“Our true nationality is mankind.”H.G.

 የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት – ጥሪ፣ ችሎታ፣ ወይስ ሹመት?

          “ከማይኾን ሹመት የሚመነጭ እኩይ ፍሬን እንደማየት አስከፊ ነገር የለም፡፡ በአንጻሩ፥ ችሎታ ያለው፣ ሠናይ እና ፍትሐዊ የኾነ ሰው በቦታው ላይ ሲሠየም እንደማየት በእጅጉ ደስ የሚያሰኝ ነገር የለም፡፡” (ቻርለስ ደብሊው ኤሊየት፣ ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ 1869)

Image result for doctor dagnachew
 ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

የአድማሱ ጸጋዬ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት መነሣት፣ ለተቋሙ እንደ አንድ ትልቅ ዕድል ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ተወስዷል፡፡ ይኹን እንጂ፣ በቅርቡ በየብዙኃን መገናኛው በሰፊው እንደተሰማውና፣ በፓርላማ ፊት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው፣ “የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ2007 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ሪፖርት ውጤት” መሠረት፣ በዩኒቨርሲቲው ከፍ ያለ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ ችግሮች በመገኘታቸው፣ የቀደሙት ዐሥር ያህል ዓመታት ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አስፈልጎ፣ ከውጪ ልዩ ኦዲተር ተሠይሞ፣ በምርመራ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት፤ እኛም እንደ ዜጋ፤ “የዐቃቤ ሕግ ያለህ!” እያልን በምጮንህበት በዚህ ሰዓት፣ መንግሥት ፕሬዝዳንቱን “አምባሳደር” ብሎ በመሾም ከዐይን እንዲርቁ ማሸሹ፣ ብዙ ቁጭት እና ንዴት ቀስቅሷል፡፡ ይህ ድርጊት ከሞራል አንጻር ሓላፊነት የጎደለው ውሳኔ ይመስላል፡፡
በተጨማሪም፣ ነገሩን አስገራሚ የሚያደርገው፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ ለአዲሶቹ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ሲሰጡ፣ ይህን እውነታ ወደ ጎን ባደረገ መልኩ፣ በታላቅ የምስጋና ቃላት የተመላ “ቃለ-ቡራኬ” መስጠታቸውም ጭምር ነው፡፡ የሌሎቹን ተሿሚዎች ትቼ፣ አድማሱ ጸጋዬ እና አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ በውዳሴ የተመላው “ቃለ ቡራኬ” ተቋዳሽ መኾናቸው፣ በእጅጉ አስገራሚ ኾኖ አግኝቼዋለኹ፡፡ በተለይ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በቦርድ ሊቀ መንበርነት፣ አድማሱ ጸጋዬ ደግሞ በፕሬዝዳንትነት ይመሩት የነበረው ዩኒቨርሲቲ፣ ከላይ የተገለጸው ዓይነት፣ ከፍ ያለ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ ችግሮች እንደተገኘበትና እነዚህ ተሿሚ ግለሰቦችም፣ ማንም እንደሚገምተው፣ በቀዳሚነት ሓላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው፣ ብሎም ከመወደስ ይልቅ ተወቃሽነታቸው የሚያመዝን ኾኖ ሳለ፤
“…በከፍተኛ የሀገር ስሜት የተጣለባችሁን ሓላፊነት ስትወጡ እንደነበረ ሁሉ፣ ወደፊትም በተሰማራችሁበት የዲፕሎማሲ መስክ ስኬታማ እንድትኾኑ እመኝላችኋለሁ፡፡…” የሚል፣ በአድናቆት የታጀበ “ቃለ ቡራኬ” እና መልካም ምኞት፣ ከኢፌዴሪው ፕሬዝዳንት አንደበት ሲቀበሉ መስማት፣ ፕሬዝዳንቱ የሚያቀርቡትን ንግግር በጥርጣሬ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላይ የተሠራው ይፋ የወጣ ጥፋት የሚያጠያይቀውን ያህል፣ አሁን ደግሞ፤ የዩኒቨርሲቲው የፕሬዝዳንት ቦታ ገና ክፍት እንደኾነ በማመን፣ አዲስ ተሿሚ ከመሠየሙ በፊት ትኩረት የሚሹ ወሳኝ ጉዳዮችን ማዘከር አስፈላጊ ኾኖ ይታያል፡፡ ከዚህም አንጻር፣ ይህን ጽሑፍ ማቅረብ ወቅታዊና ተገቢ ኾኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በተጨማሪም ይህ ጽሑፍ፣ ከላይ በጥቅስ እንደተቀመጠው፣ ችሎታ ያለው ሰው በቦታው በሚሾምበት ጊዜ ደስ ማሰኘቱ እንደማያጠያይቀው ኹሉ፣ እኔም እንደ አንድ ዜጋ፣ ለወደፊቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተሻለ ሰው እቦታው ላይ ቢቀመጥ/ብትቀመጥ፤ ለሀገርም፣ ለተቋሙም፣ ብሎም ለመላው ማኅበረሰብ በእጅጉ ይበጃል፤ ከሚል እሳቤ የማቀርበው ጽሑፍ ነው፡፡ እዚህ ላይ ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት፣ ስለ ጽሑፉ የአቀራረብ መንፈስ የሚገልጹ፣ ኹለት ነጥቦችን ላንሣ፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቀራረብ በኹለት መደብ የተከፈለ ነው፡፡ በመጀመሪያ፣ የዩኒቨርሲቲን ትርጉምና ምንነት በጥቂቱ ከገለጸ በኋላ፤ ምን ዓይነት የትምህርት፣ የልምድ፣ የአስተዳደርና የሞራል እርካብ ያለው ሰው ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት መታጨት እንዳለበት በኹለተኛ ደረጃ ያትታል፡፡ በመጨረሻም፤ አጠር ያለ መደምደሚያ በማቅረብ ያጠቃልላል፡፡
የጽሑፉ አቀራረብ መንፈስ፣ በቀዳሚነት የሚነሣው፣ አሁን በገሐድ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ በማተኮር ብቻ ሳይኾን፣ ዩኒቨርሲቲ በሐሳብ ዓለምም ውስጥ ምን ሊኾን እንደሚገባው፤ ከማጠየቅም ጭምር ነው፡፡ በመኾኑም፣ “ዩኒቨርሲቲ ምንድር ነው?” ብለን መጠየቅ ብቻ ሳይኾን፣ ጥያቄያችንን ሰፋ አድርገን፣ “ዩኒቨርሲቲ ምን መምሰል አለበት?” የሚለውንም መጠየቅ በእጅጉ የተገባ ይኾናል፣ ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ አጠይቋዊ ትንታኔ፣ አቀራረባችንን ታሪካዊ ይዘት ካለው የወግ አተራረክ፣ ወደ ፍልስፍናዊ የአጠይቆ ሐቲት እንዲሸጋገር ያደርገዋል፡፡
ኹለተኛው አቀራረብና መንፈስ ደግሞ፤ በዚህ ጽሑፍ የማቀርበው ሐተታ ለውይይት እና ለሒሳዊ ትችት አንባቢን የሚጋብዝ ነው፡፡ ይህን ሐቲት ሳቀርብ፣ ራሴን ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ እንደኾንኩ በማሰብ ሳይኾን፣ ለትቺና ሙግት ዝግጁ መኾኔን በማስታወስም ጭምር ነው፡፡ ይኸውም፣ ከሒስ በእጅጉ ተጠቃሚ እኾናለሁ፤ የሚል ልባዊ እምነት ስላለኝ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲ ምንነት እና ተገብሮ፣
ይህ ሐሳብ፣ በ20ኛው መ/ክ/ዘመን አጋማሽ ላይ፣ በፕሮፌሰር ኤድገር ደብልዩ. ናይት የተሰበሰበውና አሁን እንደ ወትረ ህልው(ክላሲክ) ድርሳን የሚታየውን፣ “What College Presidents Say” በሚል ርዕስ፣ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ በመቶ ዓመታት ውስጥ፣ በአጠቃላይ ስለ ኮሌጅ ፕሬዝደንሲ የተናገሩትን ሐሳብ የያዘውን መድበል በመመርኮዝ የቀረበ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲን ምንነት አጠይቆ ይዘን ለመነሣት የምንገደደው፣ ዩኒቨርሲቲን ማን ይምራው? የሚለው መጠይቅ፣ “ከዩኒቨርሲቲ ምንነት” ተነጥሎ ስለማይታይ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲን ምንነት በተመለከተ፣ ኹለት ተፎካካሪ ፍልስፍናዎችን እናገኛለን፡፡ ኹለቱም በዩኒቨርሲቲ ምንነትና ፍልስፍና ላይ ኹነኛ አሻራ የተዉ ፍልስፍናዎች ናቸው፡፡ አንደኛው፥ ዩኒቨርሲቲን ከኀልዮታዊ (ሥነ ሐሳባዊ) ትኩረት አንጻር የሚያይ ሲኾን፣ ኹለተኛው ደግሞ፣ ዩኒቨርሲቲን በግብራዊ(ፕራክቲካል) መደቡ የሚቃኝ ወይም የሚፈትሽ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን የተደረሰበት፣ የዩኒቨርሲቲን ምንነት የተመለከተ ስምምነት ግን፣ ኹለቱንም አዝማሚያዎችና ተቃርኖዎች አዋሕዶ ወይም አቻችሎ ማስኬድ አስፈላጊ እንደኾነ ያረጋግጣል፡፡
ከ100 ዓመታት በፊት፣ ካርዲናል ኒዩማን፣ “The Idea of A University” በሚለው አስደናቂ ድርሰታቸው ፣ ለዩኒቨርሲቲ የሚከተለውን ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ ዩኒቨርሲቲ፥ “ዕውቀት፣ ሳይንስ፣ መረጃ፣ መርሕ፣ ምርምር፣ ግኝት፣ ሙከራ፣ የመላምት ግኝት እና የአእምሮን መልክአ ሐሳብ …ወዘተ. የሚዘረጋ ተቋም፣ ነው፡፡” ስለኾነም ለካርዲናሉ፤ ዕውቀት በራሷ የምንሻትና አቅደን ለመጎናጸፍ የምንጥርባት መዳረሻ ናት፡፡ ሌላ ተቀጥያ ዐቅድ አያስፈልጋትም፡፡ እንደ ካርዲናሉ አባባል፣ የትምህርት ዓላማ እና ግብ፣ “ትምህርት” ራሷ ብቻ ናት፤ ማለት ነው፡፡
በአንጻሩ አብርሃም ፍሌክስነር፣ “The Idea of A Modern University” በሚል ጽሑፋቸው ላይ፣ ቀደም ያለውን ሐሳብ የሚቃረን ሌላ ጽንፍ ያሳዩናል፡፡ እንደ ፍሌክስነር፣ ዩኒቨርሲቲ ማለት፣ “የተወሰነ ግብ እና ዓላማ ይዞ፣ ለማኅበረሰቡ ረብሕ፣ ተጨባጭ ነገር የሚያበረክት ተቋም ማለት ነው፡፡” ዩኒቨርሲቲ ከማኅበረሰቡ በላይና ባሻገር ለብቻው ተነጥሎ የሚቀመጥ ተቋም አይደለም፡፡ የሰውን ልጅ ለመጥቀም፣ የጊዜውን መንፈስ አቅፎ የያዘና ምርምርን ማዕከል አድርጎ የሚንቀሳቀስ ከመኾኑም በላይ፣ ወደ ውጤት ለመተርጎም ምንጊዜም የተሰናዳ ተቋም ነው፤ የሚል ንጻሬ አላቸው፡፡አሁን የተደረሰበት አስተሳሰብ፣ ኹለቱን የአመለካከት አፍላጋት ያዋሐደ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ከዚህ ተነሥተው፣ ስለ ዩኒቨርሲቲ ምንነት ረዘም ላለ ጊዜ ጥናት እና ምርምር ያካሔዱ አሳቢዎች እንደሚነግሩን፣ የተቋሙ ተቀዳሚ ተልዕኮ፣ ሦስት ክፍሎችን የያዘ ነው፡፡ እነርሱም፤ አንደኛ፡- ዕውቀትን ለመጨበጥ መሻትን፣ ኹለተኛ፡- የተገኘውን ዕውቀት ለተማሪዎች ማስተላለፍን፣ ሦስተኛ፡- ዕውቀትን መተግበርን የሚሉ ክፍሎች ናቸው፡፡
አንድ ዩኒቨርሲቲ፣ በምንም መልኩ የተመሠረተበትን የአእምሯዊ ፍጽምና ማሕቀፉን (አይዲያል) መልቀቅ የለበትም፡፡ ይህንንም ዓላማ በሚገባ ለመተግበር ሲባል፣ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አካዳሚያዊ ነጻነት ያለገደብ እንዲሰጥና እንዲታወቅ የግድ ይላል፡፡ በተጨማሪም፣ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ የበጀት አቅራቢዎችን ግዳጅ ፈጻሚ ብቻ ሳይኾን፣ የራሱን ዓላማ አንግቦ የሚንቀሳቀስም ተቋም መኾን ይገባዋል፡፡
ተቋም ስንል፡-
የምንፈልገው ግብ ላይ ለመድረስ፣ ያሰበነውንና የወጠንነውን አካላዊ ህልውና የምንሰጥበት ነው፡፡ የትምህርት እንቅስቃሴም፤ ኮርሶችን፣ ካሪኩለሞችን፣ ፈተናዎችን፣ ዲፕሎማዎችን፣ ዲግሪዎችን ወዘተርፈ. ይዞ አካዳሚያዊ ሕይወትን እውን የሚያደርግ ነው፡፡ ተቋምን በአንድ ዐረፍተ ነገር መግለጽ ቢያስፈልግ፣ “የታሰበ ወይም የተወጠነ ዕቅድን፣ እንዲተገበር ወይም እውን እንዲኾን የሚያስችል፣” ማለት ነው። ያለተቋም፣ ሐሳብ ብቻውን ሕያው ሊኾን አይችልምና።
ዩኒቨርሲቲ ርእዩን በተቋሙ አማካይነት ገቢራዊ ማድረግ ካልቻለ፣ ርእዩ ብቻውን ትርጉም ያጣ ይኾናል። በመኾኑም ያንድ ዩኒቨርሲቲ የደረጃ ኹኔታ የሚለካው፣ በገነባው ተቋማዊ ብቃት ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን፣ ተቋሙ የዩኒቨርሲቲን ፍጹማዊ ቅርጽና መልክ (አይዲያል) በተሟላ መልኩ ይይዛል ማለት አይደለም። ስለዚህ፣ በዩኒቨርሲቲው “አይዲያል” እና “በተቋማዊ  አደረጃጀቱ” መካከል ውጥረት መኖሩ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ኹለቱን ለማጣጣም በየጊዜው ሒሳዊ ፍተሻ በራሱ ላይ ማካሔድ ይኖርበታል፡፡
የሰዎች ሚና፡-
ያለ ሰው፣ ተቋም ብቻውን ምንም የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ ስለኾነም፣ በተቋሙ አወቃቀር ውስጥ የሰዎች ሥፍራ ወይም ሚና ምን ይመስላል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አንድ ዩኒቨርሲቲ ወደ ልቅናው የሚመነደገው በውስጡ ባሉት ምርጥ ምሁራንና እነርሱም የማስተማር ተግባራቸውንና ምርምራቸውን ለማካሔድ የሚያስችል ምቹ ኹኔታ መፍጠር ሲችል ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲውና በውስጡ ባሉት ሰዎች መካከል የሚታየው ባሕርይ፣ ተወራራሽና አንዱ በአንዱ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ፣ የተለያዩ ዓይነት ቅራኔዎችን የተሸከመ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፣ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስላሉት ቅራኔዎችና ውጥረቶች ካቀረቡበት፣ “Powers of The Mind: The Renovation of Liberal Learning in America.” ከተሰኘው መጽሐፋቸው፣ አንዳንድ የትችት ነጥቦችን እንደ ዳራ በመውሰድ፣ እኔም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ አሉ ብዬ ስለማምናቸው ውጥረቶች በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ዩኒቨርሲቲ በኹለቱ ምክንያታዊነቶች መካከል፤
ዩኒቨርሲቲው እንደ አንድ የጥናት ተቋም በሚያቀርበው “ምክንያታዊነት” እና በበጀት አቅራቢው “ምክንያታዊነት” መካከል ውጥረት ይታያል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እንደ ጥናት ተቋምነቱ የራሱ ጥሪ ይኖረዋል። በጀት አቅራቢው አካልም የራሱ ፍላጎት ይኖረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ምክንያታዊነት ለፈተና የሚዳረገውና ህልውናውም አጠያያቂ የሚኾነው፣ የተነሣበትን ዓላማ እና ግብ ወደ ጎን ትቶ፣ የበጀት አቅራቢውን ፍላጎት ለማስፈጸም ሥምሪት ሲያደርግ ነው። ይህ በሚኾንበት ጊዜ፣ የዩኒቨርሲቲው “ምክንያታዊነት” ለበጀት አቅራቢው “ምክንያታዊነት” መሥዋዕት እንዲሆን ተፈረደበት ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ውስጥ በገሐድ የሚታየው እውነታ ይኸው ነው፡፡
ለማሳያነት የሚከተሉትን እንጥቀስ፤ የዩኒቨርሲቲውን የተማሪ ቅበላ በተመለከተ፤ ብዛቱን የመወሰን ቀጥተኛ ሓላፊነት፣ የትምህርት አስተዳደሩ ድርሻ ኾኖ ሳለ፣ መንግሥት የፈለገውን ቁጥር ያህል ተማሪዎች እንዲገቡ መደረጉ፣ በትምህርቱ ጥራት ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ችላ መባሉን ያሳያል፤ አንድን ዩኒቨርስቲ ብቁ ነው የሚያሰኘው፣ የመምህራን ችሎታ ብቻ ሳይኾን፣ ጥራትና ተወዳዳሪነት ያላቸውን ተማሪዎችንም ሲቀበል ነውና፡፡ አሁን ያለው የትምህርት ፖሊሲ ግን፣ በብዛት ላይ የተመረኮዘ በመኾኑ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች የቅበላ አቅም በላይ ተማሪዎች እንዲገቡባቸው እየተደረገ ነው፡፡
በኹለተኛ ደረጃ፡- የትምህርት ውጤት አሰጣጥ፣ ከአስተማሪዎች ቁጥጥር ውጪ በኾነ መልኩ፣ በስኬል እንዲወሰን ከመደረጉም በላይ፣ መምህሩ ተማሪዎችን በውጤት አሰጣጥ ‘ደግፎ’ (የማይገባቸውም ቢኾኑ) እንዲያሳልፍ መገደዱ፤ ሦስተኛው ግልጽ ማሳያ፤ ተማሪዎችም ኾኑ መምህራን “የአንድ ለአምስት አደራጃጀት” ተሳታፊ እንዲኾኑ መደረጉ የመሳሰሉት፤ “የዩኒቨርሲቲው ምክንያዊነት” አደጋ ውስጥ ለመውደቁ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በሊብራል ትምህርት እና በሞያ
ትምህርት መካከል፤
‘በንድፈ ሐሳብ’ እና ‘በተግባር መካከል’፣ ‘በቁጥር’ እና ‘በጥራት’ መካካከል ውጥረት ይታያል፡፡ የነገረ ሰብእ፣ የሥነ ጥበብ፣ የፍልስፍና እና የታሪክ፣ በአጠቃላይም፤ የማኅበረሰብ ሳይንስ ትምህርቶች ወደ ጎን ተገፍተው፣ በተግባራዊ ሳይንስ፣ “ችግር ፈቺ ናቸው፤” ተብለው ለተቀመጡ ትምህርቶች ብቻ የተሰጠው ትኩረት፣ በንድፈ ሐሳብ እና በተግባር የትምህርት አዝማሚያዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው የተፈጠረውን ውጥረት የሚያሳይ ነው፡፡
መኾን ይገባዋል ብዬ የማምነው ግን፣ ምሁራዊና ተግባራዊ መንገዱን አቻችለውና አጣምረው መጓዝ የሚችሉ ምሉዓን ተማሪዎችን የማፍራቱ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ማለት፥ ትጉህ፣ ውጤታማና የተኮተኮተ አእምሮ ያላቸው ዜጎች ማውጣት የዩኒቨርሲቲ ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን ይገባል፣ ማለት ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰባዊ ጥቅም እና በብሔር ጥቅም መካከል፤
የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰባዊ (ኮምዩኒያል) ጥቅም፣ የበላይነት መያዙ ቀርቶ፣ የግልና የብሔር ጥቅም የሰፈነበት ግቢ ኾኗል፡፡ ይህም የግልንና የብሔርን ጥቅም ማሳደድ፣ ያልታወጀ ሕግ ኾኗል፡፡ እዚህ ላይ ሦስት ማሳያዎችን እንጥቀስ፤
ሀ. “ብሔርተኝነት”፡-
በሀገራችን፣ በፖለቲካ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደሚታየው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ “በብሔር” እና “በዜጋ” መካከል ትልቅ ፍጥጫ አለ፡፡ ከግቢው ውጪ፣ “ብሔርተኝነት”፣ “ከሀገራዊነት”፣ የበለጠ የበላይነት እንደያዘው ኹሉ፤ በዩኒቨርሲቲውም፣ ብሔሮች በዜጎች ላይ ፍጹም የበላይነት አላቸው፡፡
“ብሔርተኝነትን” በመገለጫነት የያዙት ወገኖች፣ ጎሣንና ነገድን በበላይነትና እንደ ማንነት ብቸኛ መገለጫ በመያዝ፣ “ኢትዮጵያዊነትን” ባልተገባ መልኩ፣ የቀጨጨ ትርጉም እንዲይዝ ያደረጉት ሲኾን፤ የኹሉ ነገር መመልከቻ መነጽራቸው፣ ከብሔራቸው ህላዌና ተጠቃሚነት አኳያ ብቻ በሚመነጭ እይታ የተቃኘ ነው፤ ማለት ነው፡፡ በአንጻሩ “ዜግነትን” የያዙት ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊነትን የምሉዕ ማንነታቸው ኹለንተናዊ መገለጫ በማድረግ የተቀበሉት ናቸው፡፡
በዩኒቨርሲቲው የሚታየው የብሔርተኝነት መንገሥ፤ ጠንካራ ፍልስፍናዊ ምርኩዝ የያዘ ሳይኾን፣ ከቅጽሩ ውጭ ባለው መንግሥታዊ የፖለቲካ ድጋፍ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህን ውጫዊ አቅም በመተማመን፣ ብሔር ዘመሞቹ፣ በግቢው ውስጥ፣ በዜጎች ላይ ጫና እና ግፊት ያሳድራሉ፡፡
ለ. የአስተማሪዎች ግለኝነት፡-
በመሠረቱ፣ የአስተማሪነት ተቀዳሚ ዓላማ፣ ማስተማርና ምርምር ሲኾን፣ መምህራኑም ሙሉ ጊዜያቸውን እዚህ ተግባር ላይ ማዋል እንደሚኖርባቸው ያጠይቃል፡፡ አኹን በየኒቨርሲቲው የሚታየው የአብዛኛው መምህራን አካሔድ ግን፣ በግል ጥቅም ሩጫ የተጠመደ ኾኗል፡፡ ከማስተማሩ ይልቅ፣ ከመንግሥት እስከ ግል ተቋማት ድረስ በሞያቸው ተሠማርተው እየሠሩ ስለሚገኙ፣ “በማኅበራዊ ሠናይነት” እና “በአስተማሪዎች ግለኝነት”፣ መካከል ቀላል ያልኾነ መገዳደር ይታያል፡፡
ሐ. የተማሪዎች፣ የተማሪነት ዲሲፕሊን ድቀት፡-
በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ፣ በፈተና የተማሪዎች መኮራረጅና የጥናት ጽሑፎችም ግልበጣ በገሐድ እየታየ ነው። ተማሪዎች፥ ያልሠሩትን እንደሠሩ፣ ያልጻፉትን እንደጻፉ፣ ያልተመራመሩትን እንደተመራመሩ እያደረጉ የማይገባቸውን ውጤት ለማግኘት እየተሯሯጡ እንደ ኾነ ማስተዋል ብዙም አይከብድም፡፡
በመኾኑም፤ በአንድ በኩል፣ ለማወቅ በመፈለግ፣ በትጋት እና በድካም ለማደግ፣ በሌላ በኩል፤ ያለልፋትና ያለድካም ውጤት ለማግኘት በሚደረግ የትንቅንቅ ጉዞ መካከል ግልጽ ቅራኔ የሚታይበት ግቢ ኾኗል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ልቀት እና ዝቅጠት(Excellence vs. Mediocrity) መካከል ያለ ውጥረት፤
የዚህ ውጥረት መገለጫዎች በመምህራኑም ኾነ በተማሪዎቹ ላይ የሚታዩ ናቸው፡፡
ሀ. የዩኒቨርሲቲ መምህራን፡-
ዩኒቨርሲቲ በመሠረቱ የልሂቃን ማዕከል ነው። እዚህ ተቋም ውስጥ በምሁራዊነት ለመሠየም ልሂቅነት ያሻል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የቆየ ባህልም ይህንኑ ልማድ የሚያመለክት ነው፡፡ አሁን ግን ልሂቃዊነት እንደ መሥፈርት መወሰዱ ቀርቶ፣ የፖለቲካ ቅርርቦሽ ተተክቷል፡፡ የትምህርት ውጤታቸው ዝቅተኛ ቢኾንም፣ በፖለቲካ አስተዋፅኦና በብሔር ተዋፅኦ ተመርጠው በመምህርነት መንበር ላይ እንዲቀመጡ ኾነዋል። ይህ ዓይነቱ አካሔድ፣ በልሂቃዊነትና በጥራዝ ነጠቅነት መካከል ትልቅ መገዳደር እንዲከሠት አድርጓል፡፡
ለ. ተማሪዎች፡-
እንደ ደራሽ ውኃ እየጎረፉ በሚገቡት ተማሪዎችና የትምህርቱን ጥራት በማስጠበቅ መካከል ትልቅ ውጥረት አለ፡፡ አንዳንድ ፈላስፎች ይህን ዓይነቱን መጥለቅለቅ፣ “ሶሻል ሱናሚ” ይሉታል፡፡ በብዙዎች ትችት ውስጥ፣ የጥራት እና የቁጥር ተቃርኗዊ ወደር ተደጋግሞ ይነሣል። ኾኖም ጥራት ስንል፣ በተቀመጠው ግብ የሚለካ በመኾኑ፣ የጥራት ጥያቄ ከትምህርት ዓላማ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህም ማለት፣ ጥራት የሚለካው፣ የትምህርትን ዓላማ እና ግብ መሠረት በማድረግ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት በቀደሙ
ፕሬዝዳንቶች ዐይን፤
“አንድ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወጣት ፕሬዝዳንት፣ ዕድሜው ከገፋና ለዓመታትም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ከነበረ ሽማግሌ ጋራ ስለ ዘመነ ፕሬዚደንሲያቸው አስቸጋሪ ጊዜያት ሲወያዩ፣ ወጣቱ ፕሬዝዳንት፣ ‘ለእኔ የመጀመሪያ ዓመቱ ዘመኔ በጣም ከባድ ነበር፣’ ይለዋል። ሽማግሌው ቀበል አድርጎ፣ ‘በእኔ ተሞክሮ ደግሞ፣ ሦስተኛው ዓመት ላይ ነው እንደ ፕሬዝዳንት ችግር የገጠመኝ፤ ምክንያቱም፣ ሦስተኛ ዓመት ላይ መምህራኑ በሙሉ ውሸታምና አጭበርባሪ መኾኔን አወቁብኝ’ ይለዋል፡፡” (The College Presidents. p,16.)
የእኛው ‘ጎበዝ’ ግን፣ ዕድለኛ ኾኖ፣ እንደ ሽማግሌው ፕሬዚዳንት፣ በሦስተኛው ዓመትም ባይኾን፣ በስድስተኛው ዓመት ላይ፣ አብዛኛው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ማንነቱን ሊረዱት ችለዋል፤ ከጥቂት ካድሬዎች በስተቀር፡፡
ከላይ በጠቀስነው የፕሮፌሰር ኤድገር ደብልዩ ስብስቦች፣ የሚከተለው የሐርቫርድ ፕሬዝዳንት ቻርለስ ደብልዩ ኤልየት ጥቅስ ይገኛል፡-
“ዩኒቨርሲቲ ለዓምባገነኖች በእጅጉ የራቀ ቦታ ነው። መማር በባህርይዋ ሪፐብሊካን ናትና፡፡ በትምህርት ዓለም የምናደንቃቸው እና የምናከብራቸው ሰዎች ይኖራሉ እንጂ፣ እንደ ጌቶች የምንወስዳቸው ሰዎች አይኖሩም፡፡”
ከኹሉ አስቀድሞ፣ ዩኒቨርሲቲን በበላይነት የሚያስተዳድሩ ሰዎች፣ በሥራቸው የሚገኘውን የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ፣ በእኩል ዐይን ማየት ይገባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ፣ የአንድ ሓላፊ ድርጊት፣ ሰውን በእኩልነት ከማየት የሚመነጭ እንጂ፣ ከወገናዊነት አንጻር የሚፈጸም ሊኾን አይገባውም። የድርጊቱ መሠረትም፣ ሕግን ለኹሉ እንዲኾን አድርጎ እንደሚያወጣ ሕግ አውጪ መርሐዊነት ሊቃኝ ይገባል። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ፣ ለአጠቃላይ የተቋሙ ፍላጎት ሲል፣ ጓደኞቹንም ኾነ ወገኖቹን የሚያስቀይም እንኳ ቢኾን ወደ ኋላ ማለት አይኖርበትም፡፡
አንድ ፕሬዚዳንት፣ ሩኅሩኅ ጠባይ ሊኖረው ይገባል። ይህም ማለት ራሱን በሌሎች ቦታ አድርጎ፤ “እኔ በዚህ ቦታ ብኾንስ” ብሎ ራሱን በሌሎች ጫማ ውስጥ ከትቶ የሚያይ ሲኾን፣ የሥነ ልቡና ሊቃውንት “የማስተዋል ሐሞት”(perceptual courage) የሚሉት፣ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ፣ ይኸው የማስተዋል ሐሞት እንዴት እንደሌላቸው ደጋግመን በተለያየ ጊዜ አይተናል፡፡ ከኹሉም በላይ፣ ማንም በማይስተው መልኩ ያሳዩትን ሞራላዊ ድቀት እንጥቀስ። እንደሚታወቀው ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ዩኒቨርሲቲውን ከ30 ዓመታት በላይ አገልግለው 60 ዓመት ሲሞላቸው፣ የኮንትራት ዕደሳ ሊሰጣቸው ይገባ ነበር፡፡ ዲፓርትመንቱና ኮሌጁም እንደሚፈልጋቸው በደብዳቤ ማሳወቁም ይታወሳል። በምትኩ ግን፣ በአድማሱ ጸጋዬ ውሳኔ ያለምንም በቂ ምክንያት፣ ከዩኒቨርሲቲው ተባረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ቢሮና መንበር ዘላለማዊ ሳይኾን ጊዜያዊ ነው፡፡ በዚህች ውስን ጊዜ የምትሠራውና የምትወስነው አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ጉዳይ ግን፣ ዘላቂ አንድምታ ሊኖረው ይችላል ብለህ አስብ፡፡ የትኛውም ዓይነት ሓላፊነት ላይ ስትኾን፣ የውሳኔህ ወይም የተግባርህ ስኬት በጎም ይሁን መጥፎ፤ ለታሪክ ሚዛን ትቶ ማለፍ ተገቢ ነው፡፡
አንድ ፕሬዝዳንት፣ በምክክር ሊያምን ይገባዋል። ይህ ማለት ግን ከአማካሪዎቹ ጋራ በአንድነት መወሰንን አይመለከትም፡፡ ውሳኔ በጎ የሚኾነው፣ ፕሬዝዳንቱ የብቻውን ጥሞና ወስዶ፣ አሰላስሎ የሚደርስበት ሲኾን ነው። ጽሞናው፣ ያገኛቸውን ምክሮች የሚመዝንበትን ዕድል ይሰጠዋል። ፕሬዚዳንቱ፣ በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ውስጥ፣ በአንድ በኩል ተሳታፊ በሌላ ጎኑ ደግሞ ገለልተኛ መኾን ይኖርበታል።
ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጀምሮ፣ እስከ ዛሬ ያልተሻረው የአስተዳደር ብሂል፣ ሥልጣንን በተዋረድ የመወከሉ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ የአስተዳደር ሓላፊ ኹሉንም ነገር፣ “እኔ ብቻዬን እፈጽመዋለኹ፤” ብሎ ከተነሣ፣ ምናልባት ጥቂት ነገር ይፈጽም ይኾናል፡፡ ይችውም ጥቂት ተግባር ግን ዘላቂና የተሟላች ለመኾን አቅም ያንሳታል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ፕሬዝዳንቱ ፍጹማዊ ሥልጣን ቢሰጠው ብዙ ነገር ሊከውን ይችላል፤ ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸውን የሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትን ሐሳብ በመጋራት፣ የአንድ ሰው ጠቅላይነት ለመንግሥት በጎ ያለመኾኑን ያህል ለዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ ጥሩ አይኾንም ብለው ይሞግታሉ፡፡ እንዲያውም አውቶክራሲ አደገኛ መንገድ በመኾኑ፣ ሔዶ ሔዶ ችግርና ውድቀት ያስከትላል፤ ይላሉ፡፡
አውቶክራሲ፣ አብዛኛውን ጊዜ የሚመረኮዘው በእብሪታዊው ኹሉን አወቅነት መንፈስ ላይ በመኾኑ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ፣ ሐሳብን አሸናፊና የሚያሠራ ማድረግ የሚቻለው፣ በውይይት እንጂ በጉልበት እና በፖለቲካ ጫና መኾን የለበትም፡፡
የፕሬዚዳንት ምርጫ፤
በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የ100 ዓመታት ሒደት ውስጥ እንደታየው፣ በርካታ ኮሌጆች የተቋቋሙት፣ በፕሮቴስታንት ሚኒስትሪዎች አማካይነት ስለኾነ፣ በአብዛኛው ኮሌጆቹን በፕሬዝዳንትነት የመሩት የቤተ እምነቱ ካህናት ነበሩ። በ20ኛው መ/ክ/ዘ መባቻ ላይ ደግሞ፣ ለፕሬዝዳንትነት ምርጫ፣ ንግድን የመምራት ችሎታ አስፈላጊ ኾኖ ስለነበር፣ የኮርፖሬት መሪዎች ኮሌጆቹን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ተደርጎ ነበር፡፡ በ20ኛው መ/ክ/ዘ መካከል ላይ ግን የሚከተሉትን ሦስት መሥፈርቶች ያሟሉ፣ ማለትም፥ የዳበረ ስኮላርሺፕ እና የአስተዳደር ችሎታ ያላቸው፤ የሥነ ትምህርት ጠበብት የኾኑና የሥነ ምግባር አርኣያነትን የተላበሱ ሰዎችን በፕሬዝዳንትነት መመደብ የተሻለ እንደኾነ ታመነበት፡፡
ሀ. ስኮላርሺፕ፡-
በምሁርነቱ ነቅዕ የሌለበት እንዲሁም፣ ከተማረው ትምህርት ባሻገር የእይታ አድማሱ የሰፋ፣ በተለያዩ የዕውቀት መስኮች ላይ የማወቅና የማድነቅ ፍላጎት ያለው፣ ዘወትር ራሱን ለማስተማር የሚተጋ መኾን ይኖርበታል፡፡
ትምህርት፣ ራሱን የቻለ የማያልቅ ጉዞ መኾኑን የተረዳ፣ ኹሌም ለመማር የተዘጋጀ፣ ከየትኛውም የትምህርት መስክ ይምጣ ኹሉንም የትምህርት ዓይነቶች የሚገነዘብ፣ የነገረ ሰብእንና የሳይንስን ባህሎች በአድማሳዊ እይታ አገናኝቶ ተዋስኦ መፍጠር የሚችል መኾን ይኖርበታል፡፡
ከኹሉም በላይ፣ ዩኒቨርሲቲ የስኮላሮች አምባ ነው። እነኚህ ስኮላሮች ተቀዳሚ ሥራቸው፣ እንደ ኢንደስትሪ ወይም ፋብሪካ ዕቃ እምራች ሳይኾኑ፣ እእምሮን ኮትኳችና ተከባካቢ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል፣ ምሁሩ፣ አሶሼት ፕሮፌሰር ሲባል፣ ኦፊሴል ለመኾን እንደበቃው አነጋገር “ተባባሪ” ማለት ሳይኾን፣ የዩኒቨርሲቲው፣ የምሁራን ኮምዩኒቲ አባል ኾነ ማለት ነው፡፡ ይህ ማኅበር፣ እስከ ዘመናችን ድረስ ቁልፍ የዩኒቨርሲቲ ማዕከል ነው፡፡ የምሁራኑን ማኅበር ድጋፍ ያላገኘ ተመራጭ ፕሬዝዳንት፣ በምንም መልኩ ለወንበሩ የሚመጥን ይኹንታ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ይኸውም፣ ተመራጩ ፕሬዝዳንት፣ በችሎታው ልቅና በምሁራኑ ማኅበር ዘንድ ጥያቄ የማይነሣበትና ክብርና አመኔታ የተቸረው ሊኾን ይገባዋል፤ ማለት ነው፡፡
ለ. የአስተዳደር ችሎታ፡-
የትምህርት አስተዳደር ከማንኛውም ዓይነት የአስተዳደር ዘይቤ ልዩ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የኮርፖሬሽን ፕሬዚዳንት እና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሰፋ ያለ ልዩነት አላቸው። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት  በአስተዳዳሪነቱ፣ ሰፋ ያለ የማደራጀት አቅም አለው፡፡ ሓላፊነትን እንደሚገባ ለማደልና ሰዎችን በሚመጥናቸው ቦታ ለማስያዝ፣ ሰብእናቸውን የመለካት ችሎታ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡
የሥርዓተ ትምህርትና የትምህርት ፍልስፍና አረዳዱ ከፍ ያለ መኾን ይገባዋል፡፡ ካሪኩለም እና የትምህርት ፍልስፍና የጎደለው አስተዳዳሪ፣ ቻርት እንደሌለው የመርከብ ካፒቴን ነው፡፡ ከዚህ እውነታ ስንነሣ፣ አሁን በቅርቡ፣ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ኾነው የተሾሙት ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ፣ በትምህርታቸውም ኾነ በሥራቸው፣ የሥነ ትምህርት ባለሞያ መኾናቸው፤ ለበርካታ ዓመታት በፖሊቲካ ሹምነት ብቻ ሲያዝ የነበረውን ቦታ ሞያዊ ባርኮት እንደሰጠው አምናለሁ፡፡
ሐ. የሞራል ኮምፓስ
አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣ ስኮላርሽፑ እንኳ ጠንካራ ባይኾን፣ በግብረ ገብነት የማይታማና በምግባሩ አርኣያ መኾን አለበት፡፡ ይህ ቦታ ሰዎች እግረ መንገዳቸውን፣ በፖለቲካ ኃይሎች ስለ ተወደዱ ብቻ የሚይዙት ሳይኾን፣ ራሱን የቻለ ጥሪ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ፕሬዝዳንቶች፣ የዚህን ቦታ ሹመት እንደ መንፈሳዊ ጥሪ አድርገው የሚቆጥሩትም አሉ፡፡
ማጠቃለያ
በመንግሥት እና በዩኒቨርሲቲ መካከል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ፣ የ20ኛው መ/ክ/ዘ  ጀርመናዊ ፈላስፋ፣ ካርል ያስፐርስ፣ “The Idea of the University” በሚል ርእስ ካቀረቡት ድርሳን ውስጥ ጥቂት ነጥቦችን እንዋስ፡፡ ዩኒቨርስቲ፣ በመንግሥት ውስጥ ያለ “መንግሥት” አይደለም። እንደ ማንም የመንግሥት ተቋምም፣ ፖሊሲ አስፈጻሚም አይደለም፤ በማለት በስፋት ያብራራሉ፡፡ ታድያ ምንድር ነው? ብለን እንጠይቅ፡፡ እንደ ያስፐርስ ገለጻ፣ ከመንግሥት ዐይን ነጻ ባይኾንም፣ እንደ ፖሊሲ አስፈጻሚ አካላት በመዳፉ ውስጥ የወደቀ አይደለም፡፡ ይኸውም፣ የዩኒቨርስቲነት ርእዩን በተቀዳሚነት እያስፈጸመ፣ የማኅበረሰቡንም ችግር እያየ የሚፈቱበትን አማራጮች ማመላከት ሌላው ተግባሩ ነው፡፡
በርግጥ ዩኒቨርሲቲ፣ ያለ መንግሥትና ማኅበረሰብ ድጋፍ ህልውና አይኖረውም፡፡ መንግሥት እየደገፈውም፣ እየደጎመውም በውስጥ ሥራው ጣልቃ መግባት አይገባውም። የመንግሥት ጣልቃ ገብነት፣ በታሪክ በተደጋጋሚ እንደታየው፣ የአድሏዊነት መልክ ይዞ ይቀርባል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ልዕልናው ከተጠበቀ፣ በምንም መልኩ የተመሠረተበትን የአእምሯዊ ፍጽምና አይዲያል አያጣም፡፡
መንግሥት፣ ዩኒቨርሲቲውን ሱፐርቫይዝ የማድረግ ሓላፊነት አለበት፡፡ ኾኖም፣ ይህን ለመተግበር፣ ሥልጣን የሚሰጣቸው ግለሰቦች፥ ምሁራዊ ብቃት፣ የሥነ ትምህርት ዕውቀትና የማስተማር ተሞክሮ እንዲኖራቸው ግድ ይላል። መንግሥት፣ ከዩኒቨርሲቲ ጥቅም ፈላጊ ብቻ ሳይኾን፣ ዩኒቨርሲቲ የአንድ ሀገር “አእምሯዊ ንቃት” አስጠባቂ እንደኾነ ዕውቂያ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡
ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስንመጣ፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሦስት መልኮችን ይዞ እናገኘዋለን፡፡
“ዩኒቨርሲቲገዳም ስላልኾነና በተጨማሪም ቀለቡን የምሠፍርለት እኔ ስለኾንኩ፣ ከእኔ ጋር ተሰልፎየልማቱ አጋር መኾን አለበት፡፡ ቲዮሪ የሚለውን ወደኋላ አሽቀንጥሮ፣ ውጤት ተኮርምርምር ላይ ብቻ ማተኮር አለበት፡፡”
“ሀገሪቱ፣ ኅብረብሔራዊ ስለሆነች፣ የዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና የአካዳሚክ ሥልጣኖች ምደባ በብሔር ተዋፅኦመኾን አለበት፡፡” በመኾኑም፣ እንደ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ፣ልሂቅነትና ስኮላርሺፕ የቦታና የሓላፊነት ማደላደያ መስፈርት መኾኑ ቀርቶ፣የብሔር ተዋፅኦና የፖሊቲካ ወገንተኝነት ቅድሚያ እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡
የዩኒቨርሲቲ የተማሪ ቅበላ ምጣኔ መብት ተገፎ፣የገዢው ግንባር ሓላፊዎች፣ካድሬዎችና አባሎች ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ አቅምም ባይኖራቸው፣የአካዳሚክ ሳይኾን የፖለቲካ መስፈርት በመወሰዱ በጉልበትእስከ ፒኤችዲእንዲደርሱተደርጓል፡፡
የሀገራችንን ኹኔታ ለማሻሻል የምንችለው በትምህርት መኾኑ እየታወቀ፣ የትምህርትን ይዞታ የሚወስነው ግን መንግሥት በመኾኑ አዙሪት ውስጥ ገብተናል፡፡ ከዚህ አዙሪት ልንወጣ የምንችለው፣ ጠንካራ አመራር በመስጠት ዩኒቨርሲቲው ከተለጣፊነት መንፈስ ወጥቶ፣ መንግሥት የሚያቀርበውን መንገድ ብቻ ሳይከተል፣ በራሱ እግር ቆሞ ርእዩን መከተል ሲችል ነው፡፡
በቅርቡ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝዳንታዊ ሥልጣን ይረከባል ወይም ትረከባለች ብለን የምንጠብቀው ወይም የምንጠብቃት ሰው/ሴት፣ ከበድ ያለ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሥራቸውን ክቡድ የሚያደርገው፣ የሚገቡበት ቤት የነተበና የፈራረሰ በመኾኑ ነው፡፡ በእኔ እምነት፣ ዩኒቨርሲቲው በሚከተሉት ሦስት ጉዳዮች ላይ ግንባታ ያስፈልገዋል። መጀመሪያ፣ የህልውና ማንበር ተግባር ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፡፡ ኹለተኛው፣ ዩኒቨርሲቲውን መልሶ በምሁራን ማኅበር(Community of scholars) እጅ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ሦስተኛው፣ በግቢው ውስጥ የሰፈነውን የፍርሃት ድባብ አስወግዶ፣ አካዳሚያዊ ነጻነት ቦታውን እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሀ. ልዕለ ተቋምነት(ኢንተግሪቲ)
ከኹሉም በላይ አንድ ዩኒቨርሲቲ ራሱን የሚገልጽበትና የሚገለገልበት አካዳሚያዊ ቋንቋ እና ይትበሃል እንዲኖረው የግድ ይላል፡፡ ይህንንም የምንለው፣ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ይህ የአካዳሚው ሥርዓተ ስያሜና ይትበሃል(ኖሚና ክላቱራ) ወደ ጎን ተገፍትሮ፣ ለዩኒቨርሲቲው ባይተዋር የኾነ ፖለቲካና ካድሬያዊ ቋንቋ የበላይነት በመያዙ ነው፡፡ በመኾኑም፣ በአንድ በኩል፣ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚያዊና ሞራላዊ ልዕለ ተቋምነት የቀደመ ቦታው ላይ ሊመለስ የሚችለው፣ አካዳሚያዊ ቋንቋውና ይትበሃሉ ሲመለስለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አእምሯዊ ፍጽምናው(አይዲያል)፣ ስኮላርሺፕ፣ ተዋስዖ(ዲስኮርስ)፣ ርእይ፣ ደረጃ፣ ክሂል፣ ምርምር፣ አጠይቆ፣ አስተምህሮ፣ ትውፊት፣ ሥነ ውበታዊ ተማኅልሎ፣ ሜታ ፊዚክስ፣ ነገረ መለኰት፣ አንድምታ፣ ሥነ ድርሳን፣ ሰዋስው፣ ተጻሮ፣ የመሳሰሉት ቃላት ከነዐውዳቸው ሲመለሱ፣ የዩኒቨርሲቲው የሐሳቦች ዓምባነት ተመልሶ ቦታውን ይይዛል፡፡
ለ. የምሁራን ማኅበር
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ ዩኒቨርሲቲ ማለት አንድ የምሁራን ኁባሬ የሚገኝበት ተቋም ማለት ነው፡፡ እዚህ ተቋም ውስጥ በአባልነት ሊገቡ የሚችሉት ሰዎች፣ በተወሰነ አካዳሚያዊ ደረጃ ውስጥ ያለፉ ብቻ ናቸው፡፡ ይኸውም፣ ባሳዩት ልሂቃዊ ብቃትና ስኮላርሺፕ ነው፡፡ ወደዚህ አዳራሽ ለመግባት በየዲሲፕሊኑ የተሰለፉ የዕውቀት አጋፋሪዎች ስላሉ፣ የእነርሱን ይኹንታ ሳያገኝ ማንም ሰው፣ የአዳራሹን ደጃፍ ሊዘልቅ አይችልም፡፡
ሐ. አካዳሚያዊ ነጻነት
አንድ ዩኒቨርሲቲ፥ ምርምር የማካሔድ፣ የምርምር ግኝቱን የማሳተምና ይፋ የማድረግ ምሉዕ ነጻነት ሲኖረው፣ አካዳሚያዊ ነጻነቱ ለመከበሩ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አንድ ምሁር በሚያደርገው ምርምር አንዳች እውነት ላይ ለመድረስ፣ ከተጽዕኖ ነጻ መውጣት አለበት፡፡ በተጨማሪም ምሁሩ፣ ከተሰለፈበት ዲሲፕሊን ውጪ እንደ አንድ ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ፣ ሐሳቡን የማቅረብ መብት አለው፡፡ ይኸውም የዛሬ መቶ ዓመት ከጸደቁት አራት የአካዳሚ ነጻነት ምሶሶዎች ውስጥ አንዱ ማለትም፣ `Extra Mural Right` የሚባለው ነው። በአጠቃላይ፣ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚያዊ ነጻነት ማለት፣ ውይይት እና የተለያዩ የሐሳብ ምሕዋሮች የሚንቀሳቀሱበት ነጻ ድባብ መፍጠር ማለት ነው፡፡
የጽሑፌ መደምደሚያ፣ በአካል ንጉሤ፣ “ፍላሎት”: የነፍስ አሻራዎች፤ በሚል ርእስ፣ በ2006 ዓ.ም. ካሳተመው አስደማሚ የግጥም መድበል ውስጥ፣ “ብርሃን ከላይ” የተሰኘችው የስንኝ ቋጠሮ ናት፡፡ የዩኒቨርሲቲው የአብርሆት ተልእኮ በግዑዝ የፎቆች ጋጋታ መወረሱን ታሳይልኛለችና ማሳረጊያዬ አድርጌያታለሁ፡፡
ብርሃን ከላይ
ብርሃን እንደ ዝሃ
ህላዌን እንደ ማግ
አድርቼና አቅልሜ
ሸምኜ
ሸምኜ
ያን የብርሃን ሸማ – ደርቤ ብለብሰው
ጨለማ ወረሰው
ለካንስ)
ብርሃን መኾን እንጅ – ብርሃንን መደረብ
 አይጠቅመውም ለሰው፡፡

Related stories   ወደ ድርደር ? ከታንክ ወደ አህያ የወረደው ትህንግ በማን ሊወከል?

አዲስ አድማስ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0