና በተባበሩት መንግሥታት የሚገኙ የሴት ልጅ ግርዛት ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎችን፣ ስለ ግርዛት ማወቅ እፈልጋለሁ፣ በየትኛው አገር ይካሄዳል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በምን ያህል መጠን ይፈፀማል፣ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት የሴት ልጅ ግርዛት ላይ የሚሠራ ድርጅት ማቋቋም እፈልጋለሁ በሚል ሰበብ ስትጠይቅ እንደነበር መረጃዎች ተገኝተውባታል፡፡ ክሱ ላይ ሕፃኗ የ21 ወራት ልጅ ሳለች መገረዟን ነው የሚያሳየው፡፡ እናትየው ስለግርዛት መረጃ ማሰባሰብ የጀመረችው ግን ልጅቱ ገና የስምንት ወር ሕፃን ሳለች ነበር፡፡ ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው ቀደም ብላ እየተዘጋጀች ስለመሆኑ ወንጀሉንም በራሷ መፈፀሟን ነው ብለው ጠበቆቼ ተከራክረዋል፡፡ እሷንም አሳምነዋታል፡፡

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ሪፖርተር፡- እንደሚናገሩት ከሆነ ወንጀሉን ላለመፈፀምዎ ብዙ ማስረጃዎች አለዎት፡፡ እንደዚህም ሆኖ ግን ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደው በእርስዎ ላይ ነው፡፡ ባለቤትዎ ኬዙን እንድታሸንፍ ያደረጋት ምንድነው?

አቶ ካሊድ፡- ኬዙ በአሜሪካ እንግዳ የሆነና የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ግርዛት የሴቶችን መብት መጣስና በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እሷ ይህንን ክስ ስታመጣ በዓይን አይተውት የማያውቁትን ነገር በቀጥታ እንደመመልከት ነበር፡፡ እነሱም እንደ ምልክት ተጠቀሙበት፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ እጆች ተዘረጋጉ፡፡ የወንጀል ህጉም ወጣ፡፡ ሴናተሮቹም ተሰበሰቡ፡፡ ይህ ሥራቸው ነው፡፡ እሷን ለመርዳት ብለው ያደረጉት  አይደልም፡፡ ለዓለም ማሳየት የሚፈልጉት ነገር ስለነበር ነው፡፡ እሷ ግን ይህን ተረድታው ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡– እነዚህ ሁሉ መከላከያዎች ቢኖርዎትም በመጨረሻ ጥፋተኛ ተብለው 15 ዓመታት እስር ተፈርዶቦታል፡፡ በዚያ ቅፅበት ምን ተሰማዎት?

አቶ ካሊድ፡- ከፍተኛ ድካም ነበረብኝ፡፡ አንደኛ ለአሥር ቀናት ያህል እንቅልፍ አልተኛሁም፡፡ ስለእኔ የሚዘገበውን በሚዲያ አያለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያንም ቤት መተው አይዞህ እያሉ ያፅናኑኛል፡፡ የፍርዱ ቀን ጥፋተኛ ነህ ስባል ቤተሰቦቼና ሌሎች ሲያፅናኑኝ የከረሙ ኢትዮጵያውያን ፍርድ ቤቱ ውስጥ ሲጮሁ፣ ሲወድቁ ነበር፡፡ ቅዠት የሚመስል ስሜት ውስጥ ሆኜ አብሬያቸው እጮህ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እስር ቤት የተለያዩ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም በምዕራቡ ዓለም አዲስ እስረኞችን የማሰቃየት የመደብደብ ነገር እንዳለ በተለያዩ ፊልሞችም እናያለን፡፡ እርስዎ በመጀመሪያዎቹ የእስር ጊዜያት ምን ምን ዓይነት ነገር አጋጥሞታል?

አቶ ካሊድ፡- በአሜሪካ እስር ቤት እያንዳንዱ ቀን ከባድ ነው፡፡ በተለይም የመጀመሪያዎቹ ሳምንታትና ወራት በጣም ከብደውኝ ነበር፡፡ መጀመሪያ ከየትኛውም እስረኛ ጋር እንዳልገናኝ ለብቻዬ በጣም ቀዝቃዛ በሆነ ክፍል ውስጥ ነበር የታሰርኩት፡፡ ከዚያ አውጥተው ደግሞ ሜዲካል ዩኒት በሚባል ክፍል በአራት ነርሶች እየታየሁ እንድቆይ ተደረኩኝ፡፡ እነዛ ነገሮች ትልቅ የሥነ ልቦና ጫናና ጭንቀት አሳድረውብኛል፡፡ በኋላም ወደ ጀነራል ፖፑሌሽን ስወሰድ አይቼውና አስቤው የማላውቀው ሁኔታ ነበር የገጠመኝ፡፡ ለሕይወት አደጋ ከሚሆኑ ብዙ ወንጀል ፈፅመው ከታሰሩ ሰዎች ጋር መደባለቄ ትልቅ ፍራቻ አሳድሮብኝ ነበር፡፡ የነበረው ድብድብ፣ ግድያ በእኔ ላይ ባይደርስብኝም ማየቱ ከባድ ነበር፡፡ እንዲህ ካሉ ችግሮች ራሴን ለመጠበቅ ከክፍሌ ሳልወጣ ሳምንታት ለመቀመጥ የምገደድበት ሁኔታ በአዕምሮዬ ላይ ትልቅ ጭንቀት አሳድሮብኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- መቼም ብዙ የማይረሳዎት የእስር ቤት ገጠመኞች ይኖርዎታል፡፡ የሚያስታውሱትን ቢነግሩን፡፡

አቶ ካሊድ፡- በጣም በጣም የማይረሳኝ በአዳራሽ ውስጥ ቴሌቪዥን እያየን የሆነውን ነገር ነው፡፡ በአዳራሹ ውስጥ ሁለት ቴሌቪዥኖች አሉ፡፡ አንዱ የስፖርት ፕሮግራም መመልከቻ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ለዜናና ለተለያዩ ፕሮግራሞች የተመደበ ነው፡፡ በሁለት እስረኞች መካከል የቲቪውን ቻናል በመለወጥ አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ አንደኛው መፀዳጃ ቤት ደርሶ እስኪመለስ ድረስ ሌላኛው ዜና ለማየት ቻናሉን ቀይሮ ጠበቀው፡፡ ከዚያም ብዙ ቁልፎች በካልሲ ውስጥ ከቶ ቻናሉን የቀየረበትን እስረኛ በሚዘገንን ሁኔታ ጭንቅላቱ ላይ ደጋግሞ ይመታው ጀመረ፡፡ ልጁም ወድቆ ከጭንቅላቱ ደም መፍሰስ ጀመረ፡፡ ከዚያም ፖሊሶች እየተሯሯጡ በመምጣት አስለቃሽ ጭስ ወረወሩብን፡፡ እኛም በያለንበት ወደቅን፡፡ እንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡-  ብዙ ጊዜ በረብሻ ስማቸው የሚነሳው የጥቁሮች ነው፡፡ በቆይታዎ ይህ ጉዳይ እውነት መሆኑን አይተዋል?

አቶ ካሊድ፡- እስር ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ለሁከትና ለረባሻ ቅርብ ናቸው፡፡ በግድያ፣ በድብድብ፣ በስርቆት ነው የሚከሰሱት፡፡ ጥቁር ነጭ ሳይል ሁሉም ለሁከት ቅርብ ነው፡፡ ነገር ግን በእስር ቤት ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ እስረኞች ጥቁሮች ናቸው፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ጋንጎች አሉ፡፡ እኔ በነበርኩበት እስር ቤት ጂዲ፣ ብለድ፣ ክሪፕስ፣ ጎስት ፌስ ሌሎች ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ በቡድን ሆነው የሚደባደቡ ናቸው፡፡ ጥቁሮቹ ግን ብዛት ስላላቸው ጎልተው ይታያሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ድብድቡ በጋንጎች መካከል ይሆንና ጠቅላላ እስር ቤቱ ለሳምንትና ለሁለት ሳምንት ዝግ ይሆናል፡፡ ከክፍላችን እንዳንወጣ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአንዱ ቡድን አባል ያልሆነ ሰው የሚከላከልለት ወገን ስለማይኖረው ለብዙ ነገሮች ተጋላጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ራስዎን ከአደጋ ለመከላከል የአንደኛው ቡድን አባል ለመሆን አልሞከሩም?

አቶ ካሊድ፡- ከየትኛውም ቡድን ጋር አልተቀላቀልኩም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ባህሪም የለኝም፡፡ ነገር ግን በእስር ቤት ውስጥ በተለያዩ ሥራዎች በመሰማራት አገለግላለሁ፡፡ መጀመሪያ በፋብሪካ ውስጥ ሠራሁ፣ ቀጥሎ የሃይስኩል ተማሪዎችን ማስተማር ጀመርኩ፡፡ አብዛኛዎቹ የጋንግ መሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያልጨረሱ በመሆናቸው አስተምራቸዋለሁ፡፡ ይህም ከሁሉም ጋር ያለኝ ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን፣ እንዲያከብሩኝ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያዊ ወንድማችን ይሉኝ ነበር፡፡ በሌላ በኩልም ጥቁር ሙስሊሞች አይዞህ ማንም አይነካህም ይሉኝ ነበር፡፡

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

ሪፖርተር፡- በእስር ቤት ውስጥ ከእርስዎ ውጪ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እስረኞች ነበሩ?

አቶ ካሊድ፡- አሥር ዓመታት ስታሰር ሦስት ኢትዮጵያውያንን አግኝቻለሁ፡፡ አንደኛው ለሦስት ወራት ያህል እኔ ባለሁበት እስር ቤት ታስሮ ነበር፡፡ ሌላኛው ግን ለአንድ ዓመት ያህል አብሮኝ ቆይቶ ነበር፡፡ ስንገናኝ በጣም ነበር ደስ ያለው፡፡ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ አብረን እናሳልፋለን፡፡ በተለይ ከማደሪያችን ወጥተን ንፋስ ለመቀበል በሚፈቀድልን አንድ ሰዓት አብረን ቁጭ ብለን ስለአገራችንና ስለተለያዩ ጉዳዮች እናወራለን፡፡ ይህም ሁለታችንም ያለንበትን ዘግናኝ የእስር ቤት ሕይወት በመጠኑም ቢሆን እንድንረሳ አድርጎናል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን እነዛ አሰቃቂ የእስር ጊዜያት አልፈዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ ይፈልጋሉ?

አቶ ካሊድ፡- የኔ ፍላጎት ብዙ ነው፡፡ የመጀመሪያው ፍትሕ ማግኘት ነበር፡፡ የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ግን ይህን ሊሰጡኝ አልቻሉም፡፡ ፍርዱም ስሜን ያጠፋ፣ ባልሠራሁት ወንጀል ወንጀለኛ ያስባለኝ፣ የኢትዮጵያን ስምም ጥላሸት የቀባ ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል የተለያዩ ጥረቶች አደርጋለሁ፣ በማድረግም ላይ ነኝ፡፡ በአሜሪካም በኢትዮጵያም መገናኛ ብዙሃን ወንጀለኛ አለመሆኔን ተናግሬአለሁ፣ እየተናገርኩም ነው፡፡ ወደ አገሬ ስገባም በአሜሪካ የነበሩ ግለሰቦች ለምን ዝም ትላለህ የደረሰብህን ስቃይ ለምን አትናገርም? ወንጀለኛ አለመሆንህንም  አሳውቀህ ለምን ስምህን አታጠራም? ብለውኝ ነበር፡፡ እኔም ከመገናኛ ብዙሃን ውጪ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ተገኝቼ ወንጀሉን አለመፈፀሜን ገልጫለሁ፡፡ ነገር ግን አድርጓል አላደረገም የሚል በሁለት ጎራ የተከፈለ ክርክር አለ፡፡ እነዛ ቡድኖችም በሚቀጥሉት አምስት ወራት ስብሰባ እንደሚያዘጋጁና እኔንም እንደሚጋብዙኝ ነግረውኛል፡፡ እነዚህ ነገሮች ፍትህ ባላገኝ እንኳ ቢያንስ እውነትን ለማውጣት ይረዱኛል፡፡ የደረሰብኝን እኔ ካልተናገርኩ፣ ካልጮህኩ ማንም ሊጮህልኝ አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡– ከቀድሞ ባለቤትዎ ጋር ከዚያ በኋላ ተገናኝታችሁ ታውቃላችሁ?

አቶ ካሊድ፡- በፍፁም፡፡ በፍቺ ሒደቱ ብዙ ትዝት ነበር፡፡ አሳይሃለው፣ እኔን የተዋወክበትን ቀን እንድትጠላ አደርጋለሁ፣ ሕይወትህን እንዳልነበር አደርጋለሁ፣ ልጅህን ለዘላለሙ እንዳታይ አደርግሃለው ትለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲህ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ከተፈጠረ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ልጅዎም ራሷን የምታውቅበት የዕድሜ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ መገረዝ አለመገረዟን ማወቁ ብዙ ላይከብዳት ይችላል፡፡ በትክክል የተባለው ግርዛት ካልተፈፀመባት በቀር አባቴ በሐሰት ነው የተከሰሰው ማለቷ አይቀርም፡፡ እንዲህ ያለ ሙከራ አድርጋ ታውቃለች? ትገናኛላችሁስ?

አቶ ካሊድ፡- በተነሳው ክስ መሠረት ሁለት ነገር ነው የተደረገው፡፡ አንደኛ ልጄን ለዘላለሙ እንዳላያት ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡ በልጅህ ላይ የጭካኔ ድርጊት በመፈፀም፣ የአካል ጉድለት በማድረስ ብለው ሁለት ክሶች ነበር የተመሰረቱብኝ፡፡ በዚህም ለ40 ዓመታት የምታሰርበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ዳኛው ማቅለያ በማድረግ አሥር ዓመት በእስር፣ አምስት ዓመት የቁም እስር ተፈረደብኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ልጄን እንዳላይ ተደርጓል፡፡ ልጄ በአሁኑ ወቅት በኔ ላይ የደረሰውን ነገር ማገናዘብ ትችላለች ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አጠቃላይ የታሰሩት አሥር ዓመት ነው፡፡ ነገር ግን የ15 ዓመታት እስር እንደተፈረደብዎ  ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ አምስት ዓመቱን በአመክሮ ተቀንሶ ነው በአሥር ዓመት ብቻ የተለቀቁት?

አቶ ካሊድ፡- ዳኛው የ15 ዓመት እስር ነው የፈረዱብኝ፡፡ ነገር ግን የእስሩ ሁኔታ 10 አመት በእስር ቤት፣ አምስት ዓመት ደግሞ በአሜሪካ የምኖር ከሆነ በቁም እስር እንዳሳልፍ ነበር የተወሰነው፡፡ እኔ አሥር ዓመቱን ከጨረስኩ በኋላ የውጪ ዜጋ በመሆኔ በገዛ ፈቃዴ ወደ አገሬ እንድመለስ ለኢሚግሬሽን ጥያቄ አቀረብኩኝ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ እነሱም ከአገር እንድባረር ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ እኔም የምፈልገው ከአገር መባረር ነው ብዬ በአምስት የኢሚግሬሽን ፖሊሶች ታጅቤ ከሦስት ወር ተኩል በፊት አዲስ አበባ ገብቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– አዲስ አበባ ከገቡ ምን እየሠሩ ይገኛሉ?

አቶ ካሊድ፡- ይህንን ሀቅና እውነት ለሕዝቡ ለማድረስ ፍትሕ ያጣ እንባ የሚል መጽሐፍ አዘጋጅቻለሁ፡፡ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማትም ጉዳዩን አስመልክቶ ቃለ መጠይቅ እየሰጠሁ ነው፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥም ወደ ሥራው ዓለም ለመግባት እየተዘጋጀሁ ነው፡፡

www.ethiopianreporter.com

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *