….ምንም እንኳ የአድማው ጅኦግራፊያዊ ወሰን ክልላዊ ቢሆንም ባሳረፈው አለታዊ ተጽዕኖ ግን ከሞላ ጎደል ክልል ተሻጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ኦሮሚያ ክልል ከብዙ የሀገሪቱ ክልሎች ጋር የሚጎራበት በመሆኑ አድማው የመጓጓዣ እና ንግድ ትስስሮች ላይ እክል መፍጠር መቻሉ ነው፡፡ አድማው የመንግስት መቀመጫ እና የሀገሪቱ ዋና የኢኮኖሚ አውታር የሆነችውን አዲአበባን ከቀሪዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች መነጠል እንደሚቻል ታይቶበታል፡፡ አድማው ከሞላ ጎደል ይህንን ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን ዋዜማን ጨምሮ በአገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ያሉ መገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል፡፡ በክልሉ የተወሰኑ ዞኖች እና ወረዳዎች የአድማው ጥሪ ተቀባይነት አግኝቶ ንግድ ቤቶች ተዘግተው መሰንበታቸውን ራሱ ኦሕዴድም አምኗል፤

 

ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተደረገው ቤት የመቀመጥ አድማ ከታቀደው አስቀድሞ ግቡን ስለመታ በሶስት ቀናት ማብቃቱን የአድማው አስተባባሪዎች ተናግረዋል።
ሌሎች “አድማው አልተሳካም”  ከተቀመጡለት ግቦች አንዱን እንኳ ሳያሳካ እንዴት ስኬታማ ሊባል ይችላል? ሲሉ ይሞግታሉ። ይህ የዋዜማ ዘገባ አድማው በይፋ ከተነገረው ውጪ ተልዕኮ ነበረው ፣በአደባባይ ከተገለፀው ባሻገር ይፋ ያልተነገሩ የቅርብና የሩቅ ጊዜ ግብ አለው ይለናል። የኦሮሞ አክቲቪስቶች ከመጋረጃ ጀርባ ለኦሮሞ ህዝብ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እየሰራን ነው እያሉ ነው። ሙሉ መረጃውን በድምፅ ይዝለቁት አልያም የቻላቸው ታደሰን ዘገባ ከግርጌ ያንብቡት

Related stories   Egypt-Sudan alliance shifting in row with Ethiopia over Nile dam

መንግስት ለአምስት ቀናት ተጠርቶ በነበረው የኦሮሚያው ቤት ውስጥ የመዋልና ግብይት ማቆም አድማ ላይ አንዳንድ ርምጃዎችን ለመውሰድ መዘጋጀቱ መዘገቡን ተከትሎ አድማው ባለፈው ዐርብ በሦስተኛ ቀኑ ተቋርጧል፡፡
የአድማው አስተባባሪዎችም አድማው የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ለማስከበር መጥቀሙን ገልጸዋል፡፡ ያሁኑም ሆነ ካሁን በፊት የተጠሩት አድማዎች የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች ለረዥም ጊዜ ሲያነሱ ሲጥሉት የኖሩትን የብሄሩን የራስን እድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ምን ያህል ወደፊት መግፋት አስችለዋል? የሚለው ጉዳይ ግን መመርመር ያለበት ነው፡፡ የሰሞኑ አድማ በዚህ ረገድ ያሳካው ውጤት የለም፡፡ የአድማው አስተባባሪዎችም ቀደም ብሎ ያልተያዘውን የራስን እድል በራስ መወሰንን የአድማው አንድ ግብ እንደነበር መጥቀሳቸው ያልተጠበቀ ነው፡፡ ምናልባትም አጀንዳው በማንኛውም ህዝባዊ ጥያቄ ውስጥ ተደብቆ እንዲቀመጥ ይደረግና አስፈላጊ ሲሆን እየተመዘዘ ያለ አጀንዳ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡ የአድማው አስተባባሪዎች መግለጫ የሚጠቁመው አድማዎች በዋናነት ከመሠረታዊ ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች ይልቅ በዚሁ አጀንዳ ዙሪያ እንዲያጠነጥኑ እንደተፈለገ ነው፡፡
በርግጥ የአምናው የኦሮሚያው ህዝባዊ አመጽ ኦሮሚያ ክልል በአዲሳባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ህገ መንግስታዊ ጥቅም የሚደነግግ አዋጅ እንዲወጣና በክልሉና በአዲሳባ መካከል ያለው ድንበር እንዲካለል ገፊ ምክንያት መሆን ችሏል፡፡ የሰሞኑ አድማም ይኸው የመብት ትግል መቋጫ ሳያገኝ ወደፊትም አድማዎች እንደማይቆሙ ለማስገንዘብ መሆኑ አስተባባሪዎች ጠቁመዋል፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የተራዘመ ትግል የሚጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ይህንኑ መብት በሰላማዊ እና በሰሞኑ ዐይነት አድማ ከእስካሁኑ በላይ ወደፊት መግፋት የሚቻል መሆኑ ያጠራጥራል፡፡
የባለፈው ሳምንት አድማ የተጠራው አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ “በሃብት ራስን መቻል” የሚል አጀንዳ ቀርጸው የኦሮሞ ወጣቶችን ቀልብ ለመሳብ ተከታታይ ጥረት ማድረጉን በተያያዙበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ ነው የሚባል ማሳመኛ ባይቀርብም አንዳንድ ወገኖች የኦህዴድ ካድሬዎች አድማውን በማነሳሳት እጃቸው እንዳለበት ይገምታሉ፡፡ አድማው በውጭ ሀገራት ባሉ ወይም በሀገር ውስጥ ባሉ ጸረ-ኦሕዴድ ወገኖች ብቻ የተመራ ከሆነ ግን ኦሕዴድ ራሱ በሚመራው ክልል ለሚደረጉት ህዝባዊ ንቅናቄዎች ባይተዋር ሆኖ መቀጠሉን እና በመከላከል ስራ ላይ ብቻ መጠመዱን መታዘብ ይቻላል፡፡
መንግስት ለዘጠኝ ወራት በመላ ሀገሪቷ ጥሎት የቆየውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያነሳ በመላ ሀገሪቱ የህዝብንና መንግስትን የዕለትተለት እንቅስቃሴ የሚያውኩ ድርጊቶችን ማክሸፍ እንደሚችል ተማመኖ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም አዋጁ ከተነሳ ገና ወር ሳይሞላው የአማራ እና ኦሮሚያ አድማዎች በተከታታይ መካሄድ ችለዋል፡፡ አድማዎቹ የመንግስት ጸጥታ ሃይሎችም ሆኑ የመንግስት ፖለቲካ መዋቅር ድንገተኛ ህዝባዊ አድማዎችን የማክሸፍ ብቁ ዝግጁነት እንደሌላቸው አጋልጠዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል በድንገተኛው አድማ የተደናገጠው መንግስት ምንም ዐይነት ርምጃ ሳይወስድ የኦሮሚያው አድማ በሦስተኛ ቀኑ መቋጨት የቻለው፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሚጠራ አድማ በሌሎች ክልሎች ከሚካሄዱ አድማዎች በተለየ ውጤታማ የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ባንድ በኩል ክልሉ ከበርካታ የሀገሪቱ ክልሎች ጋር ስለሚጎራበት በክልሉ የሚካሄድ ማንኛውም አድማ አዲሳባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ላይ ቀጥተኛ እና ፈጣን ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደሞ ክልሉ ግዙፍ ቆዳ ስፋት ያለው መሆኑ፣ የሀገሪቱ በርካታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱበት በመሆኑ እና ለዋና ከተማዋ መሠረታዊ ጥሬ እቃዎች እና የምግብ እህል አቅራቢ መሆኑ የሀገሪቱን ጸጥታ የማወክ እንዲሁም መሠረታዊ የኢኮኖሚ አውታሮችን የማሽመድመድ አቅሙ ላቅ ይላል፡፡ በተለይ የተራዘሙ አድማዎች ቢደረጉ ደሞ ሀገሪቱን ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኘው የባቡር ሃዲድ ሳይቀር ክልሉን አቋርጦ ስለሚያልፍ ለጊዜውም ቢሆን የሀገሪቱን ነዳጅ አቅርቦት እና አጠቃላይ የውጭ ንግድ ፍሰቱን በማስተጓጎል በመንግስት ላይ ጉዳት የማድረስ አቅም አያጣም፡፡

Related stories   “ትህነግ ከጁንታነትም ወርዶ በየጫካው ተሹለክላኪ የእህል ሌባ ሆኗል፣ ከያለበት እየታደነ ነው “ሜ/ጀ መሐመድ ተሰማ

ሙሉ ዘገባውን ከዋዜማ ያንብቡ ፤ ምስል ከዝግጅት ክፍሉ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *