Skip to content

የተቃውሞ መከታተል መዋቅር ከናደ የ ” ዳቦ ተቆረሰ” ፖለቲካ ማየት ግድ ነው

በተደጋጋሚ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተደረጉትን ተቃውሞዎች ተከትሎ “አልተደራጀንም ፣ አላደራጀንም፣ የተቀናጀ አመራር የለም፣ … ” የሚሉት አስተያየቶች ይሰማሉ። ኢትዮጵያን ያዝ ለቀቅ የሚያደርጋት ተቃውሞና አመጽ መልኩን ሊቀየር ይችላል በሚል የሚጨነቁ ገሃድ ወጥተው ባይናገሩም በየአቅጣጫው ይደመጣሉ።በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ አለያም ሽግሽግ ሊደረገ እንደሚገባ በጥቅል ስምምነት ቢኖርም፣ ይህ ለውጥ በሰከነ መንገድ፣ በሕዝብ ውስኔ እውን ሊሆን እንደማይችል ከድመዳሜ ተደርሷል።

merera

አገሪቱን መቶ በመቶ የመምራት ውክልና ከሕዝብ እንዳገኘ በመግለጽ መንበሩ ላይ የተቀመጠው ኢህአዴግ፣ ይህንን ባለ የወራት እድሜ ውስጥ ያጋጠመው መከራ የሕዝብ ወሳኝትን በአግባቡ መቀበል ግድ እንደሆነ አመላክቷል። ይሁን እንጂ ገዢው ኢህአዴግ ችግርና ተቃውሞ በተነሳበት ቁጥር ” ራሴን አድሳለሁ” ከማለት የዘለለ ፖለቲካዊ አማራጭ መቀበል ስለማይፈልግ ተቃውሞውና የሕዝብ ቁጣ እየጠነከረ፣ በአይነትም ለየት እያለ፣ በአቅምም እየከረረ፣ በውጤት ደረጃም ቀላል የማይባል ሰባዊና ቁሳዊ ቀውስ ማስመዝገብ ደረጃ ላይ ደርሷል። መቆሚያውና መድረሻውን ለመተንበይም አስችገጋሪ ሆኗል።

በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልል አሁን ያለው የሕዝብ ስሜት የተበላሽ ይመስላል። ከትግራይ ክልል በስተቀር በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች በወቅቱ የፌደራል ስርዓት ትግበራ ላይ የሚታየው የስሜት መጎሽ ማስተባበያ የሚቀርበበት አይመስልም። ራሱ መንግስት በየዘርፉ ባሉት አካላቱና አንደበቶቹ ይህንኑ እውነት ያምናል። አምኗል። እያመነም ነው። ይሁንና የሚወሰዱት የማስተካከያ ርምጃዎች ይህንኑ የስሜት መጎሽ የሚያላዝቡ ሳይሆኑ የሚያባብሱ ናቸው።

” ሕዝብ ያነሳው ጥያቄ አግባብነት ያለው ነው፤ በየቀበሌው ሕዝብ ፊት ተቀመጠን መወያየት የማንችልበት ደረጃ ደርስናል…” በማለት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የፓርቲያቸው መደብዛዙን መልክ በተደጋጋሚ አስታውቀዋል። ” ጥልቅ ተሃድሶ ” በሚል ይህንኑ የተበላሸውን የድርጅታቸውን ፊት የማስዋብ ስራ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። ሀገ መንግስት እስከማሻሻል የሚደርስ ድርድር ለማድረግ ቃል ገብተውም ነበር። የሁሉም ውጤት ሲታይ ግን የሚፈለገውን ውጤት ያመጣ አይመስልም።

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ኢህአዴግ ራሱን የማደስና የማነጽ ስራ መስራት መብቱ ነው። ይህንን መብቱን ማንም ሊከለክለው አይችልም። ችግር የሚሆነው ኢህአዴግ በታመመ ቁጥርና ” መታደስ እፈልጋለሁ” ባለ ቁጥር ሕዝብ አስታማሚ እንዲሆን ማስገደዱና እሱ ከያዘው ካንሰር እስኪላቀቅ የኸው ሕዝብ ታግሶ እንዲጠብቅ መጨረሻ የሌለው የተጨማሪ ሰዓት መጠየቅ አለማቆሙ ነው። ለመጠበቅ ፈቃደኛ አይደለንም ያሉትን ደግሞ እሱ እስኪያገግም ማቆያና ማጎሪያ ማከማቸቱ ነው።

በዚህ መልኩ የሚነዳው የሕዝብ ጥያቄና የኢህአዴግ ” እኔ ብቻ ” የሚለው የጎሳ ፖለቲካ መስመር እያደር እየከረረ መሄዱን ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ ተራ የሚባሉ ዜጎች የሚትቹበት ጉዳይ ነው። ” ተው” ሲባል አልሰማ ብሎ ሀወሃት ያራገበው የዘር ፖለቲካ ራሱን አደጋ ውስጥ እየከተተው አገሪቱንም ወደ አሳሳቢ መበታተን እየሳባት ነው። የዘር ፖለቲካና ዘረኝነት በቀላሉ የማይድን፣ የሰውን ልጀ ወደ አውሬነት የሚቀይር መርዝ መሆኑንን ከዓለም ተሞክሮ የተረዱ ስጋታቸው የሚያነጣጠረው እዚሁ አደጋ ላይ ነው።

ኢህአዴግ በየጊዜው የተፈተሩትን ችግሮች መስመር እንዳስያዘ ቢናገርም፣ በተጋባር የሚታየው የፖለቲካው ግለት የተተከለው በዘርና በክልል አስተሳሰብ ላይ ተመስርተው በሚደረጉ አመጾች ዙሪያ ነው። አንዳንዶቹ ዘር እየለዩ ” ፍለጠው፣ ቁረጠው” የሚል መፈክር ሲያስተጋቡም እየታየ ነው። እንዲህ ያለው መርዛማ አካሄድ አደገኛ ሆኖ ሳለ ኢህአዴግ ከዚህ ጽንፈኛንት የራቁና የጸዱትን ፖለቲከኞች ማሰሩ ለጽንፈኞቹ በሩን ወለል አድርጎ የመክፈትና እውቀና የመስጠት ያህል እንደሚቆጠርበት ገለለተኞች ይተቻሉ።

Related stories   "የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀግኖች አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወሰነ

በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ታማኝ የሆኑና እውቅና የተሰጣቸውን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን እስር ቤት አጉሮ ለጽንፈኞች የመፈንጫ ሜዳ የፈቀደው ኢህአዴግ ውስኔውን ደግሞ ደጋግሞ ሊያጤን እንደሚገባው በሳል ፖለቲከኞች ይመክራሉ። ይህ ካልሆነ ግን አሁን በኦሮሚያ ሃያ ዘጠኝ ወረዳዎችን አዳረሰ የተባለው ተቃውሞ ነገ ደፍን ኦሮሚያን፣ አማራን፣ ደቡብን የማያካትትበት ምክንያት እንደማይኖር እነዚህ ክፍሎች ይናገራሉ። ቭግር እንኳን ቢከሰት እንዴት ለመቆጣጠር እንደሚቻል ከ ” ቄሮ ” በስተቀር የሚያውቅ የለም።

ዛሬ ኢትዮጵያ ” ተው ” ቢል እንኳን የሚሰማ አውራ ሰው የላትም ። ሽምግልናውም ቢሆን አገራዊ ወጉና አቅሙ ከስሟል።  በሃይማኖቱም ሆነ በፓለቲካው ዙሪያ ተሰሚነት ያላቸው፣ ሕዝብ የተቀበላቸውና አንቱ የሚላቸው መሪዎች አለመኖራቸው ከችግሮች ሁሉ በላይ እንደሆነ የሚናገሩ ክፍሎች ” ኢትዮጵያ ሳይመሽ ያላት አማራጭ እውነተኛ ፍትህ ያላበት እርቅ ማካሄድ ብቻ ነው” ይላሉ። ተሰሚነት ያላቸውን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ያገለለ፣ እስር ቤት የከተተ የፖለቲካ ድርድር ፋይዳው ዜሮ እንደሆነም ይናገራሉ።

” የተበጁና ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑ ስብስቦችን ለቃቅሞ ስለድርድር ማውራት፣ ሲጀመር ከህዝብ ጋር ያለውን ልዩነት ማንቦርቀቅ ካልሆነ በስተቀር ጠቀሜታ የለወም ። ሕዝብ ሁሉን እያወቀ እንደማያውቅ አድርጎ ማሰብ ንቀት ነው ” ሲል ለዛጎል አስተያየቱን የሰጠው በፈረንሳይ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ያለ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ ነው።

ለጊዜው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው አስተያየት ሰጪ ” ኢህአዴግ አሁን ከፊቱ በርካታ የችግር ምሰሶዎች ተደቅነውበታል” ይላል። የአባል ድርጅቶቹ መንሸራተት ፣ የጎሳ ፖለቲካ ጣጣ፣ የምንዛሬ፣ የኢንቭስትመንትና የወጪ ንግድ ችግር፣ የቅርብ አጋሮቹ እምነት መሸርሸር፣ የረሃብ አደጋ ፣ ስራ አጥነት፣ ደህነት፣ ሙስና፣ ሲል በከፊል ይዘረዝራቸዋል። በዚህ ሁሉ ችግር ላይ ካለፈው የተቃውሞ ችግር ትምህርት አለመውሰድና የፖለቲካ እስረኞችን ማበራከት የአገሪቱን ችግር የሚያወሳስቡ ናቸው።

አሁን አገሪቱን ያጋጠማት ችግሮች ኢህአዴግ በፍጹም ብቻውን የሚወታቸው ባለመሆናቸው፣ የህዝብ እና “የተቀናቃኝ” ድርጅቶች ድጋፍ ግድ ነው። ይህ እንዲሆን ሁሉንም ወገኖች የሚያስማማ መንገድ ሊዘጋጅ እንደሚገባ፣ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በፍጹም መተማመንና በሰለጠነ የእርቅ አስተሳሰብ ላይ በተመስረት ውይይት ተደርጎ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሲፈለግ ብቻ ነእንደሆነ አስተያየት ሰጪው አመልክቷል።

” ችግሩ ሁሉም ተናጋሪና ተቺ እንጂ ሰሚና ሩቅ አሳቢ አለመሆኑ ነው” የሚለው የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ  ” እየቆመ የሚበርደው ተቃውሞ አንድ ቀን ከቁጥጥር ውጪ ቢሆን ምን ይደረጋል?” ሲል ይጠይቃል።.ይህ በተበታተነ የእዝ ሰነሰለትና በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተመሰረተ ተቃውሞ እየዋለ ሲያድር ፈሩን ሊለቅ እነድሚችል ግምቱንም ያኖራል። ሲያስረዳ ” ተቃውሞው ሰው እየሞተ፣ እየታሰረ፣ ሲቀንስ ሳይሆን ሲባባስ ነው የሚታየው። ከዚህ በላይ ማሳያ የለም። በዚህ ደረጃ እያደገ ከመጣ፣ በጎረቤት አገሮች ካለው የፖለቲካ ቀውስና ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ተላቶ ስሜት ጋር ተዳምሮ ችግሩ ወደ ከፋ መንገድ ሊያመራ እንደማይችል ማረጋገጫ የለም” አክሎም ” ኢህአዴግ የራሱን የፖለቲካ ጣጣ ለራሱ ድርጅት በመተው አገርና የውስጥ ችግርን በመለየት ወደ ፖለቲካ መፍትሄ ዛሬ ነገ ሳይባል ሊያመራ ግድ ነው” ይላል። ምክንያቱም አሁን በአገሪቱ የሚታዩት ኩነቶች ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑን አመላካች ናቸውና።

“ተቃዋሚ የሚባሉት” ይላል ይህ አስተያየት ሰጪ ” ብዙ መናገር አስፈላጊ ባይሆንም መሰረታዊ ልዩነታቸው ግልጽ ያልሆነ፣ ለምን ተግባብተው እንደማይሰሩ ምክንያት ማቅረብ የማይችሉ፣ ልዩነታቸውና አንድነታቸው ለመለየት የሚያስቸግር፣ የህዝብን ባህላዊና አብሮ የመኖር መስተጋብር የማይረዱ፣ ከልዩነታቸውም በላይ መዘላለፍ የሚቀናቸው፣ በትግል ጥሪና ተገኙ በሚባሉ ድሎች በባለቤትነት የሚጣሉ፣ ልዩነታቸውን ወደሚዲያ በመውሰድ የህዝብን ስሜት የሚያጎሹና ተስፋ የሚያስቆርጡ፣ ሁሉም አርበኛ የሆነበት፣ ሁሉም የድል አብሳሪና ነጋሪት ጎሻሚ የሆነበት፣ በችግርና በደመነፍስ በሚሰሩ ስህተቶች የታጀለ …”

Related stories   የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ ምርጫ እንዲራዘም ያቀረቡት ጥሪ ብልህነት የጎደለው እጅግ አደገኛ ነው - ሎረንስ ፍሪማን

እንደ አስተያየት ሰጪው አባባል ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን ለህዝብ ፍርድ ጥለው አንድ ፈርጣማ ክንድ በመፍጠር ኢህአዴግ ወደ ድርድር እንዲመጣ እጁን መጠምዘዝ የሚችሉበትን አጋጣሚ በገዛ ራሳቸው አሳልፈው የሰጡ ናቸው። እናም በዚህ ስህተታቸው ወደፊት መራመደና ለአገሪቱ ህዝብ አስተማማኝ አማራጭ መሆናቸውን ማሳየት አልቻሉም። በዚህም ሳቢያ ትግሉም እነሱም አንካሳ ሆነዋል። ኢህአዴግም የፖለቲካ ምህዳሩን አንቆ መያዙ ይህንን ሁሉ ጣጣ እንዳመጣበት አሁን ድረስ አልተረዳም። ወይም የፈለገው ይምጣ በሚል ዝምታን መርጧል። በመካከሉ ሕዝብና አገር ያቃስታሉ። አገሪቱ መሸክም የማትችላቸው ሰው ሰራሽ ችግሮች ላይዋ ላይ እየናኙ ነው። ማን ይታደጋት?

በይፋ ባይቀርብም አሁን እነደሚሰማው በአማራ ክልል ተመሳሳይ ተቃውሞ ለማድረግ ዝገጅት አለ። በኦሮሚያም ተመሳሳይ ተቃውሞ ይኖራል። እንደውም አድማሱን ሊያሰፋ እንደሚችል ይገመታል እየተባለ ነው። በደቡብ ክልልም እንዲሁ ጭምጭምታ አለ። እናም አሁን አገሪቱ ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ቀውስና የውጭ ንግድ መዛባት፣ እንዲሁም በኑሮ ውድነት ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል ሊሆን አይችልም ተብሎ ይጠበቃል።

አንዳንድ ምንጮች እነደሚሉት ይህ ተቃውሞ ከክልል አመለካከት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ኢህአዴግ በመዋቅሩ ሊታገለውና ሊረታው አይችልም የሚል ስጋት አለ። በዚሁ መነሻ አድማው የገጠር ቀበሌዎችንና ወረዳዎችን መዋቅር መሰረት አድርጎ ሊነሳ እንደሚችልም ትንበያ ተቀምጧል። ይህ ተጋባራዊ ከሆነ “ዳቦ ተቆረሰ” አይነት ፖለቲካ እንዲፈጠር ይጋብዛል። ለሁሉም ግን ዋናው መፍትሄ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር እንዳሉት ፖለቲካዊ ምፍትሄ የሚያመጣ ድርድር፣ ንግግር፣ ውይይት ብቻ ነው።

በኦሮሚያ የተደረገውን ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማ አስመልክቶ ሪፖርተር የሚከተለውን ዘግቧል። ዘገባው የኦሮሚይ ክልልን አስተያየት በስፋት የያዘ በመሆኑ እስካሁን ላቀረበነው ዘገባ ለማመጣጠኛ ይሆን ዘንድ እንዳለ አቅርበነዋል።

በኦሮሚያ የሥራ ማቆም አድማ በ29 ወረዳዎች የትራንስፖርትና የንግድ አገልግሎቶች ተቋርጠው ነበር

  • በጅማ የቦምብ ጥቃት 13 ሰዎች ተጎድተዋል

በኦሮሚያ ክልል በማኅበራዊ ሚዲያ ከረቡዕ ነሐሴ 17 እስከ እሑድ ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በተጠራው የሥራ ማቆም አድማ፣ በ29 ወረዳዎች የትራንስፖርትና የንግድ አገልግሎቶች ተቋርጠው መሰንበታቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የክልሉ የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አረጋ ዓርብ ነሐሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በክልሉ ውስጥ ካሉ 315 ወረዳዎች መካከል በ29 ወረዳዎችና በአራት ዋና ዋና ከተሞች ለሦስት ቀናት የሥራ ማቆም አድማ ተደርጓል፡፡

ለዚህ ሥራ ማቆም አድማ መሠረታዊ ተደርጎ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በኦሮሚያ ክልል ከአዋሳኝ አካባቢዎች ጋር ያለው ድንበር በአግባቡ ባለመካለሉ ተደጋጋሚ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉ፣ የቀን ገቢ ግምቱ ትክክል አለመሆኑን፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች ይፈቱ የሚሉ መሆናቸውን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ በተጠራው የተቃውሞ ጥሪ በስድስት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተሞች የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተቋርጠው ነበር፡፡ ለአብነትም ሆሮ ወረዳ፣ አምቦ ከተማ፣ ግንደበረት፣ ጀልዱ፣ ሚዳቀኝ፣ ጮኬ፣ ጮቢ፣ አቡናና፣ ሜጀሬ፣ አሰቦ፣ መኢሶ፣ አወዳይ፣ ሀረማያ፣ ኮምቦልቻ፣ ነቀምቴ፣ ሆለታ፣ ቄለም፣ ደንቢዶሎ ወዘተ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

Related stories   "በፕሮፓጋንዳ እስካሁን የተወናበድኩት ይበቃኛል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብም ይገባል ... ወጣቱን ያለ እድሜው ህይወቱን ይቀጩታል"ሌ.ጀ ዮሐንስ

በእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች እንደነበሩም አቶ አዲሱ ጠቁመዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብም በእነዚህ ወረዳዎችና ከተሞች በተነሳው ተቃውሞ እንደተሳተፈ ገልጸው፣ የተደራጁ ቡድኖች በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያስተላልፉት መልዕክት ሐሳባቸውን በግድ የመጫን አዝማሚያ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

‹‹ሐሳብን በተለያየ መንገድ መግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደመሆኑ መጠን የሌላውንም ፍላጎት ማክበር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ መደብሮቻቸውን የዘጉ ነጋዴዎች በዚህ ሕገወጥ ድርጊት ሙሉ በሙሉ እንደማያምኑበትም አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

መደብሮቻቸውን በሚከፍቱ ነጋዴዎች ላይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች በመታገዝና ዕርምጃ ይወሰድባቸው ብሎ በማስፈራራት፣ አስገድዶ የማዘጋት እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ አቶ አዲሱ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ቀን ከፍተው በነበሩ ነጋዴዎች ላይ በሌሊት በመደብሮቻቸው ላይ ዕርምጃ ሲወስዱ እንደነበረ ጠቁመዋል፡፡ በአወዳይ ከተማ የዚህ ዓይነት ችግር መከሰቱን አቶ አዲሱ ለአብነት አንስተዋል፡፡

በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት ተከታታይ ቀናት ውስጥ በሰው አካልና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ሆለታ አካባቢ የሁለት አውቶብሶች መስታወት እንደተሰበረ ጠቁመው፣ የክልሉ መንግሥት የሠራተኞች ሰርቪስ ላይም ተመሳሳይ ጥቃት መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ደግሞ በጅማ ከተማ ቦምብ በማፈንዳት በ13 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንም አስታውቀዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ እንደተደረገላቸው፣ ከተጎጂዎቹ ውስጥም የአሥር ዓመት ታዳጊና ሁለት ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

አቶ አዲሱ ‹‹መንግሥት ቤት ውስጥ በመዋል አድማ የማድረግ ፍላጎት ያላቸውን ዜጎች መብት እንደሚያከብር ሁሉ፣ ሱቃቸውን ከፍተው መሸጥ የሚፈልጉና ሰላማዊ ሕይወት መምራት ለሚፈልጉ ሰዎች ከለላ የመስጠት ግዴታ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የአድማ ጥሪው ከተላለፈ በኋላ ጫት ከኦሮሚያ ክልል ወደ ድሬዳዋ፣ ሐረርና ሶማሌ ክልሎች እንዳይሄድ ሰፊ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበር አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ዜጎችን በመለየት እየያዘና ለሕግ ተጠያቂ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ምን ያህል ዜጎች ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደታሰሩ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ እስካሁን ቁጥሩ በውል እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ይህ የተቃውሞ ጥሪ መሠረት እንደሌለው ቢገለጽም፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ግን ይህን ሐሳብ ተቃውመዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ የሺዋስ አሰፋ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹ይህ ተቃውሞ ቀድሞ የተተነበየ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ የሺዋስ ከ2007 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ሕዝቡ መንግሥትን አልመረጥኩም እያለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 አቶ የሺዋስ ይህን ጉዳይ ሲያብራሩ፣ ‹‹መንግሥት በርካታ የፖለቲካ ጥያቄዎች እየተጠየቀ የወጣቶች ፈንድ አቋቋምኩ በማለት ለራሱ ነው መልስ የሰጠው፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት እያጭበረበረ መቀጠሉን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት ወደ ኦሮሚያ፣ ጎንደርና ባህር ዳር የጉዞ ዕገዳ በዜጎቿ የጣለ ሲሆን፣ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርተር ለውጭ ጉዳዩ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ጥያቄ አቅርቧል፡፡

አቶ መለስ በምላሻቸውም፣ ‹‹ኤምባሲዎች ዋነኛ ሥራቸው እንደዚህ ዓይነት ትንንሽ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ይህንን መሰል ማስጠንቀቂያ ማውጣት ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ኤምባሲ ባለፈው ጊዜ አውጥቶት የነበረውን የጉዞ ክልከላ ስህተት ሆኖ ስላገኘው ይቅርታ ጠይቋል፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከሦስት ሳምንት በፊት ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

0Shares
0
Read previous post:
ፌዴራል ፖሊስ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ቤተሰቦች ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው አለ

በተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ጊዜ ተፈቀደ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና ባለሀብቶች፣ ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው...

Close