ወርቃየሁ ቸኮለ

Image result for ashendaበእርግጥ ዛሬ ዛሬ በሙታኑም ሆነ በህያዋኑ የታሪክ ምሁራን እና ቁንጮ ፖለቲከኞቻችን የታሪክ ሽሚያው አይሎ ቀጥሏል:: የአንዱ አከባቢ መገለጫ የሆነውን ባህላዊ ክዋኔ ወደ ሌላኛው አከባቢ ወስዶ ለዛ ማህበረሰብ እውቅና መስጠት እየተለመደ መጥቷል:: በዚህም ሳቢያ የማህበረሰቡ መገለጫ የሆኑ ቱባ ባህሎች በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጡንቻ ባላቸው ቡድኖች እየተነጠቁ ይገኛሉ:: ከነዚህም አንዱ ሻደይ ባህላዊ ጨዋታ ነው:: በእርግጥ ታሪክን ወጥ አድርጎ ፈር ማስያዝ አይቻልም::
ዳሩ ግን የጋራ የሆነ፣ ቅቡልነት ያለው የጋራ ታሪክ ማበጀት ይቻላል:: ነባራዊ እውነታው ግን ከዚህ ባሻገር ነው:: ነገረ ሻደይም እጣ ፈንታው ይሄው ሆኗል:: ብቻ የሻደይ እምብርት ዋግና አከባቢው ነው:: ለዚህም ማሳያው ሻደይ በድምቀት የሚከበረው በዋግ፣ ከትግራይ ደግሞ በተንቤን አብይ አዲ፣(ከዛ ውጭ ባሉት በትግራይ አከባቢዎች ሻደይ እየተለመደ የመጣው በቅርቡ ነው፤ እሱም ቢሆን በጠንካራ ኢንዶክትሪኔሽን ስራ ነው::) በአማራው ደግሞ በላስታ ላል-ይበላና ራያ ቆቦ አከባቢ ብቻ ነው

የሻደይ በአል በተለያዩ አከባቢዎች በተለያየ የአከዋወን ስልትና ቅኝት የሚከወን ባህላዊ ቅርስ ሲሆን በአሉ በተለይ በዋግ ኽምራ ብሄረ ሰብ አስተዳደር ከመንደር ጀምሮ በከፍተኛ ድምቀት ይከበራል:: “በዓሉ መነሻው ሃይማኖታዊ ስርአት ሲሆን መቼ እንደተጀመረ በግልፅ ባይታወቅም በአከባቢው የክርስትና እምነት ከተስፋፋበት ጊዜ ጀምሮ ሊሆን እንደሚችል ቀደምት አባቶች/ በአፈ ታሪክ/ ይገልፃሉ፤ የታሪክ ሊቃውንት ደግሞ በእርገተ በአል/ በድንግል ማርያም እርገት/ ከሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ መከበርመጀመሩን ያትታሉ::” (ሻደይ መጽሔት 2003 ዓ.ም በአበራ ይግዛው)
በሌላ መልኩ ስለሻደይ በአል አጀማመር“መጽሐፈ ሱባኤ” የተሰኘውን የብራና ጽሁፍ ጠቅሰው የሚጽፉት መራሪስ አማን በላይ ”ዣን ሸዋ ቀዳማዊ“ በተባለው መጽሓፋቸው ላይ ሲጠቅሱ “ የሻደይ ብአል የሚከበረው ኖህ እና ቤተሰቡ ከጥፋት ውሃ በኋላ (ማለትም የዛሬ 5,744 አመታት ገደማ) ደረቅ በነበረው መሬት አረጓዴ እፅዋት መመልከት የጀመሩበትን እለት ለመዘከር ነው” ብለው ያትታሉ:: እንደዚህ መረጃ ከሆነ የሻደይ ብአል ከአባታቸው ኖህ ተቀብለው ማክበር የጀመሩት እና የቀጠሉት የኩሽ ልጆች ብቻ ነበሩ ብለን እንድናምን ያስገድዳል:: በሌላ መልኩ ደግሞ የታሪክ፣ የስነ ልሳን፣ የሰው ዘር ጥናቶች እና ልማዳዊ አተራረከ ሳይቀር የአገው ህዝብ የኩሻውያን ሁሉ በኽር እንደሆነ እኩል ያስረዳሉ::”
ይህ እውነታ ደግሞ ብአሉ መቼ መከበር እንደተጀመረ ብቻ ሳይሆን የሻደይ ብአልን የኩሽ ነገድ የሆኑ የአገው ህዝቦች ጠብቀው ማቆየት መቻላቸውንም የሚጠቁም እውነታ ሁኖ እናገኘዋለን:: ሻደይ ከፍልሰታ ፍች(ከንሃሴ 16) ጀምሮ ለተከታታይ ከ3-6 ቀናት የሚከወን ነው:: በገጠሩ አከባቢ ደግሞ ከዋዜማው (ከነሃሴ 15) ጀምሮ ይከበራል:: የሻደይ ባህላዊ ጨዋታ ስያሜ የተወሰደው ሻደይ በተባለው በክረምት ወራት ብቻ ከሚበቅል የኮባ ወይም የሙዝ ቅጠል ትልትል የሚመስል ሲነቅሉት ስሩ ነጭ ከሆነ የሳር ዝርያ ነው::
ሻደይ በዋግ ምድር ለሴቶች የነጻነት ቀን ነው:: ምክንያቱም የኽምራ ልጃገረዶች አምረውና ደምቀው፣ ያለ ምንም የእድሜ ልዩነት እና አስገዳጅነት፣ በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ሆኖ የመጫወት የሙሉ መብት ባለቤት ናቸውና:: የሻደይ ጨዋታ ከሌሎች ባህላዊ ጨዋታዎች ለየት የሚያደርገው የሴቶች ጨዋታ ብቻ በመሆኑ ነው:: ልጃገረዶቹ በዚህ ባህላዊ ጨዋታ ጊዜ አካላዊ እንቅስቃሴቸውን፣ ለባህሉ ያላቸውን ወኔ፣ የጨዋታ ልምዳቸውን፣ ክህሎታቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ተሰጥኦቸውንና አመለካከታቸውን በብቃት የሚያሳዩበት ባህላዊ ክዋኔ ነው::
ጨዋታው የራሱ የሆነ ስርአት እና አጨዋወት ስላለው እነዚህን ጠንቅቆ ማወቅ ግድ ነው:: ሻደይ ጨዋታ ብቻም አይደለም ከቸዋታነቱ ባሻገር በልጃገረዶቹ ማህበራዊ ህይወት፣ ነጻነትና ስነ ልቦና ላይ የራሱ የሆነ አንድምታ አለው:: ከቤት መውጣት የማይፈቀድላቸው ልጃገረዶች በሻደይ ወቅት ማንም የት ነሽ ወዴት ነሽ ብሎ የሚጠይቃት የለም፤ነፃነቷን ታውጃለች::
ታዲያ በዚህ ሳምንት ውስጥ ከአዳዲስ ሰዎች ጋር የመተዋወቅ እና ለጎረምሶች የመታየት አድሉን ስለሚፈጥርላት ለወደፊቱ ማህበራዊ ኑሮዋ ላይም መሰረት የምትጥልበት ጨዋታ ነው ሻደይ:: ወንዶችም ቢሆኑ ይህንን ብአል በጉጉት ይጠብቁታል:: ምክንያቱ ደግሞ ልጃገረዷ አምራና ተውባ የሻደይ ቅጠሏን ዳሌዋ ላይ ጣል አርጋ ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ በሪትም ስትውረገረግ ሲያይ ልቡ የማይመታ ጎረምሳ ከቶ የለም:: ልቡ ከመምታትም አልፎ የከጀላት ወዳጅ ለማድረግ በልቡ እያሰበ በጨዋታ በሃል ሰረቅ እያደረገ በፍቅር አይን እያየምን ባደርግ ይሻላል እያለ ያስባል፤ይብሰከሰካል::
ጨዋታው በደስታ፣ በፍቅር፣ በውበት፣ እና በነፃነት ይታጀባል:: ስለ ታሪካዊ አመጣጡ፣ ሰፊ ትዕይንተ ምስል ስለ ሚጭረው የጨዋታ ሂደቱ እና ስያሜው ይህን ካልኩ ስለሚሻው ቅድመ ዝግጅት ደግሞ ትንሽ ልበል:: ይኸውም ለበአሉ የሚለብሷቸው አልባሳት እና ጌጣጌጦችን ማዘጋጀትና ቡድኑ አባላት መመልመል፣… ቡድኑ በተለያዩ እድሜ ክልሎች በየእድሜ አቻቸው ህፃናት፣ ወጣቶችና እናቶችን በመለየት የሚደራጁ ሲሆን የአንድ ቡድን አባላት መጠን የተወሰነ ባይሆንም በአማካይ ከ10-20 አባላትን የሚያካትት ነው::
የሻደይ ተጫዋቾጭ ቡድን በእድሜ ደረጃ የተለያየ ቢሆንም ቅሉ በተለየ መስፈርት ግን ሃብት፣ ስልጣንና ዘርን መሰረት ያደረገ አይደለም:: በአንጻሩ ግን ሁሉም በእኩልነት ደስታቸውን የሚገልጹበት ባህላዊ ጨዋታ ነው:: ሌላው በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ላይ ተጨዋቾች የሚያደርጉት ክዋኔ ቢኖር እንደየ እድሜ ክልላቸው በተለያየ የጸጉር አሰራር ለጨዋታው ደምቆ መዘጋጀት ነው:: ሻደይ ጨዋታ ኮረዳዋ አምራና ደምቃ የምትታይበት ወቅት በመሆኑና ከባህሉ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው በመሆኑ ያላት የራሷ የሌላት ደግሞ በመዋዋስ ባህላዊ ቀሚስ፣ ኩል፣ ድሪ፣ አልቦ፣ ድኮት፣ መስቀልና የመሳሰሉትን ሲያዘጋጁ በጸጉር አሰራር ደግሞ ግልቭጭ፣ ጋሜና ቁንጮ፣ አልባሶ፣ ድፍን፣ ሳዱላ ፣… በሚባሉ የጸጉር አሰራር አይነቶች ስትዋብ ትሰነብታለች:: ይህ ሳምንት በኽምራዎች ምድር ልዩ ድባብን ይጭራል:: የበአሉ ዋዜማ ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ጫካ በመሄድ የሻደይ ቅጠል ይዘው ይመጣሉ።
በማስከተልም ልክ ሊሆን የሚችል ማሰሪያ በማዘጋጀት ያመጡትን የሻደይ ቅጠል ባዘጋጁት ማሰሪያ ላይ በባህላዊ አስተሳሰሩ ውበት እንዲሰጥ አድርገው ካሰሩት በኋላ አንዳይጠወልግ ጤዛ ውስጥ ያሳድሩታል:: በበአሉ እለት ጠዋት በባህላዊ ልብሳቸው፣ በጌጣጌጣቸው እንዲሁም በጸጉር አሰራራቸው አምረውና ደምቀው ጤዛ ውስጥ ያሳደሩትን የሻደይ ቅጠል ወገባቸው ላይ አስረው ከየቤታቸው ይወጡና በመሰብሰብ አለቃ ይመርጣሉ::
አለቃዋ ሁለት ነገሮችን በዋናነት ታከናውናለች:: ይኸውም የቡድኑ ገንዘብ ያዥ መሆንና ቡድኑን በበላይነት መምራት ሲሆን አለቃዋ ስትመረጥ እድሜ፣ ታማኝነት፣ ውበትና የጨዋታ ችሎታን መሰረት በማድረግ ነው:: ጨዋታው እስኪያልቅ ድረስም የቡድኑ መሰብሰቢያ የአለቃዋ ቤት ይሆናል:: የሻደይ ተጫዋቾች ቀጣይ ተግባር ጨዋታውን መጀመር ነው:: ጨዋታው የሚጀምረው በአከባቢው በሚገኝ ደብር ወይም ቤተ-ክርስትያን በመሆኑ የሻደይ አበባ በመያዝ እንዲህ እያዜሙ እና እያሸበሸቩ ወደ ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ::
እሻደይ አበባ ሻደይ
ሻደይ ነሽ አሉ በያገሩ
ወለባ ወለባ አንቺ ያይኔ አበባ
አበባየ ነሽ አበባየ
ካፋፉ ዘልቀሽ እልል በይ
ከቤተ-ክርስትያን ግቢ ከመግባታቸው በፊት ደግሞ …
አስገባኝ በረኛ —የጌታየ እረኛ(2)
አስገባኝ ከልካይ(2)—እመቤቴን ላይ፤ እያሉ ያዜማሉ::
ወደ ቤተ-ክርስትያን ግቢ ዘልቀው ከገቡ በኋላም

አሽከር አበባየ አሽከር አበባየ
ካላጉረመረመ አይበላም ነብር
ቅዱስ ሚካኤል ትልቁ ደብር
(የየደብራቸውን ታቦት እየጠሩ)
አሽከር ይሙት ይሙት አሽከር አበባ
ይላሉ የኔታ አሽከር አበባ
አሽከር አይደለም ወይ አሽከር አበባ
የሚሆነው ጌታ አሽር አበባ
ውብ አሽከር አበባ እሆ አበባየ
አቨቫየ አንቺ አበባ

በማለት የአከባቢውን ታቦት በማወደስ ይዘው ከገቡት ሻደይ አበባ በመጣል ከግቢው ወጥተው የመንገድ ዜማ እያዜሙ፣ እየጨፈሩ ወደ አገረ ገዡ (የሃገር ሽማግሌዎች) በመሄድ የፍቃድ መጠየቂያ ዜማቸውን እያዜሙ ያወድሳሉ::

አስገባኝ በረኛ — የጌታየ ዳኛ
አስገባኝ ከልካይ — እመቤቴን ላይ::

እያሉ በድምቀት ሲጨፍሩ የሻደይ ተጫዋቾችን መመለስ በባህሉ ነውር ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ በበረኛው(በአገልጋዩ) እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል:: ተጨዋቾችም …

ይኸ ጓሮ የማነው ጓሮ
የመቤቴ የሴት ወይዜሮ
ይኽ አደራሽ የማን አደራሽ
የጌታየ የድርብ ለባሽ
ተቀምጠዋል ዙፋኑ ላይ
ያበራሉ እንደ ፀሃይ …

ተጫዋቾቹ በዚህ ጊዜ ወደ ላይ በመዝለልና በማጨብጨብ ደመቅ ባለ ሁኔታ ይጫወታሉ:: በመቀጠልም አቀንቃኟ የሚከተሉትን መንታ ቃል ግጥሞች ትደረድራለች:: (ዶ/ር አፀደ ተፈራ 2000 ዓ.ም)

አሽከሮችሽሳ ደንገጡሮችስ
ሲያበራ ያመሻል እሜቴ ጥርስሽ
አንድ ገንቦ ጠላ እቤቴ አጣሁኝ
እኔስ ከጌታየ ብር ብየ መጣሁኝ
እሰይ የኔ እመቤት አመልማሎ ፈታይ
ዋሽቼም እንደሆን አገልጋይሽ ይታይ
ይኸው እዛ ማዶ ነብር ይጓጉራል
እሰይ የኔ ጌታ ገድሎ ይፎክራል::

በዚህ ወቅት የሚዜምላቸው ሰዎች በተለይ ሴቷ ተነስታ በደስታ እልል ማለት ይኖርባታል:: ይህ ካልሆነ ግን የቡድኑ አባላት ቅሬታ ይሰማቸውና ቅሬታቸውን በዚህ መልኩ ያንጎረጉራሉ …

አንችን አደለም ወይ የማወድሰው
ቀና ብለሽ እዪኝ የሰው ጡር አለው
ደግሞም በምትወጃት በእከሊት ሞት
ሳቂልኝ አባክሽ ተጨንቄ አልሙት
አኩርፈሽ ነው ወይ አንችን በማለቴ
የነ እከሊት እናት ሰላም እመቤቴ …

በማለት ያዜማሉ:: ይህን ጊዜ ታድያ ተወዳሾቹ የቡድኑ ቅር መሰኘት ይገባቸውና ያላቸውን ገንዘብ ሊሰጧቸው ሲዘጋጁ ቡድኑ በርከት ያለ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ለማግባባት …

ሰው ሁሉ ሲሰጠን አንድ ብር ነው
እሰይ የኔ ጌታ እጁ እንደ ሞላ ነው
ከነ እከሌ ደጃፍ ወድቄ ብነሳ
የሰራ አካላቴ ወርቅ ይዞ ተነሳ …

በማለት ያዜማሉ:: ግለሰቡም የአቅሙን ገንዘብ ይሰጣቸዋል:: ተጫዋቾችም ገንዘቡን እንደተቀበሉ የመጨረሻውን የእስክስታ ዜማ ያቀርባሉ

አስታ ሊለየ ለየ ስለሊለየ
አንች የኔ እመቤት አመልማሎ ፈታይ
ሃሰትም እንደሆን አገልግልሽ ይታይ
ቀጭን ኩታ ለብሶ ሲሄድ በአቀበት
ይኸ የኔ ጌታ ይመስላል ታቦት 

እንዲህ እንዳላችሁ እንዲህ እንደለን
ከርሞ ይኽን ጊዜ ደህና ያቆየን …

በማለት ካዜሙ በኋላ እስክስታ ሲመቱ ተመልካቾቹ …

ያረፈ የርጎ ሌባ
ቂጥ ቂጡን በገለባ
ወገብሽ በምን ሰላ
ነጭ ጤፍ እየበላ…

በማለት በእልልታና በከፍተኛ ጭብጨባ የደመቀ ጨዋታ በመጫወት ለከርሞ እንዲያደርሳቸው አምላካቸውን በመጠየቅ መርቀው ይወጣሉ:: በጨዋታው ሂደትም ጌታን ከሎሌ፤ እመቤትን ከአሽከር ሳይለዩ ሁሉንም ሲያወድሱ ከዋሉ በኋላ አመሻሽ ላይ የተለያዩ የሰፈር ቡድኖች አንድ ላይ በመሆን ይጎሻሸማሉ:: የሻደይ ተጨዋቾች በጨዋታ ወቅት ምሳ መብላት ትዝ አይላቸውም:: ሲጫወቱ ውለውና ሲጎሻሸሙ አምሽተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የሌላ ቡድን ተጫዋቾችን መንገድ ላይ ቢያገኙ ሰድበሽኛል ብለው ምንም አይነት ትንኮሳ አያደርጉም::
ተጨዋቾቹ አለቃቸው ቤት እንደደረሱ አለቃዋ ቀን ስታሰባስብ የዋለችውን ብር ለቡድኗ በመስጠት ታስቆጥርና መልሳ ተረክባ ግማሹን ለደብሩ ቤተ ክርስትያን ቀሪውን ደግሞ በመጨረሻው ቀን ለቡድኑ አባላት ታከፋፍላለች:: በአጠቃላይ የሻደይ ጨዋታ በኽምራዎች ምድር በዚህ መልኩ ይከወናል::

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

በእርግጥ ዛሬ ዛሬ በሙታኑም ሆነ በህያዋኑ የታሪክ ምሁራን እና ቁንጮ ፖለቲከኞቻችን የታሪክ ሽሚያው አይሎ ቀጥሏል:: የአንዱ አከባቢ መገለጫ የሆነውን ባህላዊ ክዋኔ ወደ ሌላኛው አከባቢ ወስዶ ለዛ ማህበረሰብ እውቅና መስጠት እየተለመደ መጥቷል:: በዚህም ሳቢያ የማህበረሰቡ መገለጫ የሆኑ ቱባ ባህሎች በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጡንቻ ባላቸው ቡድኖች እየተነጠቁ ይገኛሉ:: ከነዚህም አንዱ ሻደይ ባህላዊ ጨዋታ ነው:: በእርግጥ ታሪክን ወጥ አድርጎ ፈር ማስያዝ አይቻልም::

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

ዳሩ ግን የጋራ የሆነ፣ ቅቡልነት ያለው የጋራ ታሪክ ማበጀት ይቻላል:: ነባራዊ እውነታው ግን ከዚህ ባሻገር ነው:: ነገረ ሻደይም እጣ ፈንታው ይሄው ሆኗል:: ብቻ የሻደይ እምብርት ዋግና አከባቢው ነው:: ለዚህም ማሳያው ሻደይ በድምቀት የሚከበረው በዋግ፣ ከትግራይ ደግሞ በተንቤን አብይ አዲ፣(ከዛ ውጭ ባሉት በትግራይ አከባቢዎች ሻደይ እየተለመደ የመጣው በቅርቡ ነው፤ እሱም ቢሆን በጠንካራ ኢንዶክትሪኔሽን ስራ ነው::) በአማራው ደግሞ በላስታ ላል-ይበላና ራያ ቆቦ አከባቢ ብቻ ነው::
እነዚህ አከባቢዎች ደግሞ የዋግ ኩታ ገጠም፣ በሃዘንና በደስታ የሚጋሩ አልፎም ደግሞ በጋብቻ የተሳሰሩ ቅይጥ ህዝቦች ናቸው:: ሮሃ ላል-ይበላ እንዲሁ የዘአገው ስረወ መንግስት መናገሻ መአከል፣ ቀደምት የአገው ህዝቦች የስልጣኔአቸውን አሻራ ያስቀመጡበት የጥበብ ገምቦ፣ ቅዱሳኑ የአገው ነገስታት አማርኛ ቋንቋን የስረአተ መንግስቱ የስራ ቋንቋ አድርጎ የበየኑባት ምድራዊ የፍትሕ ምአድ ነች:: ስለ እነዚህ ህዝቦች አንድነት እና ምንዥላታዊ ትስስር በዚህ ጽሁፍ ማስፈር ደግሞ ለቀባሪው መርዳት ነው:: ምክንያቱም ዋግና ላስታ ድርና ማግ ናቸውና:: የተንቤን ህዝብም ቢሆን (ቅርብ ለቅርብ የሚኖሩ ሁለቱ ህዝቦች ሁለትነታቸው እስኪያጠራጥር ድረስ በመልካ
ምድር፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በኑሮ ዘዴ፣ ወዘተ አንድ አልያም ተመሳሳይ ናቸው:: ፍሬድሪክሲ. ጋምስት 2003፡139 እንዳለው) ይህን እውነታ ደግሞ ማንም ያውቀዋል:: ይህን ለመመስከርና ለመበየን በዲግሪ፣ በማስተርስና በዶክትሬት ደረጃ ታሪክን ማጥናት አይሻም፤ ምክንያቱም እውነት ነውና::
ስለዚህም ሻደይ የዋግ ኽምራ ህዝብ ባህላዊ ሃብቱ ፣ማንነቱና መገለጫው፣ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየው ጥልቅ ማህበረሰባዊ ፍልስፍናው ነው:: እንግዲህ ስለ ሻደይ ባህላዊ ጨዋታ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ አመጣጡ፣ ክዋኔው እንዲሁም ደግሞ ስለ አከባበሩና ባህሉ በጉልህ የሚደምቅበት ቦታ/አከባቢ/፣ ውልደትና እድገት ለመበየን እድሉን ለአንባቢያን እተወዋለሁ:: በመጨረሻም በገጣሚ
ኤፍሬም ስዩም ስንኝ ልሰናበት …

እስከ ምዐዜኑ አነብዕ …
ውስተ ልብየ ትካዘ፣
ማርያም ድንግል …
ኩነኒ መናዝዘ።

የከርሞ ሰው ይበለን! መልካም የሻደይ ብአል! …
23ኛ ዓመት ቁጥር 34 – ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም – ዕትም ዋጋ 2 ብር ገጽ 15

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *