በኢሬቻ በዓል ላይ ከሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሽህ በላይ ሰዎች መገኘታቸው በወቅቱ በተለያዩ ሚዲያዎች የተገለጸ አሃዝ ነበር። ይህ ሁሉ ሕዝብ በባህሉ መሰረት የልማዱን ለማድረገ የተመመው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ነው። በዚህ በዓል ላይ ከፈተኛ ቁጥር ያላቸው የፌደራልና የክልሉ የሰራዊት አባልት በተጠንቀቅ ቆመው እንደነበር የምስልና የቪዲዮ ማስረጃ አለ። ከዚም በላይ ጥይት ሲተኮስ እቦታው ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች መስማታቸውን መስክረዋል። አስለቃሽ መርዝመ ሲረጭ ነበር። ሕዝቡም ይህንኑ ሽሽት እግሬ አውጪኝ ሲል በቁጥር ስምምነት ባይደረስም ያለቀው አልቋል። ታዲያ ” በድንገት” የሚለው ሃረግ ከየት መጣ?

ለዛጎል የጽሁፍ መዕክት የላኩ የክልሉ ነዋሪዎች እንዳሉት ” ዝም ቢባል ይሻል ነበር” በሌላም በኩል ሃውልቱ ካካባቢው እርቆ የተሰራው ከወር በሁዋላ በሚደረገው ተመሳሳይ በዓል ላይ ሕዝብ ያፈርሰዋል በሚል ስጋት እንደሆነ ያመለከቱት ሰዎች ” እኛ በቦታው ነበርን። ሮጠው ካመለጡት መካከል እንደመራለን። የተኩስ ድምጽና አስለቃሽ መርዝ ሲፈነዳ ነበር። ይህ እውነት ነው። ታዲያ ሙታንን እናስብ እየተባለ ውሸትን መዋሸት የይቅርታን ልብ የሚያሻክርና የሚያጠቁር እንጂ ምስጋና የሚያሰጥ አይሆንም። ስለዚህም አንድ መላ እንዲባል ከወዲሁ እናሳስባለን” ይላሉ።

በወቅቱ ማይክራፎን በመቀማት ” ወያኔ ይውረድ” የሚል መፈክር አካባቢውን ሲያናጋው እንደነበር ሊሸሸግ እንደማይችልና ሙሉ ማስረጃ የሚቀርብበት ጉዳይ ነው። በተመሳሳይ ህዝብ መርዝ እየተረጨበት ራሱን ለማዳን ሲል ወደ ሞት መውረዱም የሚካድ አይደልም። ስለዚህም የአደባባዩን እውነት ለመካድ መሞከር እንደማያገባባ ነው አስተያየት የተሰጠው። ከዚህ በታች የጀርመን ድምጽ የዘገበው ዘገባ እንዳለ ለማመዛዘኛነት ታትሟል።

Related stories   ህወሃትና ኦነግ ሸኔ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ቀረበ

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ባለፈው ዓመት በኢሬቻ ክብረ በዓል ወቅት የሞቱ ሰዎችን ለማስታወስ ያሰራውን ሀውልት በትላንትናው ዕለት አስመርቋል፡፡ በወቅቱ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለማሰብ ሌሎች መርሃ ግብሮችም እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡ ትላንት በተመረቀው ሀውልት ላይ ላይ በድንገተኛ ሞት ህይወታቸውን እንዳጡ መጻፉ ግን ትችት ቀስቅሷል፡፡

erecha memorial 1.jpg

በሀውልቱ ላይ “ድንገተኛ ሞት” መባሉ ተተችቷል

በኢሬቻ ዓመታዊ ክብረ በዓል ወቅት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰራው ሀውልት የተመረቀው በቢሾፍቱ ከተማ ትላንት ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም ነው፡፡ ሀውልቱ የቆመበት ስፍራ 5,500 ካሬ ሜትር የሚሰፋ ሲሆን ዙሪያውን ተከልሎ በአረንጓዴ መናፈሻነት እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡ በመታሰቢያ ሀውልቱ የምረቃ ስርዓት ላይ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ እና የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ ሞሃመድን ጨምሮ ሌሎችም ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡

የክልሉ ፕሬዝዳንት በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር “የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ በሰላማዊ መንገድ አምላኩን የሚያመሰግንበት ብቻ መሆን አለበት” ማለታቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ በዚህ ዓመት ለሚካሄደው የኢሬቻ በዓል ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነም በስነ-ስርዓቱ ተገልጿል፡፡ መጪው የኢሬቻ በዓል እስከሚደርስ ባለው ጊዜ ባለፈው ዓመት በበዓሉ ላይ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ተጨማሪ የመታሰቢያ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ተነግሯል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት የመታሰቢያ ሀውልቱን ያስመረቀው የኢሬቻ ሰለባዎች አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ከመድረሱ አንድ ወር አስቀድሞ ነው፡፡ ትላንት በተመረቀው የመታሰቢያ ሀውልት ላይ ማቾቹ “በድንገተኛ ሞት” ህይወታቸውን እንዳጡ መጻፉ ግን ትችት ቀስቅሷል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ የዶይቸ ቬለ አድማጮች እና የማህበራዊ ድረ ገጽ ተከታታዮች ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

Related stories   የኢትዮጵያ “ትንሣኤዋን እውነተኛ ልጆቿ እንጂ ጠላቶቿ ወዲያው አያዩትም” ተመስገን ትሩነህ

የድሬዳዋ ነዋሪ የሆኑ ታረቀኝ የተባሉ አድማጭ “ይሄ ትንሽ ከባድ ነው፡፡ በምንም ተዓምር በአጋጣሚ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በሚሊዮን በሚቆጠር ህዝብ ላይ እየተተኮሰበት እነዚህን በአጋጣሚ ሞቱ ለማለት፣ ደፍሮ እንደዚያ ለማለት ትንሽ የሚከብድ ነገር ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በዚህ ዙሪያ ያጻፈው መልዕክት ተገቢ አይደለም፡፡ መሰረዝ አለበት የሚል አስተያየቴን ለመግለጽ እወዳለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን በዋትስ አፕ ልከውልናል፡፡

በድምጽ አስተያየት ከላኩልን አድማጮቻችን ውስጥ ስማቸውን ያልገለጹልን አንድ ግለሰብ በኢሬቻ ለደረሰው ሞት መንግስትን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ “ሰው ራሱ ያደረገውን መልሶ እንዳላደረገ፣ ከኃጢያት እና ከስህተት ራሱን ለማውጣት የእዚህን አይነት ሙከራ ማድረጉ ሰውን በጥፊ መትቶ እንዳያለቅስ መከልከል ይመስለኛል፡፡ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም” ይላሉ አድማጫችን፡፡

Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten (REUTERS/T. Negeri)

ስማቸውን ያልጠቀሱ ሌላ አድማጭም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ “በኦሮሚያ ክልል የተሰራው ሀውልት በጣም የሚያስቅ ነው፡፡ ይሄ ታሪክ አይደለም፡፡ እኔው ገድዬ እንደገና ሀውልት ለሰው ልሰራ ነው? ይሄ አስጸያፊ ነገር ነው፡፡ ሀውልት ከሚሰራላቸው ይልቅ በደንብ ይቅርታ ቢጠይቅ ጥሩ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ፣ ለሀገርም፣ ለህዝብም ምንም የማይጠቅም ነው፡፡ በዚህ ወጪ ሌላ ብዙ ነገር ቢያደርግላቸው ይሻል ነበር” ብለዋል፡፡

ሀውልት መሰራቱን የሚደግፉት ሌላኛው አድማጫችን ደግሞ የክልሉ መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች መፍታት አለበት ይላሉ፡፡ “እንደዚህ አይነት ነገር ጥሩ ሆኖ እዚህ ላይ 10 ኪሎ ሜትር ርቆ ነው የተሰራው፡፡ መሰራት ያለበት ቦታው ላይ ነው፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመበት ቦታ ላይ ነው፡፡ መስራቱ፣ አለመስራቱ ላይም አይደለም፡፡ ለቀጣይ ዓመት ወይም ለቀጣይ ወራት ምን ዓይነት ስራ ነው የሚሰራው? እዚያ [ቦታ] ላይ ድጋሚ እንዳይከሰት መንግስት ትልቁን ሚና መጫወት አለበት” ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡

Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

erecha memorial 2

በኢሬቻ ክብረ በዓል ወቅት ስለሞቱ ሰዎች ብዛት እና መንስኤው በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ መረጃዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሚያዝያ ወር ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የምርመራ ዘገባ እንዳመለከተው በበዓሉ የተሳተፉ ሰዎች ብዛት ሁለት ሚሊዮን 500 ሺህ ገደማ ይሆናሉ፡፡ እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ በወቅቱ በተፈጠረው “ብጥብጥ” 56 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ አስሩ ሴቶች መሆናቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ በበዓሉ ወቅት የነበረውን “ብጥብጥ” ለማርገብ “የጸጥታ ኃይሎች ከአስለቃሽ ጭስ ውጭ የተጠቀሙት ኃይል የለም፡፡ የወሰዱትም እርምጃ ተመጣጣኝ ነው” ሲል ከተለያዩ ወገኖች የሚቀርቡትን ውንጀላዎች አስተባብሏል፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን የጸጥታ ኃይሎች “ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ተጠቅመዋል” ባይ ናቸው፡፡ የሟቾቹም ቁጥር በመንግስት ከተገለጸው በላይ እንደሆነ ይሟገታሉ፡፡

ሀውልቱን አስመልክቶ የተነሱ አስተያቶች ላይ ምላሽ ለማግኘት ወደ ኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እና ምክትላቸው ጋር በተደጋጋሚ ብንደውልም ምላሽ አልሰጡንም፡፡ በተመሳሳይ ወደ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እና ወደ ቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ያደረግነው ሙከራም አልተሳካም፡፡

ተስፋለም ወልደየስ  አርያም ተክሌ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *