አንድ ማህበረሰብ፤ ማህበራዊ አንድነቱ፣ ግላዊ ፈቃዱ፣ ሠላሙ፣ ጥቅሙ፣ ነጻነቱ፣ መብቱ፣ ማንነቱና ውርሶቹ ሁሉ ተጠብቀው እንዲቀጥሉለት መንግስት ያስፈልገዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በታላላቆቹ የፖለቲካ ፈላስፎች በእነ ሆብስና ሩሶ አስተምህሮ መሰረት፤ ግለሰቡ ወይም ህዝቡ ስልጣኑንና በጎ ፈቃዱን በስምምነት መንግስት ለሚባለው አካል ማስገዛት አለበት። መንግስትነትን ለመመስረት ደግሞ መጀመሪያ የውላችንን አይነትና ምንነት በትክክል መለየት ይኖርብናል፡፡ ለዚህ አስተሳሰብ ሁነኛ መሰረት ጥለዋል የሚባሉት ሆብስና ሩሶ ናቸው፡፡

እንደ ሌዋታት ሁሉንም ውጣ ‹‹ዋጤ››ማንነቷን አስመስክራለች- አፍሪካችን

እንደ ሆብስ አባባል፤ መንግስት የህብረተሰቡን ደህንነትና ንብረቱን የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ለሩሶ ደግሞ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባሩ፤ የህብረተሰቡን መብትና ነጻነት ማስከበር ነው፡፡ ይህ የሩሶ አባባል ከውዴታ ይልቅ ግዴታው ያመዝናል። ሁለቱም ፈላስፎች ግብ ያደረጉት፣ የማህበረሰቡን አንድነትና  ሠላም ሲሆን ለዚህ አቋማቸው ዋነኛው ምክንያት ደግሞ፥ በመንግስታዊ መዋቅሮቻችን፣ የህብረተሰቡን ደህንነትና ንብረት እንዲሁም ነጻነትና መብት ማስከበር ከተቻለ፣ ሰላማዊ ማህበረሰብ ይገኛልና ነው።
የፍላጎት ወይም ጥቅም /interest/ ውል የሚያጋድልበት ፍልስፍና የሆብስ ሲሆን የመብት/right/ ውል ያመዘነበት ፍልስፍና ደግሞ የሩሶ ነው። የጥቅም ውልና የመብት ውል እየተባሉ ለሁለት ቡድን ተከፍለው ምሁራዊ ትንታኔ ይሰጥባቸዋል፤ የሁለቱ ፈላስፎች ማህበራዊ ውል። ጋሽ ሆብስ፤ የሰው ልጅ ክፉ፣ ቀማኛ ነው ብሎ ስለሚያምን፣ እያንዳንዳችን ጥቅማችን ተከብሮና ከቀማኞች ተጠብቀን እንኖር ዘንድ መንግስት መመስረት አለብን ስለሚል፥ በጥቅም ላይ የተመሰረተ የመንግስት ውል ይባላል ማለት ነው፡፡ ጋሽ ሩሶ ደግሞ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ቅንና የዋህ ስለሆነ፤ ክፋትን እዚህ ዓለም ላይ ሲኖር ነው የሚማረው፤ ስለሆነም ከማንኛውም ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆንና ክፋትን ከሚያስተምሩት እንዲጠበቅ መብቱን የሚያስከብርለት ውል ያስፈልገዋል ይለናል፤ ስለዚህም የመብት ውል ይባላል-የሩሶ መንግስት፡፡
“Every person and everything is either an obstacle or potential obstacle to our felicity, and the only way to surmount or remove obstacles is to increase our power. Absent the organizing power of formal society and the sustained institutions of law and politics, we slide into a state of nature that is nothing more than a ‘‘war of all against all,’’… wherein natural life is ‘‘solitary, poor, nasty, brutish and short.’’
ሆብስ፤ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ክፉ ነው ጥፋት፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ቀማኛነት፣ ጉልበተኛነት ተፈጥሯዊ ባህሪዎቹ ናቸው ብሎ ያምናል። በዚህ ተፈጥሯዊ ህይወቱ መውደምና መተላለቅ፣ የሰው ልጅ ግብ ነው ብሎ ያምናል። ነገር ግን መውደምና መተላለቅ ለጉልበተኛውም ለደካማውም ስለማይበጅ፤  ከዚህ  ተፈጥሯዊ  እልቂት  የሚገላግለው ማህበራዊ ውል ያስፈልገዋል። ይህ ማህበራዊ ውል ደግሞ የሁሉንም ጥቅም /interest/ የሚያስከብር ጉልበተኛ መሆን አለበት። ጉልበተኛው የበለጠ ተጠቃሚ እንዳይሆንና ደካማው የድካሙ ፍሬ ተጠቃሚ እንዲሆን ሁሉም “እኩል” ሆነው የሚገዙበት የጥቅም ውል መመስረት ይኖርባቸዋል። ለሆብስ መንግስት መመስረት ያለበት፣ ይህንን የጥቅም ውል ለማስጠበቅ ነው። ይህንን መንግስት ደግሞ ሆብስ ሌዋታን (Leviathan) ይለዋል።
በአባቶቻችን ትምህርት መሰረት፤ የህይወት ማስገኛ ምንጭ የሆኑ ሁለት ደመ ነፍስ እንስሳት አሉ። አንደኛው ብሔሞት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሌዋታን/ Leviathan ነው። ብሔሞት የምድር ላይ እንስሳት ሁሉ አስገኝ እናት ሲሆን ሌዋታን ደግሞ የውሃ ውስጥ እንስሳት አስገኝ እናት ነው ማለት ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው። ሆብስ፤ ሌዋታን ብሎ እርሱ ለሚፈላሰፍበት የመንግስት ሥርዓት ሥያሜ የሰጠው ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በመነሳት ነው። ምክንያቱም ሌዋታን እጅግ ግዙፍ፣ የሁሉም የውሃ ነፍሳት እናት የሆነ፣ ማንም የማይፎካከረው ገዥ ስለ ሆነ ነው። “Leviathan stands over prideful humanity as a mortal god, preserving order and ensuring equity through the ‘‘awe’’ and ‘‘terror’’ of a common power capable of controlling our prideful inclinations.”  ይሉታል፤ የፖለቲካ ፈላስፎችና ተንታኞች።
ዛሬ ዛሬ በአፍሪካችን የምናየው የመንግስት ሥርዓት የሆብስን ሃልዮት ዋቢ ያደረገ ይመስላል። የብሔሮችን ጥቅም ለማስከበር የቆምኩ ነኝ እያለ ሲለፍፍ እንሰማለንና፣ የጥቅም ውል ነው ልንለው እንችላለን። “የብሔሮችን ጥቅም የሚያስከብረው የኔ መንግስት ባይኖር፣ እርስ በርስ ትተላለቃላችሁ፤ ትልቁ አሣ ትንሹን አሣ እየበላ በመጨረሻም የትልቁ አሣ እጣ ፈንታ የሚበላው አጥቶ በረሃብ መሞት ይሆናል” ይለናል፤ መንግስታችን። a ‘‘war of all against all,’’
ስለሆነም ህገ መንግስታችን የህልውናችን መሠረት ነው ይላሉ፤ የአፍሪካ መንግስታት። ይሄን ሃሳብ ለመመስረት ይረዳቸው ዘንድ ህገ መንግስቶቻቸው በመግቢያው ላይ የሃገራችን ህዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች” ብሎ ማተት ይጀምራል። ይህን ‹‹ኦሪት ዘ አፍሪካ መንግስታት›› ልንለው እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ ሁሉም የተከፋፈለ ነበረ፤ ከዚያም እንደተከፋፈሉ የሚኖሩበትን ህግ ለማጽናት ጽሕፈት መጻፍን ተለማመዱ፥ ተለማምደውም አልቀሩ፤ በጥራዝ አሳተሙት፡፡
የሆብስ ፍልስፍና ይበልጥ የሚንጸባረቅባቸው የአፍሪካ መንግስታት ገና ጨቅላ እያሉ ‹‹የጠላቴ ጠላት ባልንጀራዬ ነው›› በሚል ብሒል፣ በአቋም ከማይመስሏቸው ጋር በመተባበር ጠላታችን የሚሉትን ተባብረው ይደመስሳሉ። ጠላቴ ከሚሉት ጋር ተነጋግሮና ተመካክሮ ልዩነትን ማጥበብ ያልቻለች የአፍሪካ መንግስት፤ እንደ ሌዋታት ሁሉንም ውጣ ‹‹ዋጤ››ማንነቷን አስመስክራለች- አፍሪካችን። የመዋጥ አባዜ እጅግ ሲጠናወታት ደግሞ የውስጥ ብዙ ታጋይ ልጆቿንም ሰበብ እየፈለገች ውጣለች። ከማንም ጋር ለመደራደርና ስልጣን ለመጋራት ስለማይፈልጉ፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ መንግስታት የምርጫ ዘመናቸው ከመጠናቀቁ በፊት ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን መደላደያ የህገ መንግስት ማሻሻያቸውን ያጠናቅቃሉ። ከዚያማ አድዮስ! በልጅነታችን በእድሜ ከምንበልጣቸው ልጆች የሚያምር መጫወቻ ለመንጠቅ እንደምንጠቀምባት ዘዴ ሁሉ፣ ‹‹ውርስ ለመንግስት›› ትባላለህ። መንግስትነት በቤተ አዝማዳት አሊያም ከቤተ ፓርቲ አትነቀልም።
የልጅነት ባህሪን ለመቀየር እንደ እሳተ ገሞራ የሚፈነዳ እጅግ ጠንካራ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ የተሳሳተው ልማዳችን እንደ ትክክለኛ ባህሪ ስለሚዋሃደን ነቅሰን ለማውጣት እንቸገራለን። “እናቴ ምነው በእንቁላሉ በቀጣሽኝ ኖሮ” እንዳለው የበሬ ሌባው። በእንቁላል ስርቆት ጊዜ ያልተቀጣ ሰብዕና፤ በሬውንም ሲሰርቅ የሚያዝና ሞት የሚፈረድበት አይመስለውም። ልክ እንደዚሁም በልጅነቷ ሁሉንም መጠቅለል የለመደች አፍሪካችን፤ ይባስ ብላ የአብዛኛው የአፍሪካ የምርጫ ውጤቶችን “መቶ በመቶ” አድርሳለች። ለዚህ መቼም ምንም ትንታኔ አይሰጠውም፤ እንደው ዝም ብሎ “ነፍስ ይማር” ነው የሚባል።
ሩሶ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከጥቅምና ከንብረት ማስከበር ሁሉ የሚቀድመው የሰው ልጅ ነጻነትና መብት ነው ብሎ ያምናል። የሰው ልጅ የቁሳቁስና የንብረት ጥገኛ ሳይሆን፣ ህልውናው የተመሰረተው ነጻነቱና ተፈጥሯዊ መብቱ ላይ ነው ይለናል። ለሩሶ፤ ሰውን ሰው ያደረገው የበጎ ፈቃድ ባለቤት በመሆኑ እንጅ እንደ እነ አርስጣጣሊስ አባባል፣ የምክንያት ባለቤት በመሆኑ አይደለም። ስለሆነም ለሩሶ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት፣ የህብረተሰቡን ነጻነትና መብት ማስከበር ነው። ‘‘How will the individual in society manage to engage one’s ‘‘own force and liberty’’ without causing harm to himself ?’’ …find a form of association which defends and protects with all common forces the person and goods of each associate, and by means of which each one, while uniting with all, nevertheless obeys only himself and remains as free as before? This is the fundamental problem for which the social contract provides the solution.
የኛ ማህበረሰብ የመንግስት አመሰራረቱ  ጥንታዊ ስለሆነ መሰረቱን በመብት ላይ አሊያም በጥቅም ላይ ያድርገው አጥርተን አልተረዳነውም። በሰሜን ከክርስቶስ ልደት አንድ ሺህ ዓ.ም. የሚደርስ ረጅም የመንግስት ሥርዓት አለን፤ በደቡብም እንዲሁ የጥያ ትክል ድንጋይና የጋሞ ድንጋይ ካብ አጥር፣ በጣም ጥንታዊ ማህበረሰባዊ መዋቅርና ውል ስለመኖሩ ምስክሮች ናቸው። የጅማው አባ ጅፋሮች ሥርዓት፣ የሐረሩ ኢማማዊና ሱልጣን ሥርዓትን ጨምረን መጥቀስ እንችላለን። በእኔ ግምት፣ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊያን ስለሆንን፣ አንዳች መለኮታዊ የመንግስት መንበር ላይ የተመሰረትን ይመስለኛል። የአባ ገዳ ሥርዓቱ፣ የሞ አንበሳው፣ የመሣፍንቱ፣ የነካዎ፣ የነዴቡሣም፣ የሡልጣኑ፣ የኢማሙ፣ የዋቆው፣ የመኳንንቱ፣ የጦና፣ የሻሬሮ፣ የአባ ቆሮ፣የነፍጠኛው የስንቱ መንፈስ ሁሉ… ወዘተ ካልተባለ፣ ስንቱ ተጠቅሶ ይዘለቃል በዚች ሃገር ላይ። አሁን አሁን፣ እንደ ሌዋታን ታላቅ ሆኖ የሚያስከብረን ዘውድ ይናፍቀኝ ጀማምሯል። የኢትዮጵያን እሴቶቿን ጠንቅቆ የተረዳና ጥቅሟን የሚያስከብር ዘውድ፤ መብትን የማይፈረፍር፣ የምዕራብንም ፍርፋሪ የማያራግፍብን፣ እኛነታችንን ከእነሙሉ መብታችን የሚጠብቀን ዘውድ።

አዲስ አማስ 

Written by  ደረጀ ኅብስቱ dhibistu@gmail.com

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *